Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናኢዜማ ገዥው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀውን አወቃቀር ተቃወመ

  ኢዜማ ገዥው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀውን አወቃቀር ተቃወመ

  ቀን:

  ገዥው ፓርቲ በደቡብ ክልል የተነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያዘጋጀው የክላስተር አወቃቀር ወይም ምደባ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሕገወጥ፣ ደቡብ ክልል ሲዋቀር የተሠራውን ስህተት በመድገም ተመሳሳይ ችግርን በአንድ ዓይነት መፍትሔ ለመቅረፍ የሚሞክር (የትልቁን ደቡብ ችግር ትንንሽ ደቡቦች በመፍጠር ለመፍታት) እና ካለፈው ችግር ትምህርት ያልወሰደ ሒደት ነው ሲል፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አስታወቀ።

  ኢዜማ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና ጥንቃቄ በሚፈልግ በዚህ ወቅት በደቡብ ክልል ራስን በራስ ለማስተዳደር የቀረቡ ግልጽ ጥያቄዎችን በፍፁም መመለስ የማይችል፣ ለችግሩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኝት ዓላማ ያደረገአመፅና ብጥብጥ ለማነሳሳት ለሚሞክሩ ኃይሎች ስንቅ እንደማቀበል የሚቆጠር ነው ሲል የገዥውን ፓርቲ ውሳኔ ተቃውሟል።

  ከምሥረታው ጀምሮ በብዙኃን ቅቡልነት ባልነበረው የደቡብ ክልል አደረጃጀት፣ ክልሉ ከተመሠረተ በኋላ ሲተገበሩ በነበሩ አግላይ ፖሊሲዎች፣ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል ኢፍትሐዊነት፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ዕጦት በብዙ የክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ የክልልነት ጥያቄዎች እንዲነሱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ኢዜማ አስታውሶ፣ ከኅብረተሰቡ ለሚነሱ ጥያቄዎች ቀጥተኛና ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ሲገባ ጊዜያዊና የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈቱ አማራጮችን በማቅረብ፣ የሕዝብን እውነተኛ የፍትሕና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን ማፈን ተገቢ እንዳልሆነ አስታውቋል። ‹‹ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ መሠረታዊ፣ የምንደግፈውና ተግባራዊ እንዲሆን የምንታገልለት ጥያቄ ነው፤›› ሲልም በመግለጫው አስረድቷል፡፡

  ገዥው ፓርቲ ይኼንን ያልታደሰና የመለወጥ ፍላጎት እያሳየ ባልሆነው የካድሬና የባለሥልጣናት መዋቅሩ በደቡብ ክልል እየቀረበ ያለውን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ለማፈን እያደረገ ያለው ሩጫ የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄ የማይመልስ ብቻ ሳይሆን፣ ፓርቲው እያሳየ ያለውን የመብት ሰጪና ነሺነት ፍላጎትንም የሚያሳይ ነው ብሏል። ይህ በየጊዜው ከለውጡ አጠቃላይ መንፈስ  እየራቀ የመጣው የገዥው ፓርቲ ፍላጎት፣ በአገሪቱ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ጭምር ነው ሲል በመግለጫው ኮንኗል።

  ‹‹ገዥው ፓርቲ ከሕግ አግባብ ውጪ በሆነ መንገድ በመብት ሰጪና ነሺነት የሕዝብን ተቀባይነት ለማግኘት የሚያደርገውን ሩጫ በአስቸኳይ እንዲያቆም ኢዜማ አጥብቆ ያሳስባል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በዚህ ምክንያት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ለሚደርስ እያንዳንዱ ጉዳት ቀጥተኛ ተጠያቂ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዩን እየገፋ ያለው ገዥው ፓርቲ እንደሚሆን በግልጽ መታወቅ አለበት፤›› ሲል አስጠንቅቋል።

  ‹‹ኢዜማ ከተመሠረተ ጀምሮ ለአገር መረጋጋትና ሰላም ቅድሚያ በመስጠት የፉክክር ጉዳዮችን ምርጫው ለሚደረግበት ጊዜ አቆይቶ፣ ለሁላችንም የሚበጀውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ከሚፈልጉ አካላት ሁሉ ጋር በትብብር መንፈስ ሲሠራ ቆይቷል። በኢዜማ እምነት ቀጣዩ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ያለው የሽግግር ወቅት በዋነኛነት አገርን ለማረጋጋት፣ ምርጫውን ነፃና ፍትሐዊ ለማድረግ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች ማከናወኛ ነው። ዘላቂ ውጤት ያላቸውን ሥራዎች የሕዝብ ፈቃድ ያላገኘ አስተዳደር፣ የሕዝብ ፍላጎት ሳይታወቅ በዚህ የሽግግር ወቅት ሊተገብር እንደማይገባ በፅኑ እናምናለን፤›› ሲልም አስታውቋል።

  ‹‹በደቡብ ክልል የምትኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ኢዜማ ደቡብ ክልል የሕዝቡን ፍላጎት ባሟላ መልኩ እንደገና እንዲዋቀር እንደሚፈልግ እንድትረዱና ለምታነሱት ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ትክክለኛና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት፣ አሁን ያለንበት ጊዜ እንደማይፈቅድና የእናንተን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ በእናንተው የተመረጡ ወኪሎቻችሁ ሳይኖሩ፣ እኔ አውቅልሃለሁ በሚሉ ካድሬዎች ሊከናወን የሚቻል እንዳልሆነ በመረዳት፣ ቀጣዩ ምርጫ ተደርጎ ፍላጎቶቻችሁን የሚያስፈጽሙ ወኪሎቻችሁን እስክትመርጡና በጥያቄያችሁ ላይ ሰፊ ውይይት አድርጋችሁ በሕዝበ ውሳኔ መወሰን የምትችሉበት ሁኔታ እስኪመቻች፣ በተለመደው ኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ትዕግሥት እንድትጠብቁ አበክረን እንጠይቃለን። ይህንን ተረድታችሁ ለጋራ አገራችን መረጋጋትና ሰላም በማሰብ ጥያቄዎቻችሁን በሰከነ መንገድ ለመፍታት ለምታሳዩት ትዕግሥት ከወዲሁ የኢትዮጵያ የከበረ ምሥጋና ያቀርባል፤›› ሲል ኢዜማ ጥሪውን አቅርቧል።

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...