Thursday, December 7, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአዲስ መዋቅር ተተካ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በሥሩ 26 ድርጅቶችን አካቶ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረውና በአንድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብቻ ይመራ የነበረው ሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ በአዲስ መዋቅር ተተካ፡፡

በአረጋ ይርዳው (ዶ/ር) ዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመራ የነበረው ሚድሮክ  ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ቀድሞ የነበረው አደረጃጀት ፈርሶ፣ በአዲስ አደረጃጀት እንዲዋቀር አራት ዋና የሥራ ኃላፊነት ሹመት መስጠታቸውን ከኅዳር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በሳዑዲ ዓረቢያ በቁም እስር ላይ የሚገኙት ሼክ መሐመድ አል አሙዲ አስታውቀዋል፡፡

ባለሀብቱ እንዳስታወቁት አቶ ጀማል አህመድን፣ አቶ ደረጀ የእየሱስ ወርቅን፣ አቶ ኃይሌ አሰግዴንና አቶ አብነት ገብረ መስቀልን በተለያዩ ዘርፎች ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ሾመዋል፡፡

አራት ዋና ዋና የሚባሉ ዘርፎችን እንዲመሩ አቶ ጀማል ሲሰየሙ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግ፣ የንግድና የማዕድን ዘርፎችን ይመራሉ፡፡ በሥራቸው አራት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ተመድበው 32 ድርጅቶችን ለማስተዳደር ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ተጠሪነታቸው ለአቶ ጀማል የሆኑት በምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚነት የተመደቡት አቶ አካለወልድ አድማሱ ናቸው፡፡ ዴይላይት አፕላይድ ቴክኖሎጂ፣ ሞደርን ቢዩልዲንግ ኢንዱስትሪ፣ ሰሚት ለስላሳ ፋብሪካ፣ አዲስ ጋዝ፣ ኮምቦልቻ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ፣ ሆራይዘን አዲስ ጎማ፣ ሐዋሳ ችፑድና ሸገር ዳቦን ጨምሮ 14 ድርጅቶችን ይመራሉ፡፡ ሌላው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተመደቡት ንግድ ሚኒስትርና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር የነበሩት በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ ኩዊንስ ሱፐር ማርኬት፣ አዲስ ሆም ዴፖና ትራንስ ናሽናል አየር መንገድን ይመራሉ፡፡ በብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሸን ሥር የሚገኙትን ሚድሮክ ጎልድ፣ ሚድሮክ ጂኦሎጂካል ምርመራ ሥራና ብሔራዊ ማዕድንን የሚመሩ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንዳሉ መዋቅሩ ቢያሳይም ማንንታቸው አልተገለጸም፡፡

አራተኛው ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና በግብርና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፍ ቀድሞ በግብርና ሚኒስቴር ሥር ሰፋፊ እርሻዎችን የሚመለከተውን ክፍል ይመሩ የነበሩት አቶ ኢሳያስ ከበደ የተመደቡ ሲሆን፣ ኢትዮ አግሪሴፍት፣ ኢትዮ ድሪም፣ ሳዑዲ ስታር፣ ኤልፎራ፣ ሊሙ ኮፊ፣ የላይኛው አዋሽ፣ ጉባ ፋርምና በበቃ እርሻ ልማትን ጨምሮ 11 ድርጅቶችን እንዲመሩ ተመድበዋል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ተጠሪነታቸው ለአቶ ጀማል  መሆኑም ታውቋል፡፡ ተቋማቱ ላለፉት ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ሥር ሆነው በአረጋ (ዶ/ር) እስከ ሚያዝያ 2012 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ሲመሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በሼክ አልአሙዲ የተሾሙት አቶ ደረጀና አቶ የእየሱስ ወርቅ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት የሚመሯቸው ድርጅቶች ደግሞ ብሔራዊ አስጎብኝ ድርጅት (ኤንቲኦ) እና ሬምቦ የመኪና ኪራይና አስጎብኝ ድርጅቶች ናቸው፡፡

የቀድሞ የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይሌ አሰግዴ የደርባ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ሼክ አል አሙዲ ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ሹመት በተጨማሪ ዩናይትድ የተሽከርካሪ ጥገና አገልግሎት ድርጅቶችን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ተወስኗል፡፡

አቶ አብነት ገብረ መስቀልም በሚድሮክ ኢትዮጵያ ሥር የሚገኙትን የኮንስትራክሽን፣ የሆቴልና ሪል ስቴት (ሁዳ ሪል ስቴት) በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡

ሼክ አል አሙዲ የሾሟቸው አራቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች ማለትም አቶ ጀማል፣ አቶ ደረጀ፣ አቶ ኃይሌና አቶ አብነት ተጠሪነታቸው ለሼክ መሐመድ ሲሆን፣ እሳቸው በማይኖሩበት ጊዜ ለልጃቸው ራሚ አል አሙዲ (ዶ/ር) መሆኑም ታውቋል፡፡ የአቶ ጀማል ሹመት ግን ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች