Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርግብፅ ዓባይን ለመቆጣጠር የፈጸመችው የረዥም ጊዜ ሴራ

ግብፅ ዓባይን ለመቆጣጠር የፈጸመችው የረዥም ጊዜ ሴራ

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ግብፅ የዓባይ ጉዳይ ራሷ በምትፈልገው መንገድ እንዲያልቅ ቢያንስ ቢያን ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን አንስቶ ጥረት አድርጋለች፡፡ በአፄ ምኒልክ ጊዜ የነበረው ስምምነት የራሱ ችግር የነበረው ሲሆን፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም የታየው ቁርጠኝነት ብዙ የተገፋበት አልነበረም፡፡ በደርግ ጊዜ ኢትዮጵያን የዓባይ ተጠቃሚ ለማድረግ ቁርጠኛነቱና ወኔው የነበረው ቢሆንም፣ ለራሱ በውስጥና በውጭ ፖለቲካ ተወጥሮ ስለነበረ በምኞት ብቻ ቀርቷል፡፡ ሆኖም ስለዓባይ የተጻፉት ግጥሞች፣ ዜማዎች፣ ዘፈኖችና ሌሎች የሥነ ጥበብ ሥራዎች በዘመኑ የነበረውን ብርቱ ፍላጎት የሚፈነጥቁ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

በሽግግሩ ዘመን ኢትዮጵያና ግብፅ በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ስምምነት መፈረማቸውን በሚመለከት ‹‹የዓባይ ውኃ ስምምነት ሚስጥር›› በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ፣ ለመሆኑ ለዘመናት ችግር ፈጥሮ የነበረ ስምምነት በምን ምክንያት እንዲህ ቀለለ? ሌላ ሚስጥር ይኖረው ይሆን? ለመሆኑ ግብፅ በወንዛችን፣ በአፈራችን፣ በተፈጥሮ ደጃችን ገብታ ‹‹መገደብ አትችልም›› በማለት የምትከለክል ማነች? ከጥንት ጀምሮ በፖለቲካችን፣ በኢኮኖሚያችንና በማኅበራዊ ሕይወታችን ጣልቃ እየገባች የምትፈተፍተውስ? የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብፅ ጋር በስምምነት ጀምሮ በስምምነት በመጨረስ ፈንታ እስካሁን ሳይስማማ የቆየው ለምንድነውና ሌሎችን ሐሳቦች አቅርቤ ነበር፡፡ ትናንት የዓባይ ወንዝ መገደብ ሲጀምር ፍፃሜ አይኖረውም ብላ ያሰበችው ግብፅ ወደ ፍፃሜ በተጠጋ ቁጥር የማንገራገሯ መጠንም በዚያው ልክ እየጨመረ ሄዷል፡፡ የዚህ ጽሑም መነሻም ግብፅ ከጥንት ከምሮ እስካሁን ስትወስደው የነበረው አፍራሽ ዕርምጃ የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን የመዳሰስ ነው፡፡  

የዚህ ጽሑፍ መነሻ ሐሳብ ከቀረቡት ጥያቄዎች ዙሪያ የሚሽከረከር ሲሆን፣ ወደ ስምምነቶቹ ፍሬ ሐሳብ ከመሄዳችን በፊት ስለዓባይ (ናይል) መጠነኛ ሐሳብ ይኖረን ዘንድ በቅድሚያ በአጭሩም ቢሆን እንደሚከተለው እንመልከት፡፡ በመሠረቱ ዓባይን የሚጨምረው ናይል በዓለም ረዥሙ ወንዝ ነው፡፡ 4,160 ማይልስ (6‚695 ኪሎ ሜትር) በላይ የሚጓጓዝ ከመሆኑም በላይ ከምድር ወገብ ተነስቶ ወደ ሰሜናዊ ነፋሻ አየር መስመር የሚጓዝ ወንዝ ነው፡፡ ናይል ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ወይም ከምዕራብ ወደ ምዕራቅ የሚያቋርጥ ቢሆን ኖሮ ዩናይትድ ስቴትስን በተጠቀሰው አቅጣጫ ከዳር እስከ ዳር ለማቋረጥ የሚችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የዚህን ወንዝ ታላቅነት ለማጉላት ካስፈለገም ከአማዞን ወንዝ 255 ኪሎ ሜትር እንደሚርቅ መመልከት ይቻላል፡፡ ይኸው ወንዝ ከጣና ሐይቅ የሚነሳው የእኛ ዓባይና ከክዩንጋ፣ ከአልበርታና ከቪክቶሪያ ሐይቅ የሚነሳው ነጭ ዓባይ ቅልቅል ሲሆን፣ መረብ ወንዝም ስሙን አትካራ ብሎ ቀይሮ ‹‹አትባራ›› ተብሎ በሚጠራው የሱዳን ግዛት ይገኛል፡፡ ዝምድናውን ከደቡብ ሱዳን የሚጀምረው ባሮ ወንዝም አንዱ የኢትዮጵያ ገባር ነው፡፡ 

በዚህ ወንዝ ዳርቻ የተጀመረው ጥንታዊ የሥልጣኔ ዘመን 5000 . በፊት እንደሆነ ሲታወቅ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ያሉ ገበሬዎች በዓለም ወደር የሌለውን ለም አፈር እየተጠቀሙ በዓመት ሁለት ጊዜ እንደሚያመርቱ ይታወቃል፡፡ ከግብፅ ሌላ ሱዳንም በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ ስትሆን፣ ወንዞች የሚመነጩባቸው አገሮች በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳና ኬንያ ግን የረባ ፋይዳ አያስገኝላቸውም፡፡ የዓባይ ጉዳይ ብዙ የሚያጽፍ ብቻ ሳይሆን የሚያጻጽፍ ቢሆንም ይህ ትውልድ ግብፅ ዓባይን ለመቆጣጠር ስትል የፈጸመችው የረዥም ጊዜ ሴራ ምን ያህል አስከፊ እንደነበር ይህ ትውልድ መጠነኛ ግንዛቤ ይኖረው ዘንድ፣ አቪሻይ ኤሊ ቤን ዶር ‹‹ኢሚሬት፣ ሐረር፣ ኢትዮጵያ›› በ2018 ለንባብ ካበቃው መጽሑፉ ያገኘውን የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደሚከተለው ያቀርባል፡፡

ግብፅ ለምን በኃይል መጠቀም ፈለገች?

ግብፅ 16ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 18ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ የኦቶማን ኢምፓየር ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡ ግብፅ አዲሱን የመስፋፋት ዕርምጃ የጀመረችው እ.ኤ.አ. 1865 ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በምሥራቅ ሱዳንና በቀይ ባህር ዳርቻ የነበሩትን ሰዋንኪንና ምፅዋን የግዛቷ አካል በማድረግ ነበር፡፡ እነዚህም የባህር ዳርቻዎች የኢትዮጵያ አካል እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡ አል ነጃሺ ሰዋንኪን መወለዳቸው የሚያወሳው ትርክት አንዱ ነው፡፡ ግብፅ ሱዳንና የቀይ ባህር ድንበር ከተሞችን ከግዛቷ ጋር የማጠቃለል ህልም ያደረባት ኢስማኢል ፓሻ የኦቶማን ኢምፓየር የግብፅ ገዥ ሆኖ ከተሾመ ወዲህ የተፀነሰ ሳይሆን በፈርኦኖችም፣ በፋጢሚዶችም፣ በመምሉኮችም ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. 1811 ወዲህ በነበሩት እንደ መሐመድ ዓሊ ፓሻ ያሉ የኦቶማን ኢምፓየርም መሪዎችም ምኞት ነበር፡፡ ስለሆነም 1865 ላይ በሰዋንኪንና በምፅዋ ላይ የሃርቂቆ ናኢብ አመራርን በማስወገድ የኦቶማን ሥልጣን ያለውን ሹም አስቀመጡ፡፡ በናኢቡ አገዛዝ ምትክም የአውሮፓውያንን የፖለቲካ ሥልት የተከተለ የከንቲባ አስተዳደር መሠረቱ፡፡ በቀይ ባህር ዳርቻም የባሪያ ንግድ እንዳይካሄድ የአውሮፓውያን ሲያካሂዱት ለነበረው ትግል አጋር ሆነው ቀረቡ፡፡

ግብፅ ምፅዋንና ሰዋንኪንን ለመቆጣጠር መቻሏም ከዲቩ ቀጣይነት ያለው መስፋፋት አመቺ ሁኔታን ፈጠረ፡፡ ከኢስታንቡል መንግሥት የበላይነት በመላቀቅ በቀይ ባህር የነበረውን የበላይነት ለማስፈን የነበረውን ምኞት አጠናከረለት፡፡ የግብፅ መሪዎች የባህር ዳርቻ ከተሞች መሪዎችንና ታላላቅ ሰዎችን በስጦታ ያጥለቀለቋቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በአዲሱ መንግሥታቸው አመራር ሥልጣን እንደሚሰጧቸው ቃል ገቡላቸው፡፡ በአንድ በኩል እየገደሉና እየዘረፉ በሌላ በኩል ደግሞ የበለጠ እየገደሉና እየዘረፉ ለመበልፀግ ይችሉ ዘንድ ሰዋንኪንና ምፅዋ ላይ የቴሌግራፍ መስመር ለመዘርጋት፣ የፖስታ አገልግሎት ለመስጠት፣ ከተማዎች ዘመናዊ የልማት ጥናትና ምዝገባ ለማካሄድ፣ በከተሞችና በገጠር ዘመናዊ የፍትሕ ሥርዓት ለማስፈን የሚያስችል  የሚመስል አስተዳደር መሠረቱ፡፡ ይህም ሌሎቹን የአፍሪካ አገሮች ለመግዛት ሲችሉ የሚፈጽሙትን በሞዴልነት የሚያመለክት አድርገው ይጠቀሙበት ነበር፡፡

ግብፅ በኢትዮጵያ ውስጥ የደረሰባት ሽንፈት

ግብፅ ሰዋንኪንና ምፅዋን እ.ኤ.አ. 1865 በቁጥጥር ሥር ካዋለችና ስዊዝ ካናል 1869 ከከፈተች በኋላ ከዲቭና አማካሪዎቹ የግብፅ አካባቢውን በቀጣይነት እንድትቆጣጠር፣ ማለትም ግዛቷን እንድታስፋፋ በነበራቸው ምኞት ዛሬ በኤርትራ ውስጥ የሚገኙትን ከረንን፣ ቦገስ ሰንሂት አውራጃን 1872 ሰኔ ላይ ያዘች፡፡ በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት እንዲነሳ አደረገች፡፡ ወርነር ሙዚንገር የተባለው የስዊሳዊ የከዲቭ ቅጥር ወታደር (ለገንዘብ ሲል በውትድርና የሚያገለግል) እና ግብፅ በግዛት ማስፋፋት ዕርምጃዋን እንድትቀጥልበት ይገፋፋው ነበር፡፡ እሱም ከረን ሰሜን ኢትዮጵያን ለማጥቃት የምትመች ሥፍራ እንደሆነች ሐሳብ ይሰጥ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1876 ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለመግጠም ያነሳሳውም የወታደራዊ ኃይሉ ጠንካራ መሆኑን በመተማመን ነበር፡፡ ‹‹በኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥትና በከዲቭ መካከል የሰላም ድርድር ማዊና እኔ ሞቼ እንጂ አይደረግም፤›› በማለቱ የዲፕሎማሲያዊ ድርድር ሐሳቡን ሳይቀበለው ቀረ፡፡

ሙዚንገር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚፈጽመው ጣልቃ ገብነት የጀመረው 1860ዎቹ አጋማሽ ላይ አንስቶ ነበር፡፡ በአንድ በኩል የከዲቭ ኢስማዒል ቅጥር ወታደር በሌላ በኩል ደግሞ ከሰላን በሚመለከት የፈረንሣይ አማካሪ ሆኖ ሲሠራ በሰሜን ትግራይ በሃማሴን አውራጃ በኩል አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ዘልቆ ገባ፡፡ ይልቁንም በቦጎስና በሃማሴን ውስጥ የነበሩ የላዛሪስት መናኩስት ችግር እንዳለባቸው ሲነግሩት ኢትዮጵያን ለማጥቃት የነበረው ፍላጎት ከፍ አደረገው፡፡

ሙዚንገር አዲሱ የምፅዋ ገዥ ተደርጎ 1871 ሲሾም ‹‹ለኢትዮጵያ ቁልፍ ሥፍራዎች ናቸው›› ብሎ ያመነባቸውን ቦጎስንና ሃማሴንን ተቆጣጠረ፡፡ እነዚህ ሥፍራዎች ‹‹መረብ ምላሽ ማለትም ከመረብ ወንዝ ባሻገር›› ተብለው የሚታወቁት የኢትዮጵያ ግዛቶች ነበሩ፡፡ ሙዚንገር በከረን ያስነሳው የጦርነት ነፋስ ካይሮ ሲደርስ አቀባበል የተደረገለት በድጋፍ መንፈስ ሲሆን፣ ከዲቭም በጋለ ስሜት ወጥመድ ውስጥ እንዲወድቅ አደረገው፡፡ በዚህ ጊዜ ካይሮ ‹‹አፄ ዮሐንስ ሊወገድ የሚገባው ባሪያ ነጋዴ ነው›› እያለች የከዲቭ መንግሥትን ደግሞ እንደዚህ ያለውን አስከፊ ባህል የምትዋጋና ዘመናዊ ሥልጣኔ ለማስፈን ተግታ የምትሠራ መንግሥት መሆኗን ለአውሮፓውያን ታሳውቅ ነበር፡፡

ግብፅ በአንድ በኩል በሃማሴን አውራጃ የቴሌግራፍና የባቡር መስመር ዝርጋታዋን እያጠናከረች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት መያዝ ቢያንስ የተወሰነውን የኢትዮጵያ ግዛትን መያዝ ለግብፃዊቷ ሱዳንን ከቀይ ባህር ጋር ከግዛቷ ጋር አንድ ለማድረግ የነበራትን ፍላጎት ለመተግበር ቅድመ ሁኔታ አድርጋ ወስዳው ነበር፡፡ የከዲቭ የመስፋፋት ፖሊሲ የተመሠረተው እንደ ዓድዋ፣ ጋላባት፣ ሐረር ያሉ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ያላቸውን ከተሞች በቁጥጥር ሥር ማድረግ ነው፡፡ በሚቀጥለው ዕርምጃ የሶማሌ የባህር ዳርቻን መቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ፣ ይህን በማድረግ የኢትዮጵያን የጨው ማዕድንን በመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ትርፍ ምንጭ ማረጋገጥ እንደሆነ አስረድቶ ነበር፡፡

የግብፅ ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ፍላጎት ከዓለም አቀፉ ሁኔታና አፍሪካን እንደ ቅርጫ ከመከፋፈል አንፃር መታየት የሚኖርበት ሲሆን፣ በተለይም አውሮፓውያን ኃይሎች ቀይ ባህርን ለመቆጣጠር ከነበራቸው ብርቱ ፍላጎት ጋር የሚታይ ነው፡፡ ከዲቭ ከብሪታንያ፣ ከፈረንሣይና ከኢጣሊያ ያልተናነሰ ድርሻ እንዲኖረው ይፈልግ ነበር፡፡ ግዛት የመከፋፈሉ ሁኔታ ሲታይ ብሪታንያ ኤደንን፣ ፈረንሣይ ጂቡቲን ቅኝ ግዛት ሲያደርጉ፣ ኢጣሊያ ደግሞ እ.ኤ.አ. 1869 የአሰብን ከፊል ግዛት የኢኮኖሚ ምሽጓ አድርጋ መያዟን ካስታወቀት በኋላ በፍጥነት በወታደራዊ ኃይል ተቆጣጥራት ነበር፡፡  

እ.ኤ.አ. በ1873 ማለትም ሙዚንገር በከዲቭ ኢስማዒል ስም ከረን ከተቆጣጠረ ከአንድ ዓመት በኋላ የግብፅ ግዛት አካል አደረጋት፡፡ በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሰላም እንዲመጣ ባለመደረጉም የግብፅ ጦር ሁለት ቦታዎች ላይ ሽንፈት ገጠመው፡፡ እነዚህም እ.ኤ.አ. በኖቬምበር 1875 በጉንደት ላይ ከጃንዋሪ እስከ ማርች 1876 በጉራዕ የተካሄዱ ጦርነቶች ናቸው፡፡

የጉራዕ ጦርነት ግብፅ ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚያስችላት አንዳች ዕድል እንደሌላት አረጋገጠ፡፡ በዚህም መሠረት ግብፅ በሦስት ወራት ውስጥ 14‚000 ሠራዊቷን አጣች፡፡ በኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት ደረሰባት፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያውያን ጦረኞች የሰይጣን መንፈስ ተላብሰው ያደረሱባት ጥቃት ኢትዮጵያን ለመውረር የወደፊት ዕድል እንደሌላት አሳወቃት፡፡ ይህም ሆኖ ደግሞ ግብፃውያን እስከ 1885 ድረስ ከረንና አካባቢዋን ተቆጣጥረው ቆይተዋል፡፡

ግብፅ በሶማሊያ የባህር ድንበር የደረሰባት ሽንፈት

የግብፅ ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ኢትዮጵያን ዙሪያ ምላሿ በመክበብ ለማስገበርና የዓባይ ምንጭ ለመሆን እንደሆ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1875 አራት መኮንኖች ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ከዲቭን የሚያገለግሉ አውሮፓውያን ቅጥር መኮንኖች ሲሆኑ፣ አንዱ ግብፃዊ ነበር፡፡ እነሱም የሶማሊያ የባህር ድንበርንና ሐረርን እንዲይዙ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ነበር፡፡ ስማቸውም ሄንሪ ማክኪሎፕ ፓሻ፣ ሙዚንገር፣ ሶርነ አረበድረፕ ቤይና ሙሐመድ ረዑፍ ፓሻ ነበሩ፡፡

ማክኪሎፕ ፓሻ በከዲቭ አስተዳደር የባህር ኃይል አዛዥ ሲሆን፣ እስከ ኪሲማዮ ያለውን የሶማሊያን ግዛትን ያስገብራል ተብሎ የሚታመንበት የጦር ሰው ነበር፡፡ እርሱን በሚመለከት ጁባ ወንዝን መቆጣጠር ማለት የዝሆን ጥርስ፣ የጎማ ምርትና ሌሎች የእንጨት ውጤት የሆኑ ምርቶች ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላት የንግድ ቀጣና የሆነችውን ደቡባዊውን የግብፃውያን በርን መያዝ ማለት ነው፡፡ በዚያ አካባቢ የባሪያ ንግድ ይካሄድ ስለነበርም፣ ‹‹ከአውሮፓውያን ጋር ሆኖ የባሪያ ንግድን ይዋጋ ለነበረው›› ከዲቭ ያንን አካባቢ ለመግዛት ምክንያት ሊሆነው ይችላል፡፡

በዚህም መሠረት የከዲቭን ባንዲራ የሚያውለበልቡ የእንፋሎት ጀልባዎች እ.ኤ.አ. 1867 ላይ በኪሲማዮ፣ በቡሃርና በበርበራ ታይተው ነበር፡፡ 1870 ውስጥ ሙሐመድ ቤይ ጀማል የከዲቭን ባንዲራ በሚያውለበልብ ጀልባ ወደ ቡሃርና በርበራ ሁለት ጊዜ ተጉዞ ነበር፡፡ 1872 ውስጥ ከዲቭ እነዚህን የወደብ ከተሞችን መያዝ በኤደን ባህረ ሰላጤ የነበረውን ይዞታ ሊያጠናክርለት እንደሚችል አስቦ ነበር፡፡

ማክኪሎፕ ፓሻ እ.ኤ.አ. በኦክቶበር 1875 ሞቃዲሾንና ኪሲማዮን በቁጥጥር ሥር አድርጎ ግብፅ ወደፊት ጁባ ወንዝን በቅኝ ገዥነት ለመያዝ የሚያስችሏት ድልድዮች እንዲሆኑ ለማድረግ ነበር፡፡ በመሆኑም የግብፃውያን ሠራዊት እነዚህን ሁለት የባህር ዳርቻ ከተሞችን ያለ ብዙ መከላከል ሊቆጣጠሯቸው ቻለ፡፡ ይሁንና ስንቅና ትጥቅ ስላነሰው የብሪታንያ ሠራዊት ከሥፍራው ደርሶ አባረረው፡፡ በዚህም መሠረት ሶማሊያን ለመያዝ ጥሩንባ እየነፋ የገባው የግብፃውያን ሠራዊት ብሪታውያን ማክኪሎፕ ዕቃውን ጠቅልሎ እንዲወጣ ሲያዘው በትንሽ ተቃውሞ ብቻ እ.ኤ.አ. በዲሴምበር 1875 አበቃለት፡፡

በከዲቭ መንግሥት አመለካከት የጨው ማዕድኑን ለመቆጣጠር ይቻል ዘንድ ወደ አውሳ የተላከው ቡድን የደረሰበት መጥፎ አጋጣሚ መራራ ነበር፡፡ ይህ አስከፊና መሪር ዕጣ ፈንታ የደረሰበትም፣ የግብፃውያን የቅኝ አገዛዝ ፖሊሲ ፕሮፓጋንዳ ዋነኛ አፈ ቀላጤ፣ የጨው ማዕድኑን መቆጣጠር ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው ያስገነዘበው፣ እንዲሆንም ፈረንሣይ ወደ አካባቢው ታደርገው የነበረውን እንቅስቃሴ ያስቆማል የሚል እምነት የነበረው ዋርነር ሙዚንገር ላይ ነበር፡፡ 

ሌላው የግብፃውያን የፖለቲካ አካሄድ እ.ኤ.አ. 1875 ከሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጋር የፈጠሩት ግንኙነት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የንጉሠ ነገሥት ዮሐንስ አራተኛ የሥልጣን ተቀናቃኝ ከነበሩት ንጉሥ ምኒልክ ጋር ጊዜያዊ የሆነ ወዳጅነትን ለመመሥረት ፈልጋ ነበር፡፡ በመካከላቸው የነበረውን ስንጥቅ በሚገባ ለማስፋትም ነገሩን ለማጦዝ ይቻልና ንጉሥ ምኒልክ የራሳቸው ጳጳስ ይኖራቸው ዘንድ መላክ አስፈላጊ ሆኖ አገኘችው፡፡ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግብፅ ወደ ኢትዮጵያ የምትልከው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የሚመራ አንድ ጳጳስ ብቻ ነበር፡፡ ስለሆነም በሙዚንገር አስታዋሽነት ሁለተኛ ጳጳስ ለንጉሥ ምኒልክ ለመላክ የተፈለገበት መሠረታዊ ምክንያት፣ በአፄ ዮሐንስ አራተኛና በንጉሥ ምኒልክ የነበረውን ግንኙነት በክርስትናው መስክም ጭምር ለመከፋፈል ነበር፡፡

ተቀባይነት አገኛለሁ ብሎ በቀየሰው ዘዴ በመኩራራትም ከግብፃውያን ወታደሮቹ ጋር የንጉሥ ምኒልክ ወታደሮች ጋር ለመገናኘት ከታጁራ ተነስቶ በስተምዕራብ ጂቡቲ በኩል ወደ አውሳ ሄደ፡፡ ሆኖም የመሬቱ አቀማመጥና የአየር ንብረቱ ሁኔታን ሊቋቋመው አልቻለም፡፡ ስለሆነም እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 14 ቀን 1875 ላይ የአካባቢው መሪ ሕዝቡን በማስተባበር ደረሰና ወጋው፡፡ በዚህም ውጊያ ዋርነር ሙዚንገር፣ ኢትዮጵያዊት (ኤርትራዊት) ሚስቱና አብዛኛዎቹ ወታደራዊ አዛዦች ሲሞቱ የተቀሩት ጥቂት ሰዎች ወደ ተጆራ ሸሽተው አመለጡ፡፡ ይህም ሽንፈት ኢትዮጵያን ለግዛት የነበረውን ህልም አከሸፈው፡፡

የሶማሊያ የባህር ዳርቻ ከተሞች

ከላይ ከተጠቀሱት ውድቀቶች በስተቀር ግብፃውያን የሱማሌ የባህር ወደብ ከተሞች የሆኑትን ዘይላዕና በርበራን በመቆጣጠር ረገድ ተሳክቶላቸው ነበር፡፡ ግብፅ በሁለቱ የወደብ ከተሞች የነበራት ሉዓላዊነትም እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 7 ቀን 1877 በተደረገው ስምምነት መሠረት የብሪታንያን ይሁንታ አግኝቶ ነበር፡፡ ይህም ስምምነት ዘይላዕን፣ በርበራን፣ ታጁራን፣ ቡሃርን ጨምሮ እስከ ጋርዳፉሪ የነበረውን ግዛት የሚያጠቃልል ሲሆን፣ በአጸፋውም የከዲቭ መንግሥት ሁሉም ወደቦች ለሁሉም አገሮች ንግድ ክፍት እንዲሆኑ፣ የባሪያ ንግድ እንዳይፈጸምባቸውና የየትኛውም አውሮፓዊ አገር ጦር እንዳይኖርባቸው እንዲያግድ የሚያግድ ስምምነት ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሁሉም ወደቦች በኩል ወደ ውጭ በሚላኩ ሸቀጦች ላይ የሚጣለው ቀረጥ አምስት በመቶ እንዳይበልጥና ብሪታንያ በሁሉም ወደቦች የቆንስላ ጽሕፈት ቤት እንድትከፍት ያጠቃለለ ስምምነት ነበር፡፡ ስምምነቱ ብሪታንያ በሶማሊያ ወደብ ከተሞችና በሃረር ከተማ የነበራት ቅኝ አገዛዝ ለቃ እንድትወጣ እስካደረገችበት እ.ኤ.አ. ከኤፕሪል እስከ ሜይ 1884 ተጠብቆ ነበር፡፡

የሐረር መያዝ

ግብፅ ሐረርና አካባቢዋን ቅኝ ለመግዛት የፈለገችበት ምክንያት ውስብስብ ነው፡፡ ሐረር የተቀመጠችበት መልክዓ ምድር፣ ለንግድ ያላት ስትራቴጂካዊነት፣ በኢትዮጵያ አምባዎች ላይ በመኖር ከሸዋው ንጉሥ ምኒሊክ ጋር ወዳጅት ለመመሥረት፣ ሐረር ውስጥ ሆና የአፍሪካ ሙስሊሞችን ለመመራት ጥቂቶቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከዓለም አቀፍ ምክንያቷም ቀደም ሲል እደተጠቀሰው ብሪታንያ፣ ፈረንሣይና ኢጣሊያ ለመያዝ እንደሚሹት ሁሉ በሶማሊያ ባህር ድንበር ከተሞች እግሯን ለመትከል ነበር፡፡

ማክኪሎፕ ፓሻ የሶማሌ የባህር ዳርቻዎችን (ኪሲማዮንና ቡሃርን) የመያዙ ተልዕኮ እ.ኤ.አ. 1875 መጨረሻ ላይ ባይሳካም ዘይላንና በርበራን እንደያዘች ነበር፡፡ ስለሆነም እ.ኤ.አ. 1875 ላይ የባሪ ነጋዴውን አቡበከር ኢብራሂም ሻሂምን የዘይላዕ ገዥ አድርጋ ሾመች፡፡ በከፊል የአፋር ዝርያ ያለው አቡበከርም በአካባቢ ሕዝብ ዘንድ በጣም ታዋቂነት ነበረው፡፡ በዚያ አካባቢ የሚገኙ ፈረንሣዮችም የዚህን ሰው በሕዝብ ዘንድ የነበረውን ተቀማጭነት ከግምት ውስጥ በማስገባትና በንግድ ለተሰማሩ ዜጎቻቸው በዘይላዕና በኦቦክ ሥፍራ ስለሰጣቸው፣ እ.ኤ.አ. 1860 የፈረንሣይ ዜግነትን የሰጡት ከመሆናቸውም በላይ የእነሱ ተወካይ እንዲሆን ሾመውት ነበር፡፡ የፈረንሣይን ዜግነት በማግኘቱ የተደሰተው አቡበከር ኢብራሂም ሻሂምን የሥልጣን አድማሱን በማደርጀት፣ በአፋርና በአውሮፓውያን ዓይን የዘይላዕ እጅግ ጠንካራ ገዥ መሆኑን አሳየ፡፡

በመሠረቱ የግብፃውያን አስተዳደር በኢኮኖሚና በፖለቲካ ኃያላን የሆኑ የባሪያ ነጋዴዎችን ማቀፍ የመጀመርያቸው አልነበረም፡፡ እ.ኤ.አ. 1873 በሱዳን የባህር አል ቐዛል አስተዳዳሪ የነበረው አል ዙበይር ራህማን መንሱር የታወቀ የባሪያ ነጋዴ ቢሆንም፣ የፓሻነት ማዕረግ ሰጥታው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ግብፃውያውን በዓል ዙበይር ድጋፍ አካባቢውን ከመቆጣጠራቸውም በላይ እ.ኤ.አ. 1874 በዓል ዙቤር የሚመራው የባሪያዎች ሠራዊት ዳርፉርን ለመቆጣጠር ችለው ነበር፡፡ በአልዙበይር ራህማን መንሱርና በአቡበከር መካከል የተወሰኑ ተመሳሳይነቶች አሉ፡፡ ስለሆነም ሁለቱም ግብፅ የመስፋፋት ፖሊሲዋንና ፖለቲካዋን ለማራመድ ስትል ያቀፈቻቸው ባሪያ ፈንጋዮች ነበሩ፡፡

እ.ኤ.አ. በ1875 ግብፅ ሐረርን ለመያዝ ዘይላዕ ዋነኛዋ የጦር ሠፈር ነበረች፡፡ እ.ኤ.አ. ኦገስት አጋማሽ 1875 ሙሐመድ ራዑፍ ፓሻ ዘይላዕ የደረሰው ወደ ሐረር ለሚያደርገው ‹‹በጂኦግራፊ ላይ የተመሠረት ጉዞ›› አስፈላጊውን ዕገዛ እንዲያደርግለት ከከዲቭ የተላከ ደብዳቤ ይዞ ነበር፡፡ ‹‹ሳይንሳዊ›› የሚል ጭምብል የለበሰበት ዋናው መሠረታዊ ምክንያት፣ ብሪታንያ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረመውን ስትራቴጂካዊ የኃይል ሚዛን መጠበቂያ ውል የሚፃረር ነው በሚል እንዳትቃወም ነው፡፡

ግብፅ ወደ ሐረር ያደረገችው ጉዞ ከሙዚንገርና አረንድረፕ ተልዕኮ ውድቀት በተቃራኒ፣ በራሷ ሰዎች ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ባወጣችው ዕቅድ መሠረት መሆኑ ነው፡፡ ይህም የተፈጸመው ከዲቭ ለሙሐመድ ራዑፍ ፓሻ በሰጠው ትዕዛዝና በዘይላዕ የግብፃውያን ወታደራዊ ኃይል ተጠናክሮ ዝግጅት እንዲያደርግ በተሰጠው መመርያ መሠረት ነው፡፡ ሙሐመድ ራዑፍ ፓሻ ዘይላዕ ሲደርስ አቡበከርን በመተካት በቀጥታ የዘይላዕ የበላይ ገዥ ሆነ፡፡ በነበረው አንፃራዊ ነፃነትና የሶማሊያ የባህር ዳርቻን፣ እንዲሁም ሐረርን በቀላሉ ለመቆጣጠር በመቻሉ በዘመናዊቱ ግብፅ ተደናቂነትን አግኝቷል፡፡ ግብፃዊው የታሪክ ምሁር አጣላህ ሸውቂ አል ጀማልም፣ ሙሐመድ ራዑፍ ፓሻ ወታደራዊ ተልዕኮውን ሲያወድስ፣ ከሱዳን ወደ አገሩ ግብፅ ከመመለሱ በፊት በአፍሪካ የምድር ወገብ ላይ በፍጥነት የተሾመ፣ በወታደሮቹ ዘንድ ተወዳጅ የሆነ ‹‹ግብፃዊ›› የሆነ የጦር መኮንን መሆኑን በአድናቆት ገልጾታል፡፡ ራዑፍ ፓሻ ‹‹ግብፃዊ ብሔራዊ ጀግና›› የሚል የክብር መጠሪያም አግኝቷል፡፡

በመሠረቱ ራዑፍ ፓሻ (1832 እስከ 1882) ፈጽሞ የግብፅ ተወላጅ አይደለም፡፡ በአባቱ በኩል የበርበራ ተወላጅ ሲሆን፣ በእናቱ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ይሁንና የተዋጣለት ዓረብኛ ተናጋሪ ከመሆኑም በላይ በከዲቭ አማካይነት ከውጭ የመጣ ቅጥር ነፍሰ ገዳይ ሳይሆን፣ በግብፅ ውስጥ ያደገ ከመሆኑም በላይ በወታደራዊ ሥልጠና ተኮትኩቶ ያደገውም በግብፃውያን ወታደራዊ ሥርዓት መሠረት ነው፡፡

መደምደሚያ

እስካሁን በቀረበው ጽሑፍ ግብፅ፣ ግብፅን በደቡብ ቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኙ እነ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ ያሉ የባህር ድንበር ከተሞችን፣ ከአሌክሳንደሪያ እስከ ደቡብ ሱዳን፣ ከምሥራቅ ሶማሊያ እስከ ግብፅ ያለውን በኃይልም ሆነ በዲፕሎማሲ ለማንበርከክ የፈለገችው፣ ሲመቻት በተንኮል ሳይመቻት ተለሳልሳ የምትቀርብበት በአንድና ዋነኛ ምክንያት ዓባይን ከምንጩ ለመቆጣጠርና ያለ ጠያቂ ለመኖር ነበር፡፡

ሃያኛው ክፍለ  ዘመን ይህን እንድታደርግ አላስቻላትም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የዓባይ ግድብ የመጨረሻ መልኩን እየያዘ ስለመጣ የመጨረሻ ተንኮሏን ከምትፈጽምበት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡ ስለዚህ ምን መደረግ አለበት? መንግሥት በዚህ ረገድ ማድረግ የሚገባው ጥንቃቄ እጅግ ከፍተኛ ወደ ሆነ ጥንቃቄ መድረስ አለበት፡፡ ሕዝብም የዓባይ ግድብ በፍጥነት እንዲጨርስ ተርቦም ሆነ ተጠምቶ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ዓባይ የዚህ ትውልድ ሐውልት ስለሆነ የግብፅ ተንኮል ማብቂያ መሆኑን ተገንዝቦ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...