Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅና የወንጀል ተጠያቂነቱ የኢትዮጵያ ሕግና አተገባበሩ

ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅና የወንጀል ተጠያቂነቱ የኢትዮጵያ ሕግና አተገባበሩ

ቀን:

‹‹ጀሶ ያበሉን የት ደረሱ?››

በፍሬሰላም አባተ

ከጥንት ጀምሮ በአገራችንም ሆነ በሌሎች የዓለማችን ክፍሎች ምግብን ከሌሎች ነገሮች ጋር መደባለቅ የተለመደ ተግባር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በተለይም ነጋዴዎች በትንሽ ወጪ ብዙ ትርፍ የማግኘት ዓላማ በመያዝ ውኃን ከወይን ጋር መደባለቅ፣ ከወተት ውስጥ ቅቤውን በማውጣትና ከውኃ ጋር በመደባለቅ መሸጥ የመሳሰሉት ተግባራት ከጥንታዊ የሮማውን ሥልጣኔ ጀምሮ ሲታይ የቆየ ተግባር እንደሆነ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በተለይ በአገራችን ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅ በብዛት እየተስተዋለ ያለ ተግባር ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የአገራችን የመገናኛ ብዙኃን አውታሮችም መሰል ተግባራትን በብዛት ሲዘግቡ ይስተዋላል፡፡ በተለይም በርበሬን ከሸክላ ጋር፣ እንጀራን ከጀሶ፣ ሰጋቱራን ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር፣ ዘይት፣ ቅቤ፣ ማርና የመሳሰሉትን ምግብ ነክ ምርቶች ካልተገቡ ባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅን የመሰሉ ተግባራት ሲፈጽሙ የቆዩ አካላትና ተግባሩ ሲፈጸምባቸው የነበሩ ዕቃዎች ጭምር በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሰፊ ሽፋን ሲሰጡ ይስተዋላል፡፡ ታዲያ እነዚህ የተያዙ ግለሰቦችና ንብረቶች በሕግ ፊት የሚዳኙት በምን አግባብ ነው? በዚህ ጉዳይ  የኢትዮጵያ ሕጎች ምን ይላሉ? አተገባበሩስ?

የምግብ ደኅንነት በጠቅላላው

ምግብ ደኅንነት ላይ የሚሰጠው ትኩረት በማደግ ላይ ባለ የሰው ልጆች ፍላጎት ውስጥ እየተከሰተ ነው፡፡ ክርስቲያን ኤለንና ፍሬንዝ የተባሉ አጥኝዎች ‹‹ኒውትሬሽን ፉድ ሴፍቲ ኤንድ ኮንስዩመር›› (አመጋገብ የምግብ ደኅንነትና የሸማቾች ጥበቃ) በተሰኘው ጥናታቸው እንዳረጋገጡት በዓለማችን 852 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከምግብ ጋር ተያያዥነት ባላቸው ችግሮች በተለይም ጥራቱንና ደረጃውን ያልጠበቀ ምግብ በመመገብ፣ ከምግብ ንጥረ ነገሮች ጋር የተገናኙ ችግሮች፣ ከምግብ እጥረት ጋር በተያያዘ ለሚከሰቱ ችግሮች ተዳርገው እንደሚገኙ ያመላክታሉ፡፡ በዚህም የተነሳ በርካቶች በተለይም ከሳህራ በታች ባሉ አገሮች ቀደም ሲል ባልተለመደ ሁኔታ እንደ ካንሰር፣ ኮሌስትሮል፣ ኩላሊት፣ ደም ግፊትና የመሳሰሉ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች እየተጠቁ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም በዋነኛነት እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ጉዳዮች መካከል የጥራት ደረጃቸውን ያልጠበቁና ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ ምግቦች ይገኙበታል፡፡

እዚህ ጋር ሊታይ የሚገባው ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብ ምን ማለት ነው? ሙሉ ለሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ ምግብስ አለ ወይ? የሚለውን ነው፡፡ ምግብን በጠቅላላው ደኅንነቱ የተጠበቀ (ሴፍ) ነው ብሎ መናገር አስቸጋሪ እንደሆነ በጉዳዩ ላይ የተጻፉ ጥናቶች ያሳያሉ:: ጆርናል ኦፍ ትራንስፎርሜሽናል ሊደርሺፕ የተሰኘው መጽሔት ‹‹ፉድ ሴፍቲ ኤንድ ናቹራል ኳሊቲ ፎር ዘ ፐሪቬንሽን ኦፍ ነን ኮሚዩኒኬብል ዲዝዝስ›› በተሰኘው ጽሑፉ እንዳስነበበው፣ ሙሉ ለሙሉ ደኅንነቱ የተጠበቀ (ሴፍ) ምግብ አለ ብሎ መደምደም አስቸጋሪ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ይልቁኑ በተወሰነ ሁኔታና ጊዜ ውስጥ የቀረበው ምግብ ከብክለት የፀዳ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን ማጣራቱ  የተሻለ እንደሆነ የዘርፉ አጥኝዎች ያሳስባሉ፡፡

የምግብ ደረጃ

የምግብ ደረጃ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ በመንግሥት ወይም በመንግሥት አስፈጻሚ አካላት የሚጣልና ሸማቹ ኅብረተሰብ ላይ ከምግብ ብክለት ወይም ጥራት ጉድለት መነሻነት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ቀድሞ ለመከላከል ጥቅም ላይ የሚውል የአሠራር ሥርዓት ነው፡፡ የምግብ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ዋነኛ ጠቀሜታ በተለይ ተጠቃሚው ከገበያ በሚጠቀማቸው ምግብ ነክ ምርቶች ላይ መተማመን እንዲኖረውና በምግብ ማምረት፣ ማስቀመጥና ማከፋፈል ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰብ፣ ነጋዴዎችና ድርጅቶች እነዚህን አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች አሟልተው ሥራቸውን እንዲያከናውኑና የተባለውን አስገዳጅ ደረጃ የማያሟሉ አካላት ላይ ተገቢውን የዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ያስችላል፡፡

በኢትዮጵያ አስገዳጅ የምግብ ደረጃ የመስጠት ኃላፊነትና ሥልጣን ለኢትዮጵያ ጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን የተሰጠ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ በአዋጅ ከተቋቋመበት 1970 .ም. ጀምሮ ለምግብ ነክና ለሌሎችም ምርቶች አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የማውጣት፣ የካሊብሬሽን ሥራዎች፣ የጥራት ቁጥጥር፣ የላቦራቶሪ ፍተሻና የጥራት ደረጃ ሰርተፍኬት የመስጠትና መሰል ሥራዎችን እንዲሠራ ተልዕኮ በመያዝ፣ በአሁኑ ወቅት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥር ሆኖ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

ይሁንና በተለይ ከምግብ ነክ ምርቶች ጋር ተያይዞ የሚሰጡ አስገዳጅ የጥራት ደረጃዎች በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ዘንድ በምግብነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የምግብ ዓይነቶችን ችላ ያለ እንደነበር በተለይ ቀደም ሲል በዘርፉ የተሠሩ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡ ይልቁንም እንደ እንጀራ፣ በርበሬ፣ ሽሮ፣ ቅቤና የመሳሰሉ በማኅበረሰባችን ዘንድ በስፋት ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ሳይወጣላቸው የቆዩ በመሆኑ፣ ከመሰል የምግብ ዓይነቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የጥራትና ተያያዥ ችግሮችን በሕግ አግባብ እልባት ለመስጠት የሚደረገውን ጥረት በአሉታዊ መልኩ ተፅዕኖ ሲያሳርፍበት ቆይቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መሰል ችግሮችን ለመፍታት በጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን እንጀራን ለመሰሉ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የምግብ ምርቶች ላይ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የመስጠት ሥራ የተሠራ ቢሆንም፣ ከቅንጅታዊ አሠራርና ሌሎች ወደ ኋላ በስፋት በምንመለከታቸው ምክንያቶች የተነሳ ከምግብ ጥራት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥፋቶችን በሕግ አግባብ የማረም ሥራ ውጤታማ መሆን ሳይቻል ዘልቋል፡፡

ሕጎቻችን

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነድን ጨምሮ የአገራችን ሕገ መንግሥትና ሌሎች ትላልቅ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሰው ልጅ የሰብዓዊ መብት ዝርዝር ውስጥ ምግብ የማግኘት መብትን አካተው ይገኛሉ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ በግልጽ መንግሥት የአገሪቱ መዋዕለ ነዋይ በፈቀደው መጠን ለዜጎቹ ምግብንና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት የሚያስችለው ፖሊሲ ቀርጾ ሊንቀሳቀስ እንደሚገባ አስቀምጦ ይገኛል፡፡ ይሁንና ምግብ የማግኘት መብት ካለ ጤንነት መብት ብቻውን ሙሉ ሊሆን አይችልምና ምግብ ከማግኘት መብት ጎን ለጎን ዜጎች ጤናው በተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ መኖር የሚችሉበትን አግባብ መንግሥት በቻለው አቅም እንዲያመቻች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 89(8) ላይ በግልጽ ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህንንና ሌሎች የሕገ  መንግሥት ክፍሎችን በመመልከት መንግሥት ለኅብረተሰቡ ምግብ የሚያገኝበት ብቻ ሳይሆን ጤናማ ምግብ የሚያገኝበትን ሁኔታ መፍጠር እንዳለበት መረዳት ይቻላል፡፡ ስለሆነም ይህንን ዓላማ ለማሳካት የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ እየተንቀሳቀሰ ያለ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ የወንጀል ድንጋጌ ይዘት ያላቸው ድንጋጌዎችን ያካተቱትን በተለይ የምግብ መድኃኒትና ቁጥጥር አዋጅ (በግንባር ቀደምትነት)፣ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅና የኢፌዴሪ ወንጀል ሕጎችን ለዚህ ጽሑፍ ዓላማ በመጠኑ ለማየት ተሞክሯል፡፡

የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ

ስለ አንድ ስለ ተወሰነ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ የሚመለከት ሕግ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበት ጊዜ ሁሉ ልዩ ሕጎች (Special Laws) እየወጡ፣ በተለይ ለሚነሱ ጉዳዮች መፍትሔ ለመስጠት ይሞከራል፡፡ በያዝነው ጉዳይም ምግብ ነክ ድንጋጌዎች በተለያዩ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተበታትነው ከሚቀመጡ ይልቅ ምግብንና ምግብ ነክ ጉዳዮችን የሚመለከት ልዩ ሕግ ወጥቶ ችግሮችን በዚህ ማዕቀፍ ለመፍታት የተሄደበት መንገድ ምግብ ከሰው ልጆች ሕይወት ጋር ካለው ቁርኝትና ከምግብ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮችም በግለሰቦች እንዲሁም በማኅበረሰብ ጤና ላይ ሊያሳድር ከሚችለው ዘርፈ ብዙ ችግር አንፃር አሌ የማይባል ተግባር ነው፡፡

ይሁንና ይህንን በሚመለከት በአገራችን በሥራ ላይ የዋሉት ሕጎች በተለይም አዋጅ ቁጥር 661/09 እና ይህንን አዋጅ አሻሽሎ የወጣው አዋጅ ቁጥር 1112/12 የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጆች ሕጎችን በተጠቃለለ መልኩ ከማቅረብ አንፃር አዎንታዊ ሚና የተጫወቱ ቢሆንም፣ በተለይ ሕጉ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ጉልህ ክፍተቶች ይስተዋሉባቸዋል፡፡ በተለይም ከወንጀል ድንጋጌዎች አንፃር በአዋጁ ሊካተቱ የሚገባቸው ነጥቦች በተገቢው መንገድ መካተት አለመቻላቸውን ማስተዋል ይቻላል፡፡

እዚህ ጋር በትኩረት የምናየው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ጉዳይ ነው፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ አዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ተግባርን የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል አድርጎ አልደነገገውም፡፡ በአገራችን ኢትዮጵያ ይልቁንም በመዲናዋ በአዲስ አበባ በየወቅቱ የምንሰማቸው አሰቃቂና የሰውን ሰብዓዊነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ተግባራት፣ የምግብን ጉዳይ በልዩ ሁኔታ ለመመልከት በወጣው ምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ የወንጀል ተጠያቂነታቸው ያላካተተ መሆኑ ግርምትን የሚፈጥር ነው፡፡

በአዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ 1112/12 አንቀጽ 67 በግልጽ እንደተቀመጠው፣ ‹‹ማንኛውም ሰው ቁጥጥር የሚደረግበት ምርት ደረጃውን ያልጠበቀ ወይም የአስተሻሸግ ጉድለት እንዲኖረው በማድረግ ወይም አስመስሎ በመሥራት ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ ያከማቸ፣ በጅምላ ያከፋፈለ ወይም በችርቻሮ የሸጠ ወይም ለኅብረተሰቡ ያቀረበ›› ከሆነ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ይሁንና የድንጋጌውን ይዘት ስንመለከተው ቁጥጥር የሚደረግበትን ምርት ደረጃውን ያልጠበቀ አድርጎ ማምረት በወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ቢሆንም፣ ይህ የወንጀል ተጠያቂነት ዕውን የሚሆነው በቅድሚያ ድርጊቱ የተፈጸመው ቁጥጥር በሚደረግበት ምርት ላይ ነው፡፡ ይህ ምርት አስገዳጅ ደረጃ በሚመለከተው ተቋም የወጣለት ሲሆንና ከዚሁ ከተቀመጠለት ደረጃ በታች ሆኖ የተመረተ እንደሆነ ከድንጋጌው መንፈስ መረዳት ይቻላል፡፡ ሌላው የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትለው አስተሻሸግ ላይ ጉድለት ማድረግ ወይም አንድን ምርት አስመስሎ መሥራትን ያካትታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተግባራት የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ቢሆንም፣ በአገራችን በስፋት የሚታየው ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ደባልቆ ለገበያ የማቅረብ ተግባር በቀጥታም ሆነ ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ የተከለከለ ስለመሆኑ አልተደነገገም፡፡ ይህ ደግሞ አዋጁ መሬት ላይ ያለውን ችግር በሚገባ ያልቃኘ ስለመሆኑ እንዲሞገት አድርጎታል፡፡

በዚህ ነጥብ ላይ ምናልባት በተቃራኒው ሊነሳ የሚችለው ክርክር ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት ማምረት፣ የአስተሻሸግ ብልሹነት ወይም አስመስሎ መሥራትን በወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ተግባራት ተደርገው መደንገጋቸው፣ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅንም ያካትታል የሚል ሊሆን ቢችልም፣ አንድን ምግብ ከመነሻው ከደረጃ በታች ነው ብሎ ለመበየን ለምርቱ የተቀመጠ አስገዳጅ ደረጃ ሊኖር እንደሚገባ እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም የተቀመጠ ደረጃ በሌለበት ከደረጃ በታች ነው ብሎ ማለት አይቻልም፡፡ በአገራችን ደግሞ አሁን ላይ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቀው ለኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ምግቦች በአብዛኛው በባህላዊ መንገድ ኅብረተሰቡ ለዘመናት ሲያዘጋጃቸውና ሲመገባቸው የቆዩ፣ አስገዳጅ ደረጃ ለማውጣትም ሆነ በደረጃው መሠረት እየተሠሩ ስለመሆናቸው ለመቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ ምግብን ከባዕድ ነገሮች ጋር መደባለቅን በተለየ መንገድ መያዝ እንደሚያስፈልግ ያመላክታል፡፡

የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጅ

በንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ አዋጁ ከምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጁ በተሻለ ሁኔታ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ለሚለው ሐሳብ በግልጽ ሽፋን የሰጠ ሲሆን፣ በአዋጁ አንቀጽ 30 ንዑስ ቁጥር 10 ‹‹ለሰው ጤናና ደኅንነት አደገኛ የሆኑ፣ ምንጫቸው ያልታወቀ፣ የጥራት ደረጃቸው ከተቀመጡላቸው ደረጃዎች የወረዱ፣ የተመረዙ፣ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈ፣ ከባዕድ ነገሮች ጋር የተደባለቁ የንግድ ዕቃዎችን ወይም አገልግሎቶችን ማዘጋጀት ወይም ለሽያጭ ማቅረብ ወይም መሸጥ የተከለከለና የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር መሆኑ በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል፡፡

አዋጁ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን በግልጽ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር ተደርጎ መደንገጉ እንደ መልካም ጎን ሊታይ የሚገባው ቢሆንም፣ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ለሚለው ሐረግ ተገቢው ትርጉም በአዋጁ ላይ ተሰጥቶት አናይም፡፡ ይህ አለመሆኑ ደግሞ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ የእንጀራ ዱቄት ወይም የጤፍ ዱቄት ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው?

የዳሰሳ ጥናቱ በተደረገበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ መምሪያ የእንጀራ ዱቄትን ከጀሶ፣ ከካሳቫ፣ በቆሎን ከመሳሰሉ ሌሎች የእህል ዘሮች ጋር ተደባልቀው ተገኝተዋል፡፡ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ የተሳተፉ የተለያዩ አካላት ለዚህ ሐረግ የተለያ የትርጉምና መረዳት እንዳላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሙሉጌታ ጽጌ ብርሃን የተባሉ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ማለት ለምግብነት በሚውል ምርት ላይ ሌላ ለምግብነት ሊውል የማይችል ነገር ሲደባለቅ ነው የሚል መረዳት አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም ውስጥ በደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ሆነው የሚሠሩት አቶ ሰለሞን ሙሉ ብርሃን በበኩላቸው፣ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው ያለ ደንበኛው ዕውቅና ከዋና ንጥረ ነገሩ ውጪ የሚጨመር ሌላ ማንኛውም ውህድ ነው በማለት ይገልጸዋል፡፡

እዚህ ጋር ልንመለከተው የሚገባው ምንም እንኳን የሸማቾች ጥበቃ አዋጁም ሆነ የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን የወንጀል  ተጠያቂነት የሚያስከትል ተግባር አድርገው የደነገጉ ቢሆንም፣ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው መቼ ነው? የሚለው በሕጎቹ ላይ ተገቢው ትርጉም ያልተሰጠው በመሆኑ ሕጉን ለማስፈጸም በተቋቋሙ የተለያዩ ተቋማትና ባለሙያዎች ስለ ጉዳዩ ያለው ግንዛቤ የተለያየ እንዲሆን ይህም  ሕግን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ ጉራማይሌ የሆነ አረዳድ እንዲኖር አድርጓል፡፡

የሌሎች አገሮች ተሞክሮ

በዚህ ነጥብ ላይ የሌሎች አገሮች ሕጎች ምን ይመስላሉ? የሚለውን ስንመለከት፣ ከአገራችን የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ ጋር አቻ የሆነው የማሌዥያ የምግብ ሕግ ግልጽ ትርጉም የሰጠ ሲሆን፣ ይኸውም ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው የምግቡን የምግብነት ደረጃ ሊያወርዱ የሚችሉ ወይም በየትኛውም ሁኔታ ከነባሩ የምግብነት ደረጃ አንፃር ዝቅ ያለ የንጥረ ምግብ ይዞታ እንዲኖረው የሚያደርግ ከሆነ፣ ምግቡ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል ሊያስብል እንደሚችል ተደንግጓል፡፡

የሲንጋፖር የምግብ ሕግ ደግሞ ምግብ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚባለው የምግብነት ይዘቱን የሚቀንሱ ንጥረ ነገሮች መጨመር ወይም መደባለቅ ብቻ ሳይሆን በምግቡ ውስጥ ሊካተቱ የሚገባቸውን አንዳንድ ይዘቶችና ንጥረ ነገሮችን አለማካተት ጭምር በትርጉም ተካቶ ይገኛል፡፡ ስለሆነም የአገራችን ሕጎችም ከዚህ አንፃር የሚታይባቸውን ክፍተት ቢያርሙ፣ ሕግን በማስፈጸም ሒደት ውስጥ እየተከሰተ ያለውን የመናበብ ችግር ሊፈታ ይችላል፡፡

ተግባራዊ ተግዳሮቶች

የአገራችን ሕግ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን በተመለከተ ምንም እንኳን ጉዳዩን በልዩ ሁኔታ እንዲመለከት ታስቦ የወጣው አዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ በጉዳዩ ላይ ዝምታን ቢመርጥም፣ የሸማቾች ጥበቃ አዋጅና የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ ከነጉድለታቸው የሕግ አተረጓጎም መርሆዎችን ተከትሎ በጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛል፡፡

ሕጉን ከነጉድለቱ ለመተርጎም እየተኬደ ባለው መንገድ ላይ ደግሞ የሚያጋጥሙ ተግባራዊ መሰናክሎች በዘርፉ የሚደረገውን ሕግ  የማስከበር ሒደት በእጅጉ እየጎዱ ይገኛሉ፡፡ ለአብነት ያህል የዳሰሳ ጥናቱ በተደረገበት የንፋስ ስልክ ላፍቶ ፖሊስ መምሪያ ውስጥ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቀዋል በሚል በቁጥጥር ከሚውሉ የምግብ ዓይነቶች ውስጥ በአመዛኙ እንጀራ፣ ቅቤና ማርን መመልከት የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 90 በመቶ የሚሆነውን ወይም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው እንጀራን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ የሚሠሩ በተለይም ከጀሶ፣ ኖራና ካሳቫን ከመሳሰሉ ነገሮች ጋር ተያይዞ የሚገኙ መዛግብት ናቸው፡፡

የመዝገቦች ተግባራዊነትን በሚመለከት እንደ ኢንስፔክተር ጥላሁን ሙላቱ የክፍለ ከተማው ኢኮኖሚክና ሸማቾች ጥበቃ ወንጀል ምርመራ ቡድን መሪ አገላለጽ እንዲሁም ከፖሊስ ማዘዣው ስታትስቲክስ መረዳት እንደሚቻለው፣ በ2011 በጀት ዓመት በመሰል ጉዮዳች ከሚጣሩ መዛግብት ውስጥ ከአምስቱ አራቱ ውጤታማ እንደማይሆኑ መረዳት ተችሏል፡፡ በክፍለ ከተማው በፌዴራል ዓቃቤ ሕግነት በመሥራት ላይ የሚገኙት ሙሉጌታ ጽጌ ብርሃንና ወ/ሪት ትዕግሥት ባዘዘው ከፖሊስ አባሉ ጋር የሚስማሙ ሲሆን፣ በተለይ አቶ ሙሉጌታ ጽጌ ብርሃን የተባሉት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ እንዳስቀመጡት ከዓመት በላይ በሚሆነው የኢኮኖሚና የሸማቾች ጥበቃ ቡድን ዓቃቤ ሕግነት ቆይታቸው ከሚመጡ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ ነክ ምርመራ መዛግብት ውስጥ ውሳኔ ለመስጠት የቻሉት በአንድ መዝገብ ላይ ብቻ ነው፡፡ የዚሁ መዝገብ ዕጣ ፈንታም ማስረጃ  ባለመሟላቱ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 42(1)(ሀ) መሠረት መዘጋቱን የገለጹልኝ ሲሆን፣ አብዛኞቹ ሌሎች መዝገቦች ፖሊስ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲያቀርብ የታዘዙ መሆናቸውንና እነዚህ ማስረጃዎች ባለመገኘታቸው መዝገቦች ተወዝፈው ለመቀመጥ እንደተገደዱ ያስረዳሉ፡፡

ምክንያቱ ምንድነው?

የወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርሆዎች ከሆኑት መካከል የሕግ፣ የፍሬ ነገርና የሐሳብ ክፍሎች ተሟልተው መገኘት ዋነኞቹ ናቸው፡፡ አንድ ወንጀል ተፈጽሟል ለማለት (ሕጋዊ ፍሬ ነገሩ) ማለትም የተደረገው ተግባር በሕግ የተከለከለና የሚያስቀጣ መሆኑ መደንገግ አለበት፣ ሌላውና ሁለተኛው ይህንን በሕግ የተከለከለ ተግባር ተጠርጣሪው ስለመፈጸሙ በማስረጃ መረጋገጥ አለበት፡፡ ሦስተኛው የሐሳብ ክፍሉ ሲሆን፣ ይህን በሕግ የሚያስቀጣ ወይም የተከለከለ ተግባር የፈጸመ ሰው ድርጊቱን የፈጸመው አስቦ ወይም በቸልተኝነት ስለመሆኑ ማረጋገጥ ነው፡፡

ወደያዝነው ጉዳይ ስንመለስ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ በሕጋችን በተለይም በሸማቾች ጥበቃ አዋጁና በወንጀል ሕጋችን በግልጽ                      የተደነገገ ቢሆንም፣ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ የሚጠረጠሩ ሰዎች ለምግብነት ከሚቀርበው ነገር ጋር ባዕድ ነገር ደባልቀዋል ብሎ በተገቢው ማስረጃ ማቅረብ ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ከእንጀራ እህል ጋር ጀሶ ቀላቅሏል ተብሎ የሚጠረጠር ሰውን በወንጀል ጥፋተኛ ለማስባል ባዕድ ነገር ተደባልቆበታል የተባለው እንጀራ ተመርምሮ፣ በትክክል ባዕድ ነገር ተደባልቆበታል ወይ?  ይህ የተደባለቀበት ባዕድ ነገር ምንድነው?  የሚሉት ነገሮች በተገቢው አካል መጣራትና መረጋገጥ አለባቸው፡፡ ለዚህም ተገቢው የላቦራቶሪ ምርመራ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የአብዛኞቹ ችግሮች መነሻ፡፡

እንደ ኢንስፔክተር ጥላሁን ሙላቱ አገላለጽና ጉዳዩን የሚከታተሉ ዓቃብያነ ሕግ ከሆነ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል በሚል የሚጠረጠረው ምርት ከባዕድ ነገር ጋር በትክክል ስለመደባለቁ በላቦራቶሪ ምርመራ እንዲያረጋግጥ የሚላከው ወደ ኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ሲሆን፣ በኢንስቲትዩቱ ለመሰል ምርመራ ከተላኩ ናሙናዎች ውስጥ ለአንዱም ናሙና ምርቱ ከባዕድ ነገር ጋር ተደባልቋል የሚል ምላሽ አልተሰጠም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ምንድነው? ስንል ለጠየቅነው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የላቦራቶሪ ባለሙያ የሆኑት አቶ ፍሬው ጨዋቃ ሲመልሱ፣ በመሰል ጉዳዮች ተጠርጥረው የሚመጡ የምግብ ናሙናዎች ላይ የመርዛማነት ምርመራ (አኪውት ቶክሲኮሎጂ) ምርመራ ይደረጋል፡፡ በዚህ የምርመራ ሒደት ውስጥ የምግብ ምርቱ ለምግብነት ሲውል በቀጥታ ሰዎችን ይመርዛል ወይስ አይመርዝም የሚለውን በተመለከት ብቻ ምርመራ የሚደረግ ሲሆን፣ መሰል ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ሒደቶች በምግቡ ላይ ቀጥተኛ መርዛማነት የሚያስከትሉ ሳይሆኑ በጊዜ ሒደት የሚመጡና ተላላፊ ላልሆኑ የጤና እክሎች የሚያጋልጡ በመሆናቸው የሚደረገው ምርመራ መርዛማነት የለውም የሚል ውጤት እንደሚያስከትል ያስረዳሉ፡፡ ይህ መርዛማነት (አኪውት ቶክሲኮሎጂ) ምርመራ ምግቡ ከምን ዓይነት ባዕድ ነገር ጋር እንደተደባለቀም ሆነ ምግቡ በጊዜ ሒደት ሊያስከትላቸው የሚችላቸውን እነዚህን የጤና እክሎች ማሳየትና ማረጋገጥ የሚችል ባለመሆኑ፣ ምርቱ መርዛማነት የሌለው እንደሆነ የበለጠ ምርመራ መደረግ እንዳለበት በመግለጽ ናሙናውን ለላኩት አካላት ተመላሽ እንደሚደረግ ይናገራሉ፡፡

አቶ ፍሬው ሲቀጥሉም መሰል ምርመራ ለማድረግ አካላዊና ኬሚካላዊ (ፊሲዮኬሚካል) ምርመራዎች ማድረግ የሚችል ላቦራቶሪና (ጂሲኤምኤስ እና ሲሲኤምኤስ) የተሰኙ የላቦራቶሪ ምርመራ ግብዓቶች እንዲሁም ከአሥር በላይ የላቦራቶሪ ምርመራ ሒደቶች የሚያስፈልጉ ቢሆንም፣ መሰል ጉዳዮችን እንዲመረምር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የምርመራ ግብዓቶች እንዲሁም በተለይ በዚህ ዘርፍ የሠለጠነ ባለሙያ ባለመኖሩ ምርመራዎቹን ማድረግ እንዳልቻለ ያስረዳሉ፡፡ ለዚህም የተሻለ የምርመራ አቅም ላለው የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም እንደሚልኩ ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና በኩል ደግሞ ሌላ ፈተና እንዳለ ይገልጻሉ፡፡ ኢስስፔክተር ጥላሁን ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከሚሰጠው ምላሽ መነሻ በማድረግ ናሙናውን ለተስማሚነት ምዘና ተቋም የምንወስድ ቢሆንም፣ ተቋሙ ለአንድ ናሙና ምርመራ የሚጠይቀው ክፍያ ከፍተኛ በመሆኑና ይህንን ክፍያ በእያንዳንዱ ምርመራ መዝገብ ላይ ለሚገኘው ናሙና ከፍሎ ማስመርመር ተቋሙ ስለማይችል ምርመራዎች በእንጥልጥል ይቀራሉ ይሉናል፡፡

ኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም የሬጉላቶሪ ተቋም ሲሆን፣ በዋነኛነት ተቋሙ የተቋቋመበት ዓላማም በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ ምርቶቹ ከወጣው አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ጋር ተስማምተው የተሠሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጥ ነው የሚሉን ደግሞ የተቋሙ የደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ናቸው፡፡ የተቋሙ ሥራ አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸውን ምርቶች ከወጣው ደረጃ ተስማሚነታቸውን መፈተሸና ማረጋገጥ ሆኖ ሳለ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ማደባለቅን አስመልክቶ በተለይ ከፖሊስ ተቋማት የሚመጡ ጥያቄዎች ግን ይህንን ያላገናዘቡ ናቸው፡፡ ፖሊስ በመሰል ጉዳዮች ላይ የሚያቀርበው ጥያቄ የሚቀርቡ ናሙናዎች ከባዕድ ነገር ጋር የተደባለቁ ስለመሆናቸው፣ እንዲሁም ናሙናው ለምግብነት ቢውል ለጤና ተስማሚነው አይደለም የሚሉት ጭብጦች ላይ እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም የሚቀርቡ ናሙናዎችን ለምግብነት ቢውሉ ከጤና አንፃር ተስማሚ ናቸው ወይስ አይደሉም ብሎ የመወሰን ሥልጣን የሌለው በመሆኑ፣ ለመሰል ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ይቸግራል ይሉናል፡፡ የላቦራቶሪ አቅምን በተመለከተ ላቦራቶሪው የትኛውንም ዓይነት ምርመራ የማድረግ አቅም ያለው ቢሆንም በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የሚሠራው ከጥራት ደረጃ ምዘና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ብቻ  መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ምንም እንኳን ተቋሙ ከጥራትና ደረጃዎች ባለሥልጣን ጋር በመሆን አስገዳጅ የጥራት ደረጃ ላልወጣላቸው የአገር ውስጥ ምርቶች አስገዳጅ ደረጃ ለማውጣት ጥረት እያደረገ ያለ ቢሆንም፣ እንዲሁም እንጀራን ለመሳሰሉ በኢትዮጵያ በግንባር ቀደምትነት ለምግብነት የሚውሉ ምግቦች አስገዳጅ የጥራት ደረጃ እ..አ. ከ2013 .ም. ጀምሮ ያወጣ እንዲሁም ከ29/03/2018 .ም. ጀምሮ ይኸው ደረጃ የተሻሻለ ቢሆንም፣ በተለይ ከፖሊስ ተቋማት የሚቀርቡ ጥያቄዎች ይህንን መሠረት ያደረጉ ባለመሆናቸው ጥያቄያቸውን በሚፈለገው ደረጃ መመለስ አልተቻለም፡፡ ክፍያን አስመልክቶ ለሚነሳው ነጥብም በዋነኛነት የተቋሙ ደንበኞች አምራቾችና አስመጪዎች በመሆናቸውና ይህንኑ አገልግሎት በክፍያ የሚያገኙ በመሆኑ፣ እንዲሁም ከፖሊስ ተቋማት ለሚነሱ ጥያቄዎች ማስተናገጃ የሚሆን አሠራር ባለመኖሩ ክፍያው ሊጠየቅ እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡

በአጠቃላይ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር የመደባለቅ ወንጀሎች ጋር ተያይዞ የሚነሱ የሕግና የአሠራር ክፍተቶች ባለመቀረፋቸው አጥፊዎች በተገቢው ሁኔታ የዕርምት ዕርምጃ ያላገኙ ከመሆኑም በላይ ሌሎች በመሰል ተግባር እንዳይሰማሩ አስተማሪ የሆኑ ውሳኔዎችን ማሰጠት አልተቻለም፡፡ ከዚህም በላይ በመሰል ተግባራት ተጠርጥረው ከሚያዙ ኤግዚቢቶች ጋር ተያይዞ የሚነሳው ችግርም በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በአንድ ምርመራ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ ማለትም የተያዘው ኤግዚቢት ከባዕድ ነገር ጋር የተደባለቀ ወይም ጎጂ ተብሎ እስካልተረጋገጠ ድረስ በመሰል ጉዳዮች የተያዙ ምርቶች ሊወገዱ ወይም ከባለንብረቱ ሊወረሱ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ በሌላ በኩል ምርቱ (ኤግዚቢቱ) ለባለቤቱ ይመለስ ቢባል ምንም እንኳን በአሠራር ክፍተቶች የምርቱን ጎጂነት ወይም ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅ  ማረጋገጥ ባይቻልም፣ ሌሎች ማስረጃዎች (ለክስ በቂ ባይሆኑም) ይህንን እያሳዩ ኤግዚቢቱን ለተጠርጣሪው መመለስ ኅብረተሰቡን ለአደጋ ሊያጋልጥ የሚችል መሆኑ፣ በጉዳዩ ላይ ያለውን ውስብስብ ችግር ያሳያል፡፡

ማጠቃለያ

መሰል ችግሮችን ለመፍታት በተለይ ሕጎቻችን ላይ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን መገንዘብና ለዚህም ተገቢውን መፍትሔ መስጠት ያሻል፡፡ ይልቁንም መሰል ጉዳዮችን እንዲመለከት የታወጀው አዲሱ የምግብ መድኃኒትና ጤና አጠባበቅ አዋጅ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን አስመልክቶ ዝምታን መምረጡ ግርምትን የሚፈጥር ቢሆንም፣ በቀጣይ ይህንን ባካተተ መልኩ የማሻሻያ ድንጋጌዎች ተካተው ቢቀርቡ የተሻለ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሕጎቻችን እንደ ሌሎች አገር ሕጎች ሁሉ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን አስመልክቶ ተገቢውን የሕግ ትርጉም መስጠት ቢችሉ፣ በተለያዩ ባለድርሻ አካላት መካከል ስለ ጉዳዩ ያለውን ጉራማይሌ አመለካከት ሊቀርፍ ይችላል፡፡

የሕግ አተገባበር ተግዳሮቶችን በተመለከተ የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ መፍትሔ ማስቀመጥና መሠረት የሚጠይቅ ሲሆን፣ ለረዥም ጊዜ በተለይ ከላቦራቶሪ ምርመራ ላይ የሚታዩ ችግሮች ጎልተው የሚነሱ ሲሆን፣ በተለይ መሰል አገራዊ ጉዳዮችን ለማየት የተቋቋመው የኅብረተሰሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለበት የአቅም ውስንነት ምክንያት በመሰል ጉዳዮች ላይ ምርመራዎችን አድርጎ ተገቢውን ውጤት መስጠት አልቻለም፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ የተቋሙን አቅም ማጎልበት በተለይም ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር መደባለቅን በተመለከተ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ የሚያስችሉ የላቦራቶሪ ግብዓቶችን ማሟላትና ባለሙያዎችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ ማስገባት ቢቻል፣ ከምንም በላይ በዘርፉ የታየውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል ቢሆንም ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የመንግሥት ቁርጠኝነትና የበጀት ድጋፍም ይጠይቃል፡፡

ሌላው በኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ተቋም ያለውን አቅም የመጠቀም ጉዳይም እንደ መካከለኛ ጊዜ መፍትሔ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ በሕግ አካላት በኩል የተቋሙን ማንዴት ተገንዝቦ የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በዚሁ አግባብ ማቅረብ አንዱ ሲሆን፣ ሌላው ከአገልግሎት ክፍያ ጋር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ለሚፈለገው ምርመራ የሚስፈልገውን መለኪያ ለይቶ በዚህ ፓራ ሜትር መለኪያ ብቻ ምርመራ እንዲደረግ በማድረግ ለምርመራ የሚወጣውን ወጪ መቀነስ ይቻላል፡፡ ሁለቱም የመንግሥት ተቋማት እስከሆኑ ድረስ ምርመራዎች ያለ ክፍያ የሚደረጉበትንም ሁኔታ መፈለግ ሌላው መፍትሔ ነው፡፡

ሦስተኛውና እንደ አጭር ጊዜ መፍትሔ ሊታይ የሚችለው ናሙናዎች ለላቦራቶሪ ምርመራ ከሚላኩ ይልቅ ምግቦች ከባዕድ ነገሮች ጋር ሲደባለቁ በቀጥተኛ እማኝ ሊሆኑ የሚችሉ የሰዎችና ሌሎች ማስረጃዎችን ለማግኘት የሚያስችሉ ፖሊሳዊ ኦፕሬሽኖችን መሥራት፣ ናሙናዎችን ልኮ በላቦራቶሪ ችግር ምክንያት ከሚከሰቱ የምርመራ መዝገብ መጓተት ችግሮችን መቅረፍ ይቻላል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...