Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናባልተፈቱ የህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳዮች ላይ የሦስቱ አገሮች መሪዎች እንዲወስኑ ሱዳን ጠየቀች

ባልተፈቱ የህዳሴ ግድብ ድርድር ጉዳዮች ላይ የሦስቱ አገሮች መሪዎች እንዲወስኑ ሱዳን ጠየቀች

ቀን:

ኢትዮጵያ ወደ መሪዎች የሚያደርስ ጉዳይ የለም ብላለች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የውኃ ሙሌትና አስተዳደር በተመለከተ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ለመሪዎች ቀርበው ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ሱዳን በመጠየቋ፣ ሲካሄድ የነበረው የሦስቱ አገሮች ድርድር ተቋረጠ።

በሱዳን መንግሥት አነሳሽነት ከሳምንት በፊት ዳግም የተጀመረው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የውኃ ሚኒስትሮችና የቴክኒክ ባለሙያዎች ድርድር በበርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንደተደረሰበት፣ የውኃ መስኖና ኢንርጂ ሚኒስቴር ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ አስታውቆ ነበር።

የሱዳን የውኃ ሚኒስትር ያስር አባስ ሐሙስ ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ድርድሩ በበርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ መግባባት የተደረሰበት መሆኑን አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ድርድሩን ለመቀጠል የሚያስፈልጉ ስምምነት ያልተደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ የሦስቱ አገሮች መሪዎች ውሳኔ እንዲሰጡበት፣ የሱዳን ተደራዳሪ ቡድን በድርድሩ ወቅት ጥያቄ ማቅረቡን ሪፖርተር ለጉዳዩ ቅርበት ካላቸው ምንጮች አረጋግጧል።

በኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በኩል ግን ወደ መሪዎች የሚያስኬድ ጉዳይ ባለመኖሩ ድርድሩ እንዲቀጥል፣ ያልተፈቱ ጉዳዮችም በድርድሩ ውስጥ እየጠሩ እንደሚሄዱ ሐሳብ መቅረቡን ለማወቅ ተችሏል።

 ነገር ግን በሱዳን በኩል ጉዳዩ የግድ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቀርቦ ውሳኔ ካላገኘ በድርድሩ ለመቀጠል እንደሚቸግር በመገለጹ የተጀመረው ድርድር ላልታወቀ ጊዜ እንዲቋረጥ ተደርጓል። የልዩነት ምንጭ የሆነው መሠረታዊ ጉዳይ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ወደ ሕጋዊነት ከተቀየሩ በኋላ፣ ቅሬታ ወይም ይግባኝ የማይቀርብባቸውና ሦስቱም አገሮች የሚገዙባቸው አስገዳጅ ስምምነት ሊሆን ይገባል፣ አይገባም የሚል አለመግባባት እንደሆነ ሪፖርተር ከምንጮች ካገኘው መረጃ ለማወቅ ችሏል።

 በተጨማሪም ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች በህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደር ላይ ብቻ የተወሰነ ይሆናል? ወይስ ቀጣይ የዓባይ ውኃ አጠቃቀምን የሚመለከት ይሆናል? የሚለውም ሌላው የልዩነት ምንጭ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። ይህ ጉዳይም ስምምነቱ ይግባኝ የማይደረግበት ሊሆን ይገባል፣ አይገባም ከሚለው ሌላው ልዩነት ጋር ቁልፍ ግንኙነት ያለው መሆኑን ምንጮች አስረድተዋል።

የግብፅ ተደራዳሪ ቡድን በዚህ ድርድር ላይ የነበረው ተሳትፎ የተቀዛቀዘ እንደነበር፣ በሱዳን በኩል ደግሞ አስታራቂ ሐሳቦች የተንፀባረቁበት ነገር ግን ቀለል ባለው ጉዳይ ላይ ደግሞ መወሰን የተቸገሩበት መሆኑ በኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች ላይ ጥያቄ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡

ግብፅ የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከቱ ሁሉም ድርድሮች ላይ ከምታቀርባቸው ሐሳቦችና የልዩነት ምክንያቶች አንዱ ይህንን ድርድር አስታኮ የኢትዮጵያን የወደፊት የዓባይ ውኃ አጠቃቀም መገደብ እንደሆነ የገለጹት ምንጮች፣ በዚህኛው ድርድርም ዳግም መነሳቱን ገልጸዋል። ይህ ድርድር ቅድሚያ ትኩረት የሰጠው በግድቡ የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅን የተመለከተ ሲሆን፣ በዚህም በበርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ስምምነት መደረሱ ታውቋል።

ቀጥሎም በሙሌት ወቅት ድርቅ ቢከሰት ጉዳቱን ለመቀነስ ኢትዮጵያ ምን ማድረግ እንደሚገባት፣ የረዥም ጊዜ የግድቡን አስተዳደር የተመለከቱ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበው ሳለ እስካሁን ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮችም ሆኑ፣ ወደፊት ስምምነት የሚደረስባቸው ጉዳዮች አስገዳጅና ሦስቱም አገሮች ያለ ይግባኝ የሚገዙባቸው ሊሆኑ ይገባል የሚል ክርክር ተነስቶ መግባባት እንዳልተደረሰበት ምንጮች ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በኩል ድርቅ ቢከሰት ጉዳቱን የመቀነስ ኃላፊነት የሦስቱም አገሮች ሊሆን ይገባል የሚል አቋም መቅረቡን የገለጹት ምንጮች፣ ግብፅና ሱዳን ግን ይህንን እንዳልተቀበሉት አስረድተዋል።

ድርቅ በሚባለው ትርጓሜ ላይም ሙሉ መግባባት አለመኖሩን፣ በዚህ ጉዳይ ላይ ስምምነት ሳይደረስ ይግባኝ የማይባልበት ስምምነት ለመፈራራም ድርድር ማድረግ የኢትዮጵያን የወደፊት የመጠቀም መብት ለመግታት የተጠነሰሰ የተለመደ የግብፅ ሴራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሉዓላዊ ግዛቷ የምታለማውን የተፈጥሮ ሀብቷን በተመለከተ ይግባኝ የማይባልበት ስምምነት ውስጥ ኢትዮጵያ እንድትገባ መጠየቅም ሉዓላዊነቷን መፈተን ነው ያሉት ምንጮች፣ በዚህ ምክንያት ሐሳቡ በኢትዮጵያ ቡድን ተቀባይነት እንዳላገኘ ገልጸዋል። በመፍትሔነትም ወደፊት የሚከሰቱ አለመግባባቶች በመሪዎች የማይቀረፉ ከሆነ፣ በሦስተኛ ወገን አስታራቂነት በዋናነትም የዓባይ ተፋሰስ አገሮችን በሚሳተፉበት ልዩ መድረክ ወይም በአፍሪካ ኅብረት ወይም በመደበኛ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት እንዲፈቱ፣ በኢትዮጵያ በኩል ሐሳብ መቅረቡንና ይህም በግብፅ ተቀባይነት አለማግኘቱን አስረድተዋል።

በዚህ የኢትዮጵያ የመፍትሔ ሐሳብ ላይ የሱዳን ተደራዳሪ ቡድን ጉዳዩ ለሦስቱ አገሮች መሪዎች እንዲመራ ጥያቄ ማቅረቡንና ውይይቱ ለተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ገልጸዋል። የድርድሩ መቋረጥን ተከትሎ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ አጽንኦት ከተሰጣቸው ጉዳዮች መካከል፣ ‹‹ድርድሩ የህዳሴ ግድቡን የተሟላ ኃይል የማመንጨት አቅም ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷ በሆነው የዓባይ ውኃ ላይ ያላትን የማይገሰስ ቋሚ መብት መጠበቅና ማክበር አለበት። በተመሳሳይም ይህ ድርድር ሉዓላዊነትንና የጋራ ተጠቃሚነትን ወደሚያረጋግጥ ዘላቂ ትብብር እንዲያደርሰን ከተፈለገ የግብፅና የሱዳንን ቀናዒነትና ሩቅ አሳቢነት ይጠይቃል፤›› የሚለው ይገኝበታል። ዳግም የተጀመረው ውይይት በሱዳን ጥያቄ መሠረት ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን ተከትሎ፣ የአሜሪካ ብሔራዊ የደኀንነት ምክር ቤት በትዊተር ገጹ ድርድሩን በተመለከተ የሰጠው ምክረ ሐሳብ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ያስገረመ፣ ያስቆጣና እያነጋገረ ነው።

የደኅንነት ምክር ቤቱ ‹‹257 ሚሊዮን የምሥራቅ አፍሪካ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ጠንካራ አመራርን ለማየት ይሻሉ፣ ይህም ማለት ፍትሐዊ ስምምነትን የሚጠይቅ ነው፤ በህዳሴ ግድብ ላይ ያሉ የቴክኒክ ጉዳዮች መፍትሔ አግኝተዋል፣ አሁን ደግሞ የህዳሴ ግድብ ውኃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት ላይ የሚደረስበት ጊዜ ሊሆን ይገባል፤›› ሲል ነው ምክረ ሐሳብ ያቀረበው።

የደኅንነት ምክር ቤቱ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1947 ሲሆን ፣ በሕግ የተሰጠው ተልዕኮም አሜሪካን በተመለከቱ ብሔራዊ የደኅንነት ጉዳዮች ላይ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ማማከር ሲሆን፣ የአገሪቱ የደኅንነት ጉዳዮች የሚመለከታቸው የፀጥታና ሌሎች ተቋማት በቅንጅት እንዲያቅዱና እንዲፈጽሙ ማድረግ መሆኑን የምክር ቤቱ ማቋቋሚያ ሕግ ያመለክታል። ሥልጣንና ኃላፊነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዴት የአሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት አጀንዳ ለመሆን እንደቻለ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ልሂቃንን እያነጋገረ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ የምክር ቤቱ ምክረ ሐሳብ፣ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ሦስቱ አገሮች በአሜሪካ ሲያደርጉ የነበረውን ድርድር እንደማትቀጥልበት አስታውቃ ስትወጣ ያቀረበችውን ምክንያት በይፋ ያረጋገጠ እንደሆነ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ የአሜሪካውን ድርድር አቋርጣ ለመውጣት ምክንያት የሆናት ድርድሩን ይታዘቡ የነበሩት አሜሪካና የዓለም ባንክ የተሰጣቸውን ሚና ወደ ጎን ትተው፣ ግብፅን የሚጠቅም አድሏዊ አቋሞችን ከማንፀባረቅ አልፈው የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን ላይ እስከ ማስፈራሪያ የደረሰ ጫና እንዳደረሱና ታማኝ ታዛቢ አለመሆናቸውን የሚገልጽ መግለጫ ማውጣቷ ይታወሳል።

ይህንንም ቅሬታዋን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ከወር በፊት በላከችው ደብዳቤ በማስታወቋ፣ የአሜሪካ የደኅንነት ምክር ቤት ሰሞኑን የሰጠው ምክረ ሐሳብ በአሜሪካ ሲደረግ የነበረው ድርድር ፍትሐዊ እንዳልነበረ ለማስረዳት ኢትዮጵያ እንደ ሁነኛ ማስረጃ ልትጠቀምበት እንደምትችልም፣ ባለሙያዎች አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ዓርብ ሰኔ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በስልክ እንደተወያዩ፣ በውይይታቸውም በህዳሴ ግድቡ ላይ የተጀመረውን ውይይት በማስቀጠል በአገሮቹ መካከል ትብብር እንዲኖርና የዓባይ ውኃን የጋራ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ መንገድ ችግሩ እንዲፈታ መምከራቸውን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ጆሴፕ ቦሬሎ ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ መወያያተቻውን፣ የውይይቱ ጭብጥ ከነበሩት መካከልም ለአውሮፓ ኅብረትና ለሳዑዲ ዓረቢያ የጋራ ትኩረት ጉዳዮች የሆኑት የህዳሴ ግድቡ ውዝግብ፣ የየመን፣ የሊቢያ፣ የሱዳን ጉዳዮች መሆናቸውን፣ እንዲሁም የመካካከለኛው ምሥራቅ የሰላም ሒደትና ሌሎች ቀጣናዊ ጉዳዮች እንደነበሩ ገልጸዋል።

በአጠቃላይ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና የዓረብ አገሮች ከራሳቸው የፖለቲካ ጥቅም አንፃር እጃቸውን በህዳሴ ግድቡ ድርድር ላይ ማስገባታቸውን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያስገነዝባሉ።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...