ግብፅ በድርድሩ ተስፋ ስላጣሁ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እሄዳለሁ አለች
ግብፅ የዓባይ ውኃን በተመለከተ የምታራምደው ግትር አቋም፣ በቅርቡ ለተጀመረው የሦስቱ አገሮች ድርድር እንቅፋት መሆኑን መንግሥት አስታወቀ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ እንዳሉት፣ አምስተኛ ቀኑን ይዞ በነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ግብፅ የራሷን ብቻ ጥቅም ለማስጠበቅ የያዘችው ግትር አቋም ድርድሩን እየተፈታተነ ነው፡፡
ግብፅ በተጀመረው ድርድር ሁለት አካሄዶችን ይዛ ቀርባለች ያሉት አቶ ገዱ፣ አንድ እግሯን ወደ ድርድሩ አንዱን እግሯን ደግሞ ወደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በማድረግ ነው የቀረበችው ብለዋል፡፡
‹‹በድርድሩ ግብፆች የፈለጉትና የጠየቁት ሁሉ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፣ የሚሰጡት ግን የላቸውም፤›› ካሉ በኋላ፣ የጋራ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት መጀመር አትችልም በማለት ተቀባይነት የሌለው ሐሳባቸውን ቀጥለዋል ሲሉ የግብፅን አቋም ነቅፈዋል፡፡
ዳግም በተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድር የመጀመርያ ዙር የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል መሠረታዊ መግባባት መፈጠሩን ኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር፡፡
ሚኒስቴሩ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀትር ላይ ባወጣው መግለጫ፣ የሦስቱ አገሮች ተወካዮች ባሉበት ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንስ ላለፉት አራት ቀናት ሲያካሂዱት በነበረው ድርድር፣ የህዳሴ ግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከቱ ጉዳዮች መሠረታዊ መግባባት መፈጠሩን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
በዚህም መሠረት የመጀመርያው ምዕራፍ የውኃ ሙሌት ለማከናወን በሚያስችሉ መርሆችና መመርያዎች ላይ፣ በሦስቱ ወገኖች ተደራዳሪዎች መካከል መግባባት መፈጠሩን ቢገልጽም፣ የግብፅ አቋም ችግር እየፈጠረ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
የግድቡን ደኅንነት፣ የማኅበራዊና የአካባቢ ጉዳት ግምገማ ጥናትና የመጀመርያ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትን የተመለከቱት መርሆዎችና መመርያዎች ተግባራዊ በሚደረጉበት ሁኔታ ላይ መግባባት መፈጠሩን በመግለጫው ሚኒስቴሩ አመልክቶ ነበር፡፡
ድርድሩ ማክሰኞ ዕለትም ቀጥሎ ለድርድር የቀረበው አጀንዳ በግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ወቅት የድርቅ ሁኔታ ቢከሰት፣ የውኃ ሙሌትና የግድቡ አስተዳደር እንዴት ይተገበራል የሚል እንደሆነ በመግለጫው ጠቁሟል።
በውኃ ሙሌቱ ወቅት የድርቅ ሁኔታ ቢከሰት ሦስቱም አገሮች ድርቁ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቋቋም፣ ይህም በሚሆንበት ወቅት በግድቡ የኃይል ማመንጨት አቅም ላይ ጉልህ ተፅዕኖ በማያደርስ ሁኔታ እንዲፈጸም የማድረግ ኃላፊነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ኢትዮጵያ አቋሟን እንደገለጸች አስታውቋል። ድርድሩ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ያስታወቀው የሚኒስቴሩ መግለጫ፣ ድርድሩ የሚካሄደው የቴክኒክና የሕግ ጉዳዮችን የሚመለከቱ ቡድኖችን አደራጅቶ መሆኑንም ገልጿል።
በዚህም መሠረት የሕግ ቡድኑ መግባባት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ወደ ሕግ ስምምነት የመቀየር ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑን፣ ቡድኑ መግባባት ያልተደረሰባቸውን የሕግ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ረቡዕ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት እንደሚያደርግ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መግለጫ ከላይ የተገለጸውን ከድርድሩ የተገለጹ መልካም ውጤቶችን ቢያስታውቅም፣ የግብፅ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ግን በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ በሚገኘው ድርድር ተስፋ እንደሌላቸው እየገለጹ ነው። ስለድርድሩ አሉታዊ መረጃዎችን እያወጡ ከሚገኙ የግብፅ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የግብርና ሚኒስትሩ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሳሜህ ሽኩሪህ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሄደው የግብፅ ንግድ ምክር ቤት ዓለም አቀፍ ትብብር ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ ሰሞኑን እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ ግብፅ ተስፋ እንደሌላት ገልጸዋል።
በመሆኑም የተሟላ ስምምነት ሳይደረስ የግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት ለመጀመር ኢትዮጵያ መወሰኗ የግብፅን ጥቅም የሚጎዳ ስለሆነ፣ ግብፅ ሰላም ለማስፈን ያለባትን ኃላፊነት ለመወጣት ለሁለተኛ ጊዜ አቤቱታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት እንደምታስገባ አስታውቀዋል።
እየተካሄደ ባለው ድርድር ኢትዮጵያ የድርቅ ወቅት ቢፈጠር ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ የቀረቡ መመርያዎችን ለመቀበል እንዳልፈለገች፣ ድርድሩ የተሟላ ሆኖ ስምምነት ሳይደረስ የውኃ ሙሌት እንደማትጀምር ማረጋገጫ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኗን በዋናነት በማውሳት ወቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት ባወጣችው መግለጫ ግብፅ በአንድ ወገን በድርድሩ ለመሳተፍ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ለመሄድ መወላወሏን አቁማ የልዩነት ምንጭ የሆነውን የቴክኒክ ጉዳይ በሦስትዮሽ የቴክኒክ ድርድር እንድትፈታ ማሳሰቧ ይታወሳል።
ይህንን ድርድር አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና አፍሪካን በመወከል ደግሞ የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሆነችው ደቡብ አፍሪካ በታዛቢነት እየተከታተሉት ነው።