Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠው የጥሬ ገንዘብ ገደብ የማይመለከታቸው ዘርፎች ተለይተው እንዲስተናገዱ ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቅርቡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በወጣው መመርያ መሠረት ልክ አልባ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲገደብ በማድረግ የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴን ለመቀነስ የሚያስችል አሠራር እየተተገበረ ይገኛል፡፡

መመርያው ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ ባንኮች ያጋጠማቸው የገንዘብ እጥረት እየተቃለለ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በዚህ መመርያ መሠረት በየዕለቱ ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች ከተቀመጠላቸው ገደብ በላይ በጥሬ ገንዘብ ለማውጣት የሚያስገድዳቸው ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ፣ የሥራ ባህሪያቸው መመርያውን ለመከተል አስቸጋሪ የሚያደርግባቸው መስኮች እንዴት ይስተናገዳሉ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አልቀረም፡፡ እነዚህን ጥያቄዎች ለማስተናገድ የሚያስችል ዝርዝር አሠራር በመመርያው አልተቀመጠም የሚል ጥያቄም እየቀረበ ነው፡፡

ክልከላ ያስቀመጠው መመርያ ወደ ትግበራ ሲገባ፣ እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች ጎልተው እየታዩ በመምጣታቸው፣ የኢትዮጵያ ባንኮች መሠረት መመርያው ለሁሉም በሚስማማ መንገድ በአግባቡ እንዲተገበር የሚያስችሉ ማሻሻያዎችን ለብሔራዊ ባንክ አቅርቧል፡፡

የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ላይ ወሰን የሚጥለው መመርያ ስለመውጣቱ ማብራሪያ የሰጡት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር)፣ ከሥራ ባህሪያቸው አኳያ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ ለመፈጸም የሚገደዱ ኩባንያዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ አስታውሰው፣ እንዴት ይስተናገዱ? የሚለው በልዩ ሁኔታ ሊታይ እንደሚችል አስታውቀው ነበር፡፡

በመመርያው ከተቀመጠው ገደብ በላይ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ የሚገደዱ ተቋማት ጉዳያቸው ታይቶ በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ የሚደረግበት አሠራር ይዘረጋል መባሉ ብቻም ሳይሆን፣ ይህንን የማስፈጸም ኃላፊነት ለየባንኮቹ ፕሬዚዳንቶች እንደተሰጣቸው ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ከመመርያው ውጭ የሚስተናገዱ ክፍያዎች የትኞቹ ዘርፎች ናቸው የሚለው ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በዚህ መነሻነት በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱትና ከተቀመጠው ገደብ በላይ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚችሉት ዘርፎችና ተቋማትን ጉዳይ ለማጥራት ባንኮች በማኅበራቸው በኩል ሲመክሩበት እንደቆዩ ታውቋል፡፡ ይበጃል ያሉትን ሐሳብም ለብሔራዊ ባንክ እንዳሳወቁ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በልዩ ሁኔታ መስተናገድ አለባቸው የተባሉትን ተቋማት በመለየት በዚሁ መሠረት ተመሳሳይ የሆነ አሠራር እንዲዘረጋ በማሰብ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ሐሳብ፣ ኃላፊነትን በአግባቡ ለመወጣት ያስችላል የሚል እምነት እንዳሳደረ ከባንኮች ማኅበር የተገኘው መረጃ ይጠቅሳል፡፡

ማኅበሩ ወጥነት ያለው አሠራር ብሎም ከተቀመጠው ገደብ በላይ ገንዘብ በጥሬ ወጪ ማድረግ እንዲችሉ የሚፈቀድላቸው ዘርፎችና ተቋማት ተለይተው ከተቀመጡ፣ ሊፈጠር የሚችል ችግር እንዳይኖር ያግዛል በማለት ብሔራዊ ባንክ ውሳኔ እንዲሰጥበት ቀርቦለታል፡፡  

በዚሁ መሠረት ይህ ገደቡ ሳይመለከታቸው በየዕለቱ ከተፈቀደው የጥሬ ገንዘብ ገደብ በላይ ከባንኮች ወጪ ሊያደርጉ ይችላሉ የተባሉት ዘርፎችና ተቋማት ተለይተው ለብሔራዊ ባንክ እንደተላኩና ማኅበሩም በዝርዝር እንዳቀረበ መረጃዎች ይጠቅሳሉ፡፡

ከእነዚህ ተቋማት ውስጥ ለተለያዩ የመከላከያ ኃይል ጦር ክፍሎች የሚከፈል ደመወዝ አንዱ ነው፡፡ ጦሩ የሚገኝባቸው አካባቢዎች ከከተማና ከባንክ ራቅ ያሉ በመሆናቸው፣ ለጦሩ አባላት የደመወዝ ክፍያ ለመፈጸም የሚፈለገው ገንዘብ ከተቀመጠው የጥሬ ገንዘብ ገደብ በላይ እንደሚሆን በመታሰቡ፣ መመርያው የመከላከያ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር ከገደብ ውጪ እንዲስተናገድ የሚል ጥያቄ ለብሔራዊ ባንክ  ቀርቦለታል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተመሳሳይ ሊታይ እንደሚገባውና በልዩ ሁኔታ በቀጥታ እንዲስተናገዱ ከተባሉት ዘርፎች ውስጥ እንዲካተት መደረጉ ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም በርካታ የግንባታ ሥራዎች ከከተማ ውጭ፣ በተራራቁ ቦታዎች የሚካሄዱ በመሆናቸው፣ በየዕለቱ ወይም በየሳምንቱ ደመወዝ የሚከፍሉ በመሆናቸው ጭምር፣ ሠራተኞቻቸውም በአቅራቢያቸው እንደ ልብ የሚገኝ ባንክ ባለመኖሩ ወደ ባንክ በመሄድ ክፍያቸውን ለማግኘት እንደሚቸገሩ ይታያል፡፡ በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ በጥሬ ገንዘብ እንዲያንቀሳቅሱ ሊደቀድላቸው ይገባል ተብለው ከተለዩት ዘርፎች ውስጥ የኮንስትራከሽን ዘርፉ እንዲካተት መደረጉ ተቅሷል፡፡

እንደ አበባና ተመሳሳይ የእርሻ ኢንቨስትመንቶችም ጉዳይ ሊታይ ይገባል ከተባሉ ዘርፎች ውስጥ ተጠቃሽ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ እነዚህም ዘርፎች ከዓመታዊ ወጪያቸው አንፃር ታሳቢ የሚያደርግ አሠራር ያስፈልጋቸዋል ተብሏል፡፡ ከገንዘብ አውጥተው ራቅ ወዳለ ቦታ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱ እንደ ማክሮ ፋይናንስ ያሉ ተቋማትም ጉዳይ በተመሳሳይ እንዲታይ ማኅበሩ ባቀረበው ፕሮፖዛል ላይ የጠቀሰ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ኤክስፖርት የሚያደርጉና ምርቶችን በተለያዩ ወቅቶች ወደ ገጠር በመሄድ የሚያሰባስቡበት ወቅት ስላለ ይህንን ጠንካራ ሥራ በሚያከናውኑበት ወቅት ጥሬ ገንዘብ መያዝ ስላለባቸው የነዚህም ጉዳይ እንዲታይ በፕሮፖዛላቸው ላይ ቀርቧል፡፡

አንዳንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጀቶችና ሌሎች ዘርፎችም በተመሳሳይ አተገባበሩ ወጥነት እንዲኖር ለማድረግ ሲሆን፣ መመርያውን የሚለው ተለይቶ ብሔራዊ ባንክ ይህንኑ ለይቶ የሚያስቀምጥ ይሁን የሚል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ዘርፎችን በመለየት እንዲሁም የትኛው ዘርፍ ልዩ ፈቃድ ማግኘት አለበት በማለት ተለይቶ እንዳበቃ ብሔራዊ ባንክ እንዲያሳውቃቸውም አመልክተዋል፡፡ እንዲህ ባለ መልኩ ተለይቶ መቅረቡ የባንክ ፕሬዚዳንት ለውሳኔ የሚያስቸግራቸው ይሆናል ተብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ባወጣው መመርያ በጥሬ ገንዘብ ዝውውርን ለመገደብ ባወጣው መመርያ መሠረት ግለሰቦች በቀን በጥሬ ገንዘብ ማንቀሳቀስ የሚችሉት 200 ሺሕ ብር ሲሆን፣ በወር ከአንድ ሚሊዮን ብር ያልበለጠ እንዲሆን እንዲሁም ኩባንያዎች በቀን 300 ሺሕ ብር በወር 2.5 ሚሊዮን ብር በጥሬ ገንዘብ ማውጣት እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ መጠን በላይ ለማንቀሳስ ግን ሌሎች ዘመናዊ የገንዘብ ማንቀሳቀሳ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የሚል መሆኑ አይዘነጋም፡፡

የዚህን መመርያ መውጣት ማኅበሩ የሚደግፈውና እንደውም የዘገየ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ የመመርያው መተግበር ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ከማጎልበትም በላይ ሕገወጥነትን ለመከላከል ጠቀሜታውን በተለያዩ መንገዶች ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች