Thursday, December 7, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የኢትዮጵያውያን የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ይከበሩ!

በዚህ ምድር ምንም ቋሚ ነገር ባይኖርም የሰው ልጆች በትውልድ ጅረት ሲቀያየሩ አንዱ ለመጪው የሚሆን ሲገነባ፣ ለራሱ የሚሆነውን ደግሞ ከቀድሞው ይቀበላል፡፡ ቀዳሚውና ተከታዩ ትናንት፣ ዛሬና ነገ በሚባሉ ዑደቶች ውስጥ እያለፉ ዘመኑ እንደ ደረሰበት የዕድገት ደረጃ የሚፈለግባቸውን ይወጣሉ፡፡ በዓለም ላይ ተነስተው የወደቁ ትልልቅ መንግሥታትም ሆኑ ሥርዓቶቻቸው፣ ቁሳዊ ቅርሶችንና ታሪካዊ መዛግብትን ትተው ከማለፍ ውጪ ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ አንዱ ያፀና የመሰለውን አንዱ እያሻረ ወይም በሌላ እየቀየረ ነው፣ የዓለም ገጽታ እየተለዋወጠ እዚህ የተደረሰው፡፡ ለአንድ ሥርዓት ወይም ትውልድ ያገለገሉ ሕጎች፣ ልማዶች፣ ባህሎች፣ የኑሮ ዘይቤዎችና መስተጋብሮች በቋሚነት መቀጠል ባይችሉም፣ መጪው ትውልድ ግን በላያቸው ላይ የተሻለ ነገር ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም የዘመኑ ሰው ለራሱ የሚመቸውን ያደላድላልና፡፡ የትናንት አሳሪ የዛሬ ታሳሪ፣ የትናንት ጉልበተኛ የዛሬ ደካማ፣ የትናንት ፈራጅ የዛሬ ፍርደኛ መሆንም በዚህ ዓለም ምንም ቋሚ ነገር እንደሌለ አመላካች ናቸው፡፡ በነበሩት ላይ እየጨመሩ ወይም አዲስ ነገር እየፈጠሩ ሕይወት ይቀጥላል፡፡ በዚህም መሠረት ሰዎች ኑሮአቸውን በአግባቡ ለመምራትና እርስ በርስ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች፣ በሥርዓት ለመኖር የሚያስችላቸው ሕግና ዳኝነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ ከበፊቱ ደህናውን በመውሰድ የማያስፈልገውን በመተው ማለት ነው፡፡ ከመደበኛው የዳኝነት ሥርዓት በተጨማሪ፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓት በብዙ አገሮች ይታወቃል፡፡ ፖሊስ፣ ዓቃቤ ሕግና ዳኛ ዘንድ በመሄድ ችሎቶችን ከማጣበብ፣ ወይም ፍትሕና ርትዕ በተሻለ መንገድ ለማግኘት በዚህ ሥርዓት መዳኘትን ፍቱን ነው የሚሉ አሉ፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ ጤናማ ግንኙነት ለመፍጠር ጠቃሚ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች የሚያስፈልጉት በእርስ በርስ ግንኙነት ጭምር መረዳዳትንና መተሳሰብን ለማጎልበት ነው፡፡ ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላው ለመሸጋገርም ያገለግላሉ፡፡ ዓለም እዚህ የደረሰችው የቀድሞው ለአዲሱ እያቀበለ በሚከናወን ሽግግር ነውና፡፡

ኢትዮጵያዊያን ከሚታወቁባቸው ነባርና አስደናቂ እሴቶቻቸው መካከል አንዱ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ በባህላዊ የሽምግልና ሥርዓት ገንዘብ ከተካካዱ ጀምሮ እስከ በደም የሚፈላለጉ ድረስ ይዳኙበታል፡፡ በየአካባቢው ስመ ጥር የሆኑ አዛውንቶች፣ የእምነትና የማኅበረሰብ መሪዎች በብልኃትና በአስተዋይነት ጉዳዮችን መርምረው ፍትሕ ስለሚያሰፍኑ ተቀባይነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በመላ አገሪቱ ባህላዊ ሽምግልና የተከበረ ሲሆን፣ በርካታ ለግጭትና ለውድመት የሚዳርጉ ችግሮች መፍትሔ ይገኝላቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባና በሌሎች ትልልቅ ከተሞች ጭምር በንግድ ሥራም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች በግለሰቦች መካከል አለመስማማት ሲፈጠር፣ ወደ ፍርድ ቤት ከመሄድ ይልቅ ያጋጠሙ ችግሮች የሚፈተቱት በዚህ አኩሪ የሽምግልና ሥርዓት ነው፡፡ በማኅበረሰቡ አንቱታ የተቸራቸው የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ሰዎች የተበደለ እንዲካስና በዳይ ደግሞ ጥፋቱን አምኖ እንዲቀጣ በማድረግ ረገድ እምነት የሚጣልባቸው ስለሆኑ፣ ያለ አድልኦና መድልኦ ፍትሕ ለማስፈን ያግዛሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በፖለቲከኞችና በጉልበተኞች እየተሸነገሉ ወይም እየተገደዱ ችግር የሚፈጥሩ ቢያጋጥሙም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሽምግልና የሚሰጠው ክብርና እምነት ላቅ ያለ ቦታ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በርካታ ግጭቶችን በማርገብና ዘላቂ መፍትሔ በማፈላለግ ያለው ሚና አሁንም ቢሆን ከፍተኛ እንደሆነ ነው ያለው፡፡

ኢትዮጵያ ይህንን የመሰለ ምሥጉንና ታላቅ እሴት ቢኖራትም በተለይ ክፋት በተጠናወታቸው ፖለቲከኞች፣ እንዳሻቸው አገር ላይ መፈንጨት በሚፈልጉ ነውጠኞችና ሥርዓተ አልበኞች የሽምግልና ሥርዓት እየተናቀ ከፍተኛ ሸፍጥ ይፈጸማል፡፡ የፍትሕ ሥርዓቱ የጉልበተኞችና የተላላኪዎቻቸው መቀለጃ ሆኖ ሕዝብ በፍትሕ ዕጦት ሲሰቃይ፣ ፍትሕ በገንዘብ እየተሸቀጠ ዜጎች በጠራራ ፀሐይ ንብረታቸው ሲዘረፍ፣ ባልፈጸሙት ወንጀል እስር ቤት ሲቆለፍባቸው፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉና ለማመን የሚቸግሩ ሥቃዮች ሲደርሱባቸው ኖረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በፍትሕ ዕጦት አቤት የሚሉ ብዙ ናቸው፡፡ ትናንት ለፍትሕና ለእኩልነት ስንታገል ነበር የሚሉ ጭምር ፍትሕን መቀለጃ አድርገው ወገን ወገኑን እንዲያሳድድ፣ እንዲዘርፍና እንዲገድል ሲያደርጉ በግላጭ ታይተዋል፡፡ አጥፊን በብሔሩ ምክንያት እንደ ንፁህ መከላከል፣ ተጠያቂነት ሲመጣ የብሔር ሰሌዳ እየለጠፉ መሟገትና ለፍትሕ መሰናክል መሆን በዚህ ዘመን ከመጠን በላይ እየተለመደ ነው፡፡ ለህሊና የሚከብድ አሰቃቂ ድርጊት ሲፈጽሙ የነበሩ ሰዎች፣ በዚህ ዓይነቱ ነውረኛ መቧደን እንደ ንፁህ ተቆጥረው ሲዘመርላቸው መስማትን የመሰለ አስከፊ ነገር የለም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር በዚህ ዓይነት ኢፍትሐዊ አስተሳሰብ ተበክሎ በመበላሸቱ፣ ባህላዊ የግጭት አፈታትና የሽምግልና ሥርዓትን ለመጠቀም ሙከራ ሲደረግ የሚሰማው ተቃርኖ ያስደነግጣል፡፡

እንደሚታወቀው የግማሽ ክፍለ ዘመኑ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ታሪክ የሚያስተምረው ደም መፋሰስን ነው፡፡ ነባሩ የሽምግልና ሥርዓት ተንቆ በምትኩ የተተካው የይዋጣልን ድንፋታ፣ በርካታ ማኅበራዊ እሴቶችን ከመገርሰስ አልፎ መጨካከንን አግንኗል፡፡ ከአገር ቤት እስከ ባህር ማዶ በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲናከሱ የነበሩ ፖለቲከኞች፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ጓዛቸውን ጠቅልለው እዚህ ቢከትሙም የያዛቸው አባዜ አለቀቃቸውም፡፡ እልህ፣ ግትርነት፣ ቂም፣ ጥላቻ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና የመሳሰሉት መርዞች ከውስጣቸው ሊወጡ አልቻሉም፡፡ ዕድሜ ልካቸውን አንድ ዓይነት ስህተት እየፈጸሙ የተለየ ውጤት መጠበቃቸው ይገርማል፡፡ በእነሱ እግር እየተተኩ ያሉ አፍለኞች ወይ ከአሳዳጊዎቻቸው ስህተት አይማሩ፣ ወይም ታሪክን አብጠርጥረው አይረዱ የተለመደውን ጥፋት እየደጋገሙ አገር ያጎሳቁላሉ፡፡ ለአገር ከፍተኛ አበርክቶ የሚኖራቸው አዛውንቶች ወደ ዳር ተገፍተው፣ ከታሪክ ለመማር ፈቃደኛ ባልሆኑ ሐኬተኞች ኢትዮጵያ እየተቸገረች ነው፡፡ ሕግ በመጣስ ሥርዓተ አልበኝነትን ማንገሥና አገር በመበጥበጥ ትርምስ መፍጠር የሚፈልጉ ነውጠኞች፣ ወጣቶች አዛውንቶችን እንዳያከብሩና የሚሉዋቸውን እንዳይሰሙ ጭምር የስም ማጥፋት ዘመቻ ያካሂዱባቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ለከፍተኛ ችግር ተጋልጣለች፡፡ አዛውንቶች የማይከበሩባት አገር እየሆነች በርካቶች ፍዳቸውን ዓይተዋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን እንደ ቅርጫ በመከፋፈል ትንንሽ አገር ለመፍጠር የሞከሩ ቅኝ ገዥዎችን ፈለግ የተከተሉ ሳይሳካላቸው ቀርተው ከመድረኩ ሲገለሉ፣ የእነሱ ወራሽ ለመሆን የሚጣጣሩ ያንኑ የማይረባ አጀንዳ እያራገቡ ሕዝብ ለማጫረስ ሴራ ሲጎነጉኑ ተስተውለዋል፡፡ ለዓላማቸው ስኬትም የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ሙከራዎቻቸው መካከል የሚጠቀሰው ከልዩነቱ ይልቅ፣ አንድነቱን አፅንቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማኅበራዊ እሴቶች ማፈራረስ ነው፡፡ እርስ በርሱ በማጋጨትና በማጋደል በጋራ የገነባቸውን ትውልድ ተሻጋሪ እሴቶቹን ለመናድ ይፈልጋሉ፡፡ ሕዝቡ ውስጥ እንዲህ ያለ በደል ሲፈጸም ተስፋ መቁረጥ፣ ራስን መጥላትና እንዳሻው ይሁን የሚባሉ ግዴለሽነቶች እየተፈጠሩ፣ አገር የማያባራ ግጭት ውስጥ እንድትገባ ይደረጋል፡፡ እብሪትና አጉል ጀብደኝነትን ስንቅ አድርገው የተነሱ ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኞች፣ ለዘመናት የተገነቡ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶችን እየናዱ አገርን መቀመቅ የሚከቱ ድርጊቶች ሲፈጽሙ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከአገር የሚቀድም የለም በማለት ኢትዮጵያ የግጭት አውድማ እንዳትሆን የተነሱ ዜጎችን ማየት ያፅናናል፡፡ አዛውንቶች እኛ እያለን አገር ችግር ውስጥ መግባት የለባትም ብለው ሲነሱ፣ መደገፍና ማበረታታት አገራቸውን የሚወዱ ኢትዮጵያዊያን ተግባር መሆን አለበት፡፡ ልዩነትን ይዞ ለአገር ብሔራዊ አንድነትና ደኅንነት ሲባል እየተጀመሩ ያሉ ጥረቶችን ማገዝ የግድ መሆን አለበት፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በሚፈጠረው ችግር የጋራ ተጠያቂነት እንደሚኖር መዘንጋት አይገባም፡፡

በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንገድ መነጋገር የሚቻለው በመቀራረብ ነው፡፡ ለመቀራረብ ደግሞ አስማሚ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ከሽምግልና ሥርዓት ውጪ ሌላ መፍትሔ በቅርብ አይታይም፡፡ ከዚህ ቀደም ማንና ማን ተጣልቶ ነው ብሔራዊ ዕርቅ የሚያስፈልገው እየተባለ፣ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ብዙዎች ያስታውሳሉ፡፡ እውነታው ግን የሚያሳየው ጥልቅና ሰፊ መከፋፈል የሚስተዋልበት የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር፣ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሽምግልና ያስፈልገዋል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት ኩርፊያና ንጭንጩ ደረጃው የተለያየ ቢሆንም፣ ጦር ሰብቀው ከሚፋለሙትና ጦር ለመስበቅ ጫፍ የደረሱትን ጨምሮ ከጀርባ ሆነው እስከ የሚያሸምቁት ድረስ ሽምግልና ያሻቸዋል፡፡ ጥላቻውና ክፋቱ ከመጠን በላይ በመድረሱ ችግሮችን አፍረጥርጦ በማውጣት መሸማገል የግድ ይሆናል፡፡ ሰሞኑን እንደተስተዋለው የሽምግልና ሙከራውን ፖለቲካዊ ካባ ደርቦ ለማበላሸት ከመሞከር ይልቅ፣ ዕድሉ ተሰጥቶ የዓመታት ችግሮች ፈር የሚይዙበት መደላድል እንዲፈጠር ዕገዛ ይደረግ፡፡ እስከ አሁን ድረስ አገር የጉልበተኞች መጫወቻ የሆነችው የጋራ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶች በመናቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሆን ተብለው እንዲፈራርሱ በመደረጋቸው ጭምር ነው፡፡ አገራቸውን በከፍተኛ ፍቅርና ወኔ ያገለገሉ ኢትዮጵያዊያን ወደ ጎን እየተገፉ፣ ጉልበተኞችና ሥርዓተ አልበኞች እንዲፈነጩ በመለቀቃቸው ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በአገርና በሕዝብ ዕጣ ፈንታ ላይ መቆመር ሊያበቃ ይገባዋል፡፡ የሽምግልና ሥርዓትን የመሳሰሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ይከበሩ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...