Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናግብፅ ድርድሩ የውኃ ክፍፍል ላይ እንዲሆን አቋም በመያዟ መግባባት አለመቻሉን ኢትዮጵያ ለፀጥታው...

ግብፅ ድርድሩ የውኃ ክፍፍል ላይ እንዲሆን አቋም በመያዟ መግባባት አለመቻሉን ኢትዮጵያ ለፀጥታው ምክር ቤት አስታወቀች

ቀን:

የህዳሴ ግድቡ የውኃ ሙሌትና አስተዳደርን በተመለከተ ሦስቱ አገሮች ሲያደርጉት የነበረው ድርድር አለመቋረጡን፣ ነገር ግን ግብፅ በግድቡ ላይ የሚደረገው ድርድር የውኃ ክፍፍልን እንዲያመለክት በመጠየቋ መግባባት አለመቻሉን ኢትዮጵያ ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስታወቀች።

በኢትዮጵያ፣ በግብፅና በሱዳን መካከል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ዳግም ሲካሄድ የነበረው ድርድር በሱዳን ጥያቄ መሠረት ባለፈው ሳምንት ከተቋረጠ በኋላ፣ ግብፅ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ በኢትዮጵያ ግትር አቋም ምክንያት ድርድሩ እንደተቋረጠ አቤቱታ አቅርባለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ለተመድ የፀጥታ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ሪቬሬ ሰኞ ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ፣ ግብፅ ላቀረበችው አቤቱታ ምላሽ ሰጥተዋል።

‹‹የሦስትዮሽ ድርድሩን ፈቀቅ ማለት ያቃተውና እንደፈለግነው በፍጥነት መቋጨት ያልተቻለው፣ ግብፅ የረዥም ዘመናት ታሪካዊና አሁናዊ የውኃ ድርሻዋ እንዲከበር በማለት በያዘችው አቋም ምክንያት ነው፤›› ሲሉ የገለጹት አቶ ገዱ፣ እነዚህ የግብፅን ታሪካዊና አሁናዊ የውኃ መጠቀም መብቶች የተመለከቱ ስምምነቶች ደግሞ በቅኝ ግዛት ወቅት ግብፅና ሱዳን ብቻ ሆነው ተፋሰሱን ለብቻቸው የተከፋፈሉበት፣ በዚህ ስምምነታቸውም ኢትዮጵያ ያልተካተተችና ድርሻዋም ዜሮ መሆኑን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ይህንን ኢፍትሐዊ ስምምነት ልታከብር እንደማትችል ያስታወቁት ሚኒስትሩ፣ በዚህ ስምምነት የተጠቀሱ መብቶችን ግብፅ ዳግም መጠየቋ በራሱ ግብፅ ተፋሰሱን በተናጠል የመጠቀም ኢፍትሐዊ ፍላጎቷን በግልጽ የሚያስረዳ መሆኑን አስታውቀዋል። እየተደረገ የነበረው ድርድር የህዳሴ ግድቡን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ እንደ ግብፅ ፍላጎትና ጥያቄ የውኃ ክፍፍልን ሦስቱ አገሮች ለብቻቸው የመወሰን መብት የላቸውም ብለዋል።

ድርድሩ የውኃ ክፍፍልን የሚመለከት ቢሆን ኖሮ ሌሎቹ የተፋሰሱ አገሮችም መሳተፍ ይገባቸው እንደነበር አመልክተዋል። ነገር ግን ይህ የግብፅን አካሄድ ኢትዮጵያ የምታውቀው እንደሆነ ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ሦስቱ አገሮች የሚደራደሩት እ.ኤ.አ. በ2015 በተፈራረሙት ህዳሴ ግድቡን ብቻ የተመለከተ የትብብር መርህ መግለጫ ስምምነት መሠረት እንደሆነ አስረድተዋል።

በዚህ ስምምነት መሠረት አገሮቹ መግባባት ካልቻሉ ደግሞ ጉዳዩን ወደ መሪዎቻቸው እንደሚወስዱት፣ ወይም ሦስቱም የተስማሙበት ሦስተኛ ወገን አሸማጋይ ለመጥራት እንደሆነ ገልጸዋል። ድርድሩ ሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትሯን በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ እንዲሰጡበት በመጠየቋ ብቻ የተስተጓጎለ ቢሆንም እንዳልተቋረጠ፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ አሁንም ለእውነተኛ ድርድር ዝግጁ መሆኗን፣ በሰሞኑ ድርድርም በርካታ የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ ስምምነቶች መደረሳቸውን በማውሳት ኢትዮጵያ በእውነተኛ ድርድር አለመግባባቶችን መፍታት እንደሚቻል እንደምታምን ገልጸዋል።

ከዚህ ውጪ አኅጉራዊ አማራጮችንና ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን በማሳተፍ አለመግባባቱን መፍታት እየተቻለ፣ ግብፅ አለመግባባቱን ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ጉዳይ በማድረግና ጥቅም የማያስገኝ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ጫና ለመፍጠር ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷን አቶ ገዱ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን የምትገነባው የሕዝቦቿን ችግር ለመቅረፍ እንደሆነ፣ ይኼንንም የምታደርገው ባላት የሉዓላዊ መብት ወሰን ውስጥ እንደሆነም አቶ ገዱ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ያሉባትን ዓለም አቀፋዊ ግዴታዎች በተመለከተ አስታዋሽ እንደማያስፈልጋትም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በማንም ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስና አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያ ልዩነቶችን በድርድር ለመፍታት ዝግጁ እንደሆነች በመግለጽ፣ የፀጥታው ምክር ቤት የግብፅን አቤቱታና ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርግ አመልክተዋል።

 የህዳሴ ግድቡ በማንም ላይ ጉልህ ጉዳት የማያደርስ መሆኑ እየታወቀ ለሰላም መደፍረስ ሥጋት እንደሆነ አድርጋ ግብፅ የምትናገረው ምክር ቤቱን ለማሳሳት እንደሆነ የገለጹት አቶ ገዱ፣ በህዳሴ ግድቡ ምክንያት የሚመጣ የፀጥታ ሥጋት ካለም ግብፅ አሁን እያደረገች በምትገኘው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማና ትንኮሳ በመሆኑ ኃላፊነቱን ልትወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አቶ ገዱ ለፀጥታው ምክር ቤት የጻፉትን ደብዳቤ በተመለከተ ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ፣ ግብፅ አለመግባባቷን በውይይት ለመፍታት እንደሚቻል የምታምን መሆኑን በመግለጽ መንግሥታቸው የፀጥታውን ምክር ቤት ጣልቃ ገብነት የጠየቀው ኢትዮጵያ ግድቡን በመጪው ሐምሌ ወር መሙላት እንዳትጀምር መሆኑን ገልጸዋል።

ግብፅ የውኃ ክፍፍልን አንስታ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄም፣ የውኃ ክፍፍልን አስመልክቶ ወደፊት በሚደረግ ስምምነት ኢትዮጵያ ከዓባይ ወንዝ በተጨማሪ ያሏትን የውኃ ሀብቶች ከግምት አስገብቶ መፈጸም እንደሚገባው ተናግረዋል።

አሜሪካ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲሰበሰብ ግብፅ ያቀረበችውን ሐሳብ ብትደግፍም፣ ተመድ ግን ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን ራሳቸው እንዲፈቱ ሲል ቻይና ደግሞ አፍሪካውያን ለችግሮቻቸው መፍትሔው ራሳቸው ዘንድ እንደሆነ ማስታወቋ ተሰምቷል፡፡

የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የህዳሴ ግድቡን ውዝግብ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ፣ ሦስቱ አገሮች ልዩነቶቻቸውን በተፈራረሙት የትብብር መርህ መግለጫ ስምምነት መሠረት እንዲፈቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

በህዳሴ ግድቡና በኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን መጠቀም መብት ላይ ታጥቃ የተነሳችውን ግብፅ ድርጊት ያበሳጫቸው ኢትዮጵያዊያን፣ መንግሥት በሐምሌ ወር ግድቡን መሙላት እንዲጀምር ከማሳሰብ አልፈው ግፊት እያደረጉበት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...