Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነዳጅ ፍጆታ በመቀነሱ 470 ሚሊዮን ዶላር ማዳን ተችሏል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሱዳን የቤንዚን አቅርቦት ተቋርጧል

የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ቀውስ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማዳከሙ ምክንያት የአገሪቱ የነዳጅ ፍጆታ በመቀነሱ፣ በሦስት ወራት ውስጥ 470 ሚሊዮን ዶላር ያህል ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ፡፡

ከመጋቢት ወር ጀምሮ በተለይ የቤንዚንና የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ በከፍተኛ መጠን በመቀነሱ፣ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባለው ጊዜ ውስጥ ከነዳጅ ግዥ ላይ 470 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደተቻለ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የዓለም የጤና ድርጅት የኮሮና ወረርሽኝን ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ብሎ ከገለጸ በኋላ የቤንዚን ፍጆታ 20 በመቶ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 70 በመቶ ቀንሷል፡፡

የአገሪቱ ዕለታዊ አማካይ የቤንዚን ፍጆታ 2.2 ሚሊዮን ሊትር፣ ናፍጣ ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር፣ የአውሮፕላን ነዳጅ 2.6 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡

እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ በአንዳንድ ክልሎች እንቅስቃሴ በመገታቱና በወረርሽኙ ምክንያት በተፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ የቤንዚን ዕለታዊ ፍጆታ ከ1.8 ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን ሊትር፣ ናፍጣ ወደ 8.5 ሚሊዮን ሊትር የአውሮፕላን ነዳጅ ከ800 ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ሊትር ቀንሷል፡፡

ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በመጋቢት ወር 50 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ለማስገባት አቅዶ ያስገባው 45 ሜትሪክ ቶን፣ በሚያዝያ 49 ሜትሪክ ቶን ቤንዚን ለማስገባት አቅዶ ያስገባው 39 ሜትሪክ ቶን፣ እንዲሁም በግንቦት ወር 49 ሚሊዮን ሜትሪክ  ቶን ቤንዚን ለማስገባት አቅዶ ያስገባው 42 ሜትሪክ ቶን ነው፡፡

ድርጅቱ በመጋቢት ወር 228 ሜትሪክ ቶን ናፍጣ ለማስገባት አቅዶ ያስገባው 210 ሜትሪክ ቶን ሲሆን፣ በሚያዝያ 224 ሜትሪክ ቶን ናፍጣ ለማስገባት አቅዶ 202 ሜትሪክ ቶን አስገብቷል፡፡ በግንቦት ወር 227 ሜትሪክ ቶን ናፍጣ ለማስገባት አቅዶ 195 ሜትሪክ ቶን አስገብቷል፡፡

የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርት ኢንዱስትሪን አሽመድምዶታል፡፡ በጉዞ ክልከላዎች ምክንያት ዓለም አቀፍ አየር መንገዶች 15,000 ያህል አውሮፕላኖች ከእንቅስቃሴ ውጭ አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም 90 ያህል አውሮፕላኖቹን በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አቁሟል፡፡ በመሆኑም የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ 70 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በመጋቢት ወር 71 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ ለማስገባት አቅዶ 29 ሜትሪክ ቶን ብቻ አስገብቷል፡፡ በሚያዝያ 74 ሜትሪክ ቶን፣ በግንቦት ወር 75 ሜትሪክ ቶን የአውሮፕላን ነዳጅ ለማስገባት ያቀደ ቢሆንም፣ በሁለት ወራት ውስጥ ምንም ዓይነት የአውሮፕላን ነዳጅ አላስገባም፡፡

‹‹በየወሩ ሁለት መርከብ የአውሮፕላን ነዳጅ እናስመጣ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን እየተጠቅምን ያለነው የአውሮፕላን ነዳጅ በመጋቢት ወር በገባችው አንድ መርከብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች ማመላለሻ ሥራ ቢዳከምበትም የጭነት በረራ ስለሚሠራ እንጂ፣ ሌሎች አየር መንገዶች ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ አቁመዋል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡

የዓለም የነዳጅ ዋጋ በመቀነሱና ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ፍጆታ በመቀነሱ፣ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ሦስት ወራት ውስጥ 470 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንደተቻለ አቶ ታደሰ ተናግረዋል፡፡ ትርፍ ነዳጅ ለማጠራቀም የሚያስችል ዴፖ ባለመኖሩ በአጋጣሚ የተፈጠረውን የነዳጅ ዋጋ ቅናሽ መጠቀም እንዳልተቻለ አክለዋል፡፡

በዓለም የነዳጅ ገበያ የአንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ከ80 እስከ 90 ዶላር ነበር፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ ግን ወደ 30 እና 40 ዶላር አሽቆልቁሏል፡፡

በጥር ወር የቤንዚን አማካይ ወርኃዊ ዋጋ በበርሜል 69 ዶላር፣ ናፍጣ 74 ዶላር፣ እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ 73 ዶላር ነበር፡፡ በሚያዝያ ወር የአንድ በርሜል ቤንዚን ዋጋ 20 ዶላር፣ ናፍጣ 24 ዶላርና የአውሮፕላን ነዳጅ 15 ዶላር ነበር፡፡

የአውሮፕላን ነዳጅ ዋጋ በጣም በረከሰ ወቅት አንድ በርሜል የአውሮፕላን ነዳጅ በአምስት ዶላር የተሸጠበት ዕለት እንደነበር ያስታወሱት አቶ ታደሰ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የአውሮፕላን ነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ባለመኖሩ አጋጣሚውን መጠቀም እንዳልተቻለ አስረድተዋል፡፡

በአገሪቱ ያሉት 13 የነዳጅ ዴፖዎች በአጠቃላይ የመያዝ አቅማቸው 420,000 ሜትር ኪዩብ ነው፡፡ በአዋሽ ከተማ የሚገኘው ዋናው ዴፖ 130,000 ሜትር ኪዩብ ነዳጅ የመያዝ አቅም አለው፡፡ የሱሉልታ ዴፖ ሙሉ በሙሉ ቤንዚን ብቻ እንዲያጠራቅም ተደርጓል፡፡ የሱሉልታ ዴፖ 60,000 ሜትር ኪዩብ ነዳጅ የማጠራቀም አቅም አለው፡፡ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በዱከም  ከተማ ዘመናዊና ግዙፍ የሆነ የነዳጅ ዴፖ ለመገንባት በዝግጅት ላይ ነው፡፡ አዲስ የሚገነባው ዴፖ 300,000 ሜትር ኪዩብ ነዳጅ የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን፣ ለግንባታው 140 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡

የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ አራት ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነው፡፡ መንግሥት በየዓመቱ ለነዳጅ ግዥ 2.9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል፡፡ ጎረቤት ሱዳን 80 በመቶ የሚሆነውን የቤንዚን ፍጆታ ስታቀርብ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት አቅርቦቱ በመቀነሱ 20 በመቶ ደርሷል፡፡ ኩዌት ፔትሮሊየም ኮርፖሬሸን 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታ፣ እንዲሁም 75 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ ይሸፍናል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ አቡዳቢ ናሽናል ኦይል ካምፓኒ 80 በመቶ የቤንዚን ፍጆታ፣ እንዲሁም 50 በመቶ የናፍጣ ፍጆታና 25 በመቶ የአውሮፕላን ነዳጅ ፍጆታ ያቀርባል፡፡

ይሁን እንጂ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ሱዳን የአየር ክልሏንና ድንበሯን ሙሉ ለሙሉ በመዝጋቷ፣ ነዳጅ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ቤንዚን ወደ ኢትዮጵያ ማጓጓዝ አልቻሉም፡፡ በዚህ ምክንያት ከመጋቢት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ቤንዚን ከሱዳን ገብቶ እንደማያውቅ ለመረዳት ተችሏል፡፡

አቶ ታደሰ ለሪፖርተር እንደተናገሩት ከሱዳን የሚገባው ቤንዚን ቢቋረጥም፣ ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በጂቡቲ ወደብ የሚገባው የቤንዚን ምርት የአገር ውስጥ የቤንዚን ፍጆታ ለመሸፈን በመቻሉ ተጨማሪ ቤንዚን ግዥ ማካሄድ አላስፈለገም፡፡ ‹‹በወረርሽኙ ምክንያት የቤንዚን ፍጆታ በመቀነሱ ከሱዳን የምናስገባውን ቤንዚን ብናቆምም፣ ተጨማሪ የቤንዚን ምርት ማዘዝ አላስፈለገንም፡፡ አቡዳቢ ናሽናል ኦይል ካምፓኒ የሚያቀርበው የቤንዚን ፍላጎትን እያሟላ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች