Friday, December 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከአበባ ዘርፍ በዘጠኝ ወራት ከ440 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓመቱ የሚጠበቀው 327 ሚሊዮን ዶላር ነበር

የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ከባድ ተፅዕኖ እንደሚያርፍባቸው ከሚጠበቁት አንዱ የነበረው የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ፣ ለበጀት ዓመቱ ከተቀመጠለት በላይ በሆነ አፈጻጸም በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ከ440 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱ ተገለጸ፡፡

በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ከተነገረ ጀምሮ ተፅዕኖውን ካሳረፈባቸው ዘርፎች አንዱ የሆርቲካልቸር መስክ፣ በዓመቱ ያስገኛል ተብሎ የሚጠበቀው የገቢ መጠን 327 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ይሁን እንጂ የአበባ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ በአንድ ጊዜ እስከ 801 በመቶ ዝቅ እንዲል ያስገደደው የኮሮና ቫይረስ፣ የኢትዮጵያን የአበባ ንግድ በማስተጓጎል አስደንጋጭ ሥጋት ደቅኖ እንደነበር የኢትዮጵያ አበባ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ዘውዴ ይገልጻሉ፡፡

ይሁን እንጂ ዘርፉ ያስገኛል ተብሎ ከታቀደው በላይ ገቢ ማስገኘት የቻለው የኮሮና ወረርሽኝ ሊያሳድርበት የሚችለውን ተፅዕኖ በመቋቋም፣ ከሚታሰበው በላይ ውጤታማ መሆን እንደቻለ አብራርተዋል፡፡

የምርቱ መዳረሻ የሆኑት የአውሮፓ አገሮች ድንበራቸውን መዝጋታቸው ከኢትዮጵያ የሚቀርብላቸውን የአበባ ምርት እጅጉን እንዲያሽቆለቁል አደረገው፡፡ በዚህ ሳቢያም ምርቱ ወደ 20 በመቶ ዝቅ በማለት በዚሁ ተወስኖ ቆየ፡፡ ይህ በየካቲት ወር መጨረሻ እንዲሁም መጋቢት ላይ ጎልቶ የታየ ከባድ ክስተት ነበር፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ዘርፉ የ25 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማጣቱን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡ 

እስከ ዓመቱ አጋማሽ ድረስ ከአበባ ዘርፍ ሲገኝ የቆየው የውጭ ምንዛሪ በታሪኩ ከፍተኛው ገቢ የተገኘበት ወቅት ቢሆንም፣ ከአጋማሽ ዓመቱ በኋላ ግን የኮሮና ወረርሽኝ በመከሰቱ ገበያውን ክፉኛ ሊመታው ችሏል፡፡ መንግሥት ወረርሽኙ በቶሎ ያጠቃቸው የቢዝነስ ዘርፎችን በመለየት የተለያዩ ዕርምጃዎች ሲወስድ፣ ባንኮች ብድር አራዘሙ፡፡ የተወሰኑ ሆቴሎች ወለድ ቅናሽ ተሰጠ፡፡ ሠራተኞች እንዳይቀንሱ የሥራ ማስኬጃ ብድር እንዲያገኙ የተለየ ድጋፍና ድጎማ ተደርጎላቸዋል፡፡

ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላም የአበባ ገበያ እንደገና መነሳትና ማንሰራራት በመጀመሩ፣ ጠውልጎ የቆየው የዘርፉ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴም ቀና እያለና እየፈካ ተመልሶ የተሻለ ገቢ ወደ ማስገኘቱ አዘንብሏል፡፡

የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር እንደገለጹት፣ አበባ መልሶ መፍካት ጀምሯል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ የተሻለ ገቢ የሚገኝበት ዕድል በመፈጠሩ ለአልሚዎችና ለላኪዎች መልካም ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡  

ይህ በመሆኑ ‹‹አበባ አሁን ከኮሮና ሥጋት ወጥቶ የተሻለ ገቢ የሚገኝበት ወቅት ላይ ለመድረሱና የተለያዩ ምክንያቶች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ አንደኛው በኢትዮጵያ በኩል መንግሥት የወሰዳቸው ውሳኔዎች ከችግሩ የቀደሙ ሆነው በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ በረራ አለማቆሙም ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የተሻለ ውጤት እንድታስመዘግብ ገልጸው፣ በንፅፅር ኬንያኖች የገጠማቸውን ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ኬንያዎች በዚህ ተበልጠዋል፡፡ የኬንያ አበባ እስካሁን ውስጥ ነው፡፡ ምክንያቱም የአበባ ፍላጎት ሲቀዘቀዝ ኬንያ የነበሩ የካርጎ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በመውጣታቸው ችግሩን አባብሶባቸዋል፤›› ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፣ ‹‹የአበባ ገበያ ዜሮ በገባበት ወቅት በዓለም ላይ የካርጎ ቢዝነስ ጥብስ እየሆነ መጣ፡፡ ድንበሮች ተዘግተው ቢቆዩም፣ የካርጎ ጭነት ማጓጓዝ ሳይቋረጥ ቀጥሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በኬንያ የካርጎ ጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች ከኬንያ በመውጣታቸው፣ የአበባ ገበያ እየተሻሻለ በመጣበት በአሁኑ ወቅት ግን የኬንያ አበባ ወደ ገበያ ሊወጣ አልቻለም፤›› በማለት ከኬንያ አኳያ ኢትዮጵያ ምን ያህል ከኬንያ በተሻለ ደረጃ በካርጎ ተጠቃሚ እንደሆነች ያብራራሉ፡፡

የኢትዮጵያ አበባ የገበያውን ወቅታዊ የተጠቃሚነት ዕድል መውሰድ በመቻሉ፣ ከዘርፉ ለተገኘው ውጤት ምክንያት እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡ በአውሮፓ የተዘጉ ድንበሮች እየተከፈቱና የታገዱ እንቅስቃሴዎች እየተፈቀዱ በመምጣታቸው፣ ለእነዚህ ገበያዎች ተደራሽ መሆን የቻለው ደግሞ የኢትዮጵያ አበባ ሆኖ በመገኘቱና የኬንያ አበባ እርሻ በጎርፍ በመመታቱ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የአበባ አቅራቢ ለመሆን የቻለችበትን ዕድል እንደተፈጠረ አብራርተዋል፡፡ በርካታ ችግሮች እንደሚያጋጥሙት ሥጋት አሳድሮ ቢቆይም፣ ዘርፉ ባጋጠሙት ዕድሎች ታግዞና በኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ አገልግሎት ተደግፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መደበኛ የንግድ እንቅስቃሴ ለመመለስ እንዳበቁት ተብራርቷል፡፡ የኢትዮጵያ አበባ ዳግም በገበያዎች ውስጥ እንደ ልብ መንቀሳቀስ በመቻሉ፣ በኮሮና ጉዳት ከደረሰባቸው ከኢኳዶር፣ ከኬንያ፣ ከኮሎምቢያና ከኔዘርላንድም አንፃር ሲታይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የቻለበት አጋጣሚ እንደተፈጠረለት ተጠቅሷል፡፡

በአጭር ጊዜ ከኮሮና አደጋ ሥጋት መውጣት መቻሉ መንግሥት በበጀት ዓመቱ ከአበባ እንደሚገኝ የያዘውን ዕቅድ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከማሳካት አልፎ ከዕቅድ በላይ ውጤት እንዲገኝበት አስችሏል፡፡ ዘርፉን ለመደገፍና ለማገዝ ወሳኝ ዕርምጃ ተወስዶ ውጤትም ስለመምጣቱ የሚጠቅሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ በመንግሥት በተወሰነ ውሳኔ ሠራተኞች እንዳይቀንሱ ማድረጉም ሌላው ጥቅም ነበረው ብለዋል፡፡ ከዚህ አንፃር ኬንያኖች ቀድመው ሠራተኛ እንዲቀንሱ ማድረጋቸውም የአበባ ዋጋ ከፍ ሲል አበባቸውን መላክ አላስቻላቸውም፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አበባ የተፈራውን ያህል ጉዳት ሳይደርስበት እንደውም ከታሰበው በላይ መላክ ተችሏል፡፡

ኮሮና ለአበባ ዘርፍ ከባድ ሥጋር ይሆናል ተብሎ የተፈራበት አንዱ ምክንያት፣ የአበባ እርሻ ሥራ እንደሌሎች የማሳ ሥራዎች በተፈለገ ጊዜ ምርት ማቆም የሚቻልበት ዘርፍ ባለመሆኑ ነበር፡፡ አበባው ምርቱን ሳያቋርጥ የሚቀጥል በመሆኑ፣ ገበያው በጠፋ ጊዜም ጭምር ምርቱ እየተመረተ፣ ሠራተኞችም ሳይቀነሱ እየሠሩ እንዲቆዩ መንግሥት በመወሰኑ ጭምር ሥጋቱ የተባባሰ እንደነበር አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡ ለአበባ በግብዓትነት የሚያስፈልጉትም ማቅረብ የግድ የሚል በመሆኑ፣ መንግሥት ሁኔታውን ተረድቶ፣ የሥራ ማስኬጃ ብድር መፍቀዱና የተፈቀደው ገንዘብም ለማዳበሪያና ለኬሚካል ግዥ እንዲውል በማገዙ፣ ለሠራተኛ የሚከፈለው ገንዘብ፣ ለባንክ የሚከፈል ብድር ማራዘሚያና የወለድ ቅናሽ መደረጋቸው ሁሉ ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ ታድጎታል፡፡ ይህ በመደረጉ የዘርፉ እንቅስቃሴ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል በማገዝ በቶሎ እንዲነቃቃና ያለ ችግር ገበያውን ለመያዝ እንዳስቻለው አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች