Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ልማት ባንክ ከ290 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የወለድ ቅናሽ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የብድር ወለዱ ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ ተደርጓል 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ በተበዳሪ ደንበኞቹ ላይ የደረሰውን ጫና ለመቀነስ የሚረዳ የብድር ወለድ ቅናሽ ማድረጉን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ስለወለድ ቅናሹ እንዳስታወቀው፣ በወረርሽኙ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ለተባሉ ተበዳሪዎች ከዚህ ቀደም በ11.5 በመቶ ሒሳብ ያቀርብ የነበረውን የብድር ወለድ ምጣኔ ወደ 7.5 በመቶ ዝቅ አድርጎላቸዋል፡፡ ከዚህ ውጭ ላሉ ዘርፎች ከሚያዝያ እስከ ሰኔ 2012 ዓ.ም. የወለድ ምጣኔው ወደ 8.5 በመቶ እንዲወርድ መወሰኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ እንዲህ ያለውን የወለድ ማስተካከያ በማድረጉ ከ480 ሚሊዮን ብር በላይ የወለድ ገቢ ያሳጣው እንደነበር የባንኩ ፕሬዚዳንት ጠቅሰው፣ ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከልማት ባንክ ማግኘት የነበረበትን የመጠባበቂያ ክምችት ገንዘብ መጠን በግማሽ እንዲቀንስ በማድረጉ ሳቢያ፣ ልማት ባንክ ሊያጣ የነበረውን የገቢ መጠን በግማሽ ያህል ዝቅ እንዳደረገለት አብራርተዋል፡፡

በመላው ዓለም ብሎም በኢትዮጵያ በተንሰራፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከልማት ባንክ ብድር ወስደው ወደ ሥራ የገቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳረፈባቸው የገለጹት አቶ ኃይለየሱስ፣ የልማት ባንክ ቦርድ ይህንን ውሳኔ ሲወስን ደንብኞቹ ላይ የደረሰው ጉዳት ምን ያህል እንደሆነና ምን ዓይነት ድጋፍ ሊደረግላቸው ይገባል የሚሉ ጉዳዮችን ለመመርመር የተበዳሪዎችን ፋብሪካዎች በመጎብኘት ጭምር ማድረግ ስለሚገባው ድጋፍ የመስክ ምልከታ እንዳካሄደ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የብድር ወለድ ቅናሽ መደረጉን ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

ደንበኞች የደረሰባቸውን ጉዳት ለማካካስ የሚያስችል ኪሣራን ሙሉ በሙሉ መጋራት ባይችል እንኳ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ችግራቸውን ለመጋራት የወለድ ምጣኔ ማስተካከያ እንደተደረገ አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ ያደረገው የወለድ ምጣኔ በሁለት መንገድ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አንዱ በወረርሽኝ በቀጥታ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው በሚል የተለዩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት ባንኩ የብድር ክፍያ ጊዜ ማራዘሚያን አስመልክቶ፣ የባንኩ እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 1 ቀን 2020 ጀምሮ ለአንድ የብድር ጊዜ (ለሦስት ወር) እንዲራዘምላቸው መደረጉን፣ የወለድ ክፍያ ማራዘሚያን አስመልክቶ፣ ጊዜው የደረሰና ወለድ ለመክፈል አቅም የሌላቸውን ደንበኞች ዋናው ብድር ላይ ሳይደመር ለአንድ የብድር ክፍያ ጊዜ እንዲራዘምላቸው መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ከዚህም ሌላ የወለድ ቅጣት ክፍያ እንዳይታሰብ፣ ይህ ውሳኔ የሚመለከተው የብድር ማራዘሚያ የተሠራላቸው ነገር ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት መክፈል የሚገባው ተከታታይ ክፍያ መጠን እስኪከፍል በተበላሸ ብድር ውስጥ የሚያዙ ብቻ ናቸውም ተብሏል፡፡ ይህም ተግባራዊ የሚደረገው እንዲሁ ለአንድ የክፍያ ጊዜ መሆኑን የሚገልጸው የባንኩ መረጃ፣ የወለድ መጠን ቅነሳን አስመልክቶ በኮቪድ-19 ምክንያት በልዩ ሁኔታ ጉዳት ለደረሰባቸው ፕሮጀክቶች በተለይም የሆቴል የዶሮ ዕርባታና የቱር ኦፕሬተር ኢንዱስትሪዎች የወለድ መጠናቸው ወደ 7.5 በመቶ ተቀንሶ እንዲስተናገዱ ውሳኔ መተላለፉንም አመልክቷል፡፡

እነዚህ  ውጭ ያሉ ፕሮጀክቶች ወይም ቢዝነሶች ደግሞ የወለድ መጠናቸው ወደ 8.5 በመቶ ቀንሶ እንዲስተናገዱ ውሳኔ መተላለፉንም መረጃው አመልክቷል፡፡ ከዚህ ሌላ የሥራው ማስኬጃ ተጨማሪ ብድርን አስመልክቶ፣ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ የሚያቀርቡ የአበባና ጨርቃ ጨርቅ አምራቾች ምርቶቻቸውን በኮቪድ-19 ምክንያት መላክ ባለመቻላቸው የደረሰባቸውን ጉዳት ባንኩ ተመልክቶ ባለው አሠራር መሠረት ተጨማሪ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲሰጣቸው ፈቅዶላቸዋል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ለእነዚህ ቢዝነሶች ደንበኞች ኤልሲያቸው ያለምንም ክፍያ እንዲራዘምላቸው መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባንኩ በጥቂት የወለድ ምጣኔን ከመቀነስ ሌላ ወረርሽኙን ከመከላከል የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን (ሳኔታይዘርና አልኮል) አከፋፍሏል፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን አድሏል፡፡ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት አመቻችቷል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ፣ ቫይረሱ የሚያደርገውን ወረርሽኝ ለመከላከል እንዲቻል በአገር አቀፍ ደረጃ ለተቋቋመው የኮቪድ-19 ግብረ ኃይል የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉንም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡

ለባንኩ ደንበኞች፣ ባንኩ የራሱን የፕሮጀክት ማገገሚያ ሥልቶችን በማዘጋጀትና ጤናማ የሆኑ ፕሮጀክቶች በመለየት፣ በባንኩ ሥራ አስፈጻሚና ሥራ አመራር ቦርድ ታይተው ተገቢው ድጋፍ እንዲደረግላቸውና የልዩ ልዩ ማሻሻያዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ውሳኔዎች መተላለፋቸውንም የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች