ምርጫው ለወራት ብቻ እንደሚራዘም ፍንጭ ሰጥተዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ምርጫው እንዳይራዘም ምርጫ ቦርድን ለመጫን ሞክረው እንደነበር፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይፋ አደረጉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኼንን የተናገሩት ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ነው። የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይችሉ የሚገልጽ ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላኩበት ወቅት፣ ጠንከር ያሉ ቃላት ተለዋውጠው እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
‹‹እናንተ ምርጫውን ለማሸነፍ ስለማትችሉ ምርጫው መቆም ያለበት ይመስሎታል ወይ?›› እንዳሏቸው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሰብሳቢዋ እናንተ ያሉት ማንን ነው ብለው ሲጠይቋቸውም፣ እናንተ ተቃዋሚዎች ብዬ እሳቸውን ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ጨፍልቄ ስላልፈለጋችሁ ነው ምርጫው እንዲራዘም የምታደርጉት። የኢትዮጵያ ሕዝብና ፓርላማው ምርጫውን በገለልተኝነት እንዲያካሂዱ ብሎ ነው ኃላፊነት የሰጠዎት፤›› እንዳሏቸው በይፋ ገልጸዋል።
ይህንን ማድረጋቸው የሚመሩት ብልጽግና ፓርቲ ለምርጫው በቂ ዝግጅት አድርጎ የነበረ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በተፈጠረባቸው ስሜት የተናገሩት ቢሆንም፣ የፈጸሙት ነገር ተገቢ እንዳልሆነ ገልጸዋል።
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካንም የዋዛ ባለመሆናቸው ኃላፊነት የተረከቡት በኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ምርጫዎች በሁሉም መመዘኛዎች የተሻለ ምርጫ ለማካሄድ እንጂ፣ ‹‹እርስዎ በፈለጉት እንደተለመደው ዓይነት የጨረባ ምርጫ ለማካሄድ ከሆነ፣ ኃላፊነቴን መልቀቄን ነገ ጠዋት ለምክር ቤቱ አሳውቄ እለቃለሁ፤” እንዳሏቸው ጠቅላይ ሚኒስተሩ አስታውቀዋል።
በኋላም ጉዳዩ ምርጫ ቦርድን ወደሚመለከተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ደርሶ አፈ ጉባዔው ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ ለምን እንደተቸገረ አስረድተው፣ ትክልል እንዳልፈጸሙ እንደ ነገሯቸውና ይቅርታም መጠየቅ እንደሚገባቸው እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ለምክር ቤቱ የተናገሩት ምርጫውን ለማራዘም መንግሥትም ሆነ እሳቸው የሚመሩት ፓርቲ ፍላጎት እንዳልነበረው፣ እንዲያውም ከማንኛውም ፓርቲ በላይ ምርጫው መካሄድ አለበት የሚል እምነት እንደነበራቸው ለማስረዳት ነው።
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ምንም እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፈጸሙት ተግባር ከተናገሩ በኋላ ከምክር ቤቱ የተሰማ አስተያየት ባይኖርም፣ በርካታ ምሁራንና ተንታኞች ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈጸምኩት ብለው ይፋ ባደረጉት ድርጊት ላይ ትችትና አሉታዊ አስተያየቶቻቸውን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች እየገለጹ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ የምክር ቤቱ ቆይታቸው ምርጫው ቢበዛ ቢበዛ ለወራት ብቻ እንደሚራዘም ፍንጭ የሰጡ ሲሆን፣ በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰጡትን ማብራሪያ በፖለቲካ ገጽ ይመልከቱ።