Wednesday, September 27, 2023

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥታቸው ላይ ለተሰነዘሩ ክሶችና ወቀሳዎች የሰጡት ምላሽና ማብራሪያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት ምክር ቤቱ የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር በወር አንድ ጊዜ ጠርቶ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረግ ይችላል።

 የቀደመው የምርጫ ዘመንም ሆነ በሥራ ላይ የሚገኘው ምክር ቤት ይኼንን ሥልጣን መሠረት አድርጎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በየወሩ በመጥራት የቁጥጥር ሥራቸውን በልኩ አከናውኗል ማለት ባይቻልም፣ ግፋ ቢል በዓመት ሁለት ጊዜ ይኼንን ሥልጣኑን በመጠቀም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለጥያቄ ሲጠራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በዚሁ መሠረትም ሥራ ላይ የሚገኘው ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ልዩ ስብሰባው ለጥያቄ ጠርቶ ነበር። በዚሁ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቅርበው ምላሽና ማብራሪያ ያገኙ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት መንግሥትን የተመለከቱ ፖለቲካዊ ክሶችና ወቀሳዎች፣ እንዲሁም ሌሎች ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን አስመልክቶ ለቀረቡ ጥያቄዎች የተሰጠው ምላሽና ማብራሪያ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር የሚከስና የሚወቅስ ጥያቄ ከሰነዘሩ የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት መካከል ወ/ሮ ፅውሃብ ታደሰ ያነሱት ተጠቃሽና የጠቅላይ ሚኒስትሩን ትኩረትም የሳበ ይመስላል።

 ‹‹የትግራይ ክልል ሕዝብ በዚህ ሁለት ዓመት የሥልጣን ዘመንዎ የተለያዩ ከባድ ተፅዕኖዎችና በደሎች ወይም አድልኦ እየተፈጸሙበት መሆኑን ያውቃሉ፣ ወይም (እርስዎ ራስዎ) እየመሩት ነው፤›› በማለት የተነሱት ጥያቄ አቅራቢዋ ወ/ሮ ፅውሃብ፣ ተፈጽመዋል ያሏቸውን በደሎችም ለዓብነት በመጥቀስ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ ጠይቀዋል። የትግራይ ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሙ እንዲዳከምና እንዲደኸይ ሌት ተቀን ያለ መሰልቸት ከላይ እስከ ታች ባሉ የመንግሥት መዋቅሮች ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በግልጽ እየተፈጸመበት እንደሆነ የተናገሩት የምክር ቤት አባሏ፣ በትግራይ ክልል ተጀምረው የቆሙ ፕሮጀክቶችን ማጣቀሻ አድርገዋል።

የመቀሌ-ሐራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት፣ በዕኸር አግሮ ኢንደስትሪ፣ የሽረ ኤርፖርት ተርሚናል ግንባታዎች መጓተትን ለአብነት አንስተዋል። ‹‹በተጨማሪም ከአዲስ አበባ-መቀሌ የሚወስደው የፌዴራል መንግሥት መንገድ ለሁለት ዓመታት መዘጋቱ ሳይበቃ ሰዎች በአየር ትራንስፖርት ተጓጉዘው ወደ ትግራይ እንዳይገቡና በትግራይ የኢንቨስትመንት ሥራ እንዳይስፋፋ የተለያዩ አገሮች ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ እንዳይጓዙ እንቅፋት በመፍጠር፣ የትግራይ ሕዝብን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም በማዳከም የማደህየት በደል እየተፈጸመበት ነው፤›› ሲሉ የምክር ቤት አባሏ ጠይቀዋል።

 የትግራይ መንግሥትና ሕዝብ ኮሮና ቫይረስን እየተከላከሉ ስድስተኛውን ምርጫ ለማካሄድ መፈለጋቸውን በመግለጻቸው ዛቻና ማስጠንቀቂያ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰጠቱ፣ የክልሉን ሕዝብ እንዳሳዘነና ይህም ሌላ ቁጣ ሊቀሰቅስ እንደሚችል ገልጸዋል።

ሰሞኑን ደግሞ የፌዴራል መንግሥት የትግራይ ሕዝብና ሕወሓትን ለመለያየት አበክሮ እንደሚንቀሳቀስ በገለጸው መሠረት፣ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ ሐሰተኛ መረጃ በመፈብረክ ሲዘምቱ መንግሥት ዝም የማለቱ ምክንያት እንዲብራራላቸው ጠይቀዋል።

 ወ/ሮ አበራሽ አድማሱ የተባሉ ሌላ የምክር ቤቱ አባልም በትግራይ ሕዝብ ላይ፣ የጥላቻና የማሸማቀቅ የሚዲያ ዘመቻዎችን መንግሥት እያስተዋለ ለምን አደብ ለማስያዝ እንዳልሞከረ ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ለዚህ ጥያቄ ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በምላሻቸውም የትግራይ ሕዝብ ጀግና፣ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራ፣ ጥሮ ግሮ የሚበላ ሕዝብ እንደሆነ ተናግረዋል። ‹‹ይኼ የሚካድ ሀቅ አይደለም፣ ችግር የሆነው የትግራይ ሕዝብንና ፓርቲን እየቀላቀሉ መመልከቱ ነው፤›› ብለዋል።

የትግራይ ሕዝብ አገሩን የሚወድ፣ ለአገሩ አንድነት የተዋደቀና የሚያኮራ ሕዝብ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይኼንን ትልቅ ሕዝብ አንድ ፓርቲ ውስጥ ብቻ አድርጎ ማሰብ ትክክል አለመሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ውስጥ እንደ አረና፣ ባይቶናና መሰል ሌሎች ፓርቲዎች እያሉ፣ በብልፅግና ውስጥም ሆነው የሚታገሉ የትግራይ ተወላጆች እያሉ፣ የትግራይ ሕዝብን በአንድ የሕወሓት የፖለቲካ አመለካከት ጨፍልቆ ማየት ስህተት ነው ብለዋል። ‹‹የትግራይ ክልል መንግሥትን በሙሉ ሌባ፣ አጥፊ፣ የማይሠራ አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ኢትዮጵያን የሚወዱ ክልሉን ለመለወጥ የሚጥሩ ብዙ ሰዎች አሉ። ሕወሓትን ከሊቀመንበሩ ጀምሮ ሁሉም ጥፋተኛ ናቸው የሚል እምነት የለንም፡፡ በፓርቲው ውስጥ ለዚህ አገርና ሕዝብ መስዋዕትነት የከፈሉ ባለውለታዎች አሉ፡፡ ይኼ ማለት ጥፋተኛ፣ የሚሳደቡ፣ ወንጀለኛ በመሀላቸው የሉም ማለት አይደለም፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹አንድ ሰው ሲወቀስ፣ ሁለት ሰው ሲወቀስ የትግራይ ሕዝብ የተወቀሰ አድርገን አንውሰድ፡፡ ጥያቄዎች ሲቀርቡም ፓርቲንና ሕዝብን በለየ መንገድ መሆን አለበት፤›› ብለዋል።

 የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ነው ለተባለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በደሎች በሰጡት ምላሽም፣ እሳቸው ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል ውስጥ እያከናወናቸው የሚገኙ ፕሮጀክቶችንና ለክልሉ መንግሥት የተሰጡ ድጋፎችን በዝርዝር አቅርበዋል።

እሳቸው ወደ ሥልጣን እስኪመጡ ድረስ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠው የበጀት ድጎማ ማደግ የቻለው እስከ ሰባት ቢሊዮን ብር ድረስ ብቻ መሆኑን የጠቆሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለቀጣዩ በጀት ዓመት ለትግራይ ክልል የተያዘው የድጎማ በጀት 10.4 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል። ይኖም ከለውጡ በኋላ ለትግራይ ክልል የሚመደበው በጀት በ42 በመቶ ማደጉን እንደሚያሳይ አስታውቀዋል።

 ይህ ዕድገት የፌዴራል መንግሥት በክልሉ ለሚያካሄዳቸው ፕሮጀክቶች የሚመደበውን ገንዘብ እንደማይጨምር በመጠቆም፣ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ እያከናወናቸው የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በዝርዝር አቅርበዋል። የፌዴራል መንግሥት የመቀሌ ከተማ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክትን ለማስጀመር 1.3 ቢሊዮን ብር ከፍሎ ፕሮጀክቱን እንዳስጀመረም የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህ ተግባር የፌዴራል መንግሥት ሊመሠገን ቢገባውም መረጃው ግን ለክልሉ ሕዝብ በግልጽ እንደማይነገረው አስታውቀዋል።

የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ግንባታ በኪሎ ሜትር 4.8 ሚሊዮን ዶላር እንደፈጀ፣ የአዋሽ ወልዲያ መስመር ደግሞ በኪሎ ሜትር 4.2 ሚለዮን ዶላር እንደሆነ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ የመቀሌ-ሐራ ገበያ የባቡር መስመር ግን በኪሎ ሜትር 7.3 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚወጣበት ውድ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህ ፕሮጀክት የቻይና መንግሥት ብድር ለመስጠት ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ በፕሮጀክቱ ወጪ መናር የተነሳ ቃሉን እንዳጠፈና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ እሳቸው ይኼንን ፕሮጀክት ለማስቀጠል ብድር የማፈላለግ ጥረት ቢያደርጉም አለመሳካቱን ተናግረዋል።

 ‹‹የመቀሌ የባቡር ፕሮጀክት ጥናቱ በኪሎ ሜትር የቀረበው ዋጋ በጣም ውድ በመሆኑ ማንም ባንክና አገር ሊያበድረን አልፈለገም፡፡ ነገር ግን ፕሮጀክቱ መቅረት የለበትም ብለን ስለምናምን፣ መንግሥት በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርጎ ሥራውን አስቀጥሏል፤›› ብለዋል።

ለትግራይ ክልል ኮሮናን የመከላከል ሥራ 46 ሚሊዮን ብር በገንዘብና በቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የደቡብና የትግራይ የክልሎች እስከ ዘንድሮ ድረስ ያለባቸውን የማዳበሪያ ዕዳ ለፌዴራል መንግሥት ባለመክፈላቸው ምክንያት በአሠራሩ መሠረት ዘንድሮ የማዳበሪያ አቅርቦት ማግኘት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ዘንድሮ የማዳበሪያ ገንዘብ የለኝም በማለቱ ሥራው መቆም ስለሌለበትና የክልሉ አርሶ አደር እንዳይጎዳ፣ የፌዴራል መንግሥት በልዩ ሁኔታ ለትግራይ ክልል 445 ሚሊዮን ብር ተበድሮ ድጋፍ ማድረጉን አስረድተዋል።

 ‹‹የትግራይ ሕዝብን የመጉዳት ዜሮ በመቶ ፍላጎት የለንም›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ ‹‹የምንወደውን የትግራይ ሕዝብ አትወዱትም፣ ጎዳችሁት የሚለን ካለ አቧራ ነው ያልፋል፣ አሻራው ይገለጣል፣ ያኔ ሕዝቡ እውነታውን ይረዳል፤›› ብለዋል።

የትግራይ ክልል ምርጫ አካሂዳለሁ ማለቱ በሐሳብ ደረጃ ሊነሳ የሚችል እንደሆነ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ፣ በሐሳብ ደረጃ መቅረብ ቢችልም ኢሕገ መንግሥታዊ በመሆኑ ተግባራዊ እንደማይሆን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ላይ የሚዲያ ዘመቻ ተከፍቷል የሚለውን ወቀሳ በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፣ ‹‹ትግራይ አካባቢ ያሉ ሚዲያዎች አስበውበትና ተዘጋጅተው እኔን ሲሳደቡ ይውላሉ፣ እኔ መልስ አልሰጥም፣ ምክንያቱም ስድብ ረብ የለሽ ነው፣ የሚጠቅመን በእጃችን አፈር መንካትና አርሶ አደሩን ማገዝ ነው፤›› ብለዋል።

ነገር ግን ጠያቂው እንዳነሱት ይህ አካሄድ ትክክል ነው ብለው እንደማያምኑ የጠቆሙ ሲሆን፣ ሚዲያዎች ለውጡን የተረዱበት መንገድ እየተስተካከለ ሰከን ማለት ሲጀምሩ እንደሚስተካከል ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት የቀረበላቸው ሌላው ወቀሳ አዘል ጥያቄ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንና ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ውዝግብ የተመለከተ ነበር።

የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ጥያቄ ካቀረቡት የምክር ቤቱ አባላት መካከል መሠረት አባተ አንዱ ሲሆኑ፣ ባቀረቡት ጥያቄም ከእውነታው ውጪ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ግለሰቦች አዲሱ አመራር የህዳሴ ግድቡን ለውጭ ኃይሎች እንደ መደራደሪያ አቅርቦታል የሚል ክስ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

ግድቡን አስመልክቶ አሜሪካ ወደ ተካሄደው ድርድር የተገባው በቸልተኝነት እንደሆነና የህዳሴ ግድቡን በገንዘብ ለመቀየር መንግሥት ሆን ብሎ የሸረበው ሴራ መሆኑን፣ አሁንም ከድርድር ተወጣ የተባለውም የሕዝቡን አዝማሚያ ለማየት እንደሆነ በተለያየ መንገድ እየተገለጸ በመሆኑ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ የመንግሥትን ግልጽ አቋም እንዲያስረዱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠይቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከመጀመራቸው አስቀድሞ፣ ‹‹ለምክር ቤቱ ክብር ሲባል በአሉባልታ ላይ ተመሥርተን ባንወያይ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የጥያቄ አቅራቢው ፍላጎት ግልጽነትን ለመፍጠር በመሆኑ ስለጉዳዩ በዝርዝር አብራራለሁ፤›› በማለት ዝርዝር ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተውበታል።

የህዳሴው ግድብ በ2003 ዓ.ም. ተጀምሮ የመጀመርያው የውኃ ሙሌት በ2007 ዓ.ም. እንዲከናወን፣ በ2009 ዓ.ም. ደግሞ ግንባታው ሙሉ በሙሉ እንዲጠናቀቅ ታቅዶ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሁንና የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ ኮንትራቱ ተፋልሶ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) እንዲገባበት መደረጉ ትልቅ ስህተት እንደሆነ መገምገሙን ገልጸዋል።

እነዚህ ኃይሎች የግድቡ ሥራ ላይ ተኝተውና አበላሽተውት ሲያበቁ፣ ዛሬ ለማረም የሚሠራውን ሥራ ግድቡ ለድርድርና ለሽያጭ ቀርቧል ማለታቸውን ነቅፈዋል። የህዳሴ ግድቡ ይጠናቀቃል ከተባለበት ጊዜ በላይ ለስድስት ዓመታት መዘግየቱን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በእነዚህ ዓመታት በየዓመቱ አገሪቱ አንድ ቢሊዮን ዶላር በጥቅሉ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ማጣቷን ገልጸዋል።

ይህም ፕሮጀክቱ በመቆየቱ ምክንያት በየጊዜው የሚያስወጣውን ተጨማሪ ወጪ እንደማያካትት አስታውቀዋል። የለውጡ አመራር ከመጣ ወዲህ ግንባታው የነበሩበትን ችግሮች በመለየትና የዕርምት ዕርምጃዎችን በመውሰድ፣ ግንባታው በጥራትና በፍጥነት እየተካሄደ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

የለውጡ አመራር እስኪመጣ ድረስ በነበሩት ዓመታት ውኃ የሚያዝበት የግድቡ መካከለኛ ክፍል የተገነባው ከባህር ጠለል በላይ 25 ሜትር ከፍታ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል ግን ዋናው የግድቡ መካከለኛ ክፍል የ35 ሜትር ከፍታ ግንባታ መከናወኑንና ይህም የመካከለኛው ክፍል ውኃ ለመያዝ ወደሚያስችለው ደረጃ እንዳሸጋገረው ተናግረዋል።

ባለፈው አንድ ዓመት ተኩል በተከናወኑ ተግባሮች ግድቡ በዚህ ዓመት በሰኔ ወር መጨረሻ 4.9 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ መያዝ እንደሚጀምርም ገልጸዋል።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተጨማሪ 35 ሜትር ከፍታ በመጨመር 595 ሜትር ርዝመት ላይ እንደሚደርስና በቀጣዩ ዓመት የክረምት ወቅት 18.4 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ፣ ወይም አሁን ከሚይዘው ከሦስት እጥፍ በላይ ውኃ እንደሚሞላ አስታውቀዋል።

‹‹የህዳሴ ግድቡ አፉን እንደከፈተ ጅብ ነው በየጊዜው ዩሮ ካልጎረሰ አይረካም፤›› ያሉት ተጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ግድቡ ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ ፕሮጀክት መሆኑንም አመልክተዋል።

የህዳሴ ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ እንደ ዘንድሮ ያለ ዲፕሎማሲያዊ ፈተና ገጥሞ አያውቅም ብለው፣ ይህ የሆነበት ምክንያትም ፕሮጀክቱ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ከመድረሱ የመነጨ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የግድቡን ግንባታ በተመለከተ የተለያዩ መሠረተ ቢስ ወሬዎች እንደሚናፈሱ ገልጸው፣ ግንባታው ከሚናፈሰው መሠረተ ቢስ ወሬ በተቃራኒ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

‹‹ግድቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የሚደራደርበት አድርጎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ አሁንም የሚደራደሩት በፊት የነበሩት ሰዎች ናቸው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ያለ ምንም ዓይነት ክፍያ አገራቸውን እያገለገሉ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

በመሆኑም ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የሚነዛው አሉባልታ የእነዚህን አገር ወዳድ ባለሙያዎች ስሜትና ሞራል እንዳይጎዳ መጠንቀቅ የተሻለ እንደሆነ አሳስበው፣ መንግሥት ለዚህ ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን በታሪክ የማይዘነጋ ምሥጋና እንደሚቸርም ገልጸዋል።

ከሱዳን ጋር የተነሳውን የድንበር ውዝግብ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የሱዳን ሕዝብ ወንድም ሕዝብና ባለውለታም አገር ነው፡፡ ከሱዳን ጋር በፍፁም ውጊያ ውስጥ አንገባም፡፡ ይህ ማለት ግን ውጊያ ውስጥ እንድንገባ የሚፈልጉ አካላት የሉም ማለት አይደለም፤›› ብለዋል።

አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን በኢትዮጵያ ተፈጽሟል ባለው የሰብዓዊ ጥሰት ሪፖርት ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የኢትዮጵያን ሕዝብ በተመለከተ ለዚያውም ሕዝባችሁን አትግደሉ የሚል ሪፖርት አውጥቶ አንሰማም አንልም፤›› ብለዋል።

መረጃውን እንደሚያጣሩ ነገር ግን ከዚያ በመለስ ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ቀለል አድርገው እንደሚመለከቷቸው ተናግረዋል። ‹‹ብዙም የሚያስጨንቀን አይደለም፣ የእኛ ጉዳይ ሕዝባችን ነው፣ ሕዝብ ሐሳባችንንም የምናደርገውንም ያውቃል፣ ስህተት ካለብንም እንታረማለን፤›› ብለዋል።

ከደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የታገቱ ተማሪዎች እስካሁን ያሉበት አለመታወቁና መንግሥትም የእነዚህን ተማሪዎች ጉዳይ በተመለከተ ቸል ማለቱ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ፣ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ መንግሥት ያላደረገው ጥረት እንደሌለ ተናግረዋል።

በታገቱ ሴት ተማሪዎች ላይ ተሳትፎ የነበራቸውን በርካታ ግለሰቦች መንግሥት በቁጥጥር ሥር ቢያውልም፣ ተማሪዎቹን በሕይወትም ሆነ ሞተው ለማግኘት አለመቻሉን ገልጸዋል። የተማሪዎቹን ስልክ ሲግናል መከተል ሲጀመር አንዴ አማራ ክልል፣ ወደዚያ ክልል ሲኬድ ሲግናሉ ወደ ጋምቤላ፣ ከዚያም ወደ ኦሮሚያ እንደሚንቀሳቀስ ገልጸዋል።

‹‹ወይ ከተደበቁበት ይወጣሉ ወይም የበላቸው ጅብ ይጮሀል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጉዳዩ ውስብስብና መንግሥትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የታለመ ቢሆንም፣ መንግሥት ክትትሉን እንዳላቆመና የሚደርስበትን ሁሉ ይፋ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -