ታላቁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ከሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. አንስቶ ዳግም ወደ ድርድር ቢመለሱም፣ ግብፅ በድርድርና ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት ለማምራት እየዋለለች በመሆኑ አንዱን ልትመርጥ ይገባል ስትል ኢትዮጵያ አሳሰበች። ድርድሩ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን የኢትዮጵያ የውኃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ድርድሩን የተመለከተ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ በዚህም መግለጫው ግብፅ በታማኝነት በድርድሩ እንድትሳተፍ ጥሪውን አቅርቧል።
ዳግም የተጀመረው የሦስትዮሽ ውይይቱ ቀጣይነት እንዲኖረው በሁሉም ተደራዳሪ አካላት መካከል መተማመን ሊኖር እንደሚገባ የመከረው መግለጫው፣ ‹‹ይሁንና የግብፅ አቀራረብ የሦስትዮሽ ድርድሩን ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለመውሰድና የውጭ ዲፕሎማቲክ ጫና ለመፍጠር የሚደረግ ጥረት ነው፤›› ብሏል። ይህ ደግሞ በድርድሩ መተማመንና ግልጽነት እንዳይኖር የሚያደርግ እንደሆነ አስታውቋል።
ሦስቱም ወገኖች በግልጽነትና በታማኝነት ወደ ድርድሩ በመምጣት የሁሉም ሐሳብ የተካተተበት የመጀመሪያው የውኃ አሞላል ሒደትና የግድቡን ዓመታዊ አሠራር ግልጽ እንዲሆን ኢትዮጵያ አቋሟ እንደሆነም በመግለጫው ገልጿል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህ እንዲሳካ የድርሻውን ጥረት ማድረግ አለበት ያለው መግለጫው፣ ኢትዮጵያም ለዚህ ስኬት የበኩሏን ድርሻ እንደምትወጣ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት ዳግም በተጀመረው ድርድር ላይ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ ኅብረትና አሜሪካ በታዛቢነት የታደሙ ሲሆን፣ የእነዚህን ታዛቢዎች ሚና በተመለከተ ኢትዮጵያና ግብፅ ልዩነት አላቸው። ኢትዮጵያ የያዘችው አቋም ታዛቢዎቹ ድርድሩን ከመታዘብና በሦስቱ አገሮች ታምኖበት ሲጠየቁ ብቻ መልካም ልምዳቸውን (ተሞክሯቸውን) ከማካፈል የዘለለ ሚና እንዳይኖራቸው የሚል አቋም ይዛለች። ግብፅ ደግሞ እነዚህ አገሮች ድርድሩን የማመቻቸት ሚና ይህም የስምምነት ሐሳብ ከማመንጨት፣ እስከ የስምምነት ሰነድ ማዘጋጀት ይችላሉ የሚል አቋም ማራመዷን ለማወቅ ተችሏል።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ዳግም የተጀመረው ድርድር በግድቡ የመጀመሪያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትንና ዓመታዊ አሠራርን በተመለከተ ብቻ ሊያተኩር እንደሚገባ የገለጸች ሲሆን፣ ይህንንም የተመለከተ መመርያና ሕግ አዘጋጅታ ማቅረቧ ታውቋል። በሱዳን በኩልም ተመሳሳይ የራሷን አቋም የሚገልጽ ሰነድ አዘጋጅታ ያቀረበች ሲሆን፣ ግብፅ ግን ድርድሩ አጠቃላይ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተመለከተ ሊሆን እንደሚገባና ድርድሩም በአምስት ቀናት ውስጥ መጠናቀቅ እንደሚገባው በመግለጽ ተቃርናለች። ከዚህ በተጨማሪ ግብፅ ሦስቱ አገሮች ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ኢትዮጵያ በተናጠል ውሳኔ የውኃ ሙሌት እንደማትጀምር ማረጋገጫ እንድትሰጣት ቅድመ ሁኔታ ያቀረበች ሲሆን፣ ቀደም ሲል በአሜሪካ አማካይነት የተረቀቀው የስምምነት ሰነድ የዚህ ድርድር መነሻ እንዲሆን ቅድመ ሁኔታ አቅርባለች።
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ አገሮች መካከል ስምምነት ባለመደረሱ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ባለፈው ሳምንት ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልክ ደውለው መወያየታቸው የኢትዮጵያ አመራሮችን አስቆጥቷል። ድርድሩ በመቀጠሉ ላይም ተስፋ እንደሌላቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ወገን ተሳታፊዎች የገለጹ ሲሆን፣ የትኛውም ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር ኢትዮጵያ ግድቡን በዕቅዷ መሠረት መሙላት እንደምትጀምር የፖለቲካ አቋም መያዙን አመልክተዋል።