Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ይወያያል

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የውሳኔ ሐሳብ ላይ ይወያያል

ቀን:

በፈቃዳቸው ከኃላፊነት የለቀቁት ወ/ሮ ኬሪያ ሌሎችም የእሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ ጥሪ አቀረቡ

ምክር ቤቱ የአፈ ጉባዔዋን ውሳኔ ድብቅ ዓላማ የያዘ እምነት ማጉደል ሲል ተቸ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተመራለት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ላይ በሥሩ ከሚገኘው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ፣ ከዛሬ ረቡዕ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ መወያየት ይጀምራል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዚያ 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁ ምክንያት፣ ምርጫ ባይደረግ የመንግሥት ሥልጣን ምን ሊሆን እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ድንጋጌ ባለመኖሩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትርጓሜ እንዲሰጥበት መላኩ ይታወሳል።

ጥያቄው የደረሰው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የቀረበውን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብለት በሥሩ ለተደራጀው የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ የመራ ሲሆን፣ ጉባዔው የቀረበለትን የትርጓሜ ጥያቄ መርምሮ የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሳምንት በፊት አቅርቧል።

በሕጉ መሠረት ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ አያስፈልገውም ብሎ ጉባዔው ከድምዳሜ ላይ ከደረሰ፣ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳያቀርብ ድምዳሜውን ይፋ ማድረግ ይችላል። ነገር ግን የደረሰበት ድምዳሜ ትርጓሜ ያስፈልገዋል የሚል ከሆነ ጉዳዩን የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማሳወቅ ይጠበቅበታል።

በመሆኑም ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የደረሰው የውሳኔ ሐሳብ ጉዳዩ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ያስፈልገዋል የሚል እንደሚሆን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች ገልጸዋል። ፓርላማው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የላከው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ የሚከተሉትን በማገናዘብ የቀረበ ነው።

‹‹ምርጫ በሚደረግበት ወቅት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰትና በዚህም ሳቢያ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን፣ የምርጫ ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ምክር ቤቶችና ሥራ አስፈጻሚው የመንግሥት አካል የሥልጣን ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? ለሚሉት ጥያቄዎች ሕገ መንግሥቱ ምላሽ ባለመስጠቱ የገጠመንን ችግር በመፍታት ረገድ ሕገ መንግሥቱ ችግር ክፍተት ያለበት የሚያስብል ነው። በመሆኑም ከፍ ብለው የተገለጹትን ድንጋጌዎች ከሕገ መንግሥቱ ዓላማና ግቦች እንዲሁም መሠረታዊ መርሆዎች ጋር በማገናዘብ ትርጓሜ እንዲሰጣቸው፤›› የሚሉ ናቸው።

በዚህ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ላይ አጣሪ ጉባዔው የደረሰበትን የውሳኔ ሐሳብ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለመወያየት ለአባላቱ ጥሪ ካደረገ ከቀናት በኋላ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም የቀረበውን የትርጓሜ ጥያቄና የውሳኔ ሐሳብ በመቃወም በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን፣ መቀሌ ከተማ ሆነው ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ፣ አፈ ጉባዔዋ ራሳቸውን ከኃላፊነት ስለማንሳታቸው በይፋ በደብዳቤ ለምክር ቤቱ እንዳላሳወቁ ገልጸዋል።

አፈ ጉባዔዋ በሰጡት መግለጫ ከምርጫ ጊዜ ከማራዘም ጋር በተያያዘ በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ስም ሕገወጥ የሥልጣን ማራዘም ተግባር እየተፈጸመ በመሆኑ፣ ለመልቀቅ መወሰናቸውን ገልጸዋል። ‹‹የብሔርና የሃይማኖት መብት የሚያስከብረው ሕገ መንግሥት ሲጣስ ማየት ስለማልፈልግ፣ ሕገ መንግሥቱ ለማክበር የገባሁት ቃል ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ለፌደሬሽኑ ካለኝ ታማኝነት በመነሳት በሕገ መንግሥት ጥሰት ተግባር ላለመሳተፍ በፈቃዴ ከሥልጣኔ ወርጃለሁ፤›› ብለዋል።

ሌሎች የምክር ቤቱ አባላትም ሕገወጥ ያሉትን ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ እንዳይቀበሉና የእሳቸውን መንገድ ተከትለው እንዲቃወሙ ጥሪ አቅርበዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባርን ለማጠናከር የወጣው አዋጅ ቁጥር 251፣ እንዲሁም የምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ የምክር ቤቱ ዋና አፈ ጉባዔ በሌሉበት ወቅት ምክትል አፈ ጉባዔው ተክተው እንደሚሠሩ ይደነግጋሉ።

ጉዳዩን በተመለከተ ለሚዲያዎች አስተያየታቸውን የሰጡት የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባዔ አቶ መሐመድ ረሺድ፣ አፈ ጉባዔዋ ምክር ቤቱ የሚያካሄደውን ስብሰባ በተመለከተ በእሳቸው ከሚመራው አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር በጥሩ ሁኔታ ተወያይተውና አጀንዳዎችን በጋራ አፅድቀው እንደነበር ገልጸዋል።

አንድ የምክር ቤት አባል የሥራ መልቀቂያ ሲያስገባ የራሱ ደንብና ሥነ ሥርዓት ቢኖረውም፣ የአፈ ጉባዔዋ ውሳኔ ግን ከዚህ ደንብና መመርያ ያፈነገጠ ድርጊት እንደሆነ ተናግረዋል። መደበኛ ስብሰባውም በተያዘለት ዕለት እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ የሕገ መንግሥትና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ወርቁ አዳሙ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት፣ ‹‹አፈ ጉባዔዋ ራሳቸው በጠሩት መደበኛ ስብሰባ ዋዜማ መልቀቃቸው፣ የፓርቲ ወገንተኝነታቸው የብሔር ብሔረሰብ ተወካይነታቸውን ያሳነሰና ተገቢነት የሌለው ውሳኔ ነው፤›› ብለውታል።

አክለውም አፈ ጉባዔዋ የፈጸሙት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰጣቸው ኃላፊነት ላይ እምነት ማጉደል ተግባር እንደሆነ፣ ድንገት በሚዲያ ወጥተው መናገራቸውም ድብቅ ዓላማ እንዳለው የሚያሳይ ነው ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...