Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የልማት ባንክ የተበላሸ ብድር 16 ቢሊዮን መድረሱ ይፋ ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ባልተገባ የብድር አሰጣጥ ሥርዓትና ክትትል ምክንያት፣ በጥቅሉ ካበደረው 44 ቢሊዮን ብር ውስጥ 16 ቢሊዮን ብር የተበላሸ ብድር መሆኑን በይፋ አስታወቀ።

የባንኩን የተበላሸ ብድር መጠን ይፋ ያደረጉት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ኃይለየሱስ በቀለ ናቸው፡፡ ይኼንንም የተናገሩት ባንኩ ከገጠመው ቀውስ ለመውጣት ያቀረበውን የ21 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ካፒታል ጥያቄ እንዲመረምር የተመራለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጉዳዩን በተመለከተበት ወቅት በሰጡት ማብራርያ ነው።

ቀደም ሲል ባንኩ ሲከተል በነበረው ያልተገባ የብድር አሰጣጥና ክትትል ሥርዓት ሳቢያ፣ በ16 ቢሊዮን ብር የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል። ባለፉት ጊዜያት የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የውጭ ባለሀብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እንዲሠሩ ለመደገፍ፣ እንዲሁም አምርተው ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ ድጋፍ እንዲደረግ በመንግሥት በወሰነው መሠረት ባንኩ ሲንቀሳቀስ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ አስታውሰዋል።

በዚህም መሠረት ልማት ባንክ ለእርሻ ኢንቨስትመንት በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች ተጀምረው ለነበሩ የሰፋፊ የእርሻ ልማት ፕሮጀክቶች፣ ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪና በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ብድር መስጠቱን ገልጸዋል።

ነገር ግን ባንኩ የተከተለው የብድር አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ተገቢ ያልሆነና የተሰጠውም ብድር በተወሰኑ ባለሀብቶች ቁጥጥር ሥር በመውደቁ የተነሳ፣ ባንኩ ለእነዚህ ዘርፎች ከሰጠው አጠቃላይ ብድር ውስጥ 16 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን ማስመለስ እንዳልቻለና በዚህም ምክንያት የተጠቀሰውን ያህል ብድር መበላሸቱን አስረድተዋል።

በባንኩ ሕግ መሠረት ለተበላሹ ብድሮች ማጣጫ የሚሆን ገንዘብ አበዳሪ ባንኮች እንዲይዙ የሚገደዱ በመሆኑና ባንኩም ይህንን የማድረግ ኃላፊነቱን በተሟላ መንገድ ባይሆንም በተወሰነ ያህል በመፈጸሙ፣ የነበረው የካፒታል መጠን ከ7.5 ቢሊዮን ብር ወደ 2.9 ቢሊዮን ብር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል።

ይህ የካፒታል መጠን ባንኩን ከዓለም አቀፍም ሆነ ከአገር አቀፍ የባንክ አሠራር መመዘኛዎች ውጪ እንዲሆን እንዳደረገው አስረድተዋል። በዚህም ምክንያት መንግሥት ተጨማሪ ካፒታል ለባንኩ ካልመደበ ለመንቀሳቀስና ኃላፊነቱን ለመወጣት እንደሚቸገር ጠቁመዋል።

ሪፖርተር ያገኘው ተጨማሪ የሰነድ ማስረጃ እንደሚገልጸው፣ ባንኩ ባለፉት ዓመታት በመስኖ ለሚለሙ ሰፋፊ እርሻዎች፣ የግብርና ውጤቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች፣ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪና በማዕድን ልማት መስኮች ለሚሰማሩ ፕሮጀክቶች የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ብድሮችን በመስጠት እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ድረስ 1,783 ለሚሆኑ ፕሮጀክቶች አበድሯል። በዚህም የተነሳ ጠቅላላ የብድር ክምችቱ 39.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን ሰነዱ ያመለክታል።

ከፕሮጀክት ፋይናንሲንግ በተጨማሪም ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሊዝ ፋይናንሲንግ (የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ) አገልግሎት ባንኩ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ድረስ 1,193 የሚሆኑ የሊዝ ፕሮጀክቶችን ይዟል። ከዚህ ጋር በተያያዘም ጠቅላላ የብድር ክምችቱ 1.68 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ባንኩ የተለያዩ የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞችን ለማስፈጸም ከአበዳሪና ከድጋፍ ሰጪ የውጭ ተቋማት የሚገኝ ሀብት (ፈንድ) ለታለመላቸው ዓላማዎች እንዲውሉ በማድረግና በማስተዳደር፣ የመንግሥትን የድህነት ቅነሳ ጥረት እያገዘ ይገኛል። ከነዚህም መካከል ለሴቶች የሥራ ፈጠራና ለታዳሽ ኃይል ማመንጫ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ድረስ በአጠቃላይ 3.53 ቢሊዮን ብር ብድር ለተጠቃሚዎች አቅርቧል። ከዚህም በተጨማሪ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማሰባሰብ ሲባል የተዘጋጀውን ቦንድ ኅትመት፣ ሥርጭትና ሽያጭ እያከናወነ በመሆኑ የቦንድ ሽያጭ ከጀመረበት እ.ኤ.አ. ከመጋቢት 2011 አንስቶ እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ 11.45 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ የቦንድ ሽያጭ ማከናወኑን ሰነዱ ያመለክታል፡፡

 የመክፈያ ጊዜያቸው ለደረሱ የቦንድ ኩፖኖችም ክፍያዎችን በመፈጸም ላይ እንደሚገኝም ሰነዱ ይገልጻል። ‹‹ባንኩ ከብድር አፈቃቀድና አስተዳደር አኳያ የሠራተኞችና የማኔጅመንት አካላት የአፈጻጸምና ሥራን በአግባቡ የመምራት ክፍተቶች፣ እንዲሁም በውጭ አካላት በነበረበት ተፅዕኖ ምክንያት የባንኩ የተበላሸ ብድር ክምችት መጠን እ.ኤ.አ. እስከ ሰኔ 30 ቀን 2018 ድረስ 39.43 በመቶ ደርሷል፤›› ሲልም ሰነዱ ያመለክታል።

የተበላሹ ብድሮች ክምችት መጨመር ለእነዚህ ብድሮች የሚያዘው መጠባበቂያ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ በማድረጉ፣ የባንኩ የተጣራ ካፒታል በዚያው ልክ እንዲቀንስ ማድረጉንም ያመለክታል፡፡ ከዚህም በላይ ሕጉ በሚያዘው መሠረት ባንኩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ሲስተምን (IFRS) ተግባራዊ ሲያደርግ በሀብትና በፋይናንስ ሰነዶች ግምት አወሳሰድ (Asset Valuation) አጠራጣሪ ለሆኑ ብድሮች የሚያዝያ መጠባበቂያ (Loan Loss Provision) አወሳሰን፣ በገቢና በወጪ አወሳሰንና በመሳሰሉት ዋና ዋና የፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ቀደም ሲል ከነበረው ዘዴ የተለየ በመሆኑ፣  ተጨማሪ ገንዘብ ለአጠራጣሪ ብድሮች መጠባበቂያነት ለመያዝ ተገዷል።

በዚህም ምክንያት የባንኩ ካፒታል በከፍተኛ ደረጃ ወርዷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ እ.ኤ.አ. ከሰኔ 30 ቀን 2018 ጀምሮ የሚተገበረው የፋይናንስ ሪፖርቲንግ ሲስተም ተጨማሪ የካፒታል መሸርሸር እንደሚያስከትል ታውቋል፡፡ በዚህም ምክንያት የባንኩ ካፒታል ቀደም ሲል በነበረው የሪፖርቲንግ ሲስተም ከነበረበት 8.04 ቢሊዮን ብር አሁን ወደ 2.99 ቢሊዮን ብር የወረደ ሲሆን፣ ሁለተኛው የሪፖርት ደረጃን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ደግሞ፣ የባንኩ ካፒታል ከዜሮ በታች 2.77 ቢሊዮን ብር እንደሚሆን ተሠግቷል።

የባንኩ ጤነኝነት በተለያዩ መመዘኛዎች ሲለካ አደጋ ላይ መሆኑን ሰነዱ ያመለክታል። የባንኮች ጤንነት መመዘኛ ከሆኑ መሣሪያዎች አንዱ የካፒታል በቂነት ምጣኔ (Capital Adequacy) ሲሆን፣ በዚህ መለኪያ መሠረት የአንድ ባንክ የካፒታል በቂነት ምጣኔ በትንሹ 15 በመቶ ሊሆን እንደሚገባ ብሔራዊ ባንክ በሕግ ያስገድዳል። የአፍሪካ ልማት ባንኮች ማኅበርም ይህንን ዝቅተኛ ምጣኔ ይቀበላል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል በቂነት ምጣኔ ግን እ.ኤ.አ. በሰኔ 2018 6.2 በመቶ እንደነበር መረጃው ያመለክታል። በመሆኑም የባንኩን ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ 21.02 ቢሊዮን ብር ካፒታል እንዲመደብለት ጠይቋል። ፓርላማው በዚህ የካፒታል ዕድገት ጥያቄ ላይ በቅርቡ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች