የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዘንድሮ መካሄድ የነበረበትን አጠቃላይ ምርጫ በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጤና ሥጋትን ለመከላከል በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት፣ ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይችል በመወሰኑና ይህንንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተቀብሎ መወሰኑ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ በሥልጣን ላይ የሚገኙ በሕዝብ የተመረጡ ምክር ቤቶች የሥልጣን ዘመን ምን ይሁን? እንዲሁም ምርጫው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መካሄድ አለበት ተብሎ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ቀርቦለታል፡፡
አጣሪ ጉባዔውም የቀረበለትን ጥያቄ በመመርመር የደረሰበትን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ የያዘ ውሳኔ ሐሳብ ለፌዴሬሽን በመላክ ምክር ቤቱ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የአጣሪ ጉባዔውን የውሳኔ ሐሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ፣ በአራት ተቃውሞና አንድ ድምፀ ተአቅቦ በ114 ድጋፍ አፅድቆታል። ይህ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄና ውሳኔ አሰጣጥ ሒደት የበርካቶችን ቀልብ የገዛ ሲሆን፣ ሒደቱም የበርካቶችን ድጋፍ ያገኘና ተቃውሞም የቀረበበት ነበር። የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ትርጓሜ ለመስጠት የተከተለውን ሒደትና የውሳኔ ሐሳቡ የተካተተበት ዝርዝር ሪፖርት ማግኘት የተቻለ ሲሆን፣ አንባቢያን ይህንን ታሪካዊ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ አሰጣጥ በተመለከተ የተሟላ ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ የሪፖርቱን መሠረታዊ ይዘት ከታች ቀርቧል።
በምክር ቤቱ የቀረበው ጥያቄ
‹‹የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶችና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ ከዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል? ምርጫውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?›› የሚል ነው፡፡ ጉባዔው ከቀረበው ጥያቄ ለመረዳት እንደሚቻለው በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝና ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተፅዕኖውን ለመቀነስ በታወጀው አዋጅ ቁጥር 3/2012 ምክንያት ምርጫ ማካሄድ የማይቻል ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ሊሆን እንደሚገባና ምርጫው መቼ ሊከናወን እንደሚገባ በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ባለመደንገጉ ነው፡፡ በመሆኑም በምክር ቤቱ ለቀረበው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎችና መሠረታዊ ምርሆዎችን መመርመርና ትርጓሜ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ በወቅቱ ባለመደረጉ በተጨባጭ ሊፈጠር የሚችለው የሥልጣን ክፍተትና የምርጫ ጊዜ መዛባት እንዴት ይፈታል ለሚለው ጥያቄ ሕገ መንግሥታዊ መፍትሔ ለማስገኘት የቀረበ በመሆኑ፣ ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ነው፡፡
በቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ላይ በጉባዔው የተለዩ ጭብጦች
ከቀረበው የሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜ ጥያቄ አንፃር ምላሽ ማግኘት ያለባቸው መሠረታዊ ጭብጦች የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትና ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተፅዕኖውን ለመቀነስ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ምክንያት የምክር ቤቶቹና የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን የሥራ ዘመንን አስመልክቶ፣ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ጥያቄ ለመመለስ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1)፣ 58(3)፣ እና 93 እንዴት ይተረጎማሉ? የኮሮና ወረርሽኝ መከሰትና ወረርሽኙን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና ተፅዕኖውን ለመቀነስ በታወጀው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ምክንያት ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ አስመልክቶ የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበውን ጥያቄ ለመመለስ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1)፣ 58(3) እና 93 እንዴት ይተረጓማሉ? የሚሉት ናቸው፡፡
የጭብጦች ትንታኔ
ጉባዔው በጭብጥነት የያዛቸውን ጉዳዮች ከተለያዩ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች፣ ከአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ መርሆዎች፣ ከሕገ መንግሥቱ ዓላማና ግብ፣ እንዲሁም ከተለያዩ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መርሆዎች አንፃር መርምሯቸዋል፡፡ በመጀመርያ የተቀመጠውን ጭብጥ ለመመለስ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦች ተለይተዋል፡፡ የመጀመርያው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3)፣ 54(1)፣ 58(3)፣ 67(2) እና 72(3) ላይ ምርጫን፣ የምርጫን ጊዜን፣ የመንግሥት የሥልጣን የሥራ ዘመን የሚመለከቱ ናቸው፡፡ ሁለተኛው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 አስገዳጅ ወይም ከአቅም በላይ የሆነ ሁኔታ በአገሪቱ ሲከሰት መወሰድ ስለሚገባቸው ዕርምጃዎች የሚመለከት ነው፡፡ ይህ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌ ከአንቀጽ 54(1) እና 58(3) ጋር ያለውን ግንኙነት መሠረት በማድረግ መተርጎም የሚገባው ነው፡፡
የምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካላት የሥራ ዘመንን በተመለከተ
የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔውም ለትርጓሜ በቀረቡት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች መሠረት የመንግሥትን ሥልጣን የሥራ ዘመን ስለምርጫ መራዘም በሚከተሉት ክፍሎች በዝርዝር በማየት ዳሷል፡፡
የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች 54(1)፣ 58(3) እና 93 ቀጥተኛ ትርጓሜን በተመለተ
የትርጓሜ ጥያቄውን ለመመለስ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) በተደነገገው የምርጫ ጊዜ ውስጥ ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ፣ በኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መከሰትና ይህንኑ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ሳይካሄድ በመቅረቱ የምርጫ ጊዜው ምን መሆን አለበት የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ መካሄድ ባለበት ሁኔታ በአምስተኛው ምርጫ የተቋቋሙት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት የሥልጣን ዘመን፣ የኮሮና ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ሲውልና ቀጣይ ጠቅላላ ምርጫ ተከናውኖ በምርጫ ያሸነፉት ተመራጮች የሥልጣን ርክክብ እስከሚደረግበት ጊዜ ድረስ የሥራ ዘመናቸው እንዴት ይሆናል የሚለውን የሚመልስ ነው፡፡ ምርጫ የአንድ አገር የዴሞክራሲ ዕድገት ደረጃ ዋና መለኪያ ነው፡፡ ይህ የዴሞክራሲያዊነት መለኪያ መሣሪያ የሆነው ምርጫ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚካሄድ ቀጣይነት ያለው፣ የማይቋረጥና በጊዜ የተገደበ መሆን ያለበት ነው፡፡ ይህም የሚገለጸው ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8(1) ላይ በግልጽ እንደተመለከተው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ይህን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት መብታቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉት በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ዕውቅና ያገኙትን ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተለይም በአንቀጽ 38 መሠረት የመምረጥና የመመረጥ መብትቸውን ተጠቅመው ነው፡፡
በአንቀጽ 38(1) መሠረት የሚደረግ ምርጫም ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛና ሚስጥራዊ የሆነ የድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንኑ የምርጫ ሒደትና ይዘት በማረጋገጥ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ፣ ከማንኛውም አካል ወይም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ በማረጋገጥ ሥራ ላይ እንዲውል የሚያደርግ፣ ከማንኛውም አካል ወይም ወገን ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ የሚሠራና ገለልተኛ የሆነ የፌዴራል ተቋም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102(1) መሠረት ተቋቁሟል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ›› በማለት ተደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) ደግሞ ሲደነግግ፣ ‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመት ነው፣ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ይጠናቀቃል፤›› ይላል፡፡ የእነዚህ ሁለቱ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች አቀማመጥ፣ አቀራረፅና ማስተላለፍ የፈለጉትን ዋና መልዕክት በየራሳቸው ተነጥለው ሲታዩ ግልጽ ቢመስሉም፣ ለሕገ መንግሥት ትርጓሜ ከቀረበው አንቀጽ 93 ጋር በጣምራ ሲነበቡ ግልጽነት ይጎድላቸዋል፡፡ በመሆኑም ድንጋጌዎቹን በሕገ መንግሥት ትርጓሜ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) ቀጥተኛ ንባብ መሠረት ሦስት መሠረታዊ ነጥቦችን የያዙ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ የመጀመርያው ነጥብ በተለይ አንቀጽ 54(1) የሚደነግገው ስለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕዝብ መመረጥ ነው፡፡ ከዚህም በመቀጠል ይህ ምርጫ መካሄድ ያለበት በየአምስት ዓመት ሲሆን፣ ምርጫው ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚጥበት ሥርዓት መሆን እንዳለበት ነው፡፡ ድንጋጌው በዋናነት ለማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ስለምርጫ መሥፈርት፣ የምርጫ ጊዜንና የምክር ቤቱ አባላት በሕዝብ መመረጥን ነው፡፡ በዚህ መሠረት የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) በይዘትና በጊዜ የተገደበ የምርጫ ሥርዓት መኖሩን የሚደነግግ ሲሆን፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) ሥር ያለውን ሁኔታ የሚያብራራ ነው፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሁለቱ ድንጋጌዎች የሚደጋገፉ መሆናቸውን ነው፡፡ በአንቀጽ 58(3) ሥር ያለው ነጥብ በአንቀጽ 54(1) ላይ ስላለው ጉዳይ የበለጠ ዘርዘር የሚያደርግና የሚያብራራ ነው፡፡ በአንቀጽ 58(3) ሥር የተደነገገው መሠረታዊ ነጥብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚመረጡት ለአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ሲሆን፣ ከምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ማብቃት ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ እንዳለበት የሚደነግግ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ በዋናነት የሚያመለክተው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስት ዓመት የሥራ ዘመን ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ እንዳለበት ነው፡፡
ከዚህ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ቢሆንም፣ ይህ አምስት ዓመት እንደተጠናቀቀ የሚቆጠረው ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ ሲከናወን ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን በአዲስ ምርጫ መካሄድ ቅድመ ሁኔታ ላይ የተመሠረተ እንጂ፣ ብቻውን የቆመ ድንጋጌ ባለመሆኑ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን የምርጫ ጊዜውን ተከትሎ የሚሄድ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) የሚያመለክቱት፣ በመደበኛው የመንግሥት አሠራር ጠቅላላ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ሊካሄድ እንደሚገባውና መደበኛው የመንግሥት የሥራ ዘመንም አምስት ዓመት መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ምርጫ መካሄድ የማይቻልበት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ፣ ይህ የአምስት ዓመት የምርጫ ጊዜና የመንግሥት ሥልጣንን የሥራ ዘመን ምን ሊሆን እንደሚችል ማየት አስፈላጊ ነው፡፡
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በኮቪጅ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ይህንኑ ለመቆጣጠርና ለመከላከል በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ቀጣይ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ እንዳልተቻለ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተረጋግጧል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከልና ለመቆጣጠር ሲባል አንዳንድ ሕገ መንግሥታዊ የዴሞክራሲ መብቶችን ለጊዜው በማገድ፣ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ጤናና ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አግባብ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት ከምርጫ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ የዴሞክራሲ መብቶች ተገድበዋል፡፡ ይህ በመሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) ሥር የተደነገገው መደበኛው የመንግሥት ሥልጣን የሥራ ዘመንና የምርጫ ማድረጊያ አምስት ዓመት ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም፡፡ በመሆኑም ይህ ዓለም አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር ውሎ ይህንኑ ቫይረስ ለመቆጣጠርና ለመከላከል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስኪነሳ ድረስ ቀጣይ ጠቅላላ ምርጫ ማካሄድ ጊዜ ሊራዘም ይገባል፣ የመንግሥት ሥልጣን የሥራ ዘመንም ሊቀጥል ይገባል፡፡
የሕገ መንገሥቱ ደንጋጌዎች 54(1)፣ 58(3) እና 93 ከአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ መርህና ዓላማ አንፃር
ጉባዔው ለትርጓሜ የቀረቡትን የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች 54(1)፣ 58(3) እና 93 ቀጥተኛ ትርጓሜ መሠረት በማድረግ ከላይ የተገለጸው አግባብ የተረጎማቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም ከሌሎች የሕገ መንግሥት ትርጓሜ መርሆዎችም አንፃርም ተመልክቷቸዋል፡፡ ጉባዔው በትርጓሜ ሒደቱ የተለያዩ የትርጓሜ መርሆዎችን የተከተለ ቢሆንም፣ በዋነኛነት የተሻለ ሆኖ የተገኘውን የሕገ መንግሥቱን ዓላማና መዋቅራዊ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም ዘዴን በመከተል ነው፡፡ ለማሳያነትም በሕገ መንግሥቱ የሠፈረ ማንኛውም ጉዳይ ትርጓሜ የሚያሻው ሆኖ ሲገኝ ትርጓሜ ሊሰጥ የሚገባው ከአጠቃላይ የሕገ መንግሥቱ ዓላማና መንፈስ፣ እንዲሁም የአንዳንዱ ለትርጓሜ የቀረቡ የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ዓላማና ሊደርስባቸው ከፈለጋቸው ግቦችና ሊያስወግድ ካሰባቸው ችግሮች አንፃር ስለሆነ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ትውልድ ተሻጋሪ የአገሪቱን ማናቸውንም ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎችና ጉዳዮች የሚመልስ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ዕድገት ሊያስገኝ የሚችልና የሕገ መንግሥቱን ፌዴራላዊ ሥርዓት ባከበረ መንገድ የዜጎችን የቡድንና የግል መብቶች የሚያስጠብቅ ሊሆን ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ድንጋጌዎች አተገባበር እርስ በርስ የሚቃረኑ ወይም አንድ ላይ ለመተግበር አስቸጋሪ ሲሆኑ፣ መፍትሔ መሰጠት ያለበት ከዚህ አንፃር ተተርጉሞ ነው፡፡ በዚህም ለሕገ መንግሥት ትርጓሜ የቀረቡት የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች 54(1)፣ 58(3) እና 93 ከሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ዓላማዎች፣ መርሆዎችና ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ እንደሚከተለው ተዳሷል፡፡
ለትርጓሜ ምክንያት የሆነው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች አንቀጽ 54(1)፣ 58(3) እና 93 ከአጠቃላይ የምርጫ መርህና ከሕዝቦች የሉዓላዊነት ሥልጣን ባለቤት አንፃር መተርጎም አስፈላጊ ነው፡፡ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጫ መሣሪያ ነው፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 8(1) ላይ እንደተደነገገው፣ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች›› መሆናቸውን፣ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የዚሁ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ መሆኑን በማያሻማ ሁኔታ ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም ሉዓላዊነታቸውን የሚገልጹት ወይም የሚተገብሩበት ዋነኛው መንገድም፣ በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው፡፡ ምርጫ ለአገሪቱ የዴሞክራሲ፣ የፌዴራሊዝምና ለዜጎች የመምረጥና መመረጥ መብት ወሳኝ መሣሪያ ነው፡፡ ከዚህ የሕገ መንግሥቱ መርህ መረዳት የሚቻለው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤቶች በመሆናቸው፣ በእነርሱ ምርጫ ካልሆነ በስተቀር የመንግሥትን ሥልጣን ሊያዝ አይችልም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው በሕዝብ የተመረጠው መንግሥትም በሕገ መንግሥት መሠረት ሥልጣኑን የመጠበቅና ቀጣይ በሕዝብ ለሚመረጡ ተወካዮች ሥልጣንን የማስረከብ ኃላፊነት አለበት፡፡
ይህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊነት መገለጫ የሆነው ምርጫ እንዴት መካሄድ እንዳለበት፣ መቼ መካሄድ እንዳለበትና የምርጫው ይዘት ምን መሆን እንዳለበት በሕገ መንግሥቱ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በተለይም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38(1) መሠረት›› ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በፆታ… ልዩነት ሳይደረግበት በቀጥታና በነፃነት በምርጫ መሳተፍ እንደሚችል›› ይደነግጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) እና 58(3) ላይ የተደነገገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሥራ ዘመንና ምርጫ የሚካሄድበት ጊዜ መተርጎም ያለበትም፣ ከዚሁ ከአጠቃላይ የምርጫ መርህና ከሕዝቦች የሉዓላዊነት ሥልጣን ባለቤትነት መርህ አንፃር ነው፡፡ የሕዝቦች የሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት የሚከበረውም ይህ የምርጫ መርህና ይዘት በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ሲሆን ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) ሥር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ መመረጥ እንዳለባቸውና የምርጫ ይዘቱም ሁሉን አቀፍ፣ ቀጥተኛና ትክክለኛ በሆነ ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት መካሄድ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡
በመሆኑም ምርጫ የዜጎች የሉላዓዊ ሥልጣን መገለጫቸው ነው የሚባለው በየአምስት ዓመቱ ስለተካሄደ ብቻ ሳይሆን፣ ይህንኑ ይዘቱን ያሟላ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ በመሠረቱ የዚህ ድንጋጌ አንቀጽ የምርጫ ጊዜ ዓላማና ግብ የምክር ቤቱ የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን ከመጠናቀቁ ከአንድ ወር በፊት በሕገ መንግሥቱ በተቀመጡ መሥፈርቶች መሠረት፣ አገረ መንግሥቱን ለማስተዳደር ከሕዝብ ውክልና የሚቀበል የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች በግልጽ እንዲለይና ለዚሁ ሥልጣንን ለማስረከብ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የአንቀጽ 58(3) ዋና ዓላማ በሕገ መንግሥታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር አገረ መንግሥቱ መንግሥት የለሽ እንዳይሆን፣ ከዚህም የተነሳ በአገሪቱ ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ህልውና ላይ አደጋ ወይም ቀውስ እንዳይፈጠር ሕገ መንግሥታዊ ጥበቃ ለማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ምርጫ ቀጣይነት ያለው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነት ወይም ምንጭነት መብት ቀጣይነት ያለው እንዲሆን በማድረግ በመንግሥት አስተዳደር የሥልጣን ክፍተት እንዳይፈጠር ማረጋገጥ ነው፡፡
የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች አንቀጽ 54(1)፣ 58(3) እና 93 ከአጠቃላይ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች አንፃር ሲታይ፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(3) ሊተረጎሙ የሚገባቸው በሕገ መንግሥቱ ከተጠበቁ የሰብዓዊ መብት ማዕቀፎችና ድንጋጌዎቹ መሠረታዊ ዓላማ አንፃር ነው፡፡ ከሕገ መንግሥቱ መግቢያ፣ መሠረታዊ መርሆዎች ከተደነገጉበት ክፍል፣ እንዲሁም ከአጠቃላይ ድንጋጌዎቹ መረዳት የሚቻለው ሕገ መንግሥቱ ሰብዓዊ መብቶችን ማዕከል ያደረገ ሰነድ መሆኑን ነው፡፡ በዚህም መሠረት በሕገ መንግሥቱ በምዕራፍ ሁለት አንቀጽ አሥር ሰብዓዊ መብቶችንና ነፃነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይጣሱና የማይገፈፉ እንደሆኑ፣ እንዲሁም የዜጎችና የሕዝቦች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ ይህንን መሠረት በማድረግ በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ ሦስት ለበርካታ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ ከዚህ አልፎ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(4) ላይ ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች የአገሪቱ ሕግ አካል መሆናቸውን በማወጅ፣ የሕገ መንግሥት መብቶች ጥበቃ እንዲሰፋ አድርጓል፡፡
ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች የቃል ኪዳን ሰነዶች ውስጥ፣ እንዲሁም በሕገ መንግሥቱ መሠረት እነዚህ መብቶች ሳይሸራረፉ ሊከበሩና ተግባራዊ ሊደረጉ እንደሚገባ ተደንግጓል፡፡ ሆኖም በሕገ መንግሥቱም ሆነ ኢትዮጵያ ባፀደቃቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም በሕጎቹ የተቀመጡ የገደብ መሥፈርቶች ሳይጣሱ፣ የአብዛኞቹ ሰብዓዊ መብቶች አፈጻጸሞች ሊገደቡ ይችላሉ፡፡ ሊገደቡ የሚችሉበት ዋነኛው ምክንያትም የአገርን ህልውናና የሕዝብ ደኅንነት ላይ የተረጋገጠ ከባድ አደጋን ለመቀልበስ በሚታወጅ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ዋነኛ ዓላማ የአገርን ደኅንነት፣ የሕዝብን ጤናና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን መጠበቅና ክስተቱን አስወግዶ አገርን ወደ መደበኛ ሁኔታዋ መመለስ በመሆኑ፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የሆነውን ክስተት ለማወስገድ በተፈለገው ደረጃ አብዛኞቹ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሊታገዱ ይችላሉ፡፡ ይህ ገደብ ደግሞ በምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ላይ ባደረሰው ተፅዕኖ፣ የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት ተግባራዊ እንዳይደረግ አድርጓል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና የምርጫ ጊዜን በተመለከተ
በተለያዩ አገሮች የሕግ ሥርዓት ውስጥ በሕገ መንግሥት ደረጃም ሆነ በሌሎች ሕጎች ውስጥ ያልታሰቡ፣ ያልተጠበቁ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች፣ እንዲሁም ከባድ የሆነና በመደበኛ ሁኔታ ለመቆጣጠር አዳጋች የሆኑ ችግሮች ወይም ክስተቶች በሚያጋጥሙበት ጊዜ፣ በፍጥነትና በበቂ ሁኔታ ለመመከት ወይም ለመቀነስ የሚረዳቸውን የአስቸኳይ ጊዜ ሕግ ይደነግጋሉ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያስከትሉ የሚችሉ አራት አጠቃላይ ሁኔታዎችን ለይቶ ያስቀምጣል፡፡ እነዚህም በአንቀጽ 93(1ሀ) ላይ እንደተደነገገው የውጭ ወረራ፣ በመደበኛው ሕግ የማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ መከሰት፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ማጋጠምና የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ መከሰት ናቸው፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሲከሰቱ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊያውጅ እንደሚችል ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡
የምርጫ ጊዜ መራዘምን በሚመለከት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 54(1) እና 58(3) ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 አንፃር ማየት ተገቢ ነው፡፡ የኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ በሰው ልጆች ጤናና ሕይወት ላይ የሚያደርሰው አደጋ የዜጎችን የጋራ መብትና ጥቅም ማስጠበቅ ሲባል፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የተወሰኑ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ገደብ አስቀምጧል፡፡ እነዚህ ገደቦች ደግሞ በምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ላይ ባደረሱት ተፅዕኖ ለሕዝብ ጤናና ደኅንነት ሲባል፣ የዜጎች የመምረጥና የመመረጥ መብት በተዘዋዋሪም ቢሆን ተግባራዊ እንዳይሆን አድርጓል፡፡ በመሆኑም በኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ወረርሽኙን ለመቆጣጠርና ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት፣ መደበኛው አምስት ዓመት የምርጫ ጊዜ ተጠብቆ ምርጫ ሊካሄድ አልቻለም፡፡ መደበኛው የምርጫ ጊዜ በኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ይህንኑ መቆጣጠርና ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ልዩ የምርጫ ጊዜ ሊኖር ይገባል፡፡ ስለሆነም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 38 መተግበር ላይ መሠረት ያደረጉት አንቀጽ 54(1) እና 58(3)፣ ቀጣይ አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ በተቀመጠለት የአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ መካሄድ ባለመቻሉ ሊራዘም ይገባዋል፡፡
የመንግሥት ሥልጣንና የሥራ ዘመንን በሚመለከት
የምርጫ ጊዜ መራዘምን ተከትሎ የሚነሳው ሌላው ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 (1)እና 58(3) መሠረት የመንግሥት ሥልጣን የሥራ ዘመን እንዴት ይሆናል የሚለውን፣ ከሕገ መንግሥቱ 93 መሠረት ማየት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥቱ ለሦስት ዓይነት የመንግሥት የሥልጣን ዘመንን ዕውቅና የሰጠ ነው፡፡ መመርያው መደበኛውን የመንግሥት የሥልጣን ዘመን የሚመለከት ሲሆን፣ ይኸውም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1)፣ 58(3)፣ 67(2) እና 72(3) ላይ የተመለከተው የአምስት ዓመት የመንግሥት ሥልጣን ዘመን ነው፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ መደበኛ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት መሆኑን ነው፡፡ ከመደበኛ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ያነሰ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን የሚመለከት፣ እነዚህም ሁኔታዎች በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12(3)፣ 54(7)እና 60 ተደንግገው ይገኛሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 12(3) እና 54(7) ላይ እንደተመለከተው፣ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ በማንኛውም ጊዜ ከቦታው ለማንሳት ይቻላል፡፡ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት የማጣት ሁኔታ በተመሳሳይ ወቅት መጠነ ሰፊ በሆነ ሁኔታ ከተከሰተ፣ የመደበኛ መንግሥት የሥልጣን ዘመን መፋለስን ሊያስከትል ይችላል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 60 ላይ እንደተመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ፣ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል፡፡ በዚህም ሕገ መንግሥታችን የመንግሥት የሥልጣን ዘመን በአንቀጽ 54(1)፣ 58(3)፣ 67(2)፣ 72(3) ከተመለከተው መደበኛው የአምስት ዓመት የሥልጣን ዘመን በታች ሊያጥር የሚችልበትን ሁኔታዎችን ደንግጎ ይገኛል፡፡
ሦስተኛው አሁን ለዚህ የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ምክንያት የሆነው፣ ከመደበኛው የመንግሥት የሥልጣን ዘመን የረዘመ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ነው፡፡ ይኸውም በምርጫ ዘመን ወይም ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጀበት ጊዜ፣ ያለውን የመንግሥት ሥልጣን ዘመን ሁኔታ ይመለከታል፡፡ በመሆኑም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 መሠረት መንግሥት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት የሆነውን የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ለማስወገድ መደበኛ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን የሚመለከቱ የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌዎች ጨምሮ፣ ሌሎች የፖለቲካ መብቶችን ለጊዜው በማገድ አጠቃላይ የማኅበረሰቡን ጤናና ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በዚህም ሕገ መንግሥቱ መደበኛ የመንግሥት የሥራ ዘመን ካለፈ በኋላ መንግሥት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ ዕውቅና በመስጠት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ወረርሽኙን እንዲያስወግድ በመንግሥት ኃላፊነት ተጥሎበታል የሚለው ሐሳብ በሕገ መንግሥቱ በተዘዋዋሪ መካተቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና መደበኛ የምርጫ ዘመን ወይም ወቅት አንድ ላይ በሚገጣጠሙበት ወቅት፣ ይኸው ሁኔታ ከምርጫ ሒደትና አፈጻጸም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ የተመለከተው መደበኛ የመንግሥት ሥልጣን የሥራ ዘመን ተፈጻሚነት አይኖረውም፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ለተለየዩ መንግሥት የሥልጣን ዘመን ዕውቅና የሰጠ መሆኑን፣ ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 እና ሌሎች ድንጋጌዎች አንድምታ መረዳት ይቻላል፡፡
በአንቀጽ 54(1)፣ 58(3) የተናጠል ንባብ መሠረት የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን አምስት ዓመት እንደሆነና በየአምስት ዓመቱ ምርጫ እየተደረገ፣ በሕዝብ የሚመረጡ ተወካዮች በሕገ መንግሥታዊ መንግድ ሥልጣን የሚረከቡበት መንገድ መሆኑና በምንም ሁኔታ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ከአምስት ዓመት በላይ ሊራዘም እንደማይችል በሕግ የተገደበ መሆኑን የሚያመለክት ወይም የሚመስል ቢሆንም፣ የሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ንባብ ከሌሎች የሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ዓላማዎች፣ መርሆዎች ድንጋጌዎች ጋር ሲታዩ ወይም ሲተረጎሙ ግን በመደበኛ ሁኔታ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን አምስት ዓመት ቢሆንም፣ እንደ ኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ይህንኑ ለመቆጣጠር ለመከካል የሚያስፈልግ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲያጋጥም ግን፣ የመንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመደበኛው አምስት ዓመት ሊረዝም እንደሚችል ከሕገ መንግሥቱ መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ስድስተኛው ብሔራዊ ጠቅላላ ምርጫ በኮሮና ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት በአንቀጽ 54(1)፣ 58(3) መሠረት በመደበኛው አምስት ዓመት የምርጫ ጊዜ ሊካሄድ ስላልቻለ፣ ቀጣይ ምርጫ ከዚህ በታች ባለው የውሳኔ ሐሳብ ክፍል በተቀመጠው ጊዜና ሁኔታ ወደፊት መካሄድ አለበት፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የሥራ ዘመንም በተመሳሳይ ሁኔታ በመደበኛው የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን መጠናቀቅ ስላልቻለ፣ ቀጣይ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ ለአሸናፊ የፖለቲካ ድርጀት/ድርጅቶች ሥልጣን እስኪያስረክብ ድረስ መቀጠል አለበት፡፡
ሥልጣኑን ይዞ የሚቀጥለው መንግሥት ኃላፊነትን በተመለከተ
ሥልጣኑን ይዞ የሚቀጥለው መንግሥት ቀጣይ አዲስ ምርጫ ተደርጎ የሥልጣን ርክክብ እስከሚደረግ ድረስ ሊኖረው የሚገባው ሥልጣንና ኃላፊነት ምን ሊሆን ይገባል የሚለው ጉዳይ፣ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ነጥብ ነው፡፡ ጉባዔውም ጉዳዩን ከሕገ መንግሥቱ ጠቅላላ ዓላማና ሊያሳካቸው ካሰባቸው ግቦች አኳያ መርምሮታል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ዓላማዎች በተገለጸበት የሕገ መንግሥቱ መግቢያ፣ ‹‹በአገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገታችን እንዲፋጠን፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣ በነፃ ፍላጎታችን፣ በሕግ የበላይነትና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት›› ተብሎ ሠፍሮ ይገኛል፡፡ ከዚህ የሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ ዓላማ አንፃር ሥልጣን ይዞ የሚቀጥለው መንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት እነዚህን የሕገ መንግሥቱን መርሆዎች ለማሳካት በሚያስችለው መንገድ መሆን ይገባዋል፡፡ መንግሥት ቀጣይ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታውንና የምርጫ ዝግጅትን ታሳቢ በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል፣ በተቻለ ፍጥነት በቁጥጥር ሥር አውሎ ክስተቱን ለማስወገድ፣ አገሪቱን ወደ መደበኛሥርዓት ለመመለስ የተቀናጀና ሁሉን አቀፍ ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(2) እና አንቀጽ 12(1) መሠረት አሠራሩን ግልጽና ተጠያቂነት የሚፈጥርን ሥርዓት በመዘርጋት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስቀጠል አለበት፡፡
ቀጣይ ምርጫ የሚደረግበትን ጊዜ በተመለከተ
በዓለም አቀፍ ደረጀ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት 53 አገሮች ጠቅላላ፣ የአካባቢ፣ የማሟያ ወይም ሕዝበ ውሳኔዎችን ሰርዘዋል፡፡ ከእነዚህ አገሮች መካከል እንደ ህንድና ካናዳ የመሳሰሉ አገሮች ሕገ መንግሥታቸው በግልጽ ድንጋጌዎች በማስፈር ሥልጣን ላይ ያለውን የሕግ አውጪውና አስፈጻሚው አካላት ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ተደርጎ፣ ምርጫው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ፣ በተወሰኑ ጊዜ ውስጥ እንዲከናወን የሥልጣን ጊዜያቸውን እንደሚያበቃ ተደንግጓል፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ግልጽ ድንጋጌ የሌለው በመሆኑ፣ ምርጫው መቼ መደረግ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱን በመተርጎም ማሟላት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ቀጣይ ምርጫ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊደረግ ይገባዋል የሚለው ጭብጥ ቀጥሎ ምላሽ የሚያስፈልገው ነው፡፡ ይህ ነጥብ ታሳቢ የሚያደርገው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በያዘለት ጊዜ እንዳይደረግ ምክንያት ከሆነው የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ሥጋትና ሥርጭቱን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ተግባራዊ የተደረጉ ክልከላዎች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በመሆኑም ጉባዔው ምርጫው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን እንደሚገባው ከመምረጥና መመረጥ መብት እንዲሁም ነፃ፣ ሁሉን አቀፍ፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ፣ በቀጥታ፣ በሚስጥር ድምፅ አሰጣጥ መራጩ ነፃ ፈቃዱን የሚገልጽበት፣ ዋስትና የሚሰጥ ምርጫ ለማድረግ አስፈላጊ የሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጉዳዩን አግባብነት ካላቸው የሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ጋር በማጠመር መርምሯል፡፡
የቫይረሱ ሥርጭት እያለ ምርጫ እንደማይችል ከተረጋገጠ የሥርጭት መጠኑ በምን ያህል ቢቀንስ ምርጫ ሊደረግ ይችላል? የሚለው ቀጣይ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93(1) (ሀ) መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ አንዱ ምክንያት የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ ድንጋኔና አሁን ካለንበት ነባራዊ ሁኔታ ሲተሳሰር፣ ኢትዮጵያ በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ የምትቆየው በሽታው የሕዝብ ጤንነት አደጋ መሆኑ እስከቀጠለበት እንጂ፣ ክስተቱ ሙሉ በሙሉ እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ ሊሆን አይችልም፡፡ በመሆኑም ከሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ መንፈስ አንፃር የተያዘው ጉዳይ ሲተረጎም፣ ቀጣይ ምርጫ ሊከናወን የሚገባበት ጊዜ ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና አደጋ መሆኑ ካበቃ ጀምሮ በሚቆጠር የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊሆን ይገባል፡፡
ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና አደጋነቱ አብቅቷል የሚባለው መቼ ነው የሚለውን ጉባዔው በአስረጂነት አስቀርቦ ከሰማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የጤና ባለሙያዎች ክትባት ሲገኝ ወይም መድኃኒት ሲገኝ፣ ወይም በሒደት የሚገኙ ሳይንሳዊ ግኝቶችን መሠረት በማድረግ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ባለበት ደረጃ ለቫይረሱ መድኃኒት ወይም ክትባት እንዳልተገኘና መቼ እንደሚገኝ በግልጽ የታወቀ ነገር የለም፡፡ በመሆኑም ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ነጥብ በሕገ መንግሥቱ መሠረት፣ ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑ በማን ሊረጋገጥ ይገባል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡
በመሠረቱ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ እንደ መሆኑ ቫይረሱ የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆኑ የሚያበቃበትን ጊዜ የሚወስነው የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብን፣ የአጎራባች አገሮች የጤና ሁኔታንና ዜጎች የሚኖራቸውን የተጋላጭነት መጠንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በየደረጃው የዓለም ጤና ድርጅት፣ በኢትዮጵያም የጤና ሚኒስቴር፣ እንዲሁም የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና ሌሎች የሳይንስ ማኅበረሰቡ አባላት ጋር በመመካከር የሚያወጡት መረጃዎች መሠረት ተደርጎ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን መረጃ መሠረት በማድረግና አገራችን አገሪቱ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የቫይረሱን ሥርጭትና የኅብረተሰቡን ተጋላጭነት ከሳይንስ ማኅበረሰቡ ጋር በመመካከርና በመቀመር፣ ጤና ሚኒስቴር ውሳኔውን ወይም የውሳኔ ሐሳቡን ሲያቀርብ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55(17) እና 55 (18) የአስፈጻሚውን አካል አሠራርን የመመርመርና አስፈላጊ የሆነውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በዚህም መሠረት ወረርሽኙ በቁጥጥር ሥር ስለመዋሉ በጤና ሚኒስቴር የቀረበለትን የውሳኔ ሐሳብ የማፅደቅ ሥልጣን ይኖረዋል፡፡
በመቀጠል ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው ሌላው ነጥብ በሽታው የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆኑ ካበቃበት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ምርጫ ሊደረግ ይገባል የሚለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ በአንቀጽ 60(3) መሠረት ከስድስት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ምርጫ ማድረግ እንደሚቻል ይደነግጋል፡፡ ይህ ድንጋጌ መደበኛ የሕግ ሥርዓትንና ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ እንጂ፣ አገር በአስቸኳይ ጊዜው ውስጥ የቆየችበትን ሁኔታ አይደለም፡፡ በመሆኑም ይህን ድንጋጌ በቀጥታ አሁን ላለንበት ሁኔታ ተግባራዊ መሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህን ጊዜ መወሰንን በሚመለከት ሕገ መንግሥቱ ምን ይላል የሚለው ሊታይ ይገባል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ምርጫ ቦርድ ነፃና ትክክለኛ ምርጫ ለማካሄድ ሙሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ያለው በመሆኑ ጉባዔው የምርጫ ቦርድን በአስረጂነት አስቀርቦ በመጠየቅና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ በኋላ የወደፊቱ የምርጫ ሁኔታ ምን ሊሆን ይችላል ለሚለው፣ በቦርዱ ሁለት የቢሆን ውሳኔዎችን ያስቀመጠበትን ሰነድ መርምሯል፡፡ ሁለቱም የቢሆን ሁኔታዎች ታሳቢ የሚያደርጉት የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሚቀጥል ሆኖ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ መነሳትን ነው፡፡ የአዋጁንም መነሳት ተከትሎ የመጀመርያ የቢሆን ሁኔታ ቦርዱ ምርጫን ለማስፈጸም ተጨማሪ የጥንቃቄ ዕርምጃዎችን ሳያደርግ በተጨማሪ በጀት በአሥር ወራት ምርጫውን ማስፈጸም እንደሚችል አስቀምጧል፡፡ በሁለተኛው የቢሆን ሁኔታ ኮቪድ 19 ቦርዱ የቫይረሱን ሥርጭት ለመቆጣጠር ተጨማሪ ዕርምጃዎችን ቢወስድ የሚፈጅበትን በጀት በመጥቀስ 13 ወራት እንደሚፈጅበት አስቀምጧል፡፡
በምርጫ ቦርድ ዳሰሳ መሠረት ቫይረሱ በሥርጭት እያለ ቦርዱ የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ምርጫውን ከአሥር እስከ 13 ወራት ውስጥ ሊያካሂድ እንደሚችል አስረድቷል፡፡ በመሆኑም ጉባዔው የቀረቡት ሁለቱን የቢሆን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባትና የምርጫ ቦርድ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሥጋትና ክልከላዎች ጋር ተያያዥነት የሌላቸውን ሥራዎችን እያከናወነ ሊቆይ እንደሚገባው ታሳቢ በማድረግ፣ የኮሮና ቫይረስ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት መሆን ካበቃበት ጊዜ አንስቶ ከዘጠኝ እስከ 12 ወራት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ምርጫው መካሄድ አለበት ብሏል፡፡
የምርጫ መራዘምና የመንግሥት ሥልጣን ሥራ ዘመን በፌዴራልና በክልሎች ያለው አንድምታ
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በምክር ቤቱ ለትርጓሜ የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄና የሚሰጠው የትርጓሜና የውሳኔ ሐሳብ ተፈጻሚነት፣ በፌዴራል ምክር ቤቶችና አስፈጻሚው አካላት ላይ ብቻ ነው? ወይስ በክልል ምክር ቤቶች፣ በአስፈጻሚው አካላትና በክልል የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ላይ ጭምር ነው? የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል፡፡ የምክር ቤቱ አጠቃላይ የትርጓሜ ጥያቄ አንደኛ በአጠቃላይ አገላለጽ የምክር ቤቶቹና የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን እንዴት ይሆናል የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ማድረግ አለመቻሉ የሚመለከተው ጠቅላላ ምርጫን እንጂ፣ ለይቶ የፌዴራል ምክር ቤቶችን ምርጫ ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ ለሕገ መንግሥት ትርጓሜ መቅረብ ምክንያት የሆነው የኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና ወረርሽኙን ለመከላከልና መቆጣጠር የወጣው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተፈጻሚነትም፣ በፌዴራል መንግሥት የተገደበ ሳይሆን ክልሎችንም የሚጨምር ነው፡፡ በሕገ መንግሥት አንቀጽ 93(ሀ) መሠረት የፌዴራል መንግሥት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር አገር አቀፍ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጥቶ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 102 መሠረት በፌዴራልና በክልሎች ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት እንዲካሄድ፣ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ እንደሚቋቋም ይደነግጋል፡፡ የዚህ ቦርድ መቋቋም ዋነኛ ዓላማ ገለልተኛ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ የሆነ ምርጫ እንዲካሄድ ለማድረግና ይህንኑ ለማስፈጸም ነው፡፡ ቦርዱ እንዲቋቋም የተደረገው በፌዴራልና በክልሎች ምርጫን ለማስፈጸም ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን የምርጫ ሕግ የማውጣት ብቻ፣ በፌዴራል መንግሥት በሚወጣው የምርጫ ሕግ አግባብ በፌዴራልና በክልሎች ሕጉን የማስፈጸም ሥልጣንና ኃላፊነትም የፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ነው፡፡
አሁን የቀረበው የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ በጥቅሉ የምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል ሥልጣን ምን እንደሚሆን የሚጠይቅ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ ምክንያት የሆነው፣ ምርጫ ቦርድ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት ጠቅላላ ምርጫ በፌዴራልና በክልሎች የምርጫ ክልሎች ለማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ቦርዱ ላለማካሄድ የዝግጅት ሥራ ጀምሮ የነበረው ጠቅላላ ምርጫን ለማካሄድ ሲሆን፣ በኮቪድ 19 ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ ምክንያት ሳያደርግ ያቋረጠው ይህንኑ ጠቅላላ ምርጫ ስለሆነ የውሳኔ ሐሳቡ በፌዴራሉና በክልሎች የምርጫ ጊዜና በምክር ቤቶችና በአስፈጻሚዎች የሥራ ዘመን ላይ ተፈጻሚነት አለው፡፡
የውሳኔ ሐሳብ
የኢፌዴሪ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ በኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበለትን የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጥያቄ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 54(1)፣ 58(3) እና 93 በመተርጎም ውሳኔ እንዲሰጠው ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የሚከተሉትን የውሳኔ ሐሳቦች በሙሉ ድምፅ አቅርቧል፡፡
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 54(1)፣ 58(3)፣ 67(1) እና 72(3) ላይ የተደነገገው የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ከአንቀጽ 93 እንዲሁም ከሕገ መንግሥቱ መሠረታዊ መርሆዎች፣ ዓላማዎችና ግቦች ጋር በማገናዘብ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሕዝብ ጤና ሥጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ሥርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 ፀንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያትና ከተነሳም በኋላ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የሥልጣን ርክክብ እስከሚፈጸምበት ጊዜ ድረስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የሥራ ዘመን እንዲቀጥል በማለት፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84(1) መሠረት የኢፌዴሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
የኮቪድ 19 ሥርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠርና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 3/2012 እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ወረርሽኝ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች የሚያወጡትን መረጃ መሠረት በማድረግ፣ ጤና ሚኒስቴር፣ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትና የሳይንሱ ማኅበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ሥጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ቀን ጀምሮ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ በማለት፣ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 84(1) መሠረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጥበት የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡