Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ባንክ ለሼሪዓው የመድን አገልግሎት ያወጣው መመርያ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለመድን ኢንዱስትሪው ተጨማሪ ሆነው ከተካተቱ አዳዲስ አገልግሎቶች መካከል የሼሪዓ ሥርዓትን የሚከተለው የታካፉል መድን አገልግሎት እንዲተገበር ለማስቻል  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ አወጣ፡፡

ብሔራዊ ባንክ ሐሙስ ሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው መመርያ የታካፉል የተሰኘው የኢንሹራንስ አገልግሎት ከመደበኛ የመድን ሥራ ጎን በመስኮት እንዲሁም ራሱን ችሎ በመደበኛ ኩባንያ ደረጃ አገልግሎቱን ማቅረብ የሚቻልበትን ፈቃድ የሚሰጥ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በመስኮት የሚቀርቡ የታካፉል መድን አገልግሎቶች ብሎም በተሟላ ኩባንያ ደረጃ ለዚሁ ዓላማ የሚቋቋሙ ድርጅቶች ማሟላት የሚጠበቁባቸው ዝርዝር ጉዳዮች በመመርያው ተካተዋል፡፡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ይኸው መመርያ ከሰኔ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡

በመመርያው ከተጠቀሱት መካከል አንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ በመስኮት የሚቀርብ የታካፉል መድን አገልግሎት ለመስጠት በመደበኛው አገልግሎቱ ከተሰየሙ የቦርድ አባላት በተጨማሪ ለታካፉል ኢንሹራንስ የሼሪዓ አማካሪ ምክር ቤት እንዲያቋቁም ይገደዳል፡፡ ይህ ምክር ቤት ሦስት አባላት ሲኖሩት፣ አንደኛው የኢንሹራንስ ዕውቀት ያለው፣ ሌላኛው በሸሪዓ መመርያዎች ላይ ዕውቀት ያለው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ሦስተኛው የምክር ቤቱ አባል ደግሞ የፋይናንስ ዕውቀት ያለው እንዲሆን መመርያው ይደነግጋል፡፡ የእነዚህ አባላት ሹመት የሚፀድቀው እንደሌሎቹ የፋይናንስ ተቋማት ሁሉ በብሔራዊ ባንክ በኩል ነው፡፡

 ራሱን ችሎ ሙሉ የታካፉል ኢንሹራንስ ለመስጠት የሚቋቋም ኩባንያም ከሚጠበቁበት ግዴታዎች መካከል ዝርዝር የአዋጭነት ጥናት ማቅረብ አንዱ እንደሆነ በመመርያው ተደንግጓል፡፡ የኩባንያውን ይዘትና አጠቃላይ ዕቅድ የሚያመላክት ዝርዝር ጥናት ከቀረበ በኋላ ወደ ሥራ ለመግባት የብሔራዊ ባንክን ይሁንታ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡ የታካፉል አገልግሎትን በመስኮት የሚያቀርቡ ድርጅቶችም ቢሆኑ ለዚህ አገልግሎት የሚውልና ከመደበኛው የኢንሹራንስ አገልግሎት ተለይቶ ራሱን የቻለ  ክፍል ማቋቋም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሒሳብ አያያዙም ለብቻው ተለይቶ ይተዳደራል፡፡

መመርያው በአብዛኛው በዚህ አገልግሎት ዙሪያ የሚሳተፉ አካላት የሚመሩበት ግልጽ አሠራር እንዲኖራቸው ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት አጠቃላይ አሠራሩን የሚያመለክት ሪፖርት ከኩባንያዎቹ የማቅረብ ግዴታ ይጥላል፡፡

በታካፉል ኢንሹራንስ ዙሪያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችን ሲያቀርቡ የቆዩትና ለዚህ ተግባራቸው ተሸላሚ የሆኑት የኢንሹራንስ ባለሙያው አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ ለሪፖርተር ስለመመርያው አብራርተዋል፡፡ የታካፉል ኢንሹራንስ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚያስችለው አዲሱ መመርያ መውጣቱ ለአገሪቱ መድን ኢንዱስትሪ ዕመርታ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

የታካፉል ኢንሹራንስ አገልግሎት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት እንደሚባለው ሁሉ በመድን ዘርፉም በተመሳሳይ መንገድ የሚሠራበት እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ፍቅሩ፣ የአገልግሎቱ መጀመር የመድን ዘርፉን ተደራሽነት ለማስፋት አስተዋጽኦው ከፍተኛ እንደሚሆን ባለሙያው ይገልጻሉ፡፡ አገልግሎቱ እንዲጀመር ለዓመታት ጥረት ሲደረግ ቢቆይም፣ ትኩረት ሊያገኝ ባለመቻሉ እስካሁን ሕግ ሳይወጣለት እንደቆየ አስታውሰው፣ በመመርያ ተደግፎ የወጣውም በቅርቡ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ አገልግሎቱ እጅጉን ዘግይቶ እንደመጣ የሚናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ በሌሎች አገሮች ግን በተለያየ ስያሜ ለበርካታ ዓመታት ሲተገበር እንደቆየ  ያወሳሉ፡፡ አንዳንዶች ‹‹ሃላል ኢንሹራንስ››፣ ‹‹ኤቲካል ኢንሹራንስ››፣ ‹‹ኢስላሚክ ኢንሹራንስ›› ወዘተ. ስያሜዎችን የሚሰጡት አሉ፡፡ ‹‹ኮፕሬቲቭ ኢንሹራንስ›› በሚል ስያሜ የሚጠሩት እንዳሉም በመግለጽ በኢትዮጵያ ታካፉል የሚለው በይፋ የሚጠራበት ስያሜ እንደሆነ ታውቋል፡፡  

ይህ አገልግሎት ቀላል ቢሆንም ፈታኝ ሁኔታዎች እንዳሉበት የሚገልጹት አቶ ፍቅሩ፣ በምሳሌ ያብራራሉ፡፡ ‹‹አገልግሎቱ አዲስ፣ ተቆጣጣሪውም አዲስ እንደመሆናቸው፣ የመድን ኩባንያዎች የሠለጠነ የሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በቂ የሰው ኃይል አለ ማለት ያስቸግራል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ለአገልግሎቱ ተግዳሮት እንዳይሆን ሥጋት አላቸው፡፡ በመሆኑም ከወዲሁ የሰው ኃይል ማሠልጠን  ትኩረት እንደሚሻ ያሳስባሉ፡፡

እንዲህ ያሉ አገልግሎቶች ከንግድ ዓላማ አኳያ ሲመዘን፣ የታካፉል አገልግሎት የሚቀርብላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችን ባህል፣ ሃይማኖትና ፍላጎት የጠበቀ አገልግሎት በማምጣት መሥራቱ ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያስልግ ባለሙያው ያብራራሉ፡፡ ‹‹ደንበኛዬ ምን ይፈልጋል፡፡ ለደንበኛዬ ምን ጥቅም ይጠሰዋል? ምን መፍትሔ ያመጣለታል? ይህንን አገልግሎት የምሰጠው ፍላጎቱን በጠበቀ መንገድ ነው ወይ? ማለት ያስፈልጋል፤›› በማለት ኩባንያዎቹ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡

 አዲሱ የመድን አገልግሎት እንዲህ ያሉ መነሻዎችን ዓላማው በማድረግ በበርካታ አገሮች መሰል የመድን አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ያስቻለ ሲሆን፣ በኢትዮጵያም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ የመጣ አማራጭ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ኢስላሚክ ኢንሹራንስ ሲባልም ሙስሊሙ ብቻ የሚጠቀምበት ተደርጎ መወሰድ የለበትም፤›› የሚሉት አቶ ፍቅሩ፣ ‹‹ማንኛውም ዕምነት ለሚከተል ሰው  የሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ ከመተባበር ጋር የተያያዘ የኢንሹራንስ ዓይነት ስለሆነ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ጠቃሚ ነው፤›› ይላሉ፡፡

እንደ አቶ ፍቅሩ ሁሉ ሌሎች የኢንሹራንስ ባለሙያዎችም በአገልግሎቱ አስፈላጊነት ላይ ችግር እንደሌለባቸው ጠቅሰው፣ ነገር ግን አዲሱ መመርያ ክፍተቶች እንዳሉበት ያምናሉ፡፡ ይህን የሚጠቅሱት አንድ የኢንሹራንስ ባለሙያ፣ መመርያው በጥድፊያ የወጣ የሚያስመስሉት ክፍተቶች እንደሚታዩበት ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የታካፉል አገልግሎት እንዲጀመር የሚረዱና መመርያው ሊያካትታቸው ይገባዋል የተባሉ ቁልፍ ሐሳቦች በመመርያው አለመካተታቸው ግር እንዳሰኛቸው ይናገራሉ፡፡

በአዲሱ መመርያ መሠረት በጥቅል የታየው ጉዳይ ሥራውን ለማስጀመር ይረዳሉ የተባሉ ዋና ዋና ጉዳዮች ቢሆኑም፣ አገልግሎቱ አዲስ ቢሆንም በጥልቀት የሚታዩ ዝርዝር ጉዳዮች እንደሚቀሩት ያነሳሉ፡፡

ከመደበኛው ኢንሹራንስ ተለይቶ የሚሠራ በመሆኑ፣ ከንግድ ሥራና ትርፍ መሰብሰብ ይልቅ በመተባበር የሚሠራበት በመሆኑ፣ እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት መመርያው ሊያካትት ይገባቸው የነበሩ ጉዳዮች አሁንም ምክረ ሐሳብ መቀበልና ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለታካፉል አገልግሎት ዕምቅ ፍላጎት እንዳለ ሲገለጽ፣ ከ11 ዓመታት በፊት በነበረው የሕዝብ ቆጠራ ከ35 እስከ 40 በመቶ በላይ ሙስሊም ሕዝብ እንደሚኖር ስለሚገመትና ይህም ለአገልግሎቱ ሰፊ ፍላጎት እንደሚኖረው አመላካች ተደርጓል፡፡ ታካፉልን ከመደበኛው ኢንሹራንስ የሚለየው የሥነ ምግባር መርህና ልምምድ የሚከተል በመሆኑ እንደሆነ ባለሙያዎች ያብራራሉ፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የንግድ ሕግ እንዲሁም በሸሪዓ ሕግና መርህ መሠረት የሚተገበር በመሆኑ፣ ሥነ ምግባርን የተበላበሰ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዚህ ሳቢያ አንዳንድ አገሮች ሥነ ምግባር ተኮር መድን ወይም ‹‹ኢቲካል ኢንሹራንስ›› በማለት እንደሚጠሩትም ይጠቀሳል፡፡

በመደበኛው መድን አገልግሎት ዓረቦን ተከፍሎ፣ በተከፈለው ዓረቦን መጠን ብቻ ተለክቶ ለሚደርስ ጉዳት ክፍያ ይፈጸማል፡፡ ‹‹በታካፉል ግን ዋናው መተባበር ነው፡፡ በአገልግሎቱ የሚካተቱ ሰዎች ተሳታፊዎች ይባላሉ፡፡ የሚገቡበት ለማትረፍ ሳይሆን ለመተጋገዝ በመሆኑ የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል፤›› በማለት አቶ ፍቅሩ አብራርተዋል፡፡

ከመደበኛው ኢንሹራንስ የሚለይበት ሌላው ጉዳይ፣ በመደበኛው ኢንሹራንስ የአደጋ ሥጋት የሚተወው ለኩባንያው ሲሆን፣ በታካፉል ግን ሥጋትን መካፈል የአገልግሎቱ ማጠንጠኛ በመሆኑ ይለያል ይሉታል፡፡ ‹‹ሰዎች ሥጋቱን እርስ በርሳቸው ይጋሩታል፡፡ ነገር ግን የታካፉልን ገንዘብ የሚያስተዳድሩት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ናቸው፤›› ያሉት አቶ ፍቅሩ፣ ይህም በመመርያ መደንገጉን አስቀምጠዋል፡፡ በመስኮት አገልግሎት የሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በታካፉል አገልግሎት ከታቀፉ ደንበኞቻቸው የአገልግሎት ክፍያቸውን በኮሚሽን ወይም በሌላ መንገድ እንዲያገኙ የሚደረገበት አሠራርም አለው፡፡

የዚህ መድን ዘርፍ የሥራ እንቅስቃሴዎች በግልጽነት የሚተገበሩ፣ ለመድን ተጋሪዎቹ ወይም ተሳታፊዎች ብሎም ለብሔራዊ ባንክና ለሕዝብ ይፋ እያደረጉ የሚንቀሳቀሱበት አግባብ በመመርያው ተመልክቷል፡፡ ለመድን የሚወጣ የተለየ የኢንቨስትመንት ፈንድ ሊኖር እንደሚገባም ተጠቅሷል፡፡ ኢንሹራንስ ኩባንያው ለአገልግሎቱ የሚከፈለው ምን ያህል ገንዘብ እንደሆነ በሕግ ማስቀጥ እንደሚገባ፣ ኪሳራ ቢያጋጥም እንኳ እንዴት እንደሚሸፈን ኩባንያዎቹ በውል ውስጥ ማስገባት እንደሚጠበቅባቸው ባለሙያዎች ይተነትናሉ፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያው የእነዚህን ሰዎች ሥጋት በማስተዳደሩ ለዚህ አገልግሎቱ ክፍያ ያገኛል፡፡ ተገልጋዮቹም በኮሚሽን መልክ ሊከፍሉት ይችላሉ፡፡ ትርፍ ሲገኝም እንደየስምምነታቸው የሚከፋፈሉበት መንገድ በውል ተደንግጎ የሚቀመጥበት አሠራር በታካፉል ከሚጠቀሱ የጋራ ተጠቃሚነት አገልግሎቶች መካከል አንዱ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች