Tuesday, January 31, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያ ተፈጥራዊ መብት ለድርድር አይቀርብም!

የዓባይ ውኃ ጉዳይ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ጣልቃ ገብነትን እየጋበዘ ነው፡፡ የዓባይ ተፋሰስ የራስጌ አገሮችን ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብትን የሚጋፉ ድርጊቶች እየበዙ ነው፡፡ የኢትዮጵያን የፍትሐዊነትና የምክንያታዊነት መርህ በመጣስ፣ በገዛ ሀብቷ የበይ ተመልካች ለማድረግ የሚደረጉ ጥረቶች ትዕግሥትን የሚፈታተኑ ሆነዋል፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲዋን በግብፅ አማካይነት የምታስፈጽመው አሜሪካ፣ የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ለማስቆም ታጥቃ ተነስታለች፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የመዳፈር አጉል ዕርምጃ ነው፡፡ ለዓባይ ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላትን ግብፅ በመደገፍ፣ ለውኃው 86 በመቶ የምታበረክተውን ኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ የተቃጣ ጥቃት ነው፡፡ አሜሪካ ኢፍትሐዊ ድርጊቷን ማቆም አለባት፡፡ ከ260 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን የሚኖሩባቸውን የተፋሰሱ አገሮችን መብት እስከ ወዲያኛው ለመገደብ አሜሪካ ጣልቃ ስትገባ፣ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም እንዲህ ዓይነቱን ዓይን አውጣ ድርጊት ማጋለጥና ማስቆም አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያን ግድቧን ከመሙላት ለማስቆም የሚደረገውን አጉል ሙከራ ማምከን ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ውኃውን በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት እንጠቀምበት በማለት ለዘመናት ያሳዩት ደግነት ተዘንግቶ፣ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድብ ሲገነቡ ግብፅ ያሳየችው ክፋት መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን አሜሪካ የገዛ ጥቅሟን ብቻ በማስላት በግድቡ ላይ የጀመረችው ዘመቻም እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይህንን እኩይ ድርጊት ተባብረው ማስቆም አለባቸው፡፡ የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብት ለድርድር አይቀርብም፡፡

ኢትዮጵያዊያን በድህነት እንዲኖሩ የተፈረደባቸው ይመስል በገዛ ሀብታቸው እንዲገለሉ በቅኝ አገዛዝ ዘመን ስምምነቶች መሠረት የተቃኘ ውል ሲቀርብላቸው፣ እንኳንስ ሊቀበሉት ቀርቶ መታሰቡ ጭምር ያስቆጣቸዋል፡፡ የዓባይን ውኃ አፍሪካውያንን ወንድማማችና እህትማማች ሕዝቦች የትብብርና የጋራ ዕድገት ማድረግ እንዳለባቸው እየተነገረ፣ ግብፅ ግን ይህንን መልካም ነገር ወደ ጎን እየገፋች ለጥፋት እያዋለችው ነው፡፡ አሜሪካ ደግሞ እንደለመደችው የጥፋት ፖሊሲዋን ይዛ ቀርባለች፡፡ አሜሪካ በእንዲህ ያለ ከፍተኛ ጥንቃቄ በሚያሻው ጉዳይ የለመደችውን ማስፈራራትና ማተራመስ ይዛ ስትቀርብ፣ ውሳኔዋ ሊያስከትል የሚችለውን አደገኛ ውጤት በግልጽ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ላይ በተሳሳቱ ውሳኔዎቿ ምክንያት ያደረሰቻቸውን ጉዳቶች ጭምር ማስታወስ የግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አቀንቃኝ ነኝ የምትለው አሜሪካ ጓዳዋ ውስጥ የሚፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች የዓለም መነጋገሪያ በሆኑበትና ገመናዋ ተገላልጦ በኃፍረት አንገቷን በደፋችበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ ተቋማቷ አማካይነት የተከፈቱ ዘመቻዎች ኢፍትሐዊ መሆናቸውን በግልጽ መንገር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በቅኝ ያልተገዛችና ግብፅን ጨምሮ በርካታ ወራሪዎችን በተደጋጋሚ አሳፍራ የመለሰች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር ስለሆነች፣ አሜሪካ የጀመረችውን ኢፍትሐዊና ሉዓላዊነትን የሚፃረር ድርጊቷን በፍጥነት ማቆም ይኖርባታል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም በዓባይ ውኃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀም መርህ የምታምን ስለሆነች፣ ሕገወጥ ድርጊቶችን እንደማትታገስ ሊታወቅ ይገባል፡፡

አሜሪካ ገለልተኛና ፍትሐዊ ሳትሆን ጥቅሟን ብቻ በማስላት የገባችበት አደገኛ ጎዳና፣ አካባቢውን ከማተራመስ የዘለለ ምንም ዓይነት አዎንታዊ ሚና የለውም፡፡ የአሜሪካ የተሳሳተ ፖሊሲ በመካከለኛው ምሥራቅና በተለያዩ ሥፍራዎች ከቀውስ ውጪ የፈየደው ስለሌለ፣ የአሜሪካ ፖሊሲ አውጭዎች አሁንም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመከራሉ፡፡ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ የመጠቀም መብት በመደፍጠጥ ኢፍትሐዊ የሆነ ስምምነት ለማስፈረም የሚደረገው ሩጫ በፍጥነት መገታት አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ግድቧን ውኃ ከመሙላቷ በፊት ስምምነቱ ይፈረም ከተባለም ግብፅም ግድቦቿን ባዶ አድርጋ ትቅረብ፡፡ ይህ የማይሆን ነው ከተባለም በሥርዓቱ ተቀምጦ ለፍትሐዊነት መነጋገር ይገባል፡፡ ለዓለም ስለእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሐዊነት የምትሰብከው አሜሪካ የምትናገረውን በተግባር ታሳይ፡፡ ቃልና ተግባር የማይገጣጠሙበትን ጥቅም አባራሪነት ይዛ፣ ግብፅን ለመደገፍ የሄደችበት ርቀት ተቀባይነት የለውም፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት 60 በመቶ ኢትዮጵያዊያን የኤሌክትሪክ ኃይል ስለማያገኙ በጨለማ ተውጠው፣ የግብፅ 30 ሺሕ ከተሞችና መንደሮች በዓባይ ውኃ በኤሌክትሪክ ደምቀው ያድራሉ፡፡ በርካታ ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ፣ ለዓባይ ውኃ ምንም ዓይነት አስተዋፅኦ የሌላት ግብፅ ዜጎች ዓሳ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ያገኛሉ፡፡ አስዋን ግድብ ላይ በዓመት በትነት ከሚባክነው አሥር ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በተጨማሪ፣ ወደ ሜዲትራኒያን ባህር የሚፈሰው ትርፍ ውኃ ግብፅን አንቀባሮ እንደሚያኖር ይታወቃል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ኢፍትሐዊነት የምትደግፈው አሜሪካ ጥቂት ጥናት ብታደርግ እውነቱን ለማወቅ አይቸግራትም፡፡ ነገር ግን የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ አስፈጻሚ ቃፊሯን ለመደገፍ ስትል፣ ኢትዮጵያን የሚበድል ነውረኛ ተግባር ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ይህም በሚገባ መታወቅ አለበት፡፡

  ኢትዮጵያዊያን ስለፍትሐዊነትና ስለምክንያታዊነት ሲጨነቁና ሲጠበቡ ምላሹ እንዲህ ዓይነት ነውረኛ ሴራ ከሆነ፣ አሁን ማሰብ ያለባቸው የቅኝ አገዛዝ ዘመን ውርስ የሆነውን የበላይነት መንፈስ መስበር እንደሚገባ ነው፡፡ ግብፅ ግትር ሆና ውኃውን በቁጥጥሯ ሥር ለማዋል ላይ ታች የምትለው፣ ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ ምድር የተከሉትን የማበጣበጥ ስትራቴጂ በማስፈጸም የበላይነቷን ለማፅናት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ የቅኝ አገዛዝ መንፈስን በታላቁ የዓድዋ ጦርነት በመስበር ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች አርዓያ ስለሆነች፣ ግድቧን በያዘችው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መሙላት በመጀመር ተምሳሌትነቷን ታጠናክራለች፡፡ በጀግንነቱ የማይታማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ክቡር ዓላማ ጀርባ ተሠልፎ በዚህ ዘመንም አንፀባራቂ ገድል ይፈጽማል፡፡ የውስጥ ተላላኪዎች ካሉም ተገቢውን ቅጣት ያሳርፍባቸዋል፡፡ አሜሪካም ሆነች ሌሎች ሊረዱት የሚገባው ተፈጥሯዊ መብት ለድርድር እንደማይቀርብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጨዋ፣ አስተዋይና ደግ በመሆኑ ጎረቤቶቹን ለመጉዳት እንደማይፈልግ የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ትዕግሥትም ገደብ አለውና አጉል ድርጊት ሲፈጸምበት እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ መታወቅ አለበት፡፡ በገዛ ገንዘቡና ጉልበቱ የሚገነባውን ግድብ መቼ መሙላት መጀመር እንዳለበት ነጋሪም አያሻውም፡፡ ግድቡን በማንም ላይ ጉዳት ሳያደርስ እንዴት መሙላት እንደሚችል በሚገባ ያውቀዋል፡፡ ከዚህ ውጪ ማንም ሊያስፈራራው አይችልም፡፡ ከተሞከረም ምላሹ ምን እንደሆነ በሚገባ ማሳየት ይችላል፡፡

የቅኝ አገዛዝ ተፅዕኖ አሁንም ድረስ ያለቀቃቸውን አንዳንድ የራስጌ ተፋሰስ አገሮች መሪዎችን ለጊዜው ዝም ማሰኘት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይዋል ይደር እንጂ ዜጎቻቸው ለምን ብለው መነሳታቸው አይቀርም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ኢትዮጵያ በአሜሪካ ጭምር ሊተገበር እየተሞከረ ያለውን የቅኝ ግዛት መንፈስ ስለምትሰባብረው ነው፡፡ ልክ እንደ ታላቁ የዓድዋ ጦርነት ድል ኢትዮጵያ በእንቢ ባይነት መነሳቷ ወሬው በዓለም እየተሠራጨ ስለሆነ፣ የተፋሰሱ አገሮች በሙሉ በዜጎቻቸው አስገዳጅነት ጭምር ከኢትዮጵያ ጎን እንደሚሠለፉ መጠራጠር አይገባም፡፡ ፍትሐዊነት በኢፍትሐዊነት ላይ የበላይነት እንደሚቀዳጅ ኢትዮጵያ ለዓለም ዳግም ታሳያለች፡፡ አሜሪካኖች እያሉ እንዳሉት ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳትሆን፣ የመላው አፍሪካ መሪ ናት፡፡ ከዚህ ቀደምም አሳይታለች፣ አሁንም ትደግመዋለች፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ፀረ ቅኝ አገዛዝ ተጋድሎን ጭምር ያስተማረች አገር ናት፡፡ አሜሪካኖች በቅጡ ባልተረዱት ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ከሚፈተፍቱ ከታሪክ ይማሩ፡፡ የመካከለኛው ምሥራቅ ቃፊራቸውን ለማስደሰት ብለው ከ110 ሚሊዮን በላይ ካላትና በአንፀባራቂ ታሪኮቿ ከምትታወቅ ትልቅ አገር ጋር አይጣሉ፡፡ ከዚህ በፊት በየቦታው ያፈሯቸው ጠላቶች ይበቁዋቸዋል፡፡ በጠማማ ፖሊሲያቸው ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ የፈጠሩትን ምስቅልቅል ሳያጠሩ ሌላ ጥፋት ለመፈጸም አይቅበዝበዙ፡፡ በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የገነቡት ሁቨር ግድብ ላይ ጥያቄ እንዲነሳባቸው የማይፈልጉትን ያህል፣ ኢትዮጵያ ላይ በተቃራኒ በማድረግ በራሳቸው ላይ ጦስ አይጥሩ፡፡ ነገ ሜክሲኮ የግብፅ ዓይነት ጥያቄ ስታቀርብ ማጣፊያው ያጥራቸዋል፡፡ ግብፅ የአስዋን ግድብን ስትገነባ ለማንም እንዳላማከረች እየታወቀ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ በትብብር መንፈስ ግድቡን እየገነባች ለውይይት መቅረቧ እንደ ድክመት ተቆጥሮ ከሆነ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ አሜሪካ አላስፈላጊ ስህተት እየሠራች መሆኑን አውቋ እጇንም አፏንም ትሰብስብ፡፡ እንዲያውም አሜሪካውያንን ከዳር እስከ ዳር በቁጣ አስነስቶ ትርምስ የቀሰቀሰውን ዘረኝነት መልክ ታስይዝ፡፡ ጥቁሮች ከሰብዓዊ ፍጡር በታች ተደርገው በሚያሳዝን ሁኔታ የሚኖሩበትን፣ ሥልታዊና ድብቅ ሥርዓቷን ታስተካክል፡፡ የራስን ቤት ሳያፀዱ የሰው ጉዳይ ውስጥ ዘው ብሎ በመግባት ሴራ መጎንጎን ተቀባይነት የለውም፡፡

አሜሪካ በጭፍን የጀመረችውን ለግብፅ ጠበቃ መሆን በፍጥነት አቁማ፣ በገለልተኝነት መርህ የታዛቢነት ኃላፊነቷን ትወጣ፡፡ የግብፅን ፍትሐዊ ያልሆነ ከንቱ ጩኸት እያስተጋባች በምንም መመዘኛ ታዛቢም ገላጋይም ሆና መቅረብ አትችልም፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ውኃውን በፍትሐዊነትና በምክንያታዊነት የመጠቀም ዓላማን እያራመደች፣ ለውኃው አንዳችም አበርክቶ ሳይኖራት ኢትዮጵያዊያን በድህነት እንዲማቅቁ የምትፈልገውን ግብፅ ዓይንን ጨፍኖ መደገፍ አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የገዛ ሀብቷን በእኩልነት እንጠቀም ብላ እጆቿን ዘርግታ ከጀርባዋ መወጋት አልነበረባትም፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ሰሞኑን ያወጣው ማሳሰቢያ አይሉት አስገዳጅ መግለጫም ሆነ፣ ከዚህ በፊት በትሬዠሪ ዲፓርትመንት ኃላፊው የተረቀቀው ኃላፊነት የጎደለው ስምምነት ተብዬ ቅዠት ተቀባይነት የለውም፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል እየተካሄደ ባለው ድርድር እያሳየ ያለው ባህሪ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው በማጤን፣ ሦስቱ አገሮች በፍትሐዊና በምክንያታዊ ተጠቃሚነት መርህ ተገዝተው መፍትሔ ላይ እንዲደርሱ ያግዝ፡፡ ከዚያ ውጪ ለማስፈራራትም ሆነ ለማስገደድ የሚደረገው ሙከራ አይሠራም፡፡ ኢትዮጵያዊያን ብሔራዊ ፕሮጀክታቸውን ለማንም አሳልፈው አይሰጡም፡፡ በግልጽ እንዲታወቅ የሚፈለገው ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ መብቷን ለመጠቀም የማንም ፈቃድ አያስፈልጋትም፣ ይህም መብት ለድርድር አይቀርብም!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

የውጭ ኢንቨስትመንት ባንኮች በኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ እንዲሠማሩ የሚፈቅድ መመርያ እየተዘጋጀ ነው

በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ የሚጠበቀው የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...

ለልማት ፕሮጀክቶች የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ተፈቀደ

የገንዘብ ሚኒስቴር በማምረቻ ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በሎጀስቲክስ፣ በኮንስትራክሽን፣ የባለኮከብ ሆቴሎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...

ፖለቲካና ሃይማኖትን እየቀላቀሉ በእሳት መጫወት አይቻልም!

ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ሃይማኖት ነው፡፡ የሃይማኖት ጉዳይ ለተቋማቱና ለምዕመናኑ ብቻ የተተወ ነው፡፡ በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥትም መንግሥትና ሃይማኖት...

አገር የጥፋት ቤተ ሙከራ አትሁን!

መንግሥት አገር ሲያስተዳድር ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የሚለዋወጡ ስትራቴጂዎች እንደሚኖሩት ዕውን ቢሆንም፣ በየጊዜው መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን መለዋወጥ ግን አይችልም፡፡ ‹‹ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ›› የሚለው መጽሐፍ...