Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትሰሚ ያጣው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ቅሬታ

ሰሚ ያጣው የእግር ኳስ ተጨዋቾች ቅሬታ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚወዳደሩ ክለቦች በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ውድድር ቢያቋርጡም፣ ተጨዋቾቻቸውን በተመለከተ ግን በገቡት ውል መሠረት ክፍያ መፈጸም እንዳለባቸው የሚያስገድድ ደንብ አለው፡፡ ይሁንና መመርያው በአንዳንድ ክለቦች ዘንድ ተፈጻሚ ሊደረግ ባለመቻሉ ክፍያ ያልተፈጸመላቸው ተጨዋቾች ለችግር እየተዳረጉ መሆኑ ይገኛል፡፡

ቀድሞውኑ ቢሆን የበጀት አጠቃቀም ክፍተት የነበረባቸው ክለቦች ታዲያ ችግሩን ምክንያት በማድረግ ተጨዋቾችን ጨምሮ ለበርካታ የዘርፉ ተዋንያን ተጨማሪ ሥጋት መሆናቸው እንዳልቀረ የሚናገሩ አልጠፉም፡፡

በወረርሽኙ ምክንያት ደመወዝ የማይከፈላቸው ተጨዋቾችን በሚመለከት የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎቹ፣ “ወረርሽኙ አስከትሏል ለሚባለው የፋይናንስ ቀውስ በተለይ አንዳንዶቹ ክለቦች ምክንያት ሊያደርጉ አይገባም፡፡ ምክንያቱም ክለቦቹ ተጨዋቾችን የሚያዘዋውሩበት የአሠራር ሥርዓትም ሆነ ወርኃዊ ክፍያ፣ አገሪቱ የምትከተለው የፋይናንስ ሥርዓት የማያውቀውና ኦዲትም ስለማይደረግ የተፈጠረ ክፍተት ካልሆነ በስተቀር በኮሮና ብቻ የመጣ ቀውስ አይደለም፤” በማለት የተጨዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ከኮሮና በፊትም ሳይከፈል የቆየ መሆኑ ተጨዋቾች ከሚያቀርቡት ቅሬታ በመነሳት መረዳት እንደሚቻል ጭምር ያስረዳሉ፡፡

ከተጫዋቾች ወርኃዊ ክፍያ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ስማቸው ሲጠቀስ ከሚደመጠው ክለቦች መካከል ጅማ አባ ጅፋር፣ ወላይታ ድቻ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ ባህዳር ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማና ሌሎችም ክለቦች ኮሮና ከመከሰቱ በፊት ለተጨዋቾቻቸው በገቡት ውል መሠረት እየከፈሉ እንዳልነበረ ቅሬታ ሲቀርብባቸው የነበሩ ናቸው፡፡

ከእነዚህ ውስጥ በተለይ የጅማ አባ ጅፋር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች የሰባት ወርና ከዚያም በላይ ክፍያ ያልተከፈላቸው መሆኑ ተጫዋቾቹ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና ለክልል እግር ኳስ ቢሮ ኃላፊዎች ከጻፏቸው የቅሬታ ደብዳቤዎች መረዳት ይቻላል፡፡

የኦሮሚያ ክልል እግር ኳስ ቢሮ የጅማ አባ ጅፋር እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾች እያቀረቡት ካለው  ቅሬታ በመነሳት በ04/10/2012 በጻፈው ደብዳቤ፣ የክለቡ ተጫዋቾች ከታኅሣሥ 2012 ጀምሮ እስከ አሁን ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው በተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን፣ በዚህም ምክንያት በራሳቸውም ሆነ በቤተሰቦቻቸው ችግር እየገጠማቸው በመገኘቱ በተጫዋቾቹና በክለቡ መካከል በተደረገው የውል ስምምነት እንዲሁም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውልና መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለተጫዋቾቹ ደመወዛቸውን ከፍላችሁ ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ከገቡበት ችግር እንዲወጡ እንድታደርጉ በማለት ማሳሰቢያ የሰጠበትን ደብዳቤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተጫዋቾች በእጃቸው መያዛቸውን ጭምር ያስረዳሉ፡፡

በተመሳሳይም ወላይታ ድቻና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለቦችም ከሦስት አስከ አራት ወር ድረስ ምንም ዓይነት ወርኃዊ ክፍያ እንዳልተፈጸመላቸው ተጫዋቾቹ ይናገራሉ፡፡

የሁለቱ ክለቦች ተጫዋቾች ይህንኑ አስመልክቶ፣ “የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ችግር እንደሆነ እንረዳለን፣ ይሁንና ይህን እንደ ምክንያት ቆጥሮ ቀደም ሲል ሳይከፈል የቆየውን ክፍያ ሳይቀር መከልከል ከሕግም ሆነ ከሞራል አኳያ ተቀባይነት የለውም፤” በማለት ክለቦች በገቡት ውል መሠረት ክፍያ እንዲፈጸምላቸው ይጠይቃሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ተደጋጋሚ ክስና ቅሬታ ሲቀርብ አዲስ እንዳልሆነ የሚናገረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው የገቡትን ውል ማክበር እንደሚጠበቅባቸው የሚያስገድድ ሕግ እንዳለው ያስረዳል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን ኮሮናን ምክንያት በማድረግ መክፈል አንችልም የሚሉ ካሉ በተቋሙ ደንብና መመርያ መሠረት ዕርምጃ እንደሚወስድ ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል፡፡

ማስጠንቀቂያው ተከትሎ ከፕሪሚየር ሊጉ ጀምሮ በተዋረድ የሚገኙ ብዙዎቹ ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው በገቡት የውል ስምምነት መሠረት ክፍያ የፈጸሙ አሉ፡፡ አሁንም ተመሳሳይ ቅሬታ እየቀረበባቸው የሚገኙ ክለቦች ክፍያ እንዲፈጽሙ፣ ካልሆነ ግን ዕርምጃ እንደሚወስድ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲሁም የሊግ ካምፓኒው አመራሮች ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ የሁለቱን ክለቦች አመራሮች ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

በሌላ በኩል እንደ እግር ኳስ ተጫዋቾች ሁሉ ውድድሮች በመቋረጣቸው ምክንያት የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ለከፋ ችግር መዳረጋቸው ሲነገር መቆየቱ አይዘነጋም፡፡

የዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ማኅበር ባለው ሁኔታ ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ ከፕሪሚየር ሊግና ብሔራዊ ሊግ ክለቦች ጋር በመነጋገር የመፍትሔ አቅጣጫ የተቀመጠ ስለመሆኑ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ያስረዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ዳኞች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሚኬኤሌ አርአያ፣ የፕሪሚየር ሊጉን፣ የከፍተኛውንና ብሔራዊ ሊጉን የሚዳኙት የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች የውሎ አበል ክፍያ ሲፈጸም የቆየው በክለቦቹ እንደነበር፣ ይህ ግን በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ውድድሮች ሲቋረጡ ክፍያውም ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተደርጎ መቆየቱን ያወሳሉ፡፡ ይሁንና ማኅበሩ ከፌዴሬሽኑና ከክለብ አመራሮች ጋር በመነጋገር ጨዋታ ከመቋረጡ በፊት ተፈቅዶ የነበረው ጭማሪ ክፍያ ጭምር ለፕሪሚየር ሊጉና ከፍተኛው ሊግ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ክፍያ ተፈጽሞላቸዋል ብለው የብሔራዊ ሊጉ ግን የማጣራቱ ሒደት ጊዜ በመውሰዱና ተዋንያኑም ብዛት ስለነበራቸው በቀጣይ እንዲከፈል ከስምምነት ስለመደረሱ ጭምር ገልጸዋል፡፡

ክፍያውና ዕገዛው በሥራ ላይ ከሚገኙት በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ምክንያቶች ከሙያው ተገለው በተለይ በሕመም ላይ የሚገኙ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ድጋፍ እንዲደረግላቸው በፌዴሬሽኑ ዋናና ምክትል ፕሬዚዳንት ይሁንታ መገኘቱም አክለዋል፡፡

የሴቶችን ሊግ የሚያጫውቱ ዳኞችና ታዛቢ ዳኞችን ክፍያ በተመለከተ አቶ ሚካኤሌ እንደገለጹት፣ የወንዶቹን ሊግ የሚዳኙት ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ክፍያ የሚፈጸመው በክለቦች ሲሆን፣ የሴቶቹ ግን ሙሉ በሙሉ ሲሸፈን የነበረው በፌዴሬሽኑ በመሆኑ ተጨማሪ ውይይት አስፈልጓል፣ እንዲከፈልም ከስምምነት ተደርሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...