Tuesday, May 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ባህሪዋን ከማትገራው ግብፅ ጋር በሚደረገው ድርድር መዘናጋት አይገባም!

የኢትዮጵያውያንን የማያወላውል አቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር ሳትወድ በግድ የተረዳችው ግብፅ ወደ ሦስትዮሽ ድርድር ብትመለስም፣ አሁንም ጊዜ ለመግዛትና ለማዘናጋት እንጂ እምነት እንደማይጣልባት መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ግብፅ የተለመደውን የማደናገሪያ አቋሟን ይዛ ስለምትቀርብ፣ ግልጽነትና መተማመን እንዲጠፋ እያደረገች ነው፡፡ አሁንም በአሜሪካ ተሞክሮ የከሸፈውን ኢትዮጵያ የውኃ ሙሌቱን እንዳትጀምር የሚያስገድደው ድርድር እንዲቀጥል ነው የምትፈልገው፡፡ ለዚህ ዓላማዋም ሱዳንን እያስተባበረች ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ የጨዋታውን ሕግ ራሷ በምትከተለው የፍትሐዊና የምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ መሠረት መቅረፅ እንጂ፣ ግብፅ በለመደችው የአሳሳችነት ወጥመድ ውስጥ እየወደቀች በቅኝ ግዛት ስምምነቶች መነታረክ የለባትም፡፡ የህዳሴውን ግድብ ግንባታና የውኃ ሙሌትና አለቃቀቅ ሥርዓቱን በተመለከተ፣ በየትኛውም ዓለም አቀፍ ሕግ ኢትዮጵያን ሊያስጠይቋት የሚችሉ ቀዳዳዎችን በመድፈን መብቷን ማስከበር አለባት፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞችና የሚዲያ ሰዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የጀመሩትን የማሳሳት ዘመቻ ኢትዮጵያዊያን ከመመከት አልፈው፣ በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን ምክንያታዊነት የማስረዳትና የግብፅን ፕሮፓጋንዳ አከርካሪውን መስበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን ተግባር እያከናወኑ ያሉ ኢትዮጵያዊያን እየተመሠገኑ፣ ሌሎች አገር ወዳዶች በስፋት እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ይገባል፡፡ ግብፅ አሁንም ለመታረም ዝግጁ እንዳልሆነች መታወቅ አለበት፡፡

ለዓባይ ውኃ 86 በመቶ የምታበረክተው ኢትዮጵያ በታሪኳ በወንዙ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ አንድ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ገነባች ተብላ ይህ ሁሉ መከራ ሲደርስባት፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የግብፅን ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነትና ክፋት መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት፣ ዕውቀቱና ክህሎቱ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን በሙሉ መረባረብ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን የሚጠቅማት እውነትን መያዟ ብቻ ሳይሆን፣ ግብፅ በሐሰት እየወነጀለቻት እንደምታሳጣት ገላልጦ ማሳየት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ ሀብቷን በእኩልነትና በፍትሐዊነት እንጠቀም እያለች ዓለም አቀፉን ሕግ እያከበረች፣ ለዚህ ሀብት ምንም አስተዋፅኦ የሌላት ግብፅ በምንም ዓይነት ሁኔታ እንድታንገላታት ሊፈቀድላት አይገባም፡፡ የዓባይ ውኃ የ11 የተፋሰሱ አገሮች የጋራ ሀብት መሆኑን መቼም ቢሆን ለመቀበል የማትፈልገው ግብፅ ትልቁ ችግሯ፣ ኢትዮጵያውያን የህዳሴውን ግድብ በራሳቸው ለመገንባት ቆርጠው ሲነሱ በአካባቢው የነበራት የበላይነት ያበቃል የሚል ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖራት ከፍተኛ ሴራ ስትጎነጉን ኖራለች፡፡ አሁንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የውስጥ ወኪሎቿን በመጠቀም ሰላም እየነሳቻት ነው፡፡ አገራቸውን ከምንም ነገር በላይ የሚያስቀድሙ ኢትዮጵያዊያን አሁን መንቃት አለባቸው፡፡ ምንም ነገር ቢያጋጥም ውስጣዊ ችግሮችን በሰላም መፍታት ከቻሉ፣ ከዚህ በኋላ እነ ማን የግብፅና መሰሎቿ ተላላኪ እንደሆኑ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃ መጠን እንዳይቀንስ የሚረዳ የተፋሰስ እንክብካቤና መጠነ ሰፊ የችግኝ ተከላ ስታካሂድ፣ የወንዙ ከፍተኛ ተጠቃሚ የሆነችው ግብፅ ግን እንኳን ይህንን ጥረት ልታግዝ ኢትዮጵያን ለማተራመስ ትታገላለች፡፡ የግብፅ ፖለቲከኞችና ሚዲያዎች ምስኪኑን የግብፅ ሕዝብ የዓባይ ወንዝ ከኢትዮጵያ ሳይሆን ከዚያው እንደሚነሳ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በህልውናው ላይ የተነሳች ጠላት አድርገው ሲያታልሉት ኖረዋል፣ አሁንም እያታለሉት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥ ቅጥረኞቻቸው አማካይነት ኢትዮጵያውያንን ሰላም እየነሱ ግድባቸውን ለማስቆም ያሴራሉ፡፡ ይህንን ቅጥፈትና አደገኛ ተግባር ከማጋለጥ በተጨማሪ፣ ቀድሞ በመሄድ መንገዳቸውን እየዘጋጉ ወደ ድርድር መድረኩ አስገድዶ ማምጣት የግድ ይሆናል፡፡ የግብፅ ባህሪ ሳይገራ ወደ ድርድር መግባት አይቻልምና፡፡

በግብፅ በየተራ የተፈራረቁ መንግሥታትና ፖለቲከኞቹ ሲያደርጉት የነበረውና አሁንም እያደረጉ ያሉት የክፋት ድርጊት አንድ ሀቅ ያስገነዝባል፡፡ ለምሳሌ ግብፅ በኢትዮጵያ ቦታ የራስጌ አገር ብትሆን ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ከዓባይ ውኃ አንድ ብርጭቆ እንደማትፈቅድላት ከድርጊታቸው መረዳት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለዘመናት ውኃው በድርቅም ሆነ በዝናባማ ወቅቶች ሳይጓደል እንዲደርሳት ስታደርግ ኖራለች፡፡ ይህ ሐሜት ወይም አሉባልታ ሳይሆን የግብፅ መሪዎችን፣ ፖለቲከኞችንና የሚዲያ ሰዎችን ሰብዓዊነት የጎደለው ድርጊት በጥቂቱ ማሳያ ነው፡፡ የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ሲጀመርም ሆነ በሒደት ላይ ሆኖ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከኢትዮጵያ በኩል ሲሰማ የነበረው፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ በሱዳንና በግብፅ ወንድምና እህት ሕዝቦች ላይ የጎላ ጉዳት እንደማይደርስ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የኢትዮጵያ መንግሥት በችላ ባይነት ወይም በዘፈቀደ ይህንን የተገባ ቃል ቢያፈርስ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በፊት ቀድሞ የሚቃወም ማንም አይኖርም፡፡ ይህ አስተዋይና ጨዋ ሕዝብ ኢፍትሐዊነትን የሚቃወም በመሆኑ ጎረቤቶቹ እንዲጎዱ በፍፁም አይፈቅድም፡፡ ለዚህም ነው ግብፆች አገራቸውን ‹‹የዓባይ ስጦታ ናት›› ሲሉ ትክክል የማይሆነው፡፡ ይልቁንም ‹‹ዓባይ የኢትዮጵያ ሲሆን ግብፅ ደግሞ የኢትዮጵያ ስጦታ ናት›› ነው መባል ያለበት፡፡ ስስታሟ ግብፅ ግን ይህንን እውነታ ለማመን ካለመፈለጓም በላይ፣ አስዋን ግድብ ላይ በዓመት ከአሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር በላይ ውኃ እያስተነነችና የተለያዩ ግድቦችን ያለ ጠያቂ እንዳሻት ስትገነባ ኖራ፣ ኢትዮጵያን በአጥፊነት ትወነጅላለች፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ግብፅ ክፋት የተጠናወታት ብትሆን እኮ በርካቶቹን የዓባይ ገባሮች ጠልፋ፣ ግብፅን የሜዲትራኒያን ባህር የጨው ውኃ እያጣራች እንድትጠቀም ወይም ለክፉ ጊዜ ብላ የደበቀችውን የከርሰ ምድር ውኃ እንድታወጣ ታስገድዳት ነበር፡፡ ግብፅ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በኢትዮጵያዊያን ልትሞገት ይገባታል፡፡ ቀልድ የለም መባል አለበት፡፡ የግብፅን ብልሹ ባህሪ መታገስ አያስፈልግም፡፡

ከሁሉም በጣም የሚገርመው ግብፅ ኢትዮጵያን በጦር ኃይል ጭምር ለማስፈራራት የምታደርገው ተደጋጋሚ ሙከራ ነው፡፡ ‹‹ግብፅ ግዙፍ የጦር ኃይል ባለቤት ናት›› ተብሎ የሚነዛው ፕሮፓጋንዳ ማንንም ሊያዘናጋ አይገባም፡፡ ኢትዮጵያ በዘመኑ ግዙፍ የተባለ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ በታላቁ የዓድዋ ጦርነት በማንበርከክ፣ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት የሆነች አገር ናት፡፡ ግብፅን ጨምሮ በተለያዩ ጊዜያት ለወረራ የመጡ ኃይሎችን አሳፍራ በመመለስ፣ ብቸኛዋ በአፍሪካ ቅኝ ያልተገዛች አገር ናት፡፡ ቬትናሞች ከኃያሉ የአሜሪካ ጦር ጋር ሲዋጉ መሪዎቻቸው ይነግሯቸው የነበሩት፣ እንደ ኢትዮጵያዊያን ጠንክረን ከተዋጋን እናሸንፋለን የሚለውን ነበር፡፡ ዛሬም ቢሆን አንዳንድ መናኛ ከሃዲዎችና ተላላኪዎች ቢኖሩም፣ የጥንቶቹ ኢትዮጵያዊያን የጀግንነት ወኔ በዚህ ትውልድ ውስጥም እንዳለ ለአፍታ መጠራጠር አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊያን መቼም ቢሆን በታሪካቸው ወረራ ሲመክቱ እንጂ የማንንም አገር ሲወሩ አይታወቁም፡፡ ሁሌም ቢሆን ቅድሚያ የሚሰጡት ለሰላምና ለወዳጅነት እንጂ ለጠብ አይደለም፡፡ ከግብፃውያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በዓባይ ውኃ ምክንያት መጋጨት አይፈልጉም፡፡ ውኃውን በጋራ ለመጠቀም አንደበታቸውም ልባቸውም ንፁህ ነው፡፡ የሁለቱን አገር ሕዝቦች ለማጨካከንና ለጥፋት ለማነሳሳት የሚጥሩ ኃይሎችን በማጋለጥ፣ ከድርድር ውጪ አማራጭ አለመኖሩን ማስገንዘብ የግድ ይላል፡፡ ከዚህ ውጪ ኢትዮጵያን ማንም ሊደፍራት እንደማይችል በቃልም በተግባርም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያውያን በፍፁም መርሳት የሌለባቸው ግብፅ መቼም ቢሆን ቃል የማታከብር መሆኑን ነው፡፡ ሲመቻት በማስፈራራት ወይም ሐሰተኛ ወሬ በመንዛት ለማሸማቀቅ፣ ሳይመቻት ሲቀር ደግሞ ጊዜ ለመግዛት ወደ ድርድር በመምጣት ማደናገር ልማዷ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከአሁን በኋላ በግብፅ መሰሪነት ሊታለል አይገባም፡፡ በምንም ዓይነት ሁኔታ የቅኝ ግዛት ቅርስ ከሆኑት ስምምነቶች የሚቀዳ ማደናገሪያም ሆነ ተንኮል እንዲጠልፈው መመቻቸት የለበትም፡፡ ከዚህ ቀደም ግድቡን በሚመለከት ግብፅ ይኖሩኛል የምትላቸውን ሥጋቶች በቀናነት ለመመልከት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ነገር ግን ግብፅ ተንኮሏን ረቀቅ እያደረገች አሜሪካ ድረስ ተሂዶ የተፈጸመው በደል ይታወሳል፡፡ አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ምስለኔዋን ጥቅም ለማስከበር የሄደችበት ርቀት፣ የህዳሴውን ግድብ እስከ መሰዋት የተቃረበ ነበር፡፡ ግብፅ ለዘመናት ዓለም አቀፍ አበዳሪዎችና ለጋሾች ለኢትዮጵያ ጀርባቸውን እንዲሰጡ በማድረግ የፈጸመችው በደል አይዘነጋም፡፡ ከግብፅ ጋር የሚደረጉ ድርድሮች በሙሉ እነዚህን በደሎች ታሳቢ ማድረግ አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ በገዛ ውኃዋ በራሷ ግዛት ውስጥ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ለመገንባት ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ አይከለክላትም፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ከመገንባት ሊያግዳት እንደማይችል መታወቅ አለበት፡፡ ኢትዮጵያዊያን ለብሔራዊ ፕሮጀክታቸው ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ከዳር እስከ ዳር እያስተጋቡ ነው፡፡ ግብፅ ይህንን ጠንቅቃ እንድታውቀው ቁርጡ ይነገራት፡፡

አሁን ኢትዮጵያውያን ለግብፅና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልጽ መንገር ያለባቸው፣ ተፈጥሯዊ መብታቸውን የመጠቀም ነፃነት እንዳላቸው ነው፡፡ ለግብፅ ሰዎችም በሚገባቸው ቋንቋ ጭምር መልዕክት መተላለፍ አለበት፡፡ በተለይ የግብፅ ፖለቲከኞችም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው ዘመን ያለፈባቸውን የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ማጣቀስ ያቁሙ፡፡ የግብፅ ሕዝብን ከአፍሪካውያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር አያጣሉት፡፡ ሐሰተኛ የማደናገሪያ ሥልቶቻቸው ስለተነቁባቸው ወደ ድርድር መድረኮች በትብብር መንፈስ ይምጡ፡፡ የዓባይ ውኃን የግዙፉ አገራዊ ችግርና ቅራኔ ማድበስበሻ አያድርጉት፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የገቡበት አሳፋሪ እሰጥ አገባ፣ ነገ ከተቀሩት የተፋሰሱ አገሮች ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ እንደሚያስገባቸው ይረዱ፡፡ እስካሁን ሲፈጽሟቸው የነበሩ ድርጊቶች ኃላፊነት የጎደላቸው፣ ከፍተኛ የሆነ ራስ ወዳድነት የተፀናወታቸው፣ በሰላም አብሮ መኖርንና ትብብርን ያጠፉ፣ ቂምና ጥላቻን የዘሩና በአጠቃላይ ወደፊት ሊኖር የሚችልን መተማመን በእጅጉ የጎዱ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የግብፅ አመራሮች አሁንም የውስጥ ተላላኪዎችን እየመለመሉ ኢትዮጵያን ለማተራመስ እንደሚንቀሳቀሱ ቢታወቅም፣ ኢትዮጵያውያን አሁንም ለሰላምና ለትብብር ዝግጁ ናቸው፡፡ ይህ ማለት ግን የግብፅ ተላላኪዎችን በኅብረት እየደቆሱ ግድባቸውን መገንባት እንደሚቀጥሉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ የተጀመረው ድርድር መልካም ቢሆንም፣ ከአሁን በኋላ ግብፅና ተላላኪዎቿን ኢትዮጵያዊያን እንደማይታገሱ መገንዘብ የግድ ይሆናል፡፡ ከግብፅ ጋር የሚደረገው ድርድር በዚህ መንፈስ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ በሐምሌ ወር የውኃ ሙሌት ካልጀመረች ለኢትዮጵያ ሕዝብ ታላቅ ውርደት ስለሆነ፣ ግብፅ ወደ ድርድሩ ስትመለስ ባህሪዋን ገርታ መሆን እንዳለባት በግልጽ ሊነገራት ይገባል፡፡ መዘናጋት አይገባም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

የሁለተኛው አብዮታዊ ሠራዊት ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ሁሴን አህመድ (1930-2015)

ኢትዮጵያ የሁለተኛውን የፋሺስት ጣሊያን ወረራ (1928-1933) በድል ከተወጣች በኋላ...

ከወለድ ነፃ ባንክ የተሰበሰበውን በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ለምን ሥራ ላይ ማዋል አልተቻለም?

  ባንኮች ከወለድ ነፃ የሚሰበስቡት ተቀማጭ ገንዘብ መጠን ዕድገት እያሳየ...

መንግሥት ባለፈው ዓመት ለማዳበሪያ የደጎመው 15 ቢሊዮን ብር ለአርሶ አደሮች አለመድረሱ ጥያቄ አስነሳ

መንግሥት ለ2014/15 በጀት ዓመት እርሻ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ያለውን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመስቀል አደባባይ የመግቢያ ክፍያ ለምን?

ወጣቶች፣ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀሩ መንፈሳቸውን የሚያድሱበት እንዲሁም ሐሳባቸውን በነፃነት...

በሕገ መንግሥቱ የተዋቀረው ‹‹የብሔር ፖለቲካ›› እና ‹‹ሥርዓቱ›› ያስከተለው መዘዝና መፍትሔው

(ክፍል አራት) በዓቢዩ ብርሌ (ጌራ) ባለፈው ጽሑፌ (በክፍል ሦስት) አሁን ያለው...

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብና የመንግሥት መሪ ምሥል

በበቀለ ሹሜ በ2015 ዓ.ም. መጋቢት ወር ውስጥ ይመስለኛል በ‹ሸገር ካፌ›...

ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ያደረገው አዋጅ የፍትሐዊነት ጥያቄ አስነሳ

በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ስምንት ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ በማድረግ ተቋማዊና...

ለመጪው ዓመት የሚያስፈልገው 4.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ነዳጅ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ይጠይቃል

ለመጪው 2016 ዓ.ም. ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ለታቀደው 4.3...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመኸር እርሻ ተዛብቶ ቀውስ እንዳይከሰት ጥንቃቄ ይደረግ!

ክረምቱ እየተቃረበ ነው፡፡ የክረምት መግቢያ ደግሞ ዋናው የመኸር እርሻ የሚጀመርበት ጊዜ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ 70 በመቶ ያህሉን የሰብል ምርት የምታገኘው በመኸር እርሻ...

የሕዝቡን ኑሮ ማቅለል እንጂ ማክበድ ተገቢ አይደለም!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ለበርካታ ወጪዎቹ ገንዘብ ስለሚያስፈልጉት አስተማማኝ የገቢ ምንጮች ሊኖሩት ይገባል፡፡ በጀት ሲይዝም ሆነ ወጪዎቹን ሲያቅድ ጠንቃቃ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወቅቱ ለመጪው ዓመት በጀት...

ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማት በሌሉበት ውጤት መጠበቅ አይቻልም!

በኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚስተዋሉ መዛነፎችና አለመግባባቶች ዋነኛ ምክንያታቸው፣ ከበፊት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋማትን ለመገንባት አለመቻል ነው፡፡ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በፀጥታ፣...