Wednesday, June 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሁለት የቴሌኮም ፈቃድ ለመውሰድ 12 ኩባንያዎች ፍላጎት ማሳየታቸው ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ሁለት አዳዲስ የቴሌኮሙዩኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ ኩባንያዎችን በጨረታ ለማስገባት የፍላጎት መግለጫ ካወጣ በኋላ፣ 12 ኩባንያዎች የፍላጎት መግለጫ ማስገባታቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዓርብ ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ከአውሮፓ፣ ከአፍሪካ፣ እንዲሁም ከእስያ ፓስፊክ የተውጣጡ ኩባንያዎች ለአንድ ወር በቆየውና ሰኔ 15 ቀን 2012 ዓ.ም. በተጠናቀቀው ቀነ ገደብ ውስጥ የፍላጎት መግለጫቸውን አስገብተዋል፡፡

ከኩባንያዎቹ መካከል ቮዳፎን፣ ቮዳኮምና ሳፋሪኮም የተሰኙት ኩባንያዎች  ‹‹ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በሚል ጥምረት ፍላጎት ሲያሳዩ፣ ኢቲሳላት፣ አግዢያን፣ ኤምቲኤን፣ ኦሬንጅ፣ ሳዑዲ ቴሌኮም ኩባንያ፣ ቴልኮም ኤስኤ፣ ሊኪድ ቴሌኮም፣ ስኔል ሞባይል በመደበኛ የቴሌኮም ኦፕሬተርነት ሥራ የሚታወቁ ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያን ገበያ ለመቀላቀል መፈለጋቸውን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ከኦፕሬተርነት ውጪ ባለው የቴሌኮም መስክ የሚታወቁ ካንዱ ግሎባል ቴሌ ኮሙዩኒኬሽንስና ኤሌክትሮሜካ ኢንተርናሽናል ፕሮጀክትስ የተባሉ ኩባንያዎች፣ በኢትዮጵያ ገበያ ፍላጎት እንዳደረባቸው አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ጎን ለጎን የቻይና ኩባንያዎች አለመሳተፋቸው ግርምት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ቻይና ሞባይል፣ ቻይና ቴሌኮም፣ እንዲሁም ቻይና ዩኒኮም የተሰኙ ዋና ዋና የመንግሥት ኩባንያዎች ሊሳተፉ እንደሚችሉ በሰፊው ተገምቶ ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም ጥያቄ ማቅረባቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

የቴሌኮም ሊባራላይዜሽን ሒደቱ አሁን የሚገኝበትንና ወደፊት የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሪፖርተር ያብራሩት የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማካሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር)፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፍላታቸውን እንዲያሳውቁ የተጋበዙት ኩባንያዎች ይህንኑ በማስታወቃቸው፣ አሁን በዝርዝር መነጋገር የሚቻልበት ምዕራፍ ላይ መገባቱን አስታውቀዋል፡፡  

በዚሁ መሠረት የኩባንያዎቹን አቅምና ብቃት ለመገምገም የሚቀርቡ መጠይቆች እየተዘጋጁ እንደሚገኙ፣ የብቃት መገምገሚያና ፈቃድ ለማግኘት የሚሰጡት ዋጋ የሚጠየቅበት ቅጽ እንደሚሰናዳ አስረድተዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን የቴክኒክና የፋይናንስ ጉዳዮች በማጠናቀቅ ጨረታውን የሚያሸንፉ ሁለት ኩባንያዎች እንዲገቡ የሚጠበቀው በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንደሚሆን ቢጠበቅም፣ የኮሮና ወረርሽኝ ባስከተለው መስተጓጎል ሳቢያ የጊዜ ሰሌዳውን ማስጠበቅ ሊያዳግት እንደሚችል ሥጋታቸውን ብሩክ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ለቁጥጥርና ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችሉት ሰባት ያህል መመርያዎች ከዚህ ቀደም እንደተዘጋጁለት፣ በአሁኑ ወቅትም ተጨማሪ አራት መመርያዎች እየተረቀቁለት እንደሚገኙ አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች