Thursday, June 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ማን ይምራው?

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትን ማን ይምራው?

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮችን ምክር ቤት ምርጫ በቅርቡ በብሔራዊ ደረጃ ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ ሆኖ እንደሚከሰት አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ምርጫ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም፣ ከአንዱ ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ የገመድ ጉተታ ከማካሄድ እንደማይቆጠብ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢስላማዊ ሆኑ ኢስላማዊ ያልሆኑ መንግሥታትም ጥቅማቸውን ለማስከበር አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ፡፡ ይህ የአውሮፓን፣ የአሜሪካንና የእስያን መንግሥታት ሊጨምር ይችላል፡፡ በተመሳሳይ በአገር ውስጥ ቀላል ያልሆነ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ዴሞክራሲያዊ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ብቻ ሳይሆን፣ ዓላማውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚያራምድለት እንዲሆን መፈለጉ ከቶ አይቀርም፡፡ ስለሆነም መጅሊሱ ሕጋዊ ሰውነት እንዲኖረው ከተደረገ ማግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ ብዙ ኢስላማዊ ጉዳዮች የሚያከናውንበት መሣሪያው በመሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ በሆነ አካሄድ መምረጥ ስለሚቻልበት ሁኔታ ውይይት የሚደረግበት ጊዜ እየተቃረበ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንደኛውና ዋነኛው ጥያቄ ‹‹ምክር ቤቱን ማን ይምራው?›› የሚለው ነው፡፡ በእርግጥም ምክር ቤቱን ማን ይምራው? ከምንስ እንጀምር? በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ በርካታ ሐሳቦች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ከዚህ በታች የሚቀርበው ግን የእኔ የዚህ ጽሑፍ አጠናቃሪ ብቻ ነው፡፡
መጅሊሱን የሚመራው የሙስሊም ኢትዮጵያዊ መብት የሚያረጋግጥ መሆን አለበት

እንደሚታወቀው ሁሉ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅና በሩቅ ምሥራቅ በርካታ የሙስሊም አገሮች አሉ፡፡ በሰሜንና በምዕራብ አፍሪካም እንደዚሁ፡፡ የሁሉንም አገሮች ባህርይ ስንመለከት ከሁሉ አስቀድሞ ሰዎች የአንድ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የሚታወቁትም በዜግነታቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የመናዊ ሙስሊም ሳዑዲያዊ ሙስሊም ልሁን ቢል አይቻለውም፡፡  ለኢስላማዊ ጉዳዮች ምክር ቤት የሚወዳደር ሰው ሌሎች የሙስሊም አገሮች የራሳቸው የሆነ ሕይወት እንዳላቸው አሳውቆ፣ በቅድሚያ ለኢትዮጵያዊ ሙስሊም መብትና ሙስሊማዊ አንድነት መረጋገጥ የሚጥር መሆን ይሆርበታል፡፡

- Advertisement -

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ለማፋጠን የተነሳ መሆን ይኖርበታል

ለአንድ የኢስላም ምክር ቤት የአገርን ልማት የማፋጠን አጀንዳ ይዞ መነሳት አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ኢስላም ዝም ብሎ ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን የጥበቦች ሁሉ ምንጭ ነው፡፡ ኢስላም ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲዳብርና ሥነ ጥበብ እንዲበለፅግ የሚያደርግ መመርያም ነው፡፡ ኢስላም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ምንጭ ስለመሆኑ በታሪክ በተጨባጭ የተረጋገጠ ነው፡፡ ኢስላማዊ አስተሳሰብን፣ ስሜትን፣ መንገድን፣ ፍልስፍናን ህያው ካደረግን ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር በመተባበር ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ እንድናመጣ የሚያስችሉን ናቸው፡፡ ስለሆነም በከፍተኛው ኢስላማዊ ምክር ቤት ለመሥራት የሚፈልግ የፍልስፍና ጥልቀት፣ የማጣራት፣ የማሻሻል፣ ወደፊት የማራመድ፣ በኪነ ጥበብና በፍልስፍናችን ውስጥ የሚገኝ በጥልቅ ዕሳቤ የተሞላ መሆን ይኖርበታል፡፡ ኢስላማዊ አመለካከቱ ጥራት ያለው፣ ሊያስኬድ የሚችል አስተሳሰብ ያለውና ለመልካም ግብ የተነሳሳ ባለራዕይ ሊሆን ይገባል፡፡ 

ተመራጮች መጅሊሱን ከመንግሥት ጣልቃ ገብነት መጠበቅ መቻል አለባቸው

እንደሚታወቀው በመንግሥት በኩል በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ እንደማይገባ ከገለጸውና በሕገ መንግሥቱ ካረጋገጠው የተለየ አቋም ለጊዜው ላይታይ ይችላል፣ ዘለዓለማዊ አቋም ግን አይደለም፡፡ ሊለወጥና ሊለዋወጥ ይችላል፡፡ ይህን በሌሎች ሙስሊም አገሮች ምሳሌ እንየው፡፡

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ከተጠነሰሰበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ኢስላማዊ መንግሥት ቢሆንም፣ የተለየ አንጃ ያላቸው ሙስሊሞች ተነስተው ሥልጣንህን አስረክበን ቢሉት፣ ወይም የምታካሂደው እምነት ከኢስላማዊ መርህ ያፈነገጠ ነውና ለእኛ አስረክበን ቢሉት በጀ ስለማይል ተቀናቃኞቹን መከርቸሙ፣ በተለያየ መንገድ መመርመሩ፣ መርምሮም የተለያዩ ዕርምጃዎችን መውሰዱ አይቀርም፡፡ ላለፉት መቶ ዓመታት ህልውናውን ጠብቆ የኖረው በዚህ መንገድ ነው፡፡ ነገሩ አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው እስከ ጎረቤት አገር ድረስ ሠራዊቱን ያዘምታል፣ ያስራል፣ ይገድላል፡፡  

በግብፅ የተለያዩ የኢስላማዊ አንጃ አቋም ይዘው በመንቀሳቀሳቸውና በመንግሥት ዕይታ ‹‹ሁከት ነው›› ተብለው ስለተፈረጁ በርካታ ሰዎች ታስረዋል፣ ተገድለዋል፡፡ ኮሎኔል ገማል አብዱልናስር ሥልጣን ላይ በወጡ ጊዜ ዓላማቸውን የተቃወሙ በርካታ ግብፃውያን የእስልምና ሊቃውንትን አስረዋል፣ ገድለዋል፡፡ ከእነዚም ሌላ የእነ ሐሰን አል በና፣ አቡዓላ አል መውዱዲ እንቅስቃሴ ይገኝበታል፡፡ ሰይድ ቑጡብ የተባለው ግብፃዊው የተክፊር አንጃ አራማጅም ባደረገው እንቅስቃሴ፣ በግብፅ መንግሥት በመጀመሪያ ዘብጥያ ወርዷል፡፡ ከዚያም በገማል አብዱልናስር መንግሥት ለፍርድ ቀርቦ በስቅላት እንዲቀጣ ተደርጓል፡፡ ከእሱም ጋር ብዙ አንጀኞች ጠፍተዋል፡፡ 

በኢራንም በኢራቅም እንደ ሁኔታው አንደኛው ሌላውን ለማስወገድ ጥረት ሲደረግ ዕርምጃ ተወስዷል፡፡ ለምን ይህ ይሆናል? የዚህ ጥያቄ መልስ በጣም አከራካሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው መልስ ግን መንግሥት ፖሊስም፣ መከላከያ ኃይልም፣ እስር ቤትም፣ የጦር መሣሪያም፣ ከሁሉም በላይ ሕግ ስላለው ነው፡፡ ሕጉን ካላስከበረ ደግሞ መንግሥት ሊሆን አይችልም፡፡ 

በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዴ መንግሥት አንድ የሃይማኖት አንጃ ብቻ ሳይሆን፣ ብዙ አንጃዎች እንዲኖሩ ሊፈልግ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ማንኛውም አንጃ በአገሪቱ ሕግና ደንብ መመራት ስላለበት፣ ‹‹እከሌ ጠፍቶ እኔ ልኑር›› ወይም ‹‹እከሌ ተነስቶ እኔ ልቀመጥ›› ማለት አያዋጣም፡፡ በእንዲህ ያለው መንግሥት የሚኖረው የመድበለ ሃይማኖት ሥርዓት ነው፡፡ ሁሉም ወኪሉን እየመረጠ በድምፅ ብልጫ ይወስናል፡፡ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊ ቢመስልም ሁሉም እንደፈለገ የሚናገርበት፣ የኢኮኖሚ አቅም ያለው ትክክልም ባይሆን ደካማውን የሚያንበረክክበት፣ አቅም የሌለው ደግሞ ምንም ያህል ትክክለኛ አቋም ቢኖረው የአንዱ ወይም የሌላው ጥገኛ የሚሆንበት፣ በአጭሩ ሁሉም እንደፈለገ የሚንጫጫበትና በዴሞክራሲ ስም የከፋፍለህ ግዛው ሥርዓት ዓይነት የሰፈነበት ሊሆን ይችላል፡፡ 

አንዳንድ መንግሥታት ደግሞ አንድ አንጃ ብቻ በበላይነት እንዲመራ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ አንጃ የመንግሥትንም ተልዕኮ የሚያስፈጽም ስለሆነ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግለት ይችላል፡፡ ይሁንና ሌሎችን አንጃዎች ዝም ለማሳኘት ወደኋላ አይልም፡፡ ስለዚህ መጅሊስን ከመንግሥት አግባብ ያልሆነ ጣልቃ ገብነት መጠበቅ አለበት፡፡

መጅሊሱን የሚመራው የሙስሊሞች አንድነት አጀንዳ ያለው መሆን ይኖርበታል

በመሠረቱ ኢስላማዊ አንድነት በማንኛውም ማኅበራዊ ደረጃና ሁኔታ ለሚገኙ ሙስሊሞች ዋነኛ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ‹‹እከሌ ቆሻሻ ነው፣ እኔ ግን ንፁህ ነኝ፣እሱ ጠማማው መንገድ ሲሆንእኔ ግን ትክክለኛው ነው›› በሚል ኢስላማዊ ያልሆነ በታታኝ የሽንፈት ቅስቀሳ መንገድ የሚከተል ሳይሆን፣ የሙስሊም ወንድማማችነት ጠቀሜታን ተረድቶ በቁርጠኛነት ስሜት በመመራት ተግባራዊ እንቅስቃሴማድረግ የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ የአስተምህሮቱ መኖር አስፈላጊ ሆኖ ቢገኝ እንኳ መጅሊሱ የሁሉም ስለሆነ፣ ልዩነትን የሚያመለክቱ ሒደቶች ከመሥራት መቆጠብ በእጅጉ የሚቆጠብ መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር ሁከት ይፈጠራል፡፡ ለማወክ ደግሞ አንድ ቡድን ሳይሆን አንድ ሰው ይበቃል፡፡

ኢስላማዊ አንድነት እንዴት ዕውን ሊሆን ይችላል?

ኢስላማዊ አንድነትን ለማምጣት ከሁሉ አስቀድሞ በቁርዓን፣ በሐዲስ፣ በነብዩ ሙሐመድ የአላህ መልእክተኛነት ማመን ነው፡፡ በተለያዩ አጋጣሚዎች እንደምንሰማው ሁሉ አንድነት ኃይል ነው፡፡ ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› ይባላል፡፡ አሸዋዎች በአንድ ላይ ሲሆኑ የደረሃ ኮረብታዎችን እንደሚፈጥሩት ማለት ነው፡፡ ወይም ጋን በጠብታ እንደሚሞላው ወይም ብዙ ጠብታዎች ባህርና ውቅያኖስ እንደሚሆኑት ማለት ነው፡፡ የሕዝቦች መተባበር ጠንካራ አገርን፣ ሰላምን፣ ልማትን፣ የተሻለ አስተዳደርን፣ መቻቻልን እንደሚፈጥርም ሳይናገሩት የሚሄድ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት በርካታ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

ሁኔታዎችን በጥቅሉ ስንመለከታቸው ሁሉም ሰው በሰላም ለመኖር እንዲችል ልዩነት እንኳን ቢኖረው መቻቻል ይኖርበታል፡፡ ስለዚህ የኢስላም አንድነትን ዕውን ለማድረግ አስፈላጊው ጉዳይ በሸሪዓው መሠረት በጋራ ተመካክሮ መሥራት ነው፡፡ የከፍተኛው ኢስላማዊ ምክር ቤት ሥራ መሆን ያለበትም ይህ ነው፡፡ 

መጅሊሱ ለሃይማኖት ሕግጋት ነጥረው መውጣት የሚታገል መሆን ይኖርበታል

እስካሁን የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ሕዝብን በሕግ ጥላ ሥር የሚያስተዳድርበት እንደሆነ ሲነገርና በዚያ መንፈስ ሲተገበር የመጣ ቢሆንም፣ አሁን ዓለም ከደረሰችበትና የሁሉም ኢትዮጵያ በሆነችው አገር ያለውን ሕግ እንደገና ማየት ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ስለሆነም መጅሊሱ በአንድ በኩል የሌሎችንም አጥብቀው የሚያከብሩ ሕጎች እየታገለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሙስሊሙን መብት የሚያረጋግጡ ሕጎች እንዲኖሩ ለማድረግ የሚጥር ሆኖ መገኘት ይኖርበታል፡፡ ትኩረት ከሚደረግባቸው ጥቂቶቹን ለአብነት እንመልከት፡፡

ሀ. በዚህ ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል ሴቶች በየትኛውም ሥፍራ ቢሆን ሒጃብ ማድረግ ከፈለጉ የማድረግ መብታቸው በሕግ እንዲጠበቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በከፍተኛ ትምህርት ቤቶች አመጋገባቸው፣ አኗኗቸው፣ ማኅበራዊ ሕይወታቸው ከእምነታቸው ጋር የተሳሰረ ነው? በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ትምህርት ቤቶች በየአገሩ እየተስፋፉ ያሉ ምን ይመስላል? ከእነዚህ አገሮች ተምረው የሚመጡና በዜግነታቸው ወደ አገራቸው መጥተው የሚማሩ ወጣቶች ጉዳይስ እንዴት ይያዛል? የትምህርት ቤቶች መሠረታዊ ተልዕኮ በአንድነት ውስጥ ስላሉት ልዩነቶችና በልዩነት ውስጥ አንድነቶችን ለመረዳት የሚያስችሉ፣ የመቻቻል ባህልን የሚያጎለብቱ፣ ግልጽነት የሰፈነባቸው እንዲሆኑ የሚማሩት ትምህርት ከሕዝባዊ ተጠያቂነት ጋር የተቀናጀ መሆኑንና ማኅበረሰባዊ ክብርን የሚያጎናፅፍ እንዲሆን የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልገዋል፡፡

ለ. በኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ታሪክ ኢስላማዊ መድረሳዎች መሠረታዊ ሃይማኖታዊ ዕውቀት ብቻ ሳይሆኑ፣ መሠረተ ትምህርት በማስፋፋት ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ተቋማት ናቸው፡፡ ስለዚህም ከመደበኛው ትምህርት በተለየ ሁኔታ ትኩረት አግኝተው የበለጠ ተጠናክረው የሚቀጥሉበት ሕጋዊ ድጋፍ ቢኖራቸው፣ አገራችንን በተቀላጠፈ ሁኔታ ለማሳደግ ለምንሻው ብሔራዊ ዓላማ ሊውሉ ይችላሉ፡፡ ይልቁንም ኢስላማዊ መድረሳዎች ከፍተኛ የኢንቨስትመንት አቅም የማይጠይቁ ከመሆናቸውም በላይ፣ ልጆች ተሰባስበው በሚገኙባቸው ቦታዎች (ለምሳሌ በእረኝነት ለተሰማሩ ልጆች፣ እሑድና ቅዳሜ ቤታቸው ለሚውሉ፣ ባለው ትርፍ ጊዜ ቤተሰብንና ጎረቤት የሆኑ ልጆች) ሁሉ መሠረታዊ ትምህርትን ለማስፋፋት አመቺ ናቸው፡፡ መጅሊሱ በዚህ ረገድ ትኩረት የሚያደርግ ቢሆን ተመራጭ ሊሆን ይችላል፡፡

ሐ. አንድ ሰው በሃይማኖቱ የተለየ ቢሆንም እን በብሔራዊ ማንነቱ አንድ ለመሆኑ አያጠያይቅም፡፡ አንዲት አገርም አፋጣኝ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ የለውጥ ዕድገት ልታመጣ የምትችለው ማኅበራዊ ማንነቱ በጥብቅ መሠረት ላይ የተገነባ እንደሆነ ነው፡፡ ዳሩ ግን አንድ ኢትጵያዊ «እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ» ለማለት ብሔራዊ ማንነቱንና እምነቱን አጣጥሞ ለመምራት የሚያስችለው ሕግ የቱ ነው? «እኔ ኩሩ ኢትዮጵያ ነኝ» ስላለ ብቻ ሊሆን ይችላል? ስለሆነም መጅሊሱ «ኩሩ ኢትዮጵያዊ» ዕውን የሚያደርግ ሕግ እንዲወጣ ማስቻል አለበት፡፡ ለዚህ በአብነት ልንጠቅሰው የምንችለው በአማራና በትግራይ ክልሎች ያሉት ሙስሊሞች መብት መረገጥን ነው፡፡ ከዚህም ሌላ በርካታ ሐረሪዎች ከአገራቸው በግፍ እንዲወጡ ተደርገው በተለያዩ ዓለማት የተሰደዱት፣ በአገራቸው ውስጥ ይኖሩ የነበሩትም የተበደሉትና በዓይነ ቁራኛ ሲጠበቁ የነበሩት ብሔራዊ ማንነታው በጥያቄ ላይ በመውደቁ ነበር፡፡ ስለሆነም ብሔራዊ ማንነት ከእምነት፣ ከአመለካከት፣ ከዜግነታችን ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያረጋግጡ ወይም ይህንን ብሔራዊ ማንነት ይበልጥ የሚያረጋግጡ በሚችሉበትና ኅብረተሰቡን ለበለጠ ልማት የሚያነሳሱ ሕግጋት ሊቀረፁ ይገባል፡፡

መ. የፕሬስ ውጤቶች ማለትም የኅትመትና የኤሌክትሮኒክስ (እንደ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ጆርናሎች፣ ብሮሹሮች፣ በራሪ ጽሑፎች፣ ፖስተሮች፣ ቢል ቦርዶች፣ የሬዲዮ፣ የቴሌቪዥን፣ የሲኒማ፣ የድምፅ፣) ውጤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገዶች የኅብረተሰቡን ተቻችሎ የመኖር ባህል እንዳይንዱ የሚከለክልና ሁሉንም ሃይማኖቶችና እምነቶች መሠረት ያደረገ ሕግ እንዲኖረን ማድረግ ተገቢ ይሆናል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የመገናኛ ብዙኃን የመንግሥትንም ጨምሮ ወደ አንድ በኩል ያጋደለ መስሎ ስለሚታይም፣ ይህም የፕሬስ ውጤት በሕግ የታገዘ ሥራ እንዲያከናውን ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው የፕሬስ ውጤቶች በውስጡ የተለያዩ የሃይማኖት ጉዳዮች የሚመለከቱ ክፍሎች እስከሌላቸው ድረስ፣ በግልጽም ሆነ በረቀቀ መንገድ የኅብረተሰቡን መብት የሚፃረሩበት ሁኔታ እንዳይኖር ከሰው ኃይል አቀጣጠርና አመዳደብ ጀምሮ ማካተት ያለባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

ሠ. ብሔራዊ ሸንጎ ፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ፣ እንዲሁም ብሔራዊና ሕዝባዊ ጉዳዮችን የሚያከናውን አካል እንደ መሆኑ በዚህ ውስጥ የሃይማኖትና የእምነቶች ጉዳዮችም፣ በአንድ ወይም በሌላ እየተሰባጠሩ የሚመጡ ስለሆነ ምርጫ ሲካሄድ ሃይማኖትም ከግምት ውስጥ ይገባ እንደሆነ፣ ወይም ሃይማኖትን የሚመለከቱ ክፍሎች እንዲኖሩት መጅሊሱ ትኩረት የሚያደርግ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ብሔራዊው ሸንጎ የአማኙ ከፍተኛአነስተኛ ቁጥር መሆን ሳይገድበውየሁሉንም ህልውና የሚያረጋግጥና ሁሉም የሸንጎ ተወካዮች የኢትዮጵያውያን ናቸው የሚያሰኝ ሆኖ መገኘትም ይኖርበታል፡፡ መጅሊስ ለዚህ ዕውን መሆን ሲተጋ ዓለም አቀፍ መዲና በሆነችው ኢትዮጵያ የሚገኝ ብሔራዊ ሸንጎ ለአፍሪካ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ ለመገኘት ይችል ዘንድ፣ ከሃይማኖት ጋር የተሰናሰሉ ሕጎችን ማለትም ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጣቸው መብቶችን ሥራ ላይ ለማዋልና ሁሉንም ሃይማኖቶች እኩል ለማስተናገድ የሚደረገውን ጥረት የሚያጠናክር፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተለያየ እምነትና አመለካከት ያላቸው ሰዎች በመቻቻልና በሰላም አብረው የሚኖሩባት አገር መሆኗን የበለጠ የሚረጋገጥባት ትሆናለች፡፡

ረ. ምንም እን ሁሉም ሃይማኖትና እምነት የራሱ የሆነ ሥነ ምግባር ያለው ቢሆንም፣ ሁሉም ሃይማኖቶች በጋራ የሚስማሙባቸው፣ የሃይማኖት ሥነ ምግባሮች በማውጣት የሃይማኖቱ ሕግ አካል ማድረግ ይቻል እንደሆነ መመካከር ያስፈልጋል፡፡ የጋራ ሥነ ምግባራዊ መመርያ ወይም ሕግ የሚያስፈልግበት መሠረታዊው ምክንያት፣  እያንዳንዱ ትኩረት የሚሰጠው ለራሱ ብቻ ከመሆኑም በላይ የጋራ የሆኑት ሥነ ምግባሮች ለአማኞች እንዳስፈላጊነቱ የማይሰራጩ በመሆናቸው ነው፡፡ የሃይማኖት የጋራ ሥነ ምግባር መመርያዎች መኖር፣ በጭፍን «ትክክሉ የእኔ ነው» ከሚል አመለካከት አውጥቶ፣ «ለካስ ሌሎችም እንደኛ ትክክል የሆነ የሥነ ምግባር መመርያ አላቸው» የሚል አዎንታዊ አመለካከት ሊያሰፍን፣ እንዲሁም ሕዝብ ለመቻቻልና በፍቅር በሰላም አብሮ ለመኖር የሚያደርገውን ጥረት የበለጠ ሊያጠናክሩ እንደሚችል ይታመናል፡፡

ሰ. ደረጃ በደረጃም ለዘመናት የነበረውን አንዱ ሌላውን እንዳያውቅ ይከለክል የነበረውን አስተሳሰብ በማስቀረት፣ አንዱ ስለሌላው እንዲያውቅ ያስችለዋል፡፡ ሃይማኖት በማወቅ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማገዝም አገር በዕውቀት የሚመራ ዕድገት እንዲኖራት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሊያግዝ ይችላል፡፡ «ስህተት እንደነበረ ሊቀጥል የማይችለው» ወይም «ስህተት መብት የለውም» የሚባለውም ዕውቀት በሒደት ትክክለኛውን ለማሳወቅ ስለሚችል ነው፡፡

ሸ. አንዳንድ ሰዎች በተለይም ፍልስፍናዎች ለዘመናዊ ሥልጣኔ በራቸው ዝግ እንደሆነ አድርገው ይመለከቷቸዋል፡፡ ኢስላም፣ ክርስቲያንና ይሁዳ አንዳቸው ከሌላው የሚወራረሱት ጥበብ በመኖሩም፣ የሳይንስና ምርምሩ ሥራ ለዘመኑ ሥልጣኔ ዝግ እንዳልሆነ ያስገነዝበናል፡፡ ስለሆነም ሳይሳዊ ምርምሮችና ሃይማኖቶች የሚገናኙበት መንገድ ይኖር እንደሆነ ታሳቢ ያደረገ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ ይገኛል፡፡

ቀ. በአሁኑ ጊዜ ስለሃይማኖታዊ አክራሪነት ሲነገር ይሰማል፡፡ ሃይማኖታዊ አክራሪነትም ከሽብርተኛነት ጋር አብሮ ሲወሳ ይስተዋላል፡፡ ነገር ግን በሃይማኖት አክራሪነትና በአሸባሪነት መካከል ያለው ግንኙነት ምንድነው? በእርግጥ ሃይማኖትን አክርሮ ወይም አጥብቆ መያዝ አሸባሪነት ነው? ወገቡን በገመድ አስሮ የሚሄድ ባህታዊ «አክራሪ ክርስቲያን ነው» ማለት እሸባሪ ነው ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለመጪው ዓለም እንጂ ስለዚች ዓለም አንዳች ነገር የማይደንቀው ሙስሊም የሃይማኖት አባት በሃይማኖቱ አክራሪ ቢሆንም፣ አሸባሪ የሚለው ቅጽል አይመለከተውም፡፡ ሁለቱም የሃይማኖት አባቶች ስለራሳቸው መጨረሻ ባለማወቅ ፈጣሪ ምን እንደሚያደርጋቸው እያሰቡ በፍርኃት የሚንቀጠቀጡ እንጂ፣ ሰውን በጦር መሣሪያ የሚያጠፉ አይደሉም፡፡

ያልበደላቸውን፣ ያልነካቸውን፣ ስለነሱ መኖርና አለመኖር ደንታ የሌለውን ሕዝብ የጦር መሣሪያ አንስተው የሚገድሉ፣ የዕለት ተዕለት አሰልቺ ሕይወቷን ለመምራት ወደ ገበያ የወጣችን የብዙ ልጆች እናትን በቦምብ የሚያጋዩ ግን ሃይማኖታቸውን በጥብቅ በመከተላቸው ሳይሆን፣ ለፖለቲካ ሥልጣን በመፈለጋቸው መሆኑ እየታወቀ አክራሪ ሃይማኖተኞችም ከእንዲህ ያለ እኩይ ተግባራት ከሚያከናውኑ ሰዎች ተርታ አሸባሪዎች ሆነው በአንድ ጊዜ የሚቀርቡበት ሁኔታ አለ፡፡ ሙስሊሙን ሁሉ በአሸባሪነት ለመመደብ የሚሹም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣ «ነጻ አውጭ ነኝ» ብሎ ራሱን የሚጠራው ቡድን የአክራሪም፣ የአሸባሪም ምሳሌ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በጥሬው ሊገባን የሚችለው ይህ ድርጅት የጦር መሣሪያ አንስቶ መንግሥትን የሚወጋ፣ በመንግሥትም ሕገወጥ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ሊሆን ይችላል፡፡ በውስጡ ግን የተለያዩ እምነት ተከታዮች ይኖሩታል፡፡ ስለዚህ ድርጅት የአሸባሪነቱን ትርጉም ለመረዳት ብንችልም፣ የአክራሪነቱ ጉዳይ ግን ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ በአጭሩ በሃይማኖት አክራሪነትናአሸባሪነት ስም ለመፈረጅ የሚያስችል የሃይማኖት ሕግ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

የምርጫውን ውጤት መቀበል

በውድድር ሁሉም አሸናፊ ወይም ሁሉም ተሸናፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ምርጫ የሚካሄደውም አብዛኛውን የሚወክል ተመርጦ ሥልጣኑን በመያዝ እንዲመራው ሲሆን፣ ያልተመረጡ ደግሞ ዓላማቸው ሕዝብን ለማገልገል በመሆኑ፣ ቢመረጡ ሊሠሩ ይችሉት የነበረውን በማከናወን የተመረጠውን በሁሉም መስክ ማገዝ ነው፡  ለምርጫው አለመሳካት በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለሆነም ውጫዊውን ምክንያት ብቻ ሳይሆንውስጣዊውንም ጭምር ለማየት መሞከር ያስፈልጋል፡፡

ከምርጫው በፊት መጥራት ያለባቸው ጉዳዮች

በኢትዮጵያ ውስጥ በሁሉም ሃይማኖቶችና እምነቶች መካከል መቻቻል እንዲኖር ግንባር ቀደም ሚና የሚጫወት ምክር ቤት እንዲኖር ያስፈልጋል፡፡ ይህ እንዲሆንን የተመራጮችን ዓላማ ተረጋግቶ መገምገም ያስፈልጋል፡፡ ሲጀመር ክርስቲያን፣ መስሊምና አይሁድ እንዲሁም ሃይማኖት አልቦ የሆኑ ሕዝቦች በሚኖሩባት ኢትዮጵያ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቻችሎ፣ ተፈቃቅሮና ተባብሮ ለመኖር የሚሻ አካል መኖር አለበት፡፡

አገራችን እንደ ሩቅ ምሥራቅ፣ መካከለኛው ምሥራቅና አፍሪካ አገሮች የቅኝ ግዛት ስላልነበረች በሌሎች ቅኝ ግዛት እንደነበሩ አገሮች ሆን ተብሎ በሚፈጠር የዘር፣ የጎሳ፣ የጂኦግራፊያዊ አሠፋፈር የሃይማኖት ክፍፍል አልደረሰብንም፡፡ በውስጣችን በገዥ መደቦች ውስጥ የመናናቅ ነገር የነበረ ቢሆንም፣ ሰፊው ሕዝብ ባልተራራቀ ማኅበረሰባዊ ኢኮኖሚ ሕይወት ስለነበረ ጎልቶ የሚታይ ችግር አልነበረም፡፡ ወይም እንደ አሜሪካውያን ከየትም ተጠራቅመን የተሰባሰብን ሕዝቦች ባለመሆናችን፣ የተራራቀ የሥነ ባህርይ አመለከት የለንም፡፡ በሃይማኖት፣ በብሔርናብሔረሰብ የተለያየን ብንሆንም ለብዙ ሺሕ ዓመታት አብረን የኖርን ብቻ ሳንሆን፣ አንዳችን ከሌላችን ጋር በጋብቻና በአሠፋፋር እየተሰናሰልን የመጣን ነን፡፡ ይሁንና የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ትስስሩ እየተጠናከረ ሲሄድ ተጋቦቱም ሊኖር ስለሚችል፣ በወንጀለኛ መቅጫችንና በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ያልተካተቱ ሃይማኖታዊ ሕጎችን ማውጣት ያስፈልጋል፡፡

ከአዘጋጁጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...