Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየኮሮና ቋንቋና ነፍሰ ጡሯ ዓለማችን (ክፍል አንድ)

የኮሮና ቋንቋና ነፍሰ ጡሯ ዓለማችን (ክፍል አንድ)

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

1 ሥልጡኑ ዓለም

የሰው ልጅ ከዘመን ዘመን፣ ከማኅበራዊ ሥርዓት ወደ ማኅበራዊ ሥርዓት እየተሸጋገረ፣ እየተስፋፋና እየተመነደገ ሲመጣ ራስ ወዳድና ስግብግብ ፍላጎቱ ምድሪቱን እያራቆተ፣ ራሱንም ሌላውንም ህያው ነገር ሁሉ የመጥፋት አፋፍ ላይ አድርሷል፡፡ እዚህ ውጤት ላይ ያደረሱት ድርጊቶች ብዙና ተወራራሽ ናቸው፡፡

ሰው የራሱን ቁጥር ያለልክ እያባዛ ወደ ዋልታዎች እስከ መቅረብና በባህር ላይ ተንሳፋፊ ቤት ሠርቶ እስከ መኖር ድረስ ምድሪቷን ወሯታል፡፡ በዚህም የሌሎች ህያው ነገሮችን (ከዕፅዋት እስከ እንስሳት ድረስ) መድረሻ አሳጥቷል፡፡

ጠንቅነቱ በሥፍራ ማጣበብ ብቻ የሚገለጽ አደለም፣ ከሚያስፈልገው በላይ የሚያመርትና የሚያጋብስ፣ ከሚበላው በላይ የሚያሰናዳ ባለ አዕምሮ “አንበጣም” ሆኗል፡፡ በኑሮው የሚፈጥረው ቆሻሻና የመብል ትራፊው ሳይቀር የምድሪቱ ችግር ነው፡፡

አግበስብሴነቱና አባካኝነቱ፣ ንፉግነትና ጨካኝነት ባለው ማኅበራዊ ሥርዓት ውስጥ የሚካሄድ እንደመሆኑ የሀብትና የቴክኖሎጂ ባለቤትነቱ በጥቂቶች መዳፍ ውስጥ እየገባ ብዙዎች ደግሞ ሀብት የለሾች እየሆኑ መጥተዋልና፣ የሀብት የለሽነቱ ደረጃ በከፋ ድህነትና በጥንታዊ አኗኗር ውስጥ የመዳከርና በረሃብ የመርገፍም ፈርጆች አሉት፡፡ እናም የሚደርሰው ጥፋት በተቀናጣ ድሎትም በኩል፣ በሞትና በሕይወት መሀል ሆኖ በጥንታዊ መንገዶች በመቅበዝበዝ በኩልም ነው፡፡

የሰው ልጅ በእርስ በርሱና በምድሪቱ ላይ የሚያካሂደው ማራቆትና መራቆት ያለበት ግብግብ በኃይል መንገድ ሲከናውን የኖረ ነው፡፡ በዚህም ረገድ ሲካሄድ የኖረው የኃይል ብልጫ እሽቅድምድም ኬሚካልን፣ ሕይወትንና የደቀቀ ቁስን ኑክሌራዊ ቅንብር ወደ ጅምላ ፍጅት ጦር መሣሪያ እስከ መቀየር አድርሷል፡፡

ሰው መሬትን ባጣበበ ተስፋፊነቱ ከዚህ በፊት ካልቀረባቸው ህያው ነገሮች ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች ጋር የመነካካት ዕድሉን በማስፋቱና የምድርን የአየር ብረት እየለወጠ፣ ባለ በካይ ተፅዕኖው የህያው ነገሮችን የአኗኗር ባህሪ ከደቂቅ እስከ ግዙፎቹ እያስቀየረ እንደ መሆኑ፣ እንዲሁም ምድሪቱ የተጀቦነችበትን ኦዞናዊ ቡልኮ እንደ ማሳሳቱና በብክለት ክምችት እንደ ማጣበቡ፣ ከዚህ በፊት ለማያውቃቸው ወይም የረባ ሚና ላልነበራቸው በሽታዎች ራሱን ማጋለጡ ከጊዜ ጊዜ ቀጥሏል፡፡

በዘመናት ምርምርና ፈጠራ ያደረጀው የፀረ ተህዋሲያን የፈውስ ሀብቶች በትርፍ አሳዳጅነት ግፊት ያላግባብ ጥቅም ላይ እየዋሉ፣ ግብርናም ውስጥ እየተሠራባቸው በቀጥተኛና ኢቀጥተኛ መንገዶች ተሃዋሲያን እየተለማመዷቸውና የፈውስ አቅማቸው እየደከመ፣ ቀድሞ ተሸንፈው በነበሩ ተሃዋሲያን እንደ ገና በገፍ የመጠቃት አደጋን ጭምር በራሱ ላይ እያጠራቀመ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ የሰው ልጅ አይጎደፍረውና አያቃጥለው የለው፣ አያጓጓውና አይሞክረው/አይፈጥረው የለው፣ አያመርተውና አይበላው የለው በሆነ አኗኗሩ የብስን፣ ባህርን፣ አየርን በብክለት እያጣበበና ሚዛን እያዛባ፣ የምድሩቱን ህልውና መመለሻ ወደ ሌላው ሕይወት አልባነት እያስጠጋ (የራሱን ጠቅላላ መጥፋት እያፋጠነ) ይገኛል፡፡ ከዚህ የሞት ጉዞው እንዲመለስ በምርምር ሥራዎች፣ ሳይንሳዊ ንቃትን በማስፋፋትና በቅዋሜዎች ወዘተ. ብዙ ብዙ ተጩኋል፡፡ እነዚህ ጩኸቶች ግን በአብዛኛው የለበጣ ጆሮና ማረሚያ ከማግኘት ባለፈ አልተሰሙም፡፡

2 የኮቪድ-19 ወረርሽኝ

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለምን (ከሥልጣኔና ከኃያልነት ቁንጮዎቹ እስከ ድሆቹ አገሮች) እየገረፈና መሸሺያ የለሽነታቸውን እያሳየ፣ የሰው ልጆችን በጥፋት የተሞላ የኑሮ ሥርዓትና የሥልጣኔ ጉዞ አግዝፎ እያጋለጠ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተገቢ ጆሮ ያላገኘውን፣ ‹‹ምድሪቱንና የሰውን ልጅ እናድን!›› ባይ ጩኸት ታይቶ በማይታወቅ የአለንጋ ቋንቋ አስተጋብቷል፡፡

የሰው ልጅ የኑሮ ፍልስፍናውንና ኑሮውን የሚዘውሩትን የትርፍ፣ የስስትና የኃያልነት እሽቅድምድም ትርታዎች እስካልቀየረ ድረስ፣ ከዛሬውም የባሰ መግቻ ባጣ ተስፋፊነቱና ሥነ ምኅዳር አዛቢነቱ ከእንስሳት ወደ ሰው የሚያመጣው የአዲስ በሽታ አደጋ አብሮት እንደሚቆይ፣ እንዲሁም ህያው ነገሮችን ወደ ጅምላ ጨራሽ ጦር መሣሪያ ከሚቀይሩ ሙከራ ቤቶችና ከማከማቻዎቻቸው በስህተትና በሻጥር ሊያመልጡ የሚችሉ የባሱ የዕልቂት ድግሶች እንዳሉለትም ኮቪድ-19 እየነገረው ነው፡፡ ኮቪድ-19 የለፈፈው ማስጠንቀቂያ በወረርሽኝ በሽታ አደጋ የታጠረ ብቻ አደለም፡፡ የኬሚካልና የኑክሌር የፍጅት ጦር መሣሪያዎችን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡

ጊዜው ዓለማችን ለውስብስብ ችግሮች መፍትሔ መስጠት የተቸገረችበት (አዎንታዊ መፍትሔ የመስጠት ዕድሎች ጠርሙስ አንገት ጋ ደርሰው የታነቁበት)፣ ከአየር ንብረት መለወጥ ጋር የተያያዙ “ተፈጥሯዊ” ጥፋቶች (የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ማዕበሎች፣ ነጎጓዶችና ጎርፎች፣ የሙቀት ክረትና ሰደድ ቃጠሎዎች፣ የበረዶ ቅልጠትና የውቅያኖሶች መስፋት) የበረቱባቸው፣ የኑሮ ቀውሶች ከሰዎች አጠገብ እጅግም አልርቅ ያሉበት ነው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2000 ወዲህ ድንገተኛ ሰበቦች፣ ዓለምን የነቀነቁ ቀውሶችና የለውጥ ማዕበል አዋላጅ የሚሆኑበት ሁኔታ ለምቷል፡፡ የሠለጠነውና የበለፀገው በሚባለው ዓለም ውስጥ ለፋሽስታዊነት ቅርብ የሆኑ የቀኝ አክራሪዎች ሕዝብን መቅዘፍ፣ ፓርላማ መግባትና መንግሥት መምራት ሲችሉ፣ ወፈፌ ባህሪ መንግሥታዊ ሥልጣን ላይ ወጥቶ እየተጎማለለ ዓለምን ሲያብጥ ማየታችን፣ በዓለማች ውስጥ የእነ ሂትለር ዓይነት የከፋ ዕብደት የመከሰት ዕድል የመብሰሉም ምልክት ነው፡፡ የአሁኑ ዘመን ፋሽስትነት ደግሞ የግድ የመንግሥት መሪ መሆንን የማይሻ ነው፡፡ ኬሚካላዊ፣ ሕይወታዊና ኑክሌራዊ የፍጅት መሣሪያዎችን በማሹለክ ወፈፌ ፋሽስቶች ጅምላ በቀል ሊፈጸሙ ይችላሉ፡፡ ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የመጣ በቀቢፀ ተስፋ መሸበር መረን ወጥቶ፣ ጠላቱን የሳተ ጥቃት (በአሜሪካ በእስያ መጥ ሰዎች ላይ፣ በቻይናም በጥቁሮች ላይ) ሲሰነዝር ማየታችን፣ ፋሽስቶች ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማስነሳት የሚችሉበት በጥላቻና በቀቢፀ ተስፋ የመታወር ተጋላጭነት እየጨመረ እንደሆነ የሚጠቁም ነው፡፡

በልዕለ ኃያላን ውስጥ የሚዛን ለውጥ መምጣት፣ የአንዱ አሽቆልቁሎ የሌላው ማሸቀብ፣ ወይም የልዕለ ኃያላዊ ግንኙነት ባለጥንድም ይሁን ባለብዙ ዋልታ፣ ወይም በልዕለ ኃያላዊ የሽርክ አሰባሳቢነት ውስጥ የሚፈጠሩ የሠልፍ ለውጦች ሁሉ ምድሪቱንና የሰው ልጆችን ከጥፋት በማዳን ረገድ መፍትሔ እንደማይሆኑ፣ ዓለም የምትመራበት ፍልስፍና ዘመን ያረጀበት መሆኑን የኮቪድ ወረርሽኝ በብርቱ አጋልጧል፡፡

የዓለም ሀብት በጥቂቶች መግበስበስ ከኃያልነት እሽቅድምድምና ከጦርነት ውጤቱ ጋር ከሥራ ውጪ ሆኖ የሰው ልጅ ራሱንና ምድሪቱን አስማምቶ ወደ መንከባከብ ካልዞረ፣ ምድሪቱ ጠፍ ልትሆን የምትችልበትና የሰው ልጅ በገፍ የሚያልቅበት ዕድል ቅርብ ነው፡፡ ከዕልቂት የተረፈ የሰው ዘር ካለም በጨረር፣ በኬሚካል፣ በበሽታ፣ በተበከለና ምግብ እጥረት በተንሰራፋበት ዓለም ውስጥ በተከረቻቸሙ መንደሮችና ጉድጓዶች ውስጥ ተደብቆ መኖር የህልውናው እውነታ እንደሚሆን ተተንብይዋል፡፡ ጉዳቱ ከዚህ ሻል ካለ የሆነ መከላከያ ኮፈን ለብሶ የመንቀሳቀስ እስረኝነት የሰርክ ኑሮው ሊሆን ይችላል፡፡

ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያመጣው ማንም ሰው የሚያደርገው ከፊል የፊት ጭምብልና የጤና ባለሟያዎች በሕክምና አካባቢ የሚለብሱት ከላይ እስከ ታች የሚጠርዝ ልብስ፣ በየኮፈን ውስጥ ሆኖ የመኖር ትንቢት ዳር ዳርታም ይመስላል፡፡ ኮሮናን ለመከላከል ጭምብል ማድረግ፣ ሲስሉና ሲያስነጥሱ በክንድ አፍን ማፈንና ሁለት ሜትር አካባቢ ከሰው መራቅ ሲነገረን፣ ቫይረሱ ክብደት ስላለው በትንፋሽ ፍንጥቅጣቂዎች ከተረጨ በኋላ በሁለት ሜትር ርቀት አካባቢ ውስጥ የመንሳፈፍ አቅሙን አጥቶ ባደረሰው ሥፍራ ላይ ያርፋል በማለት ነው፡፡ ሰው አለመንካትና አለመጨበጥ፣ የደረጃ እጀታ አለመንካት፣ የተጓዙበትን ጫማና የላይ ልብስ እንዳደረጉ እቤት አለመግባት የሚባለው ሁሉ ቫይረሱን ልናዟዙረው እንደምንችል ታሳቢ በማድረግ ነው፡፡

የሆነ ሥፍራ ላይ ያረፈ የኮቪድ-19 ቫይረስ ከመምከኑ በፊት በንክኪ ሊሸጋገር እንደሚችል ሁሉ፣ በኃይለኛ ንፋስ ሊዳረስ የማይችልበት ምክንያት የለም፡፡ ይህ ሊሆን እንደማይችል እስካሁን ያረጋገጠም የለም፡፡ እናም ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባትና መድኃኒት እስካልተገኘለትና ቅጣቱ እያዳገመ እስካስቸገረ ድረስ ኮፈን መልበስንና ወደ መጓጓዣ፣ ወደ ቤትና ወደ መሥሪያ ቤት ከመግባት በፊት በፀረ ተሃዋሲን ሙሉ ለሙሉ መፅዳትን መጠየቁ አይቀርም፡፡ የሕዝብ መገናኛ ሥፍራዎችን፣ መዝናኛዎችን፣ ስታዲየሞችን፣ ትምህርት ቤቶችንና መሥሪያ ቤቶችን መዝጋት፣ የሰው ክምችትን መቀነስ፣ ከየቤት ሆናችሁ ሥራችሁን ሥሩ/ተገበያዩ፣ ወዘተ. በሚል መመርያ ውስጥ መኖር በተዘዋዋሪ ያልተዘጋጀንበትን ኮፈን የመልበስ ኑሮና እየፀዱ የመግባትና የመውጣት ሥርዓትን የሚተካ ዘዴ መሆኑ ነው፡፡

ሰው በየቤት ተከትቶ ሁሉን ሊሠራ አይችልም፡፡ መሥሪያ ቤቶችን መዝጋትና የሠራተኛ ክምችትን መቀነስ ከኑሮ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያጎድለው ይኖራል፡፡ ባለንበት የዘመኑ የኑሮ ሥርዓት ውስጥ ሥራ ዘግቶ ሠራተኛ ቀንሶ ደመወዝ እየከፈሉ መኖር አይቻልምና የሥራ ቦታዎች መዘጋት፣ የምርትና የአገልግሎት እጥረትንና የሥራ የለሽነትን (የገቢ የለሽነትን) ችግር ማንተርከኩ አይቀርም፡፡ በአሜሪካ  በሚያዚያ ግድም (2012) የታየው በአንድ ወር 20 ሚሊዮን አካባቢ ሥራ የለሽነት መፈጠር ከፍጥነቱና ከግዝፈቱ ብዙ አገሮችን ቢያዳርስ፣ ዓለማዊ ሥርዓቱን ከመፈንዳት የሚያግደው ነገር አይኖርም፡፡ አሁንም ሲባል እንደተሰማው፣ የገቢ የለሾች ቁጥር ሦስት መቶ ሚሊዮን ተኩል አካባቢ መድረሱ አስፈሪ ነው፡፡ 

3 እስረኝነትና ነፃነት

የሰው ልጅ መረን የወጣ አኗኗሩን ለከት ሊያበጅለት እንደሚገባ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ የሕዝብ ቁጥርን መመጠን የኃይል አጠቃቀምን ጤናማ ማድረግ እንደሚገባው የግል ቤቶች፣ ደሴት አከል የግል መሬት ይዞታዎች፣ የግል መኪኖች፣ ወዘተ. የሚባሉ ነገሮች ሁሉ ብዙ ሰዎችን በሚያስተናግዱ ሥርዓቶች ውስጥ መግባት የሚያሻቸው መሆኑ ከታወቀ ቆይቷል፡፡ በሌላ ጎን በሰው ልጅ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ ውስጥ የዲጂታዊ ጥበብ ዕርምጃ፣ ዘመነ ኮተታምነትን አሰናብቶ ወደ ዘመነ ቅልጥፍና እያስገባ ነው፡፡ ይህ ሽግግር ከአድካሚ የሥራ መሣሪያዎች ጋር ትግል ያለባቸውን ሥራዎች፣ አደባባይ ድረስ የሚያስኬዱ የትምህርት፣ የሕክምና፣ የፖስታ ግንኙነቶችን፣ የባንክ ሥራንና የሱቃሱቅ ግብይትን ሁሉ አሮጌና ኋላቀር ወደ ማድረግ እየወሰደ ይገኛል፡፡  በሥራ ሥፍራና በመኖሪያ ቤት ያሉ የኑሮ ቁሳቁሶች በመረብ ተያይዘው የሥራ ኃላፊነትን ተቀባይና ፈጻሚ እየሆኑ ነው፡፡ በሰፊ መሬት ላይ የሚካሄድ የግብርና ሥራን አሮጌ የሚያደርጉ የምግብ እጥረትን የሚያስወግዱ የመረታ ቴክኖሎጂዎች መፈልሰፋቸውን ቀጥለዋል፡፡ ማነቆዎች ከተቃለሉ ገና ብዙ ምርጥ ቴክኖሎጂዎች ይፈልቃሉ፡፡ እነዚህን መሰሎች ሥር ነቀል ቴክኖሎጂዎች ስግብግብነትንና ሰቀቀን የሚረቱ፣ በኮተታ ኮተታም አኗኗር ምድሪቱ ላይ የተፈጠረውን መጣበብ የሚጠርጉ ናቸው፡፡ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ ከደቂቅ እስከ ግዙፍ ደረጃ መትባት ደግሞ፣ ሰውን ከአታካች ሥራ አውጥቶ ለምርምርና ለፈጠራ ነፃ የሚያደርግ ነው፡፡ በዚህም ጉዞው የፍዳ አስቆጣሪ ሥራን ወደ መቃብር መውረጃ ጊዜን እያቀረበ፣ ሥራ ከማወቅ ጉጉትና ከመመራመር ፍቅር ጋር የሚጋባበትን የታላቅ ሥልጣኔና የነፃነትን ዘመን እየጠራ ነው፡፡

በአሁኑ ደረጃም ቢሆን ዕቃ ለመላክ ግድ ፖስታ ቤት አለመሄድ፣ ወደ ገበያ ሳይኳትኑ የፈለጉትን መግዛት፣ ወደ ትምህርት ቤት ግቢ ለመምጣት ሳይገደዱ ትምህርትን ለመማር መቻል ነፃነት ነው፡፡ ምርጫ ጣቢያ ድረስ መሄድ ሳያስፈልግ በያሉበት በማይታማ አኳኋን ድምፅ መስጠት መቻል፣ በአዳራሽ መታጎር ሳያስፈልግ ከአገር አገር ተራርቆ ስብሰባ ለመቀመጥና ለመወያየት መቻል ነፃነትን ማስፋት ነው፡፡ በኮቪድ-19 እና እሱን በመሰለ ጉልበተኛ ወረርሽኝ እየራዱ ቤት ተዘግቶ መዋል፣ ከውጭ ወደ አገር ሲገቡ ለተወሰኑ ቀናት ተገልሎ ለመቆየት መገደድ፣ ግድ ሆኖ ከመነካካት፣ ተሰባስቦ ከመኖር፣ ከመዝናናትና ከመጨዋት ወይም ተሰባስቦ ውድድርን ከማየት መገደብ እስረኝነት ነው፡፡ እንዲህ ያለው እስረኝነት ቀደም ብሎ የተጠቆመውን ኮፈን ለባሽነት ብቻ ሳይሆን፣ ተነጣጥሎ መኖርንና ለብቻ መጓጓዝን ሁሉ ይጠራል፡፡ የግለሰብን ደኅንነት ከኮቪድ-19 ዓይነቱ ተዛማች በሽታ ጥቃት ለመጠበቅ በሚስማማ አኳኋን የሰው ልጅ አኗኗሩን ከመኖሪያ እስከ መጓጓዣ የተነጣጠለ ላድርግ ቢል እስረኝነትን ማፅደቅና የባሰ፣ ምድርን የሚያጣብብ ኮተታም ኑሮ ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር ዛሬ የሰው ልጅ የኑሮ ማነቆዎቹን ፈትቶ ህልውናን ነፃነት በማቀዳጀት ወይም ለእስረኝነት ተሸንፎና እስረኝነትን በቴክኖሎጂ አጊጦ፣ በአደጋዎች ሞርሳ ውስጥ የመኖር አጣብቂኝ ውስጥ ይገኛል፡፡ የሞርሳውም ክፍተት ከጊዜ ጊዜ እየጠበበ ነው፡፡

የሳተላይት ዲጂታል መገናኛና የመረጃ ቴክኖሎጂ ሌላም ጉድ አምጥቷል፡፡ ግለሰባዊ ነፃነትና የብቻ ሚስጥር ተብለው የሚታዩ ነገሮችን (የቤት ውስጥ ሕይወት፣ የኮምፒዩተር፣ የስልክና የደብዳቤ ሚስጥሮችን) ከሕገወጥ ብርበራና ዘረፋ መጠበቅን ትርጉም የለሽ አድርጎታል፡፡ የተደረሰበት ቴክኖሎጂ የሰዎችን ስልክ ቁጥር ይዞ ማንም ሰው ባለስልክ ቁጥሮቹ የሚኖሩባቸውን ሥፍራዎች ከቤቱ ሳይወጣ በጮሌ ስልክ አማካይነት ሊያገኝ፣ የየቤታቸውን ግቢ ሁሉ አቅርቦ ሊቃኝ ያስችላል፡፡ የግለሰቦችን እንቅስቃሴ መከታተልና መሰለል በመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን፣ በኩባንያና በግለሰብም የሚቻል ሆኗል፡፡ የግለሰብ ሚስጥሮች ከግል ኮምፒዩተር እስከ መኖሪያ ቤት፣ ከመሥሪያ ቤት እስከ ባንክ ሒሳብ ድረስ በብርበራ ቴክኖሎጂ ሊሸነቆሩና ሊዘረፉ የሚችሉበት ግራ አጋቢ ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ ይህ ሌላ የነፃነት ማጣት ገጽ ነው፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የነፃነትና የደኅንነት ጥበቃ አካል መሆን የሚችለው (ከሰው ልጅ ግላዊ መብት ጋር መጋጨቱ የሚያቆመው) በዴሞክራሲም ሆነ በፀረ ዴሞክራሲ መልክ ያለውን ብዙዎች በጥቂት ጌቶች ሥር የሚገዙበትን ሥርዓት የሰው ልጅ መቀየር ከቻለ ነው፡፡ መቻል አለመቻሉ ደግሞ በአሮጌና በአዲስ ሥርዓት መካከል ያለ ትግል ነው፡፡ ዓለም በሙሉ በዚህ ትግል ውስጥ ነው፡፡

4 ግለሰብና ኅብረተሰብ

እያንዳንዱ ግለሰብ ነፃነቱ ከተጠበቀ፣ ግላዊ ይዞታውና የማደግ/የመበልፀግ መብቱ ከተጠበቀ፣ የሥራ ከፈታ (የመዋዕለ ንዋይ አፍሳሽነት)ና የንግድ አንቅሳቃሽነት መሠረት ግለሰቡ ከሆነ ኅብረተሰቡ ያድጋል ይበለፅጋል የሚል ፍልስፍና ካፒታሊስታዊው ዓለም የኖረበት ፍልስፍና ነው፡፡ ይህ ፍልስፍና፣ ዛሬም ከአፋኝ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የመውጣት ጭላንጭል ባዩ ኅብረተሰቦች ዘንድ እንደ ትኩስ የነፃነትና የሥልጣኔ አስተሳብ እፍ እፍ እየተባለ ነው፡፡ መብትን፣ ሥራን፣ ፈጠራንና ግስጋሴን ሁሉ ከግለሰብ ጋር አጣብቆ ማየት፣ ‹‹ተጨባጩ ሰው ግሰለብ ነው. . . አዕምሮ፣ እጅ፣ ፈጠራ፣ በግለሰብነት ነው የሚገኘው. .›› የሚል ግለኛ የአስተሳሰብ አቅጣጫ ሁሉ አሮጌው ካፒታሊዝም እምብርታዊ ትርታውን (ግላዊ የሀብት አግበስብሴነት ወፍጮውን) ሰውሮ፣ የኅብረተሰብ ኑሮ መዋቅር፣ የአስተሳሰብና የጉጉት ውል ያደረገበት ዘዴ ነው፡፡ በግል ይዞታ አካባችነት አፅም ላይ እየተገነባ የመጣው የርዕዮተ ዓለም፣ የፖለቲካና የሥነ ጥበብ ሥጋ ግን የካፒታሊዝምን ወፍጮ ከመጋለጥ አላዳነውም፡፡

የዓለማችን ግለኛ ካፒታሊስታዊ ግስጋሴ በየትኛውም ዓለም ሲታይ እንደኖረው በድፍኑ ጥቅል የኑሮ መሻሻልን ቢያመጣም፣ ውስጣዊ ይዘቱ የጥቂቶች የሀብት አካባችነትና የብዙዎች መራገፍ ቅንብር መሆኑ የማይደበቅ ሆኗል፡፡ ከምንጊዜውም በበለጠ የዛሬዎቹ ዓለምን አዳርሴ የሆኑት ብሔርና አገር የለሽ ጥቂት ኩባንያዎችና ቢሊየነር ግለሰቦች የዓለም ሀብትን ጠቅልለው የያዙበት እውነታ፣ የዚህን ሥርዓት ኢፍትሐዊ እርግብግቢት ወለል አድርጎ አውጥቷል፡፡

የኮቪድ-19 ወረርሽኝም መጥቶ በከፍተኛ ደረጃ ያጋለጠው ይህንኑ እርግብግቢት ነው፡፡ ኮቪድ-19ን ከእንስሳት ወደ ሰው አስተላልፎ ለወረርሽኝ የሰጠን አይሠሩ የሚያሠራው ትርፍ አሳዳጅነት ነው፡፡ በሁለት ሦስት ወራት ውስጥ ሚሊዮኖችን ገቢ የለሽና እርጥባን ፈላጊ ያደረገው የሥርዓቱ ኢፍትሐዊነት ነው፡፡ የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ተስፋፍተው ድህነትን እንዳይጠራርጉ ገትሮ የያዘውም ያው ዓለምን የተቆጣጠረው ግላዊ የሀብትና የትርፍ አግበስባሽነት ነው፡፡ ዓለምን ብክለት በብክለት ያደረገውና ከዚያ መውጣትን የሚተናነቀው እሱው ነው፡፡ ጅምላ ጨራሽ የጦር መሣሪዎችን ዓይነት ባይነት ያመጣውም የሰው ልጅን ደኅንነት የመንከባክብ ፍላጎት ሳይሆን፣ የግል ቱጃርነትን የመንከባከብ ጉዳይ ነው፡፡ በኃያላን አገሮች መካከል የሚካሄደው ግብግብ ዞሮ ዞሮ መነሻና መድረሻው ግለኛ የሀብት አጋባሽነትን መጠበቅና ተሻሚዎችን አሸንፎ መስፋፋት ነው፡፡

ይህንን ሰውን በግለኛ አግበስብሴነቱና ስስቱ ሊያጠፋ የደረሰ ሥርዓት፣ የግል መብትን ዋልታው ባደረገ ዕይታ ውስጥ ሆኖ ማስተካከል አይቻልም፡፡ ከግለሰብ አልፎ መላ የሰው ልጅን መላ ምድሪቱን ማየት ግድ ይላል፡፡ እንኳን የዓለም ሥርዓትን ፍትሐዊና ጤናማ ማድረግ ይቅርና ወረርሽኝን እንኳ በግል መብትና እንቅስቃሴ ዕይታ ውስጥ ሆኖ መርታት እንደማይቻል ነው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያሳየው፡፡ ‹‹ግለሰቡ ራሱን ከኮሮና ቫይረስ ከጠበቀና ካዳነ መላ ኅብረተሰቡም ይጠበቃል ይድናል. . . እያንዳንዳችን ራሳችንን ከወደድን መላውን ኅብረተሰብም እንወዳለን፤›› እያልን ስብከት በየሚዲያ እያንቆረቆርን የግለሰብ መብት “አክባሪ” ሆነን በግለሰብ መብትና ነፃነት ውስጥ ግለሰቦች ኮሮናን እንዲረቱ እንሞክር ብንል፣ መካሪዎቹ ወደ ሐኪም ቤት ወይም ወደ እስር ቤት መግባት ይገባናል፡፡

ከኮሮና ወረርሽኝ የመትረፍ ትግል፣ ባጠቃላይ የሰውን ልጅ ወርሽኙን በመከላከልም ሆነ መድኃኒት በመፈለግ ተግባር ተባብሮ እንዲሠራ ነው ግድ ያለው፡፡ ከአንድ አገር ወደ ሌላ አገር የሚገባን ሰው ቢወድም ባይወድም 14 ቀናት ያህል ለይቶ ማቆየትና መመርመር ግዴታ የሆነው፣ እያንዳንዱ ግለሰብ ወደደም ጠላ በየቤቱ ተዘግቶ እንዲቆይ እስከ ማድረግና በግል መኪናው ውስጥ የሚኖረውን ተሳፋሪ እስከ መቀነስና ሲጣስ እስከ መቅጣት ያደረሰው፣ ከሁሉም በላይ ሰዎችን እንደ ኅብረተሰብ የማትረፍ ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ ህልውናና ደኅንነት በግለሰባዊ መብት መነጽር ውስጥ የሚሟላ ሳይሆን፣ የተገላቢጦሽ የግለሰቦች ደኅንነትና መብት በአጠቃላይ የሰው ልጅ ደኅንነትና ህልውና ውስጥ የሚሟላ መሆኑን (ግለሰባዊነት አልፋና ኦሜጋ፣ የሁሉ ነገር መክፈቻና መዝጊያ እንዳልሆነ) መላ ዓለም እንዲያስተውል ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓይን በልጥጧል፡፡ ዓለም ወደደም ጠላም ዛሬ መላ የሰው ልጅንና ምድሪቱን በማትረፍ ውስጥ አገሮችንና ግለሰቦችን እንድናስብ ግድ ብሏል፡፡

5 ዓለም መለወጥ እንዳለበት አያከራክርም

ለውጡ ግን እያንዳንዱ አገር ራሱን አጥር ውስጥ በማስገባት አይጨበጥም፡፡ የሰው ልጅ ሕይወት ዛሬ ካለዓለም አቀፍ መስተጋብር መኖር አይችልም፡፡ የኮቪድ-19 ዓይነቱ ዓለምን ያደረሰ ጥቃትም መነሾና መፍትሔ ዓለም አቀፋዊ መስተጋብር ነው፡፡ የለውጡን ዒላማ በትክክል ለይተን ማነጣጠር የምንችለው ዛሬ የምንገኝበት ዓብይ ችግር የመላ ሰው ልጅንና የምድሪቱን ህልውናን የሚመለከት መሆኑን፣ ይህም በመሠረቱ በዓለም ደረጃ ተባብሮ መንቀሳቀስን የሚጠይቅ መሆኑን ስንረዳ፣ ብሎም በዚሁ ዓላማዊ ተልዕኮ ውስጥ በየአኅጉር፣ በየቀጣናና በየአገሩ ያለንን ትልምና እንቅስቃሴ ስንቀይስ ነው፡፡ በዚህ ዕይታ ውስጥ ስናስብ ዓለማችን ላይ መዛባትን የሚያደርሱ ግንኙነቶችን፣ ድርጊቶችንና አሽቅድምድሞችን ሁሉ ወደ መቃውም እንደርሳለን፣ እንዲታረሙም መላ ማሰብ እንጀምራለን፡፡ በዚህ አቅጣጫ ዓለም ዛሬ ቢያንስ በኅብረተሰብ ዘንድ ያለ ገጣጣ የልማትና የኑሮ ተዛነፍንና የምድር ሚዛንን የሚያሻሽል ማቃኛ ካላደረገች፣ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ቀውሶችና “የተፈጥሮ” ግዙፍ ጥፋቶችና ቅጣቶች የሚያቀጣጥሉት በትርምስ የቀለመ ሰደዳዊ የለውጥ ማዕበል ድንገት ሊያጥለቀልቃት ይችል ይሆናል፡፡

ዓለም የሚያሻትን ለውጥ በቀላል አማርኛ “ሁሉን አቀፍ አረንጓዴ ሥልጣኔ” ብለን ልናስቀምጠው እንችላለን፡፡ ይህንን በአጭሩ ብናፍታታው ደግሞ ሁሉን አቀፍ አረንጓዴ ልማት፣ ሁሉን አቀፍ አረንጓዴ ኢኮኖሚ፣ አረንጓዴ ፖለቲካና ኑሮ (ድህነት የተሸነፈበት፣ ጦርነትና አውዳሚነት የተሸነፈበት፣ አለመግባባቶች በሰላም የሚፈቱበት፣ የነፃነት የእኩልነትና የትግግዝ ግንኙነቶች ሁለንተናዊ የሆኑበት ዓለምን የማደራጀት ጉዞ) ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ እስካለ ድረስ፣ ዓለም ይህን ጉዞ ልታመልጠው አትችልም፡፡ ግን ጉዞው ብዙ ማጓራት፣ መፈጥፈጥና ቅጣቶች ያሉበት መሆኑ አይቀርም፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በሕይወት ቀጠፋ፣ በኢኮኖሚ መኮማተርና ሥራ የለሽነትን በማባዛት ያደረሰው ጉዳት የቅጣቶች አንዱ መታያ ነው፡፡ በልዕለ ኃያላን መሀል የሚካሄደው ፈርጀ ብዙ ግብግብ የሚያስከፍለውን አስከፍሎ የሚያልፍ ነው፡፡ ሰው ግን ወደ በጎ ለውጥ መጓዙ አይቀርም፡፡ አፍን ሞልቶ ይህንን ተስፋ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚያበቁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ዓለም ዛሬ አዲስ ለውጥ ያረገዘች ነፍሰ ጡር ነች፡፡

በትርፍ የታወረው የካፒታሊስት ሥርዓተ ኑሮ ከምድር ሚዛንና ከሰው ልጅ ደኅንነት ጋር የፈጠረው ግጭት፣ “ተፈጥሮ” ገብ አደጋዎችና ማኅበራዊ ቀውሶች አምራችነቱ ከመቼውም ይበልጥ ከፍቷል፡፡

የአረንጓዴ ቴክኖሎጂዎች ምርምሮችና የፈጠራ ፍሬዎች በመላ ዓለም ለማሠራጨት የካፒታሊስት ትርፍ አሳዳጅነት ቧንቧ ጠቧቸዋል፡፡ ከዚያ ማነቆ መውጣት ይሻሉ፡፡ የቴክኖሎጂዎች በግል አዕምሮ ሀብትነትና በትርፍ ማፍሪያነት መጠበቃቸው፣ ከመላ የሰው ልጅ የኑሮ ደህንነት ጋር ያለው ቅራኔ፣ ረዥም ዕድሜ ባለው ዑደታዊ ድህነት ሲጋለጥ ቢኖርም፣ አሁን በኮሮና ወረርሽኝ አማካይነት ፍጥጫ ውስጥ ገብቷል (የተወሰኑ አገሮች ለኮሮና ወረርሽኝ መድሃኒትና ክትባት ሲገኝ በጋራ ለመጠቀም ተሰማሙ መባሉ ይህንን ቅራኔ የመፍታት ጅምርማሪ ጥረት ነው)፡፡

አሜሪካና አውሮፓ ሲመሩት የቆየው በግል ይዞታና አትራፊነት ላይ የተመሠረተው ካፒታሊስታዊ ሥርዓት ስላዘለው ጭካኔ ሲነሳ፣ “ህልም የሚጨበጥባት” እየተባለች ስትሞገስ የኖረችውን አሜሪካንና የምዕራብ ልግስናን አስበው የሥርዓቱን ጭካኔ ማስተዋል የሚጎረብጣቸው ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን የሥርዓቱ የጭካኔ ቀንዶች ላዕላዊውን የልግስናና የምፅዋት ገላ ከሥር እየተዘነጣጠሉ ከእነ ጉዳታቸው ማግጠጥ ከጀመሩ ከራርሟል፡፡ የአፍጋኒስታን፣ የኢራቅ፣ የሊቢያ፣ የየመንና የሶርያ መንኮታኮት የዚሁ መታያ ነው፡፡ እስራኤል ዛሬ ኃፍረት ያጣውን የአሜሪካ አድሎኝነት ተገን አድርጋ ፍልስጤሞች ላይ የምትፈጽመው መኖሪያ የማሳጣት ግፍ ሌላ አብነት ነው፡፡ በጣት በሚቆጠሩ አገሮች ባሉ ኩባንያዎችና ግለሰብ ዲታዎች እጅ የተሰባሰው የዓለም ሀብት የንፁህ ሥራ ውጤት ነው ወይ? ብሎ በአፍሪካውያን ላይ የተካሄደውን የባርነት ንግድንና የጉልበት ግጦሽ ታሪክ፣ ቅኝ ገዥነትን፣ ጦርነቶችንና የጦር መሣሪያ ችብቸባንና እስከ ዛሬ ያሉ የአድሎኛ ንግድና የካፒታል አዋዋል ጥበቦችን የመረመረ ሰው ትክክለኛውን ሥዕል ማግኘት አይቸግረውም፡፡

በአውሮፓውያን ሰፋሪነትና አቅኝነት የተደራጀችው ሰሜን አሜሪካ በተለይ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ አፍሪካውያንን በባርነት እያጋዙ ጉልበታቸውን ከንጋት እስከ ሌት ከማሳ እስከ ማጀት በመምጠጥ (በስተኋላም እስያዊያንም በነፃ ቀረሽ ምዝበራ ታክለዋል)፣ ለደረሰችበት ብልፅግናና ሥልጣኔ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ የጥቁሮችን ባለውለታነት በፍትሐዊና በእኩልነት አያያዝ ማክበርና ማመሥገን አልቻለችም፡፡ የነጭ ዘረኝነት እስከ ዛሬ ድረስ ጥቁሮችን በልዩ ልዩ ሥልቶች ወደ ርጋጭ ኑሮ ከመድፈቅ አልተላቀቀም፡፡ በአሜሪካ ሚኒያፖሊስ በፖሊስ ግፈኛ አያያዝ ትንፋሽ አጥቶ በሞተው ጆርጅ ፍሎይድ መነሾነት የተቀጣጠለው ኮሮና ወረርሽኝን የተዳፈረ ፀረ ዘረኝነት ቁጣ፣ ከዚህ በፊትና ዛሬም በሰሜንና በደቡብ አሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ነጭ ዘረኝነት ውስጥ የህልውና ትንፋሻቸው ተሰንጎ ሲቃትቱ ያለፉትንና አሁንም የሚቃትቱን ሁሉ የሚወክል ነው፡፡ ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰረገላና ዘረኝነትን እንቢ ባሉ ታጋዮች አጅብ ተሞሽሮ ቴክሳስ ሂውስተን ያረፈው የፍሎይድ አስከሬን፣ የዘርና የቀለም አድሎ ድል የሚመታበት ቀን እየቀረበ መሆኑንም ያስተጋባ ነበር፡፡ ለመላ ዓለም የመብት ተቆርቋሪ ነኝ ባዩ የአሜሪካ ቆዳዊ ዝናም ሬሳው ወጥቶ፣ ያለ ኃፍረት መከለያ ከፈን ወደ መቃብር የወረደውም ያን ቀን  ነበር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...