Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ሽቅብ መውጣት እየተቻለ ቁልቁል መውረድ ያሳፍራል!

  አገር በውሸት አትገነባም፣ በውሸትም አትፈርስም፡፡ ራዕይ ያላቸው ዜጎች አገራቸውን ሲገነቡ እውነትንና ቅንነትን ማዕከል አድርገው ነው፡፡ አገር ለማፍረስ የሚፈልጉ ደግሞ በህልም ወይም በቅዠት የሚታያቸውን ጭምር እውነት ለማስመሰል ውሸት ይደረድራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዓመታት የፓርቲ ፖለቲካ ሥራን ጥቂቶች ለማጭበርበር እየተጠቀሙበት፣ ብዙኃኑ ግን ‹ፖለቲካና ኮሬንቲን በሩቁ› እንዲሉ እየተደረገ ለቁጥር የሚያዳግቱ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡፡ በዚህ ዘመን ደግሞ የፖለቲካ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ለማስተናገድ የሚተጉ ቢኖሩም፣ እያንዳንዱን ልዩነት አገር ለማፍረስ ለሚያመች ዓላማ ለማዋል እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩም አሉ፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሐዲዱን ስቶ ያልተገባ ተግባር ውስጥ ሲገኝ እንዲታረም ማሳሰብ፣ መውቀስ፣ መተቸትና ማጋለጥ መልካም ተግባር ነው፡፡ አመራር ላይ ያሉ ሰዎች ሲያጠፉ ወይም አኳኋናቸው አላምር ሲል ማረም የሚደገፍ ተግባር ነው፡፡ ገዥውን ጨምሮ በተለያዩ ፓርቲዎች መካከል ግንኙነቶች ሲበላሹ ለማስተካከል መሥራት ያስመሠግናል፡፡ ችግሮች አልታረም ሲሉ ሕዝብ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲገነዘብ ማድረግ ያስከብራል፡፡ ሥልጣን በሕዝብ ድምፅ ለማግኘት የሚሠራ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ተግባሩ ይህ ነው፡፡ ነገር ግን አገር በኮሮና ወረርሽኝና በህዳሴ ግድቡ ውኃ ሙሌት ምክንያት ከግብፅ ጋር ተፋጣ፣ ሕዝብ የሚከፋፍሉና ለአደጋ የሚያጋልጡ ድርጊቶች ውስጥ ውሎ ማደር ያሳፍራል፡፡ በልጦ መገኘት ሲገባ ቁልቁል እየወረዱ አገርን ማመስ ያስወግዛል፡፡ ሁሉንም ጉዳይ የቅራኔ ምንጭ በማድረግ አገርንና ሕዝብን ለጥፋት ዒላማነት ማመቻቸት የታሪክ ባለዕዳ ያደርጋል፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ በግለሰቦችም ሆነ በማኅበረሰቦች መስተጋብር ከፍተኛ የሆነ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል አንዱ መከባበር ነው፡፡ መከባበር የጨዋነት፣ የምግባረ ሰናይነትና የአስተዋይነት መገለጫ ነው፡፡ በተጨማሪም የሞራልና የሥነ ምግባር ደረጃዎች መለኪያም ነው፡፡ በተለያዩ ዘመናት ውስጥ ያለፉ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንዲኖሩ ከረዷቸው የጋራ እሴቶቻቸው መካከል ተቀዳሚ የሆነው መከባበር፣ በጋብቻ እንዲዛመዱና እንዲዋለዱ ከማስቻሉም በላይ አገራቸውን በአንድነት እንዲጠብቁ ረድቷቸዋል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሲያጋጥሟቸውም፣ ዘመን ተሻጋሪ በሆኑ የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓቶች መጠቀም የቻሉት በመከባበር ነው፡፡ ዛሬም ለመከባበር ትልቅ ሥፍራ የሚሰጡ ኢትዮጵያውያን በርካታ ቢሆኑም፣ ቁጥራቸው የማይናቅ ወገኖች ይህንን አኩሪ ባህል ወደ ጎን እያሉ አሳዛኝ ድርጊቶች እየፈጸሙ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከአንድ ቅን ዜጋ ጀምሮ አገርን እስከሚያስተዳድሩ ሰዎች ድረስ ማንጓጠጥና መዝለፍ ቅር የማይላቸው እየበዙ ነው፡፡ መልካም ስም ያላቸውን ተቋማት የሚመሩ ሰዎችን መስደብና ስም ማጥፋት እንደ ጀብድ እየታየ ነው፡፡ ችግር ካለ በሰከነ መንገድ ቅሬታን ማቅረብ፣ መውቀስና መተቸት እየተቻለ ለመስማት የሚዘገንኑ ስድቦችን ማጉረፍ የዕለት ተግባር እየሆነ ነው፡፡ መከባበር የሚባለው ጽንሰ ሐሳብ ማዋረድ በሚለው ተተክቶ ብዙዎችን እያሳዘነ ነው፡፡

  ብዙዎች ለአገር የሚበጅ ቁምነገር ይዘው አደባባይ መውጣት እየፈሩ ነው፡፡ ተናጋሪ እንጂ አዳማጭ በጠፋበት በዚህ ጊዜ ዕውቀትንና የተከማቸ ልምድን ማካፈል የሚችሉ ሰዎች እየሸሹ ነው፡፡ አንድ ለየት ያለ ሐሳብ ሲቀርብ ከውይይት ይልቅ ማመናጨቅና መፈረጅ ላይ ስለሚተኮር፣ ለአገር ዕድገትና ለመጪው ትውልድ መማሪያ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሳቦች መና እየሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የበርካታ ሐሳቦች፣ ውይይቶች፣ ክርክሮችና ፉክክሮች አገር መሆን ሲገባት መከባበር በመጥፋቱ ለሥልጣኔ ባዕድ እየሆነች ነው፡፡ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ የሐሳብ ልውውጥ በሌለበት ሞጋች ትውልድ ሳይሆን፣ በስሜት እየተኮረኮረ በገዛ ወገኑ ላይ መዓት የሚያወርድ ትውልድ ይፈላል፡፡ አሉባልታና ሐሜት እንደ ወረደ በመቀበል አገርን በእሳት የሚያነድ ትውልድ ይበዛል፡፡ የግለሰቦች ድንገተኛ ፀብ ወደ ብሔር ወይም እምነት ተቀይሮ ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጠረው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በማኅበረሰቦች ውስጥ መከባበር በመሸርሸሩ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠሙ ችግሮች ምክንያታቸው መከባበር ሆን ተብሎ ከሕዝቡ ውስጥ እንዲወጣ በመደረጉ ነው፡፡ ለአዲሱ ትውልድም አርዓያ ሊሆኑ የሚገቡ ግለሰቦችና ስብስቦች መከባበርን ከመዝገበ ቃላታቸው ውስጥ ስላስወጡት፣ ትውልዱ ለመልካም ሥነ ምግባር ተቃራኒ የሆኑ ድርጊቶች ውስጥ ቢዘፈቅ ሊገርም አይገባም፡፡

  በማይከባበር ማኅበረሰብ ውስጥ ዝርፊያ፣ አስገድዶ መድፈር፣ መዋሸት፣ ስም ማጥፋት፣ አሉባልታ፣ ሐሜትና የመሳሰሉት የሥነ ምግባር ዝቅጠቶች ይንሰራፋሉ፡፡ በዝርፊያ በተገኘ ሀብት የደለቡ ክፉዎች ፖሊሶችን፣ ዓቃብያነ ሕግና ዳኞችን በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል ፍትሕን ይደረምሳሉ፡፡ የመንግሥት መዋቅሮችን እንደ ነቀዝ በመሰርሰር ቀፎ ያደርጓቸዋል፡፡ የግለሰቦችን ንብረት በይፋ ሲቀሙ ከልካይ የላቸውም፡፡ የራሳቸውን ሚሊሻና እስር ቤት በማደራጀት በንፁኃን ላይ ፍራቻ በመፍጠር የማፍያ ዓይነት እንቅስቃሴ እያደረጉ፣ የመንግሥትን እጅ እስከ መጠምዘዝ ይደርሳሉ፡፡ በዙሪያቸው ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጀምሮ አክቲቪስት ነን የሚሉ ግሪሳዎችን በተቀላቢነት በመኮልኮል፣ በነፃነት ለመንቀሳቀስ የሚውተረተሩ ግለሰቦችንና ተቋማትን ለማኮማተር ያስፈራራሉ፡፡ ሚዲያዎችን ጭምር በመቆጣጠር በፊታውራሪነት በሰየሟቸው አማካይነት የአገር ሰላም ይነሳሉ፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ በግላጭ እየታየ ያለው የሚሠሩ ትጉሃን በማይሠሩ ሥራ ፈቶች ሲወረፉ ነው፡፡ ከእነዚህ ጀርባ ያሉት ደግሞ ለሚፈለገው የጥፋት ዓላማ ፋይናንስ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ ተቀላቢዎቻቸውን በመረጃ ጭምር እያስታጠቁ በነጋ በጠባ አላሠራ እያሉ ሕዝቡን ያደናግራሉ፡፡ በዚህም መከባበር ጠፍቶ አገር የስድብ አውድማ እየሆነች ነው፡፡

  ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ማዕከል ያላደረጉ በርካታ ሐሰተኛ ወሬዎች በየቀኑ እየተፈበረኩ ይለቀቃሉ፡፡ እነዚህ ወሬዎች በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ለሚሊዮኖች ይደርሳሉ፡፡ ሆን ተብለው በተደራጁ ኃይሎች አማካይነት የሚለቀቁት እነዚህ ሐሰተኛ ወሬዎች በተለይ ወጣቱን ዒላማ ያደረጉ ናቸው፡፡ ስሜትን በሚያነሳሱና እውነታን በሚጋርዱ ኃይለ ቃላት ስለሚታጀቡ፣ ወገንን ከመግደል ጀምሮ ንብረት እስከ ማውደም ድረስ ይቀሰቅሳሉ፡፡ ትንሽ እውነት በብዙ ሐሰት ትቀባባና አደባባይ ስትደርስ ብዙዎች እየገነፈሉ ለፀፀት የሚዳርግ ድርጊት ይፈጽማሉ፡፡ ብሔርና ሃይማኖት በቀላሉ የሚያነሳሱ ስለሆኑም ሁሉንም ጉዳይ ማስተሳሰር ተለምዷል፡፡ አንድ ችግር አጋጥሞ የሰው ሕይወት ሲያልፍ የሚታዘነው በሰብዓዊ ፍጡርነት መሆኑ ቀርቶ፣ በብሔር ወይም በእምነት አሠላለፍ ሲሆን የሚስተዋለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በወንጀል የተጠረጠረ ሰው በቁጥጥር ሥር የመዋሉ ዜና ሲሰማ ከየጎራው የሚያላዝኑ ድምፆች የሚሰሙት፣ ለፍትሕ ሳይሆን ለምን የእኔ ሰው ተነካ በሚል ተልካሻ ሰበብ ነው፡፡ ስለሞራላዊና ሥነ ምግባራዊ እሴት ሳይሆን የእኔ ከሆነ ለምን እንዳሻው አይሆንም በሚል ግብዝነት ነው፡፡ ሹመትና ሹምሽር የብሔርና የሃይማኖት ሰሌዳ እየተለጠፈላቸው ዕውቀት፣ ብቃትና ክህሎት ዋጋ ቢስ ተደርገዋል፡፡ አሁን አሁንማ ንግግርም የሚደመጠው በያዘው የሐሳብ ጥራት ሳይሆን፣ በወንዜ ልጅ በመሆኑ እንደ አገር የተገባበትን አሳዛኝ ሁኔታ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡

  አንዱ ሲተክል ሌላው ለመንቀል፣ አንዱ ሲያመሠግን ሌላው ለመራገም፣ አንዱ መልካም ሲመኝ ሌላው ተስፋ ለማስቆረጥ፣ አንዱ ለአገር ሲያስብ ሌላው አገር ለመናድ፣ ወዘተ የተያዘው እሽቅድምድም አስገራሚ ነው፡፡ በሕይወቱ ለአገሩ ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ስለማበርከቱ ማረጋገጫ የማያቀርብ፣ ለአገራቸው የሚለፉ ሰዎችን ሲያንቋሽሽና ሲያዋርድ ማየት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ቤተሰቡን በአግባቡ መምራት የማይችል አገርን ከእነ ችግሮቿ ተሸክመው አንድ ደረጃ ለማድረስ የሚውተረተሩ ሰዎችን ሲያበሻቅጥ እንደማየት የሚያሳዝን ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ ራስህን ከኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል እጅህን ታጠብ፣ ርቀትህን ጠብቅ፣ አፍህንና አፍንጫህን ሸፍን ተብሎ ተመክሮ በየሥርቻው ከቢጤዎቹ ጋር አፍ ለአፍ ገጥሞ እየመሸተ፣ በየትኛው ሞራሉ ነው መንግሥት እያደረገ ያለውን የመከላከል ጥረት የሚያጣጥለው ቢባል ከመገረም ሌላ መልስ አይኖርም፡፡ በቤተሰብ ደረጃ ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር ይፋ ሲደረግ በደቦ እየተራገሙ ለምን ምርጫ አልተደረገም ታዲያ እያሉ የሚራቀቁ ጭምር ከማስገረም አልፈው ያሳዝናሉም፣ ያሳፍራሉም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁሉንም ነገር የልዩነት መነሻ ምክንያት ማድረግ እየተለመደ፣ ልዩነትን ግን በአግባቡ ይዞ ለጠንካራ የውይይት ባህል ለመዘጋጀት አለመፈለግ እንቆቅልሽ ነው፡፡ በምትኩ እየተዘራ ያለው ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የገነቧቸውን ወግ፣ ልማድና ባህል የሚንድ ተግባር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ደግሞ ማኅበረሰባዊ መከባበርን እያስወገደ ብልግናን እያነገሠ ነው፡፡

  አንዳንድ ወገኖች ኢትዮጵያዊያን በጋራ ያሳለፏቸውን የደስታና የመከራ ዘመናት ለመቀበል ስለማይፈልጉ፣ የሕዝቡን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን እንዳልተፈጠሩ ለማሳመን የሚሄዱበት ርቀት ያስደምማል፡፡ የጋራ ድሎችንና ሽንፈቶችን በመካድ ማኅበራዊ መስተጋብሮች እንዳልነበሩ ይሸመጥጣሉ፡፡ በደሎችን የአንድ ወገን በማድረግ አንዱን የሌላው ጠላት ያስመስላሉ፡፡ አብሮ ዘመናትን በመተሳሰብ፣ በፍቅርና በመከባበር ያሳለፈን የአንድ አገር ሕዝብ የሩቅ ጎረቤት ያስመስላሉ፡፡ በጋብቻ ተዋልደው ወንድምና እህት የሆኑ ኢትዮጵያዊያንን ጭምር አሳዛኝ ቅጽል በመስጠት ለመለያየት ይሞክራሉ፡፡ ለምን እንዲህ ዓይነት ድርጊት ይፈጸማል የሚሉ ወገኖችን በተለመደው ስድብና ማዋረድ ያሸማቅቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ በትውልዶች መስዋዕትነት እዚህ ደረጃ መድረሷን በመካድ አዲስ ታሪክ ለመጻፍ ይዳዳቸዋል፡፡ ሕዝብ ይከበር፣ የጋራ ታሪክ ይከበር፣ ማኅበራዊ እሴቶች ይከበሩ ሲባል ተቃርኖ መፍጠር የዘመኑ አዋቂነት ሆኗል፡፡ ግለሰብን ከተፈጠረበት ማኅበረሰብ አውጥቶ ባዕድ ለማድረግ የሚደረግ የፈጠራ ዘመቻ፣ ምን ያህል አሳዛኝና አሳፋሪ ደረጃ ላይ እንደተደረሰ ያሳያል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉት ደግሞ ፊደል ከመቁጠር አልፈው ልሂቃን የሚባሉት ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ከባህር ማዶ ታዋቂ የዕውቀት ደብሮች ከሚገባው በላይ ቀስመናል ብለው የሚመፃደቁ መሆናቸው ያስደምማል፡፡ የኢትዮጵያዊያን መለያ የነበሩት አስተዋይነት፣ አርቆ አሳቢነትና ጨዋነት ተደፍጥጠው በምትካቸው ጥራዝ ነጠቅነት በመስፈኑ መከባበር ትርጉም አልባ ሆኗል፡፡ ወደ ሽቅብ ማምራት ሲገባ ቁልቁለቱን መንደርደር የየዕለት ተግባር መሆኑ ያሳዝናል፣ ያሳፍራል! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በሰባት የመንግሥት ተቋማት ላይ ሰፊ የወንጀል ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተሰማ

  በስምንት የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ተወስኗል ከ1.4 ቢሊዮን...

  ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

  በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

  ጎህ ቤቶች ባንክ ወደ ቤት ልማት ለመግባት ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

  በስምንት ወራት ውስጥ 7.9 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል ኢትዮጵያ ውስጥ...

  ለካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ስድስት የቦርድ አባላት ተሾሙ

  ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቦርድ ሰብሳቢ ሆነዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...

  ወጋገን ባንክ ከገጠመው ቀውስ በማገገም በ2014 የሒሳብ ዓመት የተሻለ ትርፍ አገኘ

  ለሁለት ዓመታት የዘለቀው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸው ከተስተጓጎለባቸው...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የመንግሥት ተቀዳሚ ኃላፊነት ንፁኃንን ከአጥቂዎች መከላከል ነው!

  በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ንፁኃን ያለ ኃጢያታቸው የሚጨፈጨፉበት ምክንያት ብዙዎችን ግራ ከማጋባት አልፎ፣ የአገርና የጠቅላላው ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ከመቼውም ጊዜ በላይ እያሳሰበ ነው፡፡ መንግሥት...

  ምሁራንና ልሂቃን ከአስተዋዩ ሕዝብ ታሪክ ተማሩ!

  አገራዊ ምክክሩን ለመጀመር ዝግጅት እየተደረገ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ የኢትዮጵያን የትናንት ትውልዶችና የዛሬውን ይዘት መመርመር አስፈላጊ ነው፡፡ ያለፉት ዘመናት ትውልዶች ለአገራቸው የነበራቸው ቀናዒነት የፈለቀበት...

  ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ ዋጋ ያስከፍላል!

  በኳታር እየተከናወነ ያለው የዓለም ዋንጫ በእግር ኳስ ጨዋታ ውስጥ ያልተጠበቁ ማራኪ ቴክኒኮችንና ታክቲኮችን ከአስገራሚ ውጤቶች ጋር እያስኮመኮመ፣ ከዚህ ቀደም በነበረ ችሎታና ዝና ላይ ተመሥርቶ...