Monday, December 4, 2023

አልረጋ ያለው የሱዳን አቋም አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ጉዳትም ሆነ ሥጋት የለውም።›› ይህንን ያሉት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት እ.ኤ.አ. በ2013 ነው።

 ፕሬዚዳንት አል በሽር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን በይፋ ከመደገፍ አልፈው፣ የግድቡን ግንባታ በአካል በመጎብኘት የኢትዮጵያ መንግሥትን ያበረታቱ ነበር። ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ እስከ ዘንድሮ ድረስ፣ የሱዳን መንግሥት ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ሲያራምደው የቆየው አቋም ወጥና ለማንም ሚስጥር ያልሆነ ድጋፍ እንደነበረ በይፋ ይታወቃል።

 በሱዳን ሕዝባዊ አመፅ ፕሬዚዳንት አል በሽር ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ የተመሠረተው የሽግግር መንግሥትም፣ ተመሳሳይ አቋም ሲያራምድ ቆይቷል። የሱዳን የሽግግር መንግሥት ባለሥልጣናት የግድቡ ዕውን መሆን የሱዳንን በየዓመቱ የሚከሰት በጎርፍ የመጥለቅለቅን አደጋ በማስቀረት የተመጠነ የውኃ ፍሰት እንድታገኝ እንደሚረዳት፣ በዚህም የዝናብ ወቅትን ጠብቆ ዓመቱን ሙሉ የግብርና ልማት እንድታካሂድ እንደሚረዳት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሲገልጹ ነበር።

የዓባይ ውኃ ወደ ሱዳን ይዞት የሚመጣው ደለል እንደሚቀርና ይህም በሱዳን የሚገኙ ግድቦችን በደለል ከመሞላት እንደሚታደግ፣ የውኃ መያዝ መጠናቸውን እንዲጨምር እንደሚያደርግና የአገልግሎት ዕድሜያቸውንም እንደሚያራዝም፣ እንዲሁም ሱዳን ከግድቦቿ ደለል ለመጥረግ በየዓመቱ የምታወጣውን 60 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስቀር ባለሥልጣናቱ ሲገልጹ ነበር።

ከእነዚህ ባለሥልጣናት መካከል አሁን ያለው የሱዳን የሽግግር መንግሥት የካቢኔ አባልና ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ እየተደረገ ባለው የኢትዮጵያ፣ የግብፅና የሱዳን የቴክኒክ ድርድር የሱዳን ዋና ተደራዳሪ የሆኑት የመስኖ ሚኒስትሩ ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር) አንዱ ናቸው። ሚኒስትሩ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2020 ለሱዳን የዜና አገልግሎት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ይህንኑ የመንግሥታቸውን አቋም አንፀባርቀዋል።

 የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እየተገነባ የሚገኘው ከአፍሪካ ስምጥ ሸለቆ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ሆኖ ከሱዳን ድንበር በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ እንደሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ ያሲር አባስ፣ የህዳሴ ግድቡ የሚገነባበት አካባቢ ለአደጋ የተጋለጠ ከሆነ በአቅራቢያው የሚገኘውም የሱዳን ሮዜሬዝ ግድብ በተመሳሳይ ለአደጋ የተጋለጠ ነው ማለት እንደሚቻል ተናግረው ነበር።

 ነገር ግን እንደዚያ ተብሎ ግድቡ ሳይጠና እንዳልታለፈ ያወሱት ሚኒስትሩ፣ የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን በግድቡ ደኅንነት ላይ ሰፊ ጥናት አድርጎ ያቀረባቸውን ምክረ ሐሳቦች ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ ተግባራዊ ማድረጓን ገልጸዋል።

 ከተተገበሩት ምክረ ሐሳቦች መካከል የኮርቻ ግድቡ በኮንክሪት እንዲለበጥ መደረጉን፣ ሁለት የውኃ ማስተንፈሻ ቀዳዳዎች መጨመራቸውንና ሌሎች በርካታ ማሻሻያ ምክረ ሐሳቦች መተግበራቸውን ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የግድቡ ግንባታ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ነው ማለት እንደሚቻል አመልክተው ነበር።

ሚኒስትሩ ያሲር አባስ (ፕሮፌሰር) ከጥቂት ቀናት በፊት በሰጡት ተመሳሳይ ቃለ መጠይቅም ስለህዳሴ ግድቡ ግንባታ የጥራት ደረጃ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል። ‹‹የህዳሴ ግድቡ የግንባታ ጥራት፣ የዲዛይንና የመረጃ ግብዓት ዓለም አቀፍ ደረጃን በጠበቀ ልዩ ጥንቃቄ እየተገነባ ስለሆነ፣ ግድቡ ሊሰነጠቅ ወይም ሊደረመስ የሚችልበት ሁኔታ ጨርሶ የለም። የግንባታው የጥራት ደረጃ በሱዳን ከሚገኙት ተመሳሳይ ግድቦችም ሆነ ከግብፅ የአስዋን ግድብ በእጅጉ የተሻለ ነው፤›› ብለው ነበር። የሱዳን የመስኖ ሚኒስትር ይህንን በተናገሩበት በዚያው ሳምንት የሱዳን የሽግግር መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አስማ መሐመድ አብደላ፣ ኢትዮጵያ የግድቡ የውኃ ሙሌትን አስመልክቶ እየተደረገ ባለው የሦስትዮሽ ድርድር ስምምነት ላይ ሳይደረስ የውኃ ሙሌቱን ብትጀምር በሱዳን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትል አሳስበዋል።

 ‹‹በዚህ ግዙፍ መጠን የሚገነባው የህዳሴ ግድብ ዲዛይን በተገቢው ደረጃ የተጠና መሆኑ ካልተረጋገጠና ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ካልተገነባ፣ ስምምነቱን መሠረት አድርጎ የውኃ ሙሌቱ ካልተከናወነ በሱዳን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። ይህም ከግድቡ በታች የሚኖሩ ሚሊዮን ሱዳናዊያን ሕይወትን ለአደጋ ያጋልጣል፤›› ሲሉ በጻፉት ደብዳቤ አሳስበዋል።

 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ለተመድ በጻፉት ደብዳቤ የሚታየው የሱዳን የአቋም ለውጥ ይህ ብቻ አይደለም። ‹‹የዓባይ ውኃ ወደ ሱዳን ይዞት የሚመጣው ደለል ለሱዳን ግብርና ጥሩ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ ቢሆንም፣ ነገር ግን በህዳሴ ግድቡ ምክንያት ይህ ጥሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያነትን የያዘ ደለል የሚቀር ወይም መጠኑ የሚቀንስ በመሆኑ፣ በሱዳን የግብርና ልማት ላይ ጉዳት ያስከትላል፤›› ሲሉም የህዳሴ ግድቡ መገንባት በሱዳን ላይ ሌላ ተጨማሪ ጉዳትም እንደሚያስከትል ተናግረዋል።

በዚህም ሳያበቁ ስምምነት ሳይደረስ በሚወሰድ ማንኛውም ዓይነት የተናጠል ዕርምጃ ቀዳሚዋ ተጎጂ ሱዳን እንደሆነች በመጥቀስ፣ የግብፅን ዛቻዎች የሚያጠናክርና በዚህም ሱዳን ሥጋት እንዳላት ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ ገልጸዋል።

 በአሜሪካ ሲደረግ የነበረው ድርድር ከተቋረጠ በኋላ ግብፅ የዓረብ ሊግ አገሮችን ሰብስባ ኢትዮጵያን የሚያወግዝ መግለጫ ባስወጣችበት ወቅት፣ የዓረብ ሊግ አባል የሆነችው ሱዳን መግለጫውን ተቃውማ የያዘውን አቋም እንደማትጋራ በይፋ አስታውቃ ነበር። ይህንንም ያደረገችበት ምክንያት ህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ያለውን የሦስቱ አገሮች ልዩነት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ማላበስ አይገባም ከሚል ነበር።

ሱዳን ህዳሴ ግድቡን በመደገፍ በምታራምደው የድጋፍ አቋም ምክንያትም ሦስቱ አገሮች የደረሱበትን መግባባት መሠረት በማድረግ የህዳሴ ግድቡን የመጀመርያ ምዕራፍ ሙሌት ብቻ የተመለከተ የስምምነት ሰነድ ሱዳን እንድትፈርም፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (አህመድ) ለሱዳኑ ለአቻቸው አብደላ ሃምዶክ ሰሞኑን በሦስቱ አገሮች መካከል ሲካሄድ የነበረው ድርድር ከመጀመሩ አስቀድሞ ልከው ነበር።

ይሁን እንጂ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሁሉን አቀፍ ስምምነት በሦስቱ አገሮች መካከል ሳይደረስ፣ ሱዳን ምንም ዓይነት ስምምነት እንደማትፈርም ለኢትዮጵያ አስታውቃለች። ይህንንም ተከትሎ በሦስቱ አገሮች መካከል ዳግመኛ የቴክኒክ ድርድር በበይነ መረብ አማካይነት እንዲካሄድ ሱዳን ኢትዮጵያና ግብፅን በማግባባት፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ለነበሩ ስድስት ተከታታይ ቀናት ተካሂዶ የተሟላ ስምምነት ሳይደረስ ነው ሱዳንና ግብፅ ባነሱት ጥያቄ ምክንያት የተቋረጠው።

በሰሞኑ ድርድር የግድቡን የመጀመርያ ሙሌት በተመለከተ በሦስቱ አገሮች መካከል ስምምነት የተደረሰ ቢሆንም፣ ቀጣይ ምዕራፍ የውኃ ሙሌትና የድርቅ ሁኔታ አስተዳደር፣ እንዲሁም ስምምነቱ ከህዳሴ ግድቡ በተጨማሪ አጠቃላይ የዓባይ ወንዝን የተመለከተ ሊሆን ይገባል የሚሉ በዋናነት ግብፅ የምታነሳቸው ጥያቄዎች ላይ መግባባት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት ሱዳንና ግብፅ ጉዳዩ ለሦስቱ አገሮች መሪዎች ተመርቶ የፖለቲካ ውሳኔ እንዲሰጥበት በመጠየቃቸው ተቋርጧል።

የሱዳን አቋም መዋዠቅ ከምን ሊመነጭ ቻለ?

ሱዳን በምን ምክንያት አንዴ ወደ ኢትዮጵያ፣ አንዴ ወደ ግብፅ እየረገጠች አቋሟ አልጨበጥ አለ የሚለው በርካታ ጉዳዩን የሚከታተሉ ኢትዮጵያዊያንን እያነጋገረ ይገኛል። ለሱዳን የአቋም መወላወል ምክንያቱ በግድቡ ላይ ካደረገቸው ግምገማ የሚመነጭ ሳይሆን፣ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ከተወገዱ በኋላ የተቋቋመው የሱዳን የሽግግር መንግሥት ወቅታዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ፍላጎቶችን ለመመለስ ቅድሚያ ከሰጠው ፍላጎት የተነሳ መሆኑን፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ተንታኝ ይገልጻሉ።

ከዚህም ጀርባ የአሜሪካ መንግሥት እጅ በግልጽ እንደሚታይ እኚሁ የፖለቲካ ተንታኝ ያስረዳሉ፡፡ ሱዳን በግድቡ የጥራት ደረጃ ላይ ጥያቄና ሥጋት እንዳላት ለኢትዮጵያ አንስታ እንደማታውቅ፣ የዚህ ምክንያቱም ግድቡ በተጀመረበት ወቅት የሦስቱ አገሮች ተወካዮች ባሉበት ጥናት ያካሄዱት የዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የግድቡ ጥራትን ለማረጋገጥ ቢስተካከሉ ብሎ ያቀረባቸው ምክረ ሐሳቦች በሙሉ ተግባራዊ በመደረጋቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

ሱዳን በግድቡ ደኅንነት ላይ ሥጋት እንዳላት በይፋ ያነሳችው በአሜሪካ ሲካሄድ የነበረው ድርድር መቋረጡን ተከትሎ የታዛቢነት ሚና የነበረው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያ የግድቡን ሙሌት በተናጠል ውሳኔ ማካሄድ የለባትም በማለት ካወጣው መግለጫ በኋላ መሆኑን ያስረዳሉ።

በዚህ መግለጫ ኢትዮጵያ ስምምነት ሳይደረስ ግድቡን መሙላት እንደሌለባት ሲያሳስብ ከተጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ፣ ሱዳን በግድቡ የግንባታ ጥራት ላይ ጥያቄና ሥጋት እንዳላት የሚገልጽ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህ ወቅትም ሆነ በኋላ በነበሩት ጥቂት ወራት ከሱዳን በኩል እንዲህ ዓይነት ሥጋት እንዳልነበር፣ ለዚህ ማስረጃውም ዋና ተደራዳሪው የመስኖ ሚኒስትሩ ከአንድ ወር በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ እንኳን ስለግድቡ የጥራት ደረጃ ከኢትዮጵያ በላይ አድንቀው እንደተናገሩ በማውሳት ያስረዳሉ።

ነገር ግን በአሜሪካና በሱዳን መካከል ውስጥ ውስጡን ሲካሄዱ የነበሩ ድርድሮች እንዳሉ፣ ከእነዚህም መካከል አንዱ አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪነት መዝገብ ለመሰረዝ ማሰቧን እንደ ስጦታ ለሱዳን ማቅረቧን ያወሳሉ።

አሜሪካ በሱዳን ላይ የጣለችው የአሸባሪነት ፍረጃ ሱዳን ከዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ ኩባንያዎች ጋር ንግድና ገንዘብን የተመለከተ ግንኙነት ላለፋት ሦስት አሠርት ዓመታት በላይ እንዳይኖራት በማድረጉ፣ ኢኮኖሚዋ እንዲንኮታኮት አድርጎታል። እንዲሁም የደቡብ ሱዳን መገንጠል የሱዳንን የኢኮኖሚ መሠረት የነበረውን የነዳጅ ሀብት 75 በመቶ ይዞ በመሄዱ የሱዳን ኢኮኖሚ መንኮታኮቱን ይገልጻሉ።

በዚህ ላይ የደቡብ ሱዳን መገንጠል የቀድሞ ሱዳንን የነዳጅ ሀብት 75 በመቶ ይዞ በመሄዱ የሱዳን ኢኮኖሚ አዘቅት ውስጥ መግባቱን፣ በአሁኑ ወቅት ከዚምባቡዌ ቀጥሎ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የሚታይባት አገር መሆኗ፣ ለምዕራባዊያኑ ተፅዕኖ ያልተበገሩት ፕሬዚዳንት አል በሽር መጨረሻም ያላማረው በኢኮኖሚ ጉዳቱ የሱዳን ሕዝብ ከዚያ በላይ የማይሸከመው በመሆኑ ነው ሲሉ አስረድተዋል። በመሆኑም አሜሪካ ሱዳንን ከአሸባሪ መዝገብ አወጣለሁ ማለቷ በሥልጣን ላይ ለሚገኘው የሱዳን ሽግግር መንግሥት ትልቅ ገፀ በረከት መሆኑን ገልጸዋል።

የሽግግር መንግሥቱ የሱዳንን ኢኮኖሚ ከአዘቅት ለማውጣት የቀረበለት ትልቅ ስጦታ በመሆኑ፣ ከህዳሴ ግድቡ ይልቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ብሔራዊ ጥቅም እንደሆነበት የፖለቲካ ተንታኙ ያስረዳሉ።

ከዚህ ባለፈም የሽግግር መንግሥቱ የሱዳንን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት የኢኮኖሚ ማነቃቂያ ፕሮግራም በመንደፍ ምዕራባዊያኑ ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን፣ ምዕራባዊያኑም በጀርመን ዋነኛ አስተባባሪነት የሱዳን ወዳጆች ኮንፈረንስ የተሰኘ ግዙፍ ጉባዔ በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ በጀርመን በርሊን ከተማ እንደሚያካሂዱ ጠቁመዋል።

በዚህ ጉባዔ ላይ አሜሪካን ጨምሮ ፈረንሣይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ እንግሊዝ፣ ተመድ፣ አይኤምኤፍ፣ ዓለም ባንክና የመሳሰሉት እንደሚሳተፋበት ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሚመራው የሱዳን ሽግግር መንግሥትም፣ በዚህ ጉባዔ ላይ ለኢኮኖሚ ማነቃቂያ ፕሮግራሙ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ፈንድ ድጋፍ እንዲደረግለት ጥያቄ እንደሚያቀርብ ገልጸዋል። አሜሪካና አውሮፓዊያኑ ይህንን ድጋፍ ለሱዳን ዝም ብለው ሊያደርጉ እንደማይችሉ የሚገልጹት ባለሙያው፣ እነሱም ከሱዳን የሚፈልጉት ነገር እንደሚኖር ጠቁመዋል።

ከሱዳን ከሚፈልጉት ነገር አንዱ ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ ላይ ያላቸው ፍላጎት እንዲሳካ ግብፅን መያዝ የሚኖርባቸው በመሆኑ፣ ግብፅ ደግሞ በዓባይ ላይ ያላት የዘመናት የበላይነት ተጠብቆ እንዲቆይ የምትሻ ስለሆነ ሱዳን ይኼንን የግብፅ ፍላጎት እንድትደግፍ እንደሚሹ ተንታኙ አስረድተዋል።

በመሆኑም የሱዳን የአቋም ለውጥ ኢትዮጵያን የሚጎዳ ቢሆንም ከብሔራዊ ጥቅሟ እንፃር ተገዳ የገባችበት እንደሆነ ያስረዱት ባለሙያው፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አካሄዱን ከዚህ አንፃር ገምግሞ ማስተካከልና ምዕራባዊያኑ በዓባይ ፖለቲካ ላይ የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዴት በሥልት ማለፍ እንደሚቻል በጥንቃቄ ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -