Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በቁጥጥር ብቻ የሚፈታ ችግር አይኖርም›› አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ

አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ናቸው፡፡ በመካከሉ ለትምህርት ወደ ውጭ ከመሄዳቸው በፊት፣ ለስድስት ዓመታት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡ የክፍለ ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ወደ ታች ሲወርድም የወረዳ አመራር ሆነው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በአብዛኛው በኢኮኖሚያዊ የኃላፊነት ዘርፎች አገልግለዋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በሕግ የሠሩት አቶ ሺሰማ፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጂያግሺ የፋይናንስ የኢኮኖሚ ዩኒቨርሲቲ በዓለም ንግድና ኢኮኖሚ መስኮች፣ በንግድ ድርድሮችና በዓለም አቀፍ ግብይት፣ በንግድ አሠራርና ተሞክሮ መስኮች ላይ ያተኮሩ ትምህርት ዓይነቶችን ተከታትለው በመመረቅ ወደ አገር ቤት ተመልሰዋል፡፡ ከምሥረታው ጀምሮ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሚመሩት ተቋም፣ የአዲስ አበባ ከተማ ገቢዎች ባለሥልጣን ተብሎ እንደ አዲስ ቢቋቋምም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በቢሮነት ደረጃ ዳግም ተዋቅሮ እየሠራ ይገኛል፡፡ የገቢዎች ሚኒስቴር በተዋቀረበትና በሚመራበት አደረጃጀት መንቀሳቀስ የጀመረው የከተማው ገቢዎች ቢሮ በርካታ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ በታክስ ዕዳ ሳቢያ በወንጀል ጭምር የተጠየቁ ወገኖች ምሕረት ተደርጎላቸው ወደ ሥራ እንዲመለሱ፣ ቅጣትና ወለድ በዝቶባቸው ንብረታቸው የተያዘባቸው ሁሉ እንዲነሳላቸው በማድረግ ጭምር በመሥሪያ ቤቱና በግብር ከፋዮች መካከል ያለውን አለመግባባት ለማርገብ ብዙ ሠርቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ወረርሽኝ ቢስፋፋም፣ የገቢዎች ቢሮ በታክስ ከ43 ቢሊዮን ብር፣ ከማዘጋጃ ቤታዊና ከብድር 17 ቢሊዮን ብር  በላይ በማሰባሰብ በጠቅላላው ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ አቅዷል፡፡ ከወቅቱ ሁኔታ አኳያ ይህ ዕቅድ ምን ያህል ተጨባጭነት አለው? የአሁኑ መሥሪያ ቤት ከቀድሞው ምን ያህል ተለውጧል? የሚሉትን ጨምሮ አቶ ሺሰማ በደቡብ ክልል ስለሚታየው የማንነትና የክልል ጥያቄዎችም በጥቂቱ ያነሷቸው ሐሳቦችን ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማ ደረጃ ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመጪው ዓመት ለመሰብሰብ ታቅዷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የታክስ ገቢ ከፍተኛው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም ላይ ከተከሰተ ስድስት ወራት አስቆጥሯል፡፡ ወደ ኢትዮጵያም ከመጣ አራት ወራት ሆኖታል፡፡ ከሚታየው የንግድና የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አኳያ ዕቅዳችሁ ምን ያህል ለእውነት የቀረበ ነው?

አቶ ሺሰማ፡- በከተማ ደረጃ 60.2 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ ሲታቀድ፣ ከዚህ ውስጥ 3.5 ቢሊዮን ብር ከብድርና ዕርዳታ እንደሚገኝ ታስቦ ነው፡፡ ለውኃ፣ ለመንገድና ለከተማ ግብርና በአብዛኛው በብድር የሚገኝ ገንዘብ ነው፡፡ 43 ቢሊዮን ብር ከታክስ፣ እንዲሁም 13 ቢሊዮን ብር ደግሞ ከማዘጋጃ ቤታዊ የገቢ ምንጮች እንደሚሰበሰብ ታቅዷል፡፡ ማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ ምንም ያልተነካ መስክ ነው፡፡ ለማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት የሚከፈለው ትንንሽ ገንዘብ ስለሆነ ተገልጋዩ አንድ ጊዜ ከእነ ወለድና መቀጫው አንድ ላይ እከፍላለሁ ብሎ የሚያስበው ዓይነት ነው፡፡ ግን ቀላል አይደለም፡፡ ለምሳሌ አምስት ብር የሚከፈልበትን የካርድ አገልግሎት በወቅቱ ባለመክፈል ወለድና መቀጫ 20 ብር ሊደርስ ይችላል፡፡ ከጀርባ ያለውን አገልግሎት በሚገባ ማስተካከል ከተቻለ ብዙ እጥፍ የጨመረ ገቢ ሆኖ ይመጣል ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ማስተካከያዎችን እየሠራን ነው፡፡ የከተማውን ፋይናንስ ቢሮ የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮች ያሉባቸው እየታዩ፣ ከካቢኔም ጋር በመሆን ጭምር የተሻሻለ የገቢ ምንጭ የሚያስገኙ መስኮች ላይ እየሠራን ነው፡፡ ለገቢው መጨመር የሚያግዙ ምልክቶችም አሉ፡፡ በቅርቡ መሬት ላይ ውዝፍ የሊዝ ዕዳ ለመሰብሰብ በከተማ አስተዳደሩ የተወሰዱ ዕርምጃዎች አሉ፡፡ የሊዝ ውዝፍ ዕዳን ነባር ይዞታዎችና አዳዲስ የሊዝ መሬቶችን መነሻ በማድረግ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ብቻ ተንተርሰን ብናይ፣ ወለድና መቀጫው ብዙ ገንዘብ ይዟል፡፡ መቀጫና ወለዱ ቢነሳ እንኳ ዋናው የሊዝ ግብር ቢከፍሉ ከፍተኛ ገንዘብ ሊሰበሰብ ይችላል፡፡ መቀጫው ሰባት በመቶ ገደማ ነው፡፡ በግለሰብ ቤት ደረጃ ወለድና ቅጣት ተነስቶ እስከ 100 ሺሕ ብር የሊዝ ዕዳ መክፈል እችላለሁ የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ከ50 ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን የሚነካ ነው፡፡ ሌሎች ነባር ይዞታዎች በጠቅላላ 150 ሺሕ ሰዎችን የሚመለከተው ነው፡፡ የይዞታቸው መጠን አነስተኛም ቢሆን፣ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህ እንግዲህ በወቅቱ ግብር ባለመክፈል የመጣ ውዝፍ ዕዳ ወለዱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ፍሬ ግብር ብቻ እንዲከፍሉ ቢደረግ እንኳ በርካታ ገንዘብ ወደ መንግሥት ሊመጣ ይችላል፡፡ ትልቅ ገቢ ከወለድና ቅጣት ሊሰበሰብ ቢችልም፣ ገና ለገና እሱን እናገኛለን ብለን ከነገ አንድ ሺሕ ብር ዛሬ የሚከፈለን 100 ብር ዋጋ ስላለው ቅድሚያውን ለዚህ ዓይነቱ አሠራር በመስጠት፣ ትኩረታችንን በፍሬ ግብሩ ላይ ማድረጉን መርጠናል፡፡ ከፍተኛ በጀት የሚጠቀሙ እንደ ውኃ ክፍል ያሉ ተቋማት አሉ፡፡ ለአገልግሎታቸው የሚያስከፍሉት ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ወጪያቸው ግን ከፍተኛ በመሆኑ ቢያንስ ገቢ ሲሰበስቡ ብዙ ወጪ በማያስወጣ መንገድ በባንክና በሌሎች የክፍያ ቴክኖሎጂዎች አማካይነት እንዲያደርጉ እየተሠራ ነው፡፡ ሌሎችም በርካታ የገቢ መስኮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ከቆሻሻ መሰብሰብ ገቢ ይገኛል፡፡ እግርጥ ወጪም አለው፡፡ ሁሉም አገልግሎት መስክ ላይ ተገቢውን ማሻሻያ በማድረግና የተገልጋዩን ዕርካታ በማስፈን፣ ጥራትን በማሻሻል ተጨማሪ ገቢ ማሰባሰብ ከተቻለ የገቢ ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ መስኮች እንዳሉ ዓይተናል፡፡ ወደ ታክስ ገቢ እንምጣ፡፡ የተወሰኑ በጎ ፈቃደኞችን ተጠቅመንና የራሳችንን መዋቅር አካተን እስከ ጥቅምት በውጥረት ስንሠራ ቆይተናል፡፡ ወደ መጋቢት አካባቢ ፋታ ስናገኝ ግን ቤት ለቤት አሰሳ አድርገን ነበር፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ 55 ሺሕ የቤት ኪራይ ግብር የማይከፍሉ ሰዎችን ወደ ታክስ ሥርዓቱ ማምጣት ችለናል፡፡ የኪራይ ግብር ትንሽ ገንዘብ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንዱ ከኪራይ ገቢ ግብር መክፈል እንዳለበት አያውቅም፡፡ ከማንኛውም ገቢ ላይ ታክስ መክፈል ግዴታ ነው፡፡ የእኛም ድክመት ተጨምሮበት ሳይሰበሰብ የቆየ ብዙ ገንዘብ አለ፡፡ እንዲህ በየመንደሩ የጀመርነው አሰሳ ኮሮና እየከፋ ሲመጣ ተቋረጠ እንጂ በትንሹ 55 ሺሕ አከራዮችን አስገኝቷል፡፡ ከ15 ሺሕ በላይ ፈቃድ ማውጣት የነበረባቸው ወይም በወቅቱ ፈቃድ ማደስ የሚጠበቅባቸውን ነጋዴዎች አግኝተናል፡፡ እነዚህን ወደ ሥርዓት ማስገባት ተችሏል፡፡ ይህ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ የሕንፃዎች ልኬትና የውጭ ማስታወቂያዎች ለከተሞች ትልቅ የገቢ ምንጮች ናቸው፡፡ ከ25 ሺሕ በላይ መሰል ግብር ከፋይ ወደ ታክስ ሥርዓቱ መምጣት እንደሚቻል ታይቷል፡፡ የገቢ ማሰባሰቢያ ዘርፎቹ በሁሉም መስክ መሆን መቻል አለባቸው፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ መወሰን የለባቸውም፡፡ ብዙ አማራጮች እንዳሉ በማየታችን የከተማው ገቢ ሊያድግ እንደሚችል እንጠብቃለን፡፡ ደግሞም በሕዝቡ ላይ ጫናና ቅሬታ የሚፈጥሩ አይደሉም፡፡ በጣም ትንንሽ ገቢዎች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ከተማው ግን እኮ ለኤምባሲም ለሌሎች ትልልቅ ተቋማትም የሚከራዩ ቤቶች ያሉበት ነው፡፡ በፌዴራሉ ታክስ መሥሪያ ቤት ሥር ስለሚወድቁ ነው እንዲህ ያሉትን ያልጠቀሷቸው?

አቶ ሺሰማ፡- ከፌዴራል የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በስተቀር በከተማው የሚሰበሰብ ሁሉም ዓይነት የኪራይ ገቢ ግብር የከተማው ነው፡፡ አሰባሰቡ ላይ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ ፌዴራል ሰብሰቦ ለእኛ የሚያስተላልፈው፣ እኛም ሰብሰብን ለፌዴራል የምናስተላልፈው የታክስ ገቢ አለ፡፡ በክልሎችም እንደዚያው ነው፡፡ በከተማው በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያነት የሚተዳደሩ፣ ትልልቅ ሕንፃና የገበያ ማዕከላት ወዘተ. የሚያከራዩ ካሉ የታክስ ገቢው በፌዴራል ይሰበሰብና ወደ እኛ ይመጣል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ ጉድለት ለመመልከት ችለናል፡፡ እነዚህ ግብር ከፋዮች ኦዲት ተደርገው አያውቁም፡፡ ታክስ የሚከፍሉበት ልኬትም ትክክለኛነቱ መታየት ያስፈልገዋል፡፡ በኪራይ ገቢውና በሚከፈለው ታክስ መካከል ያለውን ስናይ ተገቢውን ግብር እያገኘን አይደለም፡፡ እነዚህ ሕንፃዎች አገልግሎት የሚሰጡትና ገቢ የሚያገኙት ውኃ፣ መብራትና ሌሎችም ተገቢው አገልግሎት ሲቀርብላቸው ነው፡፡ ይህን ማድረግ ለሚጠበቅበት የከተማው አስተዳደር ግን ተገቢውን ግብር እየከፈሉ አይደለም፡፡ ችግር አለ፡፡ የከተማው ታክስ አስተዳደር እንዲህ ዓይነት የታክስ ገቢዎችን መሰብሰብ ስለሚችልና ብቃቱም ስላለው ከፌዴራል ወደ ከተማው መመለስ አለባቸው፡፡ በዚህ ተጨማሪ ገቢ መሰብሰብ እንችላለን፡፡ ዘርፈ ብዙ የገቢ ምንጮች እያሰብን በመሆኑ በአንድ አቅጣጫ የተወሰነ የታክስ ገቢ አንጠብቅም፡፡ ሌላ ምሳሌ ልሰጥህ እችላለሁ፡፡ በአዲስ አበባ ሕንፃ ወይም  ኮንዶሚኒየም የሚሸጡ አሉ፡፡ የሚያከራዩም አሉ፡፡ በልደታ ኮንዶሚኒየም ደላሎች ባለ አንድ መኝታ በስንት ያከራያሉ? በስንት ይሸጣሉ? የሚለውን ስናይ ትልቅ ገንዘብ አለ፡፡ የካ አባዶ፣ አስኮ፣ ለገጣፎ፣ ቃሊቲና ሌላም ቦታ የሚከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ ነው፡፡ ተሻሽጦ ወደ ሕጋዊነት የሚመጣው ገንዘብ፣ በየማኅበራዊ ሚዲያው በዚህን ያህል እየተባለ ከሚገለጸው አኳያ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡

በመሠረቱ ቤት ንብረት ከመሸጥ የሚሰበሰበው የቴምብር ቀረጥና የአሹራ ወይም የሕጋዊነት ማረጋገጫ ግብር በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የቱንም ያህል ቢሻሻጥ ለመንግሥት የሚከፈለው ገንዘብ እንደ ካፒታል ስብስብና ጠቀሜታ አይደለም፡፡ ሰዎች ግን ስም ስላዛወሩ የአገልግሎት የሚከፍሏትን ሁለት በመቶ፣ የአሹራ የሚከፍሏትን አራት በመቶ ግብር ለማጭበርበር ዋጋ አሳንሰው በሰነዶች ተቋም ያረጋግጣሉ፡፡ በመንደር ውል ግን በትክክለኛው ዋጋ ተዋውለው ይሻሻጣሉ፡፡ በንግድ ቦታ ሽያጭ፣ በሕንፃ ሽያጭና በቦታ ሽያጭ፣ እንዲሁም አንዳንዴ የካፒታል ድርሻን ከማዘዋወርና ከመሸጥ የሚከፈሉ የታክስ ዓይነቶችን ላለመክፈል የሚደረጉ ናቸው፡፡ አዋዋይና ሰነድ አረጋጋጭ መሥሪያ ቤቱ አንድ ዓይነት ደረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ ቢሆንማ ኖሮ ተመራጩ መንገድ ፊስካል ካዳሰተር የሚባለው ሥርዓት ነበር፡፡ ለከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ገቢ የሚገኝበት፣ ለግብር ከፋዩ ግን አነስተኛ መጠን ያለውን ታክስ ላለመክፈል የሚደረገው ሽሽት አንዳንዴ ባለንብረቱንም ሊጎዳው ይችላል፡፡ ለምሳሌ የገዛው ቤት ወይም ሕንፃ ለሌላ ሥራ ፈራሽ ነው ቢባል፣ ባለንብረቱ የሀብቱን ግምት ለማሠራትና ካሳ ለመጠየቅ የሚያመጣው ሰነድ የትኛው ነው የሚሆነው? የመንደር ውል ወይስ የሰነዶች መሥሪያ ቤትን ውል? በሁለቱ መካከል ከፍተኛ የዋጋ ልዩነት ይኖራል፡፡ ታዲያ መንግሥት ካሳ የሚከፍለው በየትኛው ሰነድ ተመሥርቶ ሊሆን ነው? እንዲህ ያሉ ችግሮች እንዳይገጥሟቸውም ጭምር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በመደበኛው መንገድ ዋጋውን ይዘው ለአገልግሎቱ የሚከፍሉት ታክስ ብዙ ሕመም የማያመጣባቸው መሆኑ በገሃድ የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ሳይሰበሰቡ የቆዩ ገቢዎችን ታሳቢ እናደርጋለን፡፡ ተመናቸው ይፈተሻል፡፡ አገር አቀፍ ተመን ከሆነ በነበር ይቀጥላል፡፡ በርካታ የሚፈተሹ የገቢ ምንጮች አሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን ተቋሙ ለትርፍ አስቦ ሳይሆን ለአገልግሎት ቅድሚያ ሰጥቶ፣ ነገር ግን መሰብሰብ የሚጠበቅበትን ያህል ገቢ መሰብሰብ የሚችልበት ሰፊ ዕድል እንዳለ በመታየቱ፣ ገቢ የሚጨምረው እንዲህ ያሉ ሥራዎችን በማስፋፋት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በከተማው የንግድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ነው፡፡ ይህንን በተጨባጭ የሚያሳይ አኃዛዊ መረጃ አላችሁ?

አቶ ሺሰማ፡- አለን፡፡ ለምሳሌ ከታክስ ገቢ 43 ቢሊዮን ብር እንሰበስባለን ስንል፣ የቀጥታ ታክስን ብናይ የደመወዝ ገቢ ግብር፣ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የቤት ኪራይ ግብርና ሌሎችም ይካተታሉ፡፡ ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችን ካየን ተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ተርን ኦቨር ታክስና መሰል ታክሶች ይካተታሉ፡፡ በየታክስ ዓይነቱ ያሉትን ለውጦች እናያለን፡፡ ምን ያህል ታክስ ለመሰብሰብ የሚያስችል አቅም በኢኮኖሚው ውስጥ እንዳለ የምንከተላቸው አሠራሮች አሉ፡፡ በተጨባጭ የተረጋገጡ ትንተናዎችን በማዘጋጀት፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው እንቅስቃሴ አኳያ አሁን ያለው ምን እንደሚመስል በሚገባ ፈትሸን እንጂ፣ በግምት ላይ ተመሥርተን አይደለም ይህን ያህል ገቢ ከከተማው እናገኛለን የምንለው፡፡ ትልቅ የታክስ ገቢ ሊገኝባቸው የሚችሉ ነገር ግን ወጣ ያሉ በመሆናቸው የተውናቸው የገቢ ምንጮች አሉ፡፡ ለምሳሌ የሆቴል ተጠቃሚ አልጋ በያዘ ቁጥር ለከተማው ከአንድ እስከ አሥር በመቶ ታክስ መክፈል ነበረበት፡፡ ይህ በሌላው ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ እኛ ጋ የለም፡፡ ሆቴሎችም ለራሳቸው ህልውና እየተንገዳገዱ ስለሚገኙ አሁን ላይ ይህን ዓይነቱን የታክስ ገቢ ምንጭ ታሳቢ አላደረግነውም እንጂ፣ በከተማው የሚታየው የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴ ብዙ ታክስ ለመሰብሰብ የሚያስችል ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ከፀጥታ ሥራ የሚገኝ የታክስ ገቢና ሌሎችም አሉ፡፡ ሊተገበሩ የሚችሉና የታክስ መሠረቱን ሊያስፋፉ የሚችሉ የገቢ ምንጮች በርካታ ናቸው፡፡

ከታክስ አሰባሰብ አኳያ አንድ ሳልጠቅስ የማላልፈው መልዕክት አለኝ፡፡ ያለ ደረሰኝ መሸጥን በሚመለከት የታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶች ለታክስ ከፋዩ ያልነገሩት አንድ መሠረታዊ ሚስጥር አለ ብዬ አምናለሁ፡፡ ሸማቹ የሚከፍላቸውን የፍጆታ ታክሶች ያለ ደረሰኝ በመሸጥ ምክንያት ሻጩ ወይም አገልግሎት ሰጪው ንግድ ድርጅት አለመሰብሰቡ፣ በሌላ አነጋገር ያለ ደረሰኝ ግዛኝ እንጂ ወለድና ቅጣቱን ጨምሬ እኔ እከፍልልሃለሁ እንደ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም መንግሥት በወቅቱ ኦዲት ቢያደርጋቸው ኖሮ ያለ ደረሰኝ ለማን እንደሸጡና ከማን እንደገዙ በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡ ኦዲት በሚደረጉ ጊዜም ሲገኙ ነው ቅጣትና ወለድ ሲታከልባቸው ጫጫታ የሚያበዙት፡፡ እስካሁን ታክስ ከሚከፍለው ውስጥ 20 በመቶ ብቻ ነው ኦዲት የሚደረገው፡፡ የተቀረው ሒሳብህን በራስህ ሠርተህ ትክክለኛው ታክስ ክፈል በመባሉ ምክንያት የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ቁጥጥር የራሱ ችግር አለበት፡፡ በቁጥጥር ብቻ የሚፈታ ችግር አይኖርም፡፡ ሲያስፈልግ ግን ታክስ አጭበርባሪውን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ ጭምር ከተግባሩ እንዲቆጠብ ማድረግ የሚቻልባቸው ዘዴዎች አሉ፡፡ ዋናው ነገር ግን ትክክለኛ ታክስ ከፋይ እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ያጠፋ ሲገኝም ወደ ትክክኛው ሥርዓት ገብቶ ተገቢውን ታክስ እንዲክፍል ማስቻል ነው ውጤታማ የቁጥጥርና የማስተማር ሥራ የሚባለው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ኢኮኖሚው ጉዳይ እንመለስ፡፡ ኢኮኖሚው ከሚያስመዘግበው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት የዕድገት መጠን (ጂዲፒ) አኳያ የታክስ ጥመርታው እስከ 13 በመቶ እንደ ደረሰ በአገር አቀፍ ደረጃ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ በከተማ ደረጃስ ይህ አለ?

አቶ ሺሰማ፡- ጠቅላላ የኢኮኖሚ ምርት ዕድገት እንዴት ነው የሚሠራው የሚለው ግልጽነት ይፈልጋል፡፡ ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን በዚህ ላይ እየሠራበት ነው፡፡ የከተማ ጂዲፒ ላይ ስንመጣ ግን ችግር አለበት፡፡ ለምሳሌ በዚህ ከተማ ውስጥ የታክስና የኢኮኖሚ ዕድገት ጥመርታ ምጣኔ ለመሥራት ስታስብ፣ እንበልና አንድ የግል ኩባንያ የሚያመርተው፣ ግለሰብ ምን እንደሚሸምትና ለፍጆታ እንደሚያውል፣ የገቢው ምንጭና የፍጆታው መጠን ምን እንደሚመስል ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች ከተሞች የሚኖራቸውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለመለካት አሥር መመዘኛዎችን አውጥተዋል፡፡ የከተሞች የዕድገትና የልማት መመዘኛዎቹ ሁሉንም መስኮች በመመልከት፣ የከተሞቹን ደረጃ ለማወቅ የሚችሉባቸውን መንገዶች ይከተላሉ፡፡ አለበለዚያ ግን የከተማውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በመመልከት የታክስና የኢኮኖሚ ዕድገት ጥመርታ ላውጣ ስትል አሳሳች ነገር ላይ ይጥልሃል፡፡ አንዳንዱን ዘርፍ ስታየው የአምስት በመቶ ጥመርታ እንዳለ ያሳይሃል፡፡ ሌላውን ስትፈትሽ እስከ 30 በመቶ ጥመርታ እንዳለ ሊያሳይ የሚችል አኃዝ ልታገኝ ትችላለህ፡፡ ምን ላይ ተመሥርቶ ነው ይህ የመጣው የሚለው በሚገባ ካልታየ አሳሳች ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከጂዲፒ በተጓዳኝ በሰው ልማት ላይ የተመሠረተና የሰዎችን እርካታ መነሻ የሚያደርግ መመዘኛም ታሳቢ እየተደረገ ነው፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡

ወደ ከተሞች ስንመጣ ግን የከተሞች የልማት መመዘኛ ኢንዴክስ የሚባለውን አሠራር በመጠቀም፣ መረጃ ከታች ወደ ላይ በመሰብሰብ አብዛኛውን የከተማውን ለውጥና ዕድገት መገምገም የሚያስችል መመዘኛ ማምጣት ይጠበቅብናል፡፡ በእኛ ሁኔታ በከተማው ኃላፊነታቸው የተወሰኑ የግል ኩባንያዎች መኖሪያቸውና ሁሉንም አገልግሎት የሚያገኙት ከከተማው አስተዳደር ሆኖ ሳለ፣ ግብር የሚፈክሉት ግን ለፌዴራል መንግሥት ነው፡፡ የመንግሥት ባንኮችን ጨምረን ከ17 በላይ ባንኮች በከተማው አሉ፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውና ለከተማው ማዋል የሚገባቸው ጥቅም ላይ ያለውን አሠራር ስታይ ለከተማው አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ፕላን ኮሚሽን የጀመረው ሥራ እንዲህ ያለውን ነገር ሊፈታ ይችላል፡፡ የታክስና የጂዲፒ ጥመርታን ማውጣት በአገር አቀፍ ደረጃ፣ እንዲሁም በክልሎች ብዙ አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል፡፡ የከተማውን ነጥሎ ለማውጣት ግን ያስቸግራል፡፡ የአዲስ አበባን የኢኮኖሚ ደረጃ ስናይ በዝቅተኛ መካከለኛ የገቢ የደረጃ ላይ የሚቀመጠውን ደረጃ ልትሰጠው የምትችልበት አቅም ላይ ይገኛል፡፡ በተጨባጭ ግን እዚያ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚለው፣ የእያንዳንዱ ሰው የፍጆታና የገቢ ሁኔታ ከታች ወደ ላይ ሲታይ ግን ይህን ላያመላክት ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት ተቋም ከፌዴራል ተጠሪነቱ ተነጥሎ ወደ ከተማው አስተዳደር ከተመለሰ ሁለት ዓመት ሆኖታል፡፡ ከዚህ ቀደምም ራሱን ችሎ በከተማው አስተዳደር ሥር ይመራ የነበረ የታክስ መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ ከሚሰበሰበው የታክስ ገቢ እኩል ተመላሽ የሚያደረገው ከፍተኛ እንደሆነ፣ የሰበሰበውን መልሶ ለግብር ከፋዩ እንደሚሰጥ የሚነገርለት ተቋም ነበር፡፡ አሁን ተቋሙ ወደ ከተማው ተመልሶ በመምጣቱ ምን ለውጥ ታይቷል?

አቶ ሺሰማ፡- መሥሪያ ቤቱ በ2003 ዓ.ም. ገደማ ይመስለኛል ወደ ፌዴራል ገቢዎች መሥሪያ ቤት እንዲቀላቀል የተደረገው፡፡ ታክስ በባህሪው የተጣጣመ ወይም በአገር አቀፍ ደረጃ ተመሳሳይና ወጥ አሠራር ያለው መሆን መቻል አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ አንዱ ጋ የማይሰበሰብ ሌላው ጋ የማይሰበሰብ ሆኖ መገፋፋትና መጓተትን የሚያስከትል ውጤት ሊያስከትል ይችላል፡፡ ለቢዝነስ ምቹ የሆነውን ቦታ ለመምረጥ አንዱ ታክስ በመሆኑ፣ ያልተናበበ አሠራር እንዳይኖር የታክስ ‹‹ሀርመናይዜሽን›› ሥራ መተግበር በመርህ ደረጃ አለ፡፡ በእኛ አገርም ይህን ያህል ሥር የሰደደ ችግር አይታይም፡፡ የተጣጣመ የታክስ ሥርዓት መከተል ስለጀመርን ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው፣ በ2003 ዓ.ም. በከተማ ደረጃ የተሰበሰበ አራት ቢሊዮን ብር ገቢ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ተቋሙን ስንረከብ ወደ 27 ቢሊዮን ብር አድጓል፡፡ ሌሎች ነገሮች እንደተጠበቁ ሆነው ዕድገት ታይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ወደ ኋላ የቀረበ ነገርም አለ፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ ማዘጋጃ ቤታዊ የሚባል የታክስ ገቢ መስክ የለም ነበር፡፡ ነገር ግን ከተሞች 50 በመቶና ከዚያ በላይ ገቢያቸውን የሚሰበስቡት ከማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ነው፡፡ ይህ ተበድሎ የቆየና ብዙ ያልተሠራበት በመሆኑ፣ የከተማው የታክስ መሥሪያ ቤት ዳግም ወደ ከተማው እንዲመለስ በመደረጉ፣ እንዲህ ያሉትን የታክስ ምንጮች እንድንመለለከት ዕድል ሰጥቶናል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት በከተማው አስተዳደር ሥልጣን ወሰን ሥር የሚወድቁ ማነቆ የነበሩ ነገሮችን፣ በቀላሉ በከተማው አስተዳደር አማካይነት በማስወሰን በቀላሉ እየተፈቱ እንዲሄዱ ማድረግ ተችሏል፡፡ የመጣውን ለውጥ በ2009 ዓ.ም. የነበረ ሰው የሚያስታውሰው ነው፡፡ በግብር ሰብሳቢውና በግብር ከፋዩ መካከል የተከሰተ ውጥረት ነበር፡፡ በጥናት ላይ ተመሥርተን የትኛውን የገቢ መስክ እናጣለን? የትኛው ያዋጣናል? በምን መንገድ እናካክሰዋለን የሚለውን አጥንተን ለከተማው ካቢኔ በማቅረብ በአፋጣኝ እንዲሠራበት ማድረግ ተችሏል፡፡ በፌዴራል ሥር በነበረበት ወቅት ግን፣ ወደ ከተማው ካቢኔ አምጥቶ ማስወሰን መልሶ በፌዴራል ደረጃ ማስተግበር ችግሮች ነበሩበት፡፡ የፌዴራሉ ታክስ መሥሪያ ቤት በደረሰበት ደረጃ ልክ ሊባል በሚችል ደረጃ፣ የከተማው ታክስ አስተዳደርም በዚያው ልክ ሊመሠረት ችሏል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው፡፡ የሚሰበስበው ገቢም ትልቅ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- የታክስ መሥሪያ ቤት ሲነሳ የሠራተኞች ሥነ ምግባር ጉዳይም ይነሳል፡፡ የመጀመርያው የቀን ገቢ ቁርጥ ግብር በአቶ መላኩ ፈንታ አመራር ጊዜ ሲተገበር ይነሳ የነበረው ችግር የኢንተሊጀንስ ክትትሉ ነበር፡፡ በየቤቱ የሚሄዱት የተቋሙ ሠራተኞች ችግር ነበረባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ምን ዓይነት የዲስፕሊን ሥራ ተከናውኗል? ምን ዓይነት ለውጥ አለ?

አቶ ሺሰማ፡- በታክስ አስተዳደር ሥራ ውስጥ የፋይናንስ አስተዳደርም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው በመሆኑ፣ ጥንቃቄ ካልተደረገበት ትልቅ የሥነ ምግባር ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡ በአገሪቱ አነሰም በዛ የግሉ ዘርፍ እያደገ መጥቷል፡፡ የዚህ ዘርፍ ማደግ እግረ መንገዱን የባለሙያ ዕገዛ ይፈልጋል፡፡ ይህ በሚሆንበት ወቅት የፋይናንስና የታክስ ባለሙያዎችን የሚቀጥረው ከዩኒቨርሲቲዎችና ከመሰል ትምህርት ተቋማት አይደለም፡፡ ከታክስ መሥሪያ ቤቶችና ከመሰል ተቋማት በተሻለ ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም ነው የሚወስዳቸው፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ደግሞ ይሠሩባቸው የነበሩ የመንግሥት ተቋማትን የአሠራር ጉድለቶች ስለሚያውቁ፣ አንዳንዴም በሁለት ወገን በሚደረግ ስምምነት ከፍተኛ የሥነ ምግባር አደጋ ይሆናሉ፡፡ ግብር ከፋዩም የታክስ ሕጎችን ባለማክበሩ ምክንያት ማንም ሰው እየተነሳ እንዲያስፈራራው ራሱ ዕድሉን ይሰጣቸዋል፡፡ ግብር ከፋዩ የሚመጣበት ትክክለኛ የታክስ አስተዳደር ሠራተኛም ቢሆን፣ ሕግን አክብሮ የሚፈልገውን መረጃ ማግኘት እንደሚችል ማስታወቅና በዚያ መንገድ መስተናገድ አለበት፡፡ ነገር ግን ግብር ከፋዩ ራሱ ሕግ ስለማያከብር እኛ ያላሰማራነው ሰው ሲመጣበት እንኳ እምቢ የሚልበት አቅም ያጣል፡፡ ለምሳሌ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የጀመርነውን የቤት ለቤት አሰሳ ሥራ አቁመናል፡፡ የእኛ ዓላማ ቤት ለቤት እየሄድን ለማስተማር ያለመ ነበር፡፡ ያለ ደረሰኝ አትሽጡ፣ ራሳችሁ ነው የምትጎዱት የሚል ትምህርት ለማስተማር ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ ነገር ግን ከአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ እስከ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ባለው አካባቢ የመኪና ጌጣ ጌጥና ዲኮር የሚሸጥባቸው ንግድ ቤቶች አብዛኞቹ ሕግ ስለማያከብሩ፣ ይህን የተረዱ ነገር ግን እኛ ያላሰማራናቸው የእኛ ያልሆኑ ሰዎች ከእያንዳንዱ ሱቅ አምስት ሺሕ ብር አጭበርብረው እንደ ተቀበሏቸው ሰምተናል፡፡ ሌላው ቢቀር የገቢዎች ቢሮ ባልደረባ ነኝ የሚላቸው ሰው ሲመጣ እንዴት መታወቂያህን አሳየን አይሉም? የማይታወቁ ሰዎች፣ ወንድና ሴት፣ በጥንድ በጥንድ ሆነው ከእየ ነጋዴው ገንዘብ ሲቀበሉ እንደነበር መረጃ ደርሶናል፡፡ መታወቂያ መጠየቅ ባይችሉ ደግሞ ወደ መሥሪያ ቤቱ ደውለው እንዲህ ያለ ሰው አሰማርታችኋል ወይ ብሎ መጠየቅ እየተቻለ ይህ አይደረግም፡፡ ችግር አለ፡፡

በተቻለ መጠን አሠራሩን ከሰው ንክኪ ነፃ እያደረጉ መሄድ መቻል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ በአሥር ወረዳዎች ላይ ሙሉ በሙሉ በዲጂታል የታገዘ አገልግሎት የሚሰጥባቸው አሠራሮችን ጀምረናል፡፡ በትንሹ ግብር ከፋዩ ወደ መሥሪያ ቤቱ መሄድ ሳይጠበቅበት፣ ይህን ያህል ገንዘብ አለብህ ባንክ አስገባ የሚል የጽሑፍ መልዕክት ይደርሰዋል፡፡ ያላመነበት ነገር ካለ ወደ ቅሬታ ሰሚ ወደ ሌላ ተቋም ይሄዳል እንጂ ተቋሙ ዘንድ መምጣት ሳይጠበቅበት የሚከፍለው የታክስ መጠን ምን ያህል እንደሆነ አስቀድሞ የሚያውቅበት የዲጂታል ሥርዓት እየተዘረጋ ነው፡፡ ኮሮና ሲመጣ ተቀዛቀዘ እንጂ እንዲህ ያለ ሥራ እያስፋፋን ነበር፡፡ ሸማቹም ቢሆን ያለ ደረሰኝ ግብይት መፈጸሙ የገዛው ዕቃ ጉድለት ቢኖርበት በሕግ አግባብ ማስመለስ የሚችልበትን መብት ያሳጣዋል፡፡ ችግር ያለበት ዕቃ ከተሸጠለት መመለስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ያለደረሰኝ የሚገዛ ከሆነ ግን ዕቃው ችግር ኖሮበት መልሱልኝ ቢል እንኳ እኮ እንዲያውም ሳትከፍል ነው የወሰድከው፣ ስለዚህ ክፈል ብሎ ሊይዘው የሚችል ነጋዴ ሊያጋጥመው እንደሚችልም ማሰብ መቻል አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም ተቋሙ ውስጥ የሥነ ምግባር ጉድለት ማሳየቱ ብቻም ሳይሆን፣ እምነት የሚታጣበት ሠራተኛ ካለ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ማሰናበት የሚችልበት መብት አለው፡፡ ይህ በሌላውም ዓለም የሚሠራበት ነው፡፡ ለምሳሌ ያልተመዘገበ ሀብት የተገኘበት ባለሙያ እምነት ስለማይጣልበት በየጊዜው ንብረቱን ማስመዝገብ ይጠበቅበታል፡፡ ግብር ከፋዩ ሲተባበር እጅ ከፍንጅ የሚያዙ የታክስ ሠራተኞችም ይገኛሉ፡፡ አሁን ግብር ከፋዩ ከእኛ ጋር በፈጠረው መተማመን ሳቢያ መረጃ ይሰጠናል፡፡ እኛም በሚዲያ ጭምር ይፋ እስከ ማድረግ በሚደርስ ደረጃ ዕርምጃ እየወሰድን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መርካቶ የአገሪቱ የንግድ ደም ሥር ነው፣ የሕገወጦች መናኸሪያ ነው በሚል መነሻ የፌዴራሉ ታክስ ተቋም ቅንርጫፍ ከፍቶ የሚንቀሳቀስበት እስከ መሆን ከደረሰ ቆይቷል፡፡ አሁን በመርካቶ ምን ለውጥ አለ?

አቶ ሺሰማ፡- መርካቶ ላይ ብዙም ለውጥ የለም፡፡ መንስዔው ግን መርካቶ ብቻ ነው ብሎ መውሰድ ስህተት ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከመርካቶ ነጋዴዎች ጋር በቅርብ እየተገናኘን እንወያያለን፡፡ የመርካቶ ሕገወጥነት መንስዔ ምንድን ነው በሚለው ላይ የተለያየ አመለካከት አለ፡፡ አብነት ለምሳሌ ትልቅ የብረታ ብረት መሸጫ ገበያ ነው፡፡ በሸቀጥ ንግድ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግብይት ይፈጸምበታል፡፡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ የቀረጥ ነፃ ዕድልና ሌሎችም ማበረታቻዎች ከሚሰጣቸው መስኮች አንዱ ነው፡፡ ብረት እንደ ሌሎች ሸቀጦች ወይም እንደ ሞባይል የሆነ ነገር ውስጥ ሸሽገህ ወደ አገር ውስጥ የምታስገባው ነገር አይደለም፡፡ ከመነሻ እስከ መዳረሻ ያለውን ችግር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ካሁን በፊት በፌዴራል ደረጃ ተደጋግሞ የሚገለጽ አጋጣሚ አለ፡፡ በአንድ ትንሽ ከተማ ውስጥ በጣም ብዙ ሆቴሎች ለመሥራት ተብሎ ብረት፣ ሴራሚክና ሌላውም የፊኒሺንግ ዕቃ፣ ማንኪያ፣ ሹካና ስኒ ሳይቀር በገፍ ገብቷል፡፡ ይህ መነሻው ከየት ነው? ለምንድነው የሆነው የሚለውን ማየት፣ መዳረሻው ላይ ያለውን ሁኔታም ማየት ተገቢ ነው፡፡ ሁለቱም መታየት ያለባቸው ችግሮች ናቸው፡፡ በተወሰነ ደረጃ የመግዣ ዋጋን ከመሸጫ ዋጋ በታች አሳንሶ (አንደር ኢንቮይሲንግ) በማቅረብ ችግሩ የዶላር ማጣት የፈጠረው እንደሆነ የሚያነሱ ነጋዴዎች አሉ፡፡ ምርቱን ከውጭ የሚገዙበት ዋጋና እዚህ ከባንክ የሚሰጣቸው ዶላር ስለማይገናኝ ዶላር ከመንገድ እያገኙ ዕቃ ገዝተው የሚያስገቡ፣ ነገር ግን ጉምሩክ ታክስ ከፍለው የሚያስገቡበት ዋጋና ሌላም ታክስ ታክሎበት በትክክለኛው ዋጋ ሲሸጡ ለምሳሌ የ1,000 ብር ዕቃ፣ ዋጋው 100 ብር ነው ተብሎ ከገባ በኋላ፣ 1,100 ብር እንደተሸጠ ተቆጥሮ 1,000 ብር አትርፈሃልና ታክስ ክፈል ሲባል እንዲህ ያለውን ችግሩን በማስረዳት እንዲስተካከልለት እየጠየቀ ነው፡፡ ይኼን ሥርዓት አስተካክሉ እያለ ነው፡፡ የትኛውም አገር የቱንም ያህል የውጭ ምንዛሪ ክምችት ቢኖረው ለፈለገና ለጠየቀ ሁሉ ይሰጣል ማለት አይደለም፡፡ አቻችሎና አጣጥሞ ማዳረስ የማይቀር ነው፡፡ ነገር ግን የእኛን ድንበር የረገጠ፣ የጉምሩክ ድንበራችንን ያለፈ አንድ ሸቀጥ እንዴት ነው የሚቀረጠው? የሚለው መታየት አለበት እያሉ ነው፡፡ ይህ ሥራ ይጠይቃል፡፡

የግብርና ምርት አገር ውስጥ ተመርቶ መርካቶ እስኪደርስ ድረስ ከማሳ ጀምሮ በርካታ እጃቸውን በማስገባት ገንዛቸውን ወስደው፣ ጭራሽ የጅምላ ሽያጭ ገበያውን የሚያውኩበት መንገድ መፈጠሩ ሳያንስ፣ ይህ ሁሉ ኃይል ይዞ የወጣው ገንዘብ በማነው ታክስ የሚፈከልበት? ማን ላይ ነው ታክሱ የሚጫነው? የሚለው ብዙ ሥራ የሚፈልግ ነው፡፡ መንግሥት ያለችውን የውጭ ምንዛሪ በማቅረብ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ተደርጎ፣ የአገር ውስጥ ግብር ዕፎይታ ተሰጥቶት የሚገባው ዕቃ ከሚፈጥረው እሴት የሚገኘው ታክስ ነበር የመንግሥት ገቢ የሚሆነው እንጂ፣ የመንግሥት ዋናው ፍላጎት ዕቃዎቹ ኢኮኖሚያዊ ልማት ሲያስገኙ ነው፡፡ ነገር ግን ዛሬ በአሥር ሺሕ ብር የገዛኸውን ዕቃ 100 ሺሕ ብር ነው የገዛሁት ብለህ ከመሸጫ ዋጋ በላይ ያገኘኸውን 90 ሺሕ ብር ትደብቃለህ፡፡ አንዳንዱ ወደ ውጭ እልካለሁ ብሎ የተሰጠውን ጥቅማ ጥቅምና ማበረታቻ በማጭበርበር አገር ውስጥ የሚሸጥ አለ፡፡ ዛሬ ክልል ሁሉ መርካቶ ሆኗል፡፡ መገናኛም መርካቶ ነው፡፡ ብዙ ማስተካከል የሚጠይቁ ነገሮች አሉ፡፡ መርካቶ አምራች ቦታ አይደለም፡፡ ለምንድነው የምርቱን መነሻ የማትከታተሉት ይሉሃል፡፡ አንድ ተመሳሳይ ምርት ወይም ዕቃ ግን እንዴት ጎዳና ላይ መደብር ውስጥ ሊገኝ ይችላል ብለህ ስትል ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ባለሱቁ የሚሸጠውን ዕቃ ጎዳና ላይ ካገኘኸው ግን መሠረታዊ ችግሮች አሉ ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻም እርሰዎን ወደሚመለከቱ ፖለቲካዊ ጉዳዮች እንምጣ፡፡ በደቡብ ክልል የጉራጌ ማኅበረሰብ ተወላጅ እንደ መሆንዎና ራሳቸውን ችለው ክልል ለመሆን ጥያቄ ከሚያነሱ አንዱ ብሔረሰቦች አንዱ አካል እንደ መሆንዎ፣ በሒደቱ የእርስዎ ሚና ምንድነው?

አቶ ሺሰማ፡- እንደ አንድ ተወላጅ የሚታይ ሚና ነው ያለኝ፡፡ ከዚህ የተለየ ነገር የለኝም፡፡ ክልሉ ብሔራዊ ማንነቱን በሚያሳይ መንገድ ቢቀጥል ብዙ ችግር የለውም፡፡ በተለይ የሲዳማ የክልልነት ጉዳይ ገፍቶ መጥቶ የሕዝብ ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ሌሎቹ እንዳለ ይቀጥላሉ የሚል ሐሳብ ነበር፡፡ እዚህ ላይ ችግር የለም፡፡ ችግር የለም ሲባል ግን ሕዝቡ ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር አብሮ ስለሚኖር፣ የሚከፍለው መስዋዕትነት እንኳ ቢኖር እየተከፈለ አብሮ በክልሉ መኖር አለበት የሚሉ የነቁ ሐሳቦች ነበሩ፡፡ በዓለም ላይ የሚዛናዊነቱ ጉዳይ ካልሆነ በቀር የማንነት ጥያቄ ከፍ እያለ የመጣበት ወቅት ነው፡፡ ትልልቅ ሰዎች ብዙ የጻፉበት፣ ሳሙኤል ሐቲንግተን የሚባል ጸሐፊ እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ በጻፈውና ‹‹ክላሽ ኦፍ ሲቪላይዜሽን›› በተሰኘው መጽሐፉ፣ ዓለም ለ400 ዓመታት ‹‹ዩኒፖላር›› በተሰኘው አስተሳሰብ መራመዷን ያነሳል፡፡ ይህም ሰው ሁሉ እኩል የሚል መነሻ ያለው ሐሳብን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 1990ዎቹ ደግሞ ዓለም ‹‹ዩኒ ፖላር›› ሆና ቆይታለች ይላል፡፡ ይኸውም ሰው ሁሉ እኩል ነው ግን ደግሞ አሠሪና ሠራተኛ ያለባት፣ ባለቤትና ጭሰኛ እየተባለ የመደብ ሥሪት የሰፈነባት፣ የምሥራቅ ደጋፊና የምዕራብ ደጋፊ የሚባሉ ርዕዮተ ዓለሞች የሚንፀባረቁባት ሆናለች፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1990ዎቹ በኋላ ደግሞ ወደ ‹‹መልቲፖላር›› አሠላለፍ የመጣችው ዓለም የምሥራቅና የምዕራብ ጎራ ደጋፊ መሆን፣ ወይም የሰዎችን እኩልነት መቀበል ብቻም ሳይሆን፣ እኛ ማን ነን? እኔ ማን ነኝ? የሚሉ ጥያቄዎች የሚስተናገዱባት ሆነች፡፡ እኔ ማን ነኝ የሚለውን ለመመስ ደግሞ ወደ ቅድመ መነሻ ዘሮች፣ ቋንቋ፣ ባህልና የባህል ተቋማትን ወደ ማየቱ ጉዞ የተጀመረበት ጊዜ እንደሆነ ጸሐፊው ይገልጻል፡፡

እንዲህ ያሉ የማንነት ጉዳዮች፣ የሲቪል አስተሳሰብ በማራመድ ብዙ መሄድ እንደማይቻል፣ ኢትዮጵያዊነቴ ብቻ እንጂ ብሔሬ አያስፈልግም የምትልበት አመለካከት ብዙ እንደማያስኬድ በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ የመጣሁበትን ብሔረሰብ ብትወስድ ሁሉ ቦታ አገሩ እንደሆነ የሚያስብና ከሁሉ ተስማምቶ የሚኖር ነው፡፡ ቻይና ውስጥ ሱቅ፣ ቢሮ ከፍቶ እየሠራ የሚኖር ብዙ የዚህ ብሔረሰብ ተወላጅ አለ፡፡ ቋንቋውና ባህሉ እንደ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ ቀለል የሚባል አይደለም፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥም እየሠራ የሚኖር ነው፡፡ ነገር ግን የማንነት ጉዳይ መጥቷል፡፡ እየተጠየቀም ነው፡፡ ውጫዊ በሆነ ኃይል አጀንዳ እየተሰጠ አንተ ትንሽ የምታደርገውን ነገር ለልዩነት መነሻ ያደርግብሃል፡፡ ብሔርህ ይህ ነው ይልሃል፡፡ የቦታ አቀማመጥ፣ ትልቅ ወንዝ ካለ በዚሁ ወንዝ ምክንያት ልዩነት እየተፈጠረ፣ ሕዝቡ ወደ ልማትና ከድህነት እንዲወጣ የሚፈልግበትን መንገድ ወደ ሌላ ፉክክር ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ ነገሮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ክልሉ ባለበት የማይቀጥል ከሆነ የማንነት ጉዳይ አለ፡፡ ከክልሉ መውጣት አለብን የሚሉ ከሕፃን እስከ አዋቂ የሚያነሱበት ወቅት ነው፡፡ ፖለቲካ የድርድር ውጤት ነው፡፡ ተደራድረህ እገሌና እገሌ እዚህ ጋ መሆን አለባቸው ተባብለው ሲስማሙ አብሮ መኖር ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔርና  የክልልነት ጉዳይ ከሕዝቡ ይልቅ ነቅቷል የሚባለው ልሂቁ ነው የሚሉ ሰዎች፣ ሕዝቡ ያላሰበውን ጥያቄ እያስጨበጡት ነው ይላሉ፡፡

አቶ ሺሰማ፡- ፖለቲካ እኮ የልሂቅ ጉዳይ ነው፡፡ ልሂቁ ያነሳውን የፖለቲካ አጀንዳ ሕዝቡ ይቀበለዋል ወይስ አይቀበለውም የሚለው ነው ዋናው ነገር፡፡ የትኛውም የፖለቲካ አጀንዳ ልሂቅ የሚያነሳው ነው፡፡ በራሱ ጊዜ ከታች ፈንድቶ የመጣ አጀንዳ ጉዳይ የትኛው ነው፡፡ የእገሌ አርሶ አደሮች እንቅስቃሴ ሲባል የነበረው እኮ በልሂቃኑ አማካይነት ሲንቀሳቀስ በነበረ አጀንዳ አማካይነት የተስፋፋ ነው፡፡ ኤሊቲ ያነሳው ሐሳብ የሕዝብ መሆኑ የሚታወቀው ሕዝብ ይደግፈዋል የሚለው ሲታይ፣ ሲቀበለውና ድምፅ ሲሰጥበት ነው፡፡ እርግጥ የማንነት ጥያቄ አገሪቱ ከምትገኝበት ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ ይህ ዋነኛ ጉዳይ ነው ወይ የሚለው ሲታይ፣ ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ አጀንዳ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን በዋናነት የመጣው ግን በአጥኝ ቡድን ስለሆነ እንጂ፣ ከህዳሴው ግድብ በላይ ይህ ጉዳይ ይበልጥብኛል ብሎ የመጣ ያለ አይመስለኝም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...