Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ መንገደኛና ጭነት ያጓጉዛል እንጂ እስር ቤት የለውም›› አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ዓለምን ጭንቅ ውስጥ የከተተው የኮሮና ወረርሽኝ ኢኮኖሚውን እያሽመደመደው ነው፡፡ ክፉኛ ከተጎዱት የኢኮኖሚ ዘርፎች የአቪዬሽንና የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር በአጠቃላይ አየር መንገዶች 314 ቢሊዮን ዶላር፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ደግሞ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚያጡ ተንብየዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያጣ መሆኑን፣ እንዲሁም እስከ በጀት ዓመቱ መዝጊያ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሊያጣ እንደሚችል አስታውቋል፡፡ ከዘጠና በመቶ በላይ አጠቃላይ የሥራ እንቅስቃሴው የተገታበት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኛ ገበያው ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የተዘጋ ቢሆንም፣ በጭነት ማጓጓዝ ይህን የፈተና ወቅት ለመሻገር በመታገል ላይ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አየር መንገዱ በሠራተኛና በአሠሪ ግጭት ውስጥ ነው፡፡ በአየር መንገዱ ማኔጅመንት ላይ የሙስና ጥያቄ ያነሱ ግለሰቦች የሰላ ትችት በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡፡ ከድርጅቱ ያላግባብ ተባረናል የሚሉ ሠራተኞች በአየር መንገዱ ግቢ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደሚፈጸም እየተናገሩ ነው፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምን ቃለየሱስ በቀለ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የደረሰው ተፅዕኖ ምን ያህል ነው?

አቶ ተወልደ፡- ወረርሽኙ በዓለማችን ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ነው እያስከተለ ያለው፡፡ በአንድ በኩል የዓለማችን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ከቤት እንዳይወጣ ተደርጓል፡፡ ብዙ አገሮች ባወጡት ሕግ በሽታውን ለመከላከል አንዱ መንገድ ሕዝቡ ከቤት እንዳይወጣ፣ እንዳይሰባሰብና እንዳይነካካ ማድረግ በመሆኑ የዓለማችን አንድ ሦስተኛ ሕዝብ ከቤት እንዳይወጣ ተደርጓል፡፡ ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ተማሪዎች ትምህርት አቋርጠው ቤታቸው እንዲቆዩ ተደርጓል፡፡ ይህ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በማዳከሙ በዓለማችን ትልቅ የኢኮኖሚ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ የየአገሩ አጠቃላይ ምርት እያሽቆለቆለ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በርከት ያሉ ሠራተኞች ከሥራ እየወጡ ነው፡፡ በአሜሪካ 40 ሚሊዮን ሕዝብ ሥራውን አጥቷል፡፡ በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ቀዳሚ ተጎጂ የሆነው የአየር መንገድ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ በጉዞ ክልከላዎች ምክንያት ሰዎች ስለማይበሩ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ስለሌለ፣ የቱሪዝም እንቅስቃሴ ባለመኖሩ አየር መንገዶች ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ ቆመዋል፡፡ በተለይ በመንገደኛ ጉዞ ምንም እንቅስቃሴ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ የተነሳ አፍሪካ ውስጥ ብዙ አገሮች ሙሉ በሙሉ የአየር ክልላቸውን ዘግተዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኛ ገበያ ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡ ምናልባት ከአምስት እስከ አሥር በመቶ የሚሆን ነው የቀረው ገበያ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት በቆሙ አውሮፕላኖች ተጨናንቋል፡፡ ማቆሚያ ቦታ ጠቦን አውሮፕላኖቹን አቀራርበን ደርድረን ነው ያቆምናቸው፡፡ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ ስንት ሥራ የሚሠሩ አውሮፕላኖች ተደርድረው ቆመው ስታያቸው ዕንባ ያመጣል፡፡ በታሪካችን ብዙ ቀውስ አሳልፈናል፡፡ ጦርነት፣ ድርቅ፣ የተለያዩ በሽታዎች እንደ ሜርስ፣ ሳርስ፣ ኢቦላ የመሳሰሉ ወረርሽኞች ውስጥ አልፈናል፡፡ የ9/11 የሽብር ጥቃትን አሳልፈናል፡፡ ነገር ግን ኮቪድ-19 እያደረሰ ያለው ቀውስ ከእነዚህ ሁሉ ችግሮች የከፋ ነው፡፡ ኮቪድ-19 በዓለም እጅግ አስፈሪ የሆነ ቀውስ ነው የፈጠረው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ትልቁ ተጎጂ ነው፡፡ የመንገደኛ ገበያ የቀረው አሥር በመቶ ቢሆን ነው፡፡ የተቀረው ሙሉ በሙሉ ቆሟል፡፡ ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ ያለውን ወቅት የተመለከትን እንደሆነ ማግኘት የሚገባንን 550 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሳናገኝ ቀርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊያጣ እንደሚችል ተገልጿል፡፡

አቶ ተወልደ፡- እስከ በጀት ዓመት መዝጊያ ሰኔ መጨረሻ ስናስበው አንድ ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራራቢ ችግር ነው ያለበት፡፡ አንዱና ዋነኛው ኮቪድ-19 ያስከተለው ችግር ነው፡፡ በዓለም ላይ ያሉ አየር መንገዶችን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አንዳንዶቹ በከፍተኛ የመንግሥት ገንዘብ ተሰጥቷቸው ወጪያቸውን እየሸፈኑ ያሉ አየር መንገዶች ናቸው፡፡ ሌሎች የነፍስ አድን ገንዘብ ከማግኘታቸው በፊት በራሳቸው መቆም አቅቷቸው በኪሳራ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሁለቱ ውጪ ነው፡፡ ብቸኛ የሚያደርገው ከስሮ አልተዘጋም፡፡ ሠራተኛ አልቀነሰም፣ የሠራተኛ ደመወዝ አልቀነሰም፡፡ በርካታ አየር መንገዶች ሠራተኛ ቀንሰውም ያለውን ሠራተኛ ደመወዝ  ቀንሰዋል፡፡ የናይጄሪያው አሪክ ኤር 80 በመቶ፣ ኬንያ ኤርዌይስ 35 በመቶ፣ የሩዋንዳ አየር መንገድ 40 በመቶ የሠራተኛ ደመወዝ ቀንሰዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኛ አልቀነሰም፣ ደመወዝም አልቀነሰም፡፡

ሪፖርተር፡የተወሰኑ የአየር መንገዱ ሠራተኞች ተቀንሰናል እያሉ ነው፡፡

አቶ ተወልደ፡ይህ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ የሰው ኃይል ክፍላችን ማኅደር ሊታይ ይችላል፡፡ 14‚000 ያህል ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ አንድ ሺሕ የሚሆኑ ከአቪዬሽን አካዳሚ ወጥተው የሥራ ላይ ልምምድ ላይ ያሉ አሉ፡፡ አንድም ሠራተኛ እንዳልተቀነሰ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ሁለተኛው ነገር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለየት የሚያደርገው ከውጭ ምንም ዓይነት ድጋፍ ሳያገኝ፣ በራሱ እየታገለ ያለ አየር መንገድ መሆኑ ነው፡፡ ወጪውን ቆጥቦ የሚያገኘውን አነስተኛ ገቢ አቻችሎ እዚህ መድረሱ ብቻ አየር መንገዱን ብቸኛ ያደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አየር መንገዱ የገጠመውን ፈተና ለመቋቋም ምን ዓይነት ስትራቴጂ እየተገበረ ነው?

አቶ ተወልደ፡- ራዕይ 2025 ስናዘጋጅ አየር መንገዱን የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ያቀፈ ግሩፕ እናደርገዋለን ብለን ስንነሳ ተቃውሞ ገጥሞን ነበር፡፡ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች መያዝ የራሱ ጥቅምና ጉዳት ስላለው አከራካሪ ጉዳይ ነበር፡፡ ይህ የንግድ ስትራቴጂ የተለያዩ አየር መንገዶችን ገሏል የሚል ክርክር ተነስቶ ነበር፡፡ የዛሬ አሥር ዓመት የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ለማዋቀር ጥቅምና ጉዳቱን አጠናን፡፡ እንደ ምሳሌ አድርገን የወሰድናቸው ሉፍታንዛ አየር መንገድና ብሪቲሽ ኤርዌይስን ነበር፡፡ ብሪቲሽ ኤርዌይስ ቀደም ብሎ የምግብ ዝግጅት ክፍል ነበረው፣ ካርጎ ነበረው፣ የጥገና ክፍል ነበረው፣ ሆቴልም ነበረው፡፡ የተለያዩ የንግድ ተቋማት ነበሩት፡፡ በኋላ በወቅቱ የነበረው ማኔጅመንት ማተኮር ያለብን የመንገደኞች ማጓጓዝ ሥራ ላይ ነው በማለቱ ከሌሎቹ የንግድ ዘርፎች ወጡ፡፡ ዋናው ሥራችን መንገደኛ ማጓጓዝ ላይ መሆን አለበት ብለው ወሰኑ፡፡ የስትራቴጂ ለውጥ አድርገው መንገደኛ ብቻ ማመላለስ ሥራ ላይ ተሠማሩ፡፡ ሉፍታንዛ በአንፃሩ ግሩፑን እያሰፋ ሄደ፡፡ ዛሬ በጥገና ሉፍታንዛ ቴክኒክ ከዓለም ቀዳሚ የጥገና አገልግሎት ሰጪ ኩባንያ ለመሆን  በቅቷል፡፡ በምግብ ዝግጅት ስካይ ሼፍ የተሰኘ ኩባንያቸው በዓለም ቀዳሚ ነው፡፡ በካርጎ አገልግሎት ትልቅ ተቋም ገንብተዋል፡፡ ሉፍታንዛ ሲስተም የበረራ ዕቅድ መቆጣጠሪያ ሲስተም የሚሠራ ድርጅታቸው በዓለም ላይ ትልቅ ተቀባይነት ያገኘ ነው፡፡ እኛም የምንጠቀመው የእሱን ሲስተም ነው፡፡ ሉፍታንዛ በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሠማርቶ ውጤታማ መሆን ችሏል፡፡ ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ የተሻለው አማራጭ የተለያዩ የንግድ ዘርፎችን ማዋቀር ነው ብለን፣ በራዕይ 2025 ስትራቴጄያችን አካተነዋል፡፡ ቀደም ብሎ ብዙም ባያድጉ ያመጣናቸውን ክፍሎች አሉን፡፡ አሁን የአቪዬሽን አካዳሚ የሆነው የሥልጠና ማዕከል፣ የጥገና ክፍሉ ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ፣ ካርጎ ከአየር መንገዱ ጋር የቆየ ክፍል ነበር፡፡ እነዚህን አስፍተንና አዳብረን እንቀጥል ብለን ወሰንን፡፡ የንግድ ዘርፎቹን ለማስፋት ሆቴል አቋቋምን፣ ወደ ኤርፖርት ሥራ ገባን፣ አዲስ የምግብ ዝግጅት ማዕከል ገነባን፣ የጥገና ክፍሉንና አቪዬሽን አካዳሚውን አስፋፋን፡፡ የካርጎና የሎጂስቲክስ ክፍሉን በስፋት አጠናከርን፡፡ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ መግባት አከራካሪ የነበረ ቢሆንም፣ ተገቢውን ጥናት አድርገን አምነንበት የገባንበት ጉዳይ ነው፡፡ በወቅቱ ውሳኔያችን ትክክል መሆኑ ከምንጊዜውም በላይ ዛሬ አረጋግጠናል፡፡ የመንገደኛ ገበያ ሙልጭ ብሎ ሲቆም ዞር ብለን የምናየው ገበያ ካርጎ ነው፡፡

የማኔጅመንት አባላት በመጋቢት ወር ተሰብስበን የመንገደኛ ሥራ በመቆሙ መቼ እንደሚጀመር አናውቅም፣ ዛሬ በሙሉ ትኩረታችን ካርጎ ላይ መሆን አለበት ብለን ወሰንን፡፡ አጠቀላይ አሠራራችንን በፍጥነት ወደ ካርጎ እናዙረው ብለን ስንወስን የካርጎ ገበያው ተንቀሳቀሰ፡፡ ይህ የሆነው በየካቲትና በመጋቢት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ቻይና በአብዛኛው ተዘግቶ ነበር፡፡ ቻይና ሁላችንም እንደምናውቀው የዓለም የማምረቻ ማዕከል ናት፡፡ ቻይና ተዘግታ ስለነበር የአቅርቦት ሰንሰለቱ፣ ፋብሪካዎች፣ የፍጆታ ዕቃዎች መንቀሳቀስ አልቻሉም ነበር፡፡ መንገዶች ተከፋፍተው ቻይና ወደ ምርት ስትገባ ለወትሮ በመርከብ የሚጓጓዙ ዕቃዎች በሙሉ ወደ አውሮፕላን መጡ፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሕይወት አድን የሆኑ የፊት ጭምብል፣ የመመርመሪያ መሣሪያ፣ የሕክምና ሠራተኞች የመከላከያ ልብሶችና የመሳሰሉት ዕቃዎች በፍጥነት ማድረስ ያስፈልግ ነበር፡፡ በሽታው በተለይ አውሮፓ በፍጥነት ነበር የተዛመተውና እነዚህን ዕቃዎች በአፋጣኝ ከቻይና ወደ አውሮፓ ማጓጓዝ ጊዜ የማይሰጥ የሕይወት አድን ርብርቦሽ ሥራ ነበር፡፡ ይህ የአየር የጭነት አገልግሎትን በከፍተኛ ፍጥነት ተፈላጊ አደረገው፡፡ በድንገት የተፈጠረ ገበያ ሊጠቀም የሚችለው ተዘጋጅቶ የቆየ አየር መንገድ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በካርጎ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት አድርጎ ግዙፍና ዘመናዊ የጭነት አውሮፕላኖችና ትልቅ ዘመናዊ የካርጎ ተርሚናል ቀደም ብሎ መገንባቱ፣ በቅጽበት የተፈጠረውን ገበያ ተጠቃሚ እንዲሆን አስችሎታል፡፡ እኛም ቶሎ ብለን አሥር ቦይንግ 777 አውሮፕላኖች ይዘን ከመጋቢት ወር ጀምረን በአውሮፓ ስፔን፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ እንግሊዝና ጀርመን የሕክምና መሣሪያዎችን አጓጉዘናል፡፡ የካርጎ አውሮፕላኖቻችን ከአውሮፓ ኤርፖርቶች አይጠፋም ነበር፡፡ በየዕለቱ የሕክምና መሣሪያዎች በፍጥነት ከቻይና ወደ አውሮፓ አገሮች አጓጉዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንደ ሉፍታንዛ ካርጎ፣ ተርክሽ ካርጎ፣ ኳታርና ኢትሃድ ካርጎ ያሉ ግዙፍ የካርጎ አየር መንገዶች እያሉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ካርጎ እንዴት ተወዳድሮ ነው አውሮፓ ገበያ ሊገባ የቻለው?

አቶ ተወልደ፡– ትልልቅ ድርጅቶች ሲሠሩ ዝሆን ሲደንስ እንደ ማለት ነው፡፡ ዝሆን ሰውነቱ ትልቅ በመሆኑ ለመደነስ ይቸገራል፡፡ እነዚያ ግዙፍ አየር መንገዶች ሰፊ ቢሮክራሲ ያላቸው በመሆኑ፣ ቶሎ ብለው ይህን የገበያ ዕድል ለመጠቀም ይከብዳቸዋል፡፡ የስትራቴጂ ለውጥ ለማድረግ ወራት ይፈጅባቸዋል፡፡ እንደኛ ዓይነቱ አነስ ያለ፣ በኢንዱስትሪው 30 ወይም 35 ዓመታት ያገለገለና አመራር ያለበት አየር መንገድ ቶሎ ዕርምጃ ወስዶ በፍጥነት ገበያው የሚፈልገውን ያውቀዋል፡፡ ፍጥነት ወሳኝነት አለው፡፡ ዕድሉ የሚቆየው ለአጭር ጊዜ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ካልተጠቀምንበት ያልፋል፡፡ ፍጥነታችን ጠቅሞናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ካርጎና ሎጅስቲክስ ባለፉት ሦስት ወራት ምን ያህል ጭነት አጓጉዟል?

አቶ ተወልደ፡- በመጋቢት 10‚300 ቶን፣ በሚያዝያ 13‚600 ቶን፣ በግንቦት ወር አጋማሽ ድረስ 6‚000 ቶን አጓጉዘናል፡፡ ከፍተኛ መጠን ያለው ካርጎ አጓጉዘናል፡፡

ሪፖርተር፡- የጭነቱን ጭማሪ በመቶኛ ምን ያህል ይሆናል?

አቶ ተወልደ፡- የካርጎ ገበያ ጭማሪ ከ50 በመቶ በላይ ነው፡፡ እኛን የረዳን በመጋቢት ወር ካርጎና ጥገና ሥራ ላይ ለማተኮር መወሰናችን ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች የኮሮና በሽታ አላጠቃቸውም፡፡ አሥር ቢ 777 የጭነት አውሮፕላኖች አሠማርተን ገበያውን ስናየው ከዚያ በላይ በመሆኑ፣ የመንገደኛ አውሮፕላኖች ወንበር ላይ መጫን ጀመርን፡፡ የመንገደኛ አውሮፕላን ቻይና ባዶውን እንልከዋለን በሆዱ ዕቃ ይጭናል፡፡ ትልቅ አውሮፕላን መንገደኛ ወንበር ላይ ከ50 እስከ 60 ቶን ይጭናል፡፡ መካከለኛ አውሮፕላን እስከ 40 ቶን ይጭናል፡፡ ከቻይና በቀጥታ አውሮፓ የሚላክ አለ፣ በአዲስ አበባ በኩል የሚያልፍ አለ፡፡ ለተወሰነ ጊዜ በመንገደኛ ወንበር ላይ እየጫንን ከቆየን በኋላ ወንበር እንዳይጎዳብን ከቦይንግና ከኤርባስ ኩባንያዎች ጋር ተነጋግረን፣ የራሳችን ኢንጂነሮች ወንበሩን አውጥተው ለዕቃ መጫኛ ምቹ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ የአውሮፕላን ሥራ ውስብስብ በመሆነ ብዙ የተከናወነ ሥራ አለ፡፡ ብዙ ሥራዎች ተሠርተው 25 የመንገደኛ አውሮፕላኖች ወደ ካርጎ አዙረናል፡፡ ይህን በማድረጋችን ከሌሎች ግዙፍ አየር መንገዶች ቀድመን ገበያውን ለመውሰድ ችለናል፡፡

ሪፖርተር፡– ፋይናንሺያል ታይምስ በቅርቡ ባቀረበው ዘገባ የደቡብ አሜሪካ አገሮች የኢትዮጵያ ካርጎ እንደ ደረሰላቸው መግለጻቸውን አስነብቧል፡፡ ከቻይና የገዘዋቸውን የመተንፈሻ መሣሪያዎች በአሜሪካ በኩል ወደ ብራዚል ሲያጓጉዙ እንደ ተወሰደባቸው ጠቁሟል፡፡ ምንድነው የተፈጠረው?

አቶ ተወልደ፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ታዳጊ ኢኮኖሚ ከሆነችው ኢትዮጵያ ተነስቶ፣ ለእነ ብራዚልና አርጀንቲና ለችግራቸው ጊዜ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ማንም ሊያስበው አይችልም፡፡ ይህ ግን በተግባር ሆኗል፡፡ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከፍተኛ የመተንፈሻ መሣሪያ እጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሰው እንደ ቅጠል በተለይ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶች በአውሮፓ አሜሪካ እየረገፉ ነበር፡፡ ከፍተኛ የመሣሪያ እጥረት ተከስቶ ነበር፡፡ የደቡብ አሜሪካ አገሮች ለመዘጋጀት መሣሪያውን ከቻይና ገዙ፡፡ መሣሪያው ከቻይና በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ አድርጎ ወደ ደቡብ አሜሪካ ነው የሚጓጓዘው፡፡ በአሜሪካ ማያሚ በኩል አድርጎ ወደ ብራዚልና አርጀንቲና ሲጓጓዝ ማያሚ ላይ የመተንፈሻ መሣሪያ ተወስዶባቸዋል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሲያዙ ግን በቀጥታ አውሮፕላኖቹ ከቻይና በአዲስ አበባ በኩል ብራዚል ስለሚበሩ ዕቃቸው ሳይነካባቸው ይደርሳቸዋል፡፡ ነዳጅ ለመቅዳት በሚቆሙበት ወቅት ብዙ መሣሪያዎች ስለተወሰዱባቸው እኛ ከቻይና በቀጥታ በአፋጣኝ ሳይነካባቸው በማድረሳችን እንደ ትልቅ ባለውለታ ቆጥረውናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ብራዚል ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ዜጎች ያላት አገር ናት፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለብራዚል ወሳኝ አገልግሎት ሰጥቷል፣ እነርሱም አመሥግነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ካርጎ ጥሩ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ካጣችሁት የመንገደኞች ማጓጓዝ ገቢ አንፃር የካርጎ አገልግሎት ምን ያህል ገቢ እያመጣ ነው? ምን ያህል እየረዳችሁ ነው?

አቶ ተወልደ፡- የኢትዮጵያ አየር በመንገድ መጋቢት ወር ይህ ችግር እስከሚገጥመን ድረስ ዕድገት ላይ ነበር፡፡ ይህ ችግር ሲፈጠር ዕድገቱን አቁመን ህልውናን ወደ ማረጋገጥ ቀየርን፡፡ ዕድገቱን ለጊዜው በመግታት ህልውናን ወደ ማረጋገጥ ርብርብ ገባን፡፡ አየር መንገዱ ይህን የመከራ ጊዜ ማሻገር የሚለው ላይ እየሠራን ነው ያለነው፡፡ በየወሩ የምንሠራው ለትርፍና ለኪሳራ ሳይሆን ጥሬ ገንዘብ ለማግኘት ሆኗል፡፡ በዚህ የችግር ወቅት ጥሬ ገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡ አየር መንገዱ ወጪውን የሚቻለውን ያህል ቆጥቦ የማይቀሩ ግዴታ የሆኑ ወጪዎችን ይዞ መቀጠል የሚቻልበት ላይ እየሠራን ነው፡፡ የአውሮፕላን ብድር ከእነ ወለዱ፣ የአውሮፕላን ወርኃዊ ኪራይ (በኪራይ የመጡ አውሮፕላኖች)፣ የሠራተኛ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅሞች፣ የቢሮ ኪራይና የመሳሰሉ ቋሚ ወጪዎች፣ ለረጅም ጊዜ የገባናቸው ውሎች ብቻ ይዘን በቁጠባ በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡ወርኃዊ የደመወዝ ወጪያችሁ ምን ያህል ነው?

አቶ ተወልደ፡- የደመወዝ ወጪያችን በወር 650 ሚሊዮን ብር አካባቢ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የቋሚና የኮንትራት በአጠቃላይ 17‚000 ያህል ሠራተኞች ወርኃዊ ደመወዝ ማለት ነው?

አቶ ተወልደ፡- አዎ፡፡ ወርኃዊ የደመወዝ ወጪያችንን 650 ሚሊዮን ብር አካባቢ ይሆናል፡፡ ዕዳም አለ፣ የአውሮፕላን ኪራይ ክፍያ አለ፡፡ እነዚህን ወጪዎች ይዘን የሠራተኛውን ደመወዝ ሳንነካና ሠራተኛ ሳንቀንስ መቀጠል አለብን ብለን በመጋቢት ወር ነው የወሰንነው፡፡ በእኛ አገር ሠራተኛ ቀንሰህ አስቸጋሪ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ መቼም የግድ ከሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡ ይህ አውሮፓ ወይም አሜሪካ አይደለም፡፡ የመጀመርያ ውሳኔ አታደርገውም፡፡ የማኅበራዊ ዋስትና ክፍያ ስለሌለ ሠራተኛ መቀነስ የመጨረሻ አማራጭ ነው፡፡ ሠራተኛ አንቀንስም፣ የሠራተኛ ደመወዝ ካልተቸገርን በስተቀር አንቀንስም ብለን ድርጅቱን በሕይወት የማቆየት ሥራ እንሥራ ብለን ስንነሳ፣ በካርጎና በጥገና ዘርፍ የምናገኘውን ገቢ ቆጥበን እየተጠቀምን ነው፡፡ የካርጎና የጥገና ገቢ የመንገደኛን ገቢ አያክልም፡፡ ከአጠቃላይ ገቢያችን 85 በመቶ መንገደኛ በማጓጓዝ ነው የምናገኘው፡፡ ካርጎና ጥገና ተደምሮ 15 በመቶ ጥገና ገቢ አንድ ፐርሰንት ነው፡፡ የካርጎና ጥገና ገቢን በጥሬ ገንዘብ በማስገባት አሁን ያለንበት ቀን ድረስ ደርሰናል፡፡ ካርጎ ገቢው ትንሽ ቢሆንም አትራፊ ነው፡፡ ወጪያችንን ችለን የሚተርፈንን ለአውሮፕላን ኪራይ፣ ለብድር ክፍያ፣ ለሠራተኛ ወጪዎችና ለሌሎች ቋሚ ወጪዎች መድበናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከካርጎና ከጥገና የምታገኙት ደመወዝና ሌሎች ቋሚ ወጪዎችን ይሸፍናል?

አቶ ተወልደ፡– እየሸፈነልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ካርጎ ሌላው የሚጠቀሰው ተግባሩ ወደ ኢትዮጵያ የሕክምና መሣሪያዎች ማጓጓዝ ነው፡፡ ከዚህ ተጨማሪ የመተንፈሻ መሣሪያ ምርት ለመጀመር እንቅስቃሴ ጀምሯል የሚል ነገር በቅርቡ ተናግረዋልና ስለሱ ዝግጅት ቢነግሩን?

አቶ ተወልደ፡- ይህ የተለያዩ የንግድ ዘርፎች የማስፋፋት አንዱ አካል ነው፡፡ ቅድም ያልጠቀስኩት ያቋቋምነው ስካይላይት ሆቴል በመጠኑም ቢሆን እየጠቀመን ነው፡፡ ለኳራንቲን ማዕከል ከተመረጡ 18 ሆቴሎች አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የሆቴል ሥራ የተጎዳ ቢሆንም፣ ለትራንዚት መንገደኞች ማሳረፊያነትና በኳራንቲን ማዕከልነት በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ የአውሮፕላን ጥገና ማዕከላችን የሳዑዲ ቢ 777 አውሮፕላኖችን በመጠገን አነስተኛም ቢሆን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ የቬንትሌተር ምርትን በተመለከተ ለዋናው ሥራችን በጣም የራቀ ነው፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የጀመርንበት ምክንያት እንደ ንግድ ሥራ አልነበረም፡፡ የቬንትሌተር እጥረት በመፈጠሩና የነበሩት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ቬንትሌተሮች ሳይጠገኑ ረዥም ጊዜ የተቀመጡ ስለነበሩ፣ ይህ ወረርሽኝ ከተስፋፋና ከአቅም በላይ ቢሆን ምንድነው የምናደርገው ተብሎ በብሔራዊ የሚኒስትሮች ኮሚቴ ሲነሳ፣ አንደኛ ያሉትን የተበላሹ ቬንትሌተሮች አምጥተን እንድንጠግን ከዚያ ባለፈም በአጭር ጊዜ ውስጥ እዚሁ እንድናመርት የቤት ሥራ ተሰጠን፡፡ የቬንትሌተር ጥገና ሥራ በአግባቡ ተወጥተናል፡፡ ያለ ምንም ክፍያ ከ40 በላይ ቬንትሌተሮች ከየሆስፒታሉ አምጥተን ጠግነን መልሰናል፡፡ ለሥራው የሰው ኃይል ሳይጨምር ወደ 20‚000 ዶላር አውጥተናል፣ ለመለዋወጫ መግዣ፡፡ ከአንድ የቻይና ኩባንያ ጋር በመተባበር እዚሁ አገራችን ቬንትሌተር ለማምረት ዝግጅት አድርገናል፡፡ የፋብሪካው ዲዛይን ተሠርቷል፡፡ አሁን ግን በአብዛኛው ስናየው በዓለም ላይ በአጭር ጊዜ በርከት ያለ ቁጥር ቬንትሌተር ተመርቷል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ አምርተዋል፡፡ ቻይና ውስጥ 20 የሚሆኑ ደርጅቶች በስፋት አምርተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሽሚያው እየቀነሰ በመምጣቱ እኛ የማምረቱን ሒደት እንቀጥል ወይስ እንተወው የሚለውን እያየን ነው፡፡

ሪፖርተር፡የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሠራተኞች እንዳልቀነሰና የሠራተኞች ደመወዝም እንዳልቀነሰ ነግረውናል፡፡ ከመንግሥት በብድር ወይም በስጦታ ድጋፍ አልጠየቀም ብለዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ምን ያህል ሊጓዝ ይችላል?

አቶ ተወልደ፡- አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ደች ኬኤልኤም 4.2 ቢሊዮን ዩሮ፣ ኤር ፍራንስ 7.2 ቢሊዮን ዩሮ ከመንግሥታቶቻቸው አግኝተዋል፡፡ የአሜሪካ አየር መንገዶች ቃል ከተገባላቸው 58 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 25 ቢሊዮን ዶላር አግኝተዋል፡፡ የችግሩ ማብቂያ በዚህ ጊዜ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ መጪውን ጊዜ በትክክል ማወቅ ባይቻልም በዕቅዳችን መሠረት ከካርጎ፣ ከምግብ ዝግጅት፣ ከጥገናና ከሆቴል የምናገኛትን ገንዘብ ቆጥበን ለቋሚ ወጪዎች እያደረግን እንቀጥላለን የሚል ሐሳብ ነው ያለን፡፡ ይህ ህልውናን የማረጋገጥ ጥረት ነው፡፡ ምን ያህል ርቀት ይወስደናል የሚለው እጠያያቂ ነው፡፡ መቼም ሕይወት በአንድ ወቅት ወደ ነበረበት መመለሱ አይቀርም፡፡ የሰው ልጅ እንዲሠራ፣ ሠርቶ ገቢ አግኝቶ እንዲንቀሳቀስ እንጂ ቤቱ ታፍኖ እንዲኖር እይደለም የተፈጠረውና በሒደት መከፈቱ አይቀርም፡፡ አሁን እንደሚታየው አውሮፓና አሜሪካ እየተከፈተ ነው፡፡ ጥንቃቄ እየተደረገ የአየር ትራንስፖርት መከፈቱ አይቀርም፡፡ በሐምሌ ወር ይከፈታል የሚል ግምት አለን፡፡ ሐምሌ ተከፈተ ማለት መንገደኛ ወዲያው ይመለሳል ማለት አይደለም፡፡ ረዥም ጊዜ ይወስዳል ወደ ቀድሞ ቁጥር ለመመለስ፡፡ ይህን አስቸጋሪ ወቅት ለማለፍ በካርጎ ሥራ ላይ በመረባረብና ወጪን በመቆጠብ መቀጠል ነው፡፡ የአየር ትራንስፖርት በሚከፈትበት ወቅት የሚሞቱ አየር መንገዶች ብዙ ናቸው፡፡ የምንተርፈው ጥቂት አየር መንገዶች የገበያ ዕድል ይከፍትልናል፡፡ ምክንያቱም አዳዲስ ገበያዎች እናገኛለን፡፡ የሚሞቱ አየር መንገዶች ይሸፍኑ የነበረውን ገበያ ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ለዚያ ተዘጋጅተን መጠበቅ ብልህነትን ይጠይጠቃል፡፡ በተለይ አፍሪካ ድሮም ቢሆን ደካማ አየር መንገዶች የበዙበት አኅጉር እንደ መሆኑ መጠን፣ ብዙ ጉዳቶች እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡ እኛ ይህን ከባድ ጊዜ አልፈን ወደ ማገገም በምንመጣበት ጊዜ ሰፊ የገበያ ዕድል እንደሚፈጠር እንገምታለን፡፡ ያንን ዕድል ተጠቅመን በቶሎ እንደምናገግም እንገምታለን፡፡ ይህን ሁሉ ቀመር ውስጥ አስገብተን ስንገመግመው፣ ይህን የችግር ወቅት እንሻገረዋለን የሚል እምነት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችን የብድር ሽግሽግ ጠይቃችኋል? በኪራይ ያመጣችኋቸውን አውሮፕላኖችን መልሳችኋል?

አቶ ተወልደ፡- በኪራይ የመጡ አውሮፕላኖችን አልመለስንም፡፡ ይመጡ የነበሩ አዳዲስ አውሮፕላኖች እንዲዘገዩ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- በግዥ የሚመጡስ?

አቶ ተወልደ፡– በግዥም በኪራይም የሚመጡ አውሮፕላኖችን እንዲዘገዩ አድርገናል፡፡ የሚመጡ አንድ አራት አውሮፕላኖች እንዲቆዩ አድርገናል፡፡

ሪፖርተር፡በኪራይ የመጡ የመንገደኛ አውሮፕላኖች የማይሠሩ ከሆነ፣ ቦሌ ኤርፖርት ከሚቆሙ ለምን አይመለሱም?

አቶ ተወልደ፡- የኪራይ አውሮፕላኖችን የማንመልስበት ምክንያት ቅጣቱ ብዙ ስለሚሆን ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ኪራይ ውል ያመጣነውን አውሮፕላን ዛሬ እንመልስ ብንል የውለታውን ጊዜ ኪራይ ክፍያ ይጠይቁናል፡፡ ለአሥር ዓመት የተከራየነውን አውሮፕላን በሦስት ዓመቱ እንመልስ ብንል የአሥር ዓመት ኪራይ ክፍያ ያስከፍሉናል፡፡ ስለዚህ ማቆየቱ ይሻላል፡፡

ሪፖርተር፡የኪራይ ዋጋ እንዲቀንሱ አልተደራደራችሁም?

አቶ ተወልደ፡– እሱም ቢሆን የገባነው ውል ስላለ አስቸጋሪ ነው፡፡ አከራዮችና አበዳሪዎች ከእየ አየር መንገዱ ጥያቄ ስለሚጎርፍባቸውና የከሰሩ አየር መንገዶች ብዙ በመሆናቸው፣ እኛ የተሻለ ደረጃ ላይ በመሆናችን አከራዮቹም ይህን ስለሚያውቁ ብዙ አልተሳካልንም፡፡ የከሰሩ አየር መንገዶች አውሮፕላናችሁን ውሰዱ ሲሏቸው፣ ያው የኪሳራ ሒደት በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚተዳደር በመሆኑ ፍርድ ቤት ያስገድዳቸዋል፡፡ ይህ ድርጅት ስለከሰረ አውሮፕላኖቻችሁን ውሰዱ ነው የሚባሉት፡፡ እኛ ግን ከስረን ስላልዘጋን ያን ለማድረግ አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- ብድር እንዲሸጋሸግላችሁና የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላችሁ ድርድር አካሂዳችኋል?

አቶ ተወልደ፡- ሞክረናል ነገር ግን ተስፋ ያለው አይደለም፡፡ ከዓለም ባንክ፣ ከአይኤፍሲ፣፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከኤዥያ ኢንፍራስትራክቸር ዴቨሎፕመንት ባንክ ሞክረናል፡፡ ግን አልተሳካም፡፡ ቢሮክራሲው በጣም ረዥም በመሆኑ ለንግድ ተቋም የሚሆን አይደለም፡፡ ሁለተኛ የሚጠይቁት ወለድ እኛ ከምንሠራበት ይበልጣል፡፡

ሪፖርተር፡ለአውሮፕላን ግዥ ከባንኮች የወሰዳችሁት ብድርስ?

አቶ ተወልደ፡- እነሱን ብድሮች እየከፈልን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙላችሁ አልጠየቃችሁም?

አቶ ተወልደ፡- ከተቸገርን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ እስካሁን ግን መጠየቅ አልፈለግንም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ74 ዓመታት ዕድሜው ብድሩን በወቅቱ በመክፈል በጣም የታወቀ ነው፡፡ የመጨረሻ ከባድ ችግር ውስጥ ካልገባን በስተቀር የብድር መክፈያ ጊዜ እንዲራዘም አንጠይቅም፡፡ ምክንያቱም የክሬዲት ሬቲንግ ውጤታችንን ይቀንሰዋል፡፡ ስለዚህ ካልተገደድን በቀር እሱን ማድረግ አንፈልግም፡፡ ከባድ ጊዜ ውስጥ ነን፡፡ ነገር ግን የባሰ ሁኔታ መጥቶ ካልተገደድን በስተቀር የብድር መክፈያ ጊዜ ማራዘሚያ ጥያቄ አናቀርብም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብዙ ወቀሳዎች እየቀረቡበት ነው፡፡ ወቀሳዎቹን ጨመቅ አድርገን ስናቀርባቸው አንደኛ ከፍተኛ የሆነ ሙስና እንደሚፈጸም፣ በሌላ በኩል የሠራተኞች የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳለ፣ እንዲሁም ሠራተኞች ያላግባብ ይባረራሉ የሚሉ ቅሬታዎች ይሰማሉ፡፡ አየር መንገዱ በራሱ መንግሥት ሆኖ፣ ሠራተኞቹን የሚያስርበት እስር ቤት አለው የሚሉ አቤቱታዎች እየቀረቡ ነው፡፡ በፊት በማኀበራዊ የትስስር ገጾች ይቀርቡ የነበሩ ቅሬታዎች አሁን በቴሌቪዥን ጭምር እየቀረቡ ነው፡፡ ለእነዚህ አቤቱታዎች የአየር መንገዱ ማኔጅመንት ምላሽ ምንድነው?

አቶ ተወልደ፡- ጥሩ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ አቤቱታዎቹ ያስቁኛል፡፡ የምስቅበት ምክንያት አለኝ፡፡ እንዲህ ዓይነት አቤቱታዎች እየቀረቡ እንዴት ትስቃለህ የሚል ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ እኔ የምስቀው ‹በሬ ወለደ› ዓይነት ውሸት ተቀነባብሮ ስለሚቀርብ ነው፡፡ የሚቀርበው የፈጠራ ድራማ ስለሆነ ይህንን ድራማ ለሚሰማ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ግራ ሊያጋባው ይችላል፡፡ ነገር ግን ውሎ አድሮ ሀቅ መውጣቱ አይቀርም፡፡ ማንኛውም ሰው ይህን ሰምቶ ዝም አይልም፡፡ ማጣራቱ አይቀርም፡፡ መንግሥት ያጣራል፣ የሚመለከታቸው ድርጅቶች ያጣራሉ፣ አበዳሪዎች ያጣራሉ፣ ምክንያቱም ገንዘባቸው ያለው እኛ ጋ ነው፡፡ ሠራተኛው ያጣራል፣ ትልልቅ ደንበኞች አንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የመሳሰሉት ይህ ነገር እውነት ነው ወይ ብለው ማጣራታቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ሁሉ አካላት ማጣራታቸው አይቀርም፡፡ ሲያጣሩ ምንም ዓይነት ነገር እንደማያገኙ ስለማውቅ ነው የምስቀው፡፡

ሪፖርተር፡- ቀደም ሲል የተለያዩ ግለሰቦች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በብዕር ስም እያደረጉ ነበር የሚጽፉት፡፡ አሁን ግን በቴሌቪዥን ጭምር በግልጽ እየቀረቡ ነውና ይህን ነገር ሙሉ በሙሉ ፈጠራ ነው ማለት ይቻላል? በቴሌቪዥን ቀርበው ምሥላቸው እየታየ በቃለ መጠይቅ የሚቀርቡ ግለሰቦች የሚናገሩት እውነትነት የለውም? የሚያጣቅሱዋቸው መረጃዎችም አሉ እኮ?

አቶ ተወልደ፡– ጃክ ዌልች የሚባል የግዙፉ የጄኔራል ኤሌክትሪክ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆኖ የመራ ታዋቂ ግለሰብ ነበር፡፡ አሁን በሕይወት የለም፡፡ ኩባንያውን ለ20 ዓመታት የመራና በስኬት ያሸጋገረ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነበር፡፡ ጃክ ዌልች የሚጠቀስ አባባል አለው፡፡ ይህም ውጤታማ ኩባንያዎች ጠላት አያጡም የሚል ነበር፡፡ አንድ ኩባንያ ወይም አመራር ስኬታማ እየሆነ ሲሄድ ምቀኛ ይበዛበታል፣ ወደኋላ ሊጎትተው የሚሞክር አካል አያጣም ይል ነበር፡፡ በጣም ትክክል ነው፣ እውነቱን ነው፡፡ በውጭው ዓለም በስኬት ማማ ላይ የሚታየው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በየአቪዬሽን ጉባዔው የሚመሠገነው፣ የሚሸለመውና ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሚሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ አገር ቤት ስትመጣ የሚወራበት አሉባልታ የሚገርም ነው፡፡ ዓለም ያደነቀው ስኬት፣ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ያደነቁት ስኬት፣ ዕድገት፣ ትርፍና ማስፋፊያ ሙስና ቢኖረው ኖሮ፣ የመልካም አስተዳደር ችግር ቢኖረው ኖሮ እንዴት እዚህ ደረጃ ሊገኝ ይችላል ተብሎ ሊጠየቅ ይገባል፡፡ የአፍሪካ አየር መንገዶችን የገደላቸው አንዱ ምክንያት ሙስና ነው፡፡ የኬንያ ኤርዌይስን የዛሬ አራት ዓመት ስናጣራ 80 በመቶ የአውሮፕላን መለዋወጫ የሚገዛው በደላሎች አማካይነት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዕቃ ግዥ ላይ ደላላ ማስገባት በፖሊሲ የተከለከለ ነው፡፡ ይህንን የተቀነባበረ ድራማ የሚመለከተው አካል መርምሮና ኦዲት አድርጎ ስለሚያገኘው ብዙ የሚያሳስብ አይደለም፡፡

ወደ ግለሰቦቹ ስንመጣ የፈጠራ ድራማ እያቀነባበሩ በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎችም ሚዲያዎች የሚቀርቡት ግለሰቦች እነ ማን ናቸው ብለን እንጠይቅ፡፡ ሁሉም ግለሰቦች ከጥቅም ጋር የተያያዘ ጥያቄ ያላቸው ናቸው፡፡ ግለሰቦቹ ከድርጅቱ ጋር የተያያዘ የጥቅም ግጭት ያላቸውና በቀል ውስጥ የገቡ ናቸው፡፡ ስም እየጠቀስኩ መናገር እችላለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ የተለያዩ ሚዲያዎች በመጠቀም በሬ ወለደ የውሸት ጋጋታ እያቀረበ ያለ ግለሰብ ጀርመን ነዋሪ የሆነና የጀርመን ዜግነት ያለው ግለሰብ ነው፡፡ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ጀርመን አገር ብዙ ጊዜ የኖረ ሰው ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጉዞ ወኪል ሆኖ ፍራንክፈርት ትኬት ሲሸጥ ነበር፡፡ በዚያ ሒደት ውስጥ ምን እንዳጋጠመው አይታወቅም  ለኢትዮጵያ አየር መንገድ መክፈል የነበረበትን 800‚000 ዩሮ ክፍያ ሳይፈጽም ቀረ፡፡ ከዚያ ጠርተን ስናነጋግረው እከፍላለሁ ችግር አጋጥሞኝ ነው አለ፡፡ ችግሩን ስንጠይቀው የተለያየ ነገር ነው የሚነግረን፡፡ ገንዘቡን ክፈል አልነው፡፡ እሺ እከፍላለሁ በየወሩ አድርጉልኝ አለ፡፡ ትኬት ሸጦ ከሚያገኘው ኮሚሽን ገቢ በወር 10‚000 ዩሮ ለመክፈል ተስማማ፡፡ አንድ ሁለት ዓመት እንደ ከፈለ ከ800‚000 ወደ 500‚000 ዩሮ ቀነሰ፡፡ ቀሪ ሒሳቡ በኢትዮጵያ ወደ 17 ሚሊዮን ብር ይሆናል፡፡ ወደ 510‚000 ዩሮ ሲቀረው ክፍያውን አቋረጠ፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ከደንበኞች ክፍያ ተቀብሎ ትኬት ሳይሰጥ፣ መላክ ያለበትን ኤሌክትሮኒክ ትኬት  ሳይልክ ይቀራል፡፡ መንገደኞቹ ፍራንክፈርት ኤርፖርት ሄደው ሊሳፈሩ ሲሉ ትኬት የላችሁም ሲባሉ ከፍተኛ ቁጣ ውስጥ ይገባሉ፡፡ በርከት ያሉ ችግሮች ሲፈጠሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አምነው ስለሆነ ክፍያ የፈጸሙት እኛ ትኬት ሰጥተናቸው ደንበኞቹን አጓጓዝን፡፡ ለአንዳንዶቹም ግለሰቡ ራሱ ከፈለላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ግንኙነታችንን አቆምን፡፡ ከሲስተማችን የነበረውን ግንኙነት አቋረጥን፡፡ የባንክ ዋስትናውንም ወሰድን፡፡ መልሱልኝ አለ ልንመልስለት እንደማንችል አሳውቀነዋል፡፡ ልንመልስልህ የምንችለው ያለብህን 510‚000 ዩሮ ስትከፍል ነው አልነው፡፡ ያለበትን ገንዘብ መክፈል ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወሰድን፡፡

በዚያን ወቅት አንጎላ የተያዘብን ገንዘብ ነበር፡፡ በየጊዜው ሪፖርት ስናደርግ የነበረው በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ናይጄሪያ፣ ግብፅ፣ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ዚምባብዌ የተያዘብን ገንዘብ ነበረን፡፡ ይህንን ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ማኅበር የሚያውቀውና እናንተም የዘገባችሁት ጉዳይ ነው፡፡ በአንጎላ የተያዘብን ገንዘብ ማውጣት አልቻልንም፡፡ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ኤምባሲ እዚያው እንሥራበት የሚል ሐሳብ አቅበን ከውጭ ጉዳይ ጋር እየተነጋገርን ነበር፡፡ ቤትም ለመግዛት ሞክረን ነበር አልቻልንም፡፡ ይህ ግለሰብ እኔ ገንዘቡን ላስወጣላችሁ እችላለሁ አለን፡፡ እንዴት ስንለው ከአንጎላ መንግሥት ጋር ግንኙነት አለኝ እችላለሁ ብሎ ከሥራ ባልደረቦቼ ጋር ተነጋግሮ፣ ግዴለም ካወጣልን እንሞክር ብለው አንድ ሁለት ጊዜ እንደሄደ ሰምቻለሁ፡፡ የሰጠነው ምንም ዓይነት ውል የለም፡፡ ልሞክር ብሎ ሄደ አልቻለም፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ አዲሱ የአንጎላ ፕሬዚዳንት የዛሬ ሁለት ዓመት ከተሾሙ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ለአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ጥር ወር ሲመጡ አገኘኋቸውና አነጋገርኳቸው፡፡ ገንዘብ እንደተያዘብን ነገርኳቸው፡፡ እኛ አንጎላ ለረዥም ጊዜ አገልግለናል፡፡ በጦርነት ጊዜ ሁሉ አገልግለናልና አስተያየት ልታደርጉልን ይገባል አልኳቸው፡፡ ገንዘቡ ለረዥም ጊዜ ተይዞብን ተቸግረናል ስላቸው፣ ምን ያህል ነው ሲሉኝ ነገርኳቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ያህል ገንዘብ ነበር የተያዘባችሁ?

አቶ ተወልደ፡- ወደ 33 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በነዳጅ ዋጋ መውረድ ምክንያት በተፈጠረ የዶላር እጥረትና ከአይኤምኤፍ ጋር የተፈጠረ ችግር እንደነበር ገልጸው፣ ችግሩ እንደተፈታ ገንዘባችንን እንደሚያስለቅቁልን ነገሩኝ፡፡ የአንጎላ አየር መንገድ ችግር ውስጥ ስላለ ብትረዱን አሉኝ፡፡ ሐሳባቸውን ተቀብለን የአንጎላ አየር መንገድን ለመርዳት ፈቃደኝነታችንን ገልጸን ደብዳቤ ጻፍንላቸው፡፡ በወቅቱ እነሱ ከኢሚሬትስ አየር መንገድ ጋር በተመሳሳይ ችግር የተለያዩበት ወቅት ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የተያዘውን ገንዘብ ሊያስለቅቁልን ቃል ገብተዋል፡፡ ጊዜያችንን ጠብቀን ገንዘባችንን ማግነት አለብን ብዬ በኢሜይል ላኩኝ፡፡ ግለሰቡ ቅር ተሰኘ፡፡ እሱ እኔ እየሞከርኩኝ ነበር ሲል የአንተ ዕገዛ አያስፈለግም ብዬ በራሳችን እንጨርሳለን አልኩት፡፡ ቅሬታውን በኢሜይል ገልጾልኛል፡፡ ባቀረበው ቅሬታ አቶ እከሌ ቃል ገብቶልኛል ይላል፡፡ ለውስጥ ኦዲተሮች ይጣራ ብዬ ለእሱ ኢሜይል ስመልስ ለውስጥ ኦዲተሮች ኮፒ አድርጌ ልኬያለሁ፡፡ ኢንተርናል ኦዲት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ኢሜይሉን ወስዶ ኦዲተሮች መድቦ አጣራ፡፡ ምንም የተሰጠው ውልና የተገባለት ቃል እንደሌለ፣ በቃል ራሱ ብቻ እሞክራለሁ ብሎ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠው ተልዕኮ እንደሌለ አጣርተው ሪፖርት አቀረቡ፡፡ ከዚያ በኋላ የተሰጠህ ነገር የለም፣ በኦዲት አጣርቻለሁ ብዬ መለስኩለት፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ ይሰጠኝ አለ፡፡ የውስጥ ኦዲት ሪፖርት ነው ልንሰጥህ አንችልም ብለን በዚህ ዘጋን፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ ጀርመን ተመልሶ ቲኬት ሥራውን ክፈቱልኝ አለ፡፡ እኛ ያለብህን 510,000 ዩሮ ካልከፈልክ አንከፍትም አልነው፡፡

ግለሰቡ ቅሬታውን ለኢትዮጵያ መንግሥት በጽሑፍ አቅርቧል፡፡ ያለውን ቅሬታ ጨማምሮ፣ የኢሜይል ልውውጦችንና የድምፅ ጭምር አድርጎ ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ መንግሥት ቅሬታውን ዓይቶ ተጨባጭ ነገር ስላጣበት የሚመለከታቸው ኃላፊዎች ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የዳይሬክተሮች ቦርድ አቀረቡ፡፡ ቦርዱ የቀረቡትን መረጃዎች ይዞ ለቦርድ ጸሐፊ ሰጠ፡፡ ቅሬታው ማኔጅመንቱ ላይ ስለሆነ የቦርድ ጸሐፊ በቀጥታ የኦዲት ክፍሉ እንዲያጣራ ያድርግ፡፡ የኦዲት ክፍሉ ያጣራውን በቀጥታ እኛ ሳናየው ለቦርድ ያቅርብ በማለት ለቦርድ ጸሐፊው ደብዳቤ ጻፍኩኝ፡፡ ኦዲተሮች እንደገና ተመድበው የጻፈውን በሙሉ አጣሩ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያጓጉዘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገንዘብ ሁሉ እንደጠፋ ገልጿል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ገንዘብ እንዴት እንደሚጓጓዝ ባንኩ ያቀዋል፡፡ በቻርተር በረራ አጃቢ የሴኪዩሪቲ ሰዎች ተመድበው ከማተሚያ ቤቱ ተጓጉዞ አውሮፕላኑ ውስጥ ሳይከፈት ብሔራዊ ባንክ ራሱ በደኅንነትና በፖሊስ አሳጅቦ ነው ወደ ግምጃ ቤት የሚሄደው፡፡ እነዚህ የሐሰት ክሶች ስለጉዳዩ ለማያውቁ ሰዎች ለጊዜው ሊያሳስቱ ይችላሉ፡፡ የቀረቡትን አቤቱታዎች ኦዲተሮች አጣርተው ምንም ነገር እንዳላገኙ ለቦርድ ሪፖርት አቀረቡ፡፡ ቦርዱ ተመልክቶ ተጨባጭ ነገር ሲያጣ ጉዳዩ ተዘጋ፡፡ ግለሰቡ የፍራንክፈርት ቢሮ ለምን ተዘጋ? ሥራውን ለምን አልቀጠልኩም? ከአንጎላ ላስወጣሁት ገንዘብ የኮሚሽን ክፍያ ይገባኛል የሚል ቅሬታ የሚያቀርበው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ እዚህ ድርጅት ውስጥ ሊደረጉ የማይችሉ የፈጠራ ክሶች ያቀርባል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፖሊሲው ደላላ የማይቀበል ከሆነ ለዚህ ግለሰብ በአንጎላ የተያዘውን ገንዘብ እንዲያስለቅቅ ለምን ሥራው ተሰጠው? ያለበትን 510,000 ዩሮ ሳይከፍል ለአንጎላ ገንዘብ የማስለቀቅ ሥራ እንዴት ተሰጠው?

አቶ ተወልደ፡- በወቅቱ የተያዘውን ገንዘብ እናስወጣላችኋለን የሚሉ ብዙ ግለሰቦች ነበሩ፡፡ ገንዘቡ በአንጎላ ተይዞብን ረዥም ጊዜ ቆይቷል፡፡ ገንዘቡ የምንዛሪ ተመኑ ቀንሷል፡፡ በአፍሪካ አገሮች የገንዘብ ተመን ለውጥ ይደረጋል፡፡ ንብረት ላይ ማዋል ፈልገን አልቻልንም፡፡ ስለዚህ እናስወጣላችኋለን የሚሉ በተለይ ከአንጎላ ባንክ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ሊረዱን ሲሞክሩ ነበር፡፡ እኛ የሥራ ውል የሰጠነው ግለሰብ የለም፡፡ በአንጎላ ከሚገኘው የሽያጭ ወኪላችን በስተቀር፡፡ የሽያጭ ወኪላችን ያስወጣው ትንሽ ገንዘብ ነበር፡፡ አቤቱታ ያቀረበብን ግለሰብ ግን ይህን ገንዘብ ካስወጣህልን ይህን ያክል እንከፍልሃለን ብለን የሰጠነው ኮንትራት የለም፡፡ ገንዘቡን ባስወጣ ልጠቀም እችላለሁ የሚል የራሱ ሐሳብ ነው፡፡ በተረፈ የነበረበትን 510,000 ዩሮ ሊከፍለን ባለመቻሉ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስደን አስወስነናል፡፡ በጀርመን ፍራክፈርት ፍርድ ቤትን አስፈርደናል፡፡ ውሳኔው በእጃችን ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያም የጀርመን ፍርድ ቤት ውሳኔ ይዘን በዓቃቤ ሕግ በኩል ክስ መሥርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው አዲስ በተቋቋመው ሠራተኛ ማኅበር የሚነሳው ቅሬታ ሠራተኞች ያላግባብ ከሥራ ይባረራሉ የሚል ነው፡፡ አየር መንገዱ በራሱ መንግሥት ሆኗል፣ የራሱ እስር ቤት አለው የሚሉ ክሶች እየቀረቡ ነው፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

አቶ ተወልደ፡- በዚህ የፈጠራ ድራማ ላይ ሁለት ተዋናውያን አሉ፡፡ አንዱ ተዋናይ አዲሱ የሠራተኛ ማኅበር አመራር የሚባለው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኛ ማኅበር ከ59 ዓመታት በላይ የቆየ ጠንካራ የሠራተኛ ማኅበር ነው፡፡ አንጋፋ የሆነ ትልቅ ንብረት ያለው፣ 6,300 አባላት ያሉት ትልቅ ማኅበር ነው፡፡ አዲሱ ማኅበር አብራሪዎች የማኅበር አባል ይሁኑ አይሁኑ በሚለው አለመግባባት ተፈጥሮ እኛ ሌላ ማኅበር እንመሠርታለን ብለው ያቋቋሙት ነው፡፡ መሪው ፓይለት ነው፣ አሁን ከሥራ ተሰናብቷል፡፡ አዲሱ የሠራተኛና አሠሪ አዋጅ በአንድ መሥሪያ ቤት ከአንድ ሠራተኛ ማኅበር በላይ ይፈቅዳል፡፡ በዚህ መሠረት የተመሠረተ የሠራተኛ ማኅበር ነው፡፡ እንደ ሠራተኛ ማኅበር ተመዝግቧል፡፡ ግን ገና ከጅምሩ ውዝግብ ውስጥ የገባ ማኅበር ነው፡፡ የሠራተኛ ጥቅምና መብት ከማኔጅመንት ጋር ተደራድሮ ለማስከበር የተቋቋመ ማኅበር ሳይሆን በአደረጃጀቱ በሚያወጣቸው መግለጫዎች፣ ከሠራተኞች ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ትንሽ ከሠራተኛ ማኅበር ወጣ ያለ አካሄድ ነው የሚከተለው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ማኅበር ከምሥረታው ጀምሮ ማኔጅመንቱ ዕውቅና አልሰጠኝም፣ አብሮ ለመሥራት ፈቃደኝነት አላሳየም ነው የሚለው፡፡ አመራሮቹ ያላግባብ ከሥራ እንደተባረሩበት ይናገራል፡፡

አቶ ተወልደ፡- አዲሱ የሠራተኛ ማኅበር ከጅምሩ አካሄዱ ትክክል እንዳልሆነ ነግረናቸዋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ዓላማ ከማኔጅመንቱ ጋር ተወያይቶ የኢንዱስትሪ ሰላም ሳይናጋ የሠራተኛ ጥቅም ማስከበር ነው፡፡ ይህ ማኅበር ግን ከዚህ ውጪ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ የሠራተኛ መብት መከበር አለበት፣ የመናገር መብት መከበር አለበት፣ የሥራ ኃላፊዎችን ሠራተኛው መምረጥ አለበት ይላል፡፡ ሠራተኛው የማኔጅመንት አባላት መምረጥ አለበት ይላል፡፡ ይህ በጽሑፍ ያስቀመጡት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ካልሆነ  በስተቀር ሠራተኛ አመራር የሚመርጥበት ኩባንያ አላየሁም፡፡ ይህ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ ስንገልጽላቸው መጋጨት ጀመርን፡፡ እኛ ከነባሩ ሠራተኛ ማኅበር ጋር እንሠራለን፡፡ የአዲሱ ማኅበር አመራሮች የሲቪል መብቶችንና የሠራተኛ መብቶችን ለይተው ማወቅ አልቻሉም፡፡ በዚህ የተነሳ መግባባት አልተቻለም፡፡ ሁለቱን የሠራተኛ ማኅበራት ለማዋሀድ የተደረገው ጥረትም አልተሳካም፡፡

ሪፖርተር፡- የአዲሱ ማኅበር አመራሮች ከሥራ የተባረሩት ለምንድነው?

አቶ ተውልደ፡- የአዲሱ ማኅበር መሪ አብራሪ ነው፡፡ የተመደበበትን ሥራ አልሠራም አለ፡፡ ቻድ ሄዶ እንዲሠራ ተመድቦ ፈቃደኛ አልሆነም፡፡ ጓደኞቹ ተመድበው በሚሠሩበት ቻድ ተራው ደርሶ ሂድ ሲባል አልሄድም አለ፡፡ ለረዥም ጊዜ ሁለት ሦስቴ ጠይቀነው እንቢ በማለቱ፣ የድርጅቱን ስም በተደጋጋሚ በማጥፋት ሥራ በመጠመዱ የድርጅቱን መልካም ስምና ዝና አጉድፏል፡፡ ድርጅቱ በራሱ ሠራተኛ ስሙ ይህን ያህል ሊጠፋ ስለማይገባ ብዙ ታግሰን ዕርምጃ ወስደናል፡፡ ኩባንያው በራሱ ሠራተኛ ይህን ያህል ጉዳት ሊደርስበት አይገባም፡፡ በዝምታ ከዚህ በላይ ከታገስነው ድርጅቱን ማፍረስ ነው የሚሆነው፡፡ ድርጅቱ እኛ እንደ ዓይናችን ብሌን የምንጠብቀው፣ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ሕዝብ የሚወደው አየር መንገድ በመሆኑ ድርጅቱን መታደግ ስላለብን ዕርምጃ ወሰድን፡፡ ዕርምጃ ከተወሰደ በኋላ የተቀነባበረ ዘመቻ ተከፈተብን፡፡ አንድ ሠራተኛ ያላግባብ ከተሰናበተ ወደ ፍርድ ቤት ነው መሄድ ያለበት፡፡ መጀመርያ ከድርጅቱ ጋር ባለው የቅሬታ አቀራረብ መሠረት ችግሩን መፍታት ካልቻለ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል፡፡ የአዲሱ ማኅበር አመራሮች ግን በየሚዲያው እየሄዱ ስም ማጥፋት ነው የመረጡት፡፡

ሪፖርተር፡- በውስጥ አሠራር ቅራኔዎችን ለመፍታት አልተሞከረም?

አቶ ተወልደ፡- ብዙ ጊዜ ጠርተን አነጋግረናቸዋል፣ ሊፈታ አልቻለም፡፡ የዓላማ ልዩነት ነው ያለው፡፡ እነሱ የሚያስቡት ዓይነት ማኔጅመንትና ድርጅት በዓለም ላይ ሊኖር አይችልም፡፡ እኛ ደግሞ የተሰጠንን ኃላፊነት መወጣት አለብን፡፡ ይህ ልዩነት ሊፈታ አልቻለም፡፡ ሌላው በተለያዩ ጊዜያትና በተለያዩ ምክንያቶች የተሰናበቱ ሠራተኞችን እየሰበሰቡ ያቀርቧቸዋል፡፡ የተጠሩት ሠራተኞች አንዳንዶቹ ለእኔ ኢሜይል ልከውልኛል፡፡ ለአዲሱ ማኅበር ምስክርነት ስጥ ተብዬ ተጠርቻለሁ፡፡ ይህን ከማደርግ ወደ ሥራ መልሱኝ ብሎ በኢሜይል የጠየቀኝ ሠራተኛ አለ፡፡ ከድርጅቱ የተሰናበቱት ሠራተኞች የተለያየ ጥፋት ያጠፉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለመጥቀስ አንዱ አውሮፕላን ገጭቶ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ አድርሶ ዕርምጃ የተወሰደበት ሠራተኛ ነው፡፡ አንድ ሦስት የሚሆኑት በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰዎችን ያለ ቪዛ ከአገር የማስወጣት ሕገወጥ ድርጊት ላይ ተሰማርተው በመገኘታቸው ነው፡፡ ከሰዎች ጋር ተነጋግረው ገንዘብ ተቀብለው፣ የውጭ ሰዎችም አሉበት ከአገር ሲያስወጡ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ናቸው፡፡ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሊልኩ ሲሉ ተይዘዋል፡፡ በኢሚግሬሽንና በደኅንነት ተይዘው ፖሊስ ለጊዜው ኤርፖርት አቆይቷቸው ወደ ማዕከላዊ ተወስደው ተመምርምረው፣ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ታይቶ ተፈርዶባቸው የእስር ጊዜያቸውን ጨርሰው የወጡ ናቸው፡፡ እነሱ ደግሞ ፍርዳችንን ስለጨረስን መልሱን ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንዲህ ዓይነት የተቀነባበረ ወንጀል የፈጸመ ሠራተኛ መልሰን ማስገባት አንችልም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ተዋንያን በድርጅቱ ላይ ብቀላ እየፈጸሙ ያሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እያበረረ መንገደኛና ጭነት ያመላልሳል እንጂ እስር ቤት ሊኖረው አይችልም፡፡ ሕግ አይፈቅድለትም፣ ሊኖርም አይችልም፡፡ መንግሥት ያለበት አገር እኮ ነው፡፡ የተባለው ድርጊት ሲፈጸም መንግሥት ዝም ብሎ ይመለከታል? በራሱ መንገድ ያጣራል፡፡ በአየር መንገድ ውስጥ ምንም ዓይነት የተደበቀ እስር ቤት የለም፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ግን አለ፡፡ ምክንያም ኤርፖርት እንደመሆኑ መጠን ዓለም አቀፍ መንገደኞች የሚስተናገዱበት ነው፡፡ ፖሊስ አለ ሕግ ያስከብራል፡፡ የስርቆት ወንጀሎች ሲፈጸሙ፣ የጠቀስኩት ዓይነት (የጉዞ ሰነድ) ማጭበርበሮች ሲፈጸሙ፣ የተከለከሉ ዕቃዎች ይዘው ሲንቀሳሱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎችን የሚያቆይበትና የሚመረምርበት ፖሊስ ጣቢያ አለ፡፡ ይህን ከሆነ እስር ቤት የሚሉት ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ አየር መንገዱ ግን እስር ቤት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ የፈጠራ ድራማ ነው፡፡ ከመነሻው በቀል ነው፡፡ በጥፋታቸው ከድርጅቱ የተሰናበቱ ሠራተኞች የበቀል ዕርምጃ ነው፡፡ ድርጅቱ ላይ የጎላ ጉዳት ባያደርሱም ኅብረተሰቡን ለጊዜው ያሳስታሉ፡፡ ከዚህ ውጪ አየር መንገዱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የሚፈጸም ሙስና ቢኖር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ ኮምፓክት አባል ሊሆን አይቻልም፡፡ ግሎባል ኮምባክት የአካባቢ፣ የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መሥፈርቶች ያሟሉ ድርጅቶች አባል የሚሆኑበት ነው፡፡ ሁለተኛ እያዳንዱ አበዳሪ በዓመት ሁለት ጊዜ ድርጅቱን ይመረምረዋል፡፡ አበዳሪ ገንዘቡ እነዚህ አውሮፕላኖች ውስጥ ስላለ ይመረምረናል፡፡ አውሮፕላን አከራዮች ይመረምሩናል፣ የዲቨሎፕመንት ፋይናንስ ደርጅቶች አሉ፡፡ እንደ አፍሪካ ልማት ባንክና የመሳሰሉት አበዳሪዎቻችን ናቸው፡፡ እነዚህ ባንኮች በየሦስት ወሩ ዝርዝር ውስጥ ገብተው ኦዲት ያደርጉናል፡፡ የራሳችን ኦዲተሮች አሉ፣ የውጪ ኦዲተሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በአሜሪካ ሕግ ከ50 ዶላር በላይ የሚያወጣ ስጦታ መለዋወጥ አትችልም፡፡

በየጊዜው የፀረ ሙስና መግባቢያ ሰነድ እንፈርማለን፡፡ ከጄኔራል ኤሌክትሪክ ጋርም የሚደረጉ ግዥዎችና ድርድሮች በአሜሪካ ፀረ ሙስና ሕግ የሚመሩ ናቸው፡፡ ኩባንያዎቹ ይህን የሚያደርጉት ለእኛ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው የአሜሪካን ሕግ ለማሟላት ሲሉ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ከቦይንግ ወይም ለኤርባስ አውሮፕላን ለመግዛት ድርድር በምንጀምርበት ወቅት ቡድን እንመርጣለን፡፡ እኛም የራሳችንን ቡድን፣ እነርሱም የራሳቸው ቡድን ይመድቡና ሁለት ገጽ የሆነ ስምምነት እንፈርማለን፡፡ ስምምነቱ ከሁለቱም ቡድን ስጦታ እንዳይቀባበሉ፣ ለሚቀጥለው ሦስት ዓመት አንዱ የሌላኛውን ባለሙያ እንዳይቀጥር ይከለክላል፡፡ ቦይንግ የእኛን ተደራዳሪ ቡድን አባል ለሦስት ዓመት ያህል መቅጠር አይችልም፡፡ እኛም የቦይንግን ተደራዳሪ ቡድን አባል መቅጠር አንችልም፡፡ ይህ በሰነዶቻችን ውስጥ ይገኛል፡፡ ግለሰቦቹ እንደሚያወሩት በዘፈቀደ የሚካሄድ ግዥና ሽያጭ የለም፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነ በኒውዮርክ የሚገኝ ቤት ሸጬ እንደበላሁ ተነግሯል፡፡ ቤቱ በካፒቴን መሐመድ ጊዜ በኒውጀርሲ የተገዛ ነበር፡፡ ቤቱ ከካፒቴን መሀመድ በኋላ ማንም አልኖረበትም፡፡ ወደ አሥር የምንሆን ኤሪያ ማኔጀሮች አልኖርንበትም፡፡ ምክንያም ቤቱ የሚገኘው ኒውጀርሲ ሲሆን እኛ የምንሠራው ኒውዮርክ ነው፡፡ ለሥራ ስለማይመች አልኖርንበትም፡፡ ስለዚህ ቤቱ ተከራይቶ ነው የቆየው፡፡ በኋላ ተከራይ ማፈላለግ ስላልተመቸ ይሸጥ ተብሎ በማኔጅመንት ቦርድ ቀርቦ ተሸጠ፡፡ ገንዘቡም በኒውዮርክ በሚገኝ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የባንክ ሒሳብ ገቢ ተደርጓል፡፡ ከአየር መንገድ ንብረት እንኳን ቤት አንዲት ብዕር መውሰድ አይቻልም፡፡ ያን የሚፈቅድ አሠራር የለም፡፡ አንገቴን እሰጣለሁ ያላግባብ አምስት ሳንቲም የሚጠፋበት መንገድ የለም፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ ኦዲተሮች የተረጋገጠ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...