ስፖርት ለሰው ልጅ እያበረከተ ካለው ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ትስስር ጎን ለጎን ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ መስጠት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንና በቻይና ውሃን ከተማ በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መጀመሪያ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ዘርፉን ለከፍተኛ ቀውስ ዳርጎት ይገኛል፡፡
ወረርሽኙ ጉዳት ካደረሰባቸው ስፖርቶች መካከል እግር ኳስ በቀዳሚነት ሲጠቀስ፣ በርካታ አገሮች ስፖርቱን ለመታደግና ቀድሞ ወደ ነበረበት መመለስ ይችሉ ዘንድ ወቅቱን ታሳቢ ያደረጉ ዕቅዶቻችን መተለም ጀምረዋል፡፡
አውሮፓውያኑን ጨምሮ አንዳንድ አገሮች በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መርሐ ግብሮቻቸውን ዜጎቻቸው ለወረርሽኙ ተጋላጭ በማይሆኑበት አግባብ አስቀጥለዋል፣ በቅርቡም ከታላላቆቹ ሊጎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ የስፔን ላሊጋና የጣሊያን ሴሪአ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡
በዚሁ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የተቋረጠው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አሁን ባለው ሁኔታ ቀጣይ ዕጣ ፈንታውን በተመለከተ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ጨምሮ ይመለከታቸዋል ከሚባሉ ባለድርሻ አካላት ዝምታ ካልሆነ እስካሁን ባለው በመፍትሔነት የተቀመጠ አልያም የተባለ አንዳች ነገር አለመኖሩ ግርታ የፈጠረባቸው ሙያተኞች አልጠፉም፡፡
ከእነዚህ ሙያተኞች መካከል በአሜሪካ በስፖርት አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ዮሐንስ ሳህሌ አንዱ ናቸው፡፡ እግር ኳሱን ጨምሮ በርካታ ዘርፎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለከፋ ችግር የተዳረጉበት ወቅት መሆኑን የሚናገሩት ሙያተኛው፣ ችግሩን ማለፍ የሚቻለው ስፖርቱን በበላይነት ከሚያስተዳድረው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከስፖርት ኮሚሽን፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከክልልና ከተማ አስተዳደር ፌዴሬሽኖች፣ ከአሠልጣኞችና ከዳኞች ማኅበር እንዲሁም ከተጫዋቾችና ከሌሎች ዘርፉ ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጡ ሙያተኞች የተካተቱበት መድረክ በማመቻቸት ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ አማራጭ ዕቅድ ማዘጋጀት እንደሚስፈልግ ያምናሉ፡፡
“ኮሮና አሁን ባለው ሁኔታ የሥርጭት አድማሱን በማስፋት ሥነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናው እየጨመረ ነው፡፡ ለችግሩ ምንም ዓይነት መፍትሔ ባልተገኘበት፣ አውሮፓውያኑና ሌሎች አንዳንድ አገሮች ውድድሮቻቸውን ሲጀምሩ ምክንያት አላቸው፤” የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ አገሮቹ ጥንቃቄ ሳይለይ ውድድሮች እንዲደረጉ ሲወስኑ የሕዝቦቻቸውን ሥነ ልቦናና ሞራል ለመጠበቅ ጭምር በማሰብ እንደሆነ ጭምር ልብ ሊባል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮያውያንን የአኗኗር ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወራት በጉዳዩ ጥልቀት ያለው ውይይት ማድረግ እንደሚገባ የሚያስረዱት ሙያተኛው፣ ከኮቪድ በኋላ እግር ኳስ ቀድሞ ወደ ነበረበት ሊቀጥል የሚችልበት ዕድል ጠባብ በመሆኑ ቢያንስ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ወር “ከይድረስ ይድረስ” ነፃ የሆነና ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ ዕቅድ ቢዘጋጅ እንደሚሻል ይመክራሉ፡፡
ከዚህ በፊት በተለይም ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር ተያይዞ የተከሰቱ ችግሮችን ለማስወገድ በሚል፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ሳይመክሩበት ብቻውን የፕሪሚየር ሊጉን የውድድር አካሄድ አካባቢያዊ ሆኖ እንዲቀጥል የወሰነበት መንገድ ትክክል እንዳልነበረ የሚስታውሱት ሙያተኛው፣ “በጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሐሳብ በውይይት ዳብሮ፣ በተለይ እግር ኳስ ተደራሽ ባልሆነባቸው እንደ አፋር፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ በመሳሰሉት የተሻለ የውድድር ሥርዓት ብቻ ሳይሆን፣ ውጤታማ እግር ኳስ መፍጠር በተቻለ ነበር፤” በማለት የዕቅዱን አስፈላጊነት ያስረዳሉ፡፡
የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በቅርቡ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ውድድር ያቋረጡ አባል አገሮች እንደየ ሊጎቻቸው ዓይነትና ሁኔታ በቀጣይ በምን መልኩ ሊቀጥሉ እንዳሰቡ ምክረ ሐሳብ መጠየቁን የሚያስታውሱት አቶ ዮሐንስ፣ ተቋሙ የተለየ ነገር ኖሮት ሳይሆን ቀጣይ ዕቅዶቹን ቀድሞ ለማዘጋጀት ያመቸው ዘንድ በማሰብ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ወረርሽኙን ተከትሎ በአገሪቱ እግር ኳሱን ጨምሮ ማናቸውም ስፖርታዊ ክንውኖች እንዲቋረጡ የተደረገው በመንግሥት ውሳኔ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ በመነሳት የባለድርሻ አካላቱ ውይይት አድርገው የመፍትሔ አቅጣጫ ቢያስቀምጡ ምን የሚለውጠው ነገር ይኖራል? ለሚለው ጥያቄ ሙያተኛው፣ “ችግሩ ተከስቷል፣ ሕይወትም እንደቀጠለ ነው፣ የባለድርሻ አካላቱ የውይይት ማጠቃለያ ምንም ይሁን ምን እግር ኳሱ እንዴት ይቀጥል በሚለው ጉዳይ መነጋገር ምን ክፋት አለው?” በማለት ይሞግታሉ፡፡
ከወረርሽኙ ባህሪና ሁኔታ በመነሳት የዓለም ጤና ድርጅት ሁለተኛ ዙር ጥቃት ሊያስከትል የሚችልበት አጋጣሚ እንደሚኖር መግለጹን የሚያስረዱት አቶ ዮሐንስ፣ መዝጋት ብቻውን መፍትሔ አይሆንም የሚል እምነት አላቸው፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት ውድድሮች ቢቋረጡም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከደንብና መመሪያ ጋር ተያይዞ ችግር ሲያስከትሉ የቆዩ አንቀጾች እንዲሻሻሉ ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝ የፌደሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ከሰሞኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ክፍተቶችን ለማረም እየሄደበት ያለው መንገድ ክፋት እንደሌለው የሚናገሩት ሙያተኛው፣ “ባለድርሻ የሚባሉት ሙያተኞች ማንነት እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ ሲናገሩ እንደተደመጡት የደንብና መመርያዎቹን ክፍተቶች በጥልቀት ተመልክቶ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ችግሩን ማረም እንዲቻል ቀደም ሲል እንደተናገርኩት በስፖርቱ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻዎች የተሳተፉበት ቢሆን ይመረጣል፤” በማለት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እየሄድኩበት ነው የሚለው የተለመደ አካሄድ እንደሆነ በማንሳት ይተቻሉ፡፡