በአማረ ተግባሩ (ዶ/ር)
የዘር ውርስ ይዘታቸው የተለወጡ አዝርዕት (Genetically Modified Organisms) በተመለከተ ዕገዳው ተነስቶላቸው ይገቡ ይሆናል ተብለው የሚጠበቁትን የዘር ውርስ ይዘታቸው የተለወጠ ጥጥ፣ በቆሎ ወይም እንሰት ላይ ስንነጋገር መርሳት የሌለብን፣ የምንገኘው አሁንም በኮሮና ወረሽኝ ዘመን መሆኑን ነው። ይህ የኮሮና ወረርሽኝ በተናጠል የማይታይ፣ ግዙፍና ውስብስብ (Compounded) ከሆነው የምግብ ዋስትና ችግር ጋር የተገናኘ ነው። ይልቁንም መገንዘብ የሚያስፈልገው ይህ የኮሮና ወረርሽኝ ካለፈም በኋላ ጉዳቱ በድኅረ ኮሮና ዘመን ጭምር የሚከተለን መሆኑ ነው። እንደ ኮሌራና የአንበጣ መንጋ የመሳሰሉትና ሌላም ዓይነት ተመሳሳይ ወረርሽኝ፣ ወይም ተፈጥሯዊና ተፈጥሯዊ ያልሆነ መቅሰፍት በድጋሚ ሊከሰት እንደሚችል መገመት ይቻላል። በዚህ ዕይታና ግንዛቤው ውስጥ ሆነን የዘር ውርስ ይዘታቸው የተለወጡ አዝርዕት ላይ የሌሎች አገሮች ልምድ ገና ለረዥም ጊዜ መዘዙ ለሚከተለን የምግብና ጤና ዋስትና፣ የገቢ ምንጭና ሥራ ፈጠራ ላይ ምን ሊያስተምረን እንደሚችል ሊያግዘን ይችላል።
የህንድ ልምድ ምን ይመስል ይሆን?
ከዚህ በታች የማቀርበው በህንዱ ሳይንቲስት ኬ.አር. ክራንቲና ምዕራባዊው ባልደረባው ግሌን ዴቪስ ስቶን “Long-term Impacts of Bt Cotton in India” በሚል ርዕስ (Nature Plants 6(3):188-196· March 2020) ካሳተሙት ጥናት (DOI: 10.1038/s41477-020-0615-5)፣ እንዲሁም ማርክ ላይናስ፣ “Why Did India Abandoned the Production of GM Cotton?” በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ (Alliance for Science Journal) ላይ እ.ኤ.አ. ኦገስት 2 ቀን 2018 ካቀረቧቸው ጥናቶች የተገኘ ነው።
በቅድሚያ ለማስገንዝብ ያህል ጥጥ እንደ አገራችን ቡናና ጤፍ በህንድ የተገኘና በዝርያ ባለቤትነትም የተመዘገበባት ነች፡፡ የምዕራቡ ዓለም የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ የበላይነቱን እስከጨበጠ ድረስ፣ የህንድ በጥጥ ላይ የተመሠረተ የጨርቃ ጨርቅ መለስተኛ የምርት ቴክኖሎጂ ድንበር ተሻጋሪና ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰ ነበር፡፡ አሁንም በዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አርሶ አደሮች ይዞታ ከሚዘሩ የገቢ ምንጭ ማስገኛ አዝርዕቶች መካከል ጥጥ ሰፊውን ቦታ ይይዛል። ከላይ በጠቀስኳቸው ጥናቶች እንደተመለከተው የዘር ውርሱ እንዲመች ተደርጎ የተለወጠው ጥጥ ወደ ዝቅተኛና መለስተኛ ገቢ ያላቸው የህንድ ገበሬዎች ማሳ እንደገባ፣ ከአገር በቀሉና በአርሶ አደሩ እጅ ከነበረው የጥጥ ዝርያ ጋር ሲወዳደር በእርግጥም እጥፍ የምርት ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
ይህም የምርት ዕድገት ሲያሽቆለቁል ለስድስት ዓመታት መቀጠሉ ይህ “ተዓምረኛ” እና ስኬታማ የጥጥ ዝርያ በበዙ ሚሊዮን የሚሆኑ የህንድ አርሶ አደሮችን ቀልብ ሊስብ ችሏል። ከዚህም የተነሳ ከፍተኛ የባንክ ብድር በመውሰድ ይህንን የጥጥ ዝርያ ተቀብለውትና ሌሎች የምግብና የገቢ ምንጭ የሆኑትን አዝርዕቶች በመተካት አስፋፍተውት ነበር። ለ20 ዓመታት የተሰበሰበው መረጃ በሚገባ ሲመረመር ግን እውነታው ሌላ ሆኖ ተገኝቷል። ከስድስት ምርታማ ዓመታት በኋላ የምርት ማሽቆልቆል ተከስቷል። ይኸው የዘር ውርሱ የተለወጠ ጥጥ ድርቅን የመቋቋም አቅሙ እየመነመነና እንደ (Pink Bollworm, Mealybug, Aphids, and Other Sucking Insects Like Leafhoppers) በመሳሰሉት የተባይና በሽታ ዓይነቶች መጠቃት ብቻ ሳይሆን፣ ለእነዚህ በሽታዎች የመፈልፈያና መራቢያ ቋት እስከ መሆን ደርሷል።
እንደ አዲስ የተከሰቱትን የተባይና በሽታ ዓይነቶች ለመቋቋም ከፍተኛ ብርታትና መጠን ያለው መድኃኒት መጠቀም ስለሚጠይቅ ከምርት ማሽቆልቆሉ ጋር ተደርቦ፣ አርሶ አደሮቹን በወጪ ደረጃ ለተጨማሪ ኪሳራ ዳርጓቸዋል። የህንድ የጥጥ ዝርያ የነበረውን የተፈጥሮ ብዝኃነት እስከ ማውደም ከመደረሱ ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ሌላ መውጫ አማራጭ በማጣቱ፣ ይህንኑ ጥጥና የተባይ መከላከያ በማምራት ሞኖፖሉ በእጃቸው ለሚገኝ ኩባንያዎች ጥገኛ ሆኗል፡፡ በጤና ላይ ያስከተለው ጉዳት ይህ ነው የማይባል በመሆኑ ለጤና ጠንቅ የተጋለጡ የህንድ አርሶ አደሮች፣ በጥጥ ማሳው ላይ መድኃኒት በመርጨት ተቀጣሪ የነበሩ ወጣት ሴቶችና እናቶች የፅንስ መጨናገፍ በተደጋጋሚ እየደረሰባቸው የገዛ ሕይወታቸውን እስከ ማጥፋት እንደ ደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ግዙፍ ጉዳቶች ባሻገር ለሃያ ዓመታት ያህል የተሰበሰበው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የምርት ዕድገት በተከታታይ ለስድስት ዓመታት ተመዝግቦበታል የተባለውም የግብርና ሥነ ምኅዳር ቢሆን ህንድን እንደ አገር የማይወክል ነበር። በሌሎች በአገሪቱ የተለያዩ የግብርና ሥነ ምኅዳር ተሞክሮ የተገኘው ውጤት ስኬታማነቱን የሚያፈርስ እንጂ የሚደግፍ ባለመሆኑ፣ ይህንን ጥጥ አጠቃሎ አገራዊ መፍትሔ አድርጎ ለማቅረብ የሚያስችል አልነበረም፡፡ ከእጥፍ በላይ የምርት ዕድገት ተመዘገበበት በተባለው የግብርና ሥነ ምኅዳር ላይም ቢሆን ለረዥም ጊዜ ተከታታይ የጥናት ክትትል ተደርጎ በቂ መረጃ ያልተሰበሰበበት ነበር። ይህም ቢሆን የምርት ዕድገት ብቻውን በተናጠል ተወስዶ ድምዳሜ ላይ የተደረሰበት ነበር፡፡ ከሌሎች መለኪያዎች ጋር ተቀናጅቶ ያልቀረበ በመሆኑ የምርት ተመን በራሱ ለምርታማነት የስኬት መለኪያ ተደርጎ መወስድ የማይገባውና አሳሳች ድምዳሜ እንደ ነበር ከላይ የጠቀስኳቸው ጥናቶች መስክረዋል።
ይህም ቢሆን የምርት ዕድገት በተከታታይ ዓመታት አስመዘገበ የተባለው አካባቢ የህንድ ገበሬዎች ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ የተፈጥሮ ማዳበሪያን የማዘጋጀት፣ የማከማቸትና የመጠቀም ባህል ያላቸው በመሆኑ የምርቱ ዕድገት ከራሱ የዘር ውርሱ ከተለወጠው ጥጥ ብቻ የተገኘ፣ ወይም የማዳበሪያው ዕገዛ ተጨምሮበት ይሁን አይሁን ማረጋገጥ እንደማይቻል ጥናቱ አስምሮበታል፡፡ ከሁሉም የሚገርመው ከአንድ ውስን ከሆነ የአካባቢ ሥነ ምኅዳር ተነስቶ ያውም በበቂ መረጃ ሳይረጋገጥ በርካታና ውስብስብ በሆኑት የተለያየ ተፈጥሮ፣ የግብርና ባህልና ችግር ላለባቸው ሥነ ምኅዳር እንደ ጅምላ (Blanket) መፍትሔ ተወስዶ፣ አርሶ አደሩ እንዲቀበለው መደረጉ በህንድ የህንድ ጥጥ ግብርናና ሥነ ምኅዳር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለመድረሱ ምክንያት ሆኗል።
አንዳንድ የህንድ ሳይንቲስቶች የዘር ውርሱ በተለወጠ ጥጥ ላይ የተደረደረው ወቀሳ ሚዛኑን የሳተ ነው በሚል የራሳቸውን መከራከሪያ ያቀርባሉ። እነሱ እንደሚሉት በርካታና የአቅርቦት ምንጫቸውን በትክክል ማረጋገጥ የማይቻል ጥጥ ወደ ግብርናው ሥነ ምኅዳር በመግባታቸው፣ የትኞቹ ትክክለኛ የትኞቹ ደግሞ በማስመሰል (Counterfeit) የተፈበረኩ እንደሆኑ ሳይጣራ በጅምላ የዘር ውርሱ በተለወጠ ጥጥ ላይ የጨለመ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ አይደለም የሚል ነው። ይህም ሆኖ እነዚህ ወገኖች ትክክለኛ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰጣቸውም ጥጥ ቢሆኑ፣ ከተወሰነ ዘመን በኋላ የምርት ማሽቆልቆልም ሆነ ለአዲስ ዓይነት በሽታ ተጋላጭ የሆኑበትን ምክንያት ለመደበቅ አልሞከሩም። ከመጀመርያውም ቢሆን የዘር ምህንድስናው ስህተት እንደነበረው ተረድተናልና ዕድሉ ተሰጥቶን ከስህተቱ በመማር ችግሩን እንድንፈታ፣ ተጨማሪ የምርምር ዕድል ሊከፈትልን ይገባል እንጂ ዕገዳ ሊደረግብን አይገባም የሚል ነው።
በማስመሰል የተፈበረኩና የተመረቱ ጥጥና በቆሎ ወይም የምግብና መድኃኒት ዓይነቶችን የህንድ ገበያን ማጥለቅለቃቸውና በአርሶ አደሩ ላይ ኪሳራ ብቻ ሳይሆን፣ የጤና እክልና ራስን በራስ እስከ ማጥፋት የደረስ ችግር መከስቱና ከእዚያም አልፎ የጥጥ ዝርያ ብዝኃነትን በማጥፋት አማራጭ እስከ ማሳጣት የደረሰ ሁኔታ ሲፈጠር፣ የአገሪቱን የባዮ ሴፍቲ መመርያ (Biosafety Regulation) ለማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለባቸው ወገኖች የት ነበሩ? የሚል ጥያቂ ማስነሳቱ አልቀረም። ህንድ እንዲህ ዓይነት አጣብቂኝ ውስጥ ከወደቀች የእኛስ ዕጣ ምን እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም።
እነዚህ የዘር ውርሱ የተለወጠ ጥጥ አሻሻጮች ይህ ዝርያ ባስከተለው መዘዝ በሴቶች ላይ የፅንስ መጨናገፍም ቢሆን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ከማድረግ ጉድለት፣ የተከሰተ ነው በሚል ይህ አደጋ ያጋጠማቸውንና ሕይወታቸውን እስከ ማጥፋት የደረሱትን ወጣት ሴቶችና እናቶች መልሶ ተጠያቂ በማድረግ የGM (Bt) Cotton) ጥጥ አምራች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን ከተጠያቂነት ነፃ እንዲሆኑ ተከራክረዋል። አልፎ ተርፎም በህንድ የታየውን ራስን በራስ እስከ ማጥፋት የተደረሰበትንም ክስተት በተመለከተ የፀረ የዘር ውርስ ለውጥ አክቲቪስቶችና የአረንጓዴ ልማት ንቅናቄ መሪዎችውን ችላ በማለት ውድቅ አድርገውታል። ለዚህ ያቀረቡትም መከራከሪያ በህንድ የታየው ራስን በራስ የማጥፋት ክስተት በሌላው ዓለም ራስን በራስ ከማጥፋት ጋር ከተያያዙ ውስብስብ ችግሮች ጋር የተገናኘ እንጂ፣ ይህ ጥጥ ያስከተለው ኪሳራ፣ የእርሻ መሬታቸው ወደ ምድረ በዳነት መቀየርና ለችግር ጊዜ ያስቀምጡትና ከዘመን ዘመን ሲያገላብጡት የኖረው የጥጥ ዝርያ ውድመትና የተባይና በሽታ መቆጣጠሪያው መድኃኒት ያስከተለው የጤና ችግር በራሱ ምክንያት ሊሆን አይችልም የሚል ነው።
ይህ ጉዳይ በህንድ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ተከራካሪዎችንና የዚህን ጥጥ አምራች ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እስከ ፍርድ ቤት ያደረሰ ጉዳይ ሲሆን፣ እስከ ቅርብ ድረስም ቢሆን ረቺና ተረቺ የሌለውና መቋጫ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው። በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አስተያየት የፈረጠመ ዓለም አቀፍ (Global) የገንዘብና የፖለቲካ ጉልበት ያለውን በሎቢስቶች የተደገፈ እንደ ሞሳንቶ የመሰለውን ኩባንያ በሕግ ፊት በመርታት ፍትሕ እናገኛለን ማለት ዘበት ነው።
የዘር ውርሱ የተለወጠ ጥጥ አሻሻጮች እንደሚሉት ከላይ የተጠቀሱት በህንድና በሌሎችም አፍሪካ አገሮች የታዩት እንደ (Pink Bollworm, Mealybug, Aphids, and Other Sucking Insects Like Leafhoppers) የመሳሰሉት የበሽታ ዓይነቶች በቻይና፣ በአውስትራሊያ፣ በካናዳ አልተከሰተም ባዮች ናቸው። ያልተከሰተበትን ምክንያት ሲዘረዝሩ እንደ ህንድና በርካታ የአፍሪካ አገሮች ሐሰተኛ (Counterfeit) የዘር ዓይነቶች በብዛት የሚገቡበት ዕድል ባለመኖሩና የባዮ ሴርቲ ሕግና ቁጥጥር ተቋማት በሚገባ የተዘረጉና ለምንም ዓይነት ልልነትም ሆነ ሙስና ያልተጋለጡ በመሆናቸው ነው የሚል ነው። ይህንን ምክንያት እንደ እውነት እንውሰደው ብንል ኢትዮጵያን በመሰለች አገር፣ አንድ ጊዜ በዘረመል ምህንድስና ላይ የተጣለው ዕገዳ ቢነሳ ሊያጋጥም የሚችለውን ችግር ማሰብ አያዳግትም። የቻይና፣ የአውስትራሊያና የካናዳ ስኬት ሊገርም አይገባም፡፡ ምክንያቱም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ይጨምራል፡፡
የጥጥ እርሻው የተያዘው ከፍተኛ የካፒታል አቅም ባላቸው ባለ ሰፋፊ የእርሻ ባለቤቶች መሆኑ ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የገቢም ሆነ የኑሮ መሠረታቸው በዚሁ በጥጥ ተክል ላይ ብቻ ያልተመሠረተና በየዓመቱ ሌላም ዓይነት ሰብል የሚያመርቱ፣ በጠንካራ ማኅበር የተደራጁና የተኮረጀ ወይም ጊዜ ያለፈበት ዝርያም ሆነ የተባይና በሽታ መከላከያ መድኃኒት ወደ ማሳቸው እንዳይገባ፣ ዕውቀቱም የሚቆምላቸውም ተከራካሪ ያላቸው መሆናቸው ተጠቅሷል።
አንድ የጥጥ ዝርያን ለማጥቃት የሚፈለፈለውን በሽታ ለመግታት፣ የመሬቱን ምርታማነት ከማሽቆልቆል ለመጠበቅ እንዲያስችላቸው በበቂ በማፈራረቅ፣ ወይም መሬቱን ለተወሰነ የምርት ዘመናት በማሳደር (Fallow) የምርት ማሽቆልቆልን ለመግታትና የበሽታው የመፈልፈያ አዙሪት ለመስበር አስችሏቸዋል፡፡ በሽታውም ቢያጋጥማቸው ማዳበሪያም ሆነ የተባይና በሽታ መከላከያውን በሆነው ዋጋ የመግዛት አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ምርቱ የሚሰበሰብበትም እንደ ህንድና የአፍሪካ ጥጥ አርሶ አደሮች በሰው እጅ ሳይሆን፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመጠቀምና አልፎ ተርፎም ራሱን ችሎ እንደ ሮቦት በጥጥ ማሳው ላይ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ (Strippers and Pickers) ያለው መሰብሰቢያ (Cotton Harvester) የተገጠመለት በመሆኑ የጥራት ችግር አይገጥማቸውም፡፡
ከዓለም አቀፍ የጥጥ አቅርቦት ሰንሰለት (Supply Chain) ጋር ጠንካራ ትስስር ስላላቸው የጥጥ ምርታቸው በዓለም ገበያ ተመራጭና አትራፊ አድርጓቸዋል። የቡርኪና ፋሶም ሆኑ የህንድ ደሃ ገበሬዎች የጥጥ ማሳቸውን በየምርት ዘመኑ የማፈራረቅ፣ ወይም ለአንድ ዓመት እንኳን የማሳደር አቅም የላቸውም፡፡ የጥጥ እርሻቸው እንደ ቡና፣ እንሰትና ሌሎችም (Tree Crops) አንድ ጊዜ የተተከሉና በየዘመኑ ምርት የሚሰበስቡባቸው (Perennial Crop) እንጂ፣ እነሱን አስወግደው በሌላ የምግብ ዋስትና ወይም የገቢ ማስገኛ አዝርዕት በመተካት የተባይና በሽታ የመፈልፈያውን አዙሪት መስበር የሚችሉ አይደሉም። ለምርታማነት የሚያስፈልጉትንም ግብዓቶች ለመሸመትም ሆነ የዘመነ (Agronomic Practice) ለመጠቀም እንዲችሉ፣ የመንግሥት ኤክስቴንሽን ድጋፍ በበቂ የማያገኙ ናቸው።
ይህ በራሱ ለምርት ማሽቆልቆልም ሆነ ምርቱ በበሽታ ለመጠቃት ያጋለጠ መሆኑ ሲታወቅ፣ ማዳበሪያና የተባይ በሽታ መቆጣጠሪያ መድኃኒት የመግዣ አቅም የሌላቸው፣ በሰው ጉልበት ካልሆነ በስተቀር መለስተኛ የሰብል መሰብሰቢያ መሣሪያ መግዛትና መጠቀም የማይችሉ ገበሬዎች ይህንን ብዙ ወጪና ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ዝርያ እንዲቀበሉ ማድረግ መሠረታዊ ስህተት እንደነበረው፣ የቡርኪና መንግሥት በመገንዘብ ዕገዳ አድርጎበታል። ህንድ ደግሞ መውጫው የማይታወቅ አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለችና ድምፅ አልባ በሆኑት ደሃ ገበሬዎችና የዚህ የዘር ውርሳቸው የተለወጠ አዝርዕት (GMO)፣ ማዳበሪያና መድኃኒት አቅራቢ ኩባንያዎችና የጥቅሙ ተካፋይ የሆኑ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በፍርድ ቤት እንደ ተፋጠጡ አሸናፊውና ተሸናፊው በውል ባለየበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡ (ክፍል ሦስት ሳምንት ይቀጥላል)
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሲኒየር ሶሻል ሳይንቲስት ደረጃ የቀድሞ ዓለም አቀፍ ግብርናና ልማት ድርጅት ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡