Thursday, February 29, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ለመጨረሻ ውይይት የተጋበዙት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ

በመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ለመጨረሻ ውይይት የተጋበዙት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ

ቀን:

በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ውይይት ተደርጎበታል ተብሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ከቀረበ በኋላ፣ ‹‹ተፎካካሪ ፓርቲዎች ይወያዩበት›› ተብሎ እንደተመለሰ በተነገረው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ ላይ የመጨረሻ ውይይት እንዲያደርጉ የተጋበዙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን አሰሙ፡፡

ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በረቂቁ ላይ እንዲወያዩና አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ከተጋበዙት ተፎካካሪ ፓርቲዎች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ዴሞክራሲ ፓርቲና ሌሎችም ፓርቲዎች ተገኝተዋል፡፡ በረቂቁ ላይ የመጨረሻ ተወያይ ተደርገው የተጋበዙት፣ እውነተኛ ግብዓት አስተያየትና ሐሳብ እንዲሰጡ ሳይሆን ለይስሙላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሠሩት ለሕዝብና ለአገር ከመሆኑ አንፃር፣ በእያንዳንዱ አገራዊ ጉዳይ ላይ ምክክር ሲደረግ ዘመን ተሻጋሪ ሰነድ ሲዘጋጅ ሊወያዩበትና ካላቸው የፖለቲካ ፕሮግራም አኳያ አስተያየታቸውንና ሐሳባቸውን መግለጽ ሲገባቸው፣ ‹‹እንዳይጨቀጭቁን›› እና ‹‹አወያይተናቸዋል›› ብሎ በመገናኛ ብዙኃን ለመናገር የተደረገ ከአንገት በላይ የሆነ ጥሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የቅሬታቸውም ዋና ምክንያት የፖሊሲ ረቂቁ ለምን ተዘጋጀ? ሳይሆን፣ እውነተኛ ውይይት ከተፈለገና የተፎካካሪ ፓርቲዎቹ አስተያየትና ሐሳብን ለማካተት ተፈልጎ ከሆነ፣ ረቂቁ ከሁለትና ከሦስት ቀናት በፊት አስቀድሞ ሊሰጣቸው ሲገባ ውይይት በማድረጊያ ቀን መሰጠቱ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ቅሬታቸውን የገለጹት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፣ ስለፖሊሲ ረቂቁ አጭር ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ነው፡፡ ጌታቸው (ዶ/ር) ስለፖሊሲው እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ የሚመራበት ራሱን የቻለ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ የለም፡፡ በመሆኑም ዘርፉን በስፋትና በጥራት በማስፋፋት፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ዜጎች በመረጃ ተደራሽ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በመሆኑም የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ማዘጋጀት አስፈላጊ በመሆኑ የዘርፉን ችግሮችና መሥራት የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ ጉዳዮች ለይቶ ለማወቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ጥናት ተደርጎ፣ ምቹ የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ፣ የመረጃ ዕጦት መኖሩ፣ በሥራ ላይ ያሉት ሕጎች የጋዜጠኞችን የሥራ ነፃነት የሚገፋ መሆናቸውንና ሌሎችም ችግሮችን መለየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ተግዳሮቶቹን ለመፍታት የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የሚመራበትና የሚደገፍበት ‹‹የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ›› ማዘጋጀት ስለታመነበት ‹‹የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ተቀርጿል፤›› ብለዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፖሊሲ ሰነዱ በሕገ መንግሥቱና በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠውን ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትና የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ከማኅበራዊ፣ ከኢኮኖሚያዊ፣ ከፖለቲካዊና ከቴክኖሎጂ ዕድገት ጋር የሚጣጣምና ዘርፉ የሚመራበትን አገራዊ ፖሊሲ ተግባራዊ ከማድረግም አኳያም ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃንን ለማስፋፋትና አቅማቸውን ለመገንባት የሚያስችሉ የድጋፍና የማበረታቻ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ለማድረግና ምቹ የሕግ ማዕቀፍ በመዘርጋት ዘርፉን በቀጣይነት ለማሳደግ ፖሊሲው ወሳኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ፖሊሲው በአራት ክፍሎች መዋቀሩንም አክለዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ባለቤትነት በሕዝብ፣ በንግድና በልዩ ልዩ ማኅበረሰቦች መያዙን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የተለያዩ ስብጥርና ብዝኃነት ያለው የሚዲያ ምኅዳር እንዲፈጠር ለማድረግ ግለሰብን ጨምሮ የንግድ ተቋማትም የንግድ የኅትመት መገናኛ ብዙኃን ባለቤት እንዲሆኑ በፖሊሲው መካተቱን ተናግረዋል፡፡

የብሮድካስት ፈቃድን በሚመለከት እንዳስረዱት፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚያበረክቱት የካፒታልና የሙያ ሽግግር ለዘርፉ ዕድገት የራሱ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው፣ ውስን ድርሻ በመያዝ በመገናኛ ብዙኃን ዘርፍ እንዲሳተፉ በፖሊሲው መካተቱን አስረድተዋል፡፡ የውጭ አገር ዜጋም ሆነ፣ በውጭ አገር ዜጋ የተቋቋመ ድርጅት መከልከሉን አክለዋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት አስተምህሮቶቻቸውን በሚመለከት ለሕዝቡ ለማስተላለፍ ከፈለጉ እሱን ብቻ ለማስተላለፍ እንደሚፈቀድላቸው በፖሊሲው የተካተተ መሆኑን ጠቁመው፣ የብሮድካስት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 533/99 የፖለቲካ ድርጅቶች ጭምር የብሮድካስት ፈቃድ እንደተከለከሉ አስታውቀዋል፡፡ በመሆኑም የፖለቲካ ድርጅቶች ከሬዲዮና ቴሌቪዥን በስተቀር በሌሎቹ የኅትመትና የማኅበራዊ ድረ ገጾች መጠቀም እንደሚችሉም አስረድተዋል፡፡  

በፖሊሲ ረቂቁ ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ውስጥ የጋዜጠኞች ‹‹ብሔርና›› የፆታ ስብጥር መረጋገጥ እንዳለበት የተካተተው ሐሳብ፣ ‹‹ብሔር›› የሚለው ቃል ተገቢ እንዳልሆነና አገር አቀፍ ይዘት ያለው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ እንዲሆን ተደርጎ እንዲስተካከል ጥያቄ ቀርቧል፡፡  

ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችም ሆኑ ሌሎች ባለድርሻ አካላት አንድ በሚመለከተው አስፈጻሚው አካል የተዘጋጀ ረቂቅ ፖሊሲ፣ አዋጅ ወይም ሌላ አገራዊ ሰነድ ላይ ለ‹ውይይት›› ተብለው የሚጋበዙት ሰነዱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ጫፍ ከደረሰ በኋላ፣ ለይስሙላ መሆኑን የኅብረት ኢትዮጵያ ፓርቲ ተወካይ ተናግረዋል፡፡ አገራዊ ይዘት ባለው ሰነድ ላይ ከልብ ለመወያየትና ግብዓት ለመውሰድ ከሆነ ግን የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ ቀደም ብሎ ተልኮና ባለድርሻ አካላቱ ዓይተውት፣ ተወያይተውና መክረውበት ሊሆን ሲገባ፣ ‹‹እንዳያማህ ጥራው. . .›› ዓይነት ነገር መሆን እንደሌለበትም አክሏል፡፡

እዚህ አገር ሕግ የማውጣት ችግር እንደሌለና እጅግ በጣም ጥሩ ጥሩ ሕጎች መውጣታቸውን የጠቆሙት የኅብር ኢትዮጵያ ተወካይ፣ ትልቁ ችግር የአፈጻጸም በመሆኑ ሕጎቹ በብቃት ቢዘጋጁም እንዴት መፈጸም እንዳለባቸው ውይይት ማድረግና ግብዓቱንም ማካተት ተገቢ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ሕዝብ ታክስ የሚከፍልባቸው መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ተቀጥላ ሆነው የሚቆዩበትን ረቂቅ ፖሊሲ አጨብጭበው ለማሳለፍ ስላልመጡ ውይይቱ ከልብ ከሆነ ጊዜ ተሰጥቶትና የቀረበውን የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ በየፓርቲያቸው ውይይት ካደረጉበት በኋላ፣ በድጋሚ ተገናኝተው ሐሳባቸውን እንዲሰጡበት እንዲደረግ ጠይቀዋል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ ትልቅና አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ ሁሉንም በአግባቡና ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ተደራሽ የሚሆንበት ሥርዓት ተቀርፆ ለትውልድ የሚተላለፍ ሰነድ እንዲሆን፣ የግድ ተጨማሪ ውይይት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሁሉም አስፈጻሚዎች ስብሰባ የሚጠሩት (ተፎካካሪ ፓርቲዎችን) ሁሉንም ነገር ከጨረሱ በኋላ አጨብጭበው እንዲሄዱ መሆኑን የጠቆሙት ደግሞ፣ የአገው ብሔራዊ ሸንጎ ተወካይ ናቸው፡፡ ፓርቲዎች እንደ አገር መነጋገር ባሉብን ጉዳዮች ማለትም አገር አቀፍ በሆኑ ጉዳዮች ወይም ሰነዶች ላይ በመነጋገርና በመወያየት፣ ‹‹ይህ ጥሩ ነው፣ ይህ መሆን የለበትም›› በማለት መወሰን ወይም ግብዓት መስጠት አለባቸው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ትውልድ ተሻጋሪና ሕዝብ የሚጠቅሙ መሆን ስላለባቸው ሲሉ አክለዋል፡፡ ‹‹ፓርቲያችን ሥልጣን ቢይዝ የሚዲያው ፖሊሲ በዚህ መልክ እንዲሠራ አደርጋለሁ የሚል በፕሮግራማችን ላይ አሥፍሯል፡፡ ስለዚህ ገዥው ፓርቲ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ አዘጋጅቶና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ማወያየት ካለበት ጠርቶ ሰፊ ውይይት ቢደረግ ምንም ችግር የለውም፤›› ብለዋል፡፡ አዘጋጅቶ ለማፅደቅ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠን ሰነድ አምጥቶ ‹‹ለነበር›› ያህል ተወያዩ ማለት ተገቢም እንዳልሆነና ጥቅም እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

አይደለም አገራዊ ጉዳይ ቀርቶ አቅም መገንቢያ ሥልጠና እንኳን ሲዘጋጅ፣ ተጋባዥ ተዘጋጅቶና ትኩረቱን በሥልጠና ርዕሰ ጉዳይ ላይ አድርጎ እንዲሄድ ርዕሰ ገዳዩ በምን በምን ላይ እንደሚያተኩር ቀደም ተብሎ ዝርዝር ሒደቱ እንደሚላክ ጠቁመው፣ ይህንን የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ሰነድ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ትልቅ ተቋም ከመሆኑ አንፃር ይህ ይጠፋዋል የሚል ግምት ባይኖራቸውም፣ የተለመደና ባለበት የማስቀጠል የማይሻሻል ቋሚ ባህሪ መሆኑን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አስፈጻሚ አካላት ትልቁ ችግራቸው የወጡ ሕጎችን ማስፈጸም አለመቻልና የብቃት ችግር መሆኑን የጠቆሙት የውይይቱ ተካፋዮች፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከፖለቲካ ወገንተኝነት ራሱ ነፃ አድርጎ የማስፈጸም ቁርጠኝነት አለው ወይ? የሚል ጥያቄም ሰንዝረዋል፡፡ በኢትዮጵያ እስካሁን ገዥ ፓርቲዎች የራሳቸው ሚዲያ ያላቸው መሆናቸውን ጠቁመው፣ በአክሲዮን ማኅበር የተደራጁ የንግድ ሚዲያ መሆናቸውን እየገለጹ ቢሆንም፣ የመንግሥት አመራር በተለወጠ ቁጥር ራሳቸውን እንደ መሪው ሁኔታ እየቀያየሩ ለገዥ ፓርቲ ብቻ እየሠሩ የሚቀጥሉት እስከ መቼ ድረስ እንደሆነም እንዲገለጽላቸው ጥያቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ በግልጽ ለፓርቲ የቆሙ መገናኛ ብዙኃን መኖራቸው እየታወቀ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ማቋቋም እንደማይችሉ በመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ላይ መቀመጡ ተገቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የፓርቲ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆኑ የብሔር ሚዲያዎችም እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡ ባለሥልጣኑ ቁርጠኛ ሆኖ ዋጋ የሚያስከፍል ሥራ ካልሠራ በስተቀር፣ መገናኛ ብዙኃንን የሚመለከት ፖሊሲና ሕግ ማውጣቱ ብቻ መፍትሔ እንደሌለው አክለዋል፡፡ መገናኛ ብዙኃን በደል ቢፈጽሙ ተጎጂ አካል የት መሄድ እንዳለበትና በምን ያህል ጊዜ ውስጥ መፍትሔ እንደሚሰጠው በአግባቡ መቀመጥ እንዳለበትና ባለሥልጣኑ ይህንን ኃላፊነት እንደሚወስድ የሚያስገድድ ሰነድ መሆን እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

ፖሊሲው የብሔርና የፆታ ስብጥር የሚል ነገር እንዳለው ባለቻቸው አጭር ደቂቃ ውስጥ ከረቂቁ ላይ ማንበባቸውን የጠቆሙበት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ፣ መገናኛ ብዙኃኑ ኢትዮጵያን መምሰል ሲገባቸው በብሔርና በፆታ ተዋጽኦ መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች ሒደት ወቅታዊ ውይይት ለተወሰኑ ዓመታት የሚቆዩ ሲሆኑ፣ ሚዲያው ግን ዘላቂ በመሆኑ የፆታ ጉዳይ ተገቢ ቢመስልም ‹‹ብሔር›› የሚለው መግባቱ ተገቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት መገናኛ ብዙኃንን በተለይ በምርጫ ወቅቱ እንደፈለገ የሚጠቁምበትን ያልተገባ አሠራር መቆጣጠር የሚቻልበትን ሁኔታ ፖሊሲው ማካተት እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተወካይ አቶ በቀለ ገርባም እንደ ሌሎቹ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ፣ ‹‹ሰነዱ ከሁለትና ከሦስት ቀናት በፊት ሊደርሱን ይገባ ነበር፤›› ብለው፣ ‹‹ይመለከታቸዋል የተባሉ ባለድርሻ አካላት ከተወያዩበት በኋላ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተውበታል? ተብሎ ሲጠየቅ አልተወያዩበትም በመባሉ፣ እነሱንም አነጋግሯቸው፣ በኋላ አልተወያየንበትም ብለው ይጮሁብናል በመባሉ ነው እዚህ እንድንገኝ የተደረግነው፡፡ ከምር የእኛ ግብዓት ተፈልጎ ሳይሆን፣ ተወያይተውበታል ለማለትና ለሚዲያ ፍጆታ የቀረበ ይመስለኛል፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የተለመደ ነገር በመሆኑ ይስተካከል ማለት እንደማይፈልጉም አቶ በቀለ አክለዋል፡፡

ይህ ሰነድ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ በመሆኑ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ በፓርቲ ደረጃ በደንብ ውይይት የሚፈልግ ስለሆነ ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመው፣ ነገር ግን አሁን ባለበት ደረጃ ‹‹ተወያይተንበታል›› ተብለው ባለበት ሁኔታ የሚያልፍ ከሆነ፣ ኦፌኮ እንዳልተሳተፈበትና እንዳልተወያየበት እንዲቆጠርላቸው ተናግረዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ሰነድም ስለሌለና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚዲያዎች ሚና ቀላል ባለመሆኑ፣ ውይይት መደረግ እንዳለበት ደጋግመው ጠይቀዋል፡፡

አስፈጻሚው የብሮድካስት ባለሥልጣን እንዴት ነፃ ገለልተኛና ከአድልኦ የፀዳ ሆኖ እንደሚመሠረት ትኩረት ሰጥተው ሊወያዩበት እንደሚገባም አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡ ባለሥልጣኑ አሁን ባለበት ሁኔታ ገለልተኛና ነፃ ነው ብለው እንደማያምኑና ብዙ ማስረጃዎችም እንዳሏቸው ጠቁመው፣ በፖሊሲ ሰነዱ ላይ ውይይት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ አሁን ባለው የሚዲያ አሠራር ሊቀረፉ የሚችሉበት መንገድ በፖሊሲው ላይ እንዲኖር እንደሚፈልጉም አክለዋል፡፡ ከባለሥልጣን ተፅዕኖ ነፃ የሆነ አስፈጻሚ ተቋም እንዲመሠረት ስለሚፈልጉ፣ በድጋሚ ውይይት አስፈላጊ መሆኑንና ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፓርቲያቸው እንዳልተሳተፈ እንዲታወቅላቸው አቶ በቀለ ተናግረዋል፡፡

በፖሊሲ ረቂቅ ላይ ጊዜ ተሰጥቶና ረቂቁ ቀድሞ ተልኮላቸው ከተወያዩበት በኋላ፣ አንድ ላይ በዝርዝር ውይይት እንዲደረግበትና አስፈላጊው ግብዓት ተካቶበት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንጂ፣ የአራትና የስድስት ሰዓታት ውይይት ጊዜ ተሰጥቶ የፖሊሲ ማሻሻያ ተደርጓል ለማለት እንደማይቻል የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተወካይ ተናግረዋል፡፡ ሚዲያው ከጥንት ጀምሮ በአድልኦ ላይ የተመሠረተ፣ በገዥው ፓርቲ የሚመራና የገዥውን መንግሥት ሒደት ብቻ በመዘገብ ላይ የተመሠረተ መሆኑንም አክለዋል፡፡ እያንዳንዱ ተፎካካሪ ፓርቲ የሚታገለው፣ የሚደራጀውና የሚሠራው ለሕዝብ ስለሆነ ያለውን መሠረታዊ ውስንነት የሚያስተካክል ፖሊሲ ሊቀረፅ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ፓርቲዎች የየራሳቸው ሐሳብ ቢኖራቸውም በሚዲያ ሲስተናገዱ የሚታዩት በምርጫ ወቅት በምትመደብ ውስን  ጊዜ ብቻ ከመሆኑ አንፃር መታፈናቸውን የሚያስተካከል ፖሊሲ እንዲሆን፣ በቂ ጊዜ ተሰጥቶ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ሕዝቦች ፓርቲ (ቤጉሕፓ) የሶሻል ዴሞክራሲ ሕዝቦች ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ተወካዮችም ተመሳሳይ ሐሳብ አንስተው በቀረበው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ጊዜ ተሰጥቷቸው መወያየት እንዳለባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ለመወያየት የተጋበዙት የተፎካካሪ ፓርቲዎች (የተገኙት) ሰነዱ ቀድሞ ስላልተሰጣቸው ዓይተውትና ተወያይተውበት ባለመቅረባቸው አስተያየታቸውን መስጠት ስላልቻሉ፣ ጊዜ ተሰጥቷቸው ተጨማሪ ውይይት እንዲያደርጉ የብሮድካስቲንግ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው (ዶ/ር) ተስማምተዋል፡፡ የፓርቲዎቹ ተወካዮች ያነሷቸው ጥያቄዎችም ተገቢና የተቀበሏቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሕጎቹን ዓይተውና ተወያይተው ግብዓት ለመስጠት ከፈለጉም ጊዜው ሳይንዛዛና ወቅቱን ታሳቢ ያደረገ ሐሳባቸውን ለመቀበል ባለሥልጣኑ ፈቃደኛ መሆኑንም አክለዋል፡፡ የቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ጋር የሚቃረን ነገር እንደሌለው ጠቁመው፣ የተለየ ሐሳብ አለ ከተባለ ግን እንደ ግብዓት የማይወስድበት ምክንያት እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡

ረቂቁን ለውይይት ያቀረቡት ተጨማሪ ሐሳብ ለማካተት እንጂ፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎቹ እንደተነገረው ለይስሙላ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የተጠሩት ተመርጠው ሳይሆን ሁሉም መሆናቸውን የገለጹት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ወቅቱ የኮሮና ወረርሽኝ ከመሆኑ አንፃር ተጨንቀው የነበረ ቢሆንም፣ ሁሉም ፓርቲዎች ባይገኙም የተገኙት በቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የፓርቲዎቹ ተወካዮች ባነሱት ጥያቄ ፓርቲዎች የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች እንዲኖራቸው እንደማይፈቀድ በፖሊሲው ቢገለጽም፣ በሌሎች ሚዲያዎች ግን ሁሉም መጠቀም እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡ የፖሊሲው ሐሳብ አስፈጻሚው አካል ነፃና ገለልተኛ ሆኖ እንዲሠራ መሆኑን ጠቁመው፣ ብሮድካስት ባለሥልጣን ከምንም ተፅዕኖ ነፃ፣ ገለልተኛና ቁርጠኝነት ያለው ተቋም ስለመሆኑ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በወረርሽኝ ወቅት በድጋሚ አንድ ቦታ ተሰባስቦ ለመወያየት አስቸጋሪ በመሆኑ፣ ረቂቁን በደንብ ዓይተውና ተወያይተውበት ያላቸውን አስተያየትና ግብዓት በጽሑፍና በድረ ገጽ እንዲያቀርቡ ተስማምተው ለግማሽ ቀን በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ሆቴል የተደረገው ውይይት አብቅቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...