Sunday, June 23, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሦስት ጊዜ አይሞትም

በተመስገን ታረቀ

የአባቶቻችን ብሂሎች ጥልቅና ጠንካራ መልዕክት አስተላላፊዎች ናቸው። አንዱ ለጠላቱ ‹‹ዘጠኝ ሞት ይዤልህ መጥቻለሁ›› ቢለው ‹‹አንዱን ግባ በለው›› አለው ይባላል። ሞት አንድ እንጂ ዘጠኝ ሊሆን ስለማይችል። እርግጥ ነው በሕይወት ብዙ መከራና ውጣ ውረድ ሊኖር ይችላል። አኗኗሩም ከሞት ያልተሻለ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሞትን የሚሞት በሥነ ልቦና የሞተ ነገር ግን በሥጋ የሚኖር ማለት ነው። የሥነ ልቦና ሞት አይደለም ዘጠኝ ከዚያ በላይም የሚሆን አሟሟት ሊሆን ይችላል። የዕድሜያችንን ያህል የሚቆጠር አሟሟት ማለት ነው። ሥቃይ የበዛበት የሥነ ልቦና አሟሟት ከመሞት ቀልጠፍ ያለ የሥጋ ሞት ተመራጭ ነው። ለዚህም ነው ‹‹አሟሟቴን አሳምረው›› የሚባለው።

ወደ ተነሳሁበት ሐሳብ ልንደርደርና መቼም ዘለዓለማዊ ህያውነት የለምና ሀብት ይዞ ተርቦ መሞት? ወይስ ሀብትን ተጠቅሞ መኖር ያለብንን ያክል ኖሮ መሞት? የቱን እንምረጥ? በተደጋጋሚ እንደሚባለው ‹‹አፍሪካ በጉንጯ ምግብ ይዛ የምትራብ አኅጉር ናት›› ይባላል። ይህ አባባል ምናልባት ከሰሃራ በላይ ላሉት የአኅጉሪቷ አገሮችን አይመለከት ይሆናል። ከሰሃራ በታች ላሉት አገሮች ብዙ የተፈጥሮ ሀብት እያላቸው በአግባቡና በወጉ መጠቀም ያልቻሉትን የሚመለከት ነው። ከነዚህ አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ ናት። ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ኖሯት የድሆች ሁሉ ደሃ ተብላ የተፈረጀች ናት። እውነት ነው በልቶ ለማደር የሚቸገሩ ብዙ ወገኖች አሉን፣ የመብራትና የኃይል አቅርቦት የማያውቁ ገና በቤት እንስሳት ኩበትና ፍግ እንዲሁም የተመናመነውን ደን በመጨፍጨፍ ለማገዶነት የሚጠቀሙት ብዙዎች ናቸው፡፡ ረዥም ርቀት የመጠጥ ውኃ ፍለጋ በመጓዝ በጀርባዋ ከክብደቷ የበለጠ ውኃ በደረቷ ደግሞ  ልጇን ይዛ በኪሎ ሜትር የምትጓዝ ዓይነት እናቶች ብዙ ናቸው። ከእጅ ወደ አፍ  የሆነው ኑሮ አሸንፏቸው ልጆቻቸው በስደት የአሞራና የዓሳ ነባሪ ቀለብ የሚሆኑት ወገኖቻችንን ብዛት ቤት ይቁጠረው። የድህነታችንን መለኪያ ስንቱን ዘርዝረን እናስቀምጠው? ዳሩ ግን ትልቁ እንቆቅልሽ/ፓራዶክስ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ያላት አገራችን ይህ ሀብት ለምን ሊታደገን አልቻለም? ‹‹የውኃ ማማ›› እየተባለች በውኃ ሀብቷ ያልተጠቀመች አገር፣ በገፀ ምድር ውኃዋ እምቅ አቅም መጠን ከአፍሪካ ከኮንጎ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ያለች አገር ናት። የተስፋ ዳቦ ምኞት የተቀኘላት ‹‹የዳቦ ቅርጫት›› የምትባል ኢትዮጵያ ምኞቱ ከምኞት ለምን እልፍ አላለም? እርግጥ ነው ተስፋዋ ተስፋ ብቻ ምኞቷም ከንቱ ሆኖ እንዲቀር ሌት ከቀን በሥውር የሚሠሩ አሉ፡፡ ለብዙ ዘመናት በሥውር የሴራ ቀመር በመቀመር ሀብታችንን የመጠቀም አቅማችንን ከንቱ የሚያደርጉ ነበሩ። አሁንም አሉ። ይህን ሁሉ ተቋቁመን አሁን ላይ የውኃ ሀብታችንን የመጠቀም አቅማችንን ለመጠቀም የምንችል መሆናችንን ትንሽ ጭላንጭል ብልጭ ሲል ፊት ለፊት ሊዋጉን ጦር እየሰበቁ ነው።

ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የውኃ ሀብታችንን በመጠቀም ከድህነት ጠለል ከፍ ብለን ልንታይ የምንችልበት አንደኛው ማሳያ ነው። የዚህ ግድብ የግንባታ ወጪ የእኛው ምንም የሌለው ዜጋችን ከከፈለው ግብር በተጨማሪ በየግሉ ያዋጣው ገንዘብ ነው፡፡ ውኃውም የራሳችን ነው፡፡ መሬቱም የራሳችን ነው። ዳሩ ግን ግብፅ (ምስር) ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ዛቻዋን በላይ በላይ እያዥጎደጎደችብን ነው። ገንዘቡም፣ ውኃውም እንዲሁም መሬቱም የእናንተ ቢሆንም ከድህነት አዘቅት መውጣት ስለሌለባችሁ የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ማድረስ አትችሉም። ስትጀምሩትም አይጨርሱትም ብዬ ገምቼ ነው፡፡ ጀምረው የደሃ ገንዘባቸውን አፍስሰው አቅማቸውን ፈትሸው ተስፋ ቆርጠው ይተውታል ብየ ገምቼ ነው። አሁን ላይ ግን ደሃ ኢትዮጵያውያን ወገባቸውን አስረው ከፍጻሜ ሊያደርሱ መሆኑን ሳረጋግጥ ተጀምሮ ሊጠናቀቅ? ወይ እኔ አልያም እናንተ ትኖሯታላችሁ? እያለች ነው ምስር።

ወገን ሆይ ከድህነት ጋር በመኖር በረሃብ፣ በስደት፣ በበሽታ እንዲሁም በእርስ በርስ ጦርነት አንገታችንን ደፍተን መኖር አለብን ወይስ እነዚህን ሕፀፆች ቀልብሰን አንገታችንን ቀና በማድረግ ከፈጣሪ የተሰጠንን ሀብት አልምተን ወደ ብልፅግና ከፍታ መረማመድ ይኖርብናል? በተፈጥሮም ይሁን በታሪክ የተሰጡን ሀብቶች እንዳንጠቀም ለዘመናት ሲተበተብብን የነበረ አሻጥር በመበጣጠስ የመጠቀም መብታችንን ማስከበር አለብን? ወይስ ድህነት፣ በሽታ፣ ስደትና ሎሌነት ለኢትዮጵያውያን የተሰጠን ፀጋ አድርገን በመቀበል አንገታችንን ደፍተን ጀርባችንን ሰጥተን እንኑር? የቱን መምረጥ ይኖርብናል? እያለን መራብ አለብን? መሥራት ስንችል ተሰደን ለሌሎች ሎሌ እንሁን? መታከም ስንችል ሳንታከም እንሙት? ከሕዝባችን ቁጥር ሰባው እጅ ሊሠራ የሚችለው ወገናችን የሥራ ዕድል መክፈት ስንችል ሥራ አጥነትን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመርን ተስፋ ቢስ ወጣት እናድርገው? በፍርፋሪ እንጀራ የጠላት ተላላኪ በማድረግ ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ ትውልድ እንፍጠር?

በእኛ በአገራችን ቅርርባችንን ስንገልጽ የወንዜ ልጅ እንላለን። ትዳርን እንኳን ስንገልጸው ከውኃ ጋር አያይዘን ከአንድ ምንጭ የተቀዱ እንላለን። እናም ግብፃውያን (ፈርኦናውያን) ወንድሞቻችን ውኃን ተጋርቶ ሕይወቱን ሙሉ የሚኖር ሕዝብ ሊተዛዘን አይገባውም? ጥቁር ዓባይን የግል አንጡራ ገንዘባችሁ አድርጋችሁ ከጫፉ እንዳትደርሱብን ስትሉ ሰውኛ ስሜት አይሰማችሁም? ራስ ወዳድነት ቢባል አያንሰውም፡፡ ፈርኦናውያን ወንድሞቻችን ይህ ከሆነ ሐሳባችሁ ሲበዛ ራስ ወዳድ ናችሁ፡፡ ለናንተ ክብር ሲባል ሌላው ቢሞት ደንታ የማይሰጣችሁ ናችሁ። በናይል የምታገኙትን ክብር ከምታጡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በተለይ ለኢትዮጵያ ደንታ የላችሁም ማለት ነው። እናንተ ሙቱ እኛ እንኖርላችኋለን እያላችሁን እንደሆነ እየተረዳነው ነው፡፡ አብረን ተደጋግፈን መኖር ምርጫችሁ ቢሆን ኖሮ የቅኝ ግዛታችሁን ውሎች የሙጥኝ አትሉም ነበር። አንዳንችን ሌላችንን ሳንጎዳ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሁላችንንም የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም። በሰውኛ አዎንታዊ አስተሳሰብ የሚያስብ ሰው ማንንም ከፍ ወይም ማንንም ዝቅ ማድረግ የለበትም። ይህን ሁሉ ለመዘብዘብ ያነሳሳኝ መሠረታዊ አመክኖዬ ‹‹በትንሽ የሚገመት በትልቁም እንዲሁ ነው›› እንደሚባለው ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ ያላት ትሩፋት ከ85 በመቶ በላይ ሆኖ እያለ የግብፅ ምድር ለዚህ ወንዝ ምንም አስተዋጽኦ የማያበረክት እንደሆነ እየታወቀ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታን ግብፅ አምርራ መቃወሟ ነው። ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኃይል ማመንጫነት የሚውል በመሆኑ የሚቀንስ የፍሰት መጠን አለ በሚል ተጋኖ የሚወራለት ሆኖ አይደለም። ለእኛ ኢትዮጵያውያን ግን ሕይወት አድን ነው። ለግብፅና ሱዳንም ቢሆን የውኃ ዋስትና እንዲኖር በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚኖረው ነው የሚሆነው። ታዲያ የዚህ ግድብ ግንባታ ለግብፅ እንቅልፍ ያሳጣ ጉዳይ ሆኖ ለጦርነት ነጋሪት የሚያስጎሽም መሆኑ ተገቢ ነው?

ኢትዮጵያ የነዳጅ ሀብት አላት እየተባለ ጠብታው የማይታይ፣ የውኃ ማማ እየተባለች የውኃ ልማትን መሥራት አትችልም የምትባል፣ የተረጋጋ የመንግሥት አስተዳደር እንዳይኖር የእርስ በርስ መፋጠጥና መዋጋት እንዲሆን ከጀርባ ማን እንዳለ ፊት ለፊት በይፋ እያወቅነው ነው። ማደጋችንን የማትፈልገው ግብፅና የእሷ ጋሻ ጃግሬዎች መሆናቸውን በውል ፍንትው ብለው እየተገለጹ ነው። ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ እንዳይደርስ ከፍጻሜ ቢደረስ እንኳን ሰው ሠራሽ ሐይቅ ብቻ ሆኖ እንዲቀር ግብፅ ያለ የሌለ ኃይሏን ተጠቅማ እየሠራች መሆኗን እየነገረችን ነው።  ‹‹ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው›› እንደሚባለው እያስፈራራችንም ነው። በግብፅ በኩል ስለ ናይል ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት አዎንታዊ አስተሳሰብ ቢኖር ኖሮ እስካሁን ድረስ በታሪክም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍተኛ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ትስስር ሊያስገኝ እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። ይህ ትስስር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ ሊዘልቅ የሚችል ትልቅ አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። ታዲያ ተከባብሮና በእኩል ተጠቃሚነት ሊገኝ የሚችለውን የታላቁን ወንዝ ፋይዳ ፈርኦናውያን በክብራቸው ብቻ ሊኖሩበት ምርጫቸው አድርገውታል። እኛም ኢትዮጵያውያን በታላቁ የህዳሴ ግድባችን ግንባታ ሦስት ሞትን አንሞትም። አንደኛው ሞት ኢትዮጵያውያኑ እየተራቡ ለግድቡ ግንባታ ያዋጡትን የደሃ ገንዘብ ግድቡ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ መዋል ሳይችል ሲቀር ነው። ሁለተኛው ሞት በሉዓላዊ ግዛታችን ያለንን ሀብት በምንፈልገው መንገድ መጠቀም አለመቻላችን ነው። ሦስተኛው ሞት ደግሞ ከድህነት ለመውጣት አትችሉም፡፡ አይገባችሁምም መባሉ ነው።

አንደኛው የኢትዮጵያውያን ሞታችን ታላቁ የህዳሴ ግድባችን ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ ቢውል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችሮታዎችን ያስገኝልናል። ከውኃ ያገኘነው ነዳጃችን ልንለውም እንችላለን፡፡ ያውም እንደ ነዳጅ አካባቢን የማይበክል። እነዚህን ተስፋዎች ሰንቆ ደሃው የኢትዮጵያ ሕዝብ መብላት እየፈለገ ከሚበላው ቀንሶ፣ መልበስ እየፈለገ ቡቱቱ ልብሱን አገልድሞ፣ መታከም ሲኖርበት ጥርሱን በመንከስ ሕመሙን ችሎ፣ ችጋር እያሳደደው በበረሃና በውቅያኖስ ሕይወቱን እያጣ ያለውን ልጁን ሸኝቶ ለህዳሴ ግድቡ የከፈለው ገንዘብ፣ ወዘተ. ብዙ መዘርዘር ይቻላል፣ እናም ይህ ሁሉ መስዋዕትነት ተከፍሎበት የህዳሴ ግድባችን አልቦ ሆኖ ቢቀር የሞት ሞታችን ይሆናል።

ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን ሞታችን አገራችን ከሕዝቧም አልፎ ለሌሎች ሊተርፍ የሚችል የተፈጥሮም ይሁን የሰው ሠራሽ ሀብት አላት። ከተፈጥሮ ሀብታችን ማዕድናት፣ ለም አፈርና ውኃን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል። ከማዕድናት የከበሩ ድንጋዮችን ትተን በፈሳሽና በጋዝ ዕምቅ ሀብት እንዳለን ከተረጋገጠ ግማሽ ከፍለ ዘመን አልፏል። ነገር ግን ጠብታም ማየት አልቻልንም። በመስኖ ሊለማ የሚችል ለም አፈር እስከ 15 ሚሊዮን ሔክታር ማሳ አለ ይባል እንጂ ለምቷል ተብሎ የሚነገረው ቢበዛ ከአምስት በመቶ የሚዘል አይሆንም። 22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ዕምቅ የገፀ ምድር ውኃ አለን ቢባልም ከፍተኛውን መጠን ሳንጠቀምበት የምንሸኘው ነው። ያውም ለም አፈራችንንም ጨምረን ነው የምናሰናብተው። ይህን የውኃ ሀብታችንን በወጉ ተጠቅመንበት ቢሆን ኖሮ ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን ያክል ማሳ በመስኖ ባለማን ነበር፡፡ ሰማንያ በመቶ የሚሆነውን የሰው ኃይላችንን በዚህ ዘርፍ ማሰማራት በቻልን ነበር፡፡ 45 ሺሕ ሜጋ ዋት ኃይል ዕምቅ ሀብታችንን ብንጠቀም ኖር አሁን ላይ ከሦስት ፐርሰንት በላይ ያልዘለለውን የኃይል አቅርቦታችንን በመጨመር መብራት የማያገኘው 55 በመቶ ወገናችንን ከጨለማ ኑሮና ከእንስሳት እዳሪ እንዲሁም ደን በመጨፍጨፍ የሚያገኘውን ኃይል በመተካት በታደግነው ነበር፡፡ ኢንዱስትሪዎችን በብዛት ባስፋፋን ነበር። ዳሩ ግን 22 በመቶ ሕዝባችን ከድህነት ወለል በታች እየኖረ ድህነት ያጎሳቁለዋል። ረሃብ፣ ወረርሽኝ፣ ስደት፣ ኋላቀር አኗኗርና ከሦስት ሺሕ ዘመን በላይ የኖረውን የእርሻ ዘዴ የሙጥኝ ብለን ነው ያለነው። ታዲያ ያለንን ሀብት አልምተን የተሰጠንን የድህነት ታርጋ መቀልበስ አለመቻላችን፣ እንዳንቀለብሰውም በሚወረወርብን ማስፈራሪያ እጅ የምንሰጥ ከሆነ ይኸም ሌላው የሞት ሞታችን ነው።

ሦስተኛው የኢትዮጵያውያን ሞታችን እኛ ኢትዮጵያውያን ተፈጥሮ የቸረችንን የምድራት ፍሬ ሁሉ እያለን ዳሩ ግን የዓለም የድሆች ጭራ ተብለን የድህነት ታርጋ የተሰጠን ምክንያቱ ምን ይሆን? እያለን ልንራብ፣ መስጠት ስንችል ቧጋች መሆናችን፣ ሠርተን መለወጥ ስላልቻልን ነው? ወይስ እንድንሠራ ስላልተፈለገ? መሥራት አለመቻላችን እንዳይባል ስንቱ ኢትዮጵያዊ ነው አገልጋይ ሆኖ ሠርቶ ለመኖር ሲል እየተሰደደ በጉዞው ላይ በበረሃ ያሞራ ቀለብ እንዲያም ሲል በውቅያኖስ ላይ የዓሳ ነባሪ ምግብ የሆነው? ታዲያ ለራሱ ሠርቶ ሕይወቱን ታድጎ ክብሩንና ኩራቱን ይዞ መለወጥ ተስኖት ነው? አዎን የሚል ካለ ማንም ወዶና መርጦ አገልጋይነትን ምርጫው የሚያደርግ የለም፡፡ አገልጋይ መሆን ዕጣ ፈንታችሁ ስለሆነ ነው የሚሉን አሠሪዎች ካሉ በአገራችን ሠርተን ራሳችንንም ሆነ አገራችንን እንዳንለውጥ የሚጎነጎንብን ሴራ ነው ማለት አይቻልም? ለሌላው ሠርቶ ባለሀብት የሚያደርግ ኢትዮጵያዊ ለራሱ ሠርቶ ባለሀብት መሆን እንዴት አይችልም? ብቻ የድህነት ታርጋ ተሰጥቶን አንገታችንን ደፍተን ዝንተ ዓለም መኖርን የምንመርጥ ከሆነና ድህነትን በፈቃዳችን በራሳችን ላይ የምናነግሥ ከሆነ ከዚህ የበለጠ የሞት ሞት የለም፡፡

ወገን ልብ ሊለው የሚገባው እነዚህን ሦስት ሞቶች ከምንሞት ድህነትን አሽቀንጥሮ በአንድ ሞት መሞት ትልቅ ክብር አለው። አባቶቻችን አንድ ሞትን ሞተው ነው በጠላት ተደፍራ የማታውቅ ሉዓላዊት አገር ያስረከቡን፡፡ አደራ የምንበላ በመሆን አንገታችንን ደፍተን ሦስት ሞትን የምንሞት ከሆነ የዘመናችንም ሆነ የትውልድ ተወቃሽ ሆነን እናልፋለን። ግብፅ በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬቷን መቶ በመቶ አልምታለች። 98 በመቶ የሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ነው። ለዚህ ሁሉ ጠቀሜታ ከ85 በመቶ በላይ ድርሻ ያለው የናይል ወንዝ ከኢትዮጵያ መሆኑ የታወቀ ነው። በአንፃሩ ይኸው ወንዝ ለግብፅ ከርሰ ምድር ውኃ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ግልጽ ነው። ግብፅ ሌላ ወንዝም ይሁን በቂ የሚባል ዝናብ ስለሌላት ከጨዋማነት የፀዳውና ንፁህ የከርሰ ምድር ውኃ ከናይል የተገኘ ስለመሆኑ አያጠያይቅም። እኛ ኢትዮጵያውያን የግብፅ ከርሰ ምድር ውኃ 85 በመቶው  ድርሻ አለን እንበል? ኢትዮጵያ በግብፅ ምድር ስላለው ዕምቅ የከርሰ ምድር ውኃ ግብፅን ወየሁልሽ ትነኪና አትልም። ይህንን የውኃ ሀብቷን ግብፅ ብትጠቀም ኢትዮጵያ እንዳትጠቀሚ ከተጠቀምሽ ጦር እንማዘዛለን ብትል ምን ይባላል? ኢትዮጵያ ላይ የዘነበው ዝናብም ይሁን የተፈጠረው ጎርፍ ግብፅ የእኔ ተፈጥሯዊ ሥጦታ  ስለሆነ ኢትዮጵያ ንክች እንዳታደርግ  ስትል እውነትሽ ነው ኢትዮጵያ የምትጠቀምበት ከሆነ ጦር አውጂ እኛም አለንሽ የሚሉ እያየን ነው። ግብፆች በኢትዮጵያ የሚዘንበውን ዝናብ ወይም ጎርፍ ፈጠሩት? ወይስ ሰውን ሳይሆን ምድሪቷን ለራሳቸው ፈጠሯት? ዋናው ጉዳይ እውነት ሳይሆን ሐሰትም ቢሆን ከየት ተነገረ? ማን ተናገረ? የሚለው ነው የሚታየው ማለት ነው።

እኛ ኢትዮጵያውያን ከ97 በመቶ በላይ በአንድ ፈጣሪ የምናመልክ ነን። የሌሎችን እምነቶች ወክዬ ባይሆንም እነሱ በራሳቸው መንገድ መጥቀስ ከሚፈልጉበት ይጥቀሱ፡፡ እኔ ግን ከክርስትና እምነት ተከታዮች አንዱ በመሆኔ ከመጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ሕዝቅኤል ምዕራፍ 29 ከቁጥር 3 እስከ 4 እንዲህ የሚለውን ላቅርብላችሁ፦ ‹‹በወንዞች መካከል የምትተኛ እና ወንዙ የኔ ነው፤ ለራሴም ሠርቸዋለሁ የምትል ታላቅ አዞ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ሆይ እነሆ በአንተ ላይ ነኝ›› ይላል። እናም ፈርኦናውያን ይህ የፈጣሪ ቃል ኪዳን ሳይመቻቸው ቀርቶ ልክ እስራኤላውያንን ለሙሴ አንለቅም እንዳሉት እንዳይሆንባቸው ልብ ሊሉ ይገባቸዋል። ፈጣሪ የፈጠረልንን ውኃ መጠቀም የምንችል መሆናችንንም እንዲሁ በመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 73 ከቁጥር 13 እስከ 14 እንዲህ ይላል፦  ‹‹የእባቦችን ራሰ በውኃ ውስጥ ሰበርህ፤ አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጥቅጠህ ለኢትዮጵያ ሰዎች ምግባቸውን ሰጠሃቸው” ይላል። ውኃችን የፈጣሪ ስጦታችን መሆኑን ፈጣሪያችንም ማረጋገጫ ሰጥቶልናልበመሆኑም የውኃ ሀብታችንን በማልማት ድህነትን የምናራግፍ መሆኑን የሚያመላክት ነውነገር ግን ይህንን ጥረታችንን የሚያደናቅፍ ካለ እሱ ከዘንዶው ወገን ወይም ከእባቡ በመሆኑ ድል የሚደረግ መሆኑን ሊያውቀው ይገባል

በሌላ በኩል የውኃ ሀብታችንን ለማልማት ደፋ ቀና ስንል ድህነታችንን የሚፈልጉ ወገኖች የአፍራሽነት ተልዕኮ የሚሰጧቸው የራሳችን ወገኖች የሉም ማለት አይደለምይህ አባባል በጥሬው የሚኮሰኩሳቸው ወገኖቻችን አሉ ለምን እንደማይመቻቸው ባይገባንምልቡ ንፁህ የሆነ ምንም ቢባል እሱን የማይመለከተው ከሆነ ምንም አይመስለውም።  ‹‹ቁስል ያለበት ዝላይ አይችልም›› ዓይነት ከሆነ ራሱንም ጭምር አያምንምእናም ገንዘብ ጭንቅላታቸውን የገዛው ወገኖቻችን እንደ ይሁዳ አሳልፈው የሚሰጡ ከሆነ፣ እንደ ቃኤል በቅናት ወንድሙን የሚገድል ከሆነ እሱ ማንነቱን የሸጠ ነውና ሊጠነቀቅ ይገባልካለም ይህ ድርጊት ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን አዲስ አይደለምበጣሊያንና ሶማሊያ ወረራ እነዚህ ሁሉ ታይተዋልከሃዲዎች ግን አልተሳካላቸውም። የዕለት ጥቅም አስበውና አሰላስለው እናት አገራቸውን አሳልፈው እንደ ይሁዳ የሚሰጡ ከሆነ እነሱም የተሰጣቸውን ገንዘብ ሳይበሉት እንደ ይሁዳ ሕይወታቸውን  በገዛ እጃቸው ያጠፋሉ። ኢትዮጵያ ግን እስከመጨረሻው ኢትዮጵያ ሆና ትኖራለች። ዘንበል ያለች መስሏቸው ሊጥሏት ቢያስቡ እነሱ ይወድቃሉ እንጂ ኢትዮጵያ አትወድቅም።

ግብፃውያን ጫፍና ጫፍ የረገጡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሏት። የአሁኑ የግብፅ ፕሬዚዳንት ጄነራል አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በመፈንቅለ መንግሥት ነው ወደ ሥልጣን መንበር የመጡት። ሕዝብ የመረጣቸውን መሐመድ ሙርሲን ገልብጠው ወደ እስር እንደሸኟቸው በእስር ላይ እንዳሉ ሕይወታቸው አልፏል። የመሐመድ ሙርሲ ደጋፊዎችና የፓርቲያቸው አባላት የአል ሲሲን መንግሥት አምርረው የሚቃወሙ በመሆናቸው በብዙ ሺሕዎች ወደ እስር ቤት የተጋዙና አለፍም ሲል የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው ብዙ ናቸው። ዳሩ ግን በሉዓላዊ አገራችን በራሳችን ምድር፣ በራሳችን ገንዘብ፣ በደሃ ጎናችን አዋጥተን እየሠራን ያለውን የታላቁን ህዳሴ ግድባችንን ተጠናቆ ወደ ልማት እንዳይገባ ለማድረግ በአንድ አፍ ተናጋሪ በአንድ ልብ መካሪ ሆነው ለጦርነት መዘጋጀታቸውን ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት እያሉልን ነው። ሁሉም ግብፃውያን ያለ ልዩነት ፕሬዚዳንት አል ሲሲ አለንልዎት ካዘዙን ለመሞትም ዝግጁ ነን እያሏቸው ነው። እኛስ ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነታችን ላይ ክፍተት ለመፍጠር ሰበብ አስባብ እያጣቀስን አይደለም? በራሳችን ሉዓላዊ አገር ላይ ግብፆች ሊወጉን የፖለቲካ ልዩነታቸውን በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጡ እኛ ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ የፖለቲካ አጄንዳ ቀዳሚ ሊሆን ይገባል? ለሕዝባችን የሚበጅ የተሻለ የፖለቲካ ፍልስፍና አለን የምንል ፖለቲከኞች ሕዝባችሁን ለበሽታና ሉዓላዊነታችንን በረከሰ የሥልጣን ጥመኝነት አሳልፈን የምንሰጥ ከሆነ የቱን ሕዝብ ነው ልንመራው የምንሻው? ብቻ ፖለቲከኛ ነን የሚሉ ቡድኖችም ይሁኑ ሉዓላዊነትን በገንዘብ ሊሸጡ የሚመኙ ኢትዮጵያውያን ካሉ ቆም ብለው ሊያስተውሉ ይገባል።

ውኃችን ሕይወታችን ነው። ህዳሴ ግድባችንም የእያንዳንዳንችን አሻራ ያረፈበት የሉዓላዊነታችን መገለጫ ከድህነት አረንቋ የምንወጣበት መሰላላችን ነው። ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይባርካቸው። ቸር ይግጠመን!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]  ማግኘት ይቻላል።

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles