በኢትዮጵያ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ተነጥሎ ወጥቶ ራሱን በቻለ አሠራር አገልግሎት እንዲሰጥበት፣ ከጥንስሱ ጀምሮ በመደበኛ ባንክነት ለመመሥረት ሲንቀሳቀስ የቆየው ዘምዘም ባንክ፣ ከዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ ምሥረታውን ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉትን ሕጋዊ መሥፈርቶች አሟልቶ የሥራ መጀመርያ ፈቃድ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
በምሥረታ ላይ የሚገኘው ዘምዘም ባንክ ሰኔ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠውን ማረጋገጫ መሠረት በማድረግ ባወጣው መግለጫ፣ ወደ ሥራ ለመግባት የሚጠበቁበትን መሥፈርቶች ከማሟላት ባሻገር፣ የተሸጡና የተረፈሙ አክሲዮኖችን በሰነዶችና ማረጋገጫ ምዝገባ ጽሕፈት ቤት ማስመዝገቡን ገልጿል፡፡ በዚህም የመጀመርያው የተሟላ የወለድ አልባ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚችልበት የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ከ1999 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በመደበኛ ባንኮች ደረጃ መቅረብ ስለሚቻልበት መንገድ ሐሳብ በማመንጨት፣ የአዋጅ ማዕቀፍ እንዲወጣና የወለድ ነፃ ባንክ ለማቋቋም የሚያስችል ካፒታል በማሰባሰብ ሥራውን ሲያደራጅ የቆየው ዘምዘም ባንክ፣ በይፋ ባልተገለጸ ምክንያት በ2003 ዓ.ም. የምሥረታ እንቅስቃሴውን ለመቀልበስ እንደተገደደ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ባንኩን ሥራ ለማስጀመር አስፈላጊውን ሒደት በማጠናቀቅ ይፋዊ ምሥረታውን ለማብሰር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
አዲሱ የመንግሥት አስተዳደር ቦታውን ከተረከበ ከሁለት ዓመት ወዲህ የዘምዘም ባንክ አክሲዮን ማኅበር የተነሳለትን ዓላማ ለማሳካት ሲንቀሳቀስ መቆየቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ካቢኔያቸው ከመጡ ጊዜ ጀምሮ ወለድ አልባ ባንክ የመመሥረት ጥያቄውን ዳግም በማንሸራሸር አሁን ለደረሰበት ደረጃ በቅቷል፡፡ ከብሔራዊ ባንክ ባንክ ባገኘው ምላሽ መሠረት፣ ከግንቦት 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ባገኘው ማረጋገጨ መሠረት የምሥረታ ሒደቱን እንዳጠናቀቀ ዘምዘም ባንክ ይፋ አድርጓል፡፡
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ዘምዘም ባንክን በአዲስ መንገድ ለማደራጀት በተካሄደው የአክሲዮን ሽያጭ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታል ማሰባሰቡን የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡ የተከፈለ ካፒታሉ 886.02 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ሲገለጽ፣ 11,200 ሰዎች የባንኩን አክሲዮኖች መግዛታቸው ተጠቅሷል፡፡
ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ባደረገው የአክሲዮን ፈራሚዎች ጉባዔ፣ የባንኩን የመመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ በማፅደቅ የቦርድ አባላትን በመሰየም የባንክ ምሥረታ ሒደቱ የሚጠይቃቸውን የሁለተኛ ዕርከን መሥፈርቶች በማሟላት ሰኔ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ከብሔራዊ ባንክ ማረጋገጫ አግኝቷል፡፡ የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ቃለ ጉባዔ፣ መተዳደሪያ ደንብና የመመሥረቻ ጽሑፉ በገዥው ባንክ ፀድቀውና አስፈላጊውን ምዝገባ ለማጠናቀቅ ወደ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ ሰነዶች መላካቸውን ባንኩ አስታውቋል፡፡
የባንኩን ሒደት ከጫፍ ለማድረስ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ በሚያወጣው ሰሌዳ መሠረት የፊርማ ሒደቱ በቅርቡ እንደሚጀመር በመግለጹም፣ የአክሲዮን ግዥ የፈረሙ አባላት ለዚህ ይዘጋጁ ብሏል፡፡
የባለአክሲዮኖች ፊርማው ከተጠናቀቀ በኋላ በቀጥታ ሥራ እንደሚጀምር የሚያመላክተው የባንኩ መረጃ፣ ‹‹ለዚህ ታሪካዊ ስኬት እንድንበቃ በተለያየ መንገድ ላገዙንና የሥራ መስክን የመምራት ሕገ መንግሥታዊ መብት እንዲከበር ወሳኝ ዕርምጃ በመውሰድ የዜግነት ክብርን በተግባር ላሳዩን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና መንግሥታቸው ምሥጋናቸው የላቀ ነው፤›› ብሏል፡፡
የባንኩን ምሥረታና ሥራ ለማስጀመር ታቅዶ የነበረው በመስከረም 2012 ዓ.ም. ቢሆንም፣ በዚህ ዘርፍ ራሱን የቻለ ባንክ ለመመሥረት አዲስ ከመሆኑ አንፃር የተለያዩ ሒደቶችን ማለፍ የግድ ስለሚል በታሰበው ጊዜ ባንኩን ሥራ ማስጀመር አለመቻሉንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዘምዘም ባንክ ምሥረታ ጋር በተያያዘ እስካሁን በኢንዱስትሪው ውስጥ ባልተለመደ ሁኔታ የባንኩን ባለአክሲዮኖች በሕትመት ሚዲያ ላይ እንዲያሳትም ስለመታዘዙና ይህንን ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለመተግበር ክፍያ መፈጸሙም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
እንደ ዘምዘም ባንክ ሁሉ ራሱን የቻለ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ አራት ባንኮች በምሥረታ ሒደት ላይ እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ እነዚህ በምሥረታ ላይ የሚገኙ ባንኮች በተለያየ ሒደት ላይ ስለመሆናቸውም ይጠቀሳል፡፡
ሆኖም ከአንዱ ባንክ በስተቀር ሦስቱ አስፈላጊውን መሥፈርት ለማሟላት አሁንም ገና ስለመሆናቸው ተገልጿል፡፡