Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊብቸኛው የኮምፔንሳቶ ፋብሪካ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦብኛል አለ

ብቸኛው የኮምፔንሳቶ ፋብሪካ የመፍረስ አደጋ ተጋርጦብኛል አለ

ቀን:

‹‹ሌሎች ቤቶች እንጂ ፋብሪካው አይፈርስም››

የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን

‹‹መንግሥት ሠራተኞቹን ይረከበንና እኛም ማሽናችንን ነቅለን እንወጣለን››

የፋብሪካው ባለቤቶች

ከ60 ዓመታት በፊት በሦስት ጣሊያናውያን የተመሠረተው ብቸኛው የኢትዮጵያ ኮምፔንሳቶ ፋብሪካ፣ የመፍረስ አደጋ እንደተጋረጠበት ባለቤቶቹ አስታወቁ፡፡

ፋብሪካው በአዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ ስሙ ‹‹ትንሹ አቃቂ›› ተብሎ በሚጠራው ወንዝ ዳር በአሁኑ በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ውስጥ፣ በ1952 ዓ.ም. ሚስተር ፒዬሮ ቺታዲኒ፣ ሚስተር ሎሬንዞ ጐሪና ሚስተር ፒዬሮ ብሩቺ በሚባሉ ጣሊያናውያን ነበር የተመሠረተው፡፡

የፋብሪካው ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አወል ቡሰሪ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ፋብሪካው ዕድሜ ጠገብና ብቸኛው የኮምፔንሳቶ ፋብሪካ ነው፡፡ ከ200 በላይ ቋሚና እስከ 300 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሠራተኞችን አሉት ብለዋል፡፡ ፋብሪካው ባለበት ሥፍራ የማስፋፊያ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅቶችን ጨርሶ እያለ፣ ከጦር ኃይሎች ቀለበት መንገድ ጋር የሚገናኘው ከወይራ ሠፈር እስከ ቤተል የሚገነባ መንገድ ከጥቅም ውጪ ሊያደርገው ጫፍ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮምፔንሳቶ ድርጅት ከ1952 ዓ.ም. እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ በጣሊያናውያኑ ይዞታነት የቆየ ቢሆንም፣ የንጉሠ ነገሥቱ ሥርዓት አብቅቶ ደርግ ሲተካ መወረሱንና እስከ 2001 ዓ.ም. ጥር ወር ድረስ በመንግሥት ይዞታነት መቆየቱን አቶ አወል አስረድተዋል፡፡ በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሥር የነበረውን ድርጅት ወደ ግል ለማዛወር የወጣውን ጨረታ ግዮን ጋዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አሸንፎ፣ ከእነ ሙሉ ቋሚ ንብረቱ እንደገዛው ምክትል ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ግዮን ጋዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካውን ከገዛ በኋላ፣ ምርቱንና ምርታማነቱን ለማሳደግ በርካታ ሚሊዮን ብሮችን ኢንቨስት በማድረግ ማሽነሪዎችን በመትከል ሥራውን በአግባቡና በብቃት ለመንግሥታዊም ሆነ ለግል ተቋማት እያቀረበ እንደሚገኝም አቶ አወል ገልጸዋል፡፡ ፋብሪካው ከ200 በላይ ለሆኑና እንደ ሥራው ሁኔታ ከ300 እስከ 400 ለሚሆኑ ጊዜያዊ ሠራተኞች  የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ለኮምፔንሳቶ ምርት የምታወጣውን የውጭ ምንዛሪ በማዳን የራሱን አስተዋጽኦ እየተወጣ ያለ ፋብሪካ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ግዮን ጋዝ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ፋብሪካውን ገዝቶ ክፍያውን በ2007 ዓ.ም. ከፍሎ ያጠናቀቀ ቢሆንም፣ ስመ ሀብቱን ለማዛወር ባለው ቢሮክራሲ ሲጉላላ ቆይቶ በ2012 ዓ.ም. ያዘዋወረ መሆኑንም ምክትል ሥራ አስስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡

ስመ ሀብቱን ከ11 ዓመታት በኋላ የተረከበው ማኅበሩ የማስፋፊያ ሥራ ለመሥራት እየተዘጋጀ ባለበት በዚሁ ዓመት ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንና ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተጻፈለት ደብዳቤ፣ የፋብሪካውን የተወሰነ ቦታ የሚነካ የመንገድ ማስፋፊያ ግንባታ እንደሚደረግ እንደተነገረው አቶ አወል ገልጸዋል፡፡

በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም. የመንገዱ የቅየሳ ሥራ እንደተጀመረ የገለጹት አቶ አወል፣ መንገዱ ፋብሪካውንና በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የቻይና ኤምባሲ አጥር ስለሚነካ፣ አማራጭ እንዲፈለግለት በወቅቱ ኃላፊነት ላይ ለነበሩት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አቤቱታ ማቅረባቸውንም አስታውሰዋል፡፡ ከባለሥልጣኑ የተሰጣቸው ምላሽ ግን፣ በዘጠነኛውና በአሥረኛው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ውስጥ ስላለ፣ ምንም ዓይነት ማሻሻያ አይደረግም የሚል እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ ፕሮጀክቱ እስከ 2012 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ወራት ቆይቶ በኅዳር ወር 2012 ዓ.ም. ላይ ክፍለ ከተማውና ባለሥልጣኑ የመንገድ ግንባታው ሊጀመር መሆኑን ከነገሯቸው በኋላ፣ በሳምንቱ የመለካት ሥራ እንደሚጀምሩ በደብዳቤ እንዳሳወቋቸውም ተናግረዋል፡፡

የእነሱም ሥራ ልማት ስለሆነና የመንገድ ግንባታም ልማት እንደሆነ በመገንዘብ፣ ምንም እንኳን መሬቱን ቆርጦ ቢያልፍም ፋብሪካውንና የጥሬ ዕቃ መጋዘናቸውን ስለማይነካባቸው ተስማምተው እንደነበር አቶ አወል አስረድተዋል፡፡

የቻይና ኤምባሲ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ደብዳቤ በመጻፉና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ለከተማ አስተዳደሩ የ‹‹አይሆንም›› ደብዳቤ በመጻፉ፣ የከተማ አስተዳደሩ ከተማ ፕላን ኮሚሽን ዲዛይኑ እንዲቀየር ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ደብዳቤ ስለጻፈ፣ መንገዱ ሙሉ በሙሉ ወደ ፋብሪካው መምጣቱን ከባለሥልጣኑ እንደተነገራቸው አቶ አወል ገልጸዋል፡፡

የድርጅቱ ጥያቄ ‹‹ልማት ይቁም›› ሳይሆን የፋብሪካው ጥሬ ዕቃ የሚያርፍበት፣ የሚዘጋጅበት፣ ምርት ከተመረተ በኋላ እስከሚጫን ድረስ የሚቀመጡበት መጋዘኖችን ሙሉ በሙሉ ስለሚያፈርስና ሠራተኞችም ስለሚበተኑ መላ እንዲፈለግለት በተደጋጋሚ መጠየቁን ተናግረዋል፡፡ የቻይና ኤምባሲ አጥር ሳይፈርስም ቢሆን ወደ አጥሩ በመጠጋትና ከፋብሪካው መሬት ላይ ያለውን በቂ ቦታ ወስደው መንገዱን መሥራት እንደሚቻል አማራጭ ሐሳብ ቢያቀርቡም ተቀባይነት እንዳላገኘ አስረድተዋል፡፡

የፋብሪካው ጠቅላላ ይዞታ 11,020 ሜትር ካሬ መሆኑን የገለጹት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ መንገዱ ከ3,000 ሜትር ካሬ በላይ ቦታ ሲወስድ መጋዘኖቹ ሙሉ በሙሉ ስለሚፈርሱ ፋብሪካው ዋጋ እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ለልማት የሚታሰብ ከሆነ የፋብሪካው አካላት ሳይነኩ በአንድ በኩል ማስፋትና በተለይ በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ዜጎችን መታደግ እየተቻለ፣ ከሥራ ገበታቸው ላይ መበተን ተገቢና አስፈላጊ ሆኖ ስላላገኘው ድርጅቱ አቤቱታውን ለመንግሥትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከማቅረብ በስተቀር ምንም ማድረግ እንደማይችልም አቶ አወል ገልጸዋል፡፡ በተረፈው መሬት ላይ እንኳን ሌላ መጋዘን እንዳይሠሩ መንገዱ መሀል ለመሀል ቆርጦት ስለሚያልፍ፣ ግንዲላ እንጨት በሰውም ሆነ በተሽከርካሪ ይዞ መንገድ እያቋረጡ ለመሥራት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አጠቃላይ ሁኔታውን ተገንዝበው ተስፋ ያለው ምላሽ ይሰጡናል በማለት ለምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ለክፍለ ከተማው መሬት ልማትና ከተማ ማደስ ጽሕፈት ቤት፣ ለምክትል ከንቲባ እንዳወቅ አብቴ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንና ለከተማ ፕላን ኮሚሽን አቤቱታ ያስገቡ ቢሆንም እስካሁን ምላሽ አለማግኘታቸውንም ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ሁኔታውን ዓይቶ አማራጫቸውን የማይቀበላቸው ከሆነ ሠራተኞቹን ተረክቧቸው፣ ያስገቡትን ጥሬ ዕቃ ጨርሰው ማሽኖቻቸውን ነቅለው እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

ድርጅቱ እያቀረበ ያለውን አቤቱታና ቅሬታ በሚመለከት ምላሽ እንዲሰጥበት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣንን ሪፖርተር አነጋግሮ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ታከለ ሉሌና (ኢንጂነር) ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ገና ወደ ሥራ አልተገባም፡፡ መንገዱ የከተማ ፕላን ጠብቆ የሚከናወን ፕሮጀክት በመሆኑ፣ መንገዱ በሚያልፍባቸው ቦታዎች ላይ ያሉ ሕንፃዎችም እያፈረሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕላኑ በተደጋጋሚ ስለመቀየሩ ተጠይቀው ‹‹ፕላኑ እንደተቀየረ እንዴት አወቅህ?›› ካሉ በኋላ፣ ኤምባሲዎች ቤተ ክርስቲያንና መስጊዶች እንዳይነኩ የተቀመጠ አግባብ ስላለ ቻይና ኤምባሲንም መንካት እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ያረጁ ቤቶችን ከመንካት ባለፈ፣ ‹‹ፋብሪካውን አይነካም፣ አይፈርስምም›› ብለዋል፡፡ በማስተር ፕላን ፀድቆ ወደ ሥራ የተገባ ቢሆንም፣ ድርጅቱም ቅሬታ አቅርቦ  የተነገረው እንደ ማንኛውም ግለሰብ ቤት እንደሚነካና ለዚያም ካሳ ተከፍሎት እንደሚፈርስ ተናግረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ቢሆን የልማት ሥራ ይቁም ባለማለቱ ሥራው እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹ከኦነግ ሸኔ ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለን›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

መንግሥት ከ‹‹ኦነግ ሸኔ››ጋር ያለውን ግጭት በሰላም ለመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት...

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...