Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኮሮናን አታሎ ያለፈው የወጪ ንግድ የ2.4 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስመዘግቧል 

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ገቢ ከዓመት ዓመት በማሽቆለቆል ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡ የወጪ ንግድ ገቢ ላይ ዕድገት ይታያል፣ ይሻሻላል በሚባልበት ወቅት በየጊዜው ሲቀንስ የመታየቱን ዜና መስማት ከጀመርን ከስድስት ዓመታት በላይ አልፈዋል፡፡

ከወራት ወዲህም የኮሮና ወረርሽኝ፣ ለወትሮውም ታች ታች የሚለውን የወጪ ንግድ ይበልጥ እንደሚደቁሰው ሥጋት አሳድሮ ነበር፡፡ በርካታ የሥጋት ትንታኔዎችም ጎልተው ሲስተጋቡ ቆይተዋል፡፡ ዘርፉ በኮሮና እየደረሰ ካለው ዓለም አቀፍ ጉዳት ሳቢያ ከሥጋት ነፃ አይደለም፡፡ በርካታ አገሮች ድንበሮቻቸውን በመዝጋት፣ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የወሰዱት ጥብቅ ዕርምጃ የዓለምን የንግድና የሸቀጥ እንቅስቃሴ ጫና ውስጥ ከቶታል፡፡ በርካታ አገሮች ግብይት አቁመዋል፡፡ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ ሰፊ ክፍተት ተፈጥሯል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ ከታየው ቀውስ ወዲህ፣ ኮሮና ባስከተለው ተፅዕኖ ዓለም እየታመሰችበት ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ የዓለም የሸቀጦች ንግድ ከ13 እስከ 32 በመቶ በሚገመት መጠን እንደሚቀንስ የዓለም ንግድ ድርጅት በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት አስነብቧል፡፡ ይህም ይበልጥ አስከፊ ጊዜ እየመጣ እንዳለ አመላክቷል፡፡ በሽታው ቢጠፋ እንኳ፣ ጥሎት የሚያልፈው ዳፋ ዓለም ወደ ነበረችበት ለመመለስ ረዥም ዓመታት እንዲወስድባት ያስገድዳታል መባሉ፣ የዓለም የኢኮኖሚ ዕድገት ክፉኛ ማዘቅዘቁ፣ የኢትዮጵያም ዓመታዊ ዕድገት ከተተነበየው የሦስት በመቶ ቅናሽ እንዲያሳይ ማስገደዱ የኮሮና ትኩሳት ከፍተኛ እንደሚሆን፣ ከበሽታነት ወይም ከጤና ቀውስነት አልፎ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ ወደ ማስከተል መዛመቱ ዓለም ከምትሸከመው በላይ ሆኖባት ይገኛል፡፡

ይህ ሁሉ እየሆነም፣ ከጉዳቱና ከተፅዕኖው ባሻገር ጥቂት አዎንታዊ ውጤት እያስገኘ ስለመሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስታውቀዋል፡፡ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሆነ፣ በአሥር ወራት ውስጥ ከቡና ወጪ ንግድ ከ660 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተመዝግቧል፡፡ በማዕድን፣ በሥጋ  እንዲሁም በአበባ ወጪ ንግድ ላይ ሳይቀር ውጤታማ እንቅስቃሴ መታየቱን አመላክተዋል፡፡ የሥጋ ወጪ ንግድ ትልቅ እመርታ ማሳየቱ ብቻም ሳይሆን፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከሰሞኑ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይፋ ያደረገው መረጃም አዎንታዊ ገጽታዎችን አመላክቷል፡፡ ለዓመታት በቁልቁለት ሲጓዝ የከረመው የወጪ ንግድ ዘርፍ፣ ባለፉት አሥር ወራት ያሳየው አፈጻጸም፣ ከዚህ ቀደም ከተመዘገበው ይልቅ የተሻለ ውጤት እንደተገኘበት አመላክቷል፡፡

ከአሥር ወራቱ የወጪ ንግድ አፈጻጸም መረዳት እንደሚቻለው፣ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ በአፈጻጸም የተመዘገበው ግን 2.4 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ውጤት በዕቅድ ከተያዘው አንፃር ግቡን ባይመታም በአሥር ወራት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ባለፈው ዓመት ከተገኘው ግን ብልጫ አሳይቷል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወንድሙ ፍላቴ እንደገለጹት፣ ይህ አፈጻጸም በ2011 ዓ.ም. አሥር ወራት ውስጥ ከተገኘው 2.15 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነጻጸር፣ የ12.6 በመቶ ወይም የ271 ሚሊዮን ዶላር ጭማሪ አለው፡፡

በአሥሩ ወራት ውስጥ ከተያዘላቸው ዕቅድ በላይ አፈጻጸም ያስመዘገቡት አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ወደ ውጭ የተላከ የጫት ምርት ሲሆኑ፣ በዕቅድ ያስገኛሉ ተብሎ ከሚጠበቀው የገቢ መጠን ከ50 እስከ 99 በመቶ ብልጫ ያስመዘገቡ ምርቶች ናቸው፡፡ ቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ጥራጥሬ እህሎች፣ ሥጋ፣ ቅመማ ቅመሞችና ወርቅ የተሻለ አፈጻጸም እንዳላቸው ተገልጿል፡፡

የዘንድሮው የወጪ ንግድ አፈጻጸም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀሰቀሰው የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያሳደረው ጫና በኢትዮጵያም በሰፊው ሊታይ እንደሚችል ቢታሰብም፣ በወጪ ንግድ ረገድ ኢትዮጵያ ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ገቢ ማግኘት የቻለችበት ሆኗል፡፡

ሰኞ፣ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ኢትዮጵያ ከ2007 ዓ.ም. ወዲህ ከወጪ ንግድ ከፍተኛ የሚባል ውጤት መመዝገቡንና ይህም በተለያዩ ጥረቶች የተገኙ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ በጠቅላላው የዘንድሮው አፈጻጸም መልካም ቢሆንም፣ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር በውጭ ምንዛሪ ገቢ ላይ ከ50 በመቶ ያላነሰ ዝቅተኛ ገቢ ያስመዘገቡ ምርቶች እንዳለ ያሳያል፡፡ ዝቅተኛ የወጪ ንግድ አፈፃፀም የታየባቸው ምርቶች ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም የቁም እንስሳት ናቸው፡፡

በጠቅላላው ሲታይ የወጪ ንግድ ምርቶች ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አንፃር፣ በገቢ በኩል በተለይ የቡና 16 በመቶ፣ የአበባ 84 በመቶ፣ የቅባት እህሎች አሥር በመቶ፣ የጫት ሰባት በመቶ፣ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 22 በመቶ፣ የወርቅ 144 በመቶ፣ የቁም እንስሳት 22 በመቶ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች 46 በመቶ ጭማሪ ማሳየታቸውን ሚኒስትሩ አስታውቋል፡፡

‹‹ኮሮና ኤክስፖርታችን እንዲሻሻል ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደ ምሳሌ ከጠቀሱት ውስጥ የቡና የወጪ ንግድ ዋናው ነው፡፡

ባለፉት አሥር ወራት ከቡና 667 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በመገኘቱ፣ ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት አኳያ የ16 በመቶ ዕድገት አለው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የቡና ፍላጎት መጨመርና የዓለም የቡና ዋጋ መሻሻል ነው፡፡ ይህ ይባል እንጂ ከቅርብ ቀናት ወዲህ የቡና ዋጋ ማሽቆልቆል እንደጀመረ መረጃዎች እያመላከቱ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ‹‹ቡና የሚያመርቱ አገሮች በሽታው ምክንያት የገበያ ትስስራቸው ስለቀነሰና እኛም ባለን አቅም ሁሉ ለማቅረብ ጥረት በማድረጋችን ከፍተኛ ዕድገት ታይቶበታል፤›› በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በኮሮና ምክንያት ሌላው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የአበባ የወጪ ንግድ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ በአሥር ወራት ውስጥ የ440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ከአበባ አግኝታለች ብለዋል፡፡ ‹‹ማመን በሚያስቸግር ደረጃ 84 በመቶ ዕድገት አለው፤›› በማለት የአበባ የወጪ ንግድ ትልቅ ለውጥ እንዳሳየ አመላክተዋል፡፡

ወደፊትም የአገሪቱ የወጪ ንግድ የተሻለ እንደሚሆንም የገለጹት ዓብይ (ዶ/ር)፣ አሁን ያለው የገበያ ትስስር ለነገው የወጪ ንግድ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ የዘንድሮው የወጪ ንግድ እንደ ወርቅ ያሉ ምርቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ያስገኙትን ውጤት በእማኝነት በማውሳት አስገራሚ እንደሚያሰኘው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች