በታደሰ ሻንቆ
6 – እኛ ከእርጉዟ ዓለም አኳያ
ኢትዮጵያ በዚህ ዕይታ ውስጥ ራሷን ከትታ ልማቷን ብትመራ፣ የአረንጓዴ ኢኮኖሚና ፖለቲካ ግንባታ መናኸሪያ ሆና በፍትሐዊ ልማት በነፃነትና በእኩልነት ግንኙነት የሚታነፀው የሕዝብ ሰላምና መልካም ኑሮ በአገሪቱ ውስጣዊ ሥራ ብቻ የማይሟላ፣ ቢያንስ አገራዊና ቀጣናዊ ፈርጅ የሚሻ መሆኑን መረዳትና በሁለቱ ፈርጆች የሚካሄደውን መስተጋብር ተወራራሽነት በቅጡ አውቆ በአገር ደረጃና በቀጣና ደረጃ መሥራት ይጠበቅባታል፡፡ ይህንን በስኬት ለመሥራት መቻል በተዘዋዋሪ ለአኅጉረ አፍሪካም አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ዛሬ ምን ያህል ዝግጁ ነን? ብዙ ጩኸት፣ ብዙ ንቁሪያ፣ ብዙ እሳትና ዕልቂት ባለበት ዓለም ሆድ ዕቃ ውስጥ ያለውን የግስጋሴ ዝንባሌ ምን ያህል ተረድተናል? እርግጥ “አረንጓዴ ኢኮኖሚ” ማለት ጀምረናል፣ በተግባርም እየሞካከርን ነው፡፡ ቀጣናዊና አኅጉራዊ ትብብርና አብሮ መልማት ይቀነቀናል፡፡ ግን አገራዊ የተባበረ ልማት ለማካሄድ የሚያስችል የተግባባ የዕይታ መሰናዶ እንኳ ገና የለንም፡፡
የአዲስ ዓለማዊ ለውጥ አቅጣጫ ጤናማ የአኗኗር ሥርዓትንና ባህልን መተለምና ወደዚያ ማምራትን ይጠይቃል፡፡ ይህንን መስመር የያዘ ልማት በግብርና፣ በማዕድን፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ አከታተም፣ በቤት አሠራር፣ በመጓጓዣ፣ በቴክኖሎጂና በኃይል ምንጭ ሁሉ የጊዜያዊነት ፋይዳ ያላቸውንና አዛላቂ የሆኑት እየለየ ዋናና መለስተኛ ትኩረቶቹን ይቀምራል፡፡ ቀላል ምሳሌ ለማንሳት ወደፊት ዋና ማትኮሪያችን የሚሆነው የግል ቤት ነው ወይስ የጋራ ቤት? በጭስ አልባ የኃይል ምንጭ የሚሠራ ቢሆን እንኳ ባለ አራት ጎማ የግል ተሸከርካሪ ወደፊት ዕድል አለው? ከ”ሠለጠነው” ዓለም መቅዳት ያለብን (ለነገው ዓለም ጭምር የሚበጀን) የቱ የቱ ነው? በዚህ ረገድ መርጦና ተልሞ መሥራት ይፈለግብናል፡፡
የዓለም ሀብትና ቴክኖሎጂዎች በጥቂቶች እጅ መሰባሰብና የዕጦተኛነት መስፋፋት፣ ዋና የቀውስና የጥፋት መፍለቂያ መሆኑን ቀደም ብለን ዓይተናል፡፡ የዓለማችን የተሳለጠ ለውጥ ይህንን ቀይሮ ቢያንስ ጉስቁልና አልባ ኑሮን (ከጤናማ የልጆች አስተዳደግ እስከ ፍሬያማ የትምህርት አሠለጣጠንና ጤናማ የሥራ ዕድል ድረስ) የሁሉ ሰው ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ሊብራሊዝምንና የ‹ነፃ ንግድ›ን ማምለክ ወደዚህ አቅጣጫ እንደማያደርስ ከተረጋገጠ ቆየ፡፡ የመንግሥት ቃኝነትና አነቃቂነት የግልን ፈጠራና የሥራ ከፈታ እያፍለቀለቀ ፍትሐዊ የኅብረተሰብ ግስጋሴንና ተጠቃሚነትን እየጨመረ እንዲሄድ እንዴት ማድረግ እንደሚቻል፣ ማሰብና መርሐ ግብርን መቀየስም የማይታለፍ ነው፡፡ የመንግሥት ወጪ፣ የግብርና የቀረጥ ሥርዓት ከኢኮኖሚው ግስጋሴና ከማኅበራዊ ዋስትናዎች (የጤና፣ የሥራ፣ የትምህርት፣ ወዘተ. ዋስትናዎች) ጋር እንዴት መግባባት ይችላል? ዴሞክራሲ ከጥቂት ፓርቲዎች መጫዋቻነት ተሻግሮ እስከ መንደር ድረስ ሥር የያዘ የሕዝቦች ሱታፌ እንደምን መሆን ይችላል? ከወደፊት ዘመን ጋር የሚራመዱ ፓርቲዎች የአስተሳሰብ ሸንተረሮች የሚፈለቀቁት፣ የዚህ ዓይነት ጥያቄዎችን የሚያነሳና ለመመለስ የሚሞክር መስመር አካባቢ ላይ ይመስላል፡፡ ብዙዎቹ የእኛ ፖለቲከኞች ግን ይህን ፊታቸው የተገሸረ ፈተና በቅጡ ያስተዋሉ አይመስሉም፡፡ ቀደም ሕወሓት/ኢሕአዴግ የአንድ ፓርቲ አውራ ገዥነትን የሚያፀደቅ ራሱን በራሱ እንደ ሕዝብ ተወካይ እየሰበሰበ፣ እየተናገረ፣ እየወሰነ በስመ ሕዝብ ይቆምር የነበረውን “አብዮታዊ ዴሞክራሲ”ን ለመቃረን ይዘውት ከነበረው “ርዕዮተ ዓለማችን ሊበራሊዝም ነው” ከሚል ወገኝነት የዘለሉም አይመስሉም፡፡
እንደ መላ ዓለም፣ እንደ አኅጉር፣ እንደ ቀጣናና እንደ መላ ሰው ማሰብና መተጋገዝን በሚጠይቀው በዛሬው ዘመን ውስጥ እንደ አገር ማሰብ እንኳ የተቸገርን ነን እኛ፡፡ አካባቢያዊ የራስ በራስ አስተዳደርን የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ልዕልና አድርጎ ከመረዳት ይልቅ፣ የብሔርተኞች ጎጣዊ ይዞታ አድርገው የሚያስቡ፣ ከብሔርተኛ ቡድን አልፎ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ መፍጠር መከራ የሆነባቸው፣ ለብሔርተኛ ቡድናዊ የጌትነት ጥማታቸው የብሔረሰቦችን መብት መሣሪያ ለማድረግ ሲሉ፣ የብሔረሰቦችን መብት መረጋገጥ ከብሔር ፓርቲነት የማይነጣጠል አድርገው የሚያጭበረብሩ (ጥላቻን እንኳ ማሸነፍ ያልተሳካላቸው) ቡድኖች፣ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሜዳ ዛሬም እየተመናቀሩበት ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ብሔርተኞች የተቃረኑ መስሏቸው ኢትዮጵያንና የግል መብትን ያጠበቁ ግን የኢትዮጵያን እውነታ መረዳት የከበዳቸው ቡድኖች፣ “የብሔር መብት” የሚባል ነገርን የሸሸና ከኩረጃ የተለቃቀመ ፕሮግራም ይዘው ደንበር ገተር ይላሉ፡፡ አንዳንዶችም “የብሔር ሉዓላዊነት” የሚባልን ነገር የመከቱ መስሏቸው፣ ሉዓላዊነትን ግለሰባዊ አድርጎ እስከ ማሰብ ተስፈንጥረዋል፡፡
በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን ዛሬ ያለው የኢትዮጵያ “ፓርቲያዊ” ፖለቲካ በአያሌው በመንጠራወዝ፣ ባስ ሲልም በመጠራሞት ላይ ያለ ነው፡፡ “ቅንጅት” እና “ኅብረት” ይባሉ የነበሩት የ1997 ዓ.ም. ጊዜ ቡድኖች እንደ ህልም ታይተው ከፈራረሱ በኋላ የተቋቋመው “መድረክ”፣ ከቅንጅት መሰነጣጠቅ ውስጥ ነፍስ አለው የተባለውን “አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ” ቡድን (አንድነትን) ከብሔርተኛ ቡድኖች ጋር ሲያቀናብር፣ ስዬ አብረሃና ነጋሶ ጊዳዳ ብሔርተኛ ቡድንተኝነትን ጥለው “አንድነት” ቡድን ውስጥ ሲገቡና ወዲያው የአመራር አካል ሲሆኑ፣ በ‹አንድነት› ተኮርነትና በ‹ብሔር› ተኮርነት መሀል ለው ገደል መገናኛ ድልድዩን ያወቀና መገንባት የጀመረ መስሎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከብሔርተኞች ጋር መቀላቀልንና መጎዳኘትን በሚደግፉና በሚቃውሙ መሀል የአንጃ ሽኩቻ ታሪክ ለመጀመር ጊዜ አልወሰደበትም ነበር፡፡ ቅልቅሉና ጉድኝቱ ውህድ ፓርቲ ለመፍጠርም ሆነ ግንባር ለመሥራት መሠረት የሚሆኑትን የጋራ አካፋዮች ጥርት አድርጎ አልፈለቀቀም ነበር፡፡ እስከ ዛሬ የትግል ዝምድና እንዳንፈጥር ያደናቀፈን የእኛ እንከን/ጥፋት ምን ነበር በሚል ጥያቄ ራስን መመርመርና የየራስን ገመና ማየት፣ በብሔርተኞችም የአንድነት አፍቃሪ ነን በሚሉትም በኩል አልነበረም፡፡ እንዲያውም “የአንድነት ወገኖች” ራሳቸውን እንከን የለሽ፣ ከብሔርተኛ ቡድነኝነት የመጡትን እነስየ አብረሃን ከስህተተኛነት የመጡና ይቅርታ ጠያቂ አድርጎ እስከ መቁጠር ድረስ ጭንቅላት አጥተው ነበር፡፡ ይህንን ግልብነት አልፎ የኢትዮጵያን የፖለቲካ እውነታ በቅጡ ተረድቶ ሁለቱም ጎራዎች የሳቷቸውን የመብቶች ተዛማጅነትና ተመጋጋቢነት አንጥረው ሊያወጡ ባለመቻላቸው፣ ለሌሎችም ምሳሌና ብርሃን መሆን አልቻሉም፡፡ ከአንድነት ውስጥ የመጀመርያው የግትሮች አንጃ ተቦጭቆ ቢወጣም ቀሪዎቹ ወደ ጉልምሳና አልተሸጋገሩም፡፡ ተንጠውና ታምሰው እነ ስዬና ነጋሶ ጊዳዳ ከ‹አንድነት› ጋር መለያየታቸው፣ የ‹አንድነት› ቡድንም ከመድረክ ጋር መለያየቱ ውሎ አድሮ አልቀረም፡፡
ንጠቱ ከተካሄደ ባልሳሳት አሥር ዓመት ገደማ ሆነው፡፡ ግን እስከ ዛሬ ድረስ መድረክ ቆሞ ቀር ከመሆን ወጥቶ የኢትዮጵያ አንድነት አፍቃሪ ነን ባይ ቡድኖችን መሳብ የሚያስችል የፖለቲካ አተያይ፣ የትንታኔና የአንቂነት ዕድገት ማድረግ አልቻለም፡፡ “የአንድንት” ኃይል ነን ባዮችም የኢትዮጵያ እውነታ እንደገባቸው የሚያሳይና የብሔርተኞችን ካብ ሰብሮ መሳብ የሚያስችል የፖለቲካ ዕድገት አላሳዩም፡፡ “የአንድነት” ኃይሎች ብሔርተኞች ውስጥ ያለውን የአንድነት ፈርጅ አስተውለው እንዴት እንጨብጠው የሚል ሥራ እንኳ ማከናወን አልቻሉም፡፡ የብሔር መብት በኢትዮጵያ ምድር ከአንቀጽ 39 እና በብሔርተኛ ፓርቲ ከመሰባሰብ ጋር የተጣበቀ እንዳልሆነ፣ ከግልና ከዜግነት መብቶች ጋር የማይጣላ መሆኑን አጢነው ለሌላውም ማስጤንንማ በየትኛው የአመለካከት ስፋት ሊደርሱበት!! እና ጎራዊ ልዩነቱ የማይነቃነቅና የማይፈልስ ሆኖ ኖረ፡፡
“የአንድነት” ኃይል ነን ባዮቹ “በኢትዮጵያ አንድነት አንደራደርም” ከምትል ክር በቀር የሰፋ የፖለቲካ ወርድ ሳያበጁ፣ እሷኑ እያላመጡና እየተሰነጣጠቁ ከአንዱ አንጃ ወደ ሌላ አንጃና ቡድን እየተወዛወዙ፣ ከመቀላቀላቸውም እየተፈነጋገጡ እስከ ዛሬ መንጠራወዛቸውን ቀጥለዋል፡፡ የመኢአድ ታሪክ፣ የአንድነት ፓርቲ፣ የሰማያዊ፣ የኢዴፓ፣ ወዘተ. ታሪክና ህልውና ሁሉ (በአቋም ትባትም በብሔረ ብዙ ዝንጉርጉርነትም ረገድ) በድህነት መንጠራወዝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ፍላጎት የማንፀባረቃቸው ነገር ከስምና ከምኞት አላለፈም፡፡ መድረክ የኅብረ ብሔራዊ ፖለቲካ ተስፋ ይሆናል ሲባል፣ የድጋፉ ዝንጉርጉርነት እየደበዘዘ ከመንጠራወዝ ወደ መጠራሞት ያቀና ይመስላል፡፡ ዛሬ ባለበት ደረጃ እንኳን ሌሎችን እየጨመረ ሊደረጅ ቀርቶ ያሉትንም ነባር ድርጅታዊ አባሎቹን ይዞ መቆየቱ ያጠራጥራል፡፡ መድረክ ውስጥ ያለው ጉልሁ ቡድን ኦፌኮ ኦሮሞን ከጥላቻና ከዱለኛ ፖለቲካ የማላቀቅ ተፅዕኖ ለማሳደርና ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን አማርኛ ተናጋሪ ውጥንቅጥ ሕዝብ በፖለቲካው ለመሳብ አለመቻሉን ድክመቴ ብሎ ሊያፍር ቀርቶ፣ የ28 ዓመታት የብሔር አንጓላይነት የወለዳቸው ወጣቶች ነፍጠኝነትን ካሞካሹ ወዲህ የኋሊት 19ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ ተሽቀንጥሮ የነፍጠኛ ሥርዓት በደልን ከማንጎላጨት በላይ፣ ለዛሬው ዘመንም ነፍጠኝነትን አደጋዬ እስከ ማለት ቅዠት ማውራት ጀማምሮታል፡፡ ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞችም ይህንን አሮጌነት ተሻግሮ 21ኛው ክፍለ ዘመን ውስጥ የገባ የፖለቲካ ዕይታ መሰናዶ የላቸውም፡፡
በፖለቲካ ማደግና መገናኘት የተሳናቸው የ‹አንድነት›ና የብሔር ፖለቲከኞች በሚንጠራወዙባት ኢትየጵያ ውስጥ፣ የብሔር መብትንና የአገር አንድነትን አስማምቶ የሁለቱን ጎራ የሰበረው በእነ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እየተመራ ከኢሕአዴግና ከ‹አጋሮች› ስብስብነት ወደ ብልፅግና ፓርቲነት የተቀየረው ግዙፍ ቡድን ነው፡፡ ወደ ወጥ ኅብረ ብሔራዊ አተያይ የተደረገው ሽግግር ገና አዲስ እንደ መሆኑ፣ ዝንጉርጉርነትን ወደ አላላሰ ኅብራዊ እኛነት የመድረሱ የባህሪ ለውጥ (ሜታሞርፈሲስ) ገና ጥሬና ብስል ነው፡፡ የልውጠቱ ሥምረት ብዙ ቃርና ደንበር ገተር ሊኖርበት፣ ብዙ ገለፈት መግፈፍ ሊጠይቅም ይችል ይሆናል፡፡ ይህንን የልውጠት ፈተና ከአዲስ መጥነት ይበልጥ ከባድ የሚያደርጉ ሁለት የተያያዙ ሰበዞችም አሉ፡፡
አንደኛ ከ1983 ዓ.ም. የሕወሓት/ኢሕአዴግ ድል ጀምሮ በአትዮጵያ ፖለቲካና አገዛዝ ላይ የነገሠው ክፍልፋይ ብሔርተኝነት፣ የአንድ አገር ዜጎችን በብሔረሰብ ማንነታቸው ቤተኛና ባይተዋር አድርጎ ከፍሎ ባይተዋር ባላቸው ላይ ልዩ ልዩ በደል ሲፈጽምና ሲያስፈጽም መኖሩ፣ ትንሹም ትልቁም የቀመሰውና ያወቀው እውነታ ነው፡፡ የበደል ምንጩም ራሱ ብሔርተኛነት መሆኑ ትንሽ ልጅ ቢጠየቅ የሚመልሰው ዓይን የሚወጋ ሀቅ ነው፡፡ ክፍልፋይ ብሔርተኝነት የበደል መፍለቂያ ሊሆን የቻለውም የራሱን መገኛ ብሔር/ብሔረሰብ የእኔ ብሎ አቅርቦ፣ ሌላውን ስለሚያርቅና መጠቃቀምን በብሔር ውስጥ አጥብቦ ንቃትና ተግባር ስለሚያደርግ፣ በዚሁም መሠረት አድሎኛ ሕግ፣/ደንብና መመርያ እስከ ማውጣት ድረስ ስለማያፍር ነው፡፡ ሀቁ ይህን ያህል በተግባርም በሰነድም ግጥጥ ብሎ እያለ ዛሬም ብሔርተኝነትን እንደ ሃይማኖት የያዙ ፖለቲከኞች የርዕተ ዓለማቸውን የመድልኦ ምንጭነት በማመን ፈንታ በደል ሊደርስ የቻለው ዴሞክራሲ ባለመኖሩ ነው እያሉ ይሸመጥጣሉ፡፡ ዴሞክራሲ አልባነት ለዚህ ዓይነት በደል ምንጭ መሆን አለመሆኑን ለማጣራት ወደ ደርግ ዘወር ብሎ ኅብረተሰቡ በየአካባቢው ባለቤት ብሔርና መጤ ተብሎ ታምሷል ወይ ብሎ መጠየቅ ብቻ ይበቃል፡፡ ወደ ደርግም መሄድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ብሔረተኞቹ ዛሬም በራሳቸው ደጋፊዎችና በብሔርተኛ ቢጤዎቻቸው የሚካሄደውን አንጓላይነት፣ ማፈናቀልና ወርሮ ማጥቃት ለማስተዋልና ለመታገል መፍቀድ ነው፡፡ ከአንጀት እስኪመክን ሊታገሉት ከተነሱ ያለ ጥርጥር ራሳቸው ከሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ጋር መቃረናቸው አይቀርም፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ ሥሩን እስካልነኩት ድረስ ደግሞ ትግላቸው በአረም የሚመለስ ከመሆን አያልፍም፡፡ ቤተኛና ባይተዋር ብሎ ዜጎችን የሚያቀርብና የሚያርቅ ብሔርተኝነት ከዴሞክራሲ ጋር ቢገናኝም፣ በግልጽም በሥውርም ላዳላ እያለ ከዴሞክራሲ ጋር መጋጨቱ አይቀርም፡፡ ዴሞክራሲ መድልኦን ለመታገልና ለመጠየቅ መድረክ ይሆናል እንጂ፣ በብሔርተኝነት ውስጥ ያለውን አድሎኛ የአመለካከት ነፍስ አይነቅልም፡፡ ሁለቱ አብረን እንኑር ካሉ ወይ ዴሞክራሲ ብሔርተኛ አድሏዊነትን እያራወጠ ደብዛውን ያጠፋዋል፡፡ ወይ ብሔርተኛነት ዴሞክራሲን እንደ ቀበኛ በልቶ በቀፎው ያስቀረዋል፡፡ ወይም ብሔርተኛ የተወሰኑ አድሎዎችን ሕጋዊ ለማድረግ ችሎ ዴሞክራሲም ተቋማዊ ህልውና አግኝቶ፣ አድሎውን በወደዱና ባልወደዱ ኃይሎች ትንንቅ ምክንያት ከጊዜ ጊዜ የፖለቲካ ሰላም መታጣቱ አይቀርም፡፡ ብዙ የፖለቲካ ቡድኖች በብሔርተኝነት ውስጥ መንቦጫረቅን ሙጥኝ ያሉት፣ በአገራችን የተከመረው ልምድ ይህችን ታህል ግንዛቤ ለመጨበጥ አንሷቸው ነው? ወይስ አድልኦን በግልጽም በሥውርም አቋቁመው ለመግዛት ስለሚፈልጉ?
ሁለተኛ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና ባላቸው የአማራ፣ የኦሮሞና የትግራይ ልሂቃን ዘንድ ሥር የሰደደ የአስተሳሰብ መቦዝና ጠምዛዛነት መኖሩ ሁነኛ የአገሪቱ ቁርጠት ነው፡፡ በክፍለ አኅጉራዊና አኅጉር ገብ ዕይታ የታጀበ ኅብረ ብሔራዊ አዕምሮ ያለውን የአሁኑን ልውጠት የኦሮሞ ልሂቃን በዋናነት ይምሩት እንጂ፣ የኢትዮጵያ ማኅበረሰባዊ የብዝኃነት ካርታ የትኛውም ጥግ ድረስ ኦሮሟዊ መሰረጫጨት የተካሄደበት (ኦሮሞነት የኢትዮጵያነት ሥዕል ዋና ወዘናና እርግብግቢት የሆነበት) ታሪክ የተከናወነ እንደ መሆኑ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦችን አንድ ላይ ይዤና አስማምቼ እንደምን ኢትዮጵያን ላንሳት የሚለው ጉዳይ የኦሮሞ ልሂቃን ትርታ መሆን ተፈጥሮዊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይህን ኢትዮጵያነትና ኦሮሞነት የተላላሱበትን እውነታ ስተው፣ የኦሮሞን ነፃነት ያለ ኢትዮጵያ ለማግኘት የሚፈልጉ፣ ኦሮሞነት በገዳዊ ጎዳና ውስጥ ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገር ሠርቶ ሳለ የኦሮሞ መሬት ከዚህ እስከዚህ ነው፣ እነዚህ እነዚህ ሥፍራዎች የኦሮሞ ናቸው እያሉ የሚብከከኑና የበቀልና የጥላቻ ልሂቃን መበርከታቸው ከየትኞቹም ብሔርተኞች በላይ መወቀሻቸው ነው፡፡
ታሪክ ያላላላሰው በተለይም ኦሮሞነት ያላቀለመው የጠራሁ ነኝ የሚል ብሔረሰብ በኢትዮጵያ የለም፡፡ በጥራት የለሽነትም ኦሮሞንና አማራነትን የሚያክል የለም፡፡ ዛሬ ባለ አማራነት ውስጥ የሸዋ፣ የጎጃም፣ የወሎም ሆነ የጎንደር አማራነት ውስጥ በአያቴ በእናቴ በአባቴ እያለ ከሌላ ብሔረሰብ ጋር (በተለይ ከኦሮሞ፣ ከአገውና ከትግሬ ጋር) ትውልዱን የሚያጣቅስ ሰው ማግኘት ከባድ አይደለም፡፡ በሌላ አባባል አማራነት በብዙ መልኩ፣ ልዩ ልዩ ማኅበረሰባዊ ዝንቆች አማርኛ ተናጋሪ እየሆኑ የመምጣት ታሪካዊ ጉዞ ሆኖ ሳለ የአማራነትን ታሪክ እስከ ጥንት፣ ከጥንትም እስከ ዘመነ አዳም የገነት ወንዞች ድረስ የሚያደርሱ “ልሂቃን” ብቅ ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ብዙ የንግድና የማኅበረሰቦች እንቅስቃሴ መናኸሪያ የነበረውን የአክሱም ሥልጣኔን፣ ዛሬ በአካባቢው ካለ ብሔረሰባዊ ማንነት ጋር አጣብቀውና የትግራይ ይዞታ አድርገው የሚመለከቱ ብሔርተኞች አሉ፡፡ ይህም ብቻ አደለም፡፡ ትግሬነት ከትግራይ አካባቢ አልፎ እየተንቀሳቀሰና እየሠራ የመላ ኢትዮጵያን ጓዳና ጎድጓዳ የዕትብቱ መቀበሪያ አገሩ አድርጎ ብዙ ትውልድ የኖረ ሆኖ ሳለ፣ ሕወሓት ከአዲስ አበባ የሥልጣን ጌትነት ከተንሸራተተ በኋላ ይህን እውነታ በመርገጥ ትግራይን ለመቁረጥ የሚንቆራጠጡ የዱርዬ ፖለቲካ ክንፎች የብጥበጣ አንደበታቸው ረዝሟል፡፡ እነዚህ አኩራፊዎች ከግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የጀመረው ሕወሓታዊ የሥልጣን አገነባብ ብልሽቱንና ጠንቁን በነባራዊነት ገምግሞ መማሪያ በማድረግ ፈንታ፣ ሥራዬ ብለው የተያያዙት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን የተወራረሰ ዝምድና መመነጫጨር ነው፡፡ የሕወሓት አዲስ አበባ መግባትና የትግራይን ትግልና ድል የኢትዮጵያ ትግልና ድል አካል አድርጎ ማየት ልክ መሆኑን ማጤን ከባድ አደለም፡፡ በዚህ የአስተሳሰብ ግቢ ውስጥ ሆኖ ሕወሓት የሥልጣኑን ድል በራሱ ቡድንና በአሻንጉሊቶቹ መዳፍ እንዲወድቅ ማድረጉ፣ የአገዛዙንም የሥልጣን ኃይል አከርካሪ በተጋዳዮች ማዋቀሩና ይህንንም የአፈና አገዛዙ መገልገያ ማድረጉ፣ በትግራዊነት ላይ ድፍርስ ስሜት እንዲፈጠር መዘዝ መሆኑን ማስተዋልም የረቀቀ ዓይን አይጠይቅም፡፡ ብዙ ጊዜም ተተንትኗል፡፡ የሕወሓትን ተጋድሎ ያበለዙት ግን ያለፈ ጥፋትን ዓይቶ ከመቀበልና ከመስተካከል ጋር ጉዳይ የላቸውም፡፡ የእነሱ ጉዳይ ልባቸው የቆመበትን ፍላጎት በየትኛውም መንገድ አቆራርጦ ማሳካት ነው፡፡
ለዚህ ነው እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ “በኢትዮጵያ የብሔረሰቦችን እኩልነትና ዴሞክራሲን አምጥተናል. . . የቡድን (የሕወሓት) የበላይነት አልነበረም” የሚል ዓይነ ደረቅነታቸውን ያለ ኃፍረት ያጠበቁት፡፡ የሕወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ከፌዴራላዊ ቅርፁ በቀር በአፈና ይዘቱና በፕሮፓጋንዳ ሥልቱ፣ እንዲሁም በካድሬዎቹ አማካይነት ራሱ እየተናገረና እየወሰነ፣ “ሕዝብ ተናገረ/ሕዝብ ወሰነ” በሚል መልቲነቱና “ያለ እኔ መሪነትና ፖሊሲ አማራጭ የለም” በማለቱ ካሁኑ የዓብይ መንግሥት ይበልጥ ለደርግ ኢሠፓ ቅርብ የነበረ ሆኖ ሳለ፣ “ደርግ ኢሠፓ መጣላችሁ!” እያሉ ወደ እነ ዓብይ መንግሥት ጣት መቀሰሩም የዓይነ ደረቅ ውሸታምነታቸው ሌላ ፈርጅ ነው፡፡ “የትግራይ ሕዝብ ተከቧል፣ ሊወረር ነው፣ ሊያንበረከኩት ይሻሉ” የሚለው ቅጥፈትም የማፈንገጥ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል በእውነታ ላይ የተካሄደ ቁልመማ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሃሳዊ ቁልመማ እውነት መስሎ ሕዝብን እንዲያሳምን ደግሞ፣ ከሕወሓታዊ ገዥነት ጀምሮ የሠለጠኑበት ዘዴ፣ ሐሰት ሐሰትነቱ እንዳይታወቅ በመልቲ ሎጂክ ማሳመርና መተንተን፣ እርር ቅጥል ባለ “የሕዝብ ተቆቋሪነት” ስሜትና በልበ ሙሉነት ዕጣን በደንብ እያጠኑ ማቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የፍጅት አርማጌዶን እንዲፈጠር ነገር እስከ መሥራት መረን የተወጣው፣ “ሕወሓት በድል አዲስ አበባ መግባቱ መሆን ያልነበረበት፣ አለ አገሩ ምን ሊያረግ? ከትግራይ ማለፍ አልነበረነት…” እስከ ማለት ዛሬ የተደረሰውም ለሕዝቦች ዝምድና ደንታ ከማጣት ነው፡፡ አገውነትንና ቅማንትነትን ከአማራነት ለይቶ ለማጥለል የሚደረግ ሙከራም፣ እነሱው በመብት ስም ወስውሰው ያስከተሉት ውጤት ነው፡፡
ደግነቱ አኩራፊዎቹ የትግራይን ሕዝብ ዕድል የቡድን ፍላጎታቸው መጫወቻ እንዲያደርጉት አንፈቅድም የሚሉ ተቃዋሚዎች እንደ “ትዴፓ”፣ “አረና ትግራይ”፣ ወዘተ. ያሉ አለመታጣታቸው ነው፡፡ በተለይ በግንቦት ሃያዎች 2012 ዓ.ም. ውስጥ በ”ኤል ቲቪ” ሰፊው ምህዳር ፕሮግራም ላይ ንቁ ታጋዩ ይሳቅ ወልዳይ እንደተናገረው፣ የ‹ፈንቅል› ትግል እምብርታዊ ጥያቄ ከራስ ብሔር በተገኘ ቡድን በመገዛትና ራስን በራስ በማስተዳደር መካከል ያለውን ልዩነት ያወቀ፣ የሕዝብ የራስ አስተዳደርም ያለ ዴሞክራሲ እንደማይጨበጥ የተረዳና ለዚሁ የሚታገል መሆኑ፣ ለትግራይም ለሌሎቹም የኢትዮጵያ ሕዝቦች እሰየው ነው፡፡ የብልፅግና ፓርቲም የዚህ ጉዞ ሞገስ መሆን ከፈለገ ከአኩራፊዎች ጋር አፍ ከመካፈት ይበልጥ፣ ወዶ ገብ ተሳታፊነትን በሚያፈካ ሥልት ለውጡን ማራመድ ላይ ቢያተኩር ይመረጣል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን እያድፈቀፈቀ፣ የሰው ልጆች የህልውና ደኅንነት በዓለም ደረጃ እጅ ለእጅ ተያይዞ አረንጓዴ ዓለምን መገንባት የሚሻ ስለመሆኑ እየጎሰመ ካለው የለውጥ ነጋሪት አኳያ የእኛ ፖለቲከኞች የትና የት በዕይታና በዓላማ ርቀው (ከጥፋት መማር ለምኔ ብለውና ተበጣጥሰው እንዳሉ) ከላይ የቀረበው የድክመት ሀተታ በቂ ማሳያ ይመስለኛል፡፡
7ኛ – የኢትዮጵያ አረንጓዴ ፖለቲከኞች ተግባራት
ዓለማዊ ለውጡ በቅርቡ ድራማውን ይጀምርም አይጀምርም፣ አንድ ሁለት እያለም ቢሆን (ዶናልድ ትራምፕን ከመሰለ አብጤና “የአሜሪካ ህልም” ከሚባል መስተፋቅር ጋር ልብስ እየተጋፈፈም ቢሆን) ወደዚያ አቅጣጫ ማምራቱ ግን አይቀሬ ነው፡፡ ምናልባትም በኮሮና ወረርሽኝ አያያዛቸው ክፉኛ የተሳጡትና የፖለቲካ ኪሳራ የደረሰባቸው አገሮች የግል ሀብት ሩጫ ዋና አምባ የሆነችውና የዓለም ሀብት ቅርምትን 24.4 በመቶ የያዘችው አሜሪካ፣ ብሪታኒያ፣ ጣሊያን፣ ብራዚልና መሰሎቻቸው እንደ መሆናቸው፣ የዓለም የለውጥ ዓይን በአገሮች ደረጃ በደቡብ እስያና በሰሜን አውሮፓ ሶሻል ዴሞክራሲ አገሮች የሶሺዮ ኢኮኖሚ አደረጃጀት መሀል የሚባዝንና የሚሳሳብ ገጽታ ሊኖረው፣ ምናልባትም ከሶሻል ዴሞክራሲ ጋር ዓለም የበለጠ ፍቅር ይይዘው ይሆናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ቀጣናዊ ትስስርን ያስተዋለ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትልምና መንግሥታዊ እንቅስቃሴ የተጀማመረ ቢሆንም፣ የአገር ልጆችን ህሊና የከታተፈውን ብሔርተኛ ቁርጥራጭነት አሸንፎ ከሶሺዮ ኢኮኖሚ ኑሮ እስከ ፖለቲካ ድረስ አረንጓዴ ወደ መሆን ደረጃ መድረስ ከባድ ሥራን የሚጠይቅ ነው፡፡
አረንጓዴ አኗኗርና አረንጓዴ ፖለቲካ ግጭትና ጦርነትን፣ ብክለትና ውድመትን ሲኦል ቀረሽ ትርካሞ ሠፈሮችና ቸነፈሮች የማይወልድ፣ የምድሪቱን ደኅንነት ከሰው ልጅ ደኅንነት ጋር ያስማማ ሕይወትን የሚገልጽ እንደመሆኑ፣ ይህ ዓይነቱ ሕይወት በአገር ውስጥ ደረጃ ዝቅተኛ ፈር ማበጀቱ እንኳ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ ይችን ታህሏ ስኬትም ብትሆን የማይተናኮል ዓለማዊ ዝንባሌን ትሻለች፡፡ በክፍለ አኅጉራዊ አካባቢ ደረጃም አጋዥ መስተጋብርን ትፈልጋለች፡፡ ይህ ግን በመጠበቅ አይገኝምና የሚቻለውን ያህል የውስጥና የአካባቢ ሁኔታን በመግራት ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግን ከወዲሁ መጀመር ይፈልጋል፡፡ በዚህ ረገድ ለኢትዮጵያ አረንጓዴ ፖለቲከኞችና ልማተኞች ሦስት ተቀዳሚ ተግባራት ከፊታቸው ተደቅነዋል፡፡
1ኛ) – በአገር ውስጥም በውጪም ያሉ (በተለያዩ አደረጃት ውስጥና በየግል የሚገኙ) የአረንጓዴ ፖለቲካ ወገኖች ሁሉ ፈርጅ የገባ ትብብርና ሰፊ እንቅስቃሴ መፍጠር፣ ፍትሕ ዴሞክራሲና ሰላም የኢትዮጵያ ሕዝቦች የህልውና ጉዳይ መሆኑ፣ በአገር ውስጥ ደረጃም በክፈለ አኅጉራዊ ቀጣናም ውስጥ ኢትዮጵያ የምታተርፈው ከግጭትና ከጦርነት ርቆ በውይይት በድርድርና በመግባባት፣ ከመሥራትና በፍትሐዊ መተሳሰብ ተባብሮ ከማደግ መሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብሔራዊ መግባቢያ እንዲሆንና የአገሪቱ መንግሥት ፅኑ ፖሊሲ እንዲሆን መሥራት፣ ይኸው አቋም በምሥራቅ አፍሪካም በአኅጉር ደረጃና በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ መታወቂያ እንዲሆን ማድረግ፣ በዚህ ላይ ተመሥርቶና በአፍሪካና በዓለም አቀፍ መድረክ የሚገኘውን ድጋፍ ከጀርባ አድርጎ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መሀል የተያዘው ድርድር ያለ ልዕለ ኃያላዊ በጥባጭነት ፍሬያማ እንዲሆን መሥራት፡፡
በዓባይ ጉዳይ ላይ የተያዘው ድርድር ፍሬያማነት ቀደመም ተከተለ፣ የኮሮና ወረርሽኝን በሰፊ ርብርብ አዳክሞ፣ ተጓጉሎ የቆየውን አገር አቀፍ ምርጫ በቶሎ በሰመረ አኳኋን ማከናወንና ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊነትና ፌዴራላዊነት ከአረንጓዴ ፖለቲካ ጋር ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈክቶ መውጣቱን ማረጋገጥ፡፡
2ኛ) በድኅረ ኮሮና ወረርሽኝ ዓለማችን ውስጥ ያለው ዓለማዊ ሥርዓት የተወሰኑ የአኗኗርና የአሠራር ሥልቶችን እንደሚቀይር ብዙ ግምት አለ፡፡ በልዕለ ኃያላዊ ኃይልና ሚናዎች ለውጥ ምክንያት እንደ ተመድ ባሉ የብዙዮሽ ተቋማት ውስጥ በአደረጃጀትና በአወሳሰን፣ በገንዘብ አመነጫጨትና አዋዋል ረገድ የተመጠኑ ለውጦች ይደርሱም ይሆናል፡፡ ከዚያም ያለፈ ንዝረት የሚፈጥር ለውጥ ይታይም ይሆናል፡፡ ስለዓለም የተሳለጠ አደረጃጀት ትኩረት የማረኩና ንፋስ የፈጠሩ ንድፈ ሐሳቦችና እንቅስቃሴዎች ቦግ ብለው ሊወጡ ይችሉም ይሆናል፡፡ የረባ የለውጥ ዝንባሌ መጣም አልመጣም የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አኗኗርና የአረንጓዴ ፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ዛሬን በነገ ዓይን ለማሰናዳት ከትናንትና፣ ከእስካሁኑ ልምድ ብዙ የሚማሩት አለ፡፡
የ1960ዎቹ ወጣቶች የነበርንበት ዘመን በዕድገት ወደ ኋላ የቀሩ ሕዝቦች ትግል በማርክሳዊ፣ በሌኒናዊና በማኦዋዊ አስተሰሰቦች በእጅጉ የተሳበበት ጊዜ ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም ያላቸው መጻሕፍትን በቀላሉ ማግኘት በማይቻልበት የቅድመ 1966 ዓ.ም. ሁኔታ ውስጥ በአገራችን የነበረው የወጣት ተራማጅነት ምን ያህል ጥልቅ ንባብ እንደነበረው መናገር ባልችልም፣ “ፋኖ ተሰማራ. . .” የሚለው ዝነኛ መፈክራቸው እንደሚጠቁመው በኩባ፣ በቬትናምና በቻይና የትጥቅ ትግል የተማረከ ነበር፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች በውጭ ለትጥቅ ትግል ሲዘጋጁ እንደነበሩ ሁሉ ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረውን የኤርትራ የነፃነት ትግል የተቀላቀሉ ትግሪኛ የማይናገሩ ታጋዮችም ነበሩ፡፡ ይህን መሰል ነገር በተጀማመረበት ሁኔታ ውስጥ ድንገት የፈነዳው የ1966 ዓ.ም. አብዮት በራሱ፣ የአብዮታዊ ለውጥ ጅምር ገጠር/በረሃ ገብቶ ብረት ማንሳትንና ነፃ መሬት እያሰፋ ከገጠር ወደ ከተማ የሚጓዝ አብዮት መሥራትን ግድ እንደማይሻ የለፈፈ ነበር፡፡ የጊዜው አብዮተኞች ግን ይህንን ልፈፋ አድምጠው ከደጅም ከበረሃም ፈጥነው መጥተው፣ የከተማ ትግሉ ውስጥ በመሰባሰብ አብዮቱን ማራመድ አልተያያዙም፡፡ በዚህ ረገድ የግብታዊውን አብዮት ድምፅ በቶሎ የመስማትና የመደነጋገር ችግር ከመኖሩ ሌላ፣ ድረሱልኝ ይል በነበረው የ1966 ዓ.ም. አብዮትና የእነ ሆቺሚኒን ትጥቅ ትግላዊ ገድል በመድገም መሀል የተራማጆቹ ልብ ተበጥቆ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ወታደሩ በአብዮቱ ጅምር ጊዜ ትንሽ የደመወዝ ጭማሪ አግኝቶ ወደ ካምፕ መለስ ሲል የደረሰበት ትችት፣ ከትችቱ በኋላ መለስ ባለው እንቅስቃሴው አስኳል መሥራቱና አብዮቱ በተንገላጀጀበት ሁኔታ ውስጥ የወታደሩ አስኳል ፈራ ተባለ እያለ ክረምቱን ገፍቶ ሥልጣን መያዙ፣ “በአብዮተኞቹ” ዘንድ የነበረውን ፈጣን የመሪነት ጉድለት በግልጽ ያሳየ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ “በአብዮተኞቹ” የተካሄደው የሥርና የላይ ትግልም ቢሆን የኢትዮጵያ ዓይነተኛ የኅብረተሰብና የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሥሪት የሚሻውን ለውጥ በአግባቡ የተረዳና እዚያ ላይ ያነጣጠረ አልነበረም፡፡ በጊዜው በኩባ፣ በቬትናም፣ በቻይናም ሆነ በሩሲያ ስለተካሄደው ለውጥ ታላላቆቻችን የነበራቸው ግንዛቤ ቅርብና ጥልቅ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ መሆኑም ያጠራጥራል፡፡ በዚህ ረገድ የነበረው ጉድለት በጊዜው ለተከፈለው ውድ ዋጋ የራሱን ድርሻ አዋጥቷል፡፡ ዛሬም በደምም ሆነ በሌላ መልክ ውድ ዋጋ ላለመክፈል ግስጋሴያችንን በሚወስኑ ነገሮች ላይ ብስል ዕውቀት ጨብጦ ጉዞን መንደፍ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
አሁን በኢትዮጵያ የተያዘውን የአረንጓዴ ልማት ዕይታና የተግባር ጅምር ሳይለቁ፣ “ከአሮጌው ዓለም የልማት ክንዋኔ፣ ከጃፓን፣ ከቻይና፣ ከታይዋን፣ ከደቡብ ኮሪያ፣ ከሲንጋፖር፣ ከሆንግ ኮንግና ከዓረብ ኤምሬትስ፣ ከስዊድን፣ ከኖርዌይ፣ ከዴንማርክና ከፊላንድ የልማት አገነባብ በየፈርጁ ልንቀስም የምንችለውን አንጥሮ የድኅረ ኮሮና ወረርሽኝ ዓለማችንን አካሄድ በንቁና በብልህ ዓይን ማስተዋል፡፡ እያስተዋሉም በዓለማችን ውስጥ ያሉትን የአሮጌነትና የአዲስነት ይዘቶች በመረዳት የመልማት ትግልን በሚያዋጣ ትልም መምራት ይገባል፡፡ በዚህ የስኬት ጉዞ ውስጥ የሚከተሉትን የአስተሳሰብ ሐረጎች እንደ ትርታ መያዝ ሳይበጅ አይቀርም፡፡ የአገርን ልማት ሁሌም ከዓለም ስልጥነትና የአረንጓዴ ዘላቂ ዝንባሌ ጋር እንዲሳመር አድርጎ ማስኬድ፣ በዚሁ መሠረት የአዲስ ዘመን ፈጠራዎችንና ዘዴዎችን እያነፈነፉ የግስጋሴ ጉርስ ማድረግ፣ የአገርን ልማት ከዙሪያ ገብ ቀጣና ጋር በማሳለጥ ረገድ በጮካ ነጋዴነት የዙሪያ ሀብትን እየመጠጡ ከመክበር ይልቅ ተያይዞ መበልፀግ ላይ ማተኮር፣ በአገር ውስጥ ልማት ረገድ በግል ሥራ ፈጠራና ኢንቨስትመንት የሚታየው መፍለቅለቅም የጥቂት አግበስብሴ ዲታዎች መመዘዣ ከመሆን ፋንታ፣ አጠቃላይ የኅብረተሰቡን ሕይወት ከማንሳት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ፣ የዚህንም ስኬታማነት በሚከተሉት ሦስት መንገዶች መፈተሽ፡፡ የሥራ ፈጣሪዎችና የሥራ ከፋቾች እየሸሹ አለመሄዳቸው፣ የመላ ኅብረተሰቡ ሕይወት ከቀዬ እስከ መሥሪያ ቤትና ከፓርቲዎች እስከ ዕድሮች ድረስ የሐሳቦችና የፈጠራዎች መተነፋፈሻ የመሆን ዕድገት በማሳየትና ባለማሳየቱ፣ ኅብረተሰቡ ግለሰቦችን/ዜጎችን ለማፋፋትና ለመንከባከብ ባለው ትጋትና ግለሰቦችም ኅብረተሰባቸውን ለመጥቀም ባላቸው ትጋት፡፡ ፍተሻው መፋለስን የሚያሳይ ከሆነም ፈጥኖ መንስዔዎቹን እየለዩ መፍትሔ መስጠት፡፡
3ኛ – እየተዘጋጀ ነው የሚባለው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ በኮሮና ያለ መርገፍ የዛሬ ጭንቃችንን፣ ከነገ አረንጓዴ አኗኗራችን ጋር የሚያገናኝ ገመድ በደንብ መዘርጋት መቻል አለበት፡፡ ‹‹የአዲስ አበባ የዳር ገበሬና ከተሜው መሀል ቀረሽ በሆኑ ጉልቶች በኩል በየገበያ ቀናት ይገናኛሉ፡፡ ገበሬው የተወሰኑ ነገሮችን ይዞም ሠፈር ለሠፈር ያዞራል፡፡ ከተሞቻችንና ገበያዎቻችን (ከጉልት ገበያዎች እስከ ትልልቆቹ) በትርካሞነትና በትፍግፍግ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነሱን ታቅፈን ሰው ርቀት መፍጠር አልቻለም. . . አሁንም ቸልታ አለበት. . . መርካቶ ኮሮና የሚባል ወረርሽኝ መግባቱንም የምታውቅ አትመስልም. . .” የሚሉ ዓይነት ትችቶችንና ይህ እንዲለወጥ የሚወተውቱ ምክሮችን በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ፣ በየጎዳናና በየአደባባዩ በየቀኑ ብናካሂድ ፍሬያማ ውጤት ስለማግኘታችን፣ ሰዎችን በገፍ ከመርገፍ ስለማዳናችንና ወረርሽኙ ከከተሞች ወደ ገጠር ዘልቆ እንዳያመሳቅለን ስለመቆጣጠራችን እጠራጠራለሁ፡፡ ረዘም ካለ ዕቅዳችን ጋር በተግባባ መልክም ሆነ ሽግግራዊ በሆነ ደረጃ ሽርንቁላዎችንና የትፍግፍግ መናኸሪያዎችን እዚያው በዚያው ሥርዓት በማስያዝና በማዘራዘርም ሆነ ክምችትን በታቀዱ ሥፍራዎች በመዘርዘር፣ አሁን በአገራችን ከምናቃቸው ገበያዎች የተሻለ መፈናፈኛና ርቀት መጠበቂያ ያላቸውን፣ የዋጋ ቅናሽ መታወቂያቸው የሆነ ናሙና የሱቅና የገበታ ገበያዎችን በታቀዱ ሥፍራዎች በመሥራትና በማሠራት ተኮራጅ እንዲሆኑ ማድረግ ግድ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ባለው አደጋ አቅላይ ማሻሻያ ላይ አግባብ ያላቸውን መሐንዲሶች/ነዳፊዎችና አስተዳደሮች ከባለገንዘቦች፣ ከኅብረተሰቡና ከሥራ ፈላጊዎች ጋር አሳልጦ በቶሎና ከልብ ከተሠራ አስመሥጋኝ ውጤት ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በዚህ ዓይነት ኢትዮጵያ አሁንንና ነገን በብርሃን አጋምዳ ከተጓዘች፣ ማኅበራዊ ፖለቲካዊ ሰላም ብርቅ ያልሆነባት፣ በአገራቸው በሚኮሩና በበለፀገ ሰብዕናና ታታሪነት በታነፁ ዜጎች የምትምነሸነሽበት ጊዜ ርቆ አይርቃትም፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡