የኮሮና ወረርሽኝ ጭንቀት በፈጠረበት በዚህ ጊዜ ለረጅም ቀናት ከቤቴ አልወጣሁም ነበር፡፡ ከሥራ እረፍት በመውሰድ ቢያንስ ሥርጭቱን ለመቀነስ ልተባበር ብዬ ነው ቤቴ የተከተትኩት፡፡ ባለፈው ሳምንት በአንዱ ቀን ቤት መቀመጥ ሲሰለቸኝ እግሬን ለማፍታት ወጥቼ ረዘም ያለ ጉዞ ካደረግኩ በኋላ፣ ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ጎራ አልኩ፡፡ ጎራ ያልኩበት ምክንያት ከፀሎት በተጨማሪ እግረ መንገዴን ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚያደርጉትን ጥንቃቄ ጭምር ለማየት ነበር ነበር፡፡ ፀሎቴንና ትዝብቴን ጨርሼ ወደ መውጫው በር ላመራ ስል ድንገት ዓይኖቼ ከአንድ ሐውልት ጋር ተገጣጠሙ፡፡ በሐውልቱ ላይ የሚታየው ጉልህ ፎቶግራፍ ከዚህ በፊት የማውቃቸውን አንድ ሰው አስታወሰኝ፡፡ ፎቶግራፉ ምንም እንኳን በጎልማሳነት ዘመን የተነሳ ቢሆንም፣ በስተርጅና ዘመናቸው የማውቃቸው ሰው እንደሆኑ ግን አልተጠራጠርኩም፡፡ በዚህም ምክንያት ፍጥነቴን ጨምሬ ወደ ሐውልቱ ተጠጋሁ፡፡
በእርግጥም የማውቃቸው ሰው ናቸው፡፡ ስማቸውን አነበብኩት፡፡ ወይ ጉድ? መቼ ይሆን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት? አዎን ከ1918 – 2011 ዓ.ም. የሚል ተጽፏል፡፡ በግንቦት ወር 2011 ዓ.ም. ማረፋቸውን አወቅኩኝ፡፡ እኔ ደግሞ መሞታቸውን አልሰማሁም፡፡ ሐውልቱን ደገፍ ብዬ ስለሳቸው ማሰብ ጀመርኩ፡፡ መጀመሪያ የተዋወቅኳቸው በ1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ የተገናኘነውም በአጋጣሚ ለቅሶ ላይ ነበር፡፡ በዚያ ዕድሜያቸው የሟች ቤተሰቦችን ሲያፅናኑና የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሱ ሲያጫውቱን ለዛቸው ደስ ይል ነበር፡፡ ጨዋታ ከጀመሩ አይጠገቡም ነበር፡፡ ረጅም ቁመታቸውና ጥንካሬ የሚስተዋልበት ቅጥነታቸው የረዳቸው ይመስላሉ፣ ሲራመዱ እንኳ ቀጥ ብለው ነበር፡፡ እኔ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት እያገኘሁዋቸው፣ ሐሳብ ለሐሳብ እንለዋወጥ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡
መጨረሻ ያገኘሁዋቸው ግን ከሦስት ዓመት በፊት አራት ኪሎ ነው፡፡ አራት ኪሎ ቱሪስት ሆቴል ፊት ለፊት ከሚገኙት ካፌዎች አንደኛው በራፍ ላይ ሆኜ ጋዜጣ እያነበብኩ ማኪያቶ ስጠጣ፣ እኚህ አዛውንት የሕንፃውን ምሰሶ ደገፍ ብለው አየሁዋቸው፡፡ ትኩር ብዬ ሳያቸው ላብ በላብ ሆነውና ድክም ብሏቸው ምሰሶውን የሙጥኝ ያሉ ይመስላሉ፡፡ ደንገጥ ብዬ ተነሳሁና ወደ እሳቸው ቀርቤ ሰላምታ ካቀረብኩላቸው በኋላ ደገፍ በማድረግ ተቀምጬበት የነበረው ሥፍራ አምጥቼ አስቀመጥኳቸው፡፡ ባርኔጣቸውን አውልቀው ላባቸውን በመሃረባቸው ከጠራረጉ በኋላ በረጅሙ ተነፈሱ፡፡ የፀሐዩ ንዳድና መንገድ እንዳደከማቸው ነገሩኝ፡፡
እኔም፣ ‹‹ምነው ምሰሶውን ከሚደገፉ መቀመጫ ላይ አረፍ ብለው ሻይ ቡና አይሉም ነበር ወይ?›› በማለት እንደ ዘበት አስተያየቴን ጣል አደረግኩ፡፡ በዚህ መሀል አስተናጋጇ መጥታ ትዕዛዝ ስትጠይቃቸው አንዴ እኔን ሌላ ጊዜ እሷን አዩ፡፡ ነገሩ ገብቶኝ ለስላሳ፣ ቡና፣ ማኪያቶ ወይም ምን ይፈልጉ እንደሆነ ምርጫ አቀረብኩላቸው፡፡ ወፍራም ቡና እንዲመጣላቸው አዘው፣ ‹‹ሰማህ?›› አሉኝ፡፡ ጠጋ ብዬ ማዳመጥ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ምሰሶውን የተደገፍኩት እኮ መቀመጡን ጠልቼ አይደለም፤›› አሉኝ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹የጡረታ አበል ሆድ መሙላት እያቃታት በተወደደ ኑሮ ቡና ሻይ ማለት እንዴት ይቻላል?›› ብለው ሲተክዙ ገባኝ፡፡ እኚህ ከወጣትነታቸው ጀምረው ጣሊያንን የተዋጉ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር ኮሪያና ኮንጎ የዘመተው የኢትዮጵያ የሰላም አስከባሪ ኃይል ባልደረባ የሚያገኙት ጡረታ ለምግብም አይበቃም፡፡ የእሳቸው ትካዜ እኔ ላይ ተጋብቶ ለረጂም ጊዜ ፀጥ ተባብለን ቆየን፡፡
እኚህ ጀግና ሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ አገራችን አዛውንቶቿን አትጦርም፤›› አሉኝ፡፡ ብዙዎቹ እሳቸውን መሰል አዛውንቶች ከቤታቸው ወጥተው እግራቸውን ለማፍታታትና ለመንቀሳቀስ እንደማይመቻቸው፣ ብዙዎቹ የሕዝብ መናፈሻዎች መዘጋታቸውን፣ ከተማዋ ሕንፃ በሕንፃና መንገድ በመንገድ ስትሆን እንኳ ተዘዋውሮ ለመመልከት እንደማይመቻቸው፣ በየቦታው አረፍ የሚባልበት አለመኖሩን፣ ካፌ ጎራ ለማለት አቅም መጥፋቱን፣ አዛውንቶች መንቀሳቀስ ሲገባቸው በዚህ ችግር ምክንያት ተሳስረው መቀመጣቸውን በሐዘን አወጉኝ፡፡ አዎን የኑሮ ውድነቱ እንደ ወላፈን በሚጋረፍበት በዚህ ዘመን፣ ስንቶች ከረሃብ ጋር እንደሚተናነቁ ወለል ብሎ ታየኝ፡፡ ይኼንን ሁሉ ስናወራ የራሳቸውን ችግር ሳይሆን የብዙዎችን አዛውንቶች ነበር ማዕከላዊ ነጥብ አድርገው የነገሩኝ፡፡ በዚህ ሁኔታ ነበር ከእኝህ አዛውንት ጋር የተለያየነው፡፡
ሐውልቱን ተደግፌ በመጠኑ ስለሳቸው የተጻፈውን እያነበብኩ ሳለ አንዲት ወጣት ሴት አጠገቤ መጥታ ቆመች፡፡ ዞር ብዬ ሳያት፣ ‹‹ታውቀዋለህ እንዴ?›› አለችኝ፡፡ ፊቴን በሐዘን አጨማድጄ ‹‹አዎን!›› አልኳት፡፡ ወጣቷ፣ ‹‹አያቴ ነው፡፡ ኩሩ ሰው ነበር፡፡ በኮሪያ ጦርነት ጊዜ የጀግንነት ሜዳሊያ ከአሜሪካ ጄኔራልና ከጃንሆይ እጅ ተቀብሏል፡፡ እሱ ግን ይህ እንዲወራለት አይፈልግም ነበር፡፡ የፈለገ ቢከፋው ዝም ይላል እንጂ አገሬ በደለችኝ አይልም ነበር፡፡ ይልቁንም አገራችን አልፎላት ልጆቻችንና የልጅ ልጆቻችን ትልቅ ደረጃ በደረሱ እያለ ነበር የሚናገረው…›› እያለች ስትነግረኝ ዓይኖቼ በእንባ ተሞሉ፡፡ በጀግንነት አገራቸውን ያገለገሉ ሰው በስተርጅና ዘመናቸው በችግር ውስጥ ሆነው ቢያልፉም በኩራት መኖራቸው አስደሰተኝ፡፡ ስንቶቻችን እንሆን ችግሮችን ተጋፍጠን አገራችንን ሳናማርር የምንኖር? ስንቶቻችን እንሆን ከአገር በፊት ራሳችንን እያስቀደምን በኃፍረት እንደ ተሸማቀቅን የምናልፍ?
ልጅቷ እንደነገረችኝ ከሆነ ሐውልቱን ያሠሩላቸው የሚያውቋቸው ሰዎች ናቸው፡፡ ሐውልቱ ላይ በዚህ ጊዜ ተወልደው በዚህ ጊዜ ሞቱ ከሚባለው በስተቀር ምንም አልተጻፈም፡፡ ስለጀግንነታቸው ለምን እንዳልተጻፈ ጠየቅኳት፡፡ ልጅቷ፣ ‹‹አያቴ ሁሌም ያስጠነቅቀኝ የነበረው በፍፁም ምንም ዓይነት ነገር እንዲህ አደረገ ተብሎ እንዳይጻፍ ወይም እንዳይነገር ነው፡፡ እሱ ለአገሩ በፍፁም ፈቃዱ ያከናወነውን ተግባር ዝና ፍለጋ እንደማይጠቀምበት አስጠንቅቆኛል፤›› ስትለኝ ገረመኝ፡፡ ርካሽ ተወዳጅነትና ዝና ፍለጋ ስንትና ስንት ኃጢያት በሚያሠራበት በዚህ ዘመን፣ እንዲህ ዓይነት የተባረኩ ሰዎችን ማጣት አሳዘነኝ፡፡ እዚህ ግባ የማይባል የጡረታ አበል እየሰጠችና የሕዝብ መዝናኛ ፓርኮችን እየዘጋች አዛውንቶቿን የዘነጋች አገር እንዲህ ዓይነት ኩሩ ሰዎችን እያጣች፣ በሙስና የደለቡ ከንቱዎችን ስትንከባከብ ማን ይሆን ማፈር ያለበት? በነገራችን ላይ በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት እንዲህ ያሉ ጠያቂ የሌላቸው ስንት የአገር ባለውለታዎች እንዳሉ ይታወቅ ይሆን? እስኪ አካባቢያችንን እየቃኘን እንድረስላቸው፡፡ (ቶማስ ዘርጋው፣ ከእንግሊዝ ኤምባሲ)