Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጣናን የማረከው እምቦጭ አረም

ጣናን የማረከው እምቦጭ አረም

ቀን:

በሔለን ተስፋዬ

በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ቅርኛ ቀበሌ የሚወስደው መንገድ እንግልት የበዛበት ቢሆንም፣ እምቦጭ አረምን ለመንቀል ወኔ አንግቦ የተነሳውን እንዲያፈገፍግ አላደረገውም፡፡ ከቦታው ስንደርስ ከጣና ሐይቅ ይልቅ ዓይን የሚይዘው በአሳዛኝ መልኩ የተንጣለለው እምቦጭ አረም ነው፡፡

የባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለብ ደጋፊዎች፣ የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች፣ ጋዜጠኞችና አርቲስቶች የጣና ሐይቅን የማረከውን አረም ለመንቀል ወደ ቦታው ቢዘልቁም ፈቀቅ የሚል ነገር እንደማይኖር ለማየት ችለናል፡፡ አረሙ ጣናን ከመሻማት አልፎ በውስጥ የሚኖሩትን አሣዎች ሕይወት እየነጠቀ መሆኑንም ታዝበናል፡፡

አንድ የአካባቢው ወጣት ለሪፖርተር እንዳስረዳው፣ አረሙን በእጅ መንቀል እጅግ አድካሚ ነው፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች አረሙን መንቀል የዕለት ተዕለት ሥራ ቢሆንም፣ አረሙ ሰውነታቸው ላይ በሚያሳድረው የቆዳ ሕመም ምክንያት ብዙዎች ለመሸሽ ተገደዋል፡፡ ለቀድሞው በዚህ ወቅት ከጣና አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች ደጃፍ የሚደርሰው የሐይቁ ውኃ፣ በአረሙ ምክንያት በመሸሹ፣ የደረቀውን የጣና ክፍል ተከትሎ የሚያርሰው ገበሬ እንዳለ ሆኖ፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት መሬቱን ለሌሎች የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩ ችግሩን እንዳባባሰው የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡

ከተለያዩ አካባቢዎች ሚወጣው ቆሻሻና ፍሳሽ ተጨማሪ ፈተና መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ለዓመታት በጣና ዳርቻ አሣ በማስገር የሚተዳደረው ወጣት  አረሙን ለመቆጣጠር በክልሉ ተሠራ የሚባለውም እዚህ ግባ እንደማይባል ገልጿል፡፡

‹‹ከኮሮና ቫይረስ ተጠበቁ››

 

‹‹በጣና ሐይቅ እየተቆመረ የጥቂት ግለሰቦች መበልፀጊያ ነው›› የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች እናቶች ሳይቀሩ አረሙ እንዲጠፋ መቀነታቸውን ፈተው ባዋጡት ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ ተሠራ የተባለው አረሙን የማጥፋት ሥራ በዓይን የማይታይ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ለእምቦጭ አረም ጣና ምቹ የሆነበት ምክንያት ደለል፣ ገበሬዎች የሚጠቀሙበት ማዳበሪያና ከሆቴሎች የሚወጡ ፍሳሾች በክልሉም ሆነ ተቋቋመ በተባለው ኤጀንሲ እልባት እንዳልተሰጠው በአሣ አስጋሪነት የተሰማራው ወጣት ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል እምቦጭ አረምን ለማጥፋት በሚደረገው የቴክኖሎጂና አገር በቀል ዕውቀቶች መገፋታቸውን የሚያስረዳው ወጣቱ፣ ማኅበረሰቡ አረሙ እንዳይጠፋ የሚፈልግ አካል አለ የሚል ጥርጣሬ እንዲነግሥበት አድርጓል ብሏል፡፡

አረሙን ለማጥፋት የተቋቋመው ኤጀንሲ ‹‹አረሙ የሚጠፋው በሰው ኃይል ብቻ ነው›› የሚለው ነገር እንደማይሠራ እማኞች ነን የሚለው ወጣቱ አረሙን በመንቀል ፈቀቅ ያለ ሥራ እንዳልተሠራ ገልጿል፡፡ እንደርሱ አገላለጽ፣ ከዚህ ቀደም የአካባቢው ገበሬ ከጣና ዓሣ በማስገር ይተዳደር የነበረ ቢሆንም፣ እምቦጭ ባስከተለው ጉዳት ሳቢያ ምርት ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ገበሬው እየደረቀ የመጣውን ጣና እንደ አማራጭ በማረስ፣ የዕለት ጉርሱን ለማግኘት ቢጣርም አልሆነም፡፡ በኤጀንሲው አማካይነት ለአካባቢው ነዋሪዎች በቀን የተወሰነ ገንዘብ እየተከፈላቸው አረሙን የመንቀል ሥራ እየተሠራ ነበር የሚሉት የአካባቢው ነዋሪዎች አሁን እንደዚህ ዓይነት እንቅስቃሴዎች መቆማቸውን ገልጸዋል፡፡

የዓባይ ራስና ማሕፀን የሆነው የጣና ሐይቅን በተመለከተ ብዙዎች እንደሚናገሩት፣ ጣና ለረዥም ዓመታት ከመረሳቱ ጎን ለጎን የእምቦጭ አረሙ ሲሸፋፈን መቆየቱ ችግሩ እንዳይፈታ አድርጓል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ሰይፉ አድማሱ (ዶ/ር) በአረሙ ዙሪያ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡

በዋናነነት አረሙ ከዚህ ቀደም ለምን አልተከሰተም? አሁን ለምን ተከሰተ የሚለውና ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ምን እንደሚመስል እንደሚያጠኑ የገለጹት ዶ/ር ሰይፉ፣ እነዚህ ምርምሮች በዋናነነት መፍትሔ ለማምጣት የሚያግዙ እንደሆኑ  ዩኒቨርሲቲው በዋናነነት ጀልባ ላይ ማሽን በመግጠም ከሙላት ኢንጂነሪንግ ጋር በመተባበር ከዲዛይን ሥራ እስከምርት ድረስ እንደተሠራ ገልጸዋል፡፡

የእምቦጭ አረምን መስፋፋት ለመቀነስ ማሽን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ልምዶች እንደሚያስፈልጉ፣ እንደ ጢንዚዛ ያሉ በባዮሎጂካል ምርምር የማርባት በቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ያለውን ተሞክሮ በመውሰድ ውጤታማ መሆን እንደሚቻልም ያስረዳሉ፡፡

በዶ/ር ሰይፉ አገላለጽ ኬሚካሎች ቢኖሩም፣ በውኃማ አካላት ላይ መሞከር ለሐይቁና በውስጡ ለሚኖሩት አካላት ሲባል አይመከርም፡፡ ‹‹የእምቦጭ ችግር የፖለቲካ እንጂ ዕውቀትን መሠረት ያደረገ አይደም፤›› የሚሉት፣ ዶ/ር ሰይፉ እምቦጭ ለዓለም አዲስ አለመሆኑን፣ ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት የነበረው የሕዝብ ቁጥር ከአሁኑ አንፃር፣ የአሁኑ ከፍተኛ በመሆኑ የሚኖሩው ተፅዕኖ፣ የማኅበረሰቡ የመሬት አጠቃቀም ችግሮች ጣናን አደጋ ላይ መጣላቸውን አክለዋል፡፡

በጣና ዙሪያ እንደ ፓፒረስና ሌሎችም የዕፀዋት ዝርያዎች ባለመኖራቸው ጣና ለገጠመው አደጋ አንደኛው ምክንያት ነው፡፡ ጣና 80 እና 90 በመቶ የሚሆነው ዳርቻው በእርሻዎች የተከበበ መሆኑ፣ ለእርሻ የተለያዩ ማዳበሪያዎች  ጥቅም ላይ መዋላቸው የራሳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ ከዚህ በፊትም በዓለም ላይ የነበረውና አሁንም ያለው እምቦጭ አረም ጣና ላይ ተፅዕኖ ያመጣው፣ በክረምት ወቅት በዝናብ ተጠራርጎ ወደ ጣና ስለሚገባ፣ አፈሩም በፎስፈረስ የተሞላ በመሆኑ ለአረሙ ምቹ ሁኔታ ስለሚፈጥር መሆኑንም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡

ከእምቦጭ በተጨማሪ ሌሎች የአረም ዝርያዎች በሐይቁ ላይ ሊከሰቱ እንደሚችሉ፣ አረሙን ለመከላከል ዘላቂ መፍትሔ ሊሆን የሚችለውም የእርሻ መሬትን መቀነስና ለገበሬዎች አማራጭ ማቅረብ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በብዛት እምቦጭ እየተስፋፋ ያለው ወደ ሰሜን ምሥራቅ ጣና ክፍል ሲሆን ምክንያቱ ደግሞ ጥልቀቱ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚሉት፣ እምቦጭ መሬት ይፈልጋል፣ ከመሬት ጋር ተያይዞ ውኃው ላይ የሚንሳፈፍ በመሆኑም የሰው ኃይልና ማሽን በመጠቀም ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ለሥራው ተብሎ ከውጭ የገባው ማሽን ከአካባቢው ሥነ ምኅዳር ጋር የማይስማማ በመሆኑ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከዩኒቨርሲቲና ከሙላት ኢንጂነሪንግ ጋር በመሆን ወደ ማሽን ዲዛይን ማምረት መገባቱን አስታውሰው፣ ዩኒቨርሲቲው ማሽን ሠርቶና ውጤታማነቱን አረጋግጦ ለሚመለከተው አካል በማስተላለፍ ኃላፊነቱን መወጣቱን ገልጸዋል፡፡

‹‹ጣናን የሚጠብቅ ተቋም አለ ለማለት አያስደፍርም›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ችግሩን ለመቅረፍ የተቋቋመው ኤጀንሲ፣ የአደረጃጀትና ሌሎች ችግሮች ስላሉበት፣ መፈተሽ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡  

ዩኒቨርሲቲው ለጣና ሥነ ምኅዳር ምቹ የሆነ ማሽን በመሥራት፣ ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ማሽኑ እንደሚሠራ ሞክሮ ጥቅም ላይ እንዲውል ሲጠይቅ የሚረከብ አካል ማጣቱን ይገልጻሉ፡፡ የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃ ልማት ኤጀንሲ፣ ማሽኑን ተቀብሎ ሥራውን ይሠራል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ቴክኖሎጂ በመጠቀም መፍትሔ አይመጣም በሚል የራስ አመለካከት እስካሁን ወደ ሥራ እንዳልተገባ ያክላሉ፡፡

ኤጀንሲው በቂ የሰው ኃይል አደረጃጀት እንደሌለው፣ በትክክል አቅጣጫ እየሰጠ ነው ብለው እንደማያምኑ ዶ/ር ሰይፉ ተናግረው፣ ጢንዚዛን በተመለከተ ዩኒቨርሲቲው ምርምር አካሄዶ ውጤታማነቱን በተወሰነ መልኩ ለማየት ቢቻልም፣ ያንን ወስዶ ተግባራዊ የሚያደርገው አካል እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡

የሚመለከተው አካል ቴክኖሎጂውን ወስዶ ተግባራዊ ማድረግ፣ ጥርጣሬም ካለ አብሮ መመራመርና መፍትሔ መፈለግ እንደሚችል፣ ባለመጠቀምና አይሆንም በማለት ጊዜና ሀብት ማባከን እንደማይገባና አማራጮችን ተጠቅሞ ተግባራዊ የሚደረግበትን መንገድ ማመቻቸት ይቻል እንደነበረ ይገልጻሉ፡፡

አሁን ላይ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ያሉ ማሽኖች አይምጡ እየተባለ መሆኑን፣ ማሽኖች ቢገዙም እነሱን አቀናጅቶ የሚሠራበትና ማሽኖቹ የሚቆሙበት ወደብ እንደሌለም የሚያወሱት ዳይሬክተሩ እነዚህ ማሽኖች ሲመጡ ወደብና አስፈላጊው ጋራዥ ተዘጋጅቶላቸው ስምሪት አደራጅቶ ለማስኬድ ኤጀንሲው ቁርጠኝነቱን መውሰድ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ ተሞክሮንና ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን አቀናጅቶ ወደ ሥራ ለመግባት ችግር እንዳለ፣ ወደ ግለሰብ አመለካከት የማድላትና በጥርጣሬ እየታየ ሥራውን ከመፈጸም ይልቅ የመግፋት ሁኔታዎች ከመታየትቸው ባሻገር ትልቁ ችግር ተቋማዊ አደረጃጀትና ውሳኔ የመስጠት ነገር ጎልቶ እንደሚታይም አመልክተዋል፡፡

ተፈጥሮአዊ የሆኑት ደንገል፣ ቀጠት የሚባሉ ዝርያዎች በሐይቁ ዙሪያ መተከሉ ለአርሶ አደሩ ወደ ማሳው የገባውን የእምቦጭ አረም ለማጥፋት መጥቀሙ ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን አገር በቀል ዕውቀቶች ከቴክኖሎጂው ጋር በማናበብ የሚሠራ ሥራ ባለመኖሩ፣ ችግሩ እየተባባሰ መሆኑ ይገለጻል፡፡

በሌላ በኩል በሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተሠራው የእምቦጭ ማንሻ መሣሪያ የሚሠራው በውኃ ላይ በሚሄድ መርከብ ሲሆን፣ በይበልጥ ውጤታማ እንደሆነ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙላት ባዘዘው ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከሰው በይበልጥ ማሽኑ መሥራት ይችላል ያሉት አቶ ሙላት፣ አረሙ በተነሳ ቁጥር የሚሰፋ ስለሆነ ማሽን የሚችልበት ላይ ማሽን በመጠቀም ማሽን በማይቻልበት ቦታ የሰው ኃይል በመጠቀም ችግሩን በቀላሉ መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውኃ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ  አያሌው ወንዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ እስካሁን ባለው ነገር አረሙ እየተስፋፋ ቢሆንም፣ በኤጀንሲው እየተደረጉ ያሉ ሙከራዎች እንዳሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አረሙ ያለበት አንዳንድ ቦታዎች መሠረተ ልማት ባለመኖሩ አርሶ አደሩም ሆነ ሌሎች አካላት እንደ ልብ እየሄዱ እንዲሠሩ እንደማያስችል ሥራ አስኪያጁ ይገልጻሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሰው ኃይል ከሐይቁ ላይ አረሙን ለማስወገድ ተሞክሯል ያሉ ሲሆን፣ ለአርሶ አደሩ የተወሰነ ነገር በማሰብ አረሙ እንዲወገድ ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በሌላም በኩል እንዳይዛመት አጥር በማጠር ለመከላከል ታቅዷል የተባለ ቢሆንም፣ ኃላፊነት የሚሰማውና ዝግጁ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት እንዳለ አስረድተዋል፡፡ የአካባቢውን ወጣት በማሰማራት ግንዛቤው እንዲያድግ ከማድረግም በተጨማሪ በአካባቢው ደንገልና ሌሎች እፅዋቶችን በመትከል መልሶ እንዲያንሰራራ ማድረግ ይቻላል ተብሏል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲና ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከቻይና እና ከካናዳ የመጡ ስድስት ማሽኖች ይገኛሉ ያሉት ዶ/ር አያሌው፣ አመርቂ ውጤት እንዳላመጡ ይናገራሉ፡፡ ኤጀንሲው በተቋቋመው ቦርድ አማካይነት በጀት በመያዝ ወጣቶችን በማደራጀት የተለያዩ ሥራዎች መሠራቱንና ስለችግሩ ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ የቀረበ ቢሆንም፣ ምላሽ እንዳልተሰጠ ያስረዳሉ፡፡ በተለያዩ መንገዶች ጫና ሲደረግ የፌደራል መንግሥት የድርሻዬን ልወጣ ያለው በቅርቡ መሆኑንም ያክላሉ፡፡

በሌላ በኩል በሙላት ኢንጂነሪንግ የተሠራው ማሽን በቀላሉ አረሙን ለማስወገድ የሚያግዝ ነው ያሉት አቶ ሙላት፣ ከማሽን በበለጠ የሰው ኃይል በመባሉ ወደ ሥራ እንዳልገቡ  ይገልጻሉ፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ አልሠራም በማለት የተኮነነው የአማራ ክልል፣ በተለያዩ አስቸኳይ  ጉዳዮች ዝም ያለ ቢመስልም አረሙን ለማጥፋት አለመቦዘኑን አስታውቋል፡፡ የእምቦጭ አረምን ለማጥፋት ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑና የፌደራል መንግሥት እገዛ አስፈላጊነትም አፅንኦት ተሰጥቶታል፡፡

የጣና ሐይቅ ዳርቻ ዘላቂ መፍትሔ ፕሮጀክቶች ለመዘርጋት የታሰበ ሲሆን፣ እስከዚያ በሰውና በማሽን ችግሮቹን ለመቅረፍ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡ ሪፖርተርም በቦታው ተገኝቶ በሰው ኃይል የሚሠራው ሥራ አልፊና አሰልቺ መሆኑን ከመገንዘብ በበለጠ፣ አረሙ ተነቅሎ እዚያው የሚጣል በመሆኑ ዳግም እንደሚያንሰራራ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...