በጌታቸው ይልማ (ኢንጂነር)
እ.ኤ.አ በ1948 ማርና ወተት ትሠጣለች የተባለላት የእሥራኤል ምድር ስትመሠረት በረሃማና ለኑሮ የማይመች የተፈጥሮ አቀማመጥ ነበራት። ይህንን ሁኔታ ለመቀየር ትልቅ ትግል እንደሚያስፈልግ የተረዱት የእሥራኤል ሕዝቦች የተቀናጀ የደን ልማትን በጥናትና ምርምር እንደዚሁም ለሥራው የሚያስፈልገውን ሀብት ከዜጎቻቸው በማሰባሰብ ማከናወን ግዴታ መሆኑን ተገነዘቡ። በተለይም በጉልህ የሚጠቀሰው የእሥራኤልን 60 ከመቶ የቆዳ ሽፋን የሚይዘውን የኔጌቭ በረሃን በደን ለማልማት ከ1964 ጀምሮ በአይሁድ ብሔራዊ ፈንድ አማካይነት የተሠራው ሥራ ያደጉትና በማደግ ላይ ያሉ አገሮች እንደልምድ የሚቀምሩት ድንቅ ሥራ ሆነ። በዚህ የእሥራኤል በረሃ ላይ የተሠራው የደን ልማት በጥናትና ምርምር የአፈር ዓይነቶችን፣ የውኃ አጠቃቀምን እንደዚሁም ለቦታው ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ዓይነቶችን በጥንቃቄ በመለየት የተሠራ እልህ አስጨራሽ ሥራ ነበር። የዚህ የደን ልማት ውጤት ለኑሮ የተመቸን የተፈጥሮ ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ እሥራኤልን የዓለማችን ቀዳሚ የፍራፍሬና አትክልት ላኪ አገር ለመሆን አስቻላት። ለዚህም ነው የቀድሞው የእሥራኤል ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት በውቢቷ እሥራኤል የሽልማት ሥነ ሥርዓት ወቅት፣ የአይሁድ ብሔራዊ ፈንድ በደን ልማት ከ1964 ጀምሮ ላስመዘገበው ትልቅ ሥራ ሽልማት በሠጡበት ወቅት እኛ እሥራኤላውያን ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ አንድን ጠብታ ውኃ ወደ አምስት ጠብታነት በማሣደግ የመጠቀም ችሎታ ያለን ሕዝቦች በመሆን ለዓለም ምሳሌ፣ እንደዚሁም ለዲፕሎማሲያችን አንድ ጉልበት የሆነን በማለት የተናገሩት። በተጠናና በተቀናጀ መልኩ ዛፎችን መትከል ተአምርን የሚፈጥር የተፈጥሮ ገጸ በረከት መሆኑን የምንረዳው የአሁኗን ኃያሏን እሥራኤል ስትመሠረት ከነበራት ገጽታ ጋር በማነፃፀር የማይቻል ይመስል የነበረውን በመቻላቸው ነው።
ሌላዋ በደን ልማት ሥራዋ በዓለም ላይ በኢንዱስትሪ ልማት ሒደቷ በአካባቢ ላይ ትልቅ ጉዳት ካደረሱት አገሮች ዋነኛዋ ብትሆንም፣ በአረንጓዴ ልማት ፖሊሲዋ በአሁኑ ጊዜ የመሪነት ሚና የያዘችው የዓለም አንድ አምስተኛ ሕዝብ ያላት ኃያሏ ቻይና ናት። ቻይና እ.ኤ.አ በ1958 በማኦ ዚዶንግ የተሳሳተ የልማት ፖሊሲ ምክንያት ደኖችን በመጨፍጨፍ ለኢንዱስትሪ ግብአትነት፣ ለከተማና ኢንዱስትሪ ማስፋፊያነት እንዲውል ከሊቀመንበሩ የታዘዘ ስለነበር፣ ካድሬዎች በደኖቹ ላይ በመዝመታቸው የተቃወሙ ለእስርና ለሞት ተጋዙ። ከዚህም የተነሳ በከፍተኛ የበረሃማነት መስፋፋትና ለተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋ ቻይና ተጋላጭ ሆነች። በተለይም የጎቢ እና ኩቡቺ በረሃዎች በፍጥነት በመስፋፋት የአገሪቱ ብሔራዊ ሥጋት መሆናቸውን መለየት ቻለች። በዋነኛነት ከጎቤ በረሀ የሚነሳው አቧራን የያዘ የንፋስ ማዕበል የአካባቢውን ነዋሪዎች ከማፈናቀል አልፎ እስከ መዲናዋ ቤጂንግ ድረስ በመዝለቅ ጭጋግ እያለበሰ የአካባቢና የጤና ሥጋትን ደቀነ። ከቻይና ድንበር በማለፍም ጎረቤቶቿን ደቡብ ኮርያን፣ ጃፓንን፣ ሰሜን ኮርያን፣ ሞንጎሊያን አልፎም የአሜሪካዋን ኮሎራዶ ግዛትን አደገኛ በሆነ የአቧራ ማዕበል እስከ መምታት ደርሶ ነበር።
ይሁንና የዘመናዊትና ኃያሏ ቻይና አርክቴክት የነበሩት ዲንግዛኦ ፒንግ (የማኦዚ ዶንግ የተሳሳተ የልማት ፖሊሲን ከተቃወሙትና ለግዞት ከተዳረጉት አንዱ ነበሩ) እ.ኤ.አ በ1978 ወደ መሪነት ሲመጡ ቀድሞ የተሠራውን ስህተት ለማረም የተቀናጀና የተጠና የአካባቢ ጥበቃ አንዱ የፖሊሳቸው ምሰሶ በማድረግ አሁን ቻይና ለተቀዳጀችው የአረንጓዴ ልማት ጉዞ መሠረት ጣሉ። በተለይም በጎቢና ኩቡቺ በረሃዎች የማዕከላዊና የክልል መንግሥታት በመቀናጀት እልህ አስጨራሽ ሥራ መሥራት ጀመሩ። ታላቁ የአረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት ከ1978 እስከ 2050 ድረስ የተዘረጋ የደን ልማት ስትራቴጂ ተነድፎ እስካሁን በመሠራት ላይ ይገኛል። በዚህም ሥራ 66 ቢሊዮን ችግኞችን መትከል የቻሉ ሲሆን፣ በእስካሁኑ ጥረት 23 በመቶ የቻይናን የቆዳ ስፋት በደን ለመሸፈን ያስቻለና የበረሃማነትን መስፋፋት በ1,980 ኪሎ ሜትር ስኩዌር በየዓመቱ ለመቀነስ ያስቻለ ትልቅ ሥራ በማከናወን ላይ ይገኛሉ። የናሳ የሳተላይት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ ከ2000 እስከ 2017 ብቻ በተሠሩ የደን ልማት ሥራዎች በ5 ከመቶ የዓለም የደን ሽፋን ማደጉን ጠቅሶ ለዚህም ዕድገት አንድ አራተኛውን ቻይና ማበርከቷን መስክሯል።
ባለፈው ዓመት በአገራችን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሪነት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ፕሮጀክት፣ በተለይ ቻይና በ1978 ከነበረችበት የሽግግር ወቅት ጋር በብዙ መልኩ የሚመሳሰል ነው። የለውጥ አቀንቃኝና የምጡቅ አዕምሮ ባለቤት እንደነበሩ የሚነገርላቸው የኮሚኒስት ፓርቲን ትልቅ የሥልጣን እርከን ላይ ደርሰው የነበሩ ቢሆንም በማኦ ዚዶንግና ግብራበሮቻቸው ተገፍተው የነበሩት ዲንግዛ ኦፒንግ ከብዙ ውጣውረድ በኋላ መሪ በመሆናቸው እንደዚሁም ከግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እኩል የአካባቢ ጥበቃ የቻይና የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት እንዲሆን ፖሊሲ ቀርፀው መንቀሳቀሳቸው ከእኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ያመሳስላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በዚህ የለውጥ ወቅት አገሪቱን አረንጓዴ ማልበስ ከሌሎች የልማት መሠረቶች እኩል መሠራት እንዳለበት አምነው በልበ ሙሉነት መንቀሳቀሳቸው ከቻይናው መሪ ጋር የሚያመሳስላቸው ብቻ ሳይሆን ወደ ፊት በትውልድ የሚያስመሰግን ትልቅ ተግባር በመሆኑ ሁሉም ከጎናቸው ሊሰለፍ ይገባል።
ነገር ግን ይህ የአረንጓዴ አሻራ፣ ዘመቻ ከመሆን እንዴት ወደ ውጤታማነትና ዘመን ተሻጋሪነት መቀየር ይቻላል የሚለው ሁሉም ሐሳብ ሊሰጥበት የሚገባ የአገር ጉዳይ ነው። እንደተነገረው ከሆነ የዓምናውን አራት ቢሊዮን ጨምሮ ዘንድሮ ሊተከል ከታቀደው አምስት ቢሊዮን ችግኞች ጋር በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢልዮን ችግኞችን ለመትከል እንደታቀደ ታውቋል። ይህ በአራት ዓመት የተጠቀሠው ቁጥር ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የደን ሽፋን ጋር ምን ግንኙነት እንዳለው፣ አሁን በተያዘው መልኩ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለውን መመርመር ይገባል። በተጨማሪም ዓምና ከተተከሉት ችግኞች 84 በመቶ መፅደቃቸው መነገሩ ደስ የሚል ዜና ቢሆንም በተግባር ግን ምን ያህል እውነትነት ሊኖረው ይችላል ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። ከላይ ተሞክሮዎቻቸውን የተመለከትናቸው የቻይናንና የእሥራኤልን ታሪክ ስንመለከት አሁን የደረሱበት ደረጃ ለመድረስ ከ40 እስከ 50 ዓመታት አስፈልጓቸዋል። ከአርባ ዓመታት በላይ በቻይና በተደረገው የደን ልማት ወቅት ያጋጠሙት ተግዳሮቶች ማለትም የተተከሉ ችግኞች የመፅደቅ ዕድል በአማካይ ከ15 ከመቶ ያልበለጠ መሆን፣ የክልል መሪዎችና ካድሬዎች የበላይ አለቆቻቸውን ለማስደሰት ብሎም በሥልጣን ለማደግ የተሳሳተ መረጃ ወደ ማዕከል ማስተላለፍና ሙስና፣ ለአካባቢው ተስማሚ ያልሆነ የችግኝ ዓይነቶችን መትከል እንዲሁም በተሳሳተ የፕሮጀክት አስተዳደር ምክንያት ትልቅ የሀብት ብክነት በቻይና እንደደረሰ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ባለፈው ዓመት በተጀመረው የችግኝ ተከላ በግልም ሆነ በቡድን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በሚባል ደረጃ እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል፡፡ ይሁንና ከተተከሉት አራት ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ ምን ያህሉ ፀድቀው የተፈለገው ዓላማ ተሳካ የሚለው ብዙዎችን ሲያነጋግር ቆይቷል፡፡ መንግሥት በግብርና ሚኒስቴር በኩል 84 በመቶ መፅደቃቸውን ቢገልጽም2 አንዳንዶች በዘመቻ ከተተከለው አራት ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ እስከ 50 በመቶ ከፀደቀ በጣም ውጤታማ ነው ይላሉ፡፡ ይህንን በገንዘብ ስናሰላው እያንዳንዱን ችግኝ በአማካይ 20 ብር ብንገምተው ወደ 40 ቢሊዮን ብር ይባክናል ማለት ነው፡፡ ይህንን የሚባክን ገንዘብ ተጠቅሞ ከደን ልማትና እንክብካቤ ጋር የተያያዘ ሥራ ለበርካታ ወጣቶች መፍጠር ይቻላል፡፡ በመሆኑም የአረንጓዴ ልማት የባህል አብዮት ተቋማዊ መዋቅር በማበጀት ተጠያቂነትንና ማበረታቻዎችን የሚሰጥ ሥርዓት በመዘርጋት ውጤታማ ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች መንግሥት የሚያወጣውን የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲና ስትራቴጂን ተከትለው የአካባቢያቸውን ሁኔታ ለመቀየር የራሳቸውን ስትራቴጂ ቀርፀው የሚሠሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንጂ ከላይ ወደታች በሚወርድ የፓርቲና የካድሬ ዘመቻ የአረንጓዴ አሻራን ለማስፈጸም መሞከር ከራሳችን ያለፈ ታሪክ እንዲሁም ከቻይና ያለመማር ነው የሚሆነው።
ለዚህም እንዲረዳ በመጀመሪያ ደረጃ በፌዴራል ደረጃ አገሪቱ ካላት የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛትና አሰፋፈር በመነሳት ምን ያህል የደን ሽፋን እንደሚያስፈልጋት ባለሙያዎችን ያሳተፈ ጥናት በማድረግ መለየትና በቁጥር ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በደን ሊሸፈኑ የሚችሉ አባባቢዎችን በአራቱም የአገሪቱ አቅጣጫዎች በመለየት የተቀናጀ የካርታ ንድፍ ማዘጋጀት፣ በሦስተኛ ደረጃ ለደን ልማት የተለዩትን አካባቢዎች አሁን ያሉበትን ሁኔታ የሚያሳይ መረጃ ለዚሁ ዓላማ በተቋቋመ የመንግሥት መሥሪያ ቤትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በጥንቃቄ መያዝ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ከግብርና ሚኒስቴር ለይቶ ራሱን የቻለ የደንና የግጦሽ ልማት ሚኒስቴር ማደራጀት ያስፈልጋል።
በመጨረሻም ለደን ልማት የተለዩትን አካባቢዎች በመከፋፈል በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች፣ በሚቋቋመው ሚኒስቴር አማካይነት ለመንግሥትና ለግል መሥሪያ ቤቶች በስማቸው እንዲያለሙት በውል በመስጠት፣ የልማት ቦታዎቹን የተረከቡት መሥሪያ ቤቶችም ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር አጋርነትን በመፍጠር ለዚሁ ዓላማ የተደራጁ ወጣቶችን በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ ክፍያ የሚያገኙበትን ውል በመግባት፣ ሥራውን በዘላቂነት በማከናወን የሥራ ዕድሎችን ለበርካታ ወጣቶች መፍጠር ይቻላል፡፡ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲዎችና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዛፎችን መትከልና ደኖችን መንከባከብ እንደ አንድ የትምህርት አካል በመውሰድ ተማሪዎቻቸው ከሚኖሩበት ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት በጥናትና ምርምር ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲሠሩ ቢደረግ ወጣቶች የአገራቸው የለውጥ ኃይል የሚሆኑበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል።
የደንና የግጦሽ ልማት ሚኒስቴር መንግሥት የሚመድብለት በጀት እንዳለ ሆኖ ለችግኝ ተከላና እንክብካቤ የሚያስፈልገውን ሀብት ከአገርና ከውጭ አካላት ማሰባሰብ ዋነኛው ሥራው ይሆናል። ከአገር ውስጥ የገንዘብ ምንጭ መካከል ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ ከአንድ እስከ አምስት በመቶ የሚደርሰውን በፈቃደኝነት እንዲቆረጥና ለዚሁ ዓላማ በተከፈተ የባንክ ሒሳብ በማስገባትና ክፍያዎችን በመፈጸም ማከናወን አንዱ አማራጭ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ድርጅቶች በየዓመቱ ከሚያገኙት ዓመታዊ ትርፋቸው የተወሰነውን ፐርሰንት ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጫነት ለአገሪቱ አረንጓዴ ልማት እንዲያውሉ የሚያስገድድ የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖር በማድረግ የአገሪቱን ታሪክ መቀየር ይቻላል፡፡ ከተለያዩ የልማት አጋሮችም የሀብት ማሰባሰብ ሥራው በተጨማሪ መሠራት ያለበት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ሳንዘነጋ ማለት ነው።
ሌላው ትኩረት ተሰጥቶ በዘላቂነት መሠራት ያለበት ደግሞ ማንኛውም በአገሪቱ የሚሠሩ የግንባታ ሥራዎች ከዘመቻና ከጥናት አልቦነት ተላቀው የአረንጓዴ ልማትን መርሕ በተለይ መልኩ መሥራታቸውን የሚያረጋግጥና የሚያፀድቅ ተቋማዊ መሠረት ሊገነባ ይገባል። በዚህም መሠረት የመንገድ፣ የባቡር፣ የኃይል፣ የኢንዱስትሪ፣ የትምህርት ቤቶች፣ የሆስፒታሎችና ሌሎችም የግንባታ ፕሮጀክቶች ደን ልማትን የፕሮጀክቶቻቸው አካል የሚያደርጉበትን ጥብቅ መመሪያና ሕግ አስፈላጊነት ግልጽ ሊሆን ይገባል።
የደን ልማቱን ሥራ ውጤታማነት ለመገምገም በየዓመቱ ትልቅ ዝግጅት በማድረግ ለውጥ ያመጡ የግልና የመንግሥት ተቋማት አገራዊ በሆነ ትልቅ ሥነ ሥርዓት የአረንጓዴ ጀግና ሜዳሊያ ሽልማት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የክልል መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ሚኒስትሮች፣ እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች በተገኙበት ዓለም አቀፍ ትኩረትን የሚስብ ሽልማት የሚኖረውን አደረጃጀት መፍጠር ለውጤቱ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡
በተጨማሪም ክትትልና ድጋፍ የሚያደርገው የመንግሥት አካል በየጊዜው የተሠራውን የአረንጓዴ ልማት በመለየት የግምገማ ሪፖርቱን ለሕዝብ በማሳወቅ መመስገን ያለባቸው አካላት እንዲመሰገኑ ተጠያቂ መደረግ ያለባቸውን አካላት በመለየት ለውሳኔ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በማቅረብ ዕርምጃ ማስወሰድ ይኖርበታል፡፡ ሌላው ትኩረት የሚሻው የደኖችን ደኅንነት የማረጋገጥ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ የሚረዳ በደን ሀብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ግለሰቦችንም ሆነ ተቋማትን በወንጀል ተጠያቂ የሚያደርግ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከላይ የተገለጹትን ዕርምጃዎች ተቋማዊ ሥራ በማድረግ በተጠናከረ መልኩ ከተተገበሩ ለበርካታ ወጣቶቻችን የሥራ ዕድሎችን የምንፈጥርበት ይሆናል፡፡ እንደዚሁም የአገራችን የደን ሽፋን የምንለውጥበትን ዕቅድ ዕውን በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በልዩ ሁኔታ የምትታይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡
አንድ ሰው በዕድሜ ዘመኑ በአካባቢ ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት ቢያንስ 200 ዛፎችን መትከል እንዳለበት፣ እንደዚሁም እያንዳንዱ ዛፍ በሕይወት ዘመኑ 0.7 ቶን በካይ ካርቦን ዳይ ኦክሳይድን መጦ በማስቀረት የአካባቢን ብክለት እንደሚያስቀር ተገንዝበን አረንጓዴ አሻራችንን ዛሬውኑ እናኑር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡