የትግራይ ክልል ምርጫ እንዲያከናውንለት ለምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቧል
የውይይት መድረክ መፈጠር ካለበት ሁሉም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶችና ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ የፌዴራሊስት ኃይሎች የሚሳተፉበት አገራዊ መድረክ መዘጋጀት አለበት እንጂ፣ ከሕወሓት ወይም ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጋር በድብቅ የሚደረግ ውይይት እንደማይቀበሉና ትርጉም እንደሌለው፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሕወሓት ሊቀመንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡
እሳቸው ይህንን ያሉት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የታዋቂ ሰዎች መማክርት ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ.ም. መቀሌ ከተማ በመሄድ ከትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ጋር በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ አመራሮች መካከል የተፈጠረውን ችግር በውይይት መፍታት እንደሚገባ በገለጹበት ወቅት ነው፡፡
የትግራይ ክልል አመራሮች ከፌደራል መንግሥት አመራሮች ጋር ለአገራዊ መግባባት፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመፍታት በአስቸኳይ ግንኙነት እንዲያደርጉ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል፡፡ አገሪቱ ሰላም እንደሚያስፈልጋትና ሕዝብም ወደ ግጭት መግባት እንደሌለበትና ወደ ልማት መሰማራት እንደሚኖርበት፣ ልዩነቶች ቢኖሩም በውይይት ብቻ መፈታት እንዳለባቸው ማሳሰባቸው ታውቋል፡፡
ደብረ ጽዮን (ዶ/ር) ግን ማንኛውንም የአገሪቱን ችግር ለመፍታት የሚንቀሳቀስ አካል ካለ ችግሩ ወይም ውጥረቱ የተፈጠረው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በማፍረስ በአገሪቱ አምባገናናዊ ሥርዓት ለመገንባት እየተሯሯጠ በሚገኘው ብልፅግና የተሰኘው ቡድንና በኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች እንጂ፣ በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ብቻ የተፈጠረ አለመግባባት አድርጎ መመልከት የለበትም ማለታቸው ተጠቁሟል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ አንድ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ውይይቱ አገራዊ ዕሴቶችን መሠረት በማድረግ በትግራይና በፌዴራል መንግሥት መካከል የሚስተዋሉ መካረሮች በውይይት እንዲፈቱ፣ የሃይማኖት አባቶቹና የአገር ሽማግሌዎቹ ጥያቄ ያቀረቡበት ነው።
መቀሌ የሄዱት የሃይማኖት ተቋማት አመራር አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች የመጡበትን ዓላማ በጽሑፍ አቅርበው ውይይት የተካሄደ መሆኑን አመራሩ ገልጸው፣ በውይይቱ ወቅትም የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የሕወሓት ሊቀመንበር ለፖለቲካ መካረሩ ምክንያት ናቸው ብለው ያመኑባቸውን እንዳስረዱ ጠቁመዋል ብለዋል። ችግሮችን በወይይት መፍታት ተገቢ እንደሆነና የሕወሓትና የክልሉ አመራርም በሩ ለውይይት ክፍት መሆኑን እንዳስታወቁ ገልጸዋል።
ነገር ግን በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት የፖለቲካ አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ እንዳልሆነ፣ በክልሉ አመራሮችና በምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አጽንኦት ተሰጥቶ ለሃይማኖት ተቋማት አመራሮችና የአገር ሽማሌዎች መገለጹን አመራሩ አስታውቀዋል።
በትግራይና በፌዴራል መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት በውይይት ለመፍታት ከሁለቱም ወገኖች የተወጣጣ ኮሚቴ ተቋቁሞ እንደነበር፣ ነገር ግን ባልታወቀ ምክንያት የፌዴራል መንግሥት ወደ ውይይት መግባት እንዳልፈለገ በሌሎች የክልሉ አመራሮችም መገለጹን አስረድተዋል።
በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ መካረር እንዲሰክንና በውይይት ሰላም እንዲሰፍን ለማመቻቸት ወደ ክልሉ ከመጡት አባቶች መካከል በወቅቱ ምላሽ ከሰጡት መካከል የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያው መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር)፣ የልዑካን ቡድኑ ዓላማም ሁሉን አቀፍ መግባባት ለመፍጠር መሆኑን በውይይቱ ወቅት ማንሳታቸውን ጠቁመዋል። በክልሉ የተገኙት የጉዟቸው መጀመርያ በመሆኑ እንጂ ወደ ኦሮሚያና የተቀሩት ክልሎችም እንደሚያመሩ፣ ፕሮፈሰሩ መግለጻቸውን ከአመራሩ ገለጻ ለማወቅ ተችሏል።
ሕወሓት ማክሰኞ አመሻሽ ላይ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፣ የአገሪቱ ችግር የሚፈታው ሁሉን ባሳተፈ ውይይት እንደሆነ ለሃይማኖት አመራሮቹና የአገር ሽማግሌዎቹ መገለጹን አስታውቋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ የበላይ ጠባቂ አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ስለጦርነት አላስፈላጊነት መስበካቸው፣ ስለሰላምና ውይይት መናገራቸው ልክ ቢሆንም፣ ‹‹ይህ ምክር ሊለገሰው የሚገባው ምርጫ አደርጋለሁ ባለው የትግራይ ክልል ላይ ጦርነት ላወጀው ለብልፅግና አመራር ነው፤›› ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ማለታቸው በሕወሓት መግለጫ ተመልክቷል።
በመቀሌ የነበረው ውይይት ሁሉን አቀፍ ውይይት በማድረግ መፍትሔ ለመፈለግ በመስማማት ከቀኑ 10:30 ሰዓት ገደማ መጠናቀቁ ታውቋል። የሃይማኖት ተቋማት መሪዎቹና የአገር ሽማግሌዎቹ በራሳቸው ተነሳሽነት መፍትሔ ለመፈለግ እንደተነሳሱ እንደገለጹ፣ በውይይቱም የፌዴራል መንግሥት ልኳቸው ነው ለማለት የሚያስችል ጠቋሚ ነገር እንዳላስተዋሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ተናግረዋል። የትግራይ ክልል ምክር ቤት ምርጫ ለማካሄድ ሰሞኑን ያሳለፈውን ውሳኔ የተመለከተ ውይይት በወቅቱ እንዳልተካሄደም አክለዋል።
የትግራይ ክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ ያሳለፈውን ውሳኔ በተመለከተ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ ውሳኔውን እንዲያስፈጽም የሚጠይቅ ደብዳቤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መላኩን አረጋግጠዋል።
የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አመራሩ በተላከው ደብዳቤ ላይ ምርጫ ቦርድ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥበት መጠየቁን አስረድተዋል። ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ተቀብሎ በክልሉ ብቻ ምርጫ ለማድረግ እንደማይችል ምላሽ ቢሰጥ የክልሉ ምክር ቤት ቀጣይ ውሳኔ ምን እንደሚሆን ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱም፣ ‹‹እንደዚያ የሚሆን ከሆነ የክልል ምክር ቤት በክልሉ ምርጫ የሚያስፈጽም ተቋም እንዲቋቋም ውሳኔ እንዲሰጥ ይቀርብለታል። የክልሉ መንግሥት ካቢኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ቀድሞ ውሳኔ ያሳለፈ በመሆኑ፣ የትግራይ ክልል ምርጫ አስፈጻሚ ተቋም እንዲመሠረት ይደረጋል፤›› ብለዋል።