Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን 15 መንገዶችን ከ25 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ሊያስገነባ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን 25.8 ቢሊዮን ብር በጀት የሚጠይቁ 15 መንገዶችን ለማስገንባት ከአገር ውስጥና ከውጭ ተቋራጮች ጋር ስምምነት ፈረመ፡፡ የሁሉንም መንገዶች ወጪ መንግሥት በራሱ በጀት እንደሚሸፍን አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ 1,022 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ 15 መንገዶችን ለማስገንባት በወጣው ጨረታ መሠረት ሰባት የአገር ውስጥና ሦስት የቻይና ተቋራጮች ለሥራው ተመርጠዋል፡፡ ሐሙስ፣ ሰኔ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በባለሥልጣኑ ጽሕፈት ቤት ከተፈረሙት 15 የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ 11ዱን የአገር በቀል ተቋራጮች ወስደዋል፡፡ ሰባቱ አገር በቀል ተቋራጮች በጠቅላላው 786 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ 11 መንገዶችን ለመገንባት ያሸነፉበት የጨረታ ዋጋ 16.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

የተቀሩትን አራት መንገድ ለመገንባት ጨረታ አሸንፈው ስምምነት የፈረሙት ሦስት የቻይና ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ የተረከቧቸው ፕሮጀክቶች ዋጋም ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ ናቸው፡፡ የቻይና ተቋራጮች 236 ኪሎ ሜትር የሚረዝሙ የአራት መንገዶች ለመገንባት ተስማምተዋል፡፡

የአገር ውስጥ ተቋራጮች አብላጫውን የግንባታ ሥራ በመረከብ ጎልተው በታዩበት አዲስ የግንባታ ስምምነት ላይ አራት የአገር ውስጥ ተቋራጮች ሁለት ሁለት መንገዶችን ተረክበዋል፡፡ ሁለት ተቋራጮች ለመጀመርያ ጊዜ ከባለሥልጣኑ ጋር ለመሥራት ውል ማሠር ችለዋል፡፡

በዕለቱ ከ15ቱ ፕሮጀክቶች የሁለት ፕሮጀክቶችን ጨረታ በማሸነፍ ውለታ ከፈጸሙት ውስጥ ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን የተሰኘው ኩባንያ አንዱ ነው፡፡ ኩባንያው ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ መንገድ ግንባታ መመለስ የቻለበት ስምምነት ነው፡፡ ዲኤምሲ ኮንስትራክሽን የተረከባቸው መንገዶች ከፓዌ መገንጠያ-ጉባ (ማንኩሽ ከተማ) ሎት ሁለትና ጂጋ-ቋሪት ዓረብ ገበያ-ቲሊሊ ኮንት ሁለት ዓረብ ገበያ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ነው፡፡ እነዚህን 69.8 እና 62 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸውን ሁለት መንገዶች ለመገንባት በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 2.93 ቢሊዮን ብር ነው፡፡

የዲኤምሲ ወደ መንገድ ግንባታ መመለሱን በማስመልከት የኩባንያው ባለቤት አቶ ዳንኤል ማሞ ቀደም ሲል ኩባንያቸው በተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መሳተፉን አስታውሰው፣ ከዚያ በኋላ ግን በደረሰብን ከፍተኛ ተፅዕኖ ምክንያት ብዙ ሠራተኛ እንድንበትንና ከሥራው እንድንርቅ ተደርገን ነበር ይላሉ፡፡ ‹‹አሁን መንግሥት ወደ ሥራ እንድንገባ ስላደረገ እያመሠገንን፣ የእኛ ኩባንያ የሕዝብ ኩባንያ በመሆኑ በዕለቱ የተረከቡትን ሥራ በአግባቡ ጨርሰን እናስረክባለን፤›› ብለዋል

በዕለቱ የሁለት መንገዶችን ጨረታ በማሸነፍ ውለታ የፈረመው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ 61 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን የጉባ በጎንደር-ወንበራ ኮንት አንድ አይሲድ-ኮንግ መንገድ በጠጠር ለመገንባት ያሸነፈበት ዋጋ 201.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ሌላው የተረከበው መንገድ ደግሞ 91.8 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለውን ሎት ሁለት-ስዮሽነን ጉደር መንገድ ነው፡፡ ይህንን መንገድ ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈበት ዋጋ 3.64 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ዮቴክ የተባለው ሌላው አገር በቀል ኮንትራክተርም በተመሳሳይ የሁለት መንገድ ግንባታ ሥራዎችን የተረከበ ሲሆን፣ እነዚህን መንገዶች በጥቅሉ በ2.31 ቢሊዮን ብር የሚገነባቸው ናቸው፡፡ ዮቴክ የተረከባቸው መንገዶች ኦሞ-ማጂ-ሎ አንድ አምሳይና ተንታ-ጋሸና ኮንት ሁለት ኩርባ መገንጠያ (ጨጎማ) – ጋሸና መንገዶችን ነው፡፡

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር የመጀመርያን የግንባታ ሥራ ለመሥራት ውለታ በመግባት የመጀመርያው መሆኑ የተነገረለት ወላቡ ኮንስትራክሽንም በዕለቱ በድምር ከ2.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቁትን የነጂ-ጃርሶ-ቤን-ያያሎት አንድ ነጂ-ኪሎ ሜትር 66 እና ያቤ ሎት ሦስት ደርሚ-ከንቲቻ-ካኪሻ መንገዶችን ለመገንባት ውለታ የፈጸመ ሌላው አገር በቀል ኮንትራክተር ሆኗል፡፡

በዕለቱ ከውጭ ኮንትራክተሮች ሁለት የግንባታ ሥራዎችን ለመሥራት የተዋዋለው ቻይና ሬልዌይ ሰባተኛ ግሩፕ የተባለው የቻይና ተቋራጭ ሲሆን፣ ደንቢዶሎ-ሙግሒ ጋምቤላ ሎት አንድ ደንቢደሎ-ሙግሒ-ዶሎ የተሰኘውን የመንገድ ፕሮጀክትና የሻሸመኔ ሃላባን መንገድ በ1.6 ቢሊዮን ብርና በ2.9 ቢሊዮን ብር ለመገንባት ተስማምቷል፡፡

ቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ቻይና ውዩ የተባሉት የቻይና ተቋራጮች፣ ያሶ-ገላሳ-ደባቴ ሎት አንድ አንድ ያሶ-ኪሎ ሜትር 100ን እና ድሬዳዋ ሸኒሌ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ መረጃ እንደሚያሳየው የድሬዳዋ-ሼኒሌ 17 ኪሎ ሜትር መንገድ በ1.3 ቢሊዮን ብር የያሶ-ገላሳ-ደባቴ ሎት አንድ ያሶ-ኪሎ ሜትር 100 ደግሞ በ3.2 ቢሊዮን ብር የሚገነቡ ናቸው፡፡

ሁለት ሁለት ፕሮጀክቶችን ከወሰዱት አራት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች ሌላ በዕለቱ አንዳንድ የግንባታ ሥራዎችን የተረከቡት ኮንትራክተሮች ደግሞ የመከላከያ ኮንስትራክሽን፣ የኦሮሚያ መንገድ ሥራ ኮንስትራክሽን የኢንተርፕራይዝና አፈወርቅ ግደይ ጄኔራል ኮንስትራክሽን ናቸው፡፡

ከእነዚህ ኮንትራክተሮች ውስጥ የኦሮሚያ ሥራ ኢንተርፕራይዝ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ሥራ ለመጀመርያ ጊዜ የተረከበ ስለመሆኑ ታውቋል፡፡ በዕለቱ እንደተገለጸውም አንዳንድ የመንገድ ሥራ ከተረከቡት ውስጥ የመከላከያ ኮንስትራክሽን የጉሊስ ጮሊያ መንገድን በ2.24 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን፣ የኦሮሚያ መንገድ ሥራ ኢንተርፕራይዝ ደግሞ የመቱ ተላላፊ መንገድን በ661.7 ሚሊዮን ብር ይገነባሉ፡፡ አፈወርቅ ግደይ የተባለው ኮንትራክተርም የዶዶላ-ደቡብ ዋሼ-ጉባ መንገድን ከፍተኛ ጥገና ለመጠገን 202.7 ሚሊዮን ብር ለመሥራት ተስማምቷል፡፡

ግንባታቸው እንዲጀመር ስምምነት የተደረሰባቸው መንገዶች የስትራክቸር ሥራ፣ የአነስተኛ መፋሰሻ ትቦና ድልድዮች ሥራንም ያካተተ ነው፡፡ ተቋራጮቹ የተረከቧቸውን መንገዶች ገንብቶ ለማጠናቀቅ ከሦስት ዓመት አንስቶ እስከ አራት ዓመት የጊዜ ገደብ መንገዶቹ ተገንብተው ሲጠናቀቁ ለመኪኖች ደኅንነት ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ከዚህ ቀደም ይወስድ የነበረውን የጉዞ ጊዜ በማሳጠር በቂ የሆነ የመንገድ መሠረተ ልማት የሌለውን የአካባቢው ኅብረተሰብ የመንገድ ተጠቃሚ በማድረግ የነበረውን የትራንስፖርት ችግር በእጅጉ ያቃልለታል፡፡

በግንባታው ወቅት ለአካባቢው ኅብረተሰብ ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል፣ የግብርና ምርቶችን ወደ ገበያ በማውጣት የገበያ ተደራሽነትን ያቀላጥፋል፣ የከተሞች የእርስ በርስ ትስስርን ያጠናክራል፣ የጤና፣ የትራንስፖርትና የሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎቶች ሰጪ ድርጅቶችን ተደራሽነት ያቀላጥፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአካባቢው ማኅበረሰብ ኑሮና በኢኮኖሚው ዕድገት ላይ ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጡ እንደሚችሉም ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

በአጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ መገንባት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳለጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የራሱን ጉልህ ሚና እንደሚሆኑ የሚጠቅሰው የባለሥልጣኑ መረጃ፣ ይህ መንገድ በተያዘለት የጊዜ ገደብና ጥራት እንዲጠናቀቅ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጿል፡፡

 የመንገዱ ግንባታ በሚካሄድባቸው መስመሮች ላይ የሚገኙ የአካባቢ ኅብረተሰብ፣ የመስተዳድር አካልም የመንገድ ተጠቃሚዎች በሙሉ የመንገዱ ግንባታ ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሳያሳስብ አላለፈም፡፡ ባለሥልጣኑ በዚህን ያህል ዋጋ በአንድ ጊዜ 25.8 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸውን ፕሮጀክት ሲፈራረም የመጀመርያው ስለመሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ተገኝ (ኢንጂነር) በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፣ ከፍተኛ ሕዝባዊ ጥያቄ ይነሳባቸው ከነበሩት መንገዶች መካከል ወደ ግንባታ ለመሸጋገር በመብቃታቸው ለአገራችን የኢኮኖሚ ጠቀሜታ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍ ያለ ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ወደፊትም መንግሥት የያዘውን የለውጥ ጎዳና ወደ ስኬት እንዲያመራ ከፍተኛ በጀትን በመጠየቅ የሕዝብ ጥያቄዎችን መመለሱን ይቀጥላል ብለዋል፡፡ ቀደም ብለው ከተፈረሙ መንገዶች መካከል በውላቸው መሠረት የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ 20 ፕሮጀክቶች ወደ ግንባታ እንዲገቡ መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም የ21 የመንገድ ፕሮጀክቶች ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ የተደረገ ሲሆን፣ በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች የሚገኙ 15 ፕሮጀክቶች ወደ ፍጻሜአቸው እየተቃረቡ መሆናቸውን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

‹‹መንገዶቹ ከዚህ ቀደም በጠጠር መንገድ ደረጃ የነበሩ ሲሆን፣ ካላቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታ አንፃር ታይቶ በአሁኑ ወቅት በአስፋልት ደረጃ እንዲገነቡ ታቅዶ የውል ስምምነት ላይ ተደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

በጥቅሉ የመንገድ ፕሮጀክቶቹ የጎን ስፋት በገጠር 10 ሜትር ሲሆኑ በዞን፣ በቀበሌና በወረዳ እንደ አስፈላጊነቱ ተጨማሪ ስፋት ይኖራቸዋል፡፡ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ በታቀደላቸው ጊዜና የጥራት ደረጃ ተገንብቶ እንዲጠናቀቅ ተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍና ቁጥጥር እንደሚያደርግም ኢንጂነር ሀብታሙ አረጋግጠዋል፡፡

የየፕሮጀክቱ አሸናፊ ተቋራጮች በበኩላቸው በተሰጠው የግንባታ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በጥራት አጠናቆ ለማስረከብ ቃል በመግባት ኅብረተሰቡ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

በተለይ በዕለቱ ከተፈረሙት ኮንትራክተሮች ውስጥ አብዛኛዎቹ አገር በቀል ኮንትራክተሮች መሆናቸው፣ መንግሥት ለአገር በቀል ኮንትራክተሮች እየሰጠ ያለውን ዕድል ያመላክታልም ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች