አቶ ክብረት አበበ የጠብታ አምቡላንስና የጠብታ ፓራሜዲካል ኮሌጅ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ የኮሪያ ዘማች ልጅ የሆኑት አቶ ክብረት፣ በጅማ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ (ጅማ ዩኒቨርሲቲ) በነርሲንግ ሠልጥነዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአኒስቴዚያ (ሰመመን) ዲፕሎማ እንዲሁም በሶሻል ሳይንስ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን፣ በሊደርሺፕ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በሥራ ዓለም ባሌ ዞን በሚገኘው በጊኒር ሆስፒታል፣ አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በነርስነትና በሰመመን ሙያ ዘርፍ አገልግለዋል፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ በጠብታ አምቡላንስ፣ በጠብታ ፓራሜዲካል ኮሌጅና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ታደሰ ገብረ ማርያም አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ጠብታ አምቡላንስን ለማቋቋም ምን አነሳሳዎት? እንዴትስ ለማቋቋም በቁ?
አቶ ክብረት፡- ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የሰመመን ባለሙያ ሆኜ በማገልገል ላይ እያለሁ አንድ ልቡን የታመመ እንግሊዛዊ አገሩ እንዲሄድ ተፈልጎ እኔ እየተንከባከብኩት አብሬው እንድሄድ ተደረገ፡፡ እንግሊዝ አገር እንደደረሰም ሆስፒታል ያለው የድንገተኛ ሕክምና አገልግሎትና የአሠራር ቅልጥፍናቸው የያዝኩትን ሥራ ትቼ የአምቡላንስ አገልግሎት እንዳቋቁም አነሳሳኝ፡፡ ከአምስት ቀን ቆይታዬ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስኩ በደህና ጊዜ የገነባሁትን ቤቴን ሸጬ አሁን ያለውን ድርጅት ለማቋቋም በቃሁ፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው ግን ተዘርዝሮ የማያልቅ በርካታ ውስብስብ እንቅፋቶችንና ችግሮችን በዘዴና በብልሀት ተቋቁሜ በማለፌ ነው፡፡ ከችግሮችም መካከል አንደኛው የአምቡላንስ አገልግሎት ደረጃ ያልወጣለት መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ አምቡላንስና ኢመረጀንሲ ቴክኒሺያን ምን መምሰል እንዳለባቸው የሚገልጽ የ18 ገጽ ደረጃ አወጣሁ፡፡ ይህም ተቀባይነትን አገኘ፡፡
ሪፖርተር፡- የአምቡላንስ አገልግሎትን አስመልክቶ ጉዳት የደረሰበትን ሰው እንዴት መርዳት እንደሚቻል ቢያብራሩልን?
አቶ ክብረት፡- የአምቡላስ አገልግሎት የድንገተኛ ሕክምና ሥርዓት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሥርዓት ከቅድመ ሆስፒታል፣ ከሆስፒታልና ከማገገሚያ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ቅድመ ሆስፒታል ከአደጋ ቦታ እስከ ሆስፒታል ያለ ትስስር ሲሆን፣ በቅድመ ሆስፒታል ጥሩ ሥራ ካልተሠራ በሆስፒታል ጥሩ ሥራ ሊሠራ አይችልም፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በመኪና አደጋ ቢጎዳ፣ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎቱ በጥሩ ፍጥነት መሠራትና መድረስ ይገባዋል፡፡ በጥሩ ፍጥነት ካልደረሰና ተጎጂው እየደማ ከሆነ ሆስፒታል ቢደርስም ከባድ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ከደረሰ በኋላ ሙያን ባማከለ መልኩ ተጎጂን መርዳት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሠረት ከአደጋ በኋላ ጉዳተኛውን አፋፍሶ ማንሳት ይቁም እያልን እንመክራለን፡፡ አፋፍሶ ማንሳት ማለትም አንድ ሰው ጉዳት ከደሰበት በኋላ አደጋው ቦታ የሚደርሰው ሌላው ሰው ያለ ዕውቀት በማንሳት እንደሚጎዳው ካላወቀና በሚገባው መልኩ ካላነሳው፣ ወይም ከመኪናው ውስጥ እንደፈለገው ካወጣው የጉዳተኛው ነርቭ እንዲበጠስ ያደርገዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ጉዳተኛው ፓራላይዝድ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሕክምና የሚጀመረው በቅድመ ሆስፒታል እንጂ ሆስፒታል ውስጥ አይደለም፡፡ ሰዎች ችግር ውስጥ እንኳን ቢወድቁ፣ ማንሳት ራሱን የቻለ ሳይንስ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ዘርፍ የተማሩ ሰዎች በዓለም ላይ ፓራሜዲኮች ይባላሉ፡፡ እንደነዚህ ዓይነቶቹ ባለሙያዎች በኢመርጀንሲ ሜዲካል ቴክኖሎጂስት ይጀምሩና ከእዚያ በኋላ እያደጉና ዕውቀቱን እየቀሰሙ ሲሄዱ ፓራሜዲኮች ይባላሉ፡፡ በትራፊክ አደጋ የተጎዳ ሰው ብዙ ሳይደክምና ነርቩ ሳይጎዳ ሆስፒታል ቢደርስ ለማገገም ብዙ ቀን አይፈጅበትም፡፡ ከሥራም ብዙ ቀን አይቀርም፡፡ ሕይወቱም ብዙ አደጋ ውስጥ አይወድቅም፡፡ የቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት ላይ በደንብ ካልተሠራ፣ ጉዳት የደረሰበት ሰው ቶሎ አያገግምም፣ ፓራላይዝድ ሊሆንም ይችላል፡፡ ሕይወት ማጣትም ይከሰታል፡፡ ከሆስፒታል ሲወጣ ደግሞ በትክክል ማገገም አለበት፡፡ አደጋ የደረሰበት ሰው ዝም ብሎ ወደ ኅብረተሰቡ መቀላቀል የለበትም፡፡ የአካላዊና አዕምሯዊ አደጋዎች ሊደርስበት ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ጠብታ አምቡላንስ ሙያተኞችን በማሠልጠን ረገድ የሚጫወተው ሚና ምን ይመስላል?
አቶ ክብረት፡– ከተቋቋምንበት 2001 ዓ.ም. ጀምሮ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠን ነው፡፡ ሥልጠናም እንሰጣለን፡፡ ሥልጠናዎቹም የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ ሲሆን፣ ለሙያተኞች ደግሞ መሠረታዊ (ቤዚክ ላይፍ ሰፖርት) ወይም አድቫንስ ላይፍ ሰፖርት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ ለምሳሌ አንድ አደጋ የደረሰበት ሰው ልቡ ቢቆም የቆመውን ልብ ማስነሳት የሚቻለው ከወደቀበት ወይም አደጋው ከደረሰበት ቦታ ላይ እንዳለ ነው እንጂ ሆስፒታል ውስጥ አይደለም፡፡ ስለዚህ ተጎጂው ሲወድቅ ከሥፍራው የነበረው ሰው ላይፍ ሰፖርት አለ? ወይስ የለም? የሚለው ቀድሞ ሊያሳስበው ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ ቅድመ ሆስፒታል እንደ ትልቅ ኩባንያ የሚታይ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፓራሜዲኮችን ሥልጠና በተመለከተ ቢያብራሩልን?
አቶ ክብረት፡- ሥልጠናውን የጀመርነው ከመንግሥት ጋር በመተባበር ሥርዓተ ትምህርቱን አውጥተን ነው፡፡ ኖርዌይ የሚገኘውና ፓርትነርሺፕ ፎር ቼንጅ የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የ150‚000 ዶላር ዕርዳታ አግኝተናል፡፡ የፓራሜዲክ ሥልጠና በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመርያ ከመሆኑ ባሻገር በሙከራ ደረጃ የተጀመረ ነው፡፡ በሥልጠናው ላይ የተሳተፉት የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ተቀብለው ኮሌጅ መግባት ያልቻሉ ነገር ግን በህክምና ሙያ የመሠማራት ፍላጎት ያላቸው 16 ወጣቶች ናቸው፡፡ ሥልጠናውም የተከናወነው በዲፕሎማ ደረጃ ሲሆን፣ ሥልጠናውም የተሰጠው አሜሪካ ከሚገኘው ዊቨር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ጋር በመሆን ነው፡፡ ሠልጣኞቹም የምዘና ፈተና አልፈዋል፡፡ ሁሉም የድርጅታችን ሠራተኛ ሆነዋል፡፡ ሥልጠናው የተከናወነው ለሁለት ዓመት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– ስለሞተር ሳይክል አምቡላንስ ቢያብራሩልኝ?
አቶ ክብረት፡- የሞተር ሳይክል አምቡላንስ የመኪና አደጋ መከሰቱ እንደተገለጸልን ወዲያው ከሥፍራው ደርሶ የሕይወት ማዳን ሥራን ማከናወን የሚያስችል ነው፡፡ ለዚህም ዕውን መሆን ፓራሜዲኮች ሞተር ሳይክል ማሽከርከር ሠልጥነዋል፡፡ የሞተር ሳይክል አምቡላንስ ፓራሜዳኮች አደጋው የተከሰተበትን አካባቢ ካረጋገጡ በኋላ አደጋው የደረሰበትን ሰው ከመኪናው ውስጥ ወይም ከወደቀበት ቦታ በሠለጠኑት መሠረት አንገት ደግፈው ያነሳሉ፡፡ በዓለም ላይ አንገቱን ሳይደገፍ ከመኪና የሚወጣ ተጎጂ የለም፡፡ አንገት አለመደገፍ ማለት ነገ ፓራላይዝድ የሚሆን ሰው ማውጣት ማለት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በሞተር ሳይክል ከአደጋው ሥፍራ የደረሱ ሁለት ፓራሜዲስቶች በቬንትሌተር የታገዘ ኦክስጅን በመስጠት የሕይወት ማዳን ሥራ ያከናውናሉ፡፡ የመኪናው አምቡላንስ ደግሞ በትንሽ ደቂቃ ውስጥ ከአደጋው ሥፍራ ደርሶ ቀጣዩን የሕይወት ማዳንን ሥራ ያከናውናል፡፡ ይህንን የሚያከናውኑት ነርሶች ወይም ሐኪሞች ሳይሆኑ ፓራሜዲስቶች ብቻ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ወደ 24‚000 ፓራሚዲስቶች ያስፈልጓታል፡፡ እኛ ደግሞ በሚቀጥለው አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 5‚000 ፓራሜዲስቶችን ለማስገባት አቅደናል፡፡
ሪፖርተር፡– የሞተር ሳይክል አምቡላንስና የፓራሜዲስቶች አገልግሎት በዘርፉ ያለውን ክፍተት እየሞላ ነው?
አቶ ክብረት፡- በትክክል አዎ! ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ በቅድሚያ ያስጀመረውና እየሠራበት ያለው ጠብታ አምቡላንስ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የፓራሜዲክሶች ሥልጠና ቀጣይነት አለው?
አቶ ክብረት፡- ቀጣይነት አለው፡፡ ሁለተኛውን ዙር ሥልጠና ለመጀመር እንቅስቃሴ ላይ ነበርን፡፡ ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ መከሰት ምክንያት ለጊዜው አቁመናል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት ሲገታ ሥልጠናው ወዲያው ይቀጥላል፡፡ በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነርሺፕ መርህ ከመንግሥት ጋር አብረን ለመሥራት እያሰብን ነው፡፡ ሥልጠናው አዋጭ መሆኑንም በሙከራ ደረጃ በተካሄደው የመጀመርያው ዙር ሥልጠና ላይ ለመንግሥት አረጋግጠናል፡፡ ከዚህም ሌላ ሥልጠናው የሚካሄደው በዲግሪ ፕሮግራም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ዓይነት አምቡላንሶች አሏችሁ?
አቶ ክብረት፡- አንድን አምቡላንስ አምቡላንስ የሚያሰኘው ድምፅ የመኪናው ዓይነትና መብራቱ አይደለም፡፡ ሁለት መሠረታዊ ነገሮች ሊሟሉለት ይገባል፡፡ በውስጡ የሕይወት አድን መሣሪያዎች አሉት ወይ? መሣሪያዎቹን ሊጠቀም የሚችል የሠለጠነ ሙያተኛ ይዟል ወይ? የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ የተጠቀሱት ሁለት ነገሮች ከተሟሉ መኪናው አምቡላንስ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ከሌለው ግን ተራ መኪና ነው የሚባለው፡፡ አምቡላንስ ውስጥ ያለው ተጎጂ ትንፋሽ ቢያቆም ሞተ ማለት አይደለም፡፡ ትንፋሽ መቀጠል ይቻላል፡፡ ይህንን ለማድረግ ግን መሣሪያዎች ሊኖሩት ይገባል፡፡ መሣሪያዎች ቢኖሩትና ሙያተኛው ደግሞ ከመሣሪያው ጋር ካልተዋወቀ ጥቅም የለውም፡፡ ነርስ ወይም ሐኪም ቢቀመጡ በሙያው ካልሠለጠነ በስተቀር ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ሁለት ዓይነት 15 አምቡላንሶች አሉን፡፡ ከዓይነቶቹ መካከል አንደኛው ቤዚክ ላይፍ ሰፖርት ሲሆን ሁለተኛው ዓይነት ደግሞ አድቫንስ ላይፍ ሰፖርት ይባላሉ፡፡ በዓለም ላይ ያለው የአምቡላንስ ስታንዳርድ 75 ከመቶውን የሚይዘው ቤዚክ ላይፍ ሰፖርት ስታንዳርድ ነው፡፡ ቤዚክ ላይፍ ሰፖርት ማለት ሕይወት ማዳን የሚችል ማለትም ኦክስጅን የያዘ አምቡላንስ ነው፡፡