Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትመብቶችን ያለማስደፈር ዋስትናችን ሥርዓታዊ ጉትጎታና ልጓም ነው

መብቶችን ያለማስደፈር ዋስትናችን ሥርዓታዊ ጉትጎታና ልጓም ነው

ቀን:

በሲሳይ ገላው

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ከሁሉም ነገር በላይ የመቆጣጠርና የማሸነፍ ተግባር ተቀዳሚ ሆኖ የነሐሴውን የምርጫ መርሐ ግብር እንዳስተጓጎለ ሁሉ፣ ጥግ ይዞ እያሸመቀ ልማትንና መረጋጋትን የሚያጠቃ እንቅስቃሴንና ድንገት የሚደፋ ጥይትን ወይም የቦምብ ፍንዳታን ከሥራ ውጪ ማድረግም ከምርጫ ውድድር በፊት መሟላቱ የሚብስ ሥራ ነው፡፡ ከምርጫ በፊት ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ፣ የሕግና ሥርዓት መከበር እንዲሻሻል እየሠራሁ ነው የሚለው መንግሥት በሁለት መንገድ (በሕገወጥና በሕጋዊ መንገድ) ፖለቲካን የሚያካሂዱ ቡድኖች ስለመኖራቸው ይነግረናል፡፡ ግን እነ ማን እንደሆኑ በማስረጃ አጠናቅሮና ፍርጥ አድርጎ እስካሁን አላወጣልንም፡፡ ግርግር ነክ ወንጀሎች በተከሰቱበት ሥፍራ በድርጊቱ የሚጠረጠሩትን አስሬያለሁ/እያሰርኩ ነው እንደሚለን ሁሉ፣ ብሔርተኛ ሸሻጊነት አላስችል ብሎኝ ያልተያዙም አሉ ብሎናል፡፡ “ተፎካካሪ” ቡድኖችም አባሎቻችን ይሳደዳሉ፣ ይታሰሩብናል፣ እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከሉ፣ ወዘተ ሲሉ ቆይተዋል፡፡ አንዳንዶች በደሉን የሚሏቸውን “ያልታወቁ ኃይሎች” ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ የመንግሥት ኃይሎችን በቀጥታ ያማርራሉ፡፡  መንግሥት ሲጠየቅ ደግሞ በወንጀል የተጠረጠሩ ካልሆነ በቀር በፖለቲካ አመለካከቱ የታሰረ የለም ባይ ነው፡፡

የፖለቲከኞቹን ስሞታ አናምን ነገር መግደል፣ ቦምብ ማፈንዳት፣ ግርግር ፈጥሮ ንብረት (ፋብሪካ ሳይቀር) ማቃጠል. . . የትግል ዘዴ ሆኖ እንደሚሠራበት እናውቃለን፡፡ በስሞተኞቹ ፖለቲከኞች በኩል ከዚህ የትግል ዘዴ ራስን አርቆ፣ በዚህ ሥልት የቆሸሸውን ቡድን ወይም ቡድኖች አጋልጦ የመታገል ፖለቲካዊ ዕድገት የለም፡፡ ሁሉም በተለባብሶ ውስጥ እየተሻሸ የሚኖር ነው፡፡ በሚዲያዎችና በሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች አማካይነት እውነት የት አካባቢ እንዳለ አናውቅ ነገር፣ ያሉን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች ጥቃትን አነፍንፎና አጣርቶ በማጋለጥ መረባዊ አቅም ደረጃ ገና የሌሉ ያህል ናቸው፡፡ ሚዲያዎቻችንና ጋዜጠኞቻችን ከሞላ ጎደል ወይ የገዥም ፓርቲና የመንግሥት አሸርጋጅ ናቸው፣ ወይም ለተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖችና የፖለቲካ መስመሮች አገልጋይ ናቸው፡፡ ከወገንተኛነትና ከአድሏዊነት ነፃ ሆኖ ለመሥራት የሚፈራገጡ ኢምንት ታህል ቢኖሩም፣ እውነትን ፈልፍሎ ለማውጣት አቅም ያጥራቸዋል፡፡ የገንዘብ፣ የአውታርና የሙያ አቅም አስሮ የያዛቸውም ናቸው፡፡

ሌላም ዓይነት ጋዜጠኞች አሉ፡፡ ‹‹ጋዜጠኞችና ሚዲያዎች አድሏዊ ነገር መርጨት የለባቸውም፣ ሚዛናዊና እውነትን መናገር አለባቸው. . .›› እያሉን፣ ያንን ለመፈጸም የረባ ጥረት የማያደርጉ ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህም ራመድ ብለው ያላንዳች ኃፍረት ‹‹ከወገንተኛነት ውጪ መሆን አይቻልም፣ መተኮር ያለበት ወገንተኛነት ላይ ሳይሆን፣ ሚዲያና ጋዜጠኞች ወደ ማንም ያጋድሉ፣ መመዘን ያለባቸው አድሏዊ ያልሆነ ሥራ በመሥራት አለመሥራታቸው ነው›› በማለት እነ “ሲኤንኤን” እና “ፎክስ”ን እየጠቀሱ የሚከራከሩ ደፋሮችም እናገኛለን፡፡ ወገንተኛ ሆኖ ያለ አድሏዊነት ሙያዊ ኃላፊነትን የመወጣት ጉዳይ ሁለቱን በቅጡ ለይቶና አለመደበላለቃቸውን ጠብቆ ለመቆየት የሚያስችል የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ባህል መደርጀትን ይፈልጋል፡፡ ያም ተሟልቶ የደረጀ ሥርዓትና ባህል ባላቸው አገሮች ውስጥ እንኳ ፖለቲካዊ ወገናዊነት ኢአድሏዊ የሙያ ግዴታን እየተፈታተነ፣ ወደ አድሏዊነት የማንሸራተት ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ሥርዓቱና ባህሉ በሌለበት ዴሞክራሲያዊ ለመሆን ገና በድንግዝግዝ ውስጥ ዳዴ በሚባልበት በኢትዮጵያ ሁኔታ፣ እንኳን አድሏዊነት ውስጥ መንከባለል ይቅርና የኢዴሞክራሲያዊነትና የፀረ ዴሞክራሲያዊነት ቁርጠት ሲያንቆራጥጥ እያየን ሳለ፣ ገና በዳዴዬ ደረጃ ወገንተኛ ሆኜ ሳላዳላ እሠራለሁ ማለት በራስ ላይ ከማላገጥ አይሻልም፡፡

ከዴሞክራሲ አልባነት ወጥቶ የዴሞክራሲ ነፃነቶችን ለመጨበጥ ትግል በሚደረግበት ደረጃ ከሁሉ በፊት ወገንተኛ የመሆኑ ነገር ማረፍ ያለበት ለቡድናዊ ፍላጎቶችና መስመሮች በመታመን ላይ ሳይሆን፣ ከዚያ በላቀውና ለሁሉም መኖሪያ የሆነው ዴሞክራሲ እንዲዋቀርና እንዲደረጅ በመዋደቅ ላይ ነው፡፡ ህ ተቀዳሚ ተጋድሎ በሚዲያ፣ በጋዜጠኞችና በሙያ ሰዎች በኩል በአግባቡ አልተጨበጠም፡፡ የዚህ መጉደል ደግሞ አሁን ባለንበት ደረጃ፣ እውነቱን አውቆ ጥፋተኛንና ልክ የሚሠራውን እየለዩ ጥፋትን እያረሙ ወደፊት የመራመድ ተግባራችን በውዥንብር እንዲንገላጀጅ አድርጎል፡፡ በፖለቲካው ረገድም ከቡድን ፍላጎቶች በላይ ለዴሞክራሲ ወገንተኛ ሆኖና ኃይል አስተባብሮ መዋደቅ ዋነኛ ተግባር መሆኑ ገና ፈክቶ አልበራም፡፡

ከዚህ ቀደም አማርኛ ተናጋሪዎች በአገዛዙ ላይ ስለጎሉ የአማራ ሕዝብ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጉስቁልና አልተወገደም፡፡ ሕወሓቶች በቁንጮነት ሥልጣኑን ስለተቆጣጠሩና “የአማራ ትምክህት” ስለተወገረ የትግራይ ሕዝብ የአበሳ ኑሮ አልተወገደም፡፡ ኦሮሞ ግለሰቦች ወደ አናት ስለወጡም የኦሮሞ ሕዝብ ከሌላው ይበልጥ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡ የአንዱ ብሔር ወይም የሌላ ብሔር ቡድን በተራ የሥልጣን ቁንጮነቱን መያዙ፣ ወይም የፌዴራሉ ሥልጣን መዋቅር ውስጥ ደምቆ መሰግሰጉ ቡድኑ የተገኘበትን የብሔር ሕዝብ የልማትና የመብቶች ተረኛ ተንበሽባሽ አያደርገውም፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ዛሬም ኦሮሞና አማራ ብዙ “ተወካዮች” አሏቸው፣ ግን ዋና ተጠቃሚ አልሆኑም፡፡ እነ ‹ኦፌኮ›ና ጃዋር መሐመድ ከሦስት መቶ በላይ የፓርላማ ወንበር ቢያሸንፉ ኦሮሞ ዓለሙን አያይም፡፡ ‹አብን›ም እንደ ሐሳቡ በአማራ ክልልና በቀሪው ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ አማሮች አማካይነት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ድምፅ ቢያገኝ፣ “ከእንግዲህ አማራ በአማራነትህ አትጠቃም” የሚል ዲስኩር ለማድረግ እንኳ የአንድ ቀን የሥልጣን ዕድሜ ስለማግኘቱ እጠራጠራለሁ፡፡ ምክር ቤታዊ የተወካዮች ብልጫ ኖሮም ሆነ በሌላ ዘዴ የአንድ ብሔር ቡድን የበላይነት ያለበት አገዛዝ ለማስፈን መሞከር፣ ቀደም ባሉ ጊዜያት እንዳየነው በጥላቻ የተለወሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋበዝ ነው፡፡ በብሔረ ብዙነት የተነረተ ቡድን ሥልጣን በመቆጣጠሩም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሥርየት አያገኙም፡፡ ቡድኖች ዴሞክራሲ እያሉ ሲጮሁ ይህ ሃቅ የገባቸው ይምሰሉ እንጂ፣ ዴሞክራሲን የይስሙላ እንዳይሆን (እንዳይከሽፍ) አድርጎ አስፈላጊዎቹን መደላድሎችና አየር ንብረቶቹን ለማሟላት ከመሥራት ይልቅ፣ እንደ ምንም ምርጫ ተደርጎ ወንበር ለመቆጣጠር ነው ሲሽቀዳደሙ ያየናቸው፡፡

በዚሁ እሽቅድምድም ውስጥ የሚካሄድ ሌላም ትንንቅ አለ፡፡ እነ ‹አብን› ከሚመሩት የአማራ ብሔርተኛ ትግል እንደሚነገረን፣ ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በመጣው የማንነት ፖለቲካ ውስጥ አማራ ተጠቂ የሆነው በማንነቱ እውነተኛ ድርጅትና ውክልና ስላልነበረው ነበር፡፡ የእነ ‹አብን›ም እንቅስቃሴ ይህንን እውነታ ለመቀየር ነው፡፡ በኦሮሞ ቡድኖችም አካባቢ ብዙ ጊዜ ሲነፍስ እንደሚሰማው መጪው የ201. . . ምርጫ እንደ “ሬፈረንደም” ነው የሚታየው፡፡ የሬፈረንደሙንም የድል አስኳል የሰሜናዊ/ሴማዊ ገዥነት ለመጨረሻ ጊዜ ተሸንፎ ሥልጣን ወደ ደቡባዊ ሕዝቦች መዞር ዓይነት አድርገው ነው የሚያስቡት፡፡ እዚህ “ድል” ውስጥ ያለውን የተምታታ ነገር እንፈልቅቀው፡፡ “ነፍጠኛ” ወይም “የነፍጠኛ አሻንጉሊት” የሚለው ግንዛቤ ተብዬ እነ ‹ኢዜማ› እና ‹ብልፅግና› ፓርቲን ሁሉ ይጨምራል፡፡ አማርኛ ተናጋሪ ናቸው ተብለው ከሚታሰቡ ቡድኖች ጋር የኦሮሞም ሆነ የኩሽ ብሔርተኛ ቡድን መጣመር ዓላማን ከመሳት፣ ወይም የነፍጠኛ መሣሪያ የመሆን ያህል ተደርጎ ይሸሻል፡፡ ‹አብን› “ነፍጠኝነትነት”ን በአዲስ ትርጉም ማቀፉም ይህንን ሽሽት “ትክክል” ለማለት ጠቅሟል፡፡ የጊዜያችን አንዱ የፅንፈኝነት ፈርጅ የሚታየው በ‹አብን› ገታራነትና በተቃራኒዎቹ ጨለምተኛ አመለካከት ላይ ነው፡፡

በእነዚህ ቡድኖች ዓይን የሀቀኛነትና የአሻንጉሊትነት መለኪያና ለኪ እነሱ ናቸው፡፡ ደቡባዊ ተደርገው የሚታሰቡት ከ‹ለኪ›ዎቹ ጋር የሚያብሩ “ኩሻዊ” ቡድኖች ናቸው፡፡ ሥሌቱም በኦሮሞ ኩሽ ቅንብር የፓርላማን ወንበሮች መዋጥ ነው፡፡ የዚህ ሥሌት መሠረታዊ ውልቃት፣ በቡድን ሽርክናዎች የሚገኝ የወንበር ይዞታ ብልጫ የደቡባዊ ሕዝቦችን ሥልጣን አለማስገኘቱ ነው፡፡ የኦሮሞ ኩሽ ቡድኖች በተከታታይ እያሸነፉ የበላይ ገዥነትን ታሪክ ወደ ደቡብ ቢያዞሩ ለውጡ የቡድኖች ሥርዓት እንጂ፣ የሕዝቦች የሥልጣን ሥርዓት አይሆንም፡፡ ማለትም ከቡድኖች የሥልጣን ጥማት ያለፈ ውጤት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲተርፋቸው (በየትኛውም የሕዝቦች ክፍል ዘንድ ተገፋሁ/ሁለተኛ ዜጋ ተደረግሁ የሚል የብሶት ታሪክ እንዲዘጋ) ከተፈለገ፣ የትኛውም የቡድኖች ሽርክና የበላይነቱን በሕዝቦች ላይ እንዲዘረጋ የማይፈቅድ ፍትሐዊ አወካከል ያለበት፣ የትኛውም ሕዝብ የማይገለልበት፣ ሁሉም መብቶች (የብሔር፣ የዜጎች፣ የሰውነት) የሚከበሩበት የዴሞክራሲ ሥርዓትን ተጋግዞ ለመገንባት መሥራት መሠረታዊ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ የኦሮሞና የአማራ የውክልና ሽርክና ቢፈጠር፣ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ብሔረሰቦች ፍላጎታቸው ቦታ እንዲያገኝ በድምፅ የመገዳደር ችግር ቢገጥማቸውስ፣ ብሎ በአንድ ልሙጥ መሥፈርት ብቻ የማይመዝን ፍትሐዊ አወካከል እንዲኖር እስከ ማድረግ ድረስ ዴሞክራሲያችን መጠንቀቅ ሁሉ ሊኖርበት ይችላል፡፡

‹‹ኢትዮጵያዊነት ላይ ያተኮረ ፖለቲከኛ አያዳላም. . . በአማርኛ ተናጋሪነት ተቀርፆ የወጣ ሳያዳላ ለመምራት ይመቻል. . . አማራ እንኳን ለመሪነት ለተመሪነትም አይመችም. . .፣ ኦሮሞ. . .፣ ትግሬ. . . ከምባታ. . .›› ያልተባለ አሳዛኝ ግንዛቤ የለም፡፡ ጥሩ መሪነትና አለማዳላት ከብሔረሰብ ማንነት ጋር ግንኙነት የለውም፡፡ እስቲ ከዚህ ብሔረሰብ የወጣ ሰው ደግሞ ይሞከር እያሉ መባዘን የትም አያደርሰንም፡፡ አስተዋይ ዓይንና ልብ ካለን በቅርቡ በታየ የፖለቲካ ዕብደታችን ውስጥ በደቦ መስከርና መብቴን እያሉ መብት መርገጥ፣ ስንበደል ነበር እያሉ የጨከነ የበቀል በደል ውስጥ መነከር ያልተከሰተበት ማኅበረሰብ አለ ወይ? በዚህ ዓይነቱ ቅሌትና ዕብደት ያላዘነና ያልተከፋ የሕዝብ ክፍልስ አለ ወይ? ብሎ መጠየቅ ብቻ የተሻለ አመራር ፍለጋ ብሔረሰባዊ አመጣጥ ከማማረጥ ጋር ግንኙነት እንደ ሌለው እንረዳለን፡፡ ማራኪ የፓርቲ መርሐ ግብር መምረጥ እንኳ ዋነኛ መተማመኛ ሊሆነን አይችልም፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የገዥዎች የሥልጣን ሽሚያ አገርና ሕዝብን የሚጎዳ ክፍተት በተደጋጋሚ ፈጥሯል፡፡ በዚያ ክፍተት የውጭ ኃይሎች ሊያተርፉበት አድርተዋል፡፡ አድርተውም ያተረፉባቸው ጊዜያት ነበሩ፡፡ በ19ኛ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ የዮሐንስ አራተኛን አፄነት ገፍቶ የራሱን አፄነት ለመትከል ይፈልግና ይመሳጠር የነበረው የምኒሊክ ተቀናቃኝነት የፈጠረው ክፍተት ከጉልሆቹ ክፍተቶች አንዱ ነበር፡፡ በጣሊያን የቅኝ አድቢዎች ላይ ሁነኛ ምት ያሳረፈው (ዛሬም ድረስ ጣሊያኖች ያልዘነጉት) የዶጋሊ ድል ከተገኘ በኋላ ኢትዮጵያ ምፅዋን ለመያዝ ከመድፈር ከገቷት የውጭና የውስጥ ቀንበጦች መሀል አንዱ ከመሆን ባሻገር፣ ጭራሽ ጣሊያን ወደ ታች እንዲስፋፋ ጠቅሞ ነበር፡፡ ዛሬም ዓብይና ‹ብልፅግና›ን ከሥልጣን ማውረድን የሞት ሽረት ግብግብ አድርጎ መውሰድ የተጋገዘ ሥራ የሚሻውን የዴሞክራሲ ግንባታ ከማጨናገፍም በላይ፣ የኢትዮጵያን ተቆራርሶ መድከም ለሚሹ ኃይሎች ደባ የሚጋልጥም ነው፡፡ ከፊታችን የተደቀነው የምርጫ ውድድር የብሔር ገዥነት ውድድር አይደለም፡፡ ለአማራ የሚያዳላ ለኦሮሞ የሚያዳላ ወይም ለትግሬ የሚያደላ መንግሥት የማቆም ትግል የሚካሄድበት አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ጭንቅ ኢአድሏዊ የሆነ፣ በነገረኛ አቋሞችና ፍላጎቶች ሰላማቸውን የማይበጠብጥ፣ በብልህ አመራር የሌላውን ነገረኝነትም የሚያመክንና ሁሉንም መሠረታዊ መብቶች ሥር የሚያሲዝ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲመጣላቸው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ስሜት ለመንከባከብ እንሠራለን የምትሉ ካላችሁ፣ በአስተሳሰብና በፓርቲ አደረጃጀት ዕድሳታችሁን አሳዩን፡፡ ትርምስን የምንሸሽ ሰዎች ‹ብልፅግና› ፓርቲ ላይ ያዘነበልነው የአደረጃጀትና የአስተሳሰብ ዕድሳት ጅምር ስላየንባቸውና ከሚያናክሱ መስመሮች የራቀ አማካይ መስመርን ሲያቀነቅኑ ስላየን ነው፡፡

ነገር ግን ንቁሪያን የሚዘጋ የፖለቲካ አማራጭ ያለ ‹ብልፅግና› ፓርቲ አጥቶ ቢወዱም ቢጠሉም ‹ብልፅግና› ፓርቲን የመምረጥ አጣብቂኝ ላይ የመውደቅ፣ ለፓርቲው በሥልጣን ለመቀጠል ይጠቅም ይሆናል እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ጉዳት ነው፡፡ ይህ ማለት ምን እንደሆን ከዚህ በፊት ዓይተናል፡፡ በተሻለ አማራጭነት የሕዝብን ድጋፍ ይዞ ከሥልጣን እስከ መግፋት ድረስ ኢሕአዴግን የሚፈታተነው ፓርቲ ቢኖር ኖሮ፣ ምናልባት ኢሕአዴግ የተሻለ ዴሞክራሲያዊና ሕዝብን አዳማጭ ሆኖ ራሱን ባሻሻለ ነበር፡፡ ሕዝብም በተጠቀመ ነበር፡፡ ዛሬም ብልፅግና ፓርቲ እየባነነ እንዲታትር እንጂ ማናለብኝ ብሎ እንዲያናጥርብን እንሻም፡፡

እገሌ ከእገሌ ሳይባል ሁላችንም የቅድመ ዴሞክራሲ (እንዲያውም የአፈና ሥርዓት) ውላጆቹ እንደ መሆናችን የዴሞክራሲን ነፃነቶችና መብቶች ከመፈለጋችን በላይ ኢዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎች ስለሠለጠኑብን፣ ዴሞክራሲያዊ የመሆን ትግላችን ብዙ እንደሚያንገላታን ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ ሁሉም የፖለቲካ ቡድኖች በውስልትልት ዘዴዎች የተጨማለቁ እንደ መሆናቸው፣ ልክ ምርጫው ሲጀምር የሥነ ምግባር ጨዋነት፣ የሕዝብ መብት አክባሪነትና ኢአድሏዊነት ከሰማይ አይወርድላቸውም፡፡ ሸሩን፣ ስም ማጥፈቱን፣ ሾኬውን ሁሉ ሲያስነካ ከኖረ የፖለቲካ ታሪክ የመጣ ፓርቲ ልክ በምርጫው ሲያሸንፍ የዴሞክራሲያዊነት ባህርይን አይጎናፀፍም፡፡ እገሌ ከእገሌ ይሻላል ብሎ ማማረጥ ቢቻልም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ቡድኖችና ግለሰቦች ሁሉ ኢዴሞክራሲያዊ ግሳንግስ ያለብን ነን፡፡ ከውይይትና ከጋለ ክርክር በኋላ መራራ ኩርፊያ፣ ቂምና በቀል ድምፅ አጥፍቶም ሆነ ቀንድ አውጥቶ የማይጫወትብን ምን ያህሎች ነን ብለን ራሳችንን በሀቅ ለመገምገም ብንችል፣ ለዴሞክራሲ ምን ያህል እንግዳ እንደሆንን መረዳት እንችላለን፡፡

ኢዴሞክራሲያዊና ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎችን አሸንፎ በዴሞክራሲ ባህል ውስጥ ነዋሪ የመሆን ዕድልን ተጨባጭ ለማድረግ ሦስት ነገሮች ያስፈልጉናል፡፡ የራሳችንን ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ዝንባሌዎችን ለማራገፍ ፍላጎቱንና ተግባራዊ ጥረቱን ማዳበር አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ከራስ በኩል ያለው ተነሻሸነትና ተፍጨርጫሪነት ሊዝልና ወደ ኋላ ሊመለስ ይችላልና እንዲያ ስንሆን እየነቀፈ የሚያባንነን አጋዥ ከራሳችን ውጪ መኖር ነው፡፡ ሦስተኛው እየተተቻቹ በመተራረምና በዴሞክራሲያዊ ሱታፌ ሁላችንንም የሚኮተኩት ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓተ ኑሮ መገንባት ነው፡፡

የግለሰቦችና የፓርቲዎች መንግሥታዊ አመራር መብቶችን አክባሪና ኢአድሏዊ ሆኖ እንዲቀጥል መተማመኛ ሊሆነን የሚችለው የሥርዓታዊ ቤት በደንብ መገንባት ነው፡፡ የሥርዓት ግንባታችን እንደማይቀለበስ ሆኖ እየጎለበተ መሄድ ከቻለ፣ ሥልጣን ላይ የወጡና ሊወጡ የሚፎካከሩ ግለሰቦችም ሆኑ ቡድኖች ነገረ ሥራ በሥርዓቱ የገሪነት፣ የአበጣሪነት፣ የአጋላጭነትና የጠያቂነት ልጓም ውስጥ ነው፡፡ ባሻኝ ላናጥርባችሁ ባይነት መንበረ ሥልጣኑ ላይ እንዳያኮርት የሚጠብቀንም ይህ ሥርዓታዊ ልጓም ነው፡፡

እንዲህ ያለ ሥርዓት በመገንባት ላይ ከተረባረብን የኦሮሞ፣ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሲዳማ፣ ወዘተ ተወላጅ የኢትዮጵያ ቁንጮ መሪ የመሆኑ ነገር እጅግ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ቀላል ከመሆንም በላይ የትኛውም የብሔረሰብ ሰው በማንነቱ ከሥልጣን አካባቢ አለመገለሉና ዥንጉርጉሮችን አስተባብሮ በመምራት ትባቱ የዓይን ማረፊያ የሆነ፣ ከየትኛውም ብሔረሰብ የወጣ ሰው ወደ ሥልጣን እንዲመጣ መፈለግ አግባብ ነው፡፡ ጉዳያችን ግን በአመራር ሠልቶ የተገኘውን ወንበር መስጠት ብቻ አይደለም፡፡ ከየትኛውም ብሔረሰባዊ ማንነት ውስጥ ስል መሪዎች እንደወርቅ ተኮልተው እንዲወጡና ፌዴራላዊ ሥልጣኑ ብቃት ባላቸው ዥንጉርጉሮች እንዲጨፈጨፍ መሥራት፣ የዚህ ክፍለ ዘመን ፍላጎታችንና እርካታችን መሆን ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ኅብረታችንን እያጣፈጠ ያጠነክራል፣ በዓይነተ ብዙ የሰዎች ልማት ሀብታም ያደርገናል፡፡

አሁን ባለንበት ደረጃ ግን የአንዱን ገመና ሌላው እያየና እየነቀሰ ይህንን ሥርዓት በመገንባት ረገድ ያለብን የነፃ ጋዜጠኝነት፣ የመብት ተከራካሪ ተቋማትና የተደራጀ የብዙኃን ነፃ እንቅስቃሴ ቅርሳችን በጣም በጣም ደካማ ነው፡፡ ይህ ጉደለት የአዲስ ሥርዓት ግንባታችንን ይበልጥ ከባድ ያደርገዋል፡፡

ይህንን ክብደት ለማቅለል አንድ ቀዳዳ አለን፡፡ የዴሞክራሲያዊነት ጉድለትና መሰሪ አካሄድ ሁላችንንም ያጨረተ መሆኑን ተቀብለን የአዲስ ባህልና ሥርዓት ሽግግራችንን የትግግዝ ሥራ ማድረግ፡፡ ትግግዝ ሁላችንንም ከተንኮልና ‹‹ከነካኸኝማ የሚብስ ይብስበታል፡፡ ኩስ የነካው እንጨት አድርጌ በሕዝብ አስጠላሃለሁ. . .›› ከሚል እልህና በቀል እያራቀ በቅንነት ወደ መተቻቸትና ወደ መተራረም ይወስደናል፡፡ ዛሬ ያጣነው እጃችን ያለውን ይህንን ኪሳራ የሌለበትን ፍቱን መድኃኒት የመጠቀም ፈቃደኝነት ነው፡፡ አሁንም በሌላ መልክ ጫን አድርጌ ልናገረው፡፡ ጉዳዩ አንዳችን ለሌላችን በጎ እንሁን የሚል ስብከት አይደለም፣ ሁላችንም ካለንበት ማጥ ውስጥ ተያይዞ የመውጣት ግዴታችንን እንወቅ፣ አውቀንም ሚናችንን እንወጣ ነው፡፡

ስለሆነም ትንንቅ ውስጥ የቆየን ቡድኖች የእስከ ዛሬው ትንቅንቃችን ሕዝቦችን ከማመስ በቀር ትርፍ እንዳላመጣ አምነን ወደ ትግግዝ ለመዞር እንድፈር፡፡ ወደ ውይይት እንምጣ፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶችና መሬት የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ሀብት የሆኑበትን ሕገመንግሥታዊ ድንጋጌ አክብረን፣ ይህ መሬት የእኔ ነው/ከአንተ ወደ እኔ ይምጣ/እኔ ልጠቅልለው በሚሉ ፍላጎቶች የሕዝቦችን ሰላምና መረጋጋት ከመንሳት እንውጣ፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ምፅዋት የሚለመንና በበጎ ፈቃድ የሚለገስ መብት መኖር እንደሌለበት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር የሚነፈገው አካባቢ መኖር እንደሌለበት እንግባባ፡፡ የራስ በራስ አስተዳደር በተናጠልም በጋራ መልክም ሊገለጽ እንደሚችል፣ ንዑስነትና የጥንቅር ጥራት ማጣት መብት መንሻ/መንፈጊያ መሆን እንደማይገባቸው፣ በትልልቅ አካባቢያዊ አስተዳደሮች ውስጥ ጥቃቅን የራስ በራስ አስተዳደሮች ተሳልተው ሊኖሩ እንደሚችሉ እንግባባ፡፡ በአካባቢ አስተዳደሮችም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ደረጃ መኗኗሪያ የሆኑ የሥራ ቋንቋዎችን የመማር/የማውቅ ግዴታን በራስ ቋንቋ ከመማርና ከመሥራት መብት ጋር ለማስማማት እንስማማ፡፡

ፊታችን ያለው የሁለት ሺሕ አሥራ ምናምን ምርጫን ከሥጋት ጨለማ ለማውጣት ፈቃደኛነቱ ካለን፣ ከምርጫ በፊት የሚያግባባ ውል ማበጀት አይገድም፡፡ ለምሳሌ በምርጫው ማንም ያሸንፍ ማን በተከታዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝና በሌሎች ፖለቲካዊ ምክንያቶች ከደረሱ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶች ማገገሚያ፣ ሰላምን አፅንቶ ወደ እመርታ ማኮብኮቢያ በማድረግና የዴሞክራሲ ኢአድሏዊ ተቋማትን በመገንባት ተቀዳሚ ተግባሮች ላይ ተባብሮ ለመሥራት፣ ከዚያ በተረፈ ምናልባት ካስፈለገ ሁሉም የሚስማማባቸውንና ወደፊት ለመራመድ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ከመንካትና ጥናቶች እያካሄዱ በመወያየት ህሊናዊና ሰነዳዊ ዝግጅት ከማድረግ  በስተቀር፣ ሕገ መንግሥት የማሻሻልን ዓብዩን ተግባር ለአምስት ዓመታት ለማዘግየት መስማማት አንድ መላ ነው፡፡ ይህ አማራጭ ተያዘም አልተያዘም አብሮ መሥራትን የሚጠይቁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለውጥን ከሚቀናቀኑና ከሚሸፍጡ ወገኖች የሚመጣ የሰላም አደፍራሽነትን የማምከን ሥራ አንዱ ነው፡፡

  • ማኅበረሰባዊ ጂኦግራፊያዊ አካባቢዎችን ለይተው እንደ ሥልጣን “ጉልተ ርስታቸው” አድርገው እየቆጠሩ ሌሎችን ቡድኖች አትድረሱብን የሚሉ፣ በቀጥታ ባይሉም በእጅ አዙር እያስበረገጉ የሚያበርሩ ቡድኖችም ሌላ ችግር ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ኢዴሞክራሲያዊ ዝንባሌዎችን ለመመከትና ለማሳፈር የሚያስችል አቅም ካልተፈጠረ፣ የምርጫ ሒደትን ከማጉደፍ እስከ ማሰናከል ድረስ ጥፋት ሊሠሩ ይችላሉ፡፡
  • በየትኛውም ፓርቲ በኩል የሚመጣ የምርጫ አጉዳፊነትን ለመከላከልና ለማምከን የምርጫ አስፈጻሚዎችና የሕግ አስከባሪዎች፣ እንዲሁም የሕዝብ ነፃ እንቅስቃሴዎች ኢአድሏዊነትና ንቁነት መጠናከር ወሳኝ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አገራችን ያለባትን ድክመት ለማካካስ የፖለቲካ ቡድኖች ከወዲሁ ምርጫውን ሰላማዊና ነፃ ለማድረግና የፈረሙትን ሥነ ምግባር መኗኗሪያ ለማድረግ ቢጣጣሩ፣ ለምርጫ ቦርድ ተበደልኩ እያሉ በተናጠል አቤት ማለት ከሚያስገኘው የበለጠ ውጤት ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ነፃ የሕዝብና የዴሞክራሲ ማኅበራትና ነፃ ሚዲያዎች በዴሞክራሲ ተቆርቋሪነት ንቁ እንቅስቃሴ ውስጥ ቢገቡ፣ ከመንግሥትም በኩል ሆነ ከፓርቲዎች በኩል የሚመጡ አፈናዎችንና አወላካፊ ተግባራትን በማጋለጥና በማሳፈር ረገድ፣ መካሰስ ከሚያስገኘው የበለጠ ውጤት ያስገኛሉ፡፡ ከዚህ ጋር ፓርቲዎች ምን ዓይነት አቋም እንዳላቸው፣ ምን እንደሚሹና ምን ያህል ለአቋማቸው እንደሚታመኑ ሚዲያዎች ማፍረጥረጥ ቢችሉ፣ ሕዝብ ለሰላሙና ለመብቶቹ መረጋገጥ፣ ብሎም እጅ ለጅ ተያይዞ ለመገስገስ የሚያዋጣውንና የማያዋጣውን ፓርቲ መለየት ይችላል፡፡
  • በለውጡ ጊዜና ዛሬ በዓለም አቀፉ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጊዜ ኢኮኖሚያችን ላይ የደረሰው ክውታ ምን ያህል የዶላርና የውጭ ሸቀጥ ጥገኛ እንደሆንን አሳይቷል፡፡ ኢኮኖሚያችን ሚዛን የሳተ የጥሬ አቅራቢነትና የሸቀጥ ተቀባይነት ላይ የተዋቀረ ቢሆንም፣ የሰንካላነቱ ዋና መገለጫዎች የውጭ ግልባጭነት (‹ሬፕሊካ› መሆን) እና የውጭ ሸቀጥ አግበስባሽነትን የዘመናዊነትና የሥልጣኔ መለኪያ ባደረገ ከተሜነት የተገነቡ ጥገኛ ከተሞቻችን ናቸው፡፡ የማገገም እንቅስቃሴያችን የአገር ውስጥ አምራችነትን በተዋጣ ማራኪነት ከማስፋፋት ጋር በአገር ውጤት መጠቀምንና መኩራትን የማጎልበት ተግባርን ሊዘለው አይችልም፡፡ በዚህ ህሊናንም የኢኮኖሚ መዋቅርንም የመቀየር ተጋድሎ ላይ የፖለቲካኞቹ ተግባብቶ በኅብረት መንቀሳቀስም ወሳኝ ነው፡፡
  • የጥገኝነት ችግርን የማሸነፍ ተልዕኮ ጎረቤቶቻችንንም ይመለከታልና ተጋድሎው በአገር ውስጥ የሚያበቃ አደለምም፡፡ የንግድ ልውውጣችን፣ የብድር መሰጣጣታችንና የብድር አመላለሳችንን ሁሉ ከዶላር ጋር ሳይጣበቅ በደረቅ ሸቀጥ የሚካሄድበትን አካባቢያው አማራጭ ወደ መፈለግም ሊወስድ ይችላል፡፡
  • ቀጣናዊ ድግግፋችን ሰላምን የማዝለቅ፣ ተዛማጅ በሽታዎችንና ተባዮችን የመከላከል የጋራ አቅም ግንባታንና ተቀናጅቶ መንቀሳቀስንም ግድ ይላል፡፡ በእዚሁ ዕይታ ውስጥ የኢትዮ ኤርትራ ሕዝቦችና መንግሥታት ተዛምዶ ሊባርቅ በማይችልበት፣ ስደት በሚቃለልበትና የጋራ መጠቃቀም በሚገኝበት አኳኋን ተግባራዊ ትርጉም እንዲያገኝ መጪው አዲስ ፓርላማና መንግሥት እንዲሠራ አደራ አለበት፡፡

    ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...