ከሁለት ዓመት በፊት በተላለፈ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተጨማሪ ውሳኔ በጡረታ ለተሰናበቱ ከፍተኛ የአገርና የመንግሥት አመራሮች ሲሰጥ የነበረ ልዩ ጥቅማ ጥቅም ቀሪ እንዲሆን ተወሰነ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ በጡረታ ለተሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች ከአዋጅ ውጪ በልዩ ውሳኔ የተፈቀደላቸው ልዩ ጥቅማ ጥቅም ቀሪ እንዲሆን ወስኗል።
ምክር ቤቱ ባሳለፈው ውሳኔ መሠረትም የገንዘብ ሚኒስቴር በጡረታ ለተሳናበቱ አመራሮች የተፈቀዱ ልዩ ጥቅሞችን ተከታትሎ እንዲያስመልስና ወደፊትም በሕግ ከተፈቀደው ውጪ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ መሠረት በጡረታ ለተሰናበቱ አመራሮች ተፈቅዶ የነበረውን ተጨማሪ ልዩ ጥቅማ ጥቅም እንዳይፈጽም ታዟል።
የአገርና የመንግሥት አመራሮች፣ ዳኞችና የፓርላማ አባላት ሊያገኟቸው የሚገቡ መብቶችና ጥቅሞች በአዋጅ ቁጥር 653/2001 መሠረት መወሰኑ ይታወቃል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በጡረታ ለሚሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች በአዋጅ ከተፈቀደው ውጪ ተጨማሪ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲፈቀዱላቸው ወስኖ ነበር።
በዚህ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ልዩ ውሳኔ በጡረታ ለተሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች ተፈቅደው የነበሩት ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች ሦስት ጉዳዮችን የተመለከቱ ነበሩ።
እነዚህም በጡረታ የተሰናበቱ የአገርና የመንግሥት አመራሮች በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት በተሰጣቸው ቤት መኖር እንዲቀጥሉ፣ አንድ አውቶሞቢልና አንድ የመስክ ተሽከርካሪ እንዲሰጣቸው እንዲሁም በኃላፊነት በነበሩበት ወቅት ያገኙ የነበረው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲቀጥሉ የሚፈቅዱ ናቸው።
ከሳምንት በፊት የተላለፈው አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ከላይ የተገለጹት ሦስት ተጨማሪ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲሻሩና በአዋጁ መሠረት ብቻ እንዲስተናገዱ የሚል ነው:: በዚህ ውሳኔ መሠረት ቤት የተሰጣቸው በጡረታ የተሰናበቱ አመራሮች እንዲኖሩበት የተሰጣቸውን ቤትና የመስክ ተሽከርካሪ እንዲመልሱ የተባለ ሲሆን፣ የገንዘብ ሚኒስቴርም ይህንን ውሳኔ እንዲፈጽም ሰኔ 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ትእዛዝ ደርሶታል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሁለት ዓመት በፊት ያሳለፈው ውሳኔ በአዋጁ የተፈቀደ ባይሆንም በወቅቱ ከነበረው ሪፎርም አንፃር ተገቢ የነበረ መሆኑን የገለጸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት፣ በዘላቂነት እነዚህን ጉዳዮች መፈጸምና ይዞ መቀጠል ወጥ አሠራር እንዳይኖር የሚያደርግና አገር ላገለገገሉ ከፍተኛ አመራሮች የተለያየ የመብት ጥበቃ በመንግሥት እንዲደረግ የሚፈቀድ ያልተገባ አሠራር ሆኖ በመገኘቱ ወጥ የሆነ የመብት ጥበቃና አሠራር መተግበሩ ተገቢ መሆኑን ለገንዘብ ሚኒስቴር በላከው ደብዳቤ ገልጻል::