Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እውነትም አንጀት አርስ!

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከመብራት ኃይል የረር ነው። ሕይወት ዓመሏ ብዙ ነው። መልኳ እያደር ይለዋወጣል። የጠበቁት ይቀርና ያላሰቡት ይከሰታል። የሠጉበት ነገር ጭምድድ አድርጎ እያሰረ በጭንቀት ይንጣል። ይኼኔ ታዲያ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› ብለው እንዲተርቱ ይገፋፋል። ይህች ነፍስ ተብዬ በሥጋ ከተማ ውስጥ የተሸሸገች ታላቅ ሚስጥር ነች፡፡ የሁለመናን ሚዛን እየጠበቀች እስከ ፍጻሜ ትገሰግሳለች፡፡ ስለዚህም ሕይወት ምን ብትከብድ፣ ኑሮ ምን እያደር ፊቷ ቢጠቁር መኖር ይፈቀር ዘንድ ግድ ታስብላለች። ነፍስ ታሳሳለችና። በማግኘት ጎዳና ላይም ሆነ በማጣት መንገድ ላይ ወዲያ ወዲህ ስንል ቀናችንና ዘመናችን ይጠናቀቃል። እንቅፋቱ ሲበዛብን በነፍስ በኩል ለፈጣሪ፣ በሥጋ በኩል ለገዥዎቻችን እንናገር ዘንድ እንማስናለን። ጎዳናው መሀል ደግሞ ቆሞ የሚያስፈራራ ተውሳክ አይጠፋም፡፡ አሁንም የሚያስፈራራን እሱ ነው! 

ፈጣሪ በጊዜው እንደ ፈቀደ መልሱን ሲሰጥ ሰው ግን ጉዳዩ በዝቶና ኔትወርክ ተጨናንቆበት አላዳምጥ ይለናል። ይህ ቢሆንም ቅሉ መኖር ይቀጥላል። ምን መከፋት ቢነግሥ፣ ምን መሰልቸት ቢያለፋን መኖር በሕይወት ጎዳና፣ መኖር በጉዞ ውስጥ መቀጠሉን ለመታዘብ ሁሌም በቦታው እንገኛለን። እንዳልነው ነፍስ ያሳሳልና፡፡ ታክሲ ውስጥ ገብቼ እንደ ተቀመጥኩ ዓይኔ አንዱ ጥቅስ ላይ ተተከለ። ‹ራስን ከመግዛት የበለጠ ትልቅ ሥልጣን የለም› ይላል። ከፊት መቀመጫ ደልደል ብሎ የተቀመጠ ተሳፋሪ እንደ እኔ ጥቅሱን በሙሉ ልቡ አጢኖ ሲያበቃ፣ ‹‹ባይሆን በዚህ እንኳ እንፅናና እንጂ. . .›› ብሎ ፈገግ አለ። በተናገረው ቃል ውስጥ ያለው ሥውር መልዕክት ቅድሚያ ለራሱ እንደ ተገለጠለት ሊጠቁመን የፈለገ ይመስላል። ካልመሰለስ ምን ይደረጋል!

‹‹በምኑ?›› በማለት ከኋላችን የተቀመጠ ጎልማሳ ጠየቀው። ‹‹‘ራስን ከመግዛት በላይ ሥልጣን የለም’ የሚለውን ጥቅስ አላየህም እንዴ? ባይሆን እንዲህ እያልን እንጽናና እንጂ! ሂሂ አሁን ይቺ ስላቅ አይደለችምና ነው?›› ብሎ አሽሟጠጠ። አንድ ወጣት ተሳፋሪ ፈጠን ብሎ፣ ‹‹እንዴ? እንዴ? ምነው ዴሞክራሲ እየገነባን? በድምፃችን ራሳችንን ማስተዳደር እየቻልን ማሽሟጠጡን ምን አመጣው ወንድሜ?›› ብሎ በቀናነት የመሰለውን አስተያየት ጨምሮ ጠየቀው። መልሱን ከመስማታችን በፊት፣ ‹‹ከታክሲ ውስጥ የመናገር ነፃነትና ከፓርላማችን የትኛው የሚበልጥ ይመስልሃል?›› ብሎ ከኋላ የተቀመጠ ሰው ወዳጁን ሲጠይቀው ሰማን። መልሱ ተድበስብሶ አልሰማን ሲል፣ ‹ደጇን ዓይተህ ቤቷ ግባ፣ እናቷን ዓይተህ ልጅቷን አግባ› የሚሉት ምሳሌ በአዕምሮዬ ተመላለሰ። ተድበስብሶ ማድበስበስ የት ያደርሰን ይሆን? የዚህንም መልስ መስማት አማረን፡፡ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ጥያቄዎችን እንደ ሸቀጥ ማምረት ምን ይፈይድልን ይሆን? እንጃልህ አትሉም!

‹‹ምን ዋጋ አለው?›› አለ አሽሟጣጩ ተሳፋሪ ድንገት ጮክ ብሎ፡፡ በመቀጠልም፤ ‹‹ድምፃችን የሚፈለገው ለምርጫ ብቻ ነው መሰለኝ ለአቤቱታና ለአስተያየት ጊዜ የሚፀየፈን ግን አይጣል ነው፤›› ሲለው ወጣቱ ዝም አለ። ተሳፋሪዎች እየገቡ ታክሲያችን በአዲሱ ሕግ መሠረት በሃምሳ በመቶ እየሞላች ብትሆንም፣ ወያላው የያዘው ልማድ አለቅህ ብሎት ትርፍ ካልጫነ በቀላሉ የሚንቀሳቀስ አልመሰለንም። ‹‹ኧረ እንሂድ? ምናለበት ቢበቃህ?›› አለው አንድ ተሳፋሪ። መቸኮሉ ከመቁነጥነጡ ያስታውቃል። ‹‹ቀስ በላ! እንደ ፈለግኩት ጭኜ ነው የምሄደው…›› ብሎ በትዕቢት አነጋገር መለሰለት። ይኼ አልበቃው ብሎ ደግሞ፣ ‹‹ከፈለግክ መውረድ ትችላለህ…›› ብሎ ገላመጠው። ‹‹አይ ራስን መግዛት?› በማለት ቅድም ጥቅሱን እያየ ሲያሽሟጥጥ የነበረው ተሳፋሪ በሳቅ ፈነዳ። ‹‹ልጅ የአባቱን ይወርሳል ሆነና ለምንለጥፈው ጥቅስ፣ መርህ ታማኞች አልሆን አልን፤›› ብሎ ሳቁን ካቋረጠበት ቀጠለው። ሌላው ደግሞ እኔ የምፈራው ሥራው በሌለበት ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተባለ የሚነገረው ነገር ተረት ተረት እንዳይሆን ነው፤›› ብሎ አቀረቀረ። አንዳንዱ ሰው ክፉኛ ነገር ሲገባው አሳሳቅና አለቃቀስን አሳምሮ ይችላቸዋል። በአስመሳዮች ዘመን ሙዚቃው፣ ድራማው፣ ኮሜዲውና ለቅሶው እንደ ማኅበራዊ ተሰናድተው ሲቀርቡ ትወናውም የዚያኑ ያህል ቀጥሏል፡፡ ይቀጥል እንጂ!

የወያላው ነገረኝነት እጅጉን ያበሳጫቸው ተሳፋሪዎች አቤቱታቸውን ወደ ሾፌሩ ማቅረብ ጀመሩ። ‹‹ሾፌር? እንዴት እንዴት እንደሚናገር እያየህልን ነው? ገንዘባችን በእጥፍ ከፍለን ተንገላተን ለምንሄደውም ግልምጫ ይጨመርበት?›› አለ አንድ ቀጠን ያለ ተሳፋሪ። ይኼን ጊዜ ሾፌሩ ዞር አለና ወያላውን አተኩሮ አየው። አስተያየቱ የ‹አበጀህ› ይሁን ወይም የ‹ተግሳጽ› አልገባንም፡፡ ‹‹የዛሬ ልጆች የዕውቀታችሁ ጥግ ይኼ ነው?›› አሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ። ‹‹ቆይ ግዴለም!›› አለ ሾፌሩ አሁንም በቁጭት ይሁን በደንታ ቢስነት ስሜት። ጋቢና የተቀመጠ ጎልማሳ ተሳፋሪ፣ ‹‹እስከ መቼ እንዲህ ከሕዝብ እያናከሰህ ትኖራለህ አታባርረውም?›› ሲለው ጆሯችን ሰማ። ሾፌሩ፣ ‹‹ትንሽ  ቀን ነው ግድ የለም። ፓርላማ ሥራቸውን በአግባብ አላከናውን ያሉ ባለሥልጣናትን ማበረር ሲጀምር፣ የአንተና የእኔ ነገር ያከትማል፤›› ሲለው ሁላችንም በመገረም ተያየን። ጉድ እኮ ነው!

‹‹ደግሞ እናንተንና ፓርላማን ምንና ምን ያገናኝችኋል?›› ሲለው ጎልማሳው፣ ‹‹እንዴ? ላይ ያለው ሹም ሥራውን በአግባቡ አላከናወነም ተብሎ የሚሻር ከሆነ፣ ሌላው ምን ቆርጦት ሥራ እያበላሸ ይኖራል? ግን መጀመርያ ከላይ መማር አለብን። የተወራው መተግበር አለበት። ማተኮር ያለብን ቅርንጫፉ ላይ ሳይሆን ግንዱ ላይ ይሁን ተብሎ የለ? ከዚያ እኛ፣ ከእኛ ደግሞ አዲሱ ትውልድ ይኼን አካሄድ እየተከተለ እውነተኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ይሰፍናል፤›› አለ ሾፌሩ እንደ ካድሬ፡፡ አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ! በቃ ሰው የአገሩን ጉዳይ እንዲህ በዓይነ ቁራኛ መከታተል ጀመረ ማለት ነው?›› አለኝ። እንዲህ ሲል የሰማው፣ ‹‹ታዲያስ? ሌላማ ምን አለን ብለህ ነው?›› አለው። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ሁሌም ታክሲ ውስጥ ስሳፈር የተሳፋሪዎች ግልጽነት ይገርመኛል። የእውነት ነው? ወይስ አጋጣሚ ነው?›› ብሎ ይጠይቃል። አንዱ እየሳቀ፣ ‹‹አይ አጋጣሚ ነው…›› ብሎ በምፀት ይመልሳል። ከምፀቱ ጀርባ ከባድ ምሬት ይታያል፡፡ በኑሮአችን ውስጥ መርህ እየተረሳ አጋጣሚ ሲበዛ ምን ይባላል ታዲያ!

‹‹እህ. . . ጥሩ አስታወስከኝ። እኛ እኮ ስለሕዝብ አስተዳደርና አመራር ሁኔታ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያንሳል ነበር ያልነው። አንዳንዶች የአገርን ጉዳይ ትተው ስለጓዳ ሕይወታቸው በየሚዲያው ያጫውቱን ጀመር። ጎበዝ ግራ ገባን እኮ!›› አለ አንድ ጎልማሳ ሒሳብ ከኪሱ ለማውጣት እየታገለ። ‹‹ታዲያ ይኼም እኮ አንድ የዴሞክራሲ ገጽታ ነው። በሠለጠነው አገር አንድ መሪ ሥልጣን ላይ ከመቀመጡ በፊት ግለ ሕይወቱን፣ አመለካከቱንና እምነቱን በተመቸው መንገድ ለሕዝብ ያቀርባል። ችግሩ ምን ላይ ነው ታዲያ?›› ብላ አንዲት ቆንጆ ወጣት ጠየቀችው። ይኼኔ ኋላ ወንበር የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹በእርግጥ እህቴ ያልሽው ትክክል ነው። ነገር ግን የግል ጉዳይን ለማውራት አሁን ሰዓቱ አይደለም። ሩጫ ላይ ነን…›› ካላት በኋላ፣ ‹‹ኧረ የምንታዘበው ብዙ ነው። እንዲያው በየቦታው ብትሄዱ እኮ መካሪ ወይም አማካሪ የሚባሉ ሰዎችን ታገኛላችሁ፡፡ ነገር ግን ወይ ሲመክሩ ወይም ሲያማክሩ አታዩም፣ ሀሜት ብቻ…›› ብሎ ተነፈሰ። የዘንድሮ ሰው ከመምከር ይልቅ መማገዱ ላይ እየበረታ መተማመንን ከባድ አደረገው። እርስ በርሳችን ከባልንጀራችን ጀርባ የምንስለው ካራ አላጣ ብለናል። መቼ ይሆን ምቀኝነትን፣ ክፋትን፣ ተንኮልንና መሰሪነትን የምናስወግዳቸው!

አንድ ሌላ ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹ዋናው መገንዘብ የሚገባን ጉዳይ አገራችን አሁን ካለችበት አጣዳፊ ወረርሽኝ አንፃር፣ ይህን መሰል ወሬ እኛን ሥራ ማስፈታት የለበትም። በዚህ ላይ የህዳሴው ግድብ ደኅንነት ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣ ይመስለኛል። እኛ ከፖለቲከኞቻችን የምንፈልገው ማስተዋል ነው፡፡ እኛም በሥርዓት ለመመራት ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ የአሉባልታ ወሬ እንደ ሰደድ እሳት ሲግለበለብ አጫፋሪ ከመሆን፣ እያንዳንዱን ጉዳይ እየመረመርን መሪዎችን ብናግዝ መልካም ነው፡፡ ግልጽ ሊደረጉልን የሚገቡ ስንት አገራዊ ጉዳዮች እየተረሱ፣ አንገብጋቢ ያልሆኑ ጉዳዮች ላይ ጊዜያችን ባይጠፋ ጥሩ ይመስለኛል፤›› ሲል ከኋላ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሐሳቡ ከተስማሙ ሰዎች ድጋፍ ተቸረው። ‹‹አወይ ዴሞክራሲ ዓይነቷ ብዙ፣ ፈላጊዋ ብዙ፣ ተማሪዋ ብዙ። ምን ያደርጋል? አደናቃፊዎቿም የዚያን ያህል ናቸው…›› የምትለን ቆንጆዋ ናት፡፡ እውነት ነው!

ወያላው እንደለመደው ማጎር እንደማይችል ሲረዳው፣ ‹‹እንሂድ!›› ብሎ ሾፌሩን አዘዘው። ‹‹የበላዩ ታዛዥ የበታቹ አናዛዥ የሆነበት ዘመን…›› ይላል አንዱ። ‹‹እግዚኦ! ይኼንን ወረርሽኝ ፈጣሪ ወደ መጣበት ካልመለሰልን ዘንድሮ እንጃ…›› ብለው ከኋላ ጥግ ላይ የተቀመጡ አዛውንት ተናገሩ። ‹‹እውነት እኮ ነው! ነገር ግን እኛስ የሚጠበቅብንን መቼ አደረግን?›› ብሎ ጎልማሳው ጥያቄ አነሳ። ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹ለኮሮናም የትራፊክ ፖሊስ ሳያስፈልግ አይቀርም…›› ብሎ በስስ ፈገግታ ፊቱን አብርቶ እያንዳንዳችንን ተመለከተን። ‹‹ማለት?›› አለው አጠገቡ ያለው ወጣት። ‹‹እጃችሁን ታጠቡ ሲባል መከፋት፣ ሙቀታችሁ ይለካ ሲባል መነጫነጭ…›› ሲል ነገሩ ገባን። የብዙዎቻችን ሁኔታ ግን፣ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም› መሆኑ አሳዘነን። ‹‹ስንቱ አውቆ ተኝቶ ሰበብ እንደሚያፈላልግ ስናውቅ ሐዘናቸን ብሔራዊ የማይሆንልን ለምን ይሆን?›› ይላሉ አዛውንቱ፡፡ ብሔራዊ ጉዳይ ከተረሳ እኮ ቆየ!

 ታክሲያችን ጉዞዋን ቀጥላ መድረሻችን ላይ ልታወርደን ትንሽ ቀርቷታል። ወያላው ረዥም እጁን እየሰደደ ሒሳቡን ተቀብሎ መልስ ይወረውራል። አዛውንቱ ተሳፋሪ መልስ ሲሰጣቸው ጠበቁና፣ ‹‹ልጄ ከሰው ጋር ተግባባ። ሥራ የሚሠራው በመግባባት ነው። እሺ?›› አሉት። አንገቱን እያቅለሰለሰ ‹‹እሺ…›› አላቸው። ‹‹ተባረክ እሺታ ይልመድብህ። ‹እሺ ይበልጣል ከሺሕ› ብለህ ደግሞ አንድ ጥቅስ እዚያ ጋር ለጥፍ፤›› አሉት እየሳቁ። እኛም ፈገግ አልን። ‹‹አባት እውነትዎን እኮ ነው። ሥራ የሚሠራው በመግባባት ነው። መሆን የማይገባንን ሁሉ እንድንሆን የሚያደርገን እኮ አለመግባባት ነው፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹በሁለት ለሕዝብ አገልግሎት በሚሰጡ የመንግሥት ተቋማት መካከል በተነሳ አለመግባባት ውኃ ተቋረጠ ሲባል እስኪ ምን ይባላል?›› ብሎ አንዱ ሲጠይቅ፣ ‹‹ምንም!›› አለው አንድ ጎልማሳ በተሰላቸ ድምፅ። መሰላቸት በዛ!

አንዳንዱ የአንጀቱን ሲያወራ የአንዳንዱ ፌዙ አያልቅም። ይህን የተናገረውን ቀና ብለን አየነው። ሁኔታችንን ተረድቶ፣ ‹‹እኔም እኮ ከአንጀቴ ነው የመለስኩት። ዛሬ የምናየው ውኃ መቋረጡን ነው። በዚህ ዓይነት ስንት ሥራ መሰላችሁ በቅንጅት ጉድለት የሚስተጓጎለው?›› እያለ አስተያየቱ ከምር እንደሆነ አስረግጦ አብራራ። የአንዳንዱ ሰው አነጋገር ካልተብራራ ትርጉሙ ከባድ ነው። በትርጉም ስህተት ስንት ሰው ጠፍቶ ይሆን? ጉዞአችን ሊገባደድ ጥቂት መንገድ ሲቀረን ሾፌሩ የከፈተው ሬዲዮ በቴሌቪዥን ስለሚተላለፍ አንድ ፕሮግራም ተናገረ፡፡ አዛውንቱ እየተቆጡ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው እየቆራረጡ ነው የሚያቀርቡት? በዚያ ላይ ደግሞ እሑድ ያሉት ረቡዕ፣ ማክሰኞ ያሉት ዓርብ እየቀረበ ግራ ተጋባን እኮ?›› ሲሉ ድንግርግር ያልን በዛን፡፡ አንዱ ተሳፋሪ፣ ‹‹አንተም አልገባህም?›› አለኝ፡፡ እንዳልገባኝ አንገቴን በመወዝወዝ ገለጽኩለት፡፡ ‹‹ሰሞኑን በቲቪ ሲተላለፍ የነበረው የፖለቲከኞች ውይይት እኮ ነው፡፡ …›› ሲለኝ ገባኝ፡፡ ወያላው መድረሻችንን ለማብሰር ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ተንጋግተን መውረድ ጀመርን፡፡ ያው ተሳፋሪ፣ ‹‹ከሁሉ ነገር በላይ ምን እንዳስደሰተኝ ታውቃለህ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ይሆን?›› አልኩት፡፡ ‹‹አንድ ችግራችን የገባው ፖለቲከኛ የማይረቡ ነገሮች ላይ ከመረባረብ ይልቅ፣ ረሃብና ኮሮናን እንታገል ያለው አንጀቴን አራሰው ለማለት ፈልጌ ነው፤›› ሲለኝ፣ ‹‹ገባኝ!›› አልኩት፡፡ እውነትም አንጀት አርስ! ልክ ነው እኮ! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት