ውሳኔው የሕጋዊ ቅቡልነት ጥያቄ ተነስቶበታል
የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ለማድረግ ያሳለፈውን ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ የሚከለክለው ኃይል ሊኖር እንደማይችል የክልሉ መንግሥት አስታወቀ።
የክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የትግራይ ክልል የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ያልተገደበ ሥልጣን ያለው፣ ምክር ቤቱም የትግራይ ሕዝብ የሉዓላዊነቱ መገለጫ እንደሆነ ገልጿል።
በመሆኑም ምክር ቤቱ ምርጫ እንዲካሄድ ያሳለፈው ውሳኔን ተግባራዊ ከማድረግ የሚከለክለው ምንም ዓይነት ኃይል ሊኖር አይችልም ብሏል።
የክልሉ ምክር ቤት የዘንድሮው ምርጫ ወቅቱን ጠብቆ በክልሉ እንዲደረግ ሲወስን፣ የአገሪቱንና የትግራይ ሕገ መንግሥት ድንጋጌዎችን እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሥልጣንና ኃላፊነትን መሠረት አድርጎ እንደሆነ አስታውቋል።
በኢትዮዽያ ሕገ መንግሥት እንዲሁም በትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሕገ መንግሥት ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል መብት፣ ከምርጫ ውጪ ሥልጣን መያዝ ክልክል ስለመሆኑ፣ የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት፣ እንዲሁም ስለመንግሥት አሠራርና ሕጋዊ ተጠያቂነት የተቀመጡ ድንጋጌዎችን መሠረት አድርጎ መወሰኑን የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጫ ያስረዳል።
በመሆኑም ምርጫውን እንዲያስፈጽምለት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን እንደሚያቀርብ አስታወቋል። የምርጫና የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 1161/2011 የምርጫ ዓይነቶች በሚዘረዝርበት የአዋጁ ክፍል በአንቀጽ 7(2) ሥር ስለጠቅላላ ምርጫ ምንነት ተደንግጓል።
በዚህ ድንጋጌ መሠረት ጠቅላላ ምርጫ ማለት፣ ‹‹በየአምስት ዓመቱ የሚካሄድ የሕዝብ ተወካዮችና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ ነው፤›› ይላል። በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ አንቀጽ ሦስት ላይ ደግሞ፣ ‹‹ጠቅላላ ምርጫ በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ጊዜ ይካሄዳል፣ ሆኖም ቦርዱ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ጉዳዩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ በተለያየ ጊዜ እንዲካሄድ ሊያደርግ ይችላል፤›› ተብሎ ተደንግጓል።
ስለምርጫና አስፈጻሚ አካላት በሚደነግገው ምዕራፍ ሥር ከተቀመጡ ድንጋጌዎች መካከል አንቀጽ 4(2) ሥር፣ ‹‹የክልል ምክር ቤት አባላትን የሚመለከቱ የክልል ሕጎች በሕገ መንግሥቱና በዚህ ሕግ ከተቀመጡ ምርጫን የተመለከቱ ድንጋጌዎች ጋር የተጣጣሙ መሆን ይኖርባቸዋል፤›› የሚል ድንጋጌ ሠፍሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን በሰጠው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ደግሞ የሚከተለውን ወስኗል። ‹‹የኮሮና ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፀንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያትና ከተነሳም በኋላ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ እስኪፈጸም ድረስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል›› የሚል ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ትርጓሜ ሕጋዊነት ላይ የተለያዩ የሕገ መንግሥት ባለሙያዎች ትችት እያቀረቡ ሲሆን፣ የትግራይ ክልልና ክልሉን የሚያስተዳድረው ሕወሓትም ተቃውሞታል።
ሁለቱም ወገኖች በትርጓሜው ላይ ያነሱት መሠረታዊ ጥያቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በክልሎች ሕገ መንግሥትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ላይ የመወሰን መብት የለውም የሚል ነው። ይሁን እንጂ ይህ ትርጓሜ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
የሕገ መንግሥት ትርጓሜን በተመለከተ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣንና ኃላፊነትን ለመዘርዘርና ለማጠናከር የወጣው አዋጅ ቁጥር 251፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚሰጥ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንደ አዲስ የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ወይም ማሻሻያ ድንጋጌ እንደሚታይ ያመለክታል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ አንድ የሕገ መንግሥት ምሁር የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድለት የመወሰን መብት ያለው ቢሆንም፣ አሁን ካለው ነባራዊ የፖለቲካ ሁነት አንፃር ሕጋዊ ቅቡልነት እንደሌለው ገልጸዋል።
‹‹የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን በሰጠው ሕገ መንግሥት ትርጓሜ የክልሎች ሥልጣን እንዲራዘም ለመወሰን የተጠቀመበት የሕግ ትንታኔ፣ ለእኔ ሕገ መንግሥት ለመተርጎም የማያበቃና የማያሳምን መሆኑን በመጀመርያ መግለጽ እፈልጋለሁ፤›› ካሉ በኋላ፣ አሁን ባሉ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ላይ በመመሥረት በትግራይ ክልል ብቻ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የሕግ አግባብ እንደሌለ ጠቁመዋል።
ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታዎች ያሏቸውን ሲዘረዝሩም፣ ‹‹የኮሮና ወረርሽኝ የጤና ሥጋት መሆኑን፣ ሥርጭቱን ለመከላከልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላ አገሪቱ መደንገጉን፣ በዚህም ምክንያት ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ማካሄድ እንደማይችል ማሳወቁና የሥልጣን ዘመናቸውን ያጠናቀቁ ምክር ቤቶች ይህ ችግር እስኪያልፍ ድረስ በሥልጣን እንዲቆዩ የሚፈቅድ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መሰጠቱ ዋነኞቹ ናቸው፤›› ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልል መንግሥታትን የሥልጣን ዘመን እንዲራዘም በማለት የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የሰጠበት መንገድና አመክንዮ አሳማኝ ባይሆንም፣ ነገሩ ተወስኖ የተጠናቀቀና ወደፊት በሚኖሩ አማራጮች ካልሆነ በስተቀር አሁን በይግባኝ መስተካከል የሚችል ባለመሆኑ እንደ ሕግ እንደሚቆጠር ገልጸዋል።
በዚህ ምክንያት ምርጫ ቦርድ የትግራይ ክልልን ጥያቄ ሊያስተናግድ የሚችልበት የሕግ አግባብ አለመኖሩንም አስታውቀዋል። በሌላ በኩል የተሰጠውን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ አልቀበልም ብሎ ምርጫ እንዲካሄድለት የሚፈልግ ክልል ቢኖር እንኳን፣ ከሕገ መንግሥት ትርጓሜ ባለፈ በመላ አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉ ምርጫ ይካሄድልኝም ሆነ አካሂዳለሁ ማለት ቅቡልነት ያለው ሕጋዊ አካሄድ እንደማይሆን አክለዋል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 1፣ 18፣ 25፣ እና አንቀጽ 39 (1 እና 2) በስተቀር ሌሎቹ ድንጋጌዎችና መብቶች የሚገደቡ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ‹‹የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ መካሄድ አለበት ብሎ ሲወስን፣ ክልሎች ራስን በራስ የማስተዳደር የማይገደብ መብት አላቸው በማለት፣ ይኼንን መብት የሚሰጠውን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 በምክንያትነት ማንሳቱና እነዚህ አንቀጾችም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የማይገደቡ መሆናቸው ትክክል ቢሆንም፣ መብቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(3) ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገደብ የሚጣልበት ነው፤›› ብለዋል።
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39(3) ድንጋጌ፣ ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ብሔሩ፣ ብሔረሰቡ፣ ሕዝቡ በሠፈረበት መልክዓ ምድር ራሱን የሚያስተዳድርበት መንግሥታዊ ተቋማት የማቋቋም፣ እንዲሁም በክልልና በፌዴራል አስተዳደሮች ውስጥ ሚዛናዊ ውክልና የማግኘት መብትን ያጠቃልላል፤›› የሚል ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመምረጥና የመመረጥ መብት የሚሰጠው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ገደብ የተጣለበት መሆኑንም አመልክተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ተቃራኒ የፖለቲካ አቋሞችን መግለጽ መብት መሆኑን ነገር ግን ንግግሩን ወደ ተግባር በመቀየር ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል ማስታወቃቸው አይዘነጋም፡፡