Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ የመሸጥ ሒደት እንዲቆም ጠየቀ

ኢዜማ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ የመሸጥ ሒደት እንዲቆም ጠየቀ

ቀን:

የመሬት ወረራንና የኮንዲሚኒየም ቤቶች ዕደላን የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታወቀ

ለሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተወዳዳሪነት ዋነኛ ሞተር የሆነውን የቴሌኮም ኢንዱስትሪ እንደ ተራ መረጃ ማስተላለፊያ ብቻ በማየት ለውጭ ድርጅት በከፊል ለመሸጥ በመንግሥት የተጀመረው መንገድ፣ ፍፁም አደገኛና የአገርን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቆም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ጠየቀ፡፡

ከዚህ ባለፈ ግን አሁን የሚወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች፣ ‹‹አሁን ካለንበት ችግር የሚያወጡን ብቻ ሳይሆኑ፣ የወደፊቱንም ትውልድ የምጣኔ ሀብትና ማኅበራዊ ነፃነቱን በምንም ዓይነት መልኩ አደጋ ላይ የማይጥሉ መሆናቸው መረጋገጥ አለበት፤›› በማለት ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪውን ለመንግሥት ከማቅረብ በዘለለ፣ ‹‹እንደ አገር በዚህ ወቅት የምንወስናቸው ውሳኔዎች ምን እንዲያመጡልን እንፈልጋለን የሚለውን በሰከነ መንፈስ ማየት ካልተቻለ፣ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አንድንም፤›› በማለት አሳስቧል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የኮቪድ 19 ወረርሽኝ አደጋ በኢኮኖሚያችን ላይ እያመጣ ያለውንና በቀጣይነት የሚያመጣውን ጫና በቅጡ ባላየንበት፣ እንደ አገር ተረጋግተን ወደፊት ለመጓዝ በምን መልኩ እንሂድ የሚለው ባልጠራበት፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን የመገንባት ሒደቱ ፈቀቅ ባላለበት፣ የአንዱ ኃይል የተደላደለ የሚለው የመፍትሔ መንገድ ለሌላው ኃይል ገደል እንደሆነ በሚታሰብበት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለመስማማትም ሆነ ላለመስማማት በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብሎ መወያየትና መደራደር እንደ ተራራ በገዘፈበት በዚህ ውዥንብርና ምስቅልቅል ሰዓት፣ የትኛውንም ዘላቂ ተፅዕኖ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ሕዝብን ሳያማክሩ፣ እንደ አገር የሚመለከታቸውን አካላት ሳያሳትፉ፣ ብሎም ሕጋዊ ቅቡልነት ሳያረጋግጡ ይህን ዓይነት ትልቅ አገራዊ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መንደርደር፣ እንደ አገር ያሉብንን ችግሮች ከማግዘፍና ከማወሳሰብ የዘለለ ሚና ይኖረዋል ብሎ ማመን ይከብዳል፤›› ሲል ኢዜማ ሥጋቱን ገልጿል፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ ይህን መሰል ዘላቂና የወደፊት የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ላይ ትልቅ ውጤት ያላቸው፣ እንዲሁም ወደፊት ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት እንኳን ሊያስተካክላቸው የማይችሉ ውሳኔዎችን የማስተላለፍ መብት በፍፁም የለውም በማለት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡  

የ21ኛው ክፍለ ዘመን የቴሌኮም ዘርፍ እንደ ጥንቱ በመገናኛና በመረጃ አስተላላፊነት ብቻ ሳይወሰን ወታደራዊ፣ የፋይናንስ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የፈጠራ ሥርዓቱን የመቆጣጠር ሚናው እየጎላ መምጣቱን የጠቆመው ኢዜማ፣ ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም አገሪቱ ውስጥ ካሉ የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች በእጅጉ አትራፊ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

በመሆኑም በየዓመቱ በርካታ ቢሊዮን ብሮችን አትርፎ ወደ መንግሥት ካዝና የሚያስገባው ይህ ድርጅት ዘንድሮ በስድስት ወራት ብቻ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፉን በመግለጽ፣ ‹‹ይህንን ድርጅት ወደ ግል ማዛወር ከተቋሙ የሚገኘውን ከፍተኛ ገንዘብም ማጣት እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፤›› በማለት፣ ዘርፉን በመሸጥ የሚታጣው ከፍተኛ ሀብት ከግምት ውስጥ መግባት እንደሚኖርበት አሳስቧል፡፡

በኢትዮ ቴሌኮም የሚሰጠው አገልግሎት በጥራትም ሆነ በብዛት ቅርብና ሩቅ ካሉ ተመሳሳይ አገሮች አገልግሎት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አናሳና ኋላቀር ነው የሚለው ኢዜማ፣ ነገር ግን ድርጅቱን መሸጥ ጥራትን ለማሻሻል ብቸኛ መፍትሔ ተደርጎ መታየት እንደሌለበትም ይሟገታል፡፡  

‹‹ገዥው ፓርቲ ይህን በአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው ስትራቲጂክ ሴክተር ላይ ሕጋዊ ቅቡልነትን ሳያረጋግጥ፣ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ቅድሚያ ሳይሰጣቸው፣ በቂ ጥናት ሳይደረግና የንብረቱ ባለቤት የሆነው ሕዝብና ወኪሎች ሳይመካከሩ ከየትኛውም ኃይል ይሁንታን ሳይጠብቅ በውጭ ጫናና ማባበያ የወሰነውን ውሳኔ በመቀልበስ፣ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ለመሸጥ እየሄደበት ያለውን ሩጫ በአስቸኳይ ያቁም፤›› በማለት ኢዜማ አሳስቧል፡፡

ኢዜማ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝርዝር መረጃ የያዘ በምጣኔ ሀብትና በአይሲቲ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ያዘጋጁትን ምጥን ፖሊሲ በሚቀጥለው ሳምንት ይፋ እንደሚያደርግ፣ ኅብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ እንዲያገኝና ከመንግሥት ግልጽነትን እንዲጠይቅ የሚገፉ ውይይቶችን በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ይደረጋሉ ብሏል፡፡ በምጥን ፖሊሲው ላይ የተለያዩ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ‹‹ዙም ዌቢናር›› እንደሚያዘጋጅም አስታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ ኢዜማ በአዲስ አበባ ከተማ በመሬት ወረራ፣ በኮንዶሚኒየም ዕደላዎችና ከተማዋን በግለሰቦች በጎ ፈቃድ የምትንቀሳቀስ የማስመሰል አካሄድ በጊዜ ሊታረም ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡ ኢዜማ የለውጥ ባህሪን በመረዳትና የሽግግር ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በመገንዘብ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የሚከናወኑ ሥራዎችን በአጽንኦት እየተከታተለ መቆየቱን፣ የከተማው ነዋሪዎች በመረጡት ተወካይ በሚተዳደሩበት ጊዜ ይፈታሉ ብሎ የሚያስባቸው ጥያቄዎች በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል በማሰብ፣ በከተማ ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች አባሎቹን ማደራጀትና የድርጅት አቅሙን ማዳበርን ዋነኛ ትኩረት ሰጥቶ ሲሠራ እንደቆየም የሚታወቅ መሆኑን አስታውቋል፡፡

‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከራሳችን መዋቅርም ሆነ ከከተማው ነዋሪዎች የሚያደርሱን ተጨባጭ የመሬት ወረራዎች፣ የኮንዶሚኒየም ቤትደላዎችና ከተማዋን በግለሰቦች በጎ ፈቃድ የምትንቀሳቀስ የማስመሰል አካሄድ በጊዜ ካልታረሙ፣ ቀድሞውንም ውስብሰብ የነበሩ የከተማዋን ችግሮች የሚያባብሱና በዜጎች መካከል የሚፈጥሩት ቅራኔ በቀላሉ የሚፈታ አይሆንም፤›› ብሏል፡፡

ይህንን ከግምት በማስገባት የኢዜማ ብሔራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቅዳሜ ሰኔ 13 ቀን 2012 .ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ከመሬት ወረራ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለነዋሪዎችማስተላለፍናማንኛውም የመንግሥት አድልኦ አሠራሮችን በተመለከተ መረጃ የሚያሰባስብና የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ እንዳቋቋመ አስታውቋል። ለዚህ ኮሚቴ መረጃ መስጠት ለሚፈልጉ ዜጎች በስልክ፣ በዋትሳፕ፣ በቴሌግራም፣ እንዲሁም ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ የኢሜይል አድራሻ እንዲያደርሱ ጥሪ አቅርቧል የተቋቋመው ልዩ ኮሚቴም የደረሰባቸውን ማስረጃዎች በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

‹‹በዚህ አጋጣሚ በሕገወጥ መንገድ በከተማዋ ነዋሪዎች ጥቅም ላይ የሚፈጸሙ የአድልኦ አሠራሮችና የመሬት ወረራ ላይ በየትኛውም ደረጃ የሚሳተፉ በየትኛውም የሥልጣን እርከን የሚገኙ የሥራ ኃላፊዎች ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ አውቀው፣ የእስካሁን ጥፋታቸውን እንዲያርሙና ከአሁን በኋላም ከዚህ ተግባር እንዲታቀቡ አጥብቀን እናሳስባለን። ሕዝቡ በሕገወጥ መንገድ የሚፈጸሙ የመሬት ወረራዎችንና ማናቸውንም የአድልኦ አሠራሮች በጥንቃቄ እንዲከታተል እየጠየቅን፣ ከእንዲህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊት ጋር በማንኛውም መልኩ ግንኙነት ያላቸው ንብረቶችን ከመግዛት፣ እንዲሁም በማንኛውም መልኩ ልውውጥ ከመፈጸም እንዲቆጠብ እናስገነዝባለን፤›› ሲልም አሳስቧል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...