Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ለሽንኩርትም ዶላር?

የሰሞኑ ገበያ ለየት ያለ ጠባይ ማሳየት ጀምሯል፡፡ መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች ላይ የአቅርቦት እጥረት እየታየባቸው ነው፡፡ የተጋነነ ዋጋም ይጠራባቸዋል፡፡ ለጥቂት ጊዜ መለስ ብሎ እንደነበር የሚገመተው የዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት ዳግም አገርሽቶበታል፡፡

ጊዜው የአገራችንን የግብይት ሥርዓት በአግባቡ መምራት፣ የተሻለ የግብይት ሥርዓት እንዲፈጠር አዳዲስ ሥልቶችን ቀይሶ መተግበር፣ ኃላፊነት የሚሰማቸውን የግብይት ተዋንያን ማበራከት፣ ለሥነ ምግባር ያደሩ፣ በተገቢው የገበያ ዋጋ የሚሸጡና የሚሸቅጡ ነጋዴዎችን መፍጠር የሚጠይቅ ነው፡፡ ቢሆንም፣ ገበያውን የሚረብሹ ተግባራት በተለመደው አካሄድ መቀጠላቸው ግን አስቸጋሪ ነው፡፡

 እርግጥ ነው የግብይት ሥርዓታችን በልማዳዊና በዘፈቀደ አሠራር የተተበተበ፣ ብዙ ችግር ያለበትና የራስ ጥቅም እንጂ አሻግሮ በመመልከት ሌሎች እንዳይቸገሩ አልሞ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ሻጭ ማየት እንደሚቸግር ቢታወቅም፣ ቢያንስ እንዲህ ባለው የአደጋና የቀውስ ወቅት እንኳ አጋጣሚ ተጠቅሞ ገበያ ለማተራመስ የሚደረግ ጥረትን መታገስ ተገቢ አይሆንም፡፡

መንግሥት እስካሁን ከ64 ሺሕ ያላነሱ ነጋዴዎችና መደብሮቻቸው ላይ ዕርምጃ እንደወሰደ ሲገልጽ ከርሟል፡፡ ይሁን እንጂ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ሆን ተብሎ የሚደረገው የዋጋ ለውጥና ጊዜውን ያላገናዘበ የምርት እጥረት መፍጠር በእርግጥም አምራቾች ስለሌሉ ብቻም ሳይሆን፣ ገበያውን ለራሳቸው ፍላጎት ማስጎንበስ የሚችሉ ሰዎች ከመንግሥትም በላይ አቅም በመፍጠር የዋጋ ዘዋሪ መሆን እንደቻሉ የምንረዳበት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ይህ ከምንጊዜውም በላይ በተለየ የመንግሥትን ትኩረትና ቁጥጥር የሚፈልግ ነው፡፡

በርበሬን በምሳሌነት ብናነሳ፣ ምርቱ እንደተሸሸገና ሆን ተብሎ እጥረት ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት እንዳለ የሚያሳዩ ነገሮች እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ይህን ለማለት የሚያስደፍረንም ምርቱን የሸሸጉ አካላት እጥረት እንደፈጠረ በማስመሰል ዋጋ ሰቅለው ለመሸጥ የሚሠሩት ድራማ ነው፡፡ ምርቱን ጥቂት ናሙና መደብራቸው ፊት ለፊት ለምልክት ያስቀምጣሉ፡፡ ነገር ግን በፈለጉትና በሚመስላቸው የተጋነነ ዋጋ የሚገዛቸው ሸማች ሲመጣ ዋናው ምርት ከተሸሸገበት አውጥተው ይሸጣሉ፡፡ ባለፉት ሦስት ሳምንታት ብቻ በአንድ ኪሎ ዛላ በርበሬ ላይ ከእጥፍ በላይ ዋጋ የመጨመሩ አንዱ ምክንያት፣ ይኸው ጨዋነት የጎደለው ተግባር የፈጠረው እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ወቅቱ የቱንም ያህል በርበሬ የሚመረትበት ባይሆን እንኳ፣ ዋጋው የዚህን ያህል  መጨመር እንደማይችል ተሞክሮ ይነግረናል፡፡ እየሆነ ያለው ግን ሸማቹን የሚያማርር ነው፡፡ በኮሮና ወቅት ዋጋው እንዲጎን መደረጉ ግን ሸማቹን ለበለጠ ምሬት ይዳርጋል፡፡ ጤፍም ከጥቂት ሳምንት በፊት ከነበረው ዋጋ በኩንታል ከ500 ብር በላይ የመጨመሩ ምስጢር ኢኮኖሚያዊ ነው ወይም ምክንያታዊ ጭማሪ ነው ብሎ ለመቀበል አዳጋች ነው፡፡ ሌሎች ምርቶችም አንዱ የአንዱን እየተከተሉ የዋጋ ጭማሪ ሰንሰለት እያበጁ ሲሄዱ እያየን ነው፡፡ መንግሥትም እሳት በማጥፋት ሥራ ላይ በመጠመዱ ይመስላል በዋጋና በገበያ ችግሮች ላይ የሚወስዳቸው ዕርምጃዎች ይህ ነው የሚባል ለውጥ አላመጡም፡፡ ከ60 ሺሕ በላይ መደብር ታሽጎም የሚፈለገው ለውጥና የገበያ መረጋጋት አልመጣም፡፡ ለመፍትሔው የፖሊስ ዕርምጃ ብቻ ለውጥ ስለማያመጣ ምርት ከያለበት ይውጣ፡፡ ገበያው ላይ ምርት ይሰራጭ፡፡ የአንድ ኪሎ ሽንኩርት ዋጋ በቀናት ልዩነት ውስጥ ከ30 ብር በላይ የሚሸጥበት ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል የሚገልጽ ሰበብ እንኳ መስማት አለመቻል፣ የገበያው እንደልቤነትን አጉልቶ የሚያሳይና የነጋዴዎች የበላይነትና ማንአለብኝነት መሳፈሪያ ያስመስለዋል፡፡ እርግጥም የምርት እጥረት ስላለ ነው ወይ? ምላሽ ይሰጥበት፡፡ እንደተለመደው ደላላ ካልዋለበት ገብቶ ከሆነ መጠየቅ  ብቻ ሳይሆን፣ እርምት መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

የሽንኩርት ነገር ሲነሳ እንደ አገር ልናርፍበት የሚገባ አንድ እውነታን ማስታወስ ይኖርብናል፡፡  በትኛውም የአገሪቱ ክፍል በቀላሉ ሊመረት የሚችለውን ሽንኩርት ፍላጎት ለማሟላት ኢትዮጵያ ከሱዳን ሽንኩርት መግዛቷ ነው፡፡ ሰሞኑን ተፈጠረ ለተባለው የሽንኩርት እጥረትና የዋጋ ጭማሪ ችግሩ ምንድነው ተብለው የተጠየቁ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ፣ የእጥረቱ ምክንያት እየተጠና ስለመሆኑ ገልጸው፣ በመፍትሔነት  የጠቀሱት ከሱዳን ተገዝቶ እንዲገባ ማድረግ ነው፡፡ ወቸ ጉድ ነው፡፡

በኃላፊው ገለጻ መሠረት፣ ለእጥረቱ ማስተካከያ ከሱዳን ሽንኩርት ማስገባት መፍትሔ መደረጉ ኢትዮጵያ የሽንኩርት ፍላጎቷን ሟሟላት ባለመቻሏና ለሽንኩርትም የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋት መሆኗ አንገት ያስደፋል፡፡ የአዋሽ ወንዝ ሙላት ማሳ ላይ እያለ የሚያወድመው የተትረፈረፈ ሽንኩርት፣ ከእኛ አልፎ ለውጭ ገበያ መብቃት ሲገባው፣ ጭራሹኑ ለእኛም ፍጆታ አለመገኘቱ የግብይት ሥርዓታችን ላይ ወፍራም የጥያቄ ምልክት እንድናስቀምጥ ያስገድደናል፡፡ የገበያ ክፍተቶችን ለመድፈን የሚያስችል አሠራር ባለመኖሩ ችግር እየተባባሰ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር የገበያውን ፍላጎት አይቶ በቀላሉ ሊመረቱ የሚችሉ እንደ ሽንኩርት ዓይነት ምርቶችን ድንበር ተሻግሮ ከመግዛት ምን ብናደርግ ይበጃል? ብሎ አለመሥራት ሁሌም እሳት የማጥፋት ሥራ ላይ መለከፋችንን ያሳያል፡፡ ይህ የሚያስከፍለን ዋጋ እየሰፋ እንዲሄድ አድርጎታል፡፡ በእርግጥ አገር ለስንዴና ለዘይት የምታወጣውን ወጪ ለመቀነስ እንደተጀመረው ዓይነት ሥራ እንዲህ ላሉ በቀላሉ ልናመርታቸው የሚችሉ ምርቶች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቀላሉ ሥራ ነውና በአንዳንዱ ቦታዎች ጨመረ ሰበብ የሚፈጠረው ትርምስና ገበያውን በአግባቡ የመምራትና የመቆጣጠር ችግር ብቻ ሳይሆን ያለንን አቅም ተጠቅሞ ያለ መሥራት አስፈላጊ ምርቶችን መጠን ለክቶ አምራቾች ይህንን ቢያመርቱ ይህንን ደግሞ በዚህ ቢያመርቱ ይሻላል የሚል አሠራር ባለመኖሩ ጭምር ነው፡፡

በዚሁ ሳምንት በመስክ ጉብኝት ያመረቱትን ምርት ለመሸጥ የተቸገሩ አምራቾች ሲጮሁ እየሰማን፣ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ዋጋ ተሰቀለ ተብሎ ይጮሃል፡፡ ይህ የሚያሳየው  የገበያ ትስስር ለመፍጠር በአግባቡ አለመሠራቱን ነው፡፡

ስለዚህ አገር ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ችግር በእጥፍ በገባበት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች በየዕለቱ እየጨመረ በመጣበትና ማቆሚያው እዚህ ላይ ይሆናል ተብሎ በማይገመትበት በዚህ ወቅት፣ ጨዋነትና መተሳሰብን ያማከለ ግብይት ሊኖረን ይገባልና እንደ ቀድሞ ከስንጥቅ ትርፍ ራስን ‹‹አሸናፊ›› ለማድረግ የሚፈጸሙ ድርጊቶች ፈጽሞ ተቀባይነት ሊኖራቸው አይችልም፡፡

እባካችሁን ራሳችሁን ጠብቁ ይህን አትፈጽሙ ጊዜው ከባድ ነው እየተባለ መንገድ ደግሞ ገበያውን የሚያፈራርሱ ስግብግቦችን እንዲህ እንደዋዛ ችላ ብሎ መቀጠል ተገቢ አይሆንም፡፡

አገር ያለችበትን ወቅታዊ ችግር ያገናዘበ ዕርምጃና እጥረት ያለባቸው ምርቶችን በአግባቡ ለማቅረብ የሚያስችል አሠራር ያስፈልጋል፡፡

በእርግጥ በመንግሥት ዕርምጃዎች እየተወሰዱ ነው ቢባልም፣ ያዝ ለቀቅ ማለቱ በገበያ ውስጥ ያለውን ትክክለኛ መረጃ አውቆ ያለችግር ለሸማቹ እንዴት ይድረስ የሚለው ዓብይ ጉዳይም በአግባቡ መሠራት አለበት፡፡

ጊዜውን የሚመጥን አሠራር፣ የቁጥጥርና የምርት ሥርዓትና የሥርጭት መዋቅር ይኑረን ማለት ዛሬ ቅንጦት አይደለም፡፡ ይልቁንም ኋላቀርነት ነው፡፡ ይህ ዘመን ገበያ ከማሳ ወደ ምሳ የሚባልበት ወቅት በመሆኑ፣ እንደሁ ይህ ቅንጦት ቢሆን እንኳ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በተመጣጣኝ ዋጋ መገብየት የሚችልበት የተመቻቸ የገበያና የግብይት ሥርዓት መፍጠር ማስቻል በራሱ መልካም ተግባር ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት