በአዲስ አበባ ከተማ በድብቅ በጫካና በወንዝ ዳርቻዎች ሕገወጥ የእንስሳት ዕርድ በመፈጸም ለልኳንዳ ቤቶች በማቅረብ የተጠረጠሩ በርካታ ግለሰቦችና የልኳንዳ ቤቶች ባለቤቶች፣ በቁጥጥር ሥር ውለው ፍርድ ቤት መቅረባቸው ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤትና የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በጋራ ባደረጉት ጥናትና ክትትል ሕገወጥ ድርጊቱ መፈጸሙን ካረጋገጡ በኋላ፣ ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ከንጋቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች በሚገኙ ልኳንዳ ቤቶች በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ፣ 132 ሕገወጥ ዕርድ ተቀባይ ልኳንዳዎች እጅ ከፍንጅ መያዛቸው ተገልጿል፡፡
ቢሮውና ጽሕፈት ቤቱ ጥናቱን ካጠናቀቁ በኋላ በአሰሳው ላይ የአዲስ አበባ ፖሊስም መሳተፉን ለሪፖርተር የገለጹት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ፣ ምንም እንኳን ሕገወጥ ድርጊት ፈጻሚዎቹን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፀጥታ ዘርፉ የተሳተፈ ቢሆንም ዋናውን ሥራ ያከናወኑት ሁለቱ ተቋማት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤት የያዘው ጉዳይ በመሆኑና ሌሎች ምርመራዎችም ስለሚቀሩ የልኳንዳ ቤቶቹንና የግለሰቦቹን ስም መግለጽም ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡
በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎትና በሌሎች ምድብ ችሎቶች ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸው፣ በተጨማሪ ምርምራ ላይ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ አካባቢ ‹‹ዶሮ ማነቂያ›› በሚሰኘው ሥፍራ ግራና ቀኝ ያሉ ልኳንዳ ቤቶች ከጥቂቶቹ በስተቀር፣ አብዛኞቹ ሕገወጥ ዕርዱን በመቀበል ተጠርጥረው መታሸጋቸውን ሪፖርተር በሥፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡
በሕገወጥ መንገድ ተፈጽሟል በተባለው ዕርድ ከ50 በላይ ከብቶች፣ ከ360 በላይ የፍየልና የበግ ዕርድ ተፈጽሞ በአሥሩም ክፍላተ ከተሞች ለ132 ልኳንዳ ቤቶች መከፋፈሉም ተጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ዕርዱን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አዱኛ ደበላ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ እንደተናሩት፣ ጨለማ ተገን አድርገው ሕገወጥ ዕርድ በመፈጸም ላይ የነበሩ በርካታ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡
ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ የተስፋፋበትና እያንዳንዱ ዜጋ ንፅህናውን እንዲጠብቅ የጤና ባለሙያዎችና መንግሥት በየደቂቃው እያሳሰቡ ባሉበት ወቅት ቫይረሱን ይበልጥ የሚያስፋፋ፣ ንፅህናውን ያልጠበቀና ያልተመረመረ ዕርድ መፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ ድርጊቱ ምርምራ ተደርጎበትና ፍርድ ቤት ቀርቦ የማያዳግም ዕርምጃ እስከሚወሰድ ድረስ፣ 132 ልኳንዳ ቤቶች እንዲታሸጉ መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
አንዳንድ ልኳንዳ ቤቶች አንድ በሬ ቄራዎች ድርጅት ያሳርዱና እሱን ሽፋን በማድረግ፣ ተጨማሪ ዕርድ በመፈጸም ሕጋዊ አስመስለው ለሽያጭ እንደሚያቀርቡም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ኅብረተሰቡን ለጤና ችግር ከመዳረጋቸው በላይ፣ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢም በማሳጣታቸው የሕግ ተጠያቂነት እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ባደረጉት ጥናት በአዲስ አበባ 90 በመቶ የከብት ዕርድና እስከ 30 በመቶ የሚደርሰው የበግና ፍየል ዕርድ በሕገወጥ መንገድ በጫካና በወንዞች ዳርቻ እንደሚከናወን መረጋገጡን አስታውቀዋል፡፡